ድረ ገጾችን በስፋት ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት መጠቀም እንደሚገባ ጥናቶች አመለከቱ

ጥቅምት ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ማኅበረ ቅዱሳን ባዘጋጀው አዲስ ስልታዊ ዕቅድ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን የበለጠ ለማጠናከርና ከባለድርሻ አካላት ጋር እንዴት በቅንጅት ተቀራርቦ መሥራት እንደሚቻል የሚያመለክቱ ጥናታዊ ጽሑፎች መስከረም ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በማኅበሩ አዳራሽ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በጥናቶችም ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በስፋት ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት መጠቀም እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

dscf6211

ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ

በዐውደ ጥናቱ ‹‹ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮን ለማስፋፋት ፈታኝና ምቹ ኹኔታዎች›› በሚል ርእሰ ጉዳይ ጥናት ያቀረቡት ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ስትሰጥ ብትቆይም ከ፲፱፻፹-፲፱፻፺ ዓ.ም የነበራት ሐዋርያዊ አገልግሎት ይበልጥ የተጠናከረ እንደ ነበረ ጠቅሰው ለዚህም በወቅቱ የሰባክያነ ወንጌል ቍጥር መጨመር፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስፋፋትና ምእመናን ስለ ሃይማኖታቸው ለማወቅ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መኾን የመሳሰሉት ጉዳዮች ለሐዋርያዊ አገልግሎት መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ገልጠዋል፡፡

ዲ/ን ያረጋል አያይዘውም ኦርቶዶክሳዊ መንፈስና መረዳት ያላቸውን ሰባክያነ ወንጌል በብዛት በመመደብ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት መስጠት የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡

dscf6257

ዲያቆን ዶ.ር ቴዎድሮስ

‹‹በስብከተ ወንጌል የአኃት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ›› በሚል ርእስ ባዘጋጁት ጥናታቸው የመጀመሪያዎቹን ሦስቱን ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት የሚቀበሉ ኦሬንታል (አኀት) አብያተ ክርስቲያናት እንደሚባሉ ያስታወሱት ዲያቆን ዶክተር ቴዎድሮስ በለጠ ደግሞ ስብከተ ወንጌልን አጠናክሮ ለመቀጠል መልካም አጋጣሚዎችንና ተግዳሮቶችንም በጥናታቸው ዘርዝረዋል፡፡

‹‹የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች›› በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት አቶ ፋንታኹን ዋቄ በበኩላቸው እምነታቸውን በሕይወት የሚገልጡ ምእመናን መበራከት፣ የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት መጠናከር፣ የጉባኤ ቤት መምህራን እነሱን አክለውና መስለው የሚያገለግሉ ሊቃውንትን መተካትና የአፅራረ ቤተ ክርስቲያንን እንቅስቃሴ መግታት መቻል የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት መጠናከር መገለጫዎች መኾናቸውን ገልጠዋል፡፡

dscf6302

አቶ ፋንታኹን ዋቄ

‹‹የኦርቶዶክሳዊ ምእመን ተልእኮ ራስን መጠበቅ፣ ሌሎችን መጠበቅና በሌሎች ለመጠበቅ ፈቃደኛ መኾን ነው›› ያሉት አቶ ፋንታኹን አያያይዘውም የዓለም የዕውቀት ዐውድ ኢክርስቲያናዊ በኾኑ አካላት እንደተቃኘና ቴክኖሎጂውን ለጥፋትም ኾነ ለልማት መጠቀም እንደሚቻል ጠቅሰው ጊዜውን በቍሳዊ ነገር መለካትና ለመንፈሳዊ ሕይወት ትኵረት አለመስጠት በብዙዎች ዘንድ እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡ ለዚህም መፍትሔው የስብከተ ወንጌል አገልጋዮችን በብዛትም በጥራትም በማፍራት ምእመናንን ከጥፋት መጠበቅ መኾኑን በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡

‹‹ስብከተ ወንጌልን ከማስፋፋት አንጻር የማኅበራዊ ድረ ገጾች አስተዋጽዖ›› የሚለው ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ አቶ ነጻነት ተስፋዬም ማኅበራዊ ድረ ገጾች የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከቦታ ቦታ ሳይንቀሳቀሱ ወንጌልን እንዲያስተምሩ፤ ምእመናንም ባሉበት ቦታ ኾነው እንዲማሩ የሚያስችሉ መሣሪያዎች መኾናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ነጻነት ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በተፈለገው መጠን እየተጠቀመች አለመኾኗን በማስታዎስ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመጠቀም ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪና ለአገር አሳቢ ትውልድ ማፍራት እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡

dscf6182

አቶ ነጻነት ተስፋዬ

በቤተ ክርስቲያን ወጥ የኾነ የድረ ገጽ አጠቃቀምና ተቋማዊ አደረጃጀት አለመኖር፣ የሃይማኖት አባቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መኾን፤ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን የቅሰጣ መልእክት፤ ማኅበራዊ ሚዲያውን የጥፋት መሣሪያ ብቻ አድርጎ ማሰብና የመሳሰሉት ችግሮች ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ስንጠቀም ከሚገጥሙን መሰናክሎች መካከል እንደሚጠቀሱ አቶ ነጻነት አስገንዝበው የማኅበራዊ ድረ ገጾችን አጠቃቀም ከፍ ለማድረግም የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት፤ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን ልምድ መውሰድ፤ በስብከተ ወንጌል ላይ ብቻ ያተኰረ ትምህርት መስጠት፤ ሰባክያነ ወንጌል፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የራሳቸው ድረ ገጽ እንዲኖራቸውና የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ማድረግ አስፈላጊ መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም ማኅበራዊ ድረ ገጾች ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ዓይነተኛ ሚና እንዳላቸው ኹሉ በአግባቡ ካልተጠቀምንባቸው ደግሞ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ ስለሚኾን ጉዳታቸውን ከጥቅማቸው በመለየት መጠቀም እንደሚገባ አቶ ነጻነት አስታውሰዋል፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ ከጥቅምት ፲፮-፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም፤ ገጽ ፩ – ፪፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በዜማ መሣሪያዎችና በልሳነ ግእዝ ያሠለጠናቸውን ፭፻፶ ተማሪዎች አስመረቀ

ጥቅምት ፲፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በይብረሁ ይጥና

mireqa

ከምሩቃኑ መካከል ከፊሎቹ

በማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት አስተዳደር ሥር የሚገኘው የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርትና ሥልጠና ማእከል ለ፲፪ኛ ጊዜ በዜማ መሣሪያዎችና በልሳነ ግእዝ ያሠለጠናቸውን ፭፻፶ ተማሪዎች ጥቅምት ፲፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በማኅበሩ አዳራሽ አስመረቀ፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ለምሩቃኑ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ ‹‹ኹላችሁም እዚህ የተሰበሰባችሁት እግዚአብሔርን ለማገልገል ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ አገር ሰላም ሲኾን ነው፡፡ በመኾኑም እግዚአብሔር ለአገራችን ሰላሙን፣ ፍቅሩንና ቸርነቱን እንዲሰጥልን ተግተን ልንጸልይ ያስፈልጋል›› በማለት ተናግረዋል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የአገር ውስጥ ማእከላት ሓላፊና የማኅበሩ ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ሰይፈ ዓለማየሁ በበኩላቸው የማኅበሩ ተቀዳሚ ዓላማ የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት ሳይበረዝና ሳይከለስ ጠብቆ በማቆየት ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ መኾኑን ጠቅሰው ‹‹እናንተ ተመራቂዎችም የዚሁ ዓላማ አካል በመኾናችሁ የተማራችሁትን ትምህርት ለሌሎችም ማስተላለፍ አለባችሁ›› ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የትምህርትና ሥልጠና ማእከሉ ከ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከ፴፻ (ሦስት ሺሕ) በላይ ምእመናንን በመንፈሳውያን የዜማ መሣሪያዎችና በልሳነ ግእዝ በማሠልጠን ለአገልግሎት እንዲበቁ ማድረጉን በማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት አስተዳደር ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ዲያቆን ጌትነት ፍቅሬ ገልጸው በዚህ ዓመትም በበገና ድርደራ ፫፻፶፰፣ በከበሮ አመታት ፹፱፣ በመሰንቆ ቅኝት ፴፭ እና በዋሽንት ድምፅ አወጣጥ ፮፣ እንደዚሁም በልሳነ ግእዝ ፷፪ በድምሩ ፭፻፶ ተማሪዎችን አሠልጥኖ ጥቅምት ፲፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ማስመረቁን አስታውቀዋል፡፡

ከበገና ተመራቂዎች መካከል ጋዜጠኛ መስከረም ጌታቸውና የሕክምና ተማሪዋ ቤቴል ደጀኔ በገናን ለመማር ምን እንዳነሣሣቸው ለዝግጅት ክፍላችን ሲገልጹ የበገና መሣሪያ እግዚአብሔር ከሚመሰገንባቸው መንፈሳውያን የዜማ መሣሪያዎች መካከል አንደኛው ቢኾንም እንደ መንፈሳዊ ሀብትነቱና እንደ ሀገራዊ ቅርስነቱ ትኵረት ሳይሰጠው መቆየቱን ጠቅሰው ‹‹ቅርሶቻችንን መጠበቅና ማስጠበቅ የምንችለው በትምህርት በመኾኑ በገና ድርደራ ልንማር ችለናል›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ለአጋዥ ድርጅቶች፣ ለመምህራንና ለምሩቃኑ በልማት ተቋማት አስተዳደር ዋና ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ኀይሉ ፍሥሐ የምስክር ወረቀት ከተበረከተ በኋላ መርሐ ግብሩ በአባቶች ቃለ ምዕዳንና ጸሎት ተፈጽሟል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መጀመርን አስመልክቶ ከቅዱስ ፓትርያርኩ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

020

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የማኅበረ ቅዱሳን፣ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች በተገኙበት በዛሬው ዕለት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መጀመርን አብሥረዋል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ የሰጡትን ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

001

002

ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ

ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

mathew

ቅዱስ ማቴዎስ

የጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አምላካዊ ትእዛዝ ተቀብለው ወንጌልን ለመላው ዓለም በማብሠር መምለክያነ ጣዖትን ወደ አሚነ እግዚአብሔር፣ አሕዛብን ወደ ክርስትና ከመለሱ ቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ አንደኛው ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ አገሩ ናዝሬት፣ የዘር ሐረጉም ከይሳኮር ነገድ ሲኾን አባቱ እልፍዮስ (ዲቁ)፣ እናቱ ደግሞ ካሩትያስ ይባላሉ፡፡

ለደቀ መዝሙርነት ከመመረጡ በፊት ‹ሌዊ› ይባል ነበረ፤ ከተጠራ በኋላ ግን ‹ማቴዎስ› ተብሏል፡፡ ‹ማቴዎስ› ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹ጸጋ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ስጦታ)› ማለት ሲኾን ስሙን ያወጣለትም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ለወንጌል አገልግሎት የተጠራውም በቅፍርናሆም ከተማ ከቀራጭነት ሥራ ላይ ነው /ማቴ. ፱፥፱-፲፫፤ ሉቃ. ፭፥፳፯-፴፪/፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ቍጥሩ ከ፲፪ቱ ሐዋርያት ሲኾን ከ፬ቱ ወንጌሎች አንደኛውን የጻፈው እርሱ በመኾኑ ‹ወንጌላዊ› እየተባለ ይጠራል፡፡ ወንጌሉን የጻፈውም ጌታችን ባረገ በ፰ኛው ዓመት መጨረሻ በ፵፩ /፵፪ ዓ.ም፣ ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በመጀመሪያው ዘመን በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው /ማቴ.፳፰፥፳/፡፡ ጽሕፈቱንም በፍልስጥኤም ጀምሮ በህንድ ፈጽሞታል፡፡

እንደ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ወንጌሉ በውስጡ ከ፻፶ በላይ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን ማካተቱ አይሁድን ለማሳመን የተጻፈ ለመኾኑ ማስረጃ ነው፡፡ የማቴዎስ ወንጌል ከኦሪታዊ ይዘቱ አኳያ በመጀመሪያ ተቀመጠ እንጂ የተጻፈው ግን ከማርቆስ ወንጌል ቀጥሎ እንደኾነም መምህራን ይናገራሉ፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በሀገረ ስብከቱ በፍልስጥኤም ጌታችን ከፅንስ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ድረስ ያደረጋቸውን ተአምራት፣ ያስተማረውን ትምህርትና የሠራቸውን ትሩፋቶች ሲያስተምራቸው ብዙ አሕዛብ ከኦሪት ወደ ወንጌል፤ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመልሰዋል፡፡ ምእመናኑ ‹‹በቃል ያለ ይረሳል፤ በመጽሐፍ ያለ ይወረሳልና ያስተማርኸንን ጻፍልን›› ብለውት፤ አንድም እንደ አባትነቱ ከራሱ አንቅቶ /አመንጭቶ/፤ አንድም አይሁድ ክርስቲያኖችን ‹‹ክርስቶስ ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም መኾኑን ሠፍራችሁ፣ ቈጥራችሁ አስረዱን›› ቢሏቸው ለማስረዳት የዕውቀት ማነስ ነበረባቸውና እርሱ ጽፎላቸዋል፡፡

ወንጌሉን ከጻፈ በኋላም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ አፓንጌ በሚባል አገር ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን በክርስቶስ አሳምኗል፡፡ የማቴዎስን ወንጌል ወንጌላዊው /ሐዋርያው/ ዮሐንስ በእልአንሳን፣ በህንድና በኢየሩሳሌም አገሮች እየተረጐመ አስተምሮታል፡፡ የእርሱ ስብከት በመጽሐፍ ቅዱስ አለመጠቀሱም መላ ሕይወቱን ለክርስቶስ አገልግሎት የሰጠ ሐዋርያ መኾኑን እንደሚያሳይ መምህራን ይመሰክራሉ፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ‹‹ወልደ ዳዊት፣ ወልደ አብርሃም›› በማለት የክርስቶስን ምድራዊ ልደት /ሰው መኾን/ ጽፏልና ከአራቱ የኪሩቤል ገጽ መካከል በአንደኛው በገጸ ሰብእ ይመሰላል፡፡ የኤፌሶን ወንዝ ፈለገ ሐሊብ ይባላል፤ ርስትነቱም ለሕፃናት ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም በዘር የሚወለዱ አበውን ልደት ጽፏልና፤ ዳግመኛም ሄሮድስ ስላስፈጃቸው ሕፃናት ተናግሯልና በኤፌሶን ወንዝ ይመሰላል፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልን አስተምሮ ብዙዎችን ወደ አሚነ እግዚአብሔር ከመለሰ በኋላ ጌታችን ወደ ካህናት አገር እንዲሔድና የካህን ልብስ ለብሶ፣ ፀጉሩንና ጺሙን ተላጭቶ፣ በቀኝ እጁ ዘንባባ ይዞ ወደ አገሩ ቅፅር እንዲገባ ስላዘዘው በደመና ተጭኖ ሔዶ ወደ ቤተ ጣዖታቱ ገብቶ በጸለየ ጊዜ መብረቅ የመሰለ ብርሃን ወረደ፡፡ የአምላክን ከሃሊነት ለመግለጥ በተከሠተው ርዕደ መሬትም የአገሩ ጣዖታት ኹሉ ወድቀው ተሰባበሩ፡፡ አርሚስ የሚባለው የጣዖቱ ካህንም ካየው አምላካዊ ብርሃንና ድንቅ ተአምር የተነሣ በክርስቶስ አምኖ ከተጠመቀ በኋላ የቅዱስ ማቴዎስ ረድእ ኾኗል፡፡

ይህ ክሥተትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙዎችን በክርስቶስ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል፡፡ ያማኞች ቍጥርም ፬ ሺሕ እንደ ነበረ በገድለ ሐዋርያት ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ በኋላ የንጉሡ ልጅ በሞተ ጊዜ ቅዱስ ማቴዎስ ወደ እግዚአብሔር ጸልዮ ከሞት ቢያስነሣው ንጉሡ፣ ቤተሰቦቹና የአገሩ ሰዎች ኹሉ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው አጵሎን የተባለውን ጣዖት በእሳት አቃጥለው ቤተ ጣዖቱን የአምልኮተ እግዚአብሔር መፈጸሚያ ሥፍራ አድርገውታል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም አርሚስን ኤጲስ ቆጶስ በማድረግ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾሞላቸዋል፡፡

በገድለ ሐዋርያት እንደ ተጠቀሰው ቅዱስ ማቴዎስ ከማረፉ በፊት በደመና ተነጥቆ ብሔረ ብፁዓን ገብቷል፤ በዚያም ሄሮድስ በግፍ በጨፈጨፋቸው ሕፃናት ክብረ በዓል ጌታችን ወደ እነርሱ ሲመጣ፣ መላእክትም በዙሪያው ከበው ሲያመሰግኑት ያይ ነበር፡፡ ከዚያ ተመልሶም በየአገሩ እየዞረ ወንጌልን አስተምሯል፤ ካስተማረባቸው አገሮችም ፍልስጥኤም፣ ፋርስ፣ ባቢሎን፣ ኢትዮጵያና ዓረቢያ ይጠቀሳሉ፡፡ የማስተማር ተልእኮው የተከናወነውም በታንሿ እስያ ውስጥ ነው፡፡ ግሪካውያን አሕዛብ «አምላካችንን ሰደበብን» ብለው አሥረውት በነበረ ጊዜም ወኅኒ ቤት ኾኖ ይሰብክ ነበር፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በ፵ ዓ.ም በአገራችን በኢትዮጵያ እየተዘዋወረ ወንጌልን እንደ ሰበከና በዘመኑ የነበሩ ኦሪታውያን ነገሥታትን ጨምሮ በርካታ አሕዛብን አስተምሮ በማጥመቅ ወደ ክርስትና ሃይማኖት  እንደ መለሰ፤ እንደዚሁም ለምጻሞችን በማንጻት፣ አንካሶችን በማርታት፣ ሕሙማንን በመፈወስ፣ ሙታንን በማስነሣት ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እንዳደረገ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና በትግራይ ክልል በማኅበረ ጻድቃን ዴጌ ገዳም የሚገኙ የብራና መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

በአገልግሎቱ መጨረሻም በትርያ በምትባል አገር ሲያስተምር አገረ ገዥው አሠረው፡፡ በወኅኒ ቤቱም ጌታው ለንግድ የሰጠውን ገንዘብ ማዕበል ወስዶበት በዕዳ ምክንያት የሚያለቅስ አንድ እሥረኛ አገኘና አጽናንቶ መኰንኑ ገንዘቡን ከሕዝቡ ለምኖ እንዲከፍለው በመሻት ከእሥር እንደሚፈታው፤ ከባሕር ዳርቻም የወደቀ ወርቅ የተሞላ ከረጢት እንደሚያገኝ፤ ያንንም ለጌታው ከሰጠ በኋላ ከዕዳና ከእሥር ነጻ እንደሚኾን አስረዳው፡፡ ሰውየውም ቅዱስ ማቴዎስ የተናገረው ኹሉ ስለ ተፈጸመለት ለቅዱስ ማቴዎስ እየሰገደ፤ ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ›› እያለ ሃይማኖቱንና ደስታውን ገለጸ፡፡ ይህንን ድንቅ ተአምር የሰሙ ብዙ አሕዛብም በጌታችን አምነዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም አርያኖስ በሚባል ንጉሥ ትእዛዝ ጥቅምት ፲፪ ቀን አንገቱን በሰይፍ ተቈርጦ በሰማዕትነት ዐርፏል፤ ምእመናንም ሥጋውን በክብር ቀብረውታል፡፡ ትርጓሜ ወንጌል ደግሞ ብስባራ በምትባል አገር በደንጊያ ተወግሮ በሰማዕትነት ካረፈ በኋላ የቂሣርያ ክፍለ ዕጣ በምትኾን በቅርጣግና መቀበሩን ይናገራል፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ እኛንም በሐዋርያው በቅዱስ ማቴዎስ ጸሎት ይማረን፤ በረከቱም ይደርብን፡፡

ምንጭ፡-

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ጥቅምት ፲፪ ቀን፤

የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፤

የማቴዎስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ፤

ገድለ ሐዋርያት፡፡

፴፭ኛው የሰበካ መንፈሳዊ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ተፈጸመ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

35

የጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከጥቅምት ፯ – ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ለአራት ቀናት ሲካሔድ የቆየው ፴፭ኛው የሰበካ መንፈሳዊ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ተፈጸመ፡፡

በጉባኤው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅና የየመምሪያ ሓላፊዎች፣ በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት አህጉረ ስብከት ተወካዮች፣ የአድባራና ገዳማት አስተዳዳዎች፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት፣ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች፣ እንደዚሁም ጥሪ የተደረገላቸው የአገር ውስጥና የውጪ አገር እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በፓትርያርኩ ርእሰ መንበርነት፣ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ መሪነት የተካሔደው ይህ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ጥቅምት ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በቅዱስ ፓትርያርኩና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎተ ቡራኬ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ በቅዱስ ፓትርያርኩና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቃለ በረከት ተሰጥቷል፤ እንደዚሁም የኹሉም አህጉረ ስብከትና በጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ ክፍሎች ሪፖርቶች ቀርበዋል፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ዕለት ‹‹እንዘ አልብነ ኵሉ ብነ፤ ምንም የሌለን ስንኾን ኹሉ የእኛ ነው፤›› /፪ኛ ቆሮ.፮፥፲/ የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ቃለ በረከት የሰጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ‹‹… እኛ ካህናት ኹሌም መጨነቅ ያለብን ስለ ሀብት ሳይኾን ስለ ምእመናን ጥበቃ ነው፡፡ ምእመናን ካሉ ሀብቱ አለና፡፡ ከኀምሳ ሚሊዮን በላይ ምእመናን ካሉንና በእነርሱ ላይ ተገቢ ጥበቃና አገልግሎት ካበረከትን የሚጐድልብን አንዳች ነገር አይኖርም፡፡ የሰበካ ጉባኤ ዐቢይ ተልእኮም ይኸው ነው፡፡ ሰበካ ጉባኤ እኛ ካህናት ሀብታሞች መኾናችንን ያረጋገጠ ወንጌላዊ መሣሪያ እንደ ኾነ ከቶዉኑ ልንዘነጋ አይገባም …›› ብለዋል፡፡

ቃለ ቡራኬያቸውን ሲያጠቃልሉም ‹‹… ሌት ተቀን በመሥራት ምእመናንን እንደ እግዚአብሔር ቃል በመጠበቅና በመንከባከብ እንደዚሁም የሚጠበቅብንን መልካም ሥነ ምግባር ኹሉ ለምእመናን በማድረግ የቤተ ክርስቲያናችንን ዕድገትና ሉዓላዊ ክብር እስከ መጨረሻው እንድናረጋግጥ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን›› ሲሉ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

የመንበረ ፓትርያርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የመምሪያዎችንና የድርጅቶችን የ፳፻፰ ዓ.ም የሥራ ዘመን ሪፖርት ለጉባኤው ያቀረቡ ሲኾን በድምፅ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ በቅዱስ ፓትርያኩ ቡራኬ መመረቁ፣ በአፋን ኦሮሞ የተዘጋጀው መጽሐፈ ቅዳሴ አገልግሎት ላይ መዋሉ፣ የ፳፬ ሰዓት የቴሌቭዥን ሥርጭት መጀመሩና በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች አብያተ ክርስቲያናት መታነጻቸው በሪፖርቱ ውስጥ ከተካተቱ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ከዚሁ ኹሉ ጋርም ማኅበረ ቅዱሳን ለአብነት መምህራንና ተማሪዎች ወርኃዊ የገንዘብ ድጎማና የቀለብ ድጋፍ ማድረጉ፤ በልዩ ልዩ አህጉረ ስብከት የአብነት ት/ቤቶችን፣ ዘመናዊ ት/ቤቶችንና የገቢ ማስገኛ ሕንጻዎችን ማስገነባቱ፤ እንደዚሁም በኢትዮጵያ በሚገኙ ፬፻፮ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን በትምህርተ ወንጌል አሠልጥኖ ማስመረቁ፤ በደቡብ ኦሞ፣ በመተከልና በጋሞ ጎፋ አህጉረ ስብከት በድምሩ ዐሥራ ስምንት ሺሕ አምስት መቶ ሰባ ስምንት አዳዲስ አማንያንን አስተምሮ የሥላሴ ልጅነትን ማሰጠቱ፤ አዳዲስና ነባር የኅትመት ውጤቶችን አሳትሞ ማሠራጨቱ፤ በተጨማሪም ማኅበሩ በበጀት ዓመቱ በዕቅድ ያከናወነው ተግባርና ያኘው ገቢ ከነወጪና ቀሪው በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት ተገልጿል፡፡

ከአህጉረ ስብከት ሪፖርች መካከል የጋምቤላ ሀገረ ስብከት በአካባቢው ቋንቋ ወንጌልን በማስተማር የሥላሴን ልጅነት እንዲያገኙ ያደረጋቸውን የአካባቢው ተወላጅ የኾኑ የመንግሥት ሠራተኞችን በጉባኤው እንዲሳተፉ ማድረጉ በጉባኤው ተሳታፊዎች ዘንድ የተደነቀና እንደ ተሞክሮ የሚወሰድ ተግባር መኾኑ ታውቋል፡፡

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው በተከፈተበት ዕለት በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አቅራቢነት በምልአተ ጉባኤው በተመረጡ ቃለ ጉባኤ አርቃቂ አባላት አማካይነት ባለ ፳ ነጥብ የጋራ ዓቋም መግለጫ የተዘጋጀ ሲኾን በቅዱስ ሲኖዶስና በቅዱስ ፓትርያኩ የሚወጡ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን መተግበር፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መመራትና ሕግጋቱን ማስፈጸም፣ መንፈሳዊ አስተዳርን በማስፈንና ዘመናዊ ሒሳብ አያያዝን በመጠቀም ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል፣ የሕገ ወጥ ሰባክያንንና የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ መግታት፣ ለአብነት ት.ቤቶች ትኩረት መስጠት፣ ወጣቱ ትውልድ ቤተ ክርስቲያንን እንዲረከብ በትምህርተ ወንጌል አእምሮውን መገንባት፣ የተማረ የሰው ኀይልን የሚያካትቱ ተቋማትን ማስፋፋት፣ ወዘተ የመሳሰሉት ተግባራት በዓቋም መግለጨው ውስጥ ከተጠቀሱ ነጥቦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በጉባኤው ማጠቃለያ ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ቅዱስነታቸውን ጨምሮ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስና ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ቃለ በረከትና ትምህርተ ወንጌል ከሰጡ በኋላ ላለፉት ሦስት ዓመታት ጠቅላይ ቤተ ክህነትን በዋና ሥራ አስኪያጅነት፣ ቅዱስ ሲኖዶስን በዋና ጸሐፊነት ለመሩት ለብፁዕ አቡነ ማቴዎስና ለብፁዕ አቡነ ሉቃስ፤ እንደዚሁም በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አህጉረ ስብከት የምስጋና የምስክር ወረቀትና ሽልማት ከቅዱስ ፓትርያርኩ ተበርክቶላቸዋል፡፡

በመጨረሻም የሰበካ መንፈሳዊ አጠቃላይ ጉባኤው በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ ጸሎተ ቡራኬ ተፈጽሟል፡፡

ቋሚ ሲኖዶስ በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጠ

በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ላይ ቋሚ ሲኖዶስ መግለጫ መስጠቱ ይታወቃል፡፡ የመግለጫውን ሙሉ ቃል እንደሚከተለው እናቀርባለን፤

 መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

‹‹ኅሡ ሰላማ ለሀገር እስመ በሰላመ ዚአሃ ይከውን ሰላምክሙ፤ ስለ ሀገር ሰላምን ሹ፤ ፈልጉ፡፡ በእርሷ ሰላም የእናንተ ሰላም የጸና ይሆናልና›› ኤርምያስ ም.29 ቁ.7

ከቅርብ ወራት ወዲህ በአገራችን ኢትዮጵያ በአንዳንድ ቦታዎች በተፈጠረ ችግር ደርሶ በነበረው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት መውደም በወቅቱ በሞቱት ወገኖቻችን ምክንያት ቤተ ክርስቲያናችን ሐዘኗን መግለጿ ጸሎተ ምሕላ ማወጇ የሚታወቅ ነው፡፡ አሁን ደግሞ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ዓመታዊውን የእሬቻ በዓል ለማክበር ከተሰበሰቡት መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት ሕይወታቸው ስለጠፋ ወገኖቻችን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፡፡ ኅሡ ሰላማ ለሀገር እስመ በሰላመ ዚአኀ ይከውን ሰላምክሙ ስለ ሀገር ሰላምን ሹ ፈልጉ፤ በእርሷ ሰላም የእናንተ ሰላም የጸና ይሆናልና፡፡ እንዳለው ሰላም ስንል የሰላም መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብ በስምምነት በአንድነት አብሮ መኖር ማለት ነው፡፡ ሰዎች ሲገናኙ ጭምር የሚለዋወጡት የሰላምታ ቃል የሰላም ውጤት መሆኑ ሁሉም የሚገነዘበው ነው፡፡

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን!

አገራችን ኢትዮጵያ አገረ እግዚአብሔር ተብላ ከመጠራቷም በላይ ረድኤተ እግዚአብሔር የሚታይባት በተፈጥሮ ፀጋዎች እጅግ የታደለች እኛም በኢትዮጵያዊነታችንና በአንድነታችን የምንኮራባት አገር ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ በተለይም እኛ ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ በታሪክም የምንታወቅበትና ለሁሉም ዓለም ልዩ ሁነን የምንታይበት መለያችን አንድነታችንና መተሳሰባችን፣ ሌላውን እንደራሳችን አድርገን መውደዳችን፣ ያለንን ተካፍለን መኖራችን፣ ቤት የእግዚአብሔር ነው ብለን አንዱ ሌላውን ተቀብሎ ማስተናገዳችን ፍጹም የኢትዮጵያዊነት መለያችን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአገራችን በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች በሚነሱ ጥያቄዎች ምክንያት አለመግባባት እየተፈጠረ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ፣ በአገር ሀብት ላይ ውድመት መድረሱ፣ ልማታዊ እንቅስቃሴ እየተስተጓጐሉ መምጣታቸው፣ በተለይም በቢሾፍቱ ከተማ ይከበር በነበረ ዓመታዊ የእሬቻ በዓል ላይ በተከሰተ ግጭት ለበዓሉ ተሰብስበው ከነበሩት ውስጥ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ በመገናኛ ብዙኃን ከተገለፀበት ጊዜ አንስቶ ቤተ ክርስቲያናችንና ቅዱስ ሲኖዶሱን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡

በመሆኑም ይህ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ሕልፈተ ሕይወት መላውን የአገሪቱን ዜጎች አሳዝኗል፡፡ በቀጣይም በመሪዎችም ሆነ በሕዝቦች ዘንድ ፍፁም የእግዚአብሔር ሰላም ካልሰፈነ ውሎ መግባትም ሆነ አድሮ መነሳት ሥጋት ከመሆኑም በላይ ይህች በታሪኳ ሰላሟና አንድነቷ የተመሰከረላት ቅድስት አገራችን ስሟ እንዳይለወጥ ሁላችንም የመጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን፡፡ በግል ሠርቶ ለመበልፀግም ሆነ ለአገር መልካም ሥራ መሥራት የሚቻለው በአገር ፍቅርና ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ያለ ሰላም ሰው እግዚአብሔርን ቀርቶ ወንድም ወንድሙን ማየት አይችልም፡፡ በመሆኑም የሰላም ባለቤት እግዚአብሔር ለሕዝባችንና ለአገራችን ሰላም እንዲሰጥልን በነቢዩ እንደተነገረው ሁላችንም ሰላምን ልንሻ ስለ ሰላምም አጥብቀን ልንጸልይ ይገባል፡፡

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን!

ይህንኑ የወገኖቻችንን ሕልፈተ ሕይወት መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥልቅ ሐዘን የተሰማት በመሆኑ ቋሚ ሲኖዶስ በደረሰው አሳዛኝ ድርጊት ተወያይቶ የሚከተለውን ወስኖአል፡፡

  1. ከመስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በመላ አገሪቱ እና በውጭው አገር በሚገኙ አህጉረ ስብከት ገዳማት፣ አድባራትና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሕይወታቸው ለጠፋውና ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ወገኖቻችን እግዚአብሔር ዕረፍተ ነፍስን እንዲሰጥልን ለሰባት ቀናት በጸሎት እንዲታሰቡ ቋሚ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡
  2. ከዚሁ ጋር የሰላም ባለቤት እግዚአብሔር ለአገራችን ኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ሰላሙን እንዲሰጥልን በችግሩ ምክንያት ተጎድተው በሕክምና የሚገኙ ወገኖቻችንን ጤናና ፈውስ እንዲሰጥልን በእነዚሁ ሰባት ቀናት ጸሎተ ምሕላ እንዲደርስ ቋሚ ሲኖዶስ ወስኖአል፡፡
  3. እንዲሁም ስለ አገራችን ዘላቂ ሰላም በሁሉም ዘንድ የጋራ ጥረት ማድረግ የሚገባ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያናችን ግን ጥንትም ታደርገው እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ለሰላሙ መምጣት ከሚመለከታቸው ጋር ሁሉ የበኩሏን ጥረት በማድረግ የምትቀጥል ሲሆን በአገራችን ውስጥ ጥያቄ ያላቸውና ምላሽ የሚፈልጉ ዜጎች ጥያቄዎቻቸውንና ፍላጎታቸውን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ለመንግሥት እንዲያቀርቡ፤ መንግሥትም ባለበት አገራዊ ኃላፊነት መሠረት ጥያቄዎችን በአግባቡ እየተቀበለ ፍትሐዊና ወቅታዊ ምላሽ እንዲሰጣቸው ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ታሳስባለች፡፡
  • እግዚአብሔር አምላክ ከዚህ ዓለም የተለዩ ወገኖቻችንን ነፍስ ይማርልን፣
  • በሕክምና ላይ ላሉት ምሕረት ያድርግልን፣
  • አገራችንና ሕዝቦቿን በሰላም ይጠብቅልን፡፡

አሜን፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም

ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ዘመነ ጽጌ

መስከረም ፳፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዝግጅት ክፍሉ

በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ በአገራችን በኢትዮጵያ የወቅቶች ሥርዓተ ዑደት መሠረት ከመስከረም ፳፮ ቀን ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ፺ ቀናትን የሚያጠቃልለው ጊዜ ‹‹ዘመነ መጸው›› ይባላል፡፡ ‹‹መጸው›› ማለት ወርኀ ነፋስ ማለት ሲኾን ይኸውም ‹‹መጸወ ባጀ፤ መጽለወ ጠወለገ›› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ዘመነ መጸው ከዘመነ ክረምት ቀጥሎ የሚብት (የሚገባ) የልምላሜ፣ አበባ፣ የፍሬ ወቅት ነው፡፡ በውስጡም አምስት ንዑሳን ክፍሎችን የሚያካትት ሲኾን እነዚህም፡- ዘመነ ጽጌ፣ ዘመነ አስተምህሮ፣ ዘመነ ስብከት፣ ዘመነ ብርሃን እና ዘመነ ኖላዊ ናቸው /ያሬድና ዜማው፣ ገጽ ፵፰-፵፱/፡፡

ከአምስቱ የዘመነ መጸው ክፍሎች መካከል የመጀመሪያው ክፍለ መጸው ዘመነ ጽጌ ተብሎ የሚጠራ ሲኾን ይህም ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ቀን ድረስ ያሉትን ፵ ቀናት ያጠቃልላል፡፡ ‹ጽጌ› ቃሉ ‹ጸገየ አበበ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም አባባ ማለት ነው፡፡ ‹ዘመነ ጽጌ› ደግሞ ‹የአበባ ወቅት፣ የአበባ ጊዜ፣ የአበባ ዘመን› ማለት ነው፡፡ ይህ ወቅት ዕፀዋት በአበባ የሚያጌጡበት፣ ምድር በአበቦች ኅብረ ቀለማት የምታሸበርቅበት፣ ወንዞች ንጹሕ የሚኾኑበት፣ ጥሩ አየር የሚነፍስበት፣ አዕዋፍ በዝማሬ የሚደሰቱበት፣ እኛም የሰው ልጆች ‹‹አሠርጎካ ለምድር በሥነ ጽጌያት፤ አቤቱ ምድርን በአበቦች ውበት አስጌጥሃት›› እያልን የዘመናት አስገኚና ባለቤት የኾነውን ልዑል እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት፤ ከዚህም ባሻገር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከገሊላ ወደ ግብጽ ምድር መሰደዷን የምናስብበት ወቅት ነው፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ልሔም በተወለደ ጊዜ የዘመኑ ንጉሥ ሄሮድስ ሥልጣኔን ይቀማኛል በሚል ቅናት ተነሣሥቶ ጌታችንን ለማስገደል አሰበ፡፡ ያንጊዜም ጌታችን በተአምራት መዳን ሲቻለው የትዕግሥት፣ የትሕትና አምላክ ነውና በለበሰው ሥጋ በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ በመልአኩ ተራዳኢነት፣ በአረጋዊው ዮሴፍ ጠባቂነትና በሰሎሜ ድጋፍ ከገሊላ ወደ ግብጽ ተሰዶ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቆይቷል፡፡ ሄሮድስም ጌታን የጋኘሁ መስሎት በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙ ሀለት ዓመት ከዚያ በታች የኾኑ አንድ መቶ ዐርባ አራት ሺሕ ሕፃናትን በግፍ አስፈጅቷል፡፡

በተአምረ ማርያምና በማኅሌተ ጽጌ ተጽፎ እንደሚገኘው ጌታችን በግብጽ ምድር በስደት ሳለ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከልም እናቱን እመቤታችንን የዘለፏትን ትዕማንና ኮቲባ የሚባሉ ሴቶችን ከሰውነት ወደ ውሻነት መቀየሩ፤ ውሃ በጠማቸው ጊዜ ውሃ እያፈለቀ ማጠጣቱና ይህንን ውሃ ክፉዎች እንዳይጠጡት መራራ ማድረጉ፤ ለችግረኞችና ለበሽተኞች ግን ጣፋጭ መጠጥና ፈዋሽ ጠበል ማድረጉ፤ ‹‹የሄሮድስ ጭፍሮች ደርሰው ልጅሽን ሊገድሉብሽ ነው›› ብሎ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ እመቤታችንን በማስደንገጡ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ድንጋይ ኾኖ እንዲቆይ ማድረጉ፤ መንገድ ላይ የተራዳቸው ሽፍታ ሰይፉ በተሰበረች ጊዜ እንደ ቀድሞው ደኅና እንድትኾን ማድረጉ፤ እንደዚሁም የግብጽ ጣዖታትን ቀጥቅጦ ማጥፋቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የጌታችንና የእመቤታችን የስደት ወቅት በወርኀ ግንቦት ነው፤ ነገር ግን ዘመነ ጽጌ የአበባና የፍሬ ወቅት በመኾኑ እመቤታችንን በአበባ፣ ጌታችንን ደግሞ በፍሬ እየመሰሉ ለማመስገንና ለማወደስ በሚያስችል ምሥጢር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የስደቱ ጊዜ በዘመነ ጽጌ እንዲዘከር አድርገዋል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዘለዓለሙ የማይደርቀውን የሕይወት ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን ንጽሕት የማትጠወልግ አበባ ናትና፡፡ ይህ የእመቤታችን አበባነትና የጌታችን ፍሬነትም እንደ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫና አባ ጽጌ ድንግል ባሉ ሊቃውንት ድርሰቶች በሰፊው ተገልጧል፡፡

በዘመነ ጽጌ በማኅሌትና በቅዳሴ ጊዜ የሚቀርቡ መዝሙራትና የሚሰጡ ትምህርቶችም ይህንኑ ምሥጢር የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት በሚገኙ ሰንበታትም ሊቃውንቱ ሌሊቱን ሙሉ ስለ እመቤታችን አበባነትና ስለ ጌታችን ፍሬነት የሚያትት ትምህርት የያዙትን ማኅሌተ ጽጌና፣ ሰቆቃወ ድንግልን ከቅዱስ ያሬድ ዚቅ ጋር በማስማማት ሲዘምሩ፣ ሲያሸበሽቡ ያድራሉ፡፡ ቅዳሴውም በአባ ሕርያቆስ የተደረሰውና ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ሥላሴንና ነገረ ማርያምን የሚተነትነው ቅዳሴ ማርያም ነው፡፡ ምንባባቱም ከዚሁ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ናቸው፡፡

በአጠቃላይ እመቤታችን በስደቷ የደረሰባትን መከራ በማስታዎስ ዘመነ ጽጌን በፈቃዳቸው የሚጾሙ ካህናትና ምእመናን ብዙዎች ናቸው፡፡ ኾኖም ግን የጽጌ ጾም የፈቃድ ጾም እንጂ ከሰባቱ አጽዋማት ጋር የሚመደብ ስላልኾነ ጽጌን የማይጾሙ አባቶች ካህናትንና ምእመናንን ልንነቅፋቸው አይገባም፡፡ አምላካችን በአበባ የሚመሰለው ሰውነታችን የጽድቅ ፍሬን ሳያፈራ በሞት እንዳንወሰድ መልካም ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

ፀአተ ክረምት (ዘመነ ክረምት የመጨረሻ ክፍል)

መስከረም ፳፭ ቀን ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! ከአሁን በፊት ዘመነ ክረምትን የሚመለከት ትምህርት በአምስት ተከታታይ ክፍል ስናቀርብላችሁ ቆይተናል፡፡ ለመከለስ ያህል ‹‹ክረምት›› የሚለው ቃል ከረመ፣ ከረመ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም የዝናም፣ የአዝርዕት፣ የአረም ጊዜ፤ ዕፅዋት፣ አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር በአረንጓዴ ዕፀዋትና በልምላሜ የምታሸበርቅበት ወቅት ማለት መኾኑን፣ ከሰኔ ፳፭ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ ዘመነ ክረምት እንደሚባል፣ ዘመነ ክረምት ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት፤ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን (ምግብን) ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይና የሚያሳውቅ ዘመን እንደ ኾነ፤ ይህ ዘመነ ክረምትም በሰባት ንዑሳን ክፍሎች እንደሚመደብ፣ ይኸውም፡-

፩ኛ ከሰኔ ፳፭ እስከ ሐምሌ ፲፱ ቀን ያለው ጊዜ ዘርዕ፣ ደመና፤

፪ኛ ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፲ ቀን ያለው ጊዜ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል፤

፫ኛ ከነሐሴ ፲- ፳፰ ቀን ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ፤

፬ኛ ከነሐሴ ፳፰ እስከ ጳጉሜን ፭/፮ ቀን ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባህ፣ ብርሃን፣ መዐልት፤

፭ኛ ከመስከረም ፩-፰ ቀን ዮሐንስ፤

፮ኛ ከመስከረም ፱-፲፭ ቀን ፍሬ እንደሚባል ከ ‹‹በአተ ክረምት›› ጀምሮ እስከ ‹‹ዘመነ ፍሬ›› ድረስ ባሉት የዘመነ ክረምት ጽሑፎቻችን ተመልክተናል፡፡

‹‹ዘመነ ፍሬ›› በሚል ርእስ ባቀረብነው በክፍል አምስት ዝግጅታችንም ከመስከረም ፱ – ፲፭ ቀን ያለው ክፍለ ክረምት ‹ፍሬ› እንደሚባልና ይኸውም ልዩ ልዩ አዝርዕት በቅለው፣ አድገው፣ አብበው ለፍሬ የሚደርሱበት፤ የሰው ልጅ፣ እንስሳትና አራዊትም ጭምር የዕፀዋቱን ፍሬ (እሸት) የሚመገቡበት ወቅት እንደኾነ፤ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚቀርቡ ምንባባትና ትምህርቶችም ይህንኑ ምሥጢር እንደሚዳስሱ በማስገንዘብ የምእመናንን ሕይወት ከዕፀዋትና ከፍሬ ጋር በማመሳሰል ትምህርት ማቅረባችን የሚታዎስ ነው፡፡ በዛሬው የ‹‹ፀአተ ክረምት›› ዝግጅታችንም የመጨረሻውን የክረምት ክፍለ ጊዜ የሚመለከት አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

ከመስከረም ፲፮ – ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ፯ኛው የክረምት ክፍለ ጊዜ መስቀል በመባል የሚታወቅ ሲኾን ይኸውም ፀአተ ክረምትና በአተ መጸው የሚሰበክበት፣ ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን የሚቀርቡ ትምህርቶች ነገረ መስቀሉን የተመለከቱ ናቸው፡፡ ማለትም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ድኅነት ሲል በፈቃዱ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ስለ መሞቱ፣ በሞቱም ዓለምን ስለ ማዳኑ፣ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ስላፈሰሰበት ዕፀ መስቅሉ የተቀደሰ ስለ መኾኑ፣ በምእመናን ዘንድም ትልቅ ትርጕም ያለው ስለ መኾኑ ከሌሎች ጊዜያት በላይ በስፋት የሚነገረውና ትምህርት የሚሰጠው በዚህ ወቅት ነው፡፡

ከዚሁ ኹሉ ጋርም በአይሁድ ቅናት በጎልጎታ ለ፫፻ ዓመታት ያህል ተቀብሮ የቆየው የጌታችን ዕፀ መስቀልን ለማውጣት በንግሥት ዕሌኒ አማካይነት ቍፋሮ መጀመሩ፣ መስቀሉ ከወጣ በኋላም በዐፄ ዳዊትና በልጃቸው በዘርዐ ያዕቆብ ጥረት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ደብረ ከርቤ መቀመጡ የሚዘከረው በእነዚህ ዐሥር የፀአተ ክረምት ዕለታት ውስጥ ነው፡፡ ኹላችንም ሕዝበ ክርስቲያን ይህንን የመስቀሉን ነገር በልቡናችን ይዘን በክርስትናችን ምክንያት የሚገጥመንን ልዩ ልዩ ዓይነት ፈተና በትዕግሥት ማለፍ ይጠበቅብናል፡፡

‹‹ፀአተ ክረምት›› የሚለው የግእዝ ቃላት ጥምረት ‹‹የክረምት መውጣት›› የሚል ትርጕም አለው፡፡ ይህም ከመስከረም ፲፮ – ፳፭ ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል፡፡ የፀአተ ክረምት መጨረሻ የሚኾነውም መስከረም ፳፭ ቀን ነው፡፡ የክረምት መውጣት ሲባል ለዘመነ ክረምት የተሰጠው ጊዜ በዘመነ መጸው መተካቱን ለማመልከት እንጂ ክረምት ተመልሶ አይመጣም ለማለት አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወት እስከሚያበቃበት እስከ ኅልፈተ ዓለም ድረስ የወቅቶች መፈራረቅም አብሮ ይቀጥላል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ይህንን የወቅቶች መፈራረቅ ለመግለጽ ነው ‹‹መግባት፣ መውጣት›› እያሉ በክፍል የሚያስቀምጧቸው፡፡

አንድ የጊዜ ክፍል (ወቅት) ሲያልፍ ሌላው ይተካል፡፡ ‹‹ሲሞት ሲተካ፣ ሲፈጭ ሲቦካ›› እንደሚባለው የሰው ልጅ ሕይወትም እንደዚሁ ነው፡፡ አንደኛው ሲሞት ሌላኛው ይወለዳል፤ አንደኛው ሲወለድ ሌላኛው ይሞታል፡፡ ወቅቶች የጊዜ ዑደት እንደ መኾናቸው ለሰው ልጅ ምቾት እንጂ ለራሳቸው ጥቅም የተዘጋጁ ሕያዋን ፍጥረታት አይደሉም፡፡ በመኾኑም ራሳቸውን እየደጋገሙ ይመላለሳሉ፤ የሰው ልጅ ግን አምሳሉን ይተካል እንጂ ራሱ ተመልሶ አይመጣም፡፡ እንግዲህ ክርስቶስ ለፍርድ ሲመጣ እንዳናፍር ዳግም በማናገኛት በዚህች ምድራዊ ሕይወታችን የማያልፍ ክርስቲያናዊ ምግባር ሠርተን ማለፍ ይጠበቅብናል፡፡ ከሞት በኋላ ዘለዓለማዊ ፍርድ እንጂ ንስሐ የለምና፡፡

በአጠቃላይ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹እነሆ ክረምት ዐለፈ፤ ዝናቡም ዐልፎ ሔደ፡፡ አበባ በምድር ላይ ታየ፤ የመከርም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቊርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጐመራ፤ ወይኖችም አበቡ፤ መዓዛቸውንም ሰጡ …›› /መኃ.፪፥፲፩-፲፫/ በማለት እንደ ተናገረው አሁን የክረምቱ ጊዜ አብቅቶ ሌላ ወቅት ዘመነ መጸው ተተክቷል፡፡ መጭው ጊዜ የተስፋ፣ የንስሐና የጽድቅ ወቅት እንዲኾንልን እግዚአብሔርን ከፊት ለፊታችን ማስቀደም ይኖርብናል፡፡ እርሱ ከቀደመ መሰናክሎቹን ለማለፍ፣ ፈተናዎችንም ለመወጣት ምቹ ኹኔታዎችን እናገኛለንና፡፡ ክረምቱ አልፎ መጸው ሲተካ ምድር ባገኘችው ዝናም አማካይነት የበቀሉ ዕፀዋት በአበባና በፍሬ ይደምቃሉ፡፡ እንደዚሁ ኹሉ ምእመናንም በተማርነው ቃለ እግዚአብሔር ለውጥ በማምጣት እንደ ዕፀዋት በመንፈሳዊ ሕይወታችን አፍርተን ክርስቲያናዊ ፍሬ ማስገኘት ይኖርብናል፡፡ በዚህ ፍሬያችን ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔር መንግሥት ለመውረስ እንችላለንና፡፡

ይህ መንፈሳዊ ዓላማችን ይሳካልን ዘንድም እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቀው፡፡ እንደዚህ እያልን፤ ‹‹ድኅረ ኀለፈ ክረምት ወገብአ ዝናም፤ ዘአርአይከ እግዚኦ ጽጌያተ ገዳም፤ አፈወ ሃይማኖት ነዓልድ ወፍሬ ምግባር ጥዑም፤ አትግሀነ ለስብሐቲከ ከመ ትጋሆሙ አዳም፤ ለጽብስት ንህብ ወነአስ ቃህም፡፡›› ትርጕሙም፡- ክረምት ካለፈ፣ ዝናምም ወደ ቦታው ከተመለሰ በኋላ የዱር አበቦችን ያሳየህ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ! የሃይማኖት ሽቱን እናስገኝና የሚጣፍጥ የምግባር ፍሬን እናፈራ ዘንድ ተወዳጅ እንደ ኾነው የታታሪዋ ንብና የብልሃተኛዋ ገብረ ጕንዳን ትጋት እኛንም ለምስጋናህ አትጋን›› ማለት ነው /መጽሐፈ ስንክሳር፣ የመስከረም ፳፭ ቀን አርኬ/፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ብዙኃን ማርያም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፳ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

dscn9134

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ጋር (በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ውስጥ የሚገኝ ሥዕል)

በቤተ ክርስቲያናችን ከሚዘከሩ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓላት መካከል መስከረም ፳፩ ቀን የሚውለው በዓል ‹‹ብዙኃን ማርያም›› በመባል ይታወቃል፡፡ በዓሉ በሁለት ዐበይት ምክንያቶች ይከበራል፤ የመጀመሪያው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ለማዘጋጀት ከሩቅም ከቅርብም የተሰባበሰቡት ቀን፤ ሁለተኛው ደግሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል በግሸን ደብረ ከርቤ የተቀመጠበት ዕለት መኾኑ ነው፡፡ ሁለቱንም ታሪኮች ከዚህ ቀጥለን እንመለከታቸዋለን፤

በ፫፻፳፭ ዓ.ም አርዮስ የሚባል መናፍቅ የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት አልቀበልም በሚል ክህደት እርሱ ተሰናክሎ ለሌሎችም መሰናክል ኾነ፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አርዮስ ክህደቱን እንዲተው ቢመክሩትም ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይህ የአርዮስ ክህደትም በሊቃውንቱ መካከል መለያየትን ፈጥሯል፡፡ ጊዜው ታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ‹‹አብያተ ጣዖታት ይትአጸዋ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኀዋ፤ የጣዖታት ቤቶች ይዘጉ! አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ!›› የሚል ዐዋጅ የነገረበት ወቅት ነበርና ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በአርዮስ ክህደት ምክንያት በኒቅያ የሃይማኖት ጉባኤ እንዲካሔድ በየአገሩ ላሉ ሊቃውንት መልእክት አስተላለፈ፡፡

በዚህም መሠረት ከሚያዝያ ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፩ ቀን ድረስ ፳፫፻፵፰ (ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ዐርባ ስምንት) ሊቃውንት በኒቅያ ተሰበሰቡ፡፡ ኒቅያ ለዚህ ጉባኤ የተመረጠችበት ምክንያትም ጳጳሱን ከማኅበረ ካህናቱ፤ ንጉሡን ከሠራዊቱ ጋር አጠቃላ ለመያዝ የምትችል ሰፊና ምቹ ቦታ ከመኾኗ ባሻገር ለኹሉም አማካይ ሥፍራ ስለ ነበረች ነው፡፡ በጉባኤው ከተሰበሰቡ ሊቃውንት መካከልም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሙታንን ያስነሡ፣ ለምጽ ያነጹ፣ አንካሳ ያረቱ፣ የዕውራንን ዓይን ያበሩ ድውያንን የፈወሱ፣ ሌላም ልዩ ልዩ ተአምር ያደረጉ፤ እንደዚሁም ስለ ርትዕት ሃይማኖታቸው በመጋደል ዓይናቸው የፈረጠ፣ እጃቸው የተቈረጠ ይገኙበታል፡፡

ሊቃውንቱ ሱባዔ ይዘው በጸሎት ከቆዩ በኋላ ኅዳር ፱ ቀን በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ሊቀ መንበርነት፣ በእለእስክንድሮስ አፈ ጉባኤነት ጉባኤው ተጀመረ፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን ‹‹ስማችሁን፣ አገራችሁንና ሃይማኖታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ›› ባላቸው ጊዜም ከ፳፫፻፵፰ቱ መካከል ፫፻፲፰ (ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ) ሊቃውንት ሃይማኖታቸውን ሲገልጹ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና አንድ ነው›› ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ንጉሡም ‹‹ሃይማኖት እንደ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ይኹን›› ብሎ ዐዋጅ አስነግሯል፡፡ እነዚህ ሊቃውንት በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሱት ፫፻፲፰ቱ የአብርሃም ብላቴኖች ምሳሌዎች ናቸው /ዘፍ.፲፬፥፲፬/፡፡

፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በጉባኤው አርዮስን አውግዘው በመለየት ‹‹ነአምን በአሐዱ አምላክ፤ በአንድ አምላክ እናምናለን›› የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት (የሃይማኖት መሠረት) እና ሌሎችንም የሃይማኖት ውሳኔዎችን ደንግገዋል፡፡ ሊቃውንቱ ጉባኤውን ያካሔዱት ኅዳር ፱ ቀን ይኹን እንጂ በአንድነት የተሰባሰቡት መስከረም ፳፩ ቀን ስለ ነበረ ይህ ዕለት ‹‹ብዙኃን ማርያም›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለሃይማኖታዊ ጉባኤ የተሳባሰቡበት ዕለት ነውና፡፡

በሌላ በኩል መስከረም ፳፩ ቀን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በአምባሰል ተራራ በግሸን ደብረ ከርቤ የገባበትና በዓሉ የከበረበት ዕለት ነው፡፡ ታሪኩም በአጭሩ የሚከተለው ነው፤

ዐፄ ዳዊት መንፈሳዊና ደግ ንጉሥ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው በኢትዮጵያ ቸነፈር ተከሥቶ ሕዝቡ ስለ ተሰቃየባቸው እጅግ አዘኑ፤ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላኩ ባሕታዊ መጥተው ‹‹የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል አስመጥተህ በአገርህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሠርተህ ብታስቀምጥ ረሃቡ፣ ቸነፈሩ ኹሉ ይታገሥልሃል›› አሏቸው፡፡ ዐፄ ዳዊትም ከብዙ ገጸ በረከት (ስጦታ) ጋር ‹‹የጌታችንን መስቀል ላኩልኝ›› የሚል መልእክት አስይዘው መልእክተኞችን ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱ፡፡ መልእክተኞቹም በታዘዙት መሠረት መስቀሉን ይዘው መምጣታቸውን ዐፄ ዳዊት ሲሰሙ ‹‹ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት›› ብለው መስቀሉን ለመቀበል ጉዞ ጀመሩ፡፡

ዐፄ ዳዊት ስናር (ሱዳን) ደርሰው ከመልእክተኞቹ ጋር ተገናኝተው መስቀሉን በክብር አጅበው ወደ መካከል ኢትዮጵያ ለማስገባት ሲነሡም ከበቅሏቸው ወድቀው ጥቅምት ፱ ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ በዚህም ሠራዊታቸው ተደናግጠው የጌታችንን መስቀል እዚያው ትተው የዐፄ ዳዊትን አስከሬን ይዘው ተመለሱ፡፡ መስቀሉ በስናር ከቆየ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዘርዐ ያዕቆብ ሲነግሡ ወደ መሃል ኢትዮጵያ አምጥተው ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ለማስቀመጥ ቢያስቡም ምቹ ቦታ ግን ሊያገኙ አልቻሉም ነበር፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው ምቹ ቦታ ሲፈልጉ መስቀሉን በኤረር ተራራ፣ በደብረ ብርሃን፣ በመናገሻ ማርያም ዓምባ፣ በእንጦጦ ጋራ ብዙ ጊዜ አስቀምጠውት ቆይተዋል፡፡

መስቀሉ በእንጦጦ ጋራ ሳለ እግዚአብሔር አምላክ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ›› የሚል ቃል ለንጉሡ በራእይ ነገራቸው፡፡ መስቀሉን ወደ ወሎ ሀገረ ስብከት እንዲወስዱትም አዘዛቸው፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው በእግዚአብሔር መሪነት መስቀሉን ይዘው ወሎ ሲደርሱም ጌታችን ወደ አምባሰል እያመለከተ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ›› ይላቸው ነበር፤ ንጉሡ መስቀሉን ይዘው ወደ ቦታው ሲያመሩ መስቀለኛው የግሸን ተራራን አገኙ፤ በዚያም ቤተ ክርስቲያን አሠርተው በ፲፬፻፵፮ (1446) ዓ.ም የጌታችንን መስቀል በክብር አስቀምጠውታል፡፡

ከዚህ በኋላ ንጉሡ ‹‹መካከሏ ገነት፤ ዳሯ እሳት ይኹን! የበረረ ወፍ፣ የሠገረ ቆቅ አይታደንባት! በድንገት ሰው የገደለ፣ ቋንጃ የቈረጠ ወንጀለኛ አይያዝባት!›› ብለው ዐዋጅ ነግረዋል፡፡ የእመቤታችን ጽላትም አብሮ በግሸን ደብረ ከርቤ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ ስለዚህም መስከረም ፳፩ ቀን በየዓመቱ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡ ኀጢአታቸውን ለካህን ተናዘው፣ ንስሐ ገብተው በዚህ ዕለት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሔድ የሚጸልዩና የሚማጸኑ ምእመናን ኹሉ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚያገኙም ጤፉት በተባለችው መጽሐፍ ተጠቅሷል፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ ፳፻፭ ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፤ ገጽ ፫፶፬-፫፶፮፡፡

የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የክርስቶስ የመስቀሉ ኃይል፣ የአባቶቻችን ሊቃውንትና ነገሥታት በረከት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡