ዘመነ አስተምሕሮ

ኅዳር ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በቤተ ክርስቲያናችን የዘመን አከፋፈል መሠረት ከኅዳር ፮ ጀምሮ እስከ ታኀሣሥ ፲፫ ቀን ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምሕሮ ይባላል፡፡ ትርጕሙም ይቅርታ የመጠየቅ (የምልጃ) ዘመን ማለት ነው፡፡ ዘመኑ ቤተ ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት፤ ምእመናንንም ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት፤ ስለዚህም በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ባሉት እሑዶች የሚገኙ ሰንበታት (እሑዶች) አስተምሕሮ፣ ቅድስት፣ ምኵራብ፣ መጻጉዕ እና ደብረ ዘይት በመባል ይጠራሉ፤ የመጀመሪያውን ሳምንት (የአስተምሕሮ) ትምህርትም እነሆ!

እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን /ማቴ.፮፥፲፪/፡፡

ይህ ቃል የተወሰደው ጌታችን በደቀ መዛሙርቱ በኩል እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለሚኖሩ (ዛሬም ላለን) ክርስቲያኖች እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ካስተማረው ጸሎት ነው፤ ‹‹በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፡፡ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ኾነች እንዲሁ በምድር ትኹን፡፡ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፡፡ እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፡፡ ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፡፡ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለም አሜን፤›› /ማቴ.፮፥፱-፲፬/፡፡

ይህ ጸሎት በጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ሊቃውንት «የጌታ ጸሎት» ተብሎ ይጠራል፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን የጸሎቱን የመጀመሪያ ሐረግ በመያዝ «አባታችን ሆይ» ወይም በግእዝ «አቡነ ዘበሰማያት» እንለዋለን፡፡ ይህ ጸሎት ጌታችን ራሱ ያስተማረው በመኾኑ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ የሌሎች ጸሎታት ዅሉ ማሰሪያ (ማሳረጊያ) ኾኖም ያገለግላል፡፡ በውስጡም «አባታችን ሆይ» ከምትለው ከመጀመሪያዋ ሐረግ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ እጅግ ጥልቅ የኾኑና ነፍስን የሚያጠግቡ፣ ወደ ሰማይ ከፍ የሚያደርጉ መንፈሳዊና ነገረ መለኮታዊ መልእክቶችን ያዘለ ነው፡፡ ይህ የዘመነ አስተምሕሮ የመጀመሪያው ሳምንት ስለ ይቅርታ የሚሰበክበት ነውና በጸሎቱ ውስጥ ስለዚህ የሚናገረውን አንቀጽ መሠረት አድርገን እንማራለን፤

«እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን» ከሚለው ኃይለ ቃልም የሚከተሉትን ቁም ነገሮች እንረዳለን፤

፩. እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን እንደሚወድ

አምላካችን ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ባይወድ ኖሮ ይቅርታን እንድንጠይቅ አይነግረንም ነበር፡፡ አዎ፤ እኛ ከተመለስን ምንም ያህል በደለኛ ብንኾን ይቅር ሊለን፤ ምንም ያህል ብንቆሽሸ ሊያድነን ዝግጁ ነው፡፡ እንዲህ እያለ ይጠራናል፤ «እናንተ ሸክማችሁ የከበዳችሁ፤ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ፡፡» ስለዚህ በዚሀ ጸሎትም ላይ «በደላችንን ይቅር በለን» ብለን እንድንጠይቀው አስተማረን፤ ይቅር ይለን ዘንድ፡፡

፪. ይቅር ለመባል ምን ማድረግ እንዳለብን

እግዚአብሔር ይቅር ሊለን ስለ ወደደም ይቅርታን ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን በዚሁ ቃል ነግሮናል፤ ማድረግ ያለብን ምንድን ነው?

ኀጢአታችንን ማወቅ (ማመን)

ጌታ «በደላችንን ይቅር በለን» ብለን እንድንጸልይ ሲነግረን በመጀመሪያ ደረጃ በደለኛ እንደኾንን እያስታወስን (እንድናስታውስ እያደረገን) ነው፡፡ ዅልጊዜም በማሰብ፣ በመናገርና በማድረግ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የኾነውን ልባችንን (ኅሊናችንን) እና ሰውነታችንን እናቆሽሻለን፤ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የሞተለትን ማንነታችንን እናጎድፋለን፡፡ ይህም የሰው ልጆች በቅድስና እርሱን መስለን እንድንኖር በኋላም የተዘጋጀልንን የዘለዓለም መንግሥት እንድወርስ ብቻ ፈቃዱ የኾነውን እግዚአብሔርን ያሳዝናል፤ በአርአያውና በአምሳሉ ለክብር የፈጠረው ሰውነታችን መጉደፉ ያስቆጣዋል፤ ንጹሐ ባሕርይ የኾነ እርሱ ኀጢአት አይስማማውምና፡፡

እንግዲህ ይቅር ለመባል በመጀመሪያ እንዲህ ኀጢአት እየሠራን መሆኑን ማወቅና ማመን ያስፈልገናል፡፡ ወደዚህ ዕውቀት ለመድረስም የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል መማር የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ስሕተት የሚታወቀው ያለውን ኹኔታ (ድርጊታችንን ንግግራችንን፣ ሐሳባችንን…) መኾን ከነበረበት (ከትክክለኛው) ጋር በማነጻጸር በሚዛን ላይ በማስቀመጥ ነው፡፡ የማነጻጻሪያ ሚዛኖቻችን ደግሞ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉ ሕግጋትና ትእዛዛት ናቸው፡፡ እነዚህን ስናውቅ ጕድለቶቻችንና ድካሞቻችን ፍንተው ብለው ይታዩናል፡፡ ካለዚያ ግን እየበደለን ያልበደልን ሊመስለን ይችላል፡፡

የበደሉንን ይቅር ማለት

ጌታችን በዚህ ጸሎት ይቅርታ እንድንጠይቀው በማስተማር ይቅር ሊለን እንደሚወድ ቢነግረንም ይቅር ለመባል ግን እኛ የበደሉንን ይቅር ማለታችን የግድ እንደኾነ በግልጽ አስቀምጦልናል፤ «በደላችንን ይቅር በለን» ከማለታችን በፊት «እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል» እንድንል ያዘዘን እኛ ይቅርታ የምናገኘው ሌሎችን ይቅር ስንል ብቻ መኾኑን ለማመልከት ነው፡፡ በዚሁ በተራራው ስብከት ይኸው ጉዳይ ሁለት ጊዜ በጌታችን ትምህርት ተሰጥቶበታል፡፡ «እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል፤» /ማቴ.፯፥፪/፡፡

በሌላ ቦታም እንዲህ ሲል ይህንኑ ጉዳይ በምሳሌ አስተምሯል፤

 ‹‹መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ለመቈጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች፤ መቈጣጠርም በጀመረ ጊዜ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፡፡ ባለ እዳው ሰው የሚከፍለው ስላጣ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ንጉሡ አዘዘ፡፡ በዚህም ጊዜ ባርያው ወድቆ ሰገደለትና ጌታ ሆይ ታገሰኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው፡፡ የዚያም ባርያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፡፡ ይህ ባርያ ግን ወጥቶ ከባልጀሮቹ /እንደርሱ ባርያ ከኾኑት/ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው፡፡ ባልንጀራው ባርያም ወድቆ ታገሰኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፤ ብሎ ለመነው፡፡ እርሱ ግን ሊተወው አልወደደም፡፡ ዕዳውን እስኪከፍልም በወኅኒ አኖረው፡፡ ይህንን ያዩ ሰዎችም አዘኑ፤ ሄደውም የኾነውን ለንጉሡ ተናገሩ፡፡ ከዚህ ወዲያ ንጉሡ ጠርቶ፣ አንተ ክፉ ባርያ ስለ ለመንከኝ ያን ዕዳ ዅሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህን የኾነውን ባርያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን አለው፡፡ ጌታውም ተቈጣና ዕዳውን እስኪከፍለው ድረስ ለሚያሰቃዩት አሳልፎ ሰጠው፤» /ማቴ.፲፰፥፳፫-፴፭/፡፡

ጌታ ይህንን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ የምሳሌውን ትርጕም እንዲህ ሲል ገልጦታል፤ «ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል፡፡›› በአጠቃላይ ይቅር ለመባል ይቅር ማለት የግድ ነው፡፡ በእኛ ላይ የሚፈረድብን ፍርድ በእኛው እጅ ላይ ነው፡፡ ጌታችን በእነዚህ ትምህርቶች እንዲህ እያለን ነው «እኔ እናንተ ላይ የምፈርደው እናንተ በራሳችሁ ላይ በፈረዳችሁበት መንገድ ነው፡፡»

ይቅርታ መጠየቅ

ኀጢአታችንን ካወቅንና ካመንን፣ የበደሉንንም ከልብ ይቅር ካልን በኋላ ይቅር እንድንባል መጠየቅ (መለመን) አለብን ፡፡ ጌታችን «ይቅር በለን ብላችሁ ጸልዩ›› ብሎ ከማስተማሩም ይህንን እንረዳለን፡፡ ወደ ንስሐ አባት መሔድና ኀጢአትን ተናዞ ቀኖና መቀበል የሚገባው መጀመሪያ በዚህ መልኩ ስለ ኀጢአት ካለቀሱ በኋላ ነው፡፡ ከዚያም ቀኖና ተቀብለን ስንፈጽምም ይኸው ስለ ኀጢአት ይቅርታ መጠየቁ ይቀጥላል፡፡ ይቅርታ የምንጠይቀው አዳዲስ ስለ ሠራናቸውና ንስሐ ገና ስላልገባንባቸው ኀጢአቶቻችን ብቻ ሳይኾን ንስሐ ስለ ገባንባቸው ስለ ቀደሙት በደሎቻችንም ጭምር ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ዳዊት «የቀደመ በደላችንን አታስብብን፤ ምሕረትህ በቶሎ ታግኘን፤» /መዝ.፸፰፥፰/ እያልን ሰለ ቀደመው በደላችንም እያሰብን በሕይወታችን ዘመን ዅሉ ይቅርታ መጠየቅ አለብን፡፡

እንደዚሁም ይቅርታ የምንጠይቀው ስለምናውቃቸው (ስለምናስተውላቸው) ኀጢአቶቻችን ብቻ ሳይኾን ስለ ማናስተውላቸውም መኾን አለበት፡፡ ስለዚህ «ይቅር ብለን» ስንል እኛ ካስተዋልናቸው መንገዶች ውጪ በብዙ መልኩ እርሱን እንደምንበድል አስበን ይቅርታ መጠየቅ አለብን፡፡ ስለዚህ ለጸሎት ከመቆማችንና ከመጸለያችን በፊት የበደሉንን ይቅር እንዳልን እርግጠኛ መኾን ይኖርብናል ማለት ነው፤ ‹‹እኛ የበደሉንን ይቅር እንዳልን …›› ልንል ነውና፡፡ «በደላችንን ይቅር በለን» ስንልም ከላይ ያየናቸውን ነገሮች ዅሉ እያሰብን፤ ይቅር ሊለን የወደደ አምላካችንንም እያመሰገንን መኾን አለበት፡፡

በእውነት ይህንን ጸሎት የምንጸልየው በዚህ መልኩ ነውን? ካልኾነ ልምምዱን ዛሬውኑ እንጀምረው፡፡ ይህንን ማድረግ እንችል ዘንደ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር