ቅድስት ድንግል ማርያም እና ታቦተ ጽዮን – የመጀመሪያ ክፍል

ኅዳር ፳ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዲያቆን ሽመልስ መርጊያ

new

በየዓመቱ ኅዳር ፳፩ ቀን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙ ታላላቅ ተአምራት የሚታሰቡበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የታቦተ ጽዮንን ተአምራት እግዚአብሔር ቃል ቅድስት ድንግል ማርያምን ታቦቱ አድርጎ ከፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጋር በማነጻጸር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ድርሻ በስፋት ታስተምራለች፡፡ ለምሳሌ እስራኤላውያን ባሕረ ዮርዳኖስን በአቋረጡበት ወቅት ታቦተ ጽዮንን የተሸከሙ ካህናት እግራቸው የዮርዳኖስን ባሕር በመንካቱ ባሕሩ ለሁለት ተከፍሎ ነበር፡፡ ይህንን ታሪክም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድና ጥምቀትን በመመሥረት ከሰይጣን ባርነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት እንዳሸጋገረን በማመሥጠር ቤተ ክርስቲያናችን ታስተምርበታለች፡፡ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤላውያን ጋር ውጊያ በገጠሙበት ወቅት ታቦተ ጽዮንን ከእስራኤላውያን ማርከው ዳጎን በሚባለው ቤተ ጣዖታቸው ውስጥ አኑረዋት በነበረ ጊዜ ታቦቷ የዳጎንን ምስል አንኮታኩታ ጥላው ነበር፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ታሪክ እንደ ምሳሌ በመጠቀም ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ከአምልኮ ጣዖት ወጥተን አንድ አምላክን ወደ ማምለክ ስለ መመለሳችንና በእመቤታችን ምክንያት ስለ ተደረገልን የእግዚአብሔር ቸርነት ትምህርት ትሰጥበታለች፡፡ እኛም በዛሬው ዘግጅታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማናዊቷ ታቦተ ጽዮን መኾኗን የሚያስቃኝ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፤

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ካወጣቸው በኋላ የአምልኮ ሥርዐታትን ይፈጽሙበት ዘንድ የምስክሩን ድንኳን፣ የቃል ኪዳኗ ታቦትንና ለአምልኮ ሥርዐቱ ማከናወኛ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትን እንዲሠሩ አዝዟቸው ነበር፡፡ ከቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥም በእግዚአብሔር ጣት ዐሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉበት የሕጉ ጽላት፤ ዐርባ ዓመት ሙሉ እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ የተመገቡትን መና የያዘች መሶበ ወርቅ፤ አሮን ለክህነት አገልግሎት ስለ መመረጡ ምስክር የኾነችው፣ ለምልማና ፍሬ አፍርታ የተገኘችው የአሮን በትር ይገኙባታል /ዕብ.፱፥፬/፡፡ ደብተራ ድንኳኗንና በውስጧ የሚገኙ ንዋየተ ቅድሳትን እግዚአብሔር በሙሴ ሲያሠራ ለሰማያዊው ምሥጢር ምሳሌና ጥላ ናቸውና ተጠንቅቆ እንዲሠራቸው አዝዞት ነበር /ዕብ.፰፥፭/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህችን ድንኳን ‹‹የአገልግሎት ሥርዐታት የሚፈጸምባት ፊተኛይቱ ድንኳን›› ብሎ ይጠራታል፡፡ በዚህ መሠረት ደብተራ ድንኳኗና በውስጧ ያሉ ንዋያተ ቅድሳት ለሰማያዊው ምሥጢር ምሳሌና ጥላ እንደ ኾኑ እንረዳለን፡፡ የደብተራ ድንኳኗ ምሳሌ የኾችው ሰማያዊቱ ስፍራም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በውስጧ አማናዊውና ሰማያዊው ምሥጢረ መለኮት ይፈጸምባታልና፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ ስለ ኾነች፤ ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያሰጥ ምሥጢርም በውስጧ ስለሚከናወንባት በእርግጥም ሰማያዊ ስፍራ ናት፡፡

ታቦተ ጽዮን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች፡፡ ይህን ለመረዳት ግን ስለ ታቦተ ጽዮን አሠራርና መንፈሳዊ ትርጉም አስቀድመን ልንረዳ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ታቦተ ጽዮንን እንዲሠራ ብልሃትን፣ ጥበብን፣ ማስተዋልን፣ ዕውቀትን ይለይ ዘንድ መንፈሱን ያሳደረበትን ከይሁዳ ወገን የኾነውን ባስልኤልን መረጠ /ዘፀ.፳፭፥፱/፡፡ እርሱም እግዚአብሔር በሰጠው ማስተዋል ከማይነቅዝ እንጨት ርዝመቷ ሁለት ክንድ ተኩል፤ ወርዱዋ አንድ ክንድ ተኩል፤ ቁመቷ አንድ ክንድ ተኩል እንዲኖራት አድርጎ ታቦቷን ሠራት፡፡ በመቀጠል በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ ለበጣት፣ ከታቦቷም ዙሪያ የወርቅ አክሊልን አደረገላት፡፡ ካህናት ታቦተ ጽዮንን ለመሸከም እንዲረዳቸውም በአራቱም መዓዘናት በወርቅ የተሠሩ ቀለበቶችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገቡ ሁለት መሎጊያዎችን ሠራ፡፡ ከጥሩ ወርቅም የስርየት መክደኛውን በቃል ኪዳን ታቦቷ ላይ በርዝመቷና በወርደዋ ልክ ሠራ፡፡ የስርየት መክደኛውን እንዲጋርዱት አድርጎም ጥሩ ከኾነ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ኪሩቤልን ሥሎ በስርየት መክደኛው ግራና ቀኝ አስቀመጣቸው፡፡ እነዚህ በጥሩ ወርቅ የተሠሩት ሁለቱ ኪሩቤል ፊታቸው ወደ ስርየት መክደኛው ኾኖ እርስ በእርሳቸው እንዲተያዩ ተደርገው የተሠሩ ናቸው፡፡ በዚህ በስርየት መክደኛው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል እግዚአብሔር ለሙሴ እየተገለጠ ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር በግልጽ ያነጋግረው ነበር፤ ለሕዝቡም በደመና ዐምድ ይታያቸው ነበር /ዘፀ.፰፥፲፩፤ ፳፭፥፳፪-፴፫/፡፡

ወደ ምሥጢሩ ትርጓሜ ስንመለስም ታቦተ ጽዮን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ስትኾን፣ በውስጧ የያዘችው የሕጉ ጽላትም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቷ ከማይነቅዝ እንጨት መሠራቷ የእመቤታችንን ንጽሕና የሚያመለክት ሲኾን፣ በውጪም በውስጥም በጥሩ ወርቅ መለበጧ ደግሞ ቅድስናዋንና በሁለት ወገን ድንግል መኾኗን የሚያስረዳ ነው፡፡ ታቦተ ጽዮን በግራና በቀኝ በኩል በተዘጋጁ አራት ከወርቅ የተሠሩ ቀለበቶች ነበሯት፤ በእነዚያ የወርቅ ቀለበቶች ውስጥም ሁለት መሎጊያዎች ይገቡባቸው ነበር፡፡ ታቦቷን ለማንቀሳቀስ ባስፈለገ ጊዜ አራት ሌዋውያን ካህናት በመሎጊያዎቹ ይሸከሟታል፡፡ ይህ ሥርዐት በሰማያትም የሚታይ እውነታ ነው፡፡ የጌታን መንበር ገጸ ሰብእ፣ ገጸ ንሥር፣ ገጸ ላህምና ገጸ አንበሳ ያላቸው አርባዕቱ እንስሳት ይሸከሙታልና /ኢሳ.፮፥፩-፭፤ ሕዝ.፩፥፩-፲፮/፡፡ ለአማናዊቷ ታቦት ለቅድስት ድንግል ማርያምም ሰላምን የሚያወሩ፣ መልካም የምሥራችንም የሚናገሩ፣ መድኀኒትንም የሚያወሩ፣ ጽዮንንም ‹‹አምላክሽ ነግሦአል›› የሚሉ፣ እግሮቻቸው በተራሮች ላይ እጅግ ያማሩ የእርሷንና የጌታችንን ስም ተሸክመው ወንጌልን ለዓለም የሚሰብኩ ኦርቶዶክሳውያን መምህራን አሏት /ኢሳ.፶፪፥፯/፡፡ የስርየት መክደኛው መቀመጫው የንጹሐን አንስት፣ መክደኛው የንጹሐን አበው፣ ግራና ቀኙ የሐናና የኢያቄም ምሳሌ ነው፡፡ በክንፎቻቸው የጋረዱት  ኪሩቤልም የጠባቂው መልአክ ቅዱስ ሚካኤልና የአብሣሪው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ምሳሌዎች ናቸው፡፡

የስርየት መክደኛው ስርየቱ የሚፈጸምበት ስፍራ ቢኾንም ነገር ግን በዚህ ቦታ ምንም ዓይነት መሥዋዕት አይቀርብም ነበር፡፡ ይህም በጊዜው አማናዊው መሥዋዕት ገና እንዳልተሠዋ ያስገነዝበናል፡፡ ይህ ስፍራ እግዚአብሔር ለሙሴ የሚገለጥበት ቦታ ነው፤ ከእርሱ ውጪ ሌላ ነገር በእዚያ ላይ ማረፍ አይችልም ነበር፡፡ ከዚህም የምናስተውለው አንድ ምሥጢር አለ፤ ይኸውም እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን ሊፈጽም ሰው በኾነ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብበት ልዩ ስፍራ እንዳዘጋጀ ያመላክተናል፡፡ ይህ ስፍራ አማናዊ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ እንደሚያስፈልግ የሚያስገነዝብ ስፍራ ነው፡፡ ይህን ለማመልከትም ለኃጢአት ስርየት የቀረበው መሥዋዕት ከታረደ በኋላ ካህኑ ደሙን በጣቱ እየነከረ ሰባት ጊዜ በስርየት መክደኛው አንጻር በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ይረጨው ነበር /ዘሌ.፬፥፮/፡፡ ነገር ግን ይህ ደም ከስርየት መክደኛው ላይ አያርፍም ነበር፤ ምክንያቱም በዚህ ስፍራ መቅረብ የሚገባው አማናዊው መሥዋዕት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነውና፡፡

ይህ የስርየት መክደኛ ለእኛ የሚያስተላለፈው ተጨማሪ መልእክትም አለው፡፡ ይኸውም አማናዊው መሥዋዕት ክርስቶስ መሥዋዕት ኾኖ ዓለምን ማዳኑ እንደማይቀርና መሥዋዕቱ የሚቀርብበት ስፍራም በቅድስተ ቅዱሳኑ (ቤተ መቅደሱ) ውስጥ እግዚአብሔር በምሕረት በሚገለጥበት በቃሉ ማደሪያ በጽላቱ ላይ መኾን እንደሚገባው ያስገነዝበናል /ዕብ.፬፥፲፮/፡፡ ይህም እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ሚልክያስ ላይ አድሮ ‹‹ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይኾናልና በየስፍራውም ስለ ስሜ ዕጣንን ያጥናሉ፤ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፤›› /ሚል.፩፥፲፩/ በማለት እንደ ተናገረው የስርየት መክደኛው አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ቍርባንን ለምትፈጽምበት ጽላት ወይም ታቦት ምሳሌ መኾኑን ያሳየናል፡፡ የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱት በጥሩ ወርቅ የተሠሩት የኪሩቤል ምስሎችም አማናዊው መሥዋዕት በሚሠዋበት ጊዜ በዙሪያው ረበው የሚገኙ የመላእክት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችን እንዳስተማሩን ሁለቱ ኪሩቤል የተባሉት ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ናቸው፡፡ ይህን ለማስገንዘብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በመንበረ ታቦቱ ላይ ምስለ ፍቁር ወልዳ እንዲቀመጥ ታዝዛለች፡፡ ምስለ ፍቁር ወልዳን  ላስተዋለ ሰው በትክክል የታቦተ ጽዮንን መንፈሳዊ ትርጕም ይረዳል፡፡

ታቦተ ጽዮን ከሌሎች የብሉይ ኪዳን ንዋያተ ቅድሳት በተለየ መልኩ እጅግ ግሩም የኾነ ምሥጢርን በውስጧ ይዛለች፡፡ ይህን ድንቅ ምሥጢር ለመረዳትም አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑ ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ጽዮን ከተማ ባስመጣበት ወቅት በታቦቷ ፊት በሙሉ ኃይሉ በደስታ እየዘለለ ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ መዝሙርን አቅርቦ ነበር /፪ሳሙ.፮፥፲፪-፲፯/፡፡ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሚኾን ድርጊት በሐዲስ ኪዳንም ተፈጽሟል፡፡ ይኸውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅድስት ኤልሳቤጥ ሰላታ በሰጠቻት ጊዜ የስድስት ወር ፅንስ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የእመቤታችንን የሰላምታ ድምፅ በሰማ ጊዜ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ኾኖ በደስታ ዘሏል (ሰግዷል) /ሉቃ.፩፥፵፬/፡፡ ቅዱስ ዳዊት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት እየተደሰተ ለአምላኩ የምስጋና ቅኔን መቀኘቱም ለሰው ልጆች ዅሉ የመዳናችን ምክንያት የኾነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን በቃል ኪዳኗ ታቦት በኩል አስቀድሞ በዓይነ ሕሊና ስለ ተመለከታቸው ነበር፡፡

ይቆየን፡፡