የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል ሦስት

በልደት አስፋው

መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

፭. ደብረ ዘይት

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ስለዅሉም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን! ባለፈው ዝግጅታችን አራተኛውን የዐቢይ ጾም ሳምንት የተመለከተ ትምህርት አቅርበንላችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ስለ አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት (ስለ ደብረ ዘይት) አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን በተግባር ላይ እንድታውሉት እሺ? መልካም ልጆች! አሁን በቀጥታ ወደ ትምህርቱ እንወስዳችኋለን፤

ልጆች! እንደምታስታውሱት አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ደብረ ዘይት›› ይባላል፡፡ ትርጕሙም ‹‹የወይራ ተክል የሚገኝበት ተራራ›› ማለት ነው፡፡ ይህ ትልቅ ተራራ (ደብረ ዘይት) ከኢየሩሳሌም ከተማ በስተምሥራቅ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ ደብረ ዘይት ተራራ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዕለተ ምጽአትን ምልክት ለደቀ መዛሙርቱ (ለሐዋርያት) የገለጸበትና ያስተማረበት ቦታ ነው፡፡ ጌታችን በዚህ በደብረ ዘይት ተራራ ተቀመጦ ‹‹ማንም እንዳያስታችሁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፡፡ እስከ መጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል …›› እያለ ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯቸዋል፡፡

እነርሱም ስለ ዕለተ ምጽአት ምልክትና የመምጫው ጊዜ መቼ እንደሚኾን ጌታችንን ጠይቀውታል፡፡ እርሱም ቀኑን ከእርሱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም እንደማያውቀውና ክርስቲያኖች ከኀጢአት ርቀው በዝግጅት መጠባበቅ እንደሚገባቸው አስረድቷቸዋል፡፡ ልጆች! ዓለም የምታልፍበት ቀን ሲደርስ (በዕለተ ምጽአት) ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመላእከት ዝማሬ፣ በመለከት ድምፅ ታጅቦ በኃይልና በግርማ ከሰማይ ወደ ምድር ይመጣል፡፡

አምላካችን በመጣ ጊዜም በተዋሕዶ ሃይማኖትና በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንቶ የተገኘ ክርስቲያን በገነት (መንግሥተ ሰማያት) ለዘለዓለሙ በደስታ ይኖራል፡፡ ያለ ክርስቲያናዊ ምግባር ማለትም በኀጢአት ሥራ የኖረ ሰው ደግሞ ለዘለዓለሙ መከራና ስቃይ ወዳለበት ወደ ሲኦል (ገሃነመ እሳት) ይጣላል፡፡ ስለዚህ አምላካችን ለፍርድ ሲመጣ ለእያንዳንዳችን እንደ ሥራችን ኹኔታ ዋጋ ይሰጠናል ማለት ነው፡፡ የጽድቅ ሥራ ስንሠራ ከኖርን ወደ መንግሥተ ሰማያት (የጻድቃን መኖሪያ) እንገባለን፤ ኀጢአት ስንሠራ ከኖርን ግን ወደ ገሃነመ እሳት (የኀጢአተኞች መኖሪያ) እንጣላለን፡፡

ልጆች! እናንተም በዕለተ ምጽአት ወደ መንግሥተ ሰማያት እንድትገቡ በምድር ስትኖሩ ከክፉ ሥራ ማለትም ከስድብ፣ ከቍጣ፣ ከተንኮል፣ ከትዕቢት እና ከመሳሰለው ኀጢአት ርቃችሁ በእውነት፣ በትሕትና፣ ሰውን በማክበር፣ በፍቅር እና በመሳሰለው የጽድቅ ሥራ ጸንታችሁ ለወላጆቻችሁ እየታዘዛችሁ ኑሩ፡፡ ይህንን ለማድረግ እንድትችሉ ደግሞ ከዘመናዊው ትምህርታችሁ ጎን ለጎን ከወላጆቻችሁ ጋር እየተመካከራችሁ (አስፈቅዳችሁ) መንፈሳዊ ትምህርት መማር፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ መንፈሳውያን ፊልሞችን መመልከትና መዝሙራትን ማዳመጥ፣ እንደዚሁም በየጊዜው መቍረብ አለባችሁ እሺ?

በጣም ጥሩ ልጆች! ለዛሬው ከዚህ ላይ ይቆየን፡፡ በሚቀጥለው ዝግጅት ስለሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ትምህርት ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከኹላችን ጋር ይኹን!