ማኅበረ ቅዱሳን በትግራይ ሦስት ገዳማት የተገበራቸውን ፕሮጀክቶች አስመረቀ
•ለፕሮጅክቶቹ ማስፈጸሚያ ከ3 ሚሊዮን 180 ሺሕ ብር በላይ ወጪ ሆኗል፡፡
ኅዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት አማካይነት በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም፤ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት በአስገደ ጽምባላ ወረዳ በአቡነ ቶማስ ደብረ ማርያም ዘሃይዳ፤ በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በማቅናት አጽቢ ወምበርታ ወረዳ በደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳማት ያከናወናቸውን ፕሮጀክቶች አስመረቀ፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ተጀምረው የነበሩት እነዚህ ፕሮጅክቶች ከኅዳር 3/2007 ዓ.ም. – ኅዳር 8/2007 ዓ.ም. ደማቅ በሆነ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ፕሮጀክቶችን አስመርቆ ለየገዳማቱ አስረክቧል፡፡ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት በአስገደ ፅብላ ወረዳ ኅዳር 3 ቀን 2007 ዓ.ም የተመረቀው የአቡነ ቶማስ ደብረ ማርያም ዘሃይዳ አንድነት ገዳም በ630 ሺሕ ብር የተሠራ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ሲሆን፤ 150 ሺሕ ሊትር መያዝ ይችላል፡፡ ይህ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በገዳሙ ውስጥ ተገንብቶ በመጠናቀቁ ማኅበረ መነኮሳቱ የመጠጥ ውኃ ፍለጋ በቀን ከ4-5 ሰዓት በመጓዝ የሚባክንባቸውን የአገልግሎትና የጸሎት ጊዜያቸውን እንደሚያስቀርላቸው የገዳሙ አባቶች ተናግረዋል፡፡
ገዳሙ ያለበትን ችግር በማጥናት የውኃ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ሲሆን፤ መንገዱ በጣም አስቸጋሪና ከ3-4 ሰዓት በእግር የሚያስኬድ በመሆኑ አባቶች በሸክም፤ እንዲሁም ግመሎችን በመጠቀም የግንባታ ቁሳቁስ በማመላለስ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተችሏል፡፡
ገዳሙ ጥንታዊና ገዳማዊ ቀኖና እና ሥርዓት ተጠብቆ የሚገኝበት ሲሆን፤ በርካታ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን በማፍራትም ይታወቃል፡፡
በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት ከተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ደግሞ ለደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም የተገነባው ሁለገብ ሕንፃ ነው፡፡ ሁለገብ ሕንፃው በአዲግራት ከተማ የተገነባ ሲሆን፤ ለተለያየ አገልግሎት በማከራየት ገቢ ማስገኘት የሚችል ነው፡፡ ሕንፃው በብር 2,326,717.87 /ሁለት ሚሊዮን ሦስት መቶ ሃያ ስድስት ሺሕ ሰባት መቶ ዐሥራ ሰባት ብር ከ87 ሣንቲም/ ተገንብቶ የርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ተከናውኗል፡፡
ሕንፃው በ416.49 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ማኅበሩ የሠራው የምድሩን ወለል ብቻ ነው፡፡ መሠረቱ ባለ ሁለት ወለል ሕንፃን መሸከም እንዲችል ተደርጎ የተሠራ በመሆኑ ቀሪውን የግንባታ ሥራ ገዳሙ ባቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት ይገነባል፡፡
ጉንዳጉንዲ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ቀድሞ በርካታ መነኮሳት የነበሩባት ቢሆንም በደርግ መንግሥት የነበራት ሰፊ ይዞታ በመነጠቋ የመነኮሳቱ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በችግር ምክንያት እየተመናመነ ሄዶ ሁለት መነኮሳት ብቻ ቀርተው ነበር፡፡ እነሱም በገዳሟ ውስጥ የሚገኙትን ንዋያተ ቅድሳትና በሌሎች ገዳማት የማይገኙ ቅዱሳት የብራና መጻሕፍትን ለማን ጥለን እንሔዳለን በማለት ችግሩን ተቋቁመው ዛሬ ድረስ ለመዝለቅ ችለዋል፡፡
ወደ ገዳሟ ለመድረስ መንገዱ አስቸጋሪና መኪና የማይገባ በመሆኑ የአንድ ቀን ሙሉ የእግር መንገድ መጓዝ ግድ ይላል፡፡ ለመመለስም እንዲሁ የአንድ ቀን የእግር ጉዞ ማድረግ ይጠበቃል፡፡
ገዳሟ ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላት ሲሆን፤ የሁለገብ ሕንፃው መገንባት ችግሩን እንደሚቀርፍ ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የመነኮሳቱ ቁጥር ከሁለት ወደ ሰባት ከፍ ለማለት ችሏል፡፡
በተጨማሪም በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በማቅናት አጽቢ ወምበርታ ወረዳ በደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ማኅበሩ በብር 225,343.65 /ሁለት መቶ ሃያ አምስት ሺህ ሦስት መቶ አርባ ሦስት ብር ከ65 ሣንቲም/ ተግባራዊ ያደረገውን የሽመና ውጤቶችን መሥሪያ አዳራሽ ሠርቶ በማጠናቀቅ፤ የሽመና ቁሳቁስ በማሟላት፤ እንዲሁም የልብስ ሥፌት መኪናዎችን ገዝቶ በማቅረብ ርክክብ ተደርጓል፡፡
የሽመና ፕሮጀክቱ ታሳቢ ያደረገው በገዳሟ ውስጥ ለሚገኙት መነኮሳይያት ሲሆን፤ መነኮሳይያቱ ቁጥራቸው ከፍ ያለ በመሆኑ የሽመና ውጤቶችን ማምረት ያስችላቸዋል፡፡
ደብረ ቅዱሳን ዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም ጥንታዊ ከሚባሉ ገዳማት መካከል የምትመደብ ስትሆን በውስጧም ጥንታዊ ሥዕላትን ጠብቃ ለትውልድ በማቆየት ትታወቃለች፡፡ ለትኅርምት እና ለጽሞና የምትመረጥም ገዳም ናት፡፡
ማኅበሩ በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍሉ አማካይነት ለበርካታ ገዳማትና አድባራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና በመተግበር ገዳማት የልማት ሥራዎችን በመሥራት ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ ሲሆን፤ ሌሎች በጅምር ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሠራ ይገኛል፡፡



የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመተባበር ከ2004- 2007 ዓ.ም. 16,630 አዳዲስ አማንያንን በማስተማር መጠመቃቸውን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡
የጂንካ ደብረ ቀራንዮ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጀማል ዑመር /ዐምደ ሚካኤል/ ባቀረቡት ሪፖርት የቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ሥራ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ እገዛ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ የቤተ ክርስቲያኑን ዲዛይን በተመለከተም ሲገልጹ “የወንጌል አርበኞች የሆኑት የማኅበረ ቅዱሳን ጂንካ ማእከል አባላት የቤተ ክርስቲያኑን ዲዛይን በነጻ በመሥራት እገዛ አድርገዋል” ብለዋል፡፡
በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በደምቢያ ወረዳ በጣና ሐይቅ ውስጥ በ1335 ዓ.ም. ተገድማ የነበረችው የጀበራ ማርያም አንድነት ገዳም ከፈረሰች ከበርካታ ዘመናት በኋላ ዳግም ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገዳሙን መልሶ ለማቋቋም በማስተባበር ላይ የሚገኙት አባ ዘወንጌል ገለጹ፡፡
በስድስት ወራት ውስጥ የተጀመረው ግንባታም በመፋጠን ላይ ሲሆን፤ ሠርቶ ለማጠናቀቅም በርካታ ሥራዎች ይቀራሉ፡፡ የጣሪያ ቆርቆሮ፤ የበር፤ የመስኮት፤ የቤተ መቅደስ፤ የማጠናቀቂያ ሥራዎችና ሌሎችም ስለሚቀሩት በባለሙያዎች ተጠንቶ 1.2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያስፈልገውና ይህንን ለማሟላት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው በችግር ውስጥ እንደሚገኝ አባ ዘወንጌል ገልጸዋል፡፡ በጎ አድራጊ ምእመናንም ገዳሟ ያለችበትን ሁኔታ በመረዳት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡


ከአጸደ ሥጋ ዓለም በሞት ተለይተው በአጸደ ነፍስ የሚገኙ ቅዱሳን ፓትርያኮችና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት ተደረገላቸው፡፡ ሥርዓተ ጸሎተ ፍትሐቱ በተለይ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳትን እንዲሁም ቤተክርስቲያንን አገልግለው ያለፉ አበው የታሰቡበትና በረከታቸው በአጸደ ሥጋ ላለነው እንዲደርስ ጸሎት የተደረገበት ነው፡፡
ቅዱስነታቸው አያይዘውም “እናትና አባትህን አክብር የሚለውን የጌታን ትእዛዝ ለመፈጸም በዚህ ቦታ ተገኝተናል በመንፈስ ወልደውና በምግባር አሳድገው ለዚህ ስላበቁን እነሱን ማክበርና ማስታወስ ግዴታችን ነው፡፡ ስለሆነም ይህ መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ እንዲከበር በቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑ የሚመሰገን ነው፡፡” በማለት ቀደምት የቤተክርስቲያን አበውን መዘከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በዚሁ እለት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የመታሰቢያ ሐውልት ተመርቋል፡፡ የመታሰቢያ ሐውልቱ የተሠራው በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያና ትዕዛዝ ሲሆን፤ ወጭውን ደግሞ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መሸፈኑን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጁና የወላይታ ኮንታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ አስታውቀዋል፡፡ 
የ33ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ማጠቃለያ መርሐ ግብር የተጀመረው ከረፋዱ 2፡46 ነበር፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርክ አቡነ ማትያስ ጉባኤውን በጸሎት ከከፈቱ በኋላ ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገብርኤል “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕስ ከምንጊዜውም በላይ የቤተ ክርስቲያንን
በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለሦስት ቀናት በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ውይይት እንዲደረግ ጋብዘዋል፡፡ ሆኖም ግን ቅዱስ ፓትርያርኩ በጉባኤው መክፈቻ ዕለት ማኅበረ ቅዱሳንን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ላይ ብቻ ሰፊና ጠንካራ ውይይቶች ተደርጓል፡፡
በመጨረሻም በበጀት ዓመቱ በልማት፣ ዓመታዊ ገቢ
ሪፖርት አቅራቢ ሥራ አስኪያጆችና የሰሜን አሜሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በ2006 ዓ.ም የሥራ ዘመን ክንውን ሪፖርታቸውን የጉባኤው ታዳሚዎች ሲያቀርቡ የሪፖርቱ ይዘት ጉባኤውን በሐሴት እንዲሞላ፣ አንገት እንዲደፋና የዕንባ ዘለላ እንዲወርድ ያደረገ ነበር፡፡
ዓመታዊ ገቢ ማሳደግን በተመለከተ በርካታ ሀገረ ስብከቶች ካለፈው ዓመት ገቢ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ዕድገት ማሳየት መዘገቡ ይበል የሚያሰኝ ሲሆን ለነዚህ አገልግሎቶች ስኬታነት የማኅበረ ቅዱሳን ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበርና በሥልጠና፣ በስብከተ ወንጌል፣ በሕንፃ ዲዛይን በገዳማትና አብነት ትምህርት ቤት ድጋፍ ወዘተ የተደረገው ድጋፍ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን በተለይ በተደረገ ሥልጠና አንዳንድ ሀገረ ስብከቶች የሀገረ ስብከቶች ዓመታዊ ገቢያቸው የሥራ ተነሳሽነታቸው መጨመሩም በሪፖርቱ ተወስቷል፡፡
ጥቅምት 6 ቀን 2007 ዓ.ም እና ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም ትምህርተ ወንጌል በብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ትምህርተ ወንጌል የጉባኤው ታዳሚ ስለ እናት ቤተ ክርስቲያን ይበልጥ እንዲያስብ፣ እንዲሠራ፣ እንዲተጋ ያሳሰበ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስም በተለይ የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ስውር ተልዕኮ ተረድቶ ቤተ ክርስቲያኒቷን እንዲጠብቅ የሚያሳስብ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡