ካህናተ ሰማይ

ኅዳር ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ቅዱሳን መላእክት ምሕረትን ከእግዚአብሔር ወደ ሰው ልጅ፤ ጸሎትን ከሰው ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሱ ለዘለዓለም የማይሞቱ ረቂቃን መናፍስት ናቸው፡፡ በመዓርጋቸውና በነገዳቸውም ኪሩቤል፣ ሱራፌል፣ ኃይላት፣ አርባብ፣ መናብርት፣ ሥልጣናት፣ መኳንንት፣ ሊቃናትና መላእክት ተብለው ይመደባሉ፡፡ ‹‹ወኍልቆሙ ለእሙንቱ መላእክት ወሊቃነ መላእክት መናብርት ወሥልጣናት አጋእዝት ኃይላት ወሊቃናት ኪሩቤል ወሱራፌል›› እንዲል /አንቀጸ ብርሃን፤ ኵሎሙ ዘመላእክት/፡፡

በአቀማመጥም ኪሩቤል፣ ሱራፌልንና ኃይላትን በኢዮር፤ አርባብን፣ መናብርትንና ሥልጣናትን በራማ፤ መኳንንትን፣ ሊቃናትንና መላእክትን በኤረር አስፈሯቸዋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በተሰወረባቸው ጊዜ ዲያብሎስ ‹‹እኔ ነኝ ፈጣሪያችሁ›› በማለቱ መንፈስ ቅዱስ አረጋግቶ ኅቡዕ ስሙ የተጻፈበትን ሠሌዳ ሰጥቷቸው፤ አንድም እሑድ በነግህ የተፈጠረው ብርሃን ዕውቀት ኾኗቸው ቅዱሳን መላእክት ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር አብ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ›› ብለው ምሥጢረ ሥላሴን አምልተው አስፍተው ተናግረዋል /ኩፋሌ ፪፥፰፤ ኢሳ. ፮፥፫/፡፡ ይህንን ሃይማኖታቸውን ምክንያት አድርጎ በየነገዳቸው አለቃ ሹሞ ቀብቷቸዋል (አክብሯቸዋል)፡፡

በዚህም መሠረት በኢዮር ያሉት መላእክት አራት አለቃ፣ ዐርባ ነገድ ኾነው የተመደቡ ሲኾን ከእነዚህም ዐሥሩ የኪሩቤል፣ ዐሥሩ የሱራፌል ነገድ ነው /መዝ.፳፫፥፯-፲፤ ማቴ.፳፬፥፴፩/፡፡ በቍጥርም ዘጠና ዘጠኝ ነገድ ናቸው፡፡ ‹‹ኀዲጐ ተስዓ ወተስዓተ ነገደ ቆመ ማእከለ ባሕር›› እንዲል /ሰላም ዘጥምቀት፤ ራእ. ፲፪፥፱/፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ሃያ አራት ሊቃነ መላእክትን መርጦ በመንበረ መንግሥት ዙሪያ ክንፍ ለክንፍ አያይዞ አቁሟቸዋል፡፡ የብርሃን ዘውድ (አክሊል) ደፍቶላቸዋል፡፡ የብርሃን መስቀልና ማዕጠንተ ወርቅ አስይዟቸዋል፡፡ እንደዚህ አድርጎ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ እንዲያመሰግኑት አድርጓቸዋል፡፡ እነዚህም ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) ይባላሉ፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር ተመዝግቦ እንደምናገኘው በየዓመቱ ኅዳር ፳፬ ቀን በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው ሰማያዊ አገልግሎት የሚሰጡ የካህናተ ሰማይ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ስለ ካህናተ ሰማይ አገልግሎት የሚያስገነዝብ አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

ሱራፊ ማለት መልአክ፣ ከካህናተ ሰማይ አንዱ ማለት ነው፡፡ ሱራፌን፣ ሱራፌል፣ ሱራፌም (በፅርዕ ሴራፊም፣ በዕብራይስጥ ስራፊም) ማለት የነገድ ስም፣ ልዑላን መላእክት፣ ሊቃናት፣ የሚያጥኑ፣ ካህናት፣ ቀሳውስት፣ ቀዳሾች ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፰፻፹፮/፡፡ ከዚህ ላይ ሱራፊ ነጠላ ቍጥርን፤ ሱራፌል ደግሞ ብዙ ቍጥርን ያመለክታል፡፡ ሱራፌል ለቅዱሳን በሰው አምሳል በመገለጣቸው ሽማግሌዎች ተብለው ተጠርተዋል /ኢሳ.፳፬፥፳፫፤ መሳ.፲፫፥፪-፳፭፤ ዳን.፲፥፲፰-፳፩/፡፡ በግእዝ ቋንቋ ደግሞ ካህናተ ሰማይ ይባላሉ፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው የሚሰጡትን ሰማያዊ አገልግሎት የሚያመለክት ስም ነው፡፡

በመጽሐፈ ሥነ ፍጥረት እንደ ተገለጸው እግዚአብሔር አምላክ በዕለተ ሰኑይ (ሰኞ) ከኪሩቤል ሠራዊት ገጸ ሰብእና ገጸ አንበሳን፣ ከሱራፌል ሠራዊት ገጸ ንሥርና ገጸ እንስሳን ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት በላይ፣ ከሰማይ ውዱድ በታች ጀርባቸውን ወደ ውስጥ፣ ፊታቸውን ወደ ውጭ አድርጎ አቁሟቸዋል፡፡ ይኸውም ‹‹የኔን የፈጣሪያችሁን ፊት ማየት አይቻላችሁም›› ሲል ነው፡፡ የኪሩቤል አለቃቸው ማለትም ገጸ ሰብእና ገጸ አንበሳ ኪሩብ፤ የሱራፌል አለቃቸው ማለትም ገጸ ነሥርና ገጸ ላሕም ደግሞ ሱራፊ ይባላል /ሥነ ፍጥረት ዘእሑድ/፡፡

ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእዩ ‹‹በዙሪያውም ሃያ ዐራት ካህናት አሉ፡፡ በፊታቸው የበጉን ሥዕል፣ ደምን የተረጨች ልብስንም፣ የታተመ መጽሐፍንም ያያሉ፡፡ መንበሩን በዞሩ ቍጥር ለዚያ ለበጉ ሥዕልና በደም ለታለለችዋ ልብስ፣ ለታተመው መጽሐፍም ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ›› /ራእ. ፬፥፮፤ ፭፥፰/ በማለት ስለ ሱራፌል ሰማያዊ አገልግሎት የተናገረ ሲኾን፣ ‹‹በፊታቸው የበጉን ሥዕል ያያሉ›› ማለቱ የክርስቶስን ትስብእት በጌትነት ያዩታል ለማለት ነው፡፡ ‹‹ወደቁ›› ሲልም መስገዳቸውን ያመለክታል፡፡ ‹‹በግ›› የተባለውም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹ደምን የተረጨች ልብስ›› ማለቱም ክርስቶስ ስለ እኛ መከራ መቀበሉን፤ የታተመ መጽሐፍ የክርስቶስ ትስብእት የማይመረመር መኾኑን፤ ‹‹ለበጉ ሥዕል፣ ለታለለችው ልብስና ለታለለው መጽሐፍ ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ›› ሲልም ከእግዚአብሔር አብ እና ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነትም በሦስትነትም ለሚመለከው ለክርስቶስ ደግመው ደጋግመው ምስጋና ማቅረባቸውንና መገዛታቸውን ያመለክታል /የሠለስቱ ምእት ቅዳሴ አንድምታ ትርጓሜ፣ ፫፥፯-፱/፡፡

ነቢዩ ሕዝቅኤልም ካህናተ ሰማይ ያለ ዘር መገኘታቸውን ሲያመለክት ‹‹በመንበሩ ዙሪያ ቁመው ያሉ ካህናት ኅብራቸው መረግድ የሚባል ዕንቍን ይመስላል›› በማለት ተናግሯል፡፡ ጸጋቸውን ሲገልጽ ደግሞ ‹‹ብሩህ ልብስ ለብሰዋል፤›› ክብራቸውን ሲመሰክርም ‹‹በራሳቸው ላይ አክሊል ደፍተዋል›› ብሏል፡፡ ነጭ ልብስ ለብሰው መታየታቸው የንጽሕናቸውና የቅድስናቸው መገለጫ ሲኾን፣ በራሳቸው ላይ የተቀዳጁት ዘውድ ደግሞ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸውን ዘለዓለማዊ ክብር ያሳያል፡፡ ቍጥራቸው በሃያ አራት መገለጹም ምስጋናቸው ዕረፍታቸው፣ ዕረፍታቸው ምስጋናቸው ኾኗቸው ለሃያ አራት ሰዓታት ሳያቋርጡ ጸሎትና ምስጋናን ለእግዚአብሔር ማቅረባቸውን ለማጠየቅ ነው፡፡ አንድም የ፲፪ቱ ነገደ እስራኤል እና የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ሲኾን (፲፪ + ፲፪ = ፳፬) ይኸውም የብሉይና የሐዲስ ኪዳን አባቶች በአንድነት ኾነው እንደ ሱራፌል በምድር በቤተ መቅደስ፤ እንደዚሁም በሰማይ በገነት (በመንግሥተ ሰማያት) ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ የሚያመሰግኑ መኾናቸውን ያመለክታል፡፡ በዘመነ ብሉይ ደብተራ ኦሪትንና መቅደሰ ኦሪትን በሃያ አራት ሰሞን ተመድበው ያገለግሉ የነበሩ ካህናትም የ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ ምሳሌዎች ናቸው /፩ኛዜና. ፳፬፥፩-፲፱፤ ሕዝ. ፩፥፭-፳፪፤ ራእ. ፭፥፰-፲፬/፡፡

ካህናተ ሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ሲያቀርቡ አክሊሎቻቸውን ከራሳቸው ላይ አውርደው ያለማቋረጥ ይሰግዳሉ፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም ይህንን ሰማያዊ ሥርዓት እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፤ ‹‹ካህናተ ሰማይ ቅዉማን በዐውዱ አክሊላቲሆሙ ያወርዱ ቅድመ መንበሩ እንዘ ይሰግዱ ይርዕዱ ወኢይዝብጦሙ ሶበ ይበርቅ ነዱ፤ ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) በመንበሩ ዙሪያ ቆመው በፊቱ ሲሰግዱ የመለኮት እሳት ሲበርቅ እንዳይመታቸው ይንቀጠቀጣሉ፤›› /መጽሐፈ ሰዓታት/፡፡ ይህም ምስጋና በቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ የጸሎት ክፍሎች ይገኛል፡፡ ‹‹…. ወባቲ ለዛቲ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ መላእክት አርአያ ዘበሰማያት ቤተ ክርስቲያሰ ትትሜሰል በጽርሐ አርያም ዘላዕሉ ….፤ .… ለዚህች ቤተ ክርስቲያን በሰማያዊው አገልግሎት አምሳል የመላእክት የአገልግሎት ሥርዓት አላት፡፡ ቤተ ክርስቲያንስ በላይኛው (በሰማያዊው) ጽርሐ አርያም ትመሰላለች ….›› እንዳሉ አባ ጊዮርጊስ /ሰዓታት፣ ኵሎሙ ዘዘወትር/፡፡

ዛሬም ምድራውያን ካህናት ማዕጠንትና መስቀል ይዘው በመንበሩ ፊት ቆመው ሲያጥኑ የሚሰግዱት፤ እንደዚሁም ኪዳን ሲያደርሱና ወንጌል ሲያነቡ መጠምጠሚያቸውን የሚያወርዱት ከዚህ ሥርዓት በመነሣት ነው፡፡ ሱራፌል በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ ማዕጠንት ይዘው፣ እንደሚሰግዱና አክሊላቸውን እንደሚያወርዱ ኾነው በሥዕለ ሥላሴ ግራና ቀኝ የሚሣሉትም ይህንን አገልግሎታቸውን ለማስታዎስ ነው፡፡ እንደ ጸሎተ ዕጣን፣ ቅዳሴ፣ ማኅሌት፣ የመሰሉ የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ዘርፎች ዅሉ ከካህናተ ሰማይ የተወረሱ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የዜማ መሠረት የኾነው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰቱን የተቀበለው ከሱራፌል መኾኑንም ‹‹ሃሌ ሉያ ዋይዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ግናይ እንዘ ይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር መልዓ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሐቲከ፤ ‹ምስጋና ለእግዚአብሔር ይኹን፡፡ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር፣ የጌትነትህ ቅድስና በሰማይ በምድር መላ› እያሉ ሲያመሰግኑ በሰማይ ከመላእክት የሰማሁት ዜማ ምንኛ ድንቅ ነው?›› ከሚለው የአርያም ክፍል ከኾነው ጣዕመ ዜማው ለመረዳት እንችላለን፡፡ በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን በቅዳሴው፣ በማኅሌቱና በሰዓታቱ የካህናተ ሰማይ አገልግሎታቸውና ስማቸው በሰፊው ሲጠራ ይኖራል፡፡

ሠለስቱ ደቂቅ ‹‹እግዚአብሔርን አራዊትና አንስሳት ዅሉ ያመሰግኑታል›› በማለት እንደ ተናገሩት ካህናተ ሰማይ ሱራፌል ሌሊትና ቀን ምስጋና ሲያቀርቡ የክንፎቻቸውን ድምፅ ሲሰማ ዶሮ እንደሚጮኽና እግዚአብሔርንም እንደሚያመሰግን በመጽሐፈ ሥነ ፍጥረት እንዲህ ተብሎ ተጠቅሷል፤ ‹‹ቀን በስድስተኛው ሰዓት የኪሩቤል ልመና ወደ እግዚአብሔር ይደርሳል፡፡ ሌሊት በአራተኛው ሰዓት ሱራፌል ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባሉ፡፡ በዐሥረኛው ሰዓትም ሰማያት ይከፈታሉ፤ እግዚአብሔርም የሰውን ልጆች ጸሎት ይሰማል፡፡ የለመኑትንም ዅሉ ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህችም ሰዓት ከሱራፌል ከክንፎቻቸው ድምፅ የተነሣ ዶሮ ይጮኻል፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግናል፤›› /ሥነ ፍጥረት ዘእሑድ/፡፡

እኛ የሰው ልጆችም የተፈጠርንለት ዓላማ የእግዚአብሔርን ስም ለመቀደስ፣ መንግሥቱንም ለመውረስ መኾኑን በማስተዋል ስለ ግሩምና ድንቅ ሥራው ዅሉ ‹‹አቤቱ የኀያላን አምላክ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? ሥራህም ድንቅ ነው›› /መዝ. ፵፯፥፪/ እያልን ዘወትር አምላካችንን ልናመሰግነው ይገባናል፡፡ በምድር በቤተ መቅደሱ፣ በሰማይም በመንግሥቱ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያልን እግዚአብሔርን ከቅዱሳን መላእክት ጋር ለማመስገን ያብቃን፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፤ እኛንም በካህናተ ሰማይ ጸሎት ይጠብቀን፤ በረከታቸውም ይደርብን፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

የጽዮን ምርኮ – ክፍል ሦስት

ኅዳር ፳፫ ቀን ፳፻፱ .

በመምህር ብዙነህ ሺበሺ

ታቦተ ጽዮን ዳጎንን እንደ ሰባበረችው /፩ኛ ሳሙ. ፭፥፩-፭/

ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ድል አድርገው ታቦተ ጽዮንን ወደ አዛጦን ወሰዱአት፡፡ በዚያም ከቤተ ጣዖታቸው አስገብተው ዳጎን የተባለውን ጣዖት ከፍ ባለ መቀመጫ አድርገው እርሷን ግን ከታች አስቀመጧት፡፡ ሲነጋም የአዛጦን ሰዎች ማልደው ለጣዖቱ ሊሰግዱ ቢሔዱ ዳጎንን በግምባሩ ወድቆ አገኙት፡፡ አንሥተው ወደ ቦታው መለሱት፤ በነጋ ጊዜ እንደልማዳቸው ቢሔዱም እነሆ ዳጎን በታቦተ ጽዮን ፊት በምድር ላይ ወድቆ ነበር፡፡ ራሱ፣ እጆቹም ተቈራርጠው በመድረኩ ላይ ወድቀው ደረቱ ብቻውን ቀርቶ ነበር፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ንጉሥ በመንግሥቱ ገበሬ በርስቱ እንደማይታገሥ እግዚአብሔርም በአምላክነቱ ከገቡበት አይታገሥም›› እንዲሉ ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔር ማደሪያ ታቦተ ጽዮንን በጣዖት ቤት ከጣዖት እግር ሥር በማስቀመጣቸው እግዚአብሔር በቍጣ ተነሣባቸው፡፡ ኃይሉንም በታቦቱ ላይ አሳረፈ፤ ታቦተ ጽዮንም ዳጎንን ቀጠቀጠችው፤ ሰባበረችው፡፡

ይህ ታሪክ የሐዲስ ኪዳን የማዳን ሥራ ምሳሌነት አለው፡፡ ቀደም ብሎ እንዳየነው ታቦተ ጽዮን የወላዲተ አምላክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት፡፡ ታቦተ ጽዮን ዳጎንን እንደ ሰባበረችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ልጇን አዝላ ወደ ግብጽ በምታደርገው የስደት ጕዞ በምታቋርጣቸው መንገዶችና መንደሮች ዅሉ ያሉ ጣዖታት ይሰባበሩ ነበር፡፡ በግብጽ ያሉ ጣዖታት ማንም ሳይነካቸው ተሰባብረዋል፤ በውስጣቸው አድረው ሲመለኩ የነበሩ አጋንንትም በአምሳለ ሆባይ (ዝንጀሮ) እየወጡ ሲሔዱ ይታዩ ነበር /ነገረ ማርያም/፡፡ ዳጎን በታቦተ ጸዮን ፊት በግምባሩ እንደ ተደፋ እመቤታችንም በስደቷ በሲና በረሃ ስትጓዝ ያገኟት ሽፍቶች መዝረፋቸውን ትተው በፊቷ ሰግደው ሸኝተዋታል፡፡ ዳግመኛም በዕለተ ዕረፍቷ አስከሬኗን አቃጥላለሁ ብሎ የአልጋውን ሸንኮር የያዘው ታውፋንያ የተባለው አይሁዳዊ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እጁን በሰይፍ በቀጣው ጊዜ እመቤታችን ይቅር ትለውና ትፈውሰው ዘንድ ግምባሩን መሬት አስነክቶ ሰግዶላታል፡፡

እንደዚሁም ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦተ ጽዮን ይመሰላል፡፡ ዳጎን በታቦተ ጽዮን ፊት በግምባሩ ተደፍቶ እንደ ተገኘ ጌታችን በሥጋ ሰብእ ተገልጦ ወንጌለ መንግሥት በሚያስተምርበት ዘመንም አጋንንት ‹‹ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ያለ ጊዜያችን አታጥፋን›› እያሉ ይሰግዱለት እንደ ነበር በቅዱስ ወንጌል በሰፊው ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብም ‹‹አጋንንትኒ የአምኑ ቦቱ ወይደነግፁ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጡማል፤›› በማለት ተናግሯል /ያዕ. ፪፥፲፱/፡፡ ታቦተ ጽዮን ዳጎንን እንደ ቀጠቀጠችው (እንደ ሰባበረችው) ዅሉ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዲያብሎስንና ሠራዊቱን ቀጥቅጧቸዋል፡፡ ታቦተ ጸዮን የወርቅ ካሣ ተሰጥቷት ከምድረ ፍልስጥኤም እንደ ወጣች ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በወርቀ ደሙ ካሣነት የሲዖልን ነፍሳት ከሲዖል አውጥቷል፡፡

ጌታችን ለድኅነተ ዓለም በመስቀል ተሰቅሎ አዳምን ወክሎ ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምንት ኀደገኒ)፤ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ›› በማለት ሲጣራ ሰምቶ ዲያብሎስ ‹‹ሥጋውን ወደ መቃብር፣ ነፍሱን ወደ ሲዖል ላውርድ›› ብሎ ቀረበ፡፡ የጌታ ጩኸትም አንድም ለአቅርቦተ ሰይጣን ነውና ሰይጣንን በአውታረ ነፋስ /ሥልጣነ መለኮት/ ወጥሮ ያዘው፤ ያን ጊዜ ዲያብሎስ ‹‹መኑ ውእቱ መኑ ውእቱ፤ ማነው ማነው›› እያለ መለፍለፍ ጀመረ /ትምህርተ ኅቡአት/፡፡ ከብዙ መቀባጠር በኋላም ‹‹አቤቱ ጌታዬ በድዬሃለሁ፤ ነገረ ልደትህን የተናገሩትን ነቢያት እነ ኢሳይያስን በምናሴ አድሬ በመጋዝ አስተርትሬአለሁ፤ ለበደሌ የሚኾን ካሣ የለኝም፤ የሲዖልን ነፍሳት በሙሉ እንደ ካሣ አድርገህ ውሰድ፡፡ እኔንም ያለ ጊዜዬ አታጥፋኝ›› በማለት አጥብቆ ለመነው፡፡ ጌታችንም ዲያብሎስን አስሮ ከአዳም ጀምሮ በሲዖል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን አወጣ፡፡ በዚህ ጊዜ የሲዖል ኃይላት ተሰባበሩ፤ ከመለኮቱ ብርሃን የተነሣም የሲዖል ጨለማ ተወገደ፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን፣ ሊቃነ አጋንንትን፣ ሠራዊተ አጋንንትን፣ የሲዖልን ኃይላትን አጥፍቶልናልና ቅዱስ ዳዊት ከአንድ ሺሕ ዓመት በፊት ‹‹እስመ ሰበረ ኆኃተ ብርት ወቀጥቀጠ መናሥግተ ዘኀፂን፤ የናሱን ደጆች ሰብሯልና፡፡ የብረቱንም መወርወሪያ ቀጥቅጧል፤›› በማለት ዘመረ /መዝ. ፻፮፥፲፮/፡፡ ነቢዩ አጋንንትን ኆኀተ ብርት (የነሐስ ደጆች) ብሎአቸዋል፡፡ የነሐስ መዝጊያ ጠንካራ እንደ ኾነ አጋንንትም በአዳምና ልጆቹ ላይ መከራ አንጽተውባቸው ነበር፡፡ የአጋንንት ክንድ በሰው ልጆች ላይ ከብዶ ነበርና ሊቃነ አጋንንትን መናሥግተ ኀፂን (የብርት መወርወሪያ ወይም ቍልፍ) ብሏቸዋል፡፡ ቤት በብርት መወርወሪያ (ቍልፍ) ከተዘጋ እንደማይከፈት ሲዖልም ለ፶፭፻ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ) ዘመን ተዘግታ የነፍሳት ወኅኒ ቤት ኾና ኖራለችና አዳሪውን በማደሪያው ጠራው፡፡ ከመዝጊያው መወርወሪያው (ቍልፉ) እንዲጠነክር ወይም መዝጊያ በቍልፍ እንዲጠነክር ከአጋንንት አለቆች (ሊቃነ አጋንንት) ይበረታሉና መናሥግተ ኀፂን (የብረት መወርወሪያ) አላቸው፡፡ አምስቱ የፍልስጥኤም ነገሥታት ሲሰግዱለት የነበረውን ዳጎንን ታቦተ ጽዮን እንደ ቀጠቀጠችው ዅሉ መድኀኒታችን ክርስቶስም ለ፶፭፻ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ) ዘመን የተደራጀውን የአጋንንት ኃይል በሥልጣኑ ሰባብሮታል፡፡

ለታቦተ ጽዮን ካሣ እንደ ተሰጣት /፩ኛ ሳሙ. ፮፥፩-፱/

የእግዚአብሔር እጅ በአዛጦን ሰዎች ላይ በረታችባው፤ ሰዎቹንም በእባጭ ቍስልም መታቻቸው፤ አጠፋቻቸው፡፡ ታቦተ ጽዮንን ወደ አስቀሎና በወሰዷት ጊዜም አስቀሎናውያንንም በእባጭ መታቻቸው፡፡ ምድራቸውም በአይጦች መንጋ ተወረረ፡፡ እጅግ ዋይታና ጩኸት ኾነ፣ ታቦተ ጽዮን በፍልጥኤማውያን ላይ መቅሠፍት እንዳበዛችባቸው ባዩ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ በኀይል ወርዶባቸዋልና አምስቱ የፍልስጥኤም ነገሥታት (አዛጦን፣ አስቀሎና፣ አቃሮን፣ ጌትና ጋዛ) ከካህናተ ጣዖትና ከሟርተኞች ጋር እንዲህ በማለት ተማከሩ፤ ‹‹የእስራኤልን አምላክ ታቦት ብትሰዱ የበደል መሥዋዕት መልሱ እንጂ ባዶውን አትስደዱት፡፡ በዚያን ጊዜም ትፈወሳላችሁ፡፡ እጁም ከእናንተ አለመራቁ ስለ ምን እንደኾነ ታውቃላችሁ፤›› /፩ኛ ሳሙ. ፮፥፫/፡፡

በዚህ ተስማምተው በአምስቱ የፍልስጥኤም ግዛቶች ቍጥር አምስት የወርቅ አይጦችንና አምስት የወርቅ እባጮችን ቅርፅ አዘጋጁ፡፡ ቀንበር ያልተጫነባቸው ሁለት የሚያጠቡ ላሞንም ጠምደው በሠረገላ ከተዘጋጀው ወርቅ ጋር ታቦተ ጽዮንን ጫኑ፡፡ ሠረገላውን እየጐተቱ ከፍልስጥኤም ወጥተው ወደ ቤትሳሚስ ሔዱ፡፡ ሠረገላውም ወደ ቤትሳምሳዊው ወደ ኢያሱ እርሻ በደረሰ ጊዜ በዚያ ቆመ፡፡ የዚያ አገር ሰዎችም ታቦቱና ወርቁ የተጫነበትን ሣጥን ሲያወርዱ ወደ እግዚአብሔር ታቦት የተመለከቱ ሰባ ሰዎች በመቀሠፋቸው ምክንያት ቤትሳምሳውያን በፍርሃት ተዋጡ፡፡ የቂርያትይዓሪ ሰዎችም ታቦተ ጽዮንን በአሚናዳብ ቤት አኖሯት፤ አልዓዛር ወልደ አሚናዳብም ታቦቷን እንዲያገለግል ተደረገ፡፡ በዚያም ታቦተ ጽዮን ለሃያ ዓመት ኖረች፡፡ ከዚህ ታሪክ ለሐዲስ ኪዳን ምሳሌዎች የሚኾኑ ትምህርቶችን እናገኛለን፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ ዮሐንስ በነበረችበት ዘመን ወደ ቀራንዮ እየወጣች በልጇ መቃብር ላይ ትጸልይ ነበር፡፡ ጸሎቷም በሲዖል ያሉ ነፍሳትንና በሕይወተ ሥጋ ያሉ ኃጥአንን ማርልኝ በማለት ነበር እንጂ ስለራሷ ተድላ ደስታ አልነበረም፡፡ ‹‹ወእምአሜሃ ነበረት እግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ እንዘ ተኀዝን ወትስእል በእንተ ኵሎሙ ኃጥአን ዘከመ ዛቲ ዕለት አመ ፲ወ፮ ለየካቲት በከመ ልማዳ ቆመት መካነ ቀራንዮ ወሰአለቶ ለወልዳ፤ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን በዚያች በየካቲት ፲፮ ቀን ቀራንዮ በሚባል ቦታ ቆማ ልጅዋን እንደ ልማዷ ስትለምን ኖረች›› እንዲል ተአምረ ማርያም፡፡

እንኳን የእናቱን ልመና የኀጥኡን ጸሎት የሚሰማ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እልፍ አእላፋት መላእክትን፣ ቅዱሳን አበውን አስከትሎ ወረደና ‹‹ይኩን በከመ ትቤሊ እፌጽም ለኪ ኲሎ መፍቅደኪ አኮኑ ተሰባእኩ በእንተ ዝንቱ፤ የለመንሽው ዅሉ ይደረግልሽ፤ የምትወጂውን ዅሉ እፈጽምልሻለሁ፡፡ የለመንሽውን ዅሉ ላደርግልሽ ሰው ኾኛለሁና›› በማለት ታላቅ የምሕረት ኪዳን ሰጣት፡፡ በዚህ የምሕረት ኪዳንም እጅግ ብዙ ነፍሳት ከሲዖል ወጥተዋል፡፡ እስከ ምጽአትም ድረስ በቃል ኪዳኗ የሚታመኑ ምእመናን ከሲዖል ይወጣሉ፡፡ ታቦተ ጽዮን ከምድረ ፍልስጥኤም የወርቅ አይጦችና እባጮች ካሣ ተሰጥቷት እንደ ወጣች እመቤታችንም ሞተ ሥጋን የተቀበለችው በሞቷ ብዙ ነፍሳት ከሲዖል እንደሚወጡ ቃል ኪዳን ተሰጥቷት ነበርና በዕለተ ዕረፍቷ ብዙ ነፍሳት ከሲዖል ወጥተዋል፡፡ ለእመቤታችን የሞት ካሣ ኾነው የኀጥአን ነፍሳት ተሰጥተዋታል፡፡ ማለትም በሞቷ የኀጥአን ነፍሳት ከሲዖል ወጥተዋል፡፡

ይቆየን፡፡

የጽዮን ምርኮ – ክፍል ሁለት

ኅዳር ፳፪ ቀን ፳፻፱ .

በመምህር ብዙነህ ሺበሺ

 የአፍኒንና ፊንሐስ ኀጢአት ….

፬ኛ የአባታቸውን ምክር አለመስማታቸው

ካህኑ ዔሊ ልጆቹ ያደረጉትን ኃጢአት ዅሉ ሰምቶ ‹‹ስለ ክፉ ሥራችሁ ከዚህ ሕዝብ ሰምቻለሁና ስለምን እንደዚህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ? ልጆቼ ሆይ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለ እናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይኾንም፡፡ ሰውስ ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድበታል፡፡ ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለ እርሱ የሚለምን ማነው?›› በማለት ቢመክራቸውም ‹‹ልጥፋ ያለች ከተማ ነጋሪት ቢጐሰምም አትሰማም›› እንዲል የአበው ብሂል አፍኒንና ፊንሐስ የአባታቸውን ቃል አልሰሙም ነበር /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፫-፳፭/፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ደዊት ‹‹ዘይሴሰይ እክልየ አንሥአ ሰኰናሁ ላዕሌየ፤ እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ›› /መዝ.፵፥፱/ እንዳለው ዛሬም የአባቶችን ትምህርትና ተግሣፅ የማይሰሙ፤ የቤተ ክርስቲያንን እክለ ትምህርት ተመግበው አድገው ጠላቶቿ የኾኑ ውሉደ አፍኒን ወፊንሐስ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ከትእዛዛተ እግዚአብሔር አንደኛው ‹‹አባትና እናትህን አክብር›› የሚለው ነው፡፡ መቼም አባት ሲባል ማን ማንን እንደሚመለከት የማያውቅ የለም፡፡ በሐዋርያት እግር የተተኩ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳትን እያቃለሉ ‹‹በቅዱስ ሲኖዶስ አንመራም፡፡ ቤተ ክርስቲያን አርጅታለች፤ እናድሳት፤›› በማለት በክርስቶስ ደም የተመሠረተች የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና የሚጥሱ ራሳቸውን ‹‹ተሐድሶ›› እያሉ የሚጠሩ ምናምንቴዎች እጣ ፈንታቸው እንደ አፍኒንና ፊንሐስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አረጀች ከተባለ የተመሠረተችው በክርስቶስ ደም፣ በሐዋርያት ስብከት ነውና ክርስቶስ አርጅቷል፤ የሐዋርያትም ትምህርት ጊዜው አልፏል ማለት ነዋ? ለአንዲት ቃል እንኳን ትርጕም መስጠት የማይችሉ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስን እንተረጕማለን፤ ቤተ ክርስቲያንን እናድሳለን›› በማለት የሚያሳዩት ድፍረት ለእነርሱ ዕውቀታቸው መኾኑ ነው፡፡ ‹‹የሰነፍ ዕውቀቱ ድፍረቱ›› እንዲል የአበው ብሂል፡፡

ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ‹‹ተሰአሎ ለአቡከ ወይነግረከ ወለሊቃውንቲከ ይዜንዉከ፤ አባትህን ጠይቅ፤ ያስታውቅህማል፡፡ ሽማግሌዎችህንም ጠይቅ፤ ይነግሩህማል›› /ዘዳ. ፴፪፥፯/ በማለት እንደ ተናገረው አባቶች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚናገሩትን፣ ሊቃውንቱ የሚያስተምሩትን የሚሰማና በትምርታቸው የሚመራ ከስሐትት ይድናል፡፡ የዔሊ ልጆች የአባታቸውን ቃል ሰምተው ተጸጽተው ቢኾን ኖሮ በኢሎፍላውያን ሰይፍ ባልወደቁም ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን እክለ ትምህርቷን ተመግበው ያደጉ ልጆቿ ሲጠፉባት ታዝናለች፡፡ ስለዚህም ‹‹አብዳነ አጥብብ፤ ሰነፎችን አለብም›› እያለች ትጸልያለች፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዓላማዋ የራሷን ልጆች ከመጠበቅ ባገሻገር ከውጭ ያሉትንም ወደ ውስጥ ማስገባት ነውና፡፡ ‹‹ከዚህም በረት ያልኾኑ ሌሎች በጐች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፡፡ ድምፄንም ይሰማሉ አንድም መንጋ ይኾናሉ፤ እረኛውም አንድ›› እንዳለ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ /ዮሐ. ፲፥፲፮/፡፡

የካህኑ ዔሊ አለመታዘዝ

እግዚአብሔር አምላክ ዔሊን ምስፍናን ከክህነት ጋር አስተባብሮ በእስራኤል ላይ ለዐርባ ዓመት እንዲያገለግል አክብሮት ነበር፡፡ ዔሊ ግን ከእግዚአብሔር ይልቅ ለልጆቹ አደላ፡፡ የኀጥኡን ድኅነት እንጂ ጥፋቱን የማይወደው እግዚአብሔር ዔሊን በነቢዩ ላይ አድሮ መክሮት ነበር /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፯-፴፯/፡፡ ዳግመኛም ልጆቹ በእስራኤል ሕዝብ ላይ የሚያደርጉት ነውር በብላቴናው በሳሙኤል ተነግሮት ነበር፡፡ የዔሊ ትልቁ ጥፋት ልጆቹን ከሥልጣናቸው አለመሻሩ ነበር፡፡ ምክር ለማይሰማ እርምጃ መውሰድ ግድ ነውና፡፡ ስለዚሀም ካህኑ ዔሊ ‹‹ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ለምን አከበርህ?›› ተብሎ በእግዚአብሔር ተወቀሰ /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፱/፡፡ ‹‹ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊኾን አይገባውም›› /ማቴ. ፲፥፴፯/ እንዳለ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል፡፡

ካህኑ ዔሊ ከእግዚአብሔር ፍቅር ተለየ፡፡ ልጆቹን የማይገሥፅ እርሱ ልጆቹን አይወድምና፡፡ ‹‹በበትር ከመምታት የሚራራ ሰው ልጁን ይጠላል፤ ልጁን የሚወድ ግን ተግቶ ይገሥፀዋል›› /ምሳ. ፲፫፥፳፬/ እንዳለ ጠቢቡ ሰሎሞን፡፡ በበትር መምታት ማለት ጽኑዕ ተግሣፅ ማለት ነው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ተግተው የማይገሥፁ፣ ውሏቸውንም የማይከታተሉ ከኾነ ጉዳቱ ከራሳቸው አልፎ ለአገርም ይተርፋል፡፡ በምግባር፣ በሃይማኖት ኰትኵተው የሚያሳድጉ ወላጆች ተተኪ የቤተ ክርስቲያን ትውልድ፤ አገር ተረካቢ ዜጎችን ያፈራሉ፡፡ ዔሊ ልጆቹን ተግቶ ባለመገሠፁ ራሱንም ልጆቹንም አጥቷል፡፡ ዛሬም መንፈሳዊ ተልእኮአቸውን በአግባቡ የማይወጡ አገልጋዮችን የማይገሥፁ አባቶች ከዔሊ ውድቀት ሊማሩ ይገባቸዋል፡፡ እለእስክንድሮስ ከሐዲውን አርዮስን እንደ ገሠፀው እና ከስሕተቱ አልመለስም ባለ ጊዜም እንዳወገዘው ዅሉ ዛሬም አባቶች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የሚጥሱ ካህናትን ሊገሥፁና ሊያስተካክሏቸው ይገባል፡፡

በዔሊ ልጆች እኩይ ተግባርና ካህኑ ዔሊም ልጆቹን ተግቶ ባለመገሠፁ ልጆቹ በኢሎፍላውያን ጦር ወደቁ፤ እርሱም በታቦተ ጽዮን መማረክና በልጆቹ ሞት ደንግጦ ከወንበሩ ላይ ወድቆ ሞተ፡፡ የፊንሐስ ሚስት በድንጋጤ የወለደችውን ልጅ ‹ክብር ከእስራኤል ለቀቀ› ስትል ‹ኢካቦድ› ብላ ጠራችው፡፡ የእስራኤል ክብራቸው ሞገሳቸው የነበረችው ታቦተ ጽዮን ተማርካለችና፡፡ በዔሊ ልጆች ኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር ኃይልና ሞገስን ከጽዮን አነሣ፡፡ መፈራትንም ከኃያላኑ ገፈፈ፡፡ ለዚህም ነው የፊንሐስ ሚስት ልጇን ኢካቦድ በማለት የጠራችው፡፡ ታቦተ ጽዮን እግዚአብሔር ኃይሉን የሚገልጥባት የትእዛዛቱ ጽላት፤ ሕዝበ እስራኤልን ከጠላት፣ ከአባር፣ ከቸነፈር፣ ከመቅሠፍት የሚያድንባት ማደሪያው ናት፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹እስመ ኀረያ እግዚአብሔር ለጽዮን ወአብደራ ከመ ትኩኖ ማኅደሮ፤ እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፤ ማደሪያውም ትኾነው ዘንድ ወዶአታልና›› /መዝ. ፻፴፩፥፲፫/ በማለት የዘመረው ለጊዜው ስለ ታቦተ ጽዮን ነው፤ ፍጻሜው ግን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ነው፡፡

ታቦተ ጽዮን የእግዚአብሔር ትእዛዝ መቀመጫ እንደ ነበረች እመቤታችንም አማናዊትና ዘለዓለማዊት የእግዚአብሔር ማደሪያ ናትና፡፡ ‹‹ዛቲ ይእቲ ምዕራፍየ ለዓለም፤ ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት›› እንዲል /መዝ. ፻፴፩፥፲፬/፡፡ ታቦተ ጽዮን በዔሊ ልጆች ኀጢአት ምክንያት ተማርካ ወደ ምድረ ፍልስጥኤም ተሰዳለች፤ እመቤታችንም በክፉው ሄሮድስ ከምድረ እስራኤል ወደ ግብጽ ተሰዳለች፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ታቦተ ጽዮን የምእመናን ምሳሌ ናት፡፡ ታቦተ ጽዮን የእግዚአብሔር ማደሪያ እንደ ኾነች ዅሉ፣ ምእመናንም የእግዚአብሔር ማደሪያዎች ናቸውና፡፡ ‹‹ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ኾነ አታውቁምን?›› እንዳለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ /፩ኛ ቆሮ. ፮፥፲፱-፳/፡፡ በዔሊ ልጆች ኃጢአት ታቦተ ጽዮን እንደ ተማረከች ምእመናን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ሲወጡ የእግዚአብሔር ጸጋ ይለያቸዋል፡፡ ታቦተ ጽዮን በኢሎፍላውያን እንደ ተማረከች፣ ምእመናንም ራሳቸውን ለዲያብሎስ ምርኮ አሳልፈው ይሰጣሉና፡፡

ይቆየን፡፡

የጽዮን ምርኮ – ክፍል አንድ

ኅዳር ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በመምህር ብዙነህ ሺበሺ

በመጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ከምዕራፍ ፬ – ፯ ባለው ክፍል ከሚገኘው ታሪክ ውስጥ የምንረዳው ብዙ ቁም ነገር አለ፡፡ ታሪኩ የእግዚአብሔርን ኀይልና ምሕረት፣ የኀጢአትን አስከፊነት፣ የትዕቢተኞችን ውድቀት፣ የበጎዎችን በረከት፣ የደፋሮችን ጥፋት፣ ወዘተ ያስተምራል፡፡ ከዚህም በላይ ለሐዲስ ኪዳን የድኅነት ሥራ ምሳሌነት ያለው ትምህርትም ነው፡፡ ይህንን ታሪክ በአርእስት ከፋፍለን እንደሚከተለው እንመለከታለን፤

የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት (የታቦተ ጽዮን) መማረክ /፩ኛ ሳሙ. ፬፥፩-፳፪/

እስራኤላውያን ከፍልስጥኤማውያን ጋር በተዋጉ ጊዜ ድል ተነሱ፤ አራት ሺሕ ያህል እስራኤላውያንም ተገደሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎችም እንዲህ ሲሉ መከሩ ‹‹እኛ ዛሬ በፍልስጥኤማውያን የተመታነችው የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ከእኛ ጋር አብራ ባለመውጣቷ ነው፡፡ ስለዚህ ፍልስጥኤማውያንን ድል እንድንነሳ ታቦተ ጽዮን ትምጣልን፡፡›› የካህኑ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስም ታቦተ ጽዮንን ይዘው መጡ፤ ታቦተ ጽዮን ወደ ሥፍራው ስትደርስም ታላቅ ደስታና ዕልልታ ተደረገ፡፡ የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት ይዘው ሲወጡ ድል ያደርጉ ነበርና፡፡ ነገር ግን እነርሱ እንደ ጠበቁት ሳይኾን ቀርቶ ሠላሳ ሺሕ የሚሆኑ እስራኤላውያን በጦርነቱ ተገደሉ፤ ሁለቱ የሊቀ ካህናቱ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስም ሞቱ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦትም ተማረከች፡፡ ከጦርነቱ ያመለጠ አንድ ሰው ወደ ከተማው ገብቶ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት እንደ ተማረከች፣ አፍኒንና ፊንሐስም እንደ ሞቱ፣ እጅግ ብዙ ኃያላነ እስራኤል በጦርነቱ እንደ ወደቁ ለካህኑ ዔሊ በነገረው ጊዜ ዔሊ በድንጋጤ ከተቀመጠበት ወንበር ወድቆ ሞተ፡፡ ምራቱም የፊንሐስ ሚስት አርግዛ ልትወልድ ተቃርባ ነበርና የአማትዋንና የባሏን ሞት በሰማች ጊዜ ምጥ ደረሰባት፤ ወንድ ልጅም ወለደች፡፡ ስሙንም ‹ኢካቦድ› ብላ ጠራችው፤ ትርጕሙም ‹‹ክብር ከእስራኤል ለቀቀ›› ማለት ነው፡፡

ከዚህ ታሪክ ብዙ ቁም ነገሮችን እንማራለን፤ አስቀድሞ እስራኤል ታቦተ ጽዮንን ይዘው የዮርዳኖስን ባሕር ከፍለው ተሻግረዋል፤ አሞናውያንን፣ ፌርዜዎናውያንን፣ ሞዓባውያንን ድል አድርገዋል፡፡ የኢያሪኮን ግንብ አፍርሰው ምድረ ርስትንም ወርሰዋል፡፡ ከዚህ ላይ ‹‹የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ከፊታቸው በማስቀደም እነዚህን ታላላቅ ተአምራት ያደረጉ እስራኤል በፍልስጥኤማውያን እንዴት ድል ተነሱ? የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦትስ እንዴት ተማረከች?›› የሚሉ ጥያቄዎች ከተነሡ ለታቦተ ጽዮን መማረክ፣ ለኃያላነ እስራኤል ድል መነሳት፣ ለካህኑ ዔሊ ሞት፣ እንዲሁም ለልጆቹ አፍኒንና ፊንሐስ በጦርነቱ መሞት ዋና ምክንያት የአፍኒንና ፊንሐስ ኃጢአት እንደዚሁም የዔሊ አለመታዘዝ ነው፡፡

የአፍኒንና ፊንሐስ ኀጢአት

፩ኛ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው መሥዋዕት ስቡ ሳይቃጠል አስቀድመው ሥጋ መብላታቸው

መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የዔሊ ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አያውቁም ነበር›› ይላል /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፲፪/፡፡ እግዚአብሔርን አያውቁም ማለቱ ለአምላክነቱ የሚገባውን ክብር አይሰጡም ለማለት ነው እንጂ የሊቀ ካህን ልጆች ኾነው ስለ እግዚአብሔር ህልውና መግቦት፣ ገዥነት፣ ወዘተ አያውቁም ለማለት አይደለም፡፡ የአዋቂ አጥፊዎች እንደ ኾኑ ለመናገር ነው እንጂ፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ ለእግዚአብሔር የሚቃጠለው የስብ መሥዋዕት ሳይቀርብ አስቀድመው ጥሬ ሥጋ ሳይቀር ገና ሳይቀቀል ይወስዱ ነበር፡፡ እንኳን ለመሥዋዕት ከሚቀርበው ሥጋ መመገብ ከድካም ውጤት ዐሥራቱን፣ በኵራቱን፣ ቀዳምያቱን አለመስጠት በእግዚአብሔር ዘንድ ያስጠይቃል፡፡ ዐሥራት ከገንዘብ፤ በኵራት ከእንስሳት፤ ቀዳምያት ከአዝዕርት ከፍራፍሬ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ስጦታ ነው፤ ይህንን ማድረግም ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡

ስቡ ሳይቃጠል፣ መሥዋዕቱም ሳያርግ ለሆዳቸው ያደሩ አፍኒንና ፊንሐስ ሥጋ በመብላታቸው ምክንያት ‹‹ምናምንቴዎች›› እንደ ተባሉ፣ ዛሬም እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ የቤተ ክርስቲያንን ዕድገትና ልማት የሚናፍቁ ደጋግ ክርስቲያኖች የሚያስገቡትን ዐሥራት፣ በኵራት፣ ቀዳምያት በመዝረፍ ቤተ ክርስቲያንን የሚበድሉ ብዙ ምናምንቴዎች አይታጡም፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ ሲስገበገቡለት የነበረው ሥጋ አላዳናቸውም፡፡ እነርሱ ያለ ቀባሪ በጠላት ሰይፍ ተመተው እንደ ወደቁ ዛሬም ቤተ ክርስቲያንን የሚዘርፉ፣ ሙዳየ ምጽዋት የሚገለብጡ ዅሉ ሥጋቸው በደዌ፣ በመቅሠፍት፤ ነፍሳቸውም በሲዖል መቀጣቱ አይቀርም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉት እኛ እንድንማርባቸው እንድንገሠፅባቸው ነውና ከዚህ ታሪክ ትምህርት ወስደን ሰማያዊውን ጸጋ በምድራዊው ጥቅም ለውጠን እንዳንጐዳ ሰውና እግዚአብሔርን ከሚያስቀይም መጥፎ ድርጊት ለመመለስ ዛሬውኑ መወሰን ይኖርብናል፡፡ ‹‹ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ /ሮሜ. ፰፥፮/፡፡

፪ኛ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር መሰሰናቸው

ዝሙት በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተጠላ፣ ሰውነትን ዅሉ የሚያረክስ ኃጢአት ነው፡፡ ሌሎቹ ኃጣውእ በአፍኣ ይሠራሉ፤ ዝሙት ግን በገዛ ሥጋ ላይ ስለሚሠራ ሰውነትን ዅሉ ያሳድፋል፡፡ ‹‹ከዝሙት ሽሹ፤ ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ዅሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙት የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአት ይሠራል፤›› /፩ኛ ቆሮ. ፮፥፲፰/ ተብሎ እንደ ተጻፈ፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ይሰስኑ ነበር፡፡ የእነዚህን ሰዎች ኃጢአት እጅግ የከፋ የሚያደርገው በመገናኛው ድንኳኑ ውስጥ ዝሙት መፈጸማቸው ነው /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፪/፡፡ እግዚአብሔር ፍጹም ቅዱስ ነውና በቅድስና እንድናገለግለው ይፈልጋል፡፡ ‹‹ኩኑ ቅዱሳነ ወቀድሱ ርእሰክሙ እስመ ቅዱስ አነ እግዚአብሔር አምላክክሙ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ እንደ ኾንኩ እናንተም ቅዱሳን ኹኑ፤ ሰውነታችሁንም ቀድሱ›› /ዘሌ. ፲፩፥፵፬/ በማለት በሊቀ ነቢያቱ ቅዱስ ሙሴ አንደበት የተናገረው ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

ከእግዚአብሔር ውጭ በማንኛውም ነገር መመካት ወይም መታመን ዝሙት ነው፡፡ ሰው በወገን፣ በሥልጣን፣ በሀብት ወይም በዕውቀት እየታበየ የሚያቀርበው መባዕ፣ የሚጸልየው ጸሎት በአጠቃላይ መንፈሳዊ አገልግሎት ከንቱ ነው፡፡ መጀመሪያ እነዚህን ዝሙታት ማስወገድ አለበት፡፡ በእውነት የእኛስ አገልግሎታችን በንጽሕና በቅድስና የታጀበ ነውን? ብዙ ንጹሐን ቀሳውስትና መነኮሳት እንደዚሁም ዲያቆናት እንዳሉ ዅሉ ሥጋቸውን በዝሙት እያሳደፉ በድፍረት ማገልገል አለብኝ በማለት ማኅበረ ካህናቱና ሕዝበ ክርስቲያኑን የሚበጠብጡ እንዳሉ የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በአፍኒንና ፊንሐስ የዝሙት ኀጢአት ምክንያት በአስራኤል ላይ ያደረሰው ቍጣና መቅሠፍት ዛሬም በረከሰ ሰውነታቸው ቤተ መቅደሱን በሚደፋፈሩ ሰዎች ምክንያት የምናጣው በረከትና የሚመጣው መቅሠፍት ቀላል አይኾንም፡፡

እስራኤል ከግብጽ ወጥተው ወደ ምድረ ርስት ሲጓዙ የአሕዛብን መንደሮች ያቋርጡ ነበር፡፡ በሰጢን መንደር በሰፈሩበት ጊዜ የእስራኤል ጐበዛዝት /ጐልማሶች/ በአሕዛብ ቈነጃጅት በዝሙት ተነደፉ፡፡ ከእስራኤል አንዱ ከምድያማዊቷ ሴት ጋር በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ተኛ፡፡ የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ለእግዚአብሔር ሕግ በመቅናት ሁለቱንም በአንድ ጦር ሆዳቸውን ወግቶ ገደላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ከቍጣው ተመለሰ፤ መቅሠፍቱም ቆመ፡፡ ስለዚህም ‹‹ለእርሱ፣ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘለዓለም ክህነት ቃል ኪዳን ይኾንለታል፤›› በማለት እግዚአብሔር አምላክ ለፊንሐስ ወልደ አልዓዛር ቃል ኪዳን እንደ ሰጠው በመጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል /ዘኊ. ፳፭፥፲፫/፡፡

ዛሬም በዝሙት ሰውነታቸውን እያረከሱ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ካላገለገልን የሚሉትን እንደ አልዓዛር ልጅ እንደ ፊንሐስ በመንፈሳዊ ቅንዓት ተነሳሥተን ልንገሥፀቸው ይገባል፡፡ ራሳቸውን ያረከሱ አገልጋዮች በድፍረት ቤተ መቅደስ ሲገቡ ርኵሰታቸውን እያወቀ ዝም ብሎ የሚያይ ምእመን መልካም ሥራ መሥራት መልካም እንደ ኾነ እያወቀ ባለመሥራቱ ፍርድ ያገኘዋል፡፡ ሰዎች የእግዚአብሔር ቤተ መቅደሶች ናቸው፡፡ ወገኖቻችን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የኾነውን ሰውነታቸውን በዝሙት፣ በዘረኝነት፣ በትዕቢት፣ በስርቆት፣ በአጠቃላይ በኃጢአት ሲያረክሱ እያየን ዝም አንበል፡፡ ቢሰማን ያን ሰው እንጠቅመዋለን፤ ባይሰማንና በክፉ ሥራው ቢጸና ግን በራሱ ላይ የእሳት ፍሕም ያከማቻል /ምሳ. ፳፭፥፳፪/፡፡

፫ኛ ሌሊት ሲነድ የሚያድረውን እሳት ማጥፋታቸው

አፍኒንና ፊንሐስ ሌሊት በደብተራ ኦሪት ሲነድ የሚያድረውን ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የእሳት ቍርባን ያጠፉ ነበር /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፰/፡፡ ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት ማስቀረት ክብር ይግባውና ባለቤቱን ማቃለል ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የሚያቃልለውን እንደሚያዋርድ፣ የሚያከብረውን እንደሚያከብር ራሱ እንዲህ በማለት ተናግሯል፤ ‹‹ያከበሩኝን አከብራለሁና፤ የናቁኝም ይናቃሉና፤›› /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፴/፡፡ ቀደምት አባቶቻችን ለእግዚአብሔር ያቀርቡ የነበረውን ዐሥራት፣ በኵራት፣ ቀዳምያት እኛስ እያቀረብን ነውን?

ይቆየን፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያም እና ታቦተ ጽዮን – ካለፈው የቀጠለ

ኅዳር ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዲያቆን ሽመልስ መርጊያ

new

አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ባቀረበ ጊዜ፣ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድኅት ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ እንደሚያድናቸው በምሳሌው ተረድቶ ተደስቶ ነበር፡፡ ጌታችን ይህን ሲያስረዳን ‹‹አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤትን አደርገ፡፡ አየም፤ ደስም አለው፤›› ብሎ ገለጠልን /ዮሐ.፰፥፶፮/፡፡ እንደ ልቤ የተባለው ንጉሥ ዳዊት በቃል ኪዳኗ ታቦት ፊት በደስታ መዘመሩም እግዚአብሔር ቃል የአዳም ተስፋ ከኾነችው ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ዓለምን እንደሚያድን በማስተዋሉ ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ይህንን እውነት መስክረዋል፡፡

ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ሲል ይናገራል፤ ‹‹ከአዳም ጎን በተገኘችው አንዲት ዐጥንት ምክንያት ሰይጣን ከአዳም ማስተዋልን አራቀ፡፡ ነገር ግን ከእርሱ አብራክ በተገኘችው በቅድስት ድንግል ማርያም ምክንያት በእርሱ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን እንደ ዳጎን ተንኮታኩቶ ወደቀ፡፡ በታቦቱ በተመሰለችው በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ባደረው በጌታችን በመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የድል ዐዋጅ ታወጀ፡፡ በቃል ኪዳኗ ታቦት ሥር ዳጎን ተሰባብሮ እንደተገኘ እንደዚሁ ክፉው ሰይጣን በታመኑበት ፊት ድል ተነሣ፡፡ ለነገር ጥላ አለውና እግዚአብሔር የማደሪያው ምሳሌ በኾነችው በቃል ኪዳኗ ታቦት ኃይሉን በዳጎን ጣዖት ላይ እንዳሳየ እንደዚሁ አጥፊያችንን በማጥፋት እግዚአብሔር ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ በኃጢአት ምክንያት በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ሰይጣንን ድል ነሳው፡፡ የእግዚአብሔር በግ በኾነው በክርስቶስ እኛን ያዳነን እግዚአብሔር አብ ስሙ የተመሰገነ ይኹን፡፡››

ቅዱስ ጀሮም እንደዚሁ ‹‹ቅድስት ድንግል ማርያም ለጌታዋ በእርግጥ እውነተኛ አገልጋዩ ነበረች፡፡ እርሷ እንደ ቃል ኪዳኗ ታቦት በሕሊናዋ ከእግዚአብሔር ሕግጋት ውጪ ሌላ ምንም ሐሳብ አልነበራትም፡፡ በውስጥም በውጪም ነውር የሌለባት ንጽሕት ናት፡፡ እንደ ቃል ኪዳኗ ታቦት በውጪም በውስጥም በቅድስና የተጌጠችና ሕጉንም ጠብቃ የተገኘች የክርስቶስ ሙሽራ ናት፡፡ በቃል ኪዳን ታቦቱ ውስጥ ከሕጉ ጽላት ውጪ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ እንዲሁ አንቺም ቅድስት ሆይ በሕሊናሽ ምንም ነውር የሌለብሽ ንጽሕት ነሽ›› ሲል የእመቤታችንን ንጽሕና አስረድቷል፡፡ እስክንድርያዊው ዲዮናስዮስም ‹‹ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካህን ይኾን ዘንድ በሰው እንዳልተመረጠ እንደዚሁ የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን የእርሱ ማደሪያ ይኾን ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ ማደሪያ የቅድስት ድንግል ማርያምን ቅድስናና ንጽሕና ያውጅ ዘንድ ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ታትሞአል፤ ታትሞም ለዘለዓለም ይኖራል›› ይላል፡፡

የሚላኑ ቅዱስ አምብሮስ ደግሞ ‹‹ነቢዩ ዳዊት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት በደስታ እየዘለለ ለአምላኩ ዘመረ፡፡ የቃል ኪዳኗ ታቦት የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌና ጥላ ካልኾነች የማን ምሳሌና ጥላ ልትኾን ትችላለች? ይህቺ ታቦት በውስጧ የሕጉን ጽላት እንደ ያዘች እንደዚሁ ቅድስት ድንግል ማርያምም የሕጉ ባለቤት የኾነውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማኅፀኗ ተሸክማዋለች፡፡ የቃል ኪዳኗ ታቦት የኦሪትን ሕግ በውስጧ እንደያዘች አማናዊቱ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያምም ወንጌል የተባለው ክርስቶስን ይዛዋለች፡፡ የመጀመሪያይቱ ታቦት የእግዚአብሔር ትእዛዛትን የያዘች ስትኾን ሁለተኛይቱና አማናዊቱ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም ግን እግዚአብሔር ቃልን በውስጧ ተሸክማዋለች፡፡ የቃል ኪዳን ታቦቱ በእርግጥ በውስጥም በውጪም በወርቅ የተለበጠ ነበር፡፡ አማናዊቱ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም ግን በውስጥም በውጪም በድንግልና የተጌጠች ናት፡፡ የቃል ኪዳኗ ታቦት የተጌጠችው ምድራዊ በኾነ ወርቅ ሲኾን አማናዊቱ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ሰማያዊ በኾኑ ጸጋዎች የተሸለመች ናት፤›› በማለት እመቤታችን የታቦተ ጽዮን ምሳሌ ስለ መኾኗ አስተምሮናል፡፡

አባታችን አዳም ድኅነቱ የሚፈጸመው በሚስቱ ምክንያት እንደ ኾነ ተረድቶ ለሚስቱ ‹‹ሔዋን›› የሚል ስም እንደ ሰጣት ንጉሥ ዳዊትም በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሚድን በመረዳቱ እመቤታችንን ‹‹አምባዬ መጠጊያ ነሽ›› ሲላት ‹‹ጽዮን›› በሚል ስም እመቤታችንን መጥራቱን ከመዝሙሩ ለመረዳት እንችላለን፡፡ ይህን ይዘው ብዙዎች ነቢያት ስለ ድንግል ማርያም ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም ተጠቅመዋል፡፡ ‹‹ጽዮን›› ማለት ትርጕሙ ‹‹አምባ፣ መጠጊያ›› ማለት ነውና፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳይያስ የራሳቸውን ሥርዐትና ሕግ ለማስጠበቅ ሲሉ በክርስቶስ ስላላመኑ አይሁድ ሲናገር፡- ‹‹እነሆ በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ ዐለት አኖራለሁ፤›› አለ /ኢሳ.፰፥፮፬፤ ፳፰፥፲፮/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ትንቢት ስለ ክርስቶስ የተነገረ መኾኑን በሮሜ መልእክቱ ጽፎልናል /ሮሜ.፱፥፴፪-፴፫/፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስና ቅዱስ ጳውሎስ ጽዮን ያሏት ቅድስት ድንግል ማርያምን መኾኑንም በዚህ ኃይለ ቃል ለመረዳት እንችላለን፡፡ የማሰናከያ ዐለት የተባለው ክርስቶስ መኾኑንም ‹‹እነሆ የብዙዎች ልብ ሐሳብ ይገለጥ ዘንድ ይህ ለእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሹሞአል፤›› በሚለው ኃይለ ቃል ማረጋገጥ ይቻላል /ሉቃ.፪፥፴፬-፴፭/፡፡ ስለዚህ የማሰናከያ ዐለት የኾነውን ክርስቶስን ፀንሳ የወለደችው ቅድስት ድንግል ማርያም ጽዮን ተብላ መጠራቷንም በእነዚህ ጥቅሶች እንረዳለን፡፡

ቅዱስ ዳዊትና ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ከጽዮን ታዳጊ ይመጣል፤ ከያዕቆብም ኃጢአትን ያርቃል፤›› /መዝ.፲፫፥፲፤ ኢሳ.፶፱፥፳/ በማለት ስለ ክርስቶስ የዓለም መድኀኒትነት አስቀድመው ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ይህን ምሥጢርም ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ ፲፩፥፳፮ ላይ ጠቅሶታል፡፡ በዚህም ቦታ ጽዮን የተባለችው ቅድስት ድንግል ማርያም መኾኗን ለማስተዋል እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ጌታችን የተወለደው ከእመቤታችን ነውና፡፡ ‹‹መድኀኒት›› የተባለው ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑንም ‹‹… በዳዊት ከተማ መድኀኒት እርሱ ክርስቶስ ተወለደ፤›› /ሉቃ.፪፥፲/ በማለት ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ገለጾልናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ኢየሱስ›› ማለት ‹‹መድኀኒት›› ማለት ነው /ማቴ.፩፥፳፩/፡፡ በዚህ መሠረት ነቢያቱ ‹‹መድኀኒት ከጽዮን ይወጣል፤›› ሲሉ መናገራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽዮን ከተባለችው ከቅድስት ድንግል ማርያም ይወለዳል ማለታቸው እንደ ኾነ ግልጽ ነው፡፡

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹ዓለም ሁለት ዓይነት ሰዎች  የሚኖሩባት ሥፍራ ናት፡፡ አንደኛው ሰው የሔዋን ዐይነት ዐይኖች ስላለው በእነዚህ ዐይኖቹ ድንጋዩንና እንጨቱን አምላክ ነው እያለ ይገዛለታል፡፡ ሌላኛው ደግሞ የቅድስት ድንግል ማርያም ዓይነት ዐይኖች ስላሉት ክርስቶስ ኢየሱስን ይመለከታል ለእርሱም ይገዛል›› ብሎ ያስተምራል /ውርስ ትርጕም/፡፡ እኛም የእመቤታችን ዓይነት ዐይኖች ስላሉን፤ እይታችንም ፍጹም፣ ንጹሕና በማስተዋል ላይ የተመሠረተ ስለ ኾነ ታቦታትን ስንመለከት እመቤታችንን፤ እመቤታችንን ስንመለከት ደግሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንመለከተዋለን፡፡ ምእመናን በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች በመኾናችን በጸጋ የክርስቶስ ወንድሞች ተብለን ተጠርተናል፡፡ ይህም የቅድስት ድንግል ማርያም ልጆች መኾናችንን ያመላክታል፡፡ ‹‹ወላጁን የሚወድ ከእርሱ የተወለደውንም ይወዳል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /፩ኛዮሐ.፭፥፩/ እኛ ኦርቶዶክሳውያንም ቅድስት ድንግል ማርያምን ስለምንወዳት ከእርሷ በሥጋ የተወለደውን ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንወደዋለን፡፡ እግዚአብሔር አብን እንደምንወድና እንደምናመልከው ዅሉ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስንም እንደ ባሕርይ አባቱ እኩል እንወደዋለን፤ እናመልከዋለን፡፡ በአጠቃላይ ሥላሴን እንደምንወድ ዅሉ ከሥላሴ አብራክ የተወለዱ ክርስቲያኖችንና በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረውን የሰውን ፍጥረት እንወዳለን፡፡

በአጠቃላይ ስለ ታቦተ ጽዮን የተጻፉ ዅሉ እግዚአብሔር ቃል ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ለፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጥላና ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በብሉይ ኪዳን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ተአምራት ለድንግል ማርያምና ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመስጠት ለልጆቿ ታስተምራለች፡፡ ነገር ግን ጽዮን የሚል ንባብ ዅሉ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የሚናገር ነው ማለታችን አይደለም፡፡ ከላይ እንደ ተመለከትነው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታችን ሲናገር ስለ እርሱ የተነገሩ ምሥጢራን ብቻ መርጦ እንደ ተጠቀመና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጽዮን የሚል ምንባብ በሙሉ ስለ ጌታችንና ስለ እመቤታችን የተጻፈ ነው ብሎ እንዳልተረጐመ ዅሉ፣ እኛም ጽዮን የሚል ቃል ባገኘን ቍጥር ስለ ድንግል ማርያም የተጻፈ ነው ብለን አንተረጕምም፡፡ እንደዚህ የምንል ከኾነ ግን ትልቅ ስሕተት ውስጥ እንገባለንና፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት ያሳትፈን፡፡ የእግዚአብሔር አብ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት በዅላችን ላይ ይደር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያም እና ታቦተ ጽዮን – የመጀመሪያ ክፍል

ኅዳር ፳ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዲያቆን ሽመልስ መርጊያ

new

በየዓመቱ ኅዳር ፳፩ ቀን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙ ታላላቅ ተአምራት የሚታሰቡበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የታቦተ ጽዮንን ተአምራት እግዚአብሔር ቃል ቅድስት ድንግል ማርያምን ታቦቱ አድርጎ ከፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጋር በማነጻጸር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ድርሻ በስፋት ታስተምራለች፡፡ ለምሳሌ እስራኤላውያን ባሕረ ዮርዳኖስን በአቋረጡበት ወቅት ታቦተ ጽዮንን የተሸከሙ ካህናት እግራቸው የዮርዳኖስን ባሕር በመንካቱ ባሕሩ ለሁለት ተከፍሎ ነበር፡፡ ይህንን ታሪክም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድና ጥምቀትን በመመሥረት ከሰይጣን ባርነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት እንዳሸጋገረን በማመሥጠር ቤተ ክርስቲያናችን ታስተምርበታለች፡፡ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤላውያን ጋር ውጊያ በገጠሙበት ወቅት ታቦተ ጽዮንን ከእስራኤላውያን ማርከው ዳጎን በሚባለው ቤተ ጣዖታቸው ውስጥ አኑረዋት በነበረ ጊዜ ታቦቷ የዳጎንን ምስል አንኮታኩታ ጥላው ነበር፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ታሪክ እንደ ምሳሌ በመጠቀም ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ከአምልኮ ጣዖት ወጥተን አንድ አምላክን ወደ ማምለክ ስለ መመለሳችንና በእመቤታችን ምክንያት ስለ ተደረገልን የእግዚአብሔር ቸርነት ትምህርት ትሰጥበታለች፡፡ እኛም በዛሬው ዘግጅታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማናዊቷ ታቦተ ጽዮን መኾኗን የሚያስቃኝ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፤

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ካወጣቸው በኋላ የአምልኮ ሥርዐታትን ይፈጽሙበት ዘንድ የምስክሩን ድንኳን፣ የቃል ኪዳኗ ታቦትንና ለአምልኮ ሥርዐቱ ማከናወኛ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትን እንዲሠሩ አዝዟቸው ነበር፡፡ ከቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥም በእግዚአብሔር ጣት ዐሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉበት የሕጉ ጽላት፤ ዐርባ ዓመት ሙሉ እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ የተመገቡትን መና የያዘች መሶበ ወርቅ፤ አሮን ለክህነት አገልግሎት ስለ መመረጡ ምስክር የኾነችው፣ ለምልማና ፍሬ አፍርታ የተገኘችው የአሮን በትር ይገኙባታል /ዕብ.፱፥፬/፡፡ ደብተራ ድንኳኗንና በውስጧ የሚገኙ ንዋየተ ቅድሳትን እግዚአብሔር በሙሴ ሲያሠራ ለሰማያዊው ምሥጢር ምሳሌና ጥላ ናቸውና ተጠንቅቆ እንዲሠራቸው አዝዞት ነበር /ዕብ.፰፥፭/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህችን ድንኳን ‹‹የአገልግሎት ሥርዐታት የሚፈጸምባት ፊተኛይቱ ድንኳን›› ብሎ ይጠራታል፡፡ በዚህ መሠረት ደብተራ ድንኳኗና በውስጧ ያሉ ንዋያተ ቅድሳት ለሰማያዊው ምሥጢር ምሳሌና ጥላ እንደ ኾኑ እንረዳለን፡፡ የደብተራ ድንኳኗ ምሳሌ የኾችው ሰማያዊቱ ስፍራም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በውስጧ አማናዊውና ሰማያዊው ምሥጢረ መለኮት ይፈጸምባታልና፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ ስለ ኾነች፤ ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያሰጥ ምሥጢርም በውስጧ ስለሚከናወንባት በእርግጥም ሰማያዊ ስፍራ ናት፡፡

ታቦተ ጽዮን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች፡፡ ይህን ለመረዳት ግን ስለ ታቦተ ጽዮን አሠራርና መንፈሳዊ ትርጉም አስቀድመን ልንረዳ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ታቦተ ጽዮንን እንዲሠራ ብልሃትን፣ ጥበብን፣ ማስተዋልን፣ ዕውቀትን ይለይ ዘንድ መንፈሱን ያሳደረበትን ከይሁዳ ወገን የኾነውን ባስልኤልን መረጠ /ዘፀ.፳፭፥፱/፡፡ እርሱም እግዚአብሔር በሰጠው ማስተዋል ከማይነቅዝ እንጨት ርዝመቷ ሁለት ክንድ ተኩል፤ ወርዱዋ አንድ ክንድ ተኩል፤ ቁመቷ አንድ ክንድ ተኩል እንዲኖራት አድርጎ ታቦቷን ሠራት፡፡ በመቀጠል በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ ለበጣት፣ ከታቦቷም ዙሪያ የወርቅ አክሊልን አደረገላት፡፡ ካህናት ታቦተ ጽዮንን ለመሸከም እንዲረዳቸውም በአራቱም መዓዘናት በወርቅ የተሠሩ ቀለበቶችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገቡ ሁለት መሎጊያዎችን ሠራ፡፡ ከጥሩ ወርቅም የስርየት መክደኛውን በቃል ኪዳን ታቦቷ ላይ በርዝመቷና በወርደዋ ልክ ሠራ፡፡ የስርየት መክደኛውን እንዲጋርዱት አድርጎም ጥሩ ከኾነ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ኪሩቤልን ሥሎ በስርየት መክደኛው ግራና ቀኝ አስቀመጣቸው፡፡ እነዚህ በጥሩ ወርቅ የተሠሩት ሁለቱ ኪሩቤል ፊታቸው ወደ ስርየት መክደኛው ኾኖ እርስ በእርሳቸው እንዲተያዩ ተደርገው የተሠሩ ናቸው፡፡ በዚህ በስርየት መክደኛው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል እግዚአብሔር ለሙሴ እየተገለጠ ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር በግልጽ ያነጋግረው ነበር፤ ለሕዝቡም በደመና ዐምድ ይታያቸው ነበር /ዘፀ.፰፥፲፩፤ ፳፭፥፳፪-፴፫/፡፡

ወደ ምሥጢሩ ትርጓሜ ስንመለስም ታቦተ ጽዮን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ስትኾን፣ በውስጧ የያዘችው የሕጉ ጽላትም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቷ ከማይነቅዝ እንጨት መሠራቷ የእመቤታችንን ንጽሕና የሚያመለክት ሲኾን፣ በውጪም በውስጥም በጥሩ ወርቅ መለበጧ ደግሞ ቅድስናዋንና በሁለት ወገን ድንግል መኾኗን የሚያስረዳ ነው፡፡ ታቦተ ጽዮን በግራና በቀኝ በኩል በተዘጋጁ አራት ከወርቅ የተሠሩ ቀለበቶች ነበሯት፤ በእነዚያ የወርቅ ቀለበቶች ውስጥም ሁለት መሎጊያዎች ይገቡባቸው ነበር፡፡ ታቦቷን ለማንቀሳቀስ ባስፈለገ ጊዜ አራት ሌዋውያን ካህናት በመሎጊያዎቹ ይሸከሟታል፡፡ ይህ ሥርዐት በሰማያትም የሚታይ እውነታ ነው፡፡ የጌታን መንበር ገጸ ሰብእ፣ ገጸ ንሥር፣ ገጸ ላህምና ገጸ አንበሳ ያላቸው አርባዕቱ እንስሳት ይሸከሙታልና /ኢሳ.፮፥፩-፭፤ ሕዝ.፩፥፩-፲፮/፡፡ ለአማናዊቷ ታቦት ለቅድስት ድንግል ማርያምም ሰላምን የሚያወሩ፣ መልካም የምሥራችንም የሚናገሩ፣ መድኀኒትንም የሚያወሩ፣ ጽዮንንም ‹‹አምላክሽ ነግሦአል›› የሚሉ፣ እግሮቻቸው በተራሮች ላይ እጅግ ያማሩ የእርሷንና የጌታችንን ስም ተሸክመው ወንጌልን ለዓለም የሚሰብኩ ኦርቶዶክሳውያን መምህራን አሏት /ኢሳ.፶፪፥፯/፡፡ የስርየት መክደኛው መቀመጫው የንጹሐን አንስት፣ መክደኛው የንጹሐን አበው፣ ግራና ቀኙ የሐናና የኢያቄም ምሳሌ ነው፡፡ በክንፎቻቸው የጋረዱት  ኪሩቤልም የጠባቂው መልአክ ቅዱስ ሚካኤልና የአብሣሪው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ምሳሌዎች ናቸው፡፡

የስርየት መክደኛው ስርየቱ የሚፈጸምበት ስፍራ ቢኾንም ነገር ግን በዚህ ቦታ ምንም ዓይነት መሥዋዕት አይቀርብም ነበር፡፡ ይህም በጊዜው አማናዊው መሥዋዕት ገና እንዳልተሠዋ ያስገነዝበናል፡፡ ይህ ስፍራ እግዚአብሔር ለሙሴ የሚገለጥበት ቦታ ነው፤ ከእርሱ ውጪ ሌላ ነገር በእዚያ ላይ ማረፍ አይችልም ነበር፡፡ ከዚህም የምናስተውለው አንድ ምሥጢር አለ፤ ይኸውም እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን ሊፈጽም ሰው በኾነ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብበት ልዩ ስፍራ እንዳዘጋጀ ያመላክተናል፡፡ ይህ ስፍራ አማናዊ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ እንደሚያስፈልግ የሚያስገነዝብ ስፍራ ነው፡፡ ይህን ለማመልከትም ለኃጢአት ስርየት የቀረበው መሥዋዕት ከታረደ በኋላ ካህኑ ደሙን በጣቱ እየነከረ ሰባት ጊዜ በስርየት መክደኛው አንጻር በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ይረጨው ነበር /ዘሌ.፬፥፮/፡፡ ነገር ግን ይህ ደም ከስርየት መክደኛው ላይ አያርፍም ነበር፤ ምክንያቱም በዚህ ስፍራ መቅረብ የሚገባው አማናዊው መሥዋዕት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነውና፡፡

ይህ የስርየት መክደኛ ለእኛ የሚያስተላለፈው ተጨማሪ መልእክትም አለው፡፡ ይኸውም አማናዊው መሥዋዕት ክርስቶስ መሥዋዕት ኾኖ ዓለምን ማዳኑ እንደማይቀርና መሥዋዕቱ የሚቀርብበት ስፍራም በቅድስተ ቅዱሳኑ (ቤተ መቅደሱ) ውስጥ እግዚአብሔር በምሕረት በሚገለጥበት በቃሉ ማደሪያ በጽላቱ ላይ መኾን እንደሚገባው ያስገነዝበናል /ዕብ.፬፥፲፮/፡፡ ይህም እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ሚልክያስ ላይ አድሮ ‹‹ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይኾናልና በየስፍራውም ስለ ስሜ ዕጣንን ያጥናሉ፤ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፤›› /ሚል.፩፥፲፩/ በማለት እንደ ተናገረው የስርየት መክደኛው አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ቍርባንን ለምትፈጽምበት ጽላት ወይም ታቦት ምሳሌ መኾኑን ያሳየናል፡፡ የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱት በጥሩ ወርቅ የተሠሩት የኪሩቤል ምስሎችም አማናዊው መሥዋዕት በሚሠዋበት ጊዜ በዙሪያው ረበው የሚገኙ የመላእክት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችን እንዳስተማሩን ሁለቱ ኪሩቤል የተባሉት ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ናቸው፡፡ ይህን ለማስገንዘብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በመንበረ ታቦቱ ላይ ምስለ ፍቁር ወልዳ እንዲቀመጥ ታዝዛለች፡፡ ምስለ ፍቁር ወልዳን  ላስተዋለ ሰው በትክክል የታቦተ ጽዮንን መንፈሳዊ ትርጕም ይረዳል፡፡

ታቦተ ጽዮን ከሌሎች የብሉይ ኪዳን ንዋያተ ቅድሳት በተለየ መልኩ እጅግ ግሩም የኾነ ምሥጢርን በውስጧ ይዛለች፡፡ ይህን ድንቅ ምሥጢር ለመረዳትም አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑ ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ጽዮን ከተማ ባስመጣበት ወቅት በታቦቷ ፊት በሙሉ ኃይሉ በደስታ እየዘለለ ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ መዝሙርን አቅርቦ ነበር /፪ሳሙ.፮፥፲፪-፲፯/፡፡ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሚኾን ድርጊት በሐዲስ ኪዳንም ተፈጽሟል፡፡ ይኸውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅድስት ኤልሳቤጥ ሰላታ በሰጠቻት ጊዜ የስድስት ወር ፅንስ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የእመቤታችንን የሰላምታ ድምፅ በሰማ ጊዜ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ኾኖ በደስታ ዘሏል (ሰግዷል) /ሉቃ.፩፥፵፬/፡፡ ቅዱስ ዳዊት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት እየተደሰተ ለአምላኩ የምስጋና ቅኔን መቀኘቱም ለሰው ልጆች ዅሉ የመዳናችን ምክንያት የኾነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን በቃል ኪዳኗ ታቦት በኩል አስቀድሞ በዓይነ ሕሊና ስለ ተመለከታቸው ነበር፡፡

ይቆየን፡፡

ጽላተ ሕጉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ተመለሰ

ኅዳር ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በይብረሁ ይጥና

st-mic

ከግራ ወደ ቀኝ፡- ቅዱስ ሚካኤል፣ መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ደብር እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ተቋም ሙዚየም ውስጥ የተገኘው የቅዱስ ሚካኤል ጽላት ወደ ቤተ ክርስቲያን ተመለሰ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት የቅርስ ጥበቃ፣ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ሓላፊ መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ እንዳስታወቁት፤ ጽላቱ ወደ ፊት ለብቻው ቤተ ክርስቲያን እስኪታነጽለት ድረስ ኅዳር ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን በአደራ መልክ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡

‹‹ጽላቱ መቼ፣ እንዴትና በማን አማካይነት ወደ ዩኒቨርስቲው ሊገባ ቻለ?›› ለሚለው ጥያቄአችን መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ምላሽ ሲሰጡም ‹‹ከየትና እንዴት እንደገባ የሚገልጥ ማስረጃ ባይገኝም ሰኔ ፲፪ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ.ም ሚስተር እስቲፈን ሮቶ በተባለ ግለሰብ ወደ ዩኒቨርስቲው እንደገባ ከዩኒቨርስቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፤›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም ጽላቱ በዐፄ ኃይለ ሥላሴና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዘመን የነበረ መኾኑ ከጽላቱ ላይ ተጽፎ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

እንደ መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ማብራሪያ ለጽላቱ መገኘትና ወደ መንበሩ መመለስ መነሻ የኾነው አቶ በለጠ ዘነበ የተባሉ የ፹ ዓመት አረጋዊ የተመለከቱት ራእይና ያደረጉት ጥረት ነው፡፡ እኒህ አባት ‹‹የቅዱስ ሚካኤል ጽላት በዩኒቨርሲቲው ሙዚየም ውስጥ ተቀብሮ ይገኛልና መውጣት አለበት›› በማለት በተደጋጋሚ መምሪያውን ሲያሳስቡ እንደነበረ ያስታወሱት መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን በልዩ ልዩ ጊዜያት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ለዩኒቨርሲቲው የተጻፉ ደብዳቤዎችን መሠረት በማድረግ ጽላቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለስ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም የቅዱስ ሚካኤል ጽላት ለቤተ ክርስቲያናችን እንዲመለስ ጥረት ላደረጉትና ለተባበሩት ለአቶ በለጠ ዘነበ፣ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ለመንግሥት አካላት በሙሉ መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ በቤተ ክርስቲያን ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)

ኅዳር ፲፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጾመ ነቢያት በየዓመቱ ከኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ እስከ በዓለ ልደት ዋዜማ ድረስ የሚጾም፤ ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንደኛው ጾም ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ለማዳን ሲል የሰውን ሥጋ ስለ መልበሱ፤ ወደ ግብጽ ስለ መሰደዱ፤ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለ መጠመቁ፤ በትምህርቱ ብርሃንነት ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፤ ለሰው ልጆች ድኅነት ልዩ ልዩ መከራን ስለ መቀበሉ፤ ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱና ዳግም ምጽአቱ በየዘመናቱ የተነሡ ቅዱሳን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ትንቢት ተናግረዋል፤ ትንቢቱ ደርሶ፣ ተፈጽሞ ለመመልከትም ‹‹አንሥእ ኃይለከ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሣ፤ እጅህን ላክ›› እያሉ በጾም በጸሎት ተወስነው አምላክ ሰው የሚኾንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት እያሰሉ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡

ይህ ጾም የእግዚአብሔርን ሰው መኾን ሲጠባበቁ የኖሩት የነቢያት ትንቢትና ጸሎት በጌታችን መወለድ ፍጻሜ ያገኘበት ወቅት በመኾኑ ‹‹ጾመ ነቢያት (የነቢያት ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ለአዳም የተነገረው የድኅት ተስፋ ስለ ተፈጸመበትም ‹‹ጾመ አዳም (የአዳም ጾም)›› ይባላል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ሰው መኾን በስፋት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበት ወቅት በመኾኑም ‹‹ጾመ ስብከት (የስብከት ጾም)››፤ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት በመኾኑ ደግሞ ‹‹ጾመ ልደት (የልደት ጾም)›› በመባል ይታወቃል፡፡ እንደዚሁም ‹‹ጾመ ሐዋርያት›› ይባላል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹በዓለ ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብረዋለን፤ በዓለ ልደትንስ ምን አድርገን እናከብረዋለን?›› በማለት ነቢያት የጾሙትን ከልደተ ክርሰቶስ በፊት ያለውን ጾም ጾመዋልና፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ይህ ጾም ‹‹ጾመ ፊልጶስ (የፊልጶስ ጾም)›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በአፍራቅያና አውራጃዋ ዅሉ እየተዘዋወረ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወንጌልን በማስተማር፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ብዙዎችን ወደ አሚነ እግዚአብሔር ሲመልስ ቆይቶ ትምህርቱን በማይቀበሉ የአፍራቅያ ሰዎች አማካይነት በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሊቀብሩ ሲሉም ስለ ተሰወረባቸው የሐዋርያውን ሥጋ ይመልስላቸው ዘንድ ሱባዔ ይዘው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በለመኑት ጊዜ እግዚአብሔር ልመናቸውን ተቀብሎ በ፫ኛው ቀን መልሶላቸው ሥጋውን (አስከሬኑን) በክብር አሳርፈውታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የሐዋርያውን ሥጋ ካገኙ በኋላ እስከ ጌታችን ልደት ድረስ ጾመዋል፡፡ ስለዚህም ጾመ ነቢያት ‹‹ጾመ ፊልጶስ›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ወልደ አምላክ ክርስቶስን በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደምትፀንሰው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ካበሠራት በኋላ እመቤታችን ‹‹ሰማይና ምድር የማይወስኑትን አምላክ ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ?›› በማለት ጌታችንን ከመውለዷ አስቀድማ ጾማዋለችና ይህ ጾም ‹‹ጾመ ማርያም›› በመባልም ይታወቃል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ በገና ጾም ነቢያትም ሐዋርያትም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም እንደ እነርሱ በረከትን እናገኝ ዘንድ ይህንን ጾም መጾም እንደሚገባን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሥርዐት ሠርተውልናል፡፡ በዚህም መሠረት የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን፤ መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ዅላችንም በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል፡፡

ምንጭ፡-

ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፣ አንቀጽ ፲፭፡፡

ጾምና ምጽዋት፣ ዲያቆን ቃኘው ወልዴ፤ ገጽ ፵፯ -፶፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ዘመነ አስተምሕሮ

ኅዳር ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በቤተ ክርስቲያናችን የዘመን አከፋፈል መሠረት ከኅዳር ፮ ጀምሮ እስከ ታኀሣሥ ፲፫ ቀን ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምሕሮ ይባላል፡፡ ትርጕሙም ይቅርታ የመጠየቅ (የምልጃ) ዘመን ማለት ነው፡፡ ዘመኑ ቤተ ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት፤ ምእመናንንም ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት፤ ስለዚህም በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ባሉት እሑዶች የሚገኙ ሰንበታት (እሑዶች) አስተምሕሮ፣ ቅድስት፣ ምኵራብ፣ መጻጉዕ እና ደብረ ዘይት በመባል ይጠራሉ፤ የመጀመሪያውን ሳምንት (የአስተምሕሮ) ትምህርትም እነሆ!

እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን /ማቴ.፮፥፲፪/፡፡

ይህ ቃል የተወሰደው ጌታችን በደቀ መዛሙርቱ በኩል እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለሚኖሩ (ዛሬም ላለን) ክርስቲያኖች እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ካስተማረው ጸሎት ነው፤ ‹‹በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፡፡ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ኾነች እንዲሁ በምድር ትኹን፡፡ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፡፡ እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፡፡ ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፡፡ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለም አሜን፤›› /ማቴ.፮፥፱-፲፬/፡፡

ይህ ጸሎት በጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ሊቃውንት «የጌታ ጸሎት» ተብሎ ይጠራል፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን የጸሎቱን የመጀመሪያ ሐረግ በመያዝ «አባታችን ሆይ» ወይም በግእዝ «አቡነ ዘበሰማያት» እንለዋለን፡፡ ይህ ጸሎት ጌታችን ራሱ ያስተማረው በመኾኑ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ የሌሎች ጸሎታት ዅሉ ማሰሪያ (ማሳረጊያ) ኾኖም ያገለግላል፡፡ በውስጡም «አባታችን ሆይ» ከምትለው ከመጀመሪያዋ ሐረግ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ እጅግ ጥልቅ የኾኑና ነፍስን የሚያጠግቡ፣ ወደ ሰማይ ከፍ የሚያደርጉ መንፈሳዊና ነገረ መለኮታዊ መልእክቶችን ያዘለ ነው፡፡ ይህ የዘመነ አስተምሕሮ የመጀመሪያው ሳምንት ስለ ይቅርታ የሚሰበክበት ነውና በጸሎቱ ውስጥ ስለዚህ የሚናገረውን አንቀጽ መሠረት አድርገን እንማራለን፤

«እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን» ከሚለው ኃይለ ቃልም የሚከተሉትን ቁም ነገሮች እንረዳለን፤

፩. እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን እንደሚወድ

አምላካችን ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ባይወድ ኖሮ ይቅርታን እንድንጠይቅ አይነግረንም ነበር፡፡ አዎ፤ እኛ ከተመለስን ምንም ያህል በደለኛ ብንኾን ይቅር ሊለን፤ ምንም ያህል ብንቆሽሸ ሊያድነን ዝግጁ ነው፡፡ እንዲህ እያለ ይጠራናል፤ «እናንተ ሸክማችሁ የከበዳችሁ፤ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ፡፡» ስለዚህ በዚሀ ጸሎትም ላይ «በደላችንን ይቅር በለን» ብለን እንድንጠይቀው አስተማረን፤ ይቅር ይለን ዘንድ፡፡

፪. ይቅር ለመባል ምን ማድረግ እንዳለብን

እግዚአብሔር ይቅር ሊለን ስለ ወደደም ይቅርታን ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን በዚሁ ቃል ነግሮናል፤ ማድረግ ያለብን ምንድን ነው?

ኀጢአታችንን ማወቅ (ማመን)

ጌታ «በደላችንን ይቅር በለን» ብለን እንድንጸልይ ሲነግረን በመጀመሪያ ደረጃ በደለኛ እንደኾንን እያስታወስን (እንድናስታውስ እያደረገን) ነው፡፡ ዅልጊዜም በማሰብ፣ በመናገርና በማድረግ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የኾነውን ልባችንን (ኅሊናችንን) እና ሰውነታችንን እናቆሽሻለን፤ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የሞተለትን ማንነታችንን እናጎድፋለን፡፡ ይህም የሰው ልጆች በቅድስና እርሱን መስለን እንድንኖር በኋላም የተዘጋጀልንን የዘለዓለም መንግሥት እንድወርስ ብቻ ፈቃዱ የኾነውን እግዚአብሔርን ያሳዝናል፤ በአርአያውና በአምሳሉ ለክብር የፈጠረው ሰውነታችን መጉደፉ ያስቆጣዋል፤ ንጹሐ ባሕርይ የኾነ እርሱ ኀጢአት አይስማማውምና፡፡

እንግዲህ ይቅር ለመባል በመጀመሪያ እንዲህ ኀጢአት እየሠራን መሆኑን ማወቅና ማመን ያስፈልገናል፡፡ ወደዚህ ዕውቀት ለመድረስም የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል መማር የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ስሕተት የሚታወቀው ያለውን ኹኔታ (ድርጊታችንን ንግግራችንን፣ ሐሳባችንን…) መኾን ከነበረበት (ከትክክለኛው) ጋር በማነጻጸር በሚዛን ላይ በማስቀመጥ ነው፡፡ የማነጻጻሪያ ሚዛኖቻችን ደግሞ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉ ሕግጋትና ትእዛዛት ናቸው፡፡ እነዚህን ስናውቅ ጕድለቶቻችንና ድካሞቻችን ፍንተው ብለው ይታዩናል፡፡ ካለዚያ ግን እየበደለን ያልበደልን ሊመስለን ይችላል፡፡

የበደሉንን ይቅር ማለት

ጌታችን በዚህ ጸሎት ይቅርታ እንድንጠይቀው በማስተማር ይቅር ሊለን እንደሚወድ ቢነግረንም ይቅር ለመባል ግን እኛ የበደሉንን ይቅር ማለታችን የግድ እንደኾነ በግልጽ አስቀምጦልናል፤ «በደላችንን ይቅር በለን» ከማለታችን በፊት «እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል» እንድንል ያዘዘን እኛ ይቅርታ የምናገኘው ሌሎችን ይቅር ስንል ብቻ መኾኑን ለማመልከት ነው፡፡ በዚሁ በተራራው ስብከት ይኸው ጉዳይ ሁለት ጊዜ በጌታችን ትምህርት ተሰጥቶበታል፡፡ «እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል፤» /ማቴ.፯፥፪/፡፡

በሌላ ቦታም እንዲህ ሲል ይህንኑ ጉዳይ በምሳሌ አስተምሯል፤

 ‹‹መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ለመቈጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች፤ መቈጣጠርም በጀመረ ጊዜ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፡፡ ባለ እዳው ሰው የሚከፍለው ስላጣ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ንጉሡ አዘዘ፡፡ በዚህም ጊዜ ባርያው ወድቆ ሰገደለትና ጌታ ሆይ ታገሰኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው፡፡ የዚያም ባርያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፡፡ ይህ ባርያ ግን ወጥቶ ከባልጀሮቹ /እንደርሱ ባርያ ከኾኑት/ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው፡፡ ባልንጀራው ባርያም ወድቆ ታገሰኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፤ ብሎ ለመነው፡፡ እርሱ ግን ሊተወው አልወደደም፡፡ ዕዳውን እስኪከፍልም በወኅኒ አኖረው፡፡ ይህንን ያዩ ሰዎችም አዘኑ፤ ሄደውም የኾነውን ለንጉሡ ተናገሩ፡፡ ከዚህ ወዲያ ንጉሡ ጠርቶ፣ አንተ ክፉ ባርያ ስለ ለመንከኝ ያን ዕዳ ዅሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህን የኾነውን ባርያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን አለው፡፡ ጌታውም ተቈጣና ዕዳውን እስኪከፍለው ድረስ ለሚያሰቃዩት አሳልፎ ሰጠው፤» /ማቴ.፲፰፥፳፫-፴፭/፡፡

ጌታ ይህንን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ የምሳሌውን ትርጕም እንዲህ ሲል ገልጦታል፤ «ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል፡፡›› በአጠቃላይ ይቅር ለመባል ይቅር ማለት የግድ ነው፡፡ በእኛ ላይ የሚፈረድብን ፍርድ በእኛው እጅ ላይ ነው፡፡ ጌታችን በእነዚህ ትምህርቶች እንዲህ እያለን ነው «እኔ እናንተ ላይ የምፈርደው እናንተ በራሳችሁ ላይ በፈረዳችሁበት መንገድ ነው፡፡»

ይቅርታ መጠየቅ

ኀጢአታችንን ካወቅንና ካመንን፣ የበደሉንንም ከልብ ይቅር ካልን በኋላ ይቅር እንድንባል መጠየቅ (መለመን) አለብን ፡፡ ጌታችን «ይቅር በለን ብላችሁ ጸልዩ›› ብሎ ከማስተማሩም ይህንን እንረዳለን፡፡ ወደ ንስሐ አባት መሔድና ኀጢአትን ተናዞ ቀኖና መቀበል የሚገባው መጀመሪያ በዚህ መልኩ ስለ ኀጢአት ካለቀሱ በኋላ ነው፡፡ ከዚያም ቀኖና ተቀብለን ስንፈጽምም ይኸው ስለ ኀጢአት ይቅርታ መጠየቁ ይቀጥላል፡፡ ይቅርታ የምንጠይቀው አዳዲስ ስለ ሠራናቸውና ንስሐ ገና ስላልገባንባቸው ኀጢአቶቻችን ብቻ ሳይኾን ንስሐ ስለ ገባንባቸው ስለ ቀደሙት በደሎቻችንም ጭምር ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ዳዊት «የቀደመ በደላችንን አታስብብን፤ ምሕረትህ በቶሎ ታግኘን፤» /መዝ.፸፰፥፰/ እያልን ሰለ ቀደመው በደላችንም እያሰብን በሕይወታችን ዘመን ዅሉ ይቅርታ መጠየቅ አለብን፡፡

እንደዚሁም ይቅርታ የምንጠይቀው ስለምናውቃቸው (ስለምናስተውላቸው) ኀጢአቶቻችን ብቻ ሳይኾን ስለ ማናስተውላቸውም መኾን አለበት፡፡ ስለዚህ «ይቅር ብለን» ስንል እኛ ካስተዋልናቸው መንገዶች ውጪ በብዙ መልኩ እርሱን እንደምንበድል አስበን ይቅርታ መጠየቅ አለብን፡፡ ስለዚህ ለጸሎት ከመቆማችንና ከመጸለያችን በፊት የበደሉንን ይቅር እንዳልን እርግጠኛ መኾን ይኖርብናል ማለት ነው፤ ‹‹እኛ የበደሉንን ይቅር እንዳልን …›› ልንል ነውና፡፡ «በደላችንን ይቅር በለን» ስንልም ከላይ ያየናቸውን ነገሮች ዅሉ እያሰብን፤ ይቅር ሊለን የወደደ አምላካችንንም እያመሰገንን መኾን አለበት፡፡

በእውነት ይህንን ጸሎት የምንጸልየው በዚህ መልኩ ነውን? ካልኾነ ልምምዱን ዛሬውኑ እንጀምረው፡፡ ይህንን ማድረግ እንችል ዘንደ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ንስሐን በአስተርጓሚ

ጥቅምት ፳፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

dscn0116

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

በማኅበረ ቅዱሳን የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር ጥቅምት ፳ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በማኅበሩ ሕንጻ ፮ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያካሒድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ተገኝተው ቃለ ምዕዳን ሲሰጡ በጠረፋማ አካባቢዎች የሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በቋንቋቸው የሚያስተምሯቸውና ንስሐ የሚሰጧቸው ሰባክያነ ወንጌልና ካህናት በብዛት እንደሚያስፈልጓቸው ገለጹ፡፡

‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ዕድለኞች ነን፤ እንደ ሰባቱ ኅብረ ቀለማት መልካችን ዝጕርጕር ነው›› ያሉት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔረሰብና ቋንቋ መገኛ መኾኗን አድንቀው በኢትዮጵያ ጠረፋማ አካባቢዎች የሚገኙ አብዛኞቹ ምእመናን ከአባቶች ካህናት ጋር በቋንቋቸው መግባባት ባለመቻላቸው ንስሐ የሚቀበሉት በአስተርጓሚ በመኾኑ ምእመናኑ ኀጢአታቸውን ሰው እንዳይሰማባቸው ሲሉ ለአስተርጓሚዎች በአግባቡ ላይናገሩ እንደሚችሉ፣ ይህም ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት መስፋፋት መሰናክል እንደሚኾን በአንዳንድ የሀገረ ስብከታቸው አካባቢዎች የሚታዩ ችግሮችን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ አስገንዝበዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ቀደም ሲል እንደ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ያሉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በየጠረፋማ አካባቢዎች በእግራቸው እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክ ያጠመቋቸው ብዙ ሺሕ ምእመናን ቢኖሩም ነገር ግን በቋንቋቸው ወንጌልን የሚሰብኩላቸውና ንስሐ የሚሰጧቸው መምህራንና ካህናት ባለመገኘታቸው የተነሣ ወደ ሌላ እምነት እየተወሰዱ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹በጠረፋማው የአገራችን ክፍል የሚኖሩ ወገኖች የሚጠይቃቸው አጥተዋልና ልንደርስላቸው ይገባል›› የሚሉት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ማሠልጠኛ ተቋማትንና የአብነት ትምህርት ቤቶችን በየቦታው በማስፋፋት በልዩ ልዩ ቋንቋ ማስተማር የሚችሉ ሰባክያነ ወንጌልንና ካህናትን ማሠልጠን ለዚህ ዅሉ ችግር መፍትሔ እንደሚኾን ጠቁመዋል፡፡

new

የጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል

በዕለቱ ‹‹ዘፀአት›› በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል የሰጡት ዲያቆን ብርሃኑ አድማስም የእስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ የመውጣት ታሪክ መነሻ አድርገው እያንዳንዱ ምእመን በፈቃዱ ከተያዘበት የሕሊና  ባርነት ነጻ በመውጣት ራሱን ከጥፋትና ከኑፋቄ ከመጠበቅ ባሻገር ሌሎችንም ወደ ክርስትና ሃይማኖት በመመለስ ክርስቲያናዊ ግዴታውን መወጣት እንደሚኖርበት አስተምረዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ አቶ ታምሩ ለጋ በበኩላቸው ማኅበሩ ከአሁን በፊት አዳዲስ አማንያንን በማስጠመቅ፣ አብያተ ክርስቲያናትን በማስገንባትና ሰበክያነ ወንጌልን በማሠልጠን በጠረፋማ አካባቢዎች ላከናወናቸው ተግባራት ዅሉ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ የሚገኙ አባቶች በጸሎትና በምክር፤ በጎ አድራጊ ምእመናን በዐሳብ፣ በቍሳቍስ አቅርቦት፣ በገንዘብና በጕልበት ላደረጉት ዕገዛና ድጋፍ ምስጋናቸውን በእግዚአብሔር ስም ካቀረቡ በኋላ ማኅበሩ ለወደፊቱ በሰፊው ዐቅዶ ለሚተገብረው የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብርም ምእመናን ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ጥቅምት ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ባዘጋጀው ልዩ መርሐ ግብር ገዳማትንና የአብነት ትምህርት ቤቶችን መደገፍ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለመርዳት ስለሚያስችል ዅሉም ሕዝበ ክርስቲያን የበኩሉን ድርሻ ቢወጣ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስቀጠልና የመናፍቃንን ተጽዕኖ መግታት እንደሚቻል ተገልጿል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ‹‹የነገራችሁኝ ሽማግሌ አባታችሁ ደኅና ነውን?›› /ዘፍ.፵፫፥፳፯/ በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል የሰጡት ዲያቆን ሄኖክ ኀይሌ የቅዱሳን አባቶችን ሕይወታቸውንና የትሩፋት ሥራቸውን በማስረዳት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ቅዱሳት መካናትንና አብነት ትምህርት ቤቶችን መከባከብና መጠበቅ ተገቢ ተግባር መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡