የዐቢይ ጾም ሳምንታት

በመምህር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

መጋቢት ፲፩ ቀን ፳፻፱ .

ዘወረደ

ትርጕሙ ‹ከሰማየ ሰማያት የወረደ› ማለት ነው፡፡ ከሰማየ ሰማያት የወረደውን፣ ከድንግል ማርያም የተወለደውን በጥንት ስሙ ወልድ፣ ቃል በኋላ ስሙ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አማኑኤል የተባለውን ሰው የኾነውን አምላክ ለማመስገን ርደቱን (ከሰማየ ሰማያት መውረዱን) ለመዘከር የሚጾም ጾም ነው፡፡ ጌታችን ጾመ ከማለት አስቀድሞ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም መወለዱን መናገር አስፈላጊ ነውና የመጀመሪያው ሳምንት ‹ዘወረደ› ተብሏል፡፡ ‹‹አንተ በሰማይ ወአንተ በምድር ወአንተ በባሕር ወአንተ በየብስ፤ አንተ በሰማይ አለህ፤ በምድር በባሕርም በየብስም አለህ፤›› የተባለውን በሰማይ በምድር ምሉዕ የኾነውን አምላክ ‹ወረደ፤ መጣ› ብሎ መናገር ‹ሰው ኾነ› ማለት ነው፡፡ ሰው ኾኖ መገለጡን ለማስረዳት ነው እንጂ መውረድ መውጣት የሚባሉ ቃላት በዅሉ ምሉዕ ለኾነው መለኮት አይስማሙትም፡፡ ቃላቱ ሰውኛ አነጋገርን የሚያመለክቱ ናቸውና፡፡ መተርጕማን አበው ‹‹‹ዘወረደ› ማለት ‹ሰው የኾነ› ማለት ነው›› ብለው ይተረጕማሉ፡፡ አምላካችን ሰው ከኾነ በኋላ ‹መጣ፤ ሔደ፤ ወረደ፤ ዐረገ› የሚሉ ቃላት ይስማሙታል፡፡ ምልዓቱን ሳይለቅ በሰው አካል ተወስኖ ታይቷልና፡፡ ስለዚህ ‹ወረደ› እግዚአብሔር ሰው ኾኖ መገለጡን፤ ‹ዐረገ› ደግሞ የሰውነቱን ሥራ መፈጸሙን ያሳያል፡፡ ዐረገ ስንልም ቀድሞ በሰማይ የለም ለማለት አይደለም፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ በዓለሙ ዅሉ ምሉዕ ነውና፡፡

ጾሙን ሐዋርያት፣ ስያሜውንና የምስጋናውን ሥርዓት ቅዱስ ያሬድ አዘጋጅተዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ነቢያትን በንባብ፤ ሐዋርያትን በስብከት፤ ሊቃውንትን በትርጓሜ፤ መላእክትን በዜማ ይመስላቸዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ የመላእክትን የምስጋና ሥርዓት ወደ ምድር አምጥቷል፡፡ የነቢያትን ትንቢት፣ የሐዋርያትን ትምህርት በሚገባ ተርጒሞ፣ አብራርቶ፣ አመሥጥሮ አዘጋጅቶታል፡፡ ሐዋርያት ጾሙን ጾመው የጾም ሕግ ደንግገዋል፤ ቅዱስ ያሬድም ለጾሙ ስያሜ ሰጥቶ ምስጋና ከነሥርዓቱ አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡ቤተ ክርስቲያናችንም የመጀመሪያው የዐቢይ ጾም ሳምንትን (ዘወረደን) ስያሜ እንደ ቅዱስ ያሬድ ከሐዋርያት ተቀብላ ታስተምራለች፡፡ ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ‹ጾመ ሕርቃል› እየተባለም ይጠራል፡፡ ሕርቃል (ኤራቅሊዮስ) በ፮፻፲፬ ዓ.ም የነበረ የቤዛንታይን ንጉሥ ነው፡፡ ለክርስቲያኖች ባደረገው ርዳታ ምክንያት አንድ ሳምንት ጾመውለት ነበር፡፡ ያላወቁ ‹ጾመ ሕርቃል› ብለው አንድ ጊዜ ጾመው ትተውታል፡፡ ጥንቱን የቅዱሳን ሐዋርያት መኾኑን ያወቁ ምእመናን ግን ዅልጊዜ በየዓመቱ ይጾሙት ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ጾመ ሕርቃል እየተባለ ይጠራል፡፡ ሙሉ ታሪኩ በፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ አንቀጽ ፲፭ ላይ ይገኛል፡፡

ቅድስት

‹ቅድስት› ማለት ‹የተለየች፣ የነጻች፣ የከበረች› ማለት ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን ጾም የጀመረባት፣ ልዩ፤ የተቀደሰች፤ የከበረች፤ ልዩ፣ ንጹሕ፣ ክቡር በሚኾን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጾመች መኾኗን ያመላክታል፡፡ ይህች ጾም በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አራት የተገለጠችው የጌታችን ጾም ስትኾን፣ ስያሜዋና የዕለቷ የምስጋና ሥርዓትም የቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ አምላካችን በገዳመ ቆሮንቶስ ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት በጾመበት ጊዜያት እነዚህ ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ ድል አድርጓል፡፡ ሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ የሚባሉትም፡- ትዕቢት፣ ስስትና ፍቅረ ንዋይ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሦስት ኃጢአቶች ጌታችን በዲያሎስ በተፈተነ ጊዜ በትዕቢት ቢመጣበት በትሕትና፤ በስስት ቢመጣበት በትዕግሥት፤ በፍቅረ ንዋይ ቢመጣባት በጸሊዓ ንዋይ ጌታችን ዲያሎስን ድል አድርጎታል፡፡ ለእኛም እነዚህን ድል ለማድረግ የምንችልበትን ጥበብ – ጾምን ገልጦልናል፡፡ ትዕቢት ያልተሰጠንን መሻት፣ ስስት አልጠግብ ባይነት ስግብግብ መኾን፣ ፍቅረ ንዋይ ለገንዘብ ሲሉ ፈጣሪን መካድ ነው፡፡ አንደ ክርስቲያን ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ ድል ካደረገ ሌሎችን ኃጣውእ በቀላሉ ድል ማድረግ ይቻለዋል፡፡

ምኵራብ

ሦስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹ምኵራብ› ይባላል፡፡ ምኵራብ አምልኮተ እግዚአብሔር ሲፈጸምበት፣ ሕገ ኦሪት ሲነበብበት የነበረ በአይሁድ የሚሠራ መካነ ጸሎት ነው፡፡ ዘወትር ቅዳሜ ብዙ ሕዝብ ይሰበሰብበት ስለ ነበር ጌታችን ለማስተማር ብዙ ጊዜ በምኵራብ ተገኝቶአል፡፡ ስያሜው የተወሰደው በዮሐንስ ፪፥፲፬ ‹‹ወረከበ በምኵራብ እለ ይሠይጡ አልህምተ ወአባግዐ ወአርጋበ …፤ በመቅደስም በሬዎችን፣ ላሞችን፣ በጎችን፣ ርግቦችን፣ የሚሸጡትን አገኘ …›› ተብሎ ከተገለጸው ኃይለ ቃል ላይ ሲኾን፣ ‹ምኵራብ› የሚለው ቃልም በአማርኛ ‹መቅደስ› ተብሎ ተተርጕሟል፡፡ ምኵራብ የሚባለው ሳምንት ጌታችን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማሩ የሚነገርበት፤ ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፤ እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት›› ብሎ በምኵራብ ይሸጡ፣ ይለውጡ የነበሩትን የገሠፀበት፤ ቤተ መቅደስን የከብት መንጃ የወርቅና የብር መነገጃ ያደረጉ ሰዎችን ከነሸቀጣቸው ከቤተ መቅደስ ያስወጣበት፤ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ የስሙ መጠሪያ፣ የጸሎት ሥፍራ መኾኗን ያስረዳበትና ያወጀበት፤ በቤተ መቅደስ የንግድ ሥራ ማከናወን እንደማይገባ ያረጋገጠበት ዕለት ነው፡፡

መጻጒዕ

አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹መጻጒዕ› ይባላል፡፡ ስያሜው በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፩ ላይ ከሚገኘው ኃይለ ቃል የተወሰደ ነው፡፡ በዚህ የወንጌል ክፍል ጌታችን በቤተ ሳይዳ ሕሙማንን እንደ ፈወሰ ተነግሮአል፡፡ ብዙ ሕሙማን ፈውስ ሽተው አንዲት የመጠመቂያ ሥፍራን ከበው ይኖሩ ነበር፡፡ በዚያች ሥፍራ ቀድሞ የወረደ እና የተጠመቀ አንድ በሽተኛ ብቻ ይፈወስ ነበር፡፡ ጌታችን በዚህ ሥፍራ ተገኝቶ በሽተኞችን ጐብኝቷል፡፡ በዚያም ልዩ ልዩ ደዌ ያለባቸው አምስት ዓይነት ሕሙማን እንደ ነበሩ ተገልጧል፤ እነዚህም፡- ሰውነታቸው የደረቀ፣ የሰለለና ያበጠ፤ እንደዚሁም ዕውራን እና ሐንካሳን ነበሩ፡፡ ከዚህ አምስት የተለያየ ዓይነት በሽታ ከተያዙ ሰዎች መካከል ደዌው የጸናበት፣ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በደዌ ዳኛ፣ ባልጋ ቍራኛ ተይዞ የኖረው፤ ከደዌው ጽናት የተነሣ ‹መጻጒዕ› ተብሎ የተጠራው በሽተኛ አንዱ ነበር፡፡ መጻጒዕ ስም አይደለም፡፡ ደዌ የጸናበት በሽተኛ ሕመምተኛ ማለት ነው እንጂ፡፡ ሰውየው ከበሽታው ጽናት የተነሣ ስሙ ጠፍቶ በበሽታው ሲጠራ የነበረ ነው፡፡ አምላካችን ይህን ሰው ‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› ብሎ ሠላሳ ስምንት ዘመን የተኛበትን አልጋ ተሸክሞ ወደ ቤቱ እንዲገባ ማድረጉ የሚነገርበት ወቅት በመኾኑ ሳምንቱ ‹መጻጒዕ› ተብሎ በተፈወሰው በሽተኛ ስም ተሰይሟል፡፡ (ሙሉ ታሪኩን በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፩-፲፯ ይመልከቱ)፡፡ ዛሬም ቢኾን በሰዎች ላይ ልዩ ልዩ ደዌያት አሉ፤ የሥጋውን ደዌ ሐኪሞች ያውቁታል፡፡ ከዚህ የከፉ የነፍስ ደዌያት እጅግ ብዙዎች ናቸው፡፡ በኃጢአት ብዛት ልባቸው የደረቀና ያበጠ፤ ሰውነታቸው የሰለለ፤ ዓይነ ሕሊናቸው የታወረ፤ እግረ ልቡናቸው የተሰበረ ብዙዎች ሕሙማን አሁንም አሉ፡፡ ፈውስን ይሻሉ፤ ድኅነትን ይፈልጋሉ፡፡ እንደ መጻጕዕ ቦታቸውን ሳይለቁ እግዚአብሔርን በተስፋ ቢጠብቁት አንድ ቀን ይፈወሳሉ፡፡

ደብረ ዘይት

አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹ደብረ ዘይት› ይባላል፡፡ ስያሜው የተወሰደውም ከማቴዎስ ወንጌል ፳፬፥፫ ካለው ትምህርት ነው፡፡ ደብረ ዘይት ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኝ በወይራ ዛፎች የተሸፈነ ትልቅ ተራራ ነው፡፡ ጌታችን ምሥጢራትን በተለያየ ቦታ ገልጧል፡፡ ምሥጢረ ጸሎትን በጌቴሴማኒ፤ ምሥጢረ መንግሥቱን በደብረ ታቦር፤ ምሥጢረ ቊርባንን በቤተ አልዓዛር፤ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን በቤተ ኢያኢሮስ፤ ምሥጢረ ምጽአቱን ደግሞ በደብረ ዘይት ገልጧል፡፡ ደብረ ዘይት ጌታችን ዳግም ለፍርድ መምጣቱንና ምሥጢረ ምጽአቱን ለደቀ መዛሙርቱ በሚገባ የገለጠበት ዕለት ነው፡፡ ደብረ ዘይትን ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ለማደሪያነት ተጠቅሞበታል፡፡ ቀን ቀን በምኲራብ ያስተምራል፤ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በደብረ ዘይት ያድራል፡፡ ይህንም ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይመሰክራል፤ ‹‹ዕለት ዕለት በመቅደስ ያስተምር ነበር፡፡ ሌሊት ግን ደብረ ዘይት ወደምትባል ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር፡፡ ሕዝቡ ዅሉ ይሰሙት ዘንድ ማልደው በመቅደስ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር›› (ሉቃ. ፳፩፥፴፯)፡፡ በዚህ ለማደሪያነት ባገለገለው ተራራ ምሥጢረ ምጽአቱን ስለ ገለጠበት አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ደብረ ዘይት የሚል ስያሜ ተሰጥተታል፡፡ ደብረ ዘይት ጾሙ እኩል የሚኾንበት፤ አምላካችን በግርማ መንግሥቱ ለፍርድ በመጣ ጊዜ መልካም ለሠሩ ክብርን፣ ክፉ ለሠሩ ቅጣቱን የሚያስተላልፍ መኾኑ የሚነገርበት፤ ስለ ዓለም መጨረሻ እና ስለሚመጣው ሕይወት የምንማርበት የክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ዕለት ነው፡፡

ገብር ኄር

ስድስተኛው ሳምንት ‹ገብር ኄር› የሚል ስያሜ አለው፡፡ ‹ገብር ኄር› ማለት ‹በጎ፣ ታማኝ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡ ስያሜው ከማቴዎስ ወንጌል ፳፭፥፲፬ የተወሰደ ሲኾን፣ ታሪኩም እግዚአብሔር በሰጠው ጸጋ በታማኝነት ማገልገል የሚያስገኘውን ዋጋ ያስረዳል፡፡ አንድ ሰው አገልጋዮቹን ጠርቶ ወጥተው፣ ወርደው፣ ነግደው እንዲያተርፉ ለአንዱ አምስት፤ ለአንዱ ሁለት፤ ለአንዱ ደግሞ አንድ መክሊት ሰጣቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው በተሰጠው መክሊት ነግዶ፣ ሌላ አምስት መክሊት አትርፎ፣ ዐሥር አድርጎ፣ ‹‹ጌታዬ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ወጥቼ ወርጄ አምስት አትርፌአለሁ›› ብሎ ለጌታው አቀረበ፡፡ ጌታውም ‹‹አንተ ጎበዝ እና ታማኝ ባሪያ! በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለውም ወጥቶ፣ ወርዶ፣ አትርፎ አራት አድርጎ አቀረበ፡፡ እርሱንም ጌታው ‹‹አንተ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡ አንድ የተቀበለው ሰው ግን መክሊቱን ወስዶ ቀበራት፡፡ ጌታው በተቈጣጠረው ጊዜም የቀበራትን መክሊት አምጥቶ ‹‹አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ እንደ ኾንኽ ዐውቃለሁ፡፡ ስለዚህ ፈራሁና የሰጠኸኝን መክሊት ቀበርኳት፤ እነሆ መክሊትህ!›› ብሎ ምንም ሳያተርፍ መክሊቱን ለጌታው መልሶ አስረከበ፡፡ ጌታውም ‹‹አንተ ክፉና ሐኬተኛ ባሪያ! ወርቄን በጊዜው አታስረክበኝም ነበር? ነግዶ ለሚያተርፍ እሰጠው ነበር፡፡ ይህን ክፉና ሐኬተኛ ባሪያ እጅ እግሩን አስራችሁ ጨለማና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ሥፍራ ውሰዱት! መክሊቱን ቀሙና ለባለ ዐሥሩ ጨምሩለት!›› ብሎ አዘዘ፡፡

በዚህ ታሪክ እንደምናየው በተሰጠው መክሊት ያተረፈ ሰው (ክርስቲያን) ዋጋ አለው፡፡ በፈጣሪው ዘንድ መልካም፣ በጎ፣ ታማኝ ባሪያ ተብሎ ይሸለማል፡፡ ባያተርፍ ደግሞ ሐኬተኛ ባሪያ (አገልጋይ) ይባላል፤ ቅጣቱንም ይቀበላል፡፡ እንግዲህ እኛም ታማኝ አገልጋይ መኾን ይጠበቅብናል፡፡ ሳምንቱ ይህ መልእክት የሚተላለፍበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ዘመን በመክሊታቸው የሚያተርፉ እንዳሉ ዅሉ፣ መክሊታቸውን (ጸጋቸውን) ዝገት እስከሚያጠፋው ድረስ የሚቀብሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ መክሊትን (ጸጋን) መቅበር ዋጋ የማያሰጥ መኾኑን ተገንዝበን በቻልነው መጠን ለማትረፍ መትጋት እና ታማኝ አገልጋይ መኾን እንደሚገባን ከገብር ኄር ታሪክ እንማራለን፡፡

ኒቆዲሞስ

ሰባተኛው ሳምንት ‹ኒቆዲሞስ› የሚል ስያሜ ያለው ሲኾን፣ የስያሜው መነሻም በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፫ የተመዘገበው ኒቆዲሞስ የተባለው የአይሁድ አለቃ ታሪክ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ በሦስት መንገድ የአይሁድ አለቃ ነበር፤ በሥልጣን፣ በዕውቀትና በሀብት፡፡ ሰው ሥልጣን ቢኖረው ሀብትና ዕውቀት ላይኖረው ይችላል፡፡ ዕውቀት ቢኖረው ደግሞ ሀብትና ሥልጣን ላይኖረው ይችላል፡፡ ሀብት ቢኖረውም ዕውቀትና ሥልጣን ላይኖረው ይችላል፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ሦስቱንም አንድ ላይ አስተባብሮ የያዘ የአይሁድ አለቃ ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ወንጌልን ለመማር ከአይሁድ ዅሉ ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ይሔድ ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ፈሪሳውያን ማመን ባልቻሉበት በዚያን ዘመን ጆሮውን ለቃለ እግዚአብሔር፤ ልቡን ለእምነት የከፈተ ሰው ነው፡፡ ብዙ ሰዎችን እናውቃለን ማለት ከመልካም ነገር ሲከለክላቸው ኒቆዲሞስ ግን ዐዋቂ ሳለ ራሱን ዝቅ አድርጎ፣ እምነት በማጣት የነጠፈችውን የፈሪሳውያንን ኅብረት ጥሎ፣ ሐዋርያትን መስሎ ጌታውን አግኝቶታል፡፡ ጌታችን ዓለምን ለማዳን ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በለየባት በዚያች አስጨናቂ ሰዓት፤ ሐዋርያት በተበተኑባት አይሁድ በሠለጠኑባት በዕለተ ዓርብ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን በድርብ በፍታ ገንዞ የቀበረ፣ እሱን ያገኘ ያገኘኛል ሳይል በድፍረት ከእግረ መስቀሉ የተገኘ ሰው ነው – ኒቆዲሞስ፡፡ ስለዚህም ሰባተኛው ሳምንት በእርሱ ስም ተሰይሟል፡፡

ሆሣዕና

‹ሆሣዕና› ስምንተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ሲኾን፣ የሰሙነ ሕማማት መጀመሪያ ነው፡፡ ሆሣዕና ስያሜው በማቴዎስ ወንጌል ፳፩፥፱ ከሚገኘው ትምህርት የተወሰደ ሲኾን ትርጕሙም ‹መድኀኒት ወይም ‹አሁን አድን› ማለት ነው፡፡ ክብር ይግባውና አምላካችን በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ‹‹ሆሣዕና በአርያም›› የሚሉ የአዕሩግ፣ የሕፃናት ምስጋና እየቀረበለት ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ጉዞ ያደረገበት፤ ትሕትናውን የገለጠበት፤ ይህን ዓለም ከማዕሠረ ኃጢአት መፍታቱን በምሳሌ ያስረዳበት ዕለት ነው፡፡ ‹‹ተጽዕኖ›› ተብሎ ከሚጠራው የዐቢይ ጾም መጨረሻ (ዕለተ ዓርብ) እና ከሰሙነ ሕማማት መግቢያ ጀምሮ ያለው ሳምንት ሆሣዕና ይባላል፡፡ የክርስቶስን ነገረ ሕማሙን፣ ስቅለቱን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን ሆሣዕና ተብሎ ዓለምን ማዳኑን የሚናገሩ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚነበቡበት፤ አምላካችን ለሰው ልጅ መዳን መከራ መቀበሉና የማዳን ሥራው በሰፊው የሚታወጅት፤ በሰሙነ ሕማማት ለሚያርፉ ምእመናን ጸሎተ ፍትሐት የሚደረግበት፤ ወንጌል በአራቱ ማዕዘን የሚሰበክበት ሳምንት ነው – ሆሣዕና፡፡ ከዚያው አያይዞም ሰሙነ ሕማማት ይቀጥላል፤ ወቅቱም የክርስቶስን ነገረ ሕማሙንና ዓለምን ያዳነበት ጥበቡን የምንሰማበት ሳምንት ነው፡፡ በሞቱ ሞታችንን አጥፍቶ መንግሥቱን እንድንወርስ የፈቀደልን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይኹን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡