ድንቅ ቀን /ለሕፃናት/

መጋቢት 28/2004 ዓ.ም.

በልያ አበበ


ልጆች የዕረፍት ጊዜያችሁ ወይም የጨዋታ ሰዓት ሲደርስ በጣም ትደሰታላችሁ አይደል? እኔና ዘመዶቼ ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ሰዎችን በማገልገል እነርሱንና ዕቃዎቻቸው ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ ስንለፋ እና ስንደክም የምንኖር ቢሆንም በዓመቱ ውስጥ ግን ልክ እንደሰዎች እጅግ ተደስተንባቸው የምናሳለፋቸው በዓላት አሉ፡፡

 

Hosaena

 

አንደኛው በዓል የሁላችን ፈጣሪ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነው ለዚያ ቀን እርሱ ቤተልሔም በሚገኝ የዘመዶቻችን ቤት /በሰዎች አጠራር በረት/ ውስጥ ሲወለድ አንደኛ በትሕትና በእንስሳት ቤት ለመወለድ በመምረጡ ሁለተኛ እጅግ ብርዳማ በነበረው የልደቱ ዕለት የእኛ ዘመዶች የሰው ልጆች እንኳን ያላደረጉትን በትንፋሻቸው እንዲሞቀው ስላደረጉ በጣም ደስተኞች ነን፡፡

ስሜ ደስተኛዋ አህይት ነው፡፡ አሁን የምነግራችሁ በሕይወቴ እጅግ የተደሰትኩበትና እኔና ዘመዶቼ እስካሁን የምንወደውን ሌላኛውን ቀን ነው፡፡ ቀደም ብዬ የነገርኳችሁን የቤተልሔሙን ልደት የነገረችኝ አንደኛዋ አክስቴ አህያ ናት፡፡ ሁል ጊዜም ያንን ታሪክ እንደ አክስቴ እኔም በቤተልሔም በረት ውስጥ በነበርኩ እል ነበር፡፡

 

ያ ቤተልሔም በሚኖሩ ዘመዶቻችን ቤት የተወለደው የዓለም ሁሉ ፈጣሪ እኛ እንኖርበት በነበረው ሀገር ለ30 ዓመት ከኖረ በኋላ የሀገራችን ሰዎች ሁሉ ማስተማር ጀመረ፡፡

 

እኔና እናቴ የምንኖረው ደብረ ዘይት ቤተ ፋጌ ከሚባለው ቦታ ጥቂት እንደተሔደ በምትገኘው ትንሽ መንደር ነበር፡፡ የእኛ ባለቤት የሆነው ሰው ፈጣሪያችን በትንሽዬዋ የእንስሳት ቤት ሲወለድ የተደረጉትን ነገሮች ማለቴ የእረኞችና የመላእክትን ዝማሬ የሦስቱ ነገሥታት ስጦታን ማምጣት ሰምቶ ስለነበር ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ቦታ ሁሉ እየሔደ ይማር እጅግም ይወደው ነበር፡፡

 

ታዲያ አንድ ቀን ምን ሆነ መሰላችሁ፡፡ እናቴ ባለቤታችን አንድ ሁል ጊዜው ለብርቱ ሥራ ሊፈልገን ስለሚችል ብላ በጠዋት ቀሰቀሰችኝ፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ ሌላ ቀን ስትቀሰቅሰኝ ተኝቼ ማርፈድ የሚያምረኝ ቢሆንም የዚያን ቀን ወዲያውኑ ነበር የተነሣሁት፡፡ ፊቴን ከታጠብኩ እና ሰውነቴ ላይ ያለውን አቧራ ካራገፍኩ በኋላ ከእናቴ ጋር ሆነን ለዛ ቀን ያደረሰንን እና ጣፋጯን የጠዋት ፀሐይ እንድንሞቅ ላደረገው ፈጣሪያችን ጮክ ብለን እየጮህን ምስጋና አቀረብን፡፡

 

አሳዳሪያችን ከበረታችን አውጥቶ የቤቱ በር ላይ ባለ የእንጨት ምሰሶ ላይ አሰረንና ወደ ሌሎች ሥራዎች ተሰማራ፡፡ አሳዳሪያችን እንዲህ የሚያደርገው እርሱ ወደገበያ የማይወጣ እኛንም የሚያሥረን ሥራ ከሌለው ነው፡፡ እኔም እናቴም ቀኑን በሙሉ በማናውቀው ምክንያት ደስ ሲለን ዋለ፡፡

 

የሆነ ሰዓት ላይ ከሩቅ ሁለት ሰዎች ወደ እኛ መንደር ሲመጡ አየናቸው፡፡ ሰዎቹ እየቀረቡ መጡና እኛ ጋር ሲደርሱ አጎንብሰው የታሠርንበትን ገመድ ፈቱልን፡፡ ሰዎቹ ለጌታችን ፈጣሪያችን እንደሚፈልገን ነገሩን፡፡ እኛም በደስታ አብረናቸው ሔድን፡፡

 

ፈጣሪያችን ወደነበረበት ስንደርስ ምን እንደተደረገ ልንገራችሁ? ፈጣሪያችን በእኔ ላይ ልብስ ተነጥፎለት ተቀመጠና ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ ጀመርን፡፡ ምን ያህል እንደተደሰትኩ ልነግራችሁ አልችልም፡፡ በመንገድ የምናገኛቸው ሰዎች በሙሉ ሆሣዕና በአርያም እያሉ እየዘመሩ ልብሶቻቸውና የዘንባባ ዝንጣፊ በምናልፍበት መንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር፡፡ ትንንሽ ሕፃናትም በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እያሉ ዘመሩ፡፡ ትልልቆቹ መምህራን ግን ልጆቹን ተቆጥተው ዝም በሉ አሏአቸው፡፡ ነገር ግን አንድ ተአምራዊ ነገር ተከሰተ፡፡ በመንገድ ላይ የነበሩ ድንጋዮች ሁሉ ልክ እንደ ሰው መዘመርና ፈጣሪያችንን ማመስገን ጀመሩ፡፡

 

ልጆች በዚያን ቀን ፈጣሪዬን በጀርባዬ ተሸክሜ 16 ምዕራፍ ያክል ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ወሰድኩት ታዲያ ይህንን ቀን እኛ አህዮችና ሌሎችም እንስሳት በታላቅ ደስታ እናከብረዋለን፡፡ ሆሣዕና ሕፃናት ፈጣሪያችንን ያመሰገኑበት ቀን ስለሆነ በቤተ ክርስቲያን ተገኝታችሁ አክብሩት እሺ ልጆች፡፡

ከ175 በላይ በገና ደርዳሪዎች ይመርቃሉ፡፡

መጋቢት 26/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደጀኔ

በማኅበረ ቅዱሳን ልማት ተቋማት አስተዳደር የአቡነ ጎርጎርዮስ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል ከ175 በላይ በገና ደርዳሪዎችን መጋቢት 29 ቀን 2004 ዓ.ም. እንደሚያስመርቅ አስታወቀ፡፡

የትምህርትና ሥልጠና ማእከሉ ሓላፊ አቶ አብዮት እሸቱ እንደገለጹት ማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ በፊት በዜማ ማሠልጠኛ ክፍሉ በርካታ በገና ደርዳሪዎችን ማስመረቁን ገልጸው የአሁኖቹን ተመራቂ ጨምሮ ከ1200 በላይ በገና ደርዳሪዎቹን በማእከሉ ማሠልጠኑን ገልጸዋል፡፡

 

መጋቢት 29 ቀን 2004 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ከቀኑ 7፡30 በሚካሔደው የምረቃ መርሐ ግብር ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የተመራቂ ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ የገለጹት የማእከሉ ሓላፊ ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ ሥርዐት፣ ትውፊትና ዶግማ ተጠብቆ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የተሰጠውን ሓላፊነት እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

የአቡነ ጎርጎርዮስ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል በአሁኑ ወቅት ከ KG እስከ 9ኛ ክፍል ተማሪዎችን በቀለም ትምህርት እያስተማረ የሚገኝ ሲሆን በዜማና በአብነት የትምህርት መስክ ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ አቶ አብዮት ገልጸዋል፡፡

የዐብይ ጾም ስብከት /ክፍል 7/

መጋቢት 26/2004ዓ.ም.

በአያሌው ዘኢየሱስ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤


ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የከምባታ፣ ሀድያ፣ ጉራጌና ስልጢ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤በአዲስ አበባ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የበላይ ኃላፊ፤ቀደም ሲል በዚሁ ደብር አስተዳዳሪ ሆነው ባገለገሉባቸው ዓመታት ውስጥ ለማጠቃለያ ከሰበኳቸው በርካታ የወንጌል ስብከቶች መካከል የተወሰደ፡፡/መጋቢት 21 ቀን 1985 ዓ.ም./

እውነት እውነት እልሃለሁ፡- ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም፡፡ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን የተናገረው ለኒቆዲሞስ ነው፡፡

ኒቆዲሞስ የሃይማኖት ሊቅ ነው፡፡ ብዙ የተማረ ብዙ ያወቀ ሰው ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ሊቅ – ምሁር – አለቃ ተብሎ ተጠርቶአል፡፡ በጊዜው ከነበሩ ሰዎች ከፍ ያለና የላቀ ዕውቀት የነበረው ሰው ነበር፡፡ በሌሊት ወደ ጌታ እየመጣ ይማር ነበር፡፡ የማታ ተማሪ ነበር፡፡ ቀን – ቀን የምኩራብ አስተማሪ ሆኖ ብዙ ሰዎችን ያስተምር ስለ ነበረና እርሱ የሚያስተምራቸው አይሁድ ጌታን ስላልተቀበሉ ቀን ለቀን መጥቶ የሚማርበት አመቺ ጊዜ አልነበረውም፡፡

በአይሁድ ሕግ ጌታን የሚከተልና የሚቀበል ሰው ከምኲራብ የሚባረር ስለሆነ እነርሱን ላላማስቀየም ማታ ነበር የሚማረው፡፡ ኒቆዲሞስ ለጌታ ከሰው ችሎታ በላይ የሆኑ ተአምራትን ስለምትሠራ እኛን ለማስተማርና ለመምከር ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልከህ የመጣህ ነህ ብሎ መስክሮለታል፡፡ ጌታም ለእናንተ ተልኬ የመጣሁ ከሆነና እናንተን ለማስተማር እንደ መጣሁ ከተረዳህ ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም አለው፡፡

ኒቆዲሞስ ስላልገባው እኔ አርጅቼአለሁ፤ እንዴት ነው ወደ እናቴ ማኅጸን ተመልሼ የምገባውና ዳግም የምወለደው? ብሎ ኢየሱስ ክርስቶስን ጠየቀው፡፡ ጌታም፡- ሰው ከሰው ከተወለደ ሥጋዊ ነው፤ የሰው ልጅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን በመንፈስ መወለድ አለበት፡፡ ከእግዚአብሔር መወለድ ነፋስ ከየት ተነሥቶ ወዴት እንደሚነፍስ እንደማይታወቅ ያለ ረቂቅ ምሥጢር ነው አለው፡፡ አሁንም ያ ሊቅ፤ ያ አዋቂ አልገባኝም አለ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም፡- አንተ የእስራኤል ሊቅና አዋቂ ሆነህ እንዴት ይህን አታውቅም አለው፡፡ ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የሚወጣ የለም፤ የምናውቀውንም እንናገራለን ካለው በኋላ ጥያቄውን በዚህ ገታ፡፡

ኒቆዲሞስ  ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ መማሩ የምያስመሰግነው ተግባር ነው፡፡ አይሁድ ወገኖቹ ጌታን ሳይከተሉት እርሱ ጌታን መውደዱ የሚያስደንቅ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ የሚያመሸው ከጌታ ጋር ነበር፡፡ ባለችው ትርፍ ጊዜው ሁሉ ወደ ፈጣሪው ይሔድ ነበር፡፡ ይህ ታላቅ ዕድል ነው፡፡ ቀን ሲያስተምርና ሲደክም ስለሚውል ማታ – ማታ ማረፍ ይገባው ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ቤቴ ገብቼ ልረፍ አላለም፡፡ ባለ ሥልጣንና ባለጸጋ ስለ ነበር ደጅ የሚጠናው ሕዝብና መሰል ባልንጀሮቹ ይፈልጉት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከእነርሱ ጋር አላመሸም፡፡

ከዚህ አባት ታላቅ ትምህርት ልንማር ያስፈልጋል፡፡ እኛ ዛሬ የምናመሸው የት ነው? የምናመሸውስ ከማን ጋር ነው? ምን ስናደርግ ነው የምናመሸው? ኒቆዲሞስ ቤቱ አልነበረም የሚያመሸው፤  ከእውነተኛው መምህር ጋር እንጂ፡፡ ኒቆዲሞስ ጽድቁንና በረከቱን እየያዘ ነበር ወደ ቤቱ ይገባ የነበረው፡፡ እኛ ወደ ቤታችን የምንገባው እየከበርን ነው ወይ? ጸድቀን ነው የምንገባው ወይስ ጎስቁለን?

የዛሬው ሰው እየሰከረ፣ እየጨፈረ፣ እየደማ፣ እየቆሰለ አብዶ ነው የሚመለሰው፡፡ በቤት ያሉትም እንቅፋት ያገኘው ይሆን? ይሞት ይሁን? እያሉ እየተሳቀቁ ነው የሚያመሹት፡፡ የሚሞትም አለ፡፡ ማምሸት እንደ ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር ነው እንጂ! ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር በማምሸቱ ፈጣሪውን አወቀ፡፡ ጌታን ማወቅ ብቻ ደግሞ አይበቃም፡፡ ማወቅማ አጋንንትም ያውቁታል፡፡ ከመንፈስ መወለድ መወለድ ያስፈልጋል፡፡

ሰው ዕፀ በለስን በበላ ጊዜ የእግዚአብሔር ልጅነቱን ተነጥቆ ነበር፡፡ ጌታ መጥቶ ዳግም ሰው እስከሚያደርገን ድረስ የሰይጣል ልጆች ሆነን ነበር፡፡ ከዚያም በአርባና በሰማኒያ ቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስና ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ተወልደናል፡፡ አባታችን የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ከእርሱ ከተወለድንና ልጅነትን ካገኘን እንደገና ልጅነታችንን ካገኘን እንደገና ልጅነታችንን እንዳናጣ አክብረን እንያዘው፡፡ መጀመሪያም አላወቅንበትም ነበር፡፡ አዳም ከገነት የሚወጣ አልመሰለውም ነበር፡፡ ሰይጣን አታሎታል፡፡ እኛም እንደገና እንዳንታለል ልጅነታችን እንዳይሰረዝ እንጠንቀቅ፡፡

የብዙዎቻችን ልጅነት ዛሬ እየተወሰደ ነው፡፡ ልጅነታችንን እያስነጠቅነው ነው፡፡ እነ ኤሳው እየነጠቁን ነው፡፡ ብዙዎች እንደ ያዕቆብ ልጅነታችንን ሊወስዱብን አሰፍስፈዋል፡፡ ሰይጣን እንደ አዳም ሊነጥቀን አሰፍስፏል፡፡ ዛሬ በጣም አርጅተናል፡፡ ኒቆዲሞስ አርጅቶ ነበር፡፡ በጥምቀትና በንስሓ ግን አዲስ ሕይወት አግኝቶአል፤ ታድሷል፡፡ ያረጀው ሕይወቱ ለመለመ፡፡ ያረጀው ሰውነታችንን በሥጋውና በደሙ በንስሓ እናድሰው፡፡ ይህ ከሆነ ነው የእግዚአብሔርን መንግሥት የምንወርሰው፡፡

 

 

baba shenouda

‹‹ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ›› መዝ 118፥98 ፤ በእንተ ቅዱስነታቸው አቡነ ሲኖዳ

መጋቢት 25/2004 ዓ.ም.

በአያሌው ዘኢየሱስ


/ይህ ጽሑፍ ካይሮ በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር አቶ ሜናርደስ “የግብጽ የሁለት ሺህ ዓመት ክርስትና” በሚል ርዕስ ካዘጋጁት መጽሐፍ የተወሰደ ሲሆን የጽሑፍን የአርትኦት ሥራ ያከናወኑት አባ አውጉስጢኖስ ሐና ናቸው፡፡ የዘመን አቆጣጠሩ እንደ አውሮፓውያን ቀመር ነው፡፡/


baba shenoudaየግብጽ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ለመዝለቅ ያሳየችው ያልተጠበቀ መነቃቃት በዓለም የክርስትና እምነት ውስጥ ታላላቅ ከሚባሉት ታሪኮች መካከል አንዱ ነበር፡፡ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ውስጥ ወንዶቹና ሴቶቹ የግብጽ ልጆች /ፈርዖኖች/Pharaohs/ በቤተ ክርስቲያናቸው አማካይነት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመመሥረትና ወንጌልን ለማስፋፋት ያሳዩት ትጋት ተሰምቶ የማይታወቅ ነበር፡፡

ይህ መንፈሳዊ መንሠራራት ጅምሩን ያደረገው ግን ከግማሽ ምእተ ዓመት በፊት ሲሆን ይህም በአሥራ ዘጠኝ አርባዎቹና በአሥራ ዘጠኝ ሀምሳዎቹ በካይሮ፣ በጊዛና በአሲዩት በሚገኙ የቅብጥ/coptic/ የሰንበት ትምህርት ቤቶች እንቅስቃሴ ውስጥ ነበር፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በሚደረጉ ትምህርታዊ ውድድሮች የተነሣሱት ወጣት ወንዶች ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር በመቀደስ፥ በበረሀ የሚኖሩ አባቶቻቸውን ለመከተል ወደዚያው ወጥተዋል፡፡ እነዚህ ወጣቶች በተለይም በሶርያውያን ገዳም ውስጥ በሚገኙት በአባ ቴዎፍሎስ /Bishop Theophilus/ ብቃት ያለው አመራር አማካይነት ለቤተ ክርስቲያናቸው የማነቃቃት ሥራ ለመሥራት ራሳቸውን አዘጋጁ፡፡

 

በ1959 ዓ.ም. አቡነ ቄርሎስ 6ኛ ፓትርያርክ ሆነው ከተሾሙ በኋላ የቀድሞዎቹ የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች ከነበሩት መምህራን፣ መነኮሳትና ባሕታውያን መካከል ጥቂቶቹ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ተጠርተው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕይወትና አደረጃጀት ውስጥ ቁልፍ የሓላፊነት ሥልጣን እንዲጨብጡ ተደረገ፡፡ ከእነዚህ ወጣቶች መካከል አቡነ እንጦንስ አል ሱሪያኒ /1954-2012//Fr. Antonyos (Anthony) El-Souryani/፣ በኋላም ሲኖዳ ተብለው የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን የሥነ መለኮትና የትምህርት ተቋማት ጳጳስ /1962-71/ የተባሉትና በመጨረሻም አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ በሚል ስም የተሾሙት የአሁኑ ጳጳስና ፓትርያርክ የቀድሞው ናዚር ጋዪድ (Nazir Gayyid) ናቸው፡፡ የአቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ የጵጵስና ሕይወት በታላቅ ጥረትና ጥልቀት ባለው መንፈሳዊነት የተቃኘ ስለ ነበር ሕይወቱን ለማጣት ተቃርቦ ለነበረው የስብከት ተቋም አዲስ ራእይና ሕይወት በመስጠት ስኬታማ ሊሆን ችሏል፡፡ ይህ በመሆኑም ከፍተኛ ወግ ተሰጥቶአቸው የነበሩትና ከተመሠረቱ ረዥም ጊዜያት ያስቆጠሩትን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶችን ያዝ በማድረግ በአዲስ መንፈሳዊ ስሜት እንዲሞሉ አድርጓል፡፡

 

የአቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ መንፈሳዊና ትምህርታዊ መነሻ አሁን ያለውን የቤተ ክርስቲያኒቷን የእንቅስቃሴ አቅጣጫ በስፋት የወሰነ ነው፡፡ ናዚር ጋዪድ /የአቡነ ሲኖዳ የመጀመሪያ የቤተሰብ ስማቸው ነው/ ሹብራ(Shubra) በሚገኘው የቅዱስ እንጦንስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሰንበት ትምህርት ቤት አባል የሆኑት ገና በ16 ዓመታቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን የዚሁ ሰንበት ትምህርት አስተማሪ በመሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ግብጻውያንን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ አድርገዋል፡፡

 

ናዚር ጋዪድ በብዙ መንገድ በላይ በቅብጥ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለተቋቋመው አዲስ የወጣቶች አገልግሎት አጠቃላይ መሪ ሆነዋል፡፡ በ1947 ዓ.ም. በካይሮ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛና በታሪክ የቢ.ኤ. (B.A.) ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ንግግራቸው፣ ስብከታቸውና መጻሕፍቶቻቸው እንከን የማይወጣላቸው የእንግሊኛ ቋንቋ ተጠቃሚ መሆናቸውን ያንጸባርቃሉ፡፡ በሥነ መለኮት ኮሌጅ ውስጥ የተሰጡትን ጥናቶች ብሩህ በሆነ የትምህርት ብቃት ስለ ፈጸሙ በዚያው ኮሌጅ ውስጥ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መምህር ሆነው ለመሾም በቅተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ 1953 ዓ.ም. ሄልዋን (Helwan) በሚገኘው የምንኩስና ኮሌጅ ውስጥ የሙሉ ሰዓት አስተማሪ ሆነው ተመድበዋል፡፡

 

ሐምሌ 19 ቀን 1954 ዓ.ም. በሶሪያውያን ገዳም ውስጥ በሚገኙት በጳጳስ ቴዎፍሎስ (Bishop Tawfilus) አማካይነት ምንኩስናን ተቀብለዋል፡፡ በዚህ ዕለት ናዚር ጋዪድ የሚከተለውን ቃል ኪዳን ፈጽመዋል፡-

 

ምንኩስና ማለት ሀብትና ንብረትን፤ ዘመዶችንና ጓደኞችን፤ ሹመትንና ሥልጣንን አስመልክቶ ለዓለም ሙሉ ለሙሉ መሞት መሆኑን አረጋግጣለሁ፡፡ ምንኩስና የአምልኮና ራስን ለእግዚአብሔር የመስጠት ሕይወት መሆኑን አረጋግጣለሁ፡፡ የንስሓ፣ራስን የመተው፣ ፍጹም የመታዘዝ፣ የብቸኝነትና የድህነት ሕይወት መሆኑንም አረጋግጣለሁ፡፡ በእግዚአብሔር በመላእክቱና በቅዱስ መሠዊያው ፊት እንዲሁም ቅዱስ አባቴ በሆኑት በጳጳሱ ፊት፤ በተሰበሰቡ አባቶች ፊት፤ በመነኮሳት ፊት እና በዚህ ቅዱስ ጉባኤ ፊት ከዓለም ተለይቼ በድንግልና እና በንጽሕና እኖር ዘንድ ሕይወቴን ለእግዚአብሔር አቀርባለሁ፡፡ እውነተኛውን የምንኩስና ሥርዓት ለመቀበልና ቅዱሳን አባቶቻችን ለእኛ ያስቀመጡልንን ይህን መላእክታዊ የሕይወት ጠባይ ለመከተል ቃል እገባለሁ፡፡ ይህ ከሆነ ከአንድ ዓመት በኋላ ክህነትን ተቀብለዋል፡፡ ካህን፣ ጳጳስና ፓትርያርክ ሆነው በኖሩበት የሕይወት ዘመናቸው በሶሪያውያን ገዳም ውስጥ በምትገኘው የድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን የገቡትን ቃል ኪዳን እስከ አሁን ድረስ በታማኝነት ጠብቀዋል፡፡

 

በገዳሙ ውስጥ የቤተ መጻሕፍቱ ሓላፊ ሆኖ አገልግለዋል፡፡ እነዚህ ሥራዎች ጥናታቸውን በቤተ ክርስቲያን አባቶችና ሐኪሞች ላይ እንዲያደርጉ አስችለውታል፡፡ ይህ ይሁን እንጂ እርሳቸው ይናፍቁ የነበረው የብቸኝነትን ሕይወት ነበር፡፡ በመሆኑም በመጀመሪያ የመረጡት ከገዳሙ በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ዋሻ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ይህንን የባሕታዊ መኖሪያ ከገዳሙ አሥር ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በሚገኘው ባኸር አል ፋራይ (Bahr al-Farigh) ዋሻ እንዲለውጡ ሆነዋል፡፡ በ1984 ዓ.ም. መግቢያ ላይ “ባሕታዊው” በሚል ርዕስ የጻፉት ግጥም በ1954 ዓ.ም. በሰንበት ትምህርት ቤቱ መጽሔት ላይ ታትሞ ወቷል፡፡

 

ከመጽሔቱ የተወሰደ፡-

ብቻዬን በበረሀ ውስጥ የራሴን ነገር እየሰላሰልሁ፤

በተራራው ጫፍ  ባለ ዋሻ ገብቼ ተከልያለሁ፤

እና አንድ ቀን ትቼው እሔዳለሁ፤

የምኖርበትን ወደማላውቀው፡፡


በ1959 ዓ.ም. ፓትርያርኩ ቄርሎስ 6ኛ የግል ጸሐፊያቸው አድርገው ቢሾሟቸውም አባ እንጦንዮስ የመረጡት የብቸኝነት ሕይወት ነበር፡፡ አባ እንጦንስ ለብዙ ዓመታት የጵጵስና ማዕረግ እንዲቀበሉ የተለያዩ ጫናዎች ቢደረጉባቸውም ሁሉንም በተሳካ ሁኔታ ሊከላከሉ ችለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በመስከረም ወር 1962 ዓ.ም. ፓትርያርኩ አቡነ ቄርሎስ በገዳሙ ውስጥ አለመግባባት ስለ ፈጠሩት ጥቂት የአስተዳደር ነክ ጉዳዮች ከባሕታዊው ከአባ እንጦንስ ጋር ለመወያየት በሚል ካይሮ ወደሚገኘው መንበረ ፓትርያርክ እንዲመጡ ያስጠሯቸዋል፡፡ አባ እንጦንስ በፓትርያርኩ ፊት ተንበርክከው ይቅርታ በመጠየቅና ከአስተዳደር ሥራ እንዲለዩ በማሳሰብ ለጥያቄያቸው መልስ በመጠባበቅ ላይ ሳሉ ፓትርያርኩ ቄርሎስ እጆቻቸውን በባሕታዊው ራስ ላይ በመጫን የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን የሥነ መለኮት እና የትምህርት ተቋማት ጳጳስ አድርገው ይሾሟቸዋል፡፡

 

ይህ ሹመት በመንበረ ፓትርያርኩ መስከረም 30 ቀን 1962 ዓ.ም. ተሰጠ፡፡ ከዚህ በኋላ እኔ ራሴ /የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ/ “እንኳን ደስ አልዎ” በማለት ለአቡነ ሲኖዳ ለጻፍኩላቸው ደብዳቤ የጻፉልኝ የመልስ ደብዳቤ ከዚህ የሚከተለው ነው፡-

 

“ከአምላካችንና ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የሆነ ጸጋና ሰላም ለአንተ ይሁን፡፡ ወደ እኔ ስለላክሃቸው የ”እንኳን ደስ አልዎ” መልካም ቃላት አመሰግንሃለሁ፡፡ ወዳጅነትህንና ፍቅርህን በጭራሽ ልዘነጋ አልችልም፡፡ እውነቱን ለመናገር ግን አሁን ለገጠመኝ ሁኔታ የሚገባኝ የማጽናኛ ደብዳቤ እንጂ የእንኳን ደስ ያለህ ደብዳቤ አልነበረም፡፡ አንድ መነኩሴ የበረሀውን ፀጥታ ትቶ በከተማ ሁከት ለመታጀብ በመሔዱ እንዴት እንኳን ደስ ያለህ ሊባል ይችላል? ማርያም ከክርስቶስ እግር አጠገብ ያለ ቦታዋን ትታ ከማርታ ጋር በኩሽና ለመገኘት በመሔዷ እንኳን ደስ አለሽ የሚላት ማነው? በእርግጥም ይህ ለእኔ በጣም የሚያሳፍር ነገር ነው፡፡ ለጵጵስና የተመረጥሁባትን ያቺን ቀን የማስታውሳት በዕንባና በሰቆቃ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ግን የብቸኝነትና የተመስጦ ክብር ከመናገር በላይ ነው፡፡ ከኤጲስ ቆጶስነትና ከጳጳስነት ጋር አይነጻጸርም፡፡ ውድ ወዳጄ ሆይ፤ እውነተኛው መቀደስ ልብን ለእግዚአብሔር ቅዱስ ቤተ መቅደስ አድርጎ መቀደስ ነው፤ እርሱ በመጨረሻው ቀን የሚጠይቀን የእረኝነት ማዕረጋችንን ሳይሆን የልባችንን ንጽሕና ነውና፡፡ ይህን ደብዳቤ የጻፍሁልህ ከምወደውና ዋዲ አል-ንጥራን (Wadi al-Natrun) ውስጥ ከሚገኘው ከባሕር አል ፋራይ (Bahr al-Farigh) ዋሻ ሆኜ ነው፡፡ ወደ ካይሮ ከመመለሴ በፊት የምቆየውና የጥምቀትን በዓል የማከብረው በዚህ ዋሻ ውስጥ ነው፡፡››

 

ይሁን እንጂ በተገኘው አመቺ ጊዜ ሁሉ ጳጳሱ አባ ሲኖዳ የሚሔዱት ወደዚህ ገዳም ነው፡፡ በክርስቲያን የትምህርት መስክ ውስጥ የአቡነ ሲኖዳ አመራር ዋጋውን ያገኘው በ1969 ዓ.ም. የመካከለኛው ምሥራቅ የሥነ መለኮት ኮሌጆች ኅብረት ፕሬዝዳንት (President of the Association of Middle East Theological Colleges) ሆነው ሲመረጡ ነው፡፡ የአቡነ ሲኖዳ እጅግ ጠቃሚ የአገልግሎት ዘርፍ በየሳምንቱ የሚያቀርቧቸው ስብከቶች አቀራረብ ሲሆን በዚህም ለሥነ መለኮታዊና ለማኅበረሰባዊ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችም የዚህ አገልግሎት ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡ አቡነ ሲኖዳ የሳምንቱን እኩሌታ በካይሮና በእስክንድርያ በማስተማርና በመስበክ ከቆዩ በኋላ የሳምንቱን እኩሌታ የሚያሳልፉት በዚህ ገዳም ውስጥ ነው፡፡

 

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከቅብጥ ቤተ ክርስቲያን ዓላማዎች አንዱ ለመቶ ዓመታት አብሯት ከቆየው የሥነ መለኮት ልዩነት ራስዋን ነጻ ማውጣት ነበር፡፡ አቡነ ሲኖዳ ቤተ ክርስቲያናቸውን በመወከል ብዛት ባላቸው የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጉባኤዎች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ የትምህርት ጳጳስ ሳሉ ለመጨረሻ ጊዜ የተሳተፉበት ጉባኤ በ1971 ዓ.ም. ቪየና ውስጥ በምሥራቃውያን ኦርቶዶክስና በካቶሊካውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል የተደረገው የመጀመሪያው ጠቃሚ የምክክር ጉባኤ ነው፡፡ ይህ የሆነው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ሆነው ሊሾሙ ልክ አንድ ወር ሲቀራቸው ነበር፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ አቡነ ሲኖዳ የእስክንድርያው ቅዱስ ቄርሎስ ያዘጋጀውን የክርስቶስ ትምህርት ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርገዋል፡፡ ይህ አንቀጽ ኋላ ላይ በሮማው ጳጳስ በዮሐንስ ጳውሎስ አራተኛና በአቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ በይፋ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡

 

ተቀባይነት ያገኘውና የእስክንድርያው ቅዱስ ቄርሎስ ስለ ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት አንቀጽ የሚከተለው ነው፡-

“እኛ ሁላችን አምላካችን እግዚአብሔር መሆኑንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ የለበሰው ቃል መሆኑን እናምናለን፡፡ እርሱ በመለኮቱና ሰው በመሆኑ ፍጹም እንደሆነ እናምናለን፡፡ አምላክነቱ ከሰውነቱ ለቅጽበት እንኳ እንዳልተለየም እናምናለን፡፡ ሰው መሆኑ ከመለኮቱ ጋር ያለ መቀላቀለ፣ ያለ መለወጥ፣ ያለ መከፋፈልና ያለ መለያየት የሆነ ነው፡፡”


ፓትርያርኩ አቡነ ቄርሎስ አራተኛ መጋቢት 9 ቀን 1971 ዓ.ም. በሞተ ሥጋ ሲለዩ ቅዱስ ሲኖዶሱ ማርች 22 ቀን 1971 ዓ.ም. ተከታዩን ፓትርያርክ ለመምረጥ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት ወሰነ፡፡ ጥቅምት 29 ቀን 1971 ዓ.ም. ይፋ የነበረው ምርጫ ከአምስት ወደ ሦስት እጩዎች ዝቅ አለ፡፡ ከዚህ በኋላ አይማን ሙኒር ካሚል የተባለና ዐይኖቹ በጨርቅ የታሰሩ አንድ ልጅ የዕጩዎቹ ጳጳሳት ስሞች ተጽፈውባቸው ከተጠቀለሉት ቁርጥራጭ ወረቀቶች መካከል አንዱን በማንሣት ለከተማዋ ጳጳስ ለእንጦኒዮስ ሰጠ፡፡ እርሳቸውም ለቅብጥ ቤተ ክርስቲያን እረኛ ይሆን ዘንድ የተመረጠው ጳጳሱ ሲኖዳ መሆኑን በይፋ አስታወቁ፡፡ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ኅዳር 14 ቀን 1971 ዓ.ም. ጳጳሱ ሲኖዳ “ቅዱስነታቸው አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ በማርቆስ መንበር 117ኛው ፓትርያርክ” ተብለው በይፋ ተሰየሙ፡፡

 

ምንም እንኳን ጳጳስና ፓትርያርክ ቢሆኑም በሥነ መለኮት ኮሌጅና በቅብጥ ጥናት ከፍተኛ ተቋም ውስጥ ማስተማራቸውን አላቋረጡም፡፡ በመሆኑም በታሕታይ ግብጽና በላዕላይ ግብጽ ውስጥ ቅርንጫፍ የሆኑ ስድስት ተጨማሪ የሥነ መለኮት ኮሌጆች ሲከፈቱ ሌሎች ተጨማሪ ሦስት ኮሌጆች በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካና በአውስትራሊያ ተመሠረቱ፡፡

 

እንደ ሊቅነታቸው አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ በቅብጥ ላይ የሚደረጉ የተለያዩ ጥናቶችን አበረታተዋል፤ በዚህም ታላቁ የቅብጥ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲታተም አድርገዋል፡፡ በሚያዝያ ወር 1988 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርኩ ውስጥ ያለው የቅብጥ መዝገብ ቤት በማይክሮ ፊልም እንዲነሣ አል አህራም (Al-Ahram) ከተባለ የዜና ድርጅት ጋር ኮንትራት ተፈራርመዋል፡፡

 

የቤተ ክርስቲያኗ የበላይ ጠባቂ በመሆናቸው ከ80 የሚበልጡ ጳጳሳትንና ከ500 የሚበልጡ ካህናትን ግብጽ ውስጥ ለምትገኘው ለቅብጥ ቤተ ክርስቲያንና በውጪ ለሚኖሩ የቅብጥ አብያተ ክርስቲያናት አማኞች ሾመዋል፡፡ በየጊዜው ከካህናቱ አባላት ጋር የሚያደርጓቸው ሴሚናሮች የካህናቱንና የጳጳሳቱን የእረኝነቱን፣ የመንፈሳዊነቱንና የትምህርቱን ሕይወት አበረታትዋል፡፡ እርሳቸው ለወጣቱ ትውልድ ልዩ ትኩረት ስለሰጡ በአቡነ ሙሳ የበላይ ሓላፊነት በጣም ድንቅ የሆነ የወጣቶች የአገልግሎት ዘርፍ እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ ታይቶ የማይታወቅ የአብያተ ክርስቲያናት ቁጥር በተለይም በውጪ ሀገራት እየጨመረ ስለመጣ አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ መጠኑ የበዛ ቅዱስ ሜሮን ወይም የምሥጢር ዘይት በ1981፣ በ1983፣ በ1993 እና በ1995 ዓ.ም. በቅዱስ ቢሶይ ገዳም ውስጥ ባርከዋል፡፡ የክርስቲያኖች አንድነት እንዲኖር ጥልቅ ፍላጎት ስለነበራቸው የተሻለ የምክክር መግባባት ይፈጠር ዘንድ ሰፊ ጊዜና ጥረት አድርገዋል፡፡ በክርስቲያኖች አንድነት ላይ ምንጊዜም አጽንዖት ሰጥተው የሚናገሩት የክርስቲያኖች አንድነት ሊመሠረት የሚገባው በእምነት ላይ እንጂ በሥልጣን ላይ አለመሆኑን ነው፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ በምሥራቅ ኦርቶዶክስ፣ በሮማ ካቶሊክ፣ በአንጀሊካን፣ በፕሬስባይቴሪያን፣ በስዊድን ሉተራን እና በተሐድሶ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሥነ መለኮት ውይይት እንዲደረግ አነሣሥተዋል፡፡

 

ይህ በመሆኑም በግንቦት ወር 1973 ዓ.ም. አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ በሮማው ጳጳስ በጳውሎስ 6ኛ ጥሪ ሮምን እንዲጎበኙ ተጋብዘው ነበር፡፡ ከ451 ዓ.ም. በኋላ በአንድ እስክንድርያዊና በአንድ ሮማዊ ጳጳስ መካከል እንዲህ ያለው ግንኙነት ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ በዚህ ግንኙነት ሁለቱም በክርስቶስ ላይ ያላቸውን የጋራ እምነት በፊርማቸው አጽድቀዋል፡፡ በ1979፣ በ1987 እና በ1995 ዓ.ም. አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ ከካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ (Archbishop of Canterbury) ጋር ተገናኝተው በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ያላቸውን የጋራ ግንዛቤ ተወያይተዋል፡፡ በኖቬምበር ወር 1988 ዓ.ም. ደግሞ በቅብጥና በፕሬስባይቴሪያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሥነ መለኮት ክርክር እንዲካሔድ አበረታተዋል፡፡ ይህ ክርክር በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ ኦርቶዶክሶችና ፕሮቴስታንቶች መካከል ተፈጥረው የነበሩትን አንዳንድ የሥነ መለኮት የአመለካከት ችግሮት ለማስታረቅ መንገዱን ጠርጓል፡፡

 

ከሌሎች የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ አቡነ ሲኖዳ ሳልሳዊ በደማስቆ፣ በኢስታንቡል፣ በሞስኮ፣ በቡካሬስትና በሶፊያ ያሉትን የኦርቶዶክስ መንበረ ፓትርያርኮች ጎብኝተዋል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ታላቅ በአፍሪካም ጥንታዊት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን መሪ እንደመሆናቸው መጠን ቤተ ክርስቲያናቸው በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት እና ከመላው አፍሪቃ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ጋር ላላት ተሳትፎ ልዩ ትኩረት ሰጥተዋል፡፡

 

በየካቲት ወር 1991 ዓ.ም. በካንቤራ አውስትራሊያ በተካሔደው በ7ኛው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ለመገኘት አሥራ አንድ የቅብጥ አባላትን ያካተተውን የልዑካን ቡድን መርተዋል፡፡ በስብሰባው ማብቂያ ላይ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዘዳንቶች መካከል አንዲ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ በኅዳር ወር 1994 ዓ.ም. ቆጵሮስ (Cyprus) ውስጥ በተካሔደው ስብሰባ ላይ ደግሞ የመካከለኛው ምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት አራት ፕሬዘዳንቶች መካከል አንዱ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ምንም እንኳ የዓለም የክርስትና እምነትን ለማገልገል ሰፊ ጊዜያቸውን መሥዋዕት አድርገው ቢያቀርቡም ሲኖዳ ሳልሳዊ በልባቸው መነኩሴ መሆናቸው አልቀረም ነበር፡፡

 

ከዚህ ሌላ በመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሰው የተራቆቱ ብዛት ያላቸው ገዳማት እንዲታደሱና ተመልሰው እንዲገነቡ መሣሪያ ሆነው ቆይተዋል፡፡ የጵጵስና መኖሪያቸው የተመሠረተው ቅዱስ ቢሶይ ገዳም ውስጥ ነው፡፡ ይህ መኖሪያቸው በውስጡ የጸሎት ቤት፣ የስብሰባና የስብከት አዳራሾችን እና እንግዳ መቀበያ ክፍሎች ያካተተ ነው፡፡ አቡነ ሲኖዳ ሳልሳዊ የእያንዳንዱን ሳምንት እኩሌታ በተመስጦና በአርምሞ የሚያሳልፉት በዚህ ገዳም ውስጥ ነው፡፡

 

በ1971 ዓ.ም. ከግብጽ ውጪ ለሚኖሩ ግብጻውያን የነበሩት የቅብጥ አብያተ ክርስቲያናት ሰባት ብቻ ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ ብቻ አንድ መቶ፣ በአውስትራሊያ ሃያ ስድስት በአውሮፓ ደግሞ ከሠላሳ የሚበልጡ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ በውጪ ሀገራት በሚገኙ በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚያገለግሉ አሥራ አምስት የቅብጥ ጳጳሳትም አሉ፡፡

 

በ1994 ዓ.ም. በእንግሊዝ ደሴቶች (British Isles) ላይ የሚኖሩና አሥራ ዘጠኝ የሚደርሱ የእንግሊዝ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከቶች ከቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ሙሉ ኅብረት ፈጥረዋል፡፡ በ1994 ዓ.ም. በተከበረው የበዓለ አምሳ ላይ አባ ሱሪፌል የግላስተንበሪ (Glastonbury) ጳጳስ ሆነው ተሾመዋል፡፡ ኤርትራ የራስዋን መንግሥት ካቋቋመችና አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ የኤርትራ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ በመንበረ ማርቆስ የስብከት አሰጣጥ ደንብ የሚመራ ነጻ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንዲቋቋምላቸው አቡነ ሲኖዳ ሳልሳዊን ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዲስ ሲኖዶስ መስከረም 28 ቀን 1993 ዓ.ም. ባካሔደው ስብሰባ የኤርትራውያን ክርስቲያኖችን ጥያቄ ለመቀበል ተስማምቷል፡፡ በዚህ መሠረት 1994 ዓ.ም. በዋለው በዓለ ሀምሳ አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ አምስት ኤርትራውያን ጳጳሳትን በመሾም የኤርትራውያንን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ነጻ ሲኖዶስ ለመመሥረት መሠረት አስቀመጡ፡፡ ግንቦት 7 ቀን 1998 ዓ.ም. ቅዱስነታቸው አቡነ ሲኖዳ የ93 ዓመቱን ጳጳስ አቡነ ፊልጶስን የኤርትራ የመጀመሪያው ፓትርያርክ በማድረግ ሾሙ፡፡ ካይሮ በሚገኘው የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ውስጥ በዓለ ሲመቱ ሲከናወን ከሀምሳ የሚበልጡ የቅብጥ ጳጳሳትና ሰባት የኤርትራ ጳጳሳት ተገኝተው ነበር፡፡

 

አስቀድመን ካነሳነው ተጋድሎአቸው መካከል፥ ፕሬዝዳንት አንዋር አል ሳዳት አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊን በትክክል ባለመረዳት በተደጋጋሚ ከሰዋቸው እንደነበር ነው፡፡ በተለይም አቡነ ሲኖዳ ግንቦት 14 ቀን 1980 ዓ.ም. በፓርላማው ፊት ያሰሙት ንግግር በቅብጥ ቤተ ክርስቲያንና በግብጽ መንግሥት መካከል ያለውን የፖለቲካ አየር ክፉኛ በከለው ተባለ፡፡ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ተደማምሮ መስከረም 3 ቀን 1981 ዓ.ም. ፕሬዝዳንት ሳዳት ከቤተ መንግሥት ባስተላለፉት ትእዛዝ መሠረት አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ በቅዱስ ቢሾይ ገዳም በግዞት እንዲቀመጡ አደረጉ፡፡ ከዚህ በተመሳሳይ ጊዜ ስምንት ጳጳሳት፣ ሃያ አራት ቀሳውስትና ሌሎች እውቅና ያላቸው ብዙ የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን አባላት ታሠሩ፡፡ ሳዳት ይህን ካደረጉ በኋላ አምስት ጳጳሳትን ያቀፈ አንድ የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ኮሚቴ አዘጋጁ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ግን የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን መሪ አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ መሆናቸውን በአጽንዖት አረጋገጠ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ፕሬዝዳንት ሳዳት አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊን ይጠሩ የነበረው “የቀድሞው ፓትርያርክ” እያሉ ነበር፡፡

 

አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ በቅዱስ ቢሶይ ገዳም በግዞት ሳሉ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International) “የኅሊና እስረኛ” (‘Prisoner of Conscience’) በማለት ነሐሴ 26 ቀን 1983 ዓ.ም. በይፋ ሰይሟቸዋል፡፡ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ብዛት ያላቸው ክርስቲያኖች ጥልቅ ሃዘናቸውን ገልጠዋል፡፡ ይፈቱ ዘንድ በሰኔ ወር 1982 ዓ.ም. እና በኅዳር ወር 1984 ዓ.ም. ልዩ የጸሎት መርሐ ግብር ተደርጎላቸዋል፡፡ የጊዛው ጳጳስ ዱማዴዎስ የቀድሞ ባልንጀራቸውን በየሳምንቱ ይጠይቋቸው ነበር፡፡ ፕሬዝዳንት ሳዳት ነሐሴ 3 ቀን 1981 ዓ.ም. ያስተላለፉትን የግዞት ትእዛዝ ፕሬዝዳንት ሙባረክ ታኅሣሥ 2 ቀን 1985 ዓ.ም. ሻሩት፡፡ አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ ከስደት ዓመት ከአራት ወራት ግዞት በኋላ ታኅሣሥ 4 ቀን 1985 ዓ.ም. በአሥራ አራት ጳጳሳት ታጅበው ወጡ፡፡ በሚቀጥለው ቀን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ሲያከብሩ ከአሥር ሺህ የሚበልጥ ሕዝብ ተገኝቶ ፓትርያርኩን ተቀብሏል፡፡

 

ከዚህ በኋላ በመንግሥትና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት አመርቂ በሆነ መልኩ ተሻሻለ፡፡ ከብዙኀኑ የእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር ስለ ተፈጠረው መልካም ግንኙነት ምስክር የሚሆነው በረመዳን የጾም ወር ውስጥ ቅዱስነታቸው አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ በፖለቲካውና በሃይማኖቱ ውስጥ የሚገኙትን የሀገሪቱን የበላይ አመራር አባላት በየዓመቱ የአፍጥር መጋበዛቸው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከ1986 ዓ.ም. ጀምሮ የአል አዛር ሼህ፤ ታላቁ ሙፍቲ እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን ትርጉም ባለው የመልካም ፈቃድ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡ ይህ ይሁን እንጂ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ የአናሳ ክርስቲያኖች መሪ ተብለው ሊጠሩ እንደማይፈቅዱ በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም “ቅብጥ እንደ መሆናችን በግብጽ ክፍል የምንኖር ግብጻውያን ነን፡፡” በማለት አዘውትረው ይናገራሉ፡፡

 

ምንጭ፡-

  • ST.JOHN-NOVEMBER 2004
  • አዘጋጅ፡- ኦክተር አቶ ሜናርደስ
  • ተርጓሜ፡- አያሌው ዘኢየሱስ

ሀገር ዕርቃኗን እንዳትቀር

መጋቢት 25/2004 ዓ.ም.

ከጥቂት ዓመታት በፊት በታተመ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ጥናት፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2020 ሙሉ በሙሉ ደን አልባ አገር ትኾናለች፡፡ እንደ ጥናቱ ከ40 ዓመታት በፊት የሀገሪቱ 40 በመቶ መሬት በደን ተሸፍኖ ነበር፡፡ ጥናቱ በታተመበት ዓመት ግን ወደ 2.7 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡ ጥናቱ ማስረጃን በመጥቀስ እንዳስቀመጠው ቁጥሩ በሚያስደንቅ ሁኔታ እንዲህ ያሽቆለቆለው በሀገሪቱ 200,000 ሄክታር መሬት በልዩ ልዩ መንገድ ስለሚወድም ነው፡፡ የዚህን ጥናት ግኝት ሌሎች ጥናቶችም ይጋሩታል፡፡ ይህ መረጃ አስደንጋጭ ነው፡፡ በልምላሜና ልምላሜው በሚያመጣው በረከት ለሚኖር እንደኛ ዓይነት ሕዝብ ደግሞ ሁኔታው አስጨናቂ ነው፡፡

ከሀገራችን የተፈጥሮ ደኖች ውስጥ 35 ሺ የሚኾኑት በአድባራትና ገዳማት ዙሪያ ያሉ ደኖች እንደኾኑ ልዩ ልዩ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ እነዚህ ደኖች የሚገኙት በተለይ በሀገሪቱ የሰሜን፣ ሰሜን ምዕራብና መካከለኛው ክፍል እንደመኾናቸው አካባቢው ተፈጥሮ ካደረሰበት መራቆት የተነሣ የችግሩን ስፋትና ግዝፈትም ባያህል የቻሉትን ያህል ሲታደጉት ኖረዋል፤ አሁንም በመታደግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እነዚህ ባለውለታ ደኖች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አደጋ እንደተቃጣባቸው ወይም እንደደረሰባቸው እናያለን፤ ከሰሞኑ እንኳን በአሰቦት ደብረ ወገግ አቡነ ሳሙኤልና ቅድስት ሥላሴ ገዳም፤ እንዲሁም ደግሞ በዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ደን ላይ ላይ የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ በዚህም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችንም ብቻ ሳይኾን እንደ ኢትዮጵያዊነታችን ደንግጠናል፤ ተጨንቀናልም፡፡ ለምን?

ደኖቻችን የመንፈሳዊ ሀብታችን ምንጮች ናቸው፡፡ ለቅዱሳን አበውና እመው የተመስጧቸው መሠረት፣ የጸሎታቸውም ትኩርት፣ ለዐጽማቸው ማረፊያ ለስውራኑም መናኸሪያ ከተማ ናቸው፡፡ መንፈሳዊ ጥበብ፣ ፍልስፍናና ዕውቀትም በእነሱ በኩል አግኝተናል፤ እናገኛለንም፡፡ ቅዱስ ያሬድ የዜማ ዕውቀትን ያገኘው በዐጸድ መካከል ነው፡፡ የቅኔው ፍልስፍና፣ የአቋቋሙ ጥበብ፣ የመጻሕፍት ምሥጢር የፈላውና በመልክ በመልኩ የተደራጀው በደኖቻችን ሆድ ውስጥ ነው፡፡ ዛሬ ከሀገራችን አልፎ በዓለም ሊቃውንት ቢቀዱና ቢጠኑ የማያልቁት ቅዱሳት ድርሰቶች በአበው ሊቃውንት የተጻፉት ደኖቻችን ቀለምና ብርዕ ኾነው ነው፡፡ ሀገሪቱ በበርካታ ጦርነቶች ያለፈች እንደመኾኗ ደኖቻችን በየዘመኑ በርካታ ቅርሶችን በአደራነት ተቀብለው አኑረዋል፡፡ የተገኙት ተገኝተዋል፡፡ አደራ መቀበላቸውን ያየ ወይም የሰማ ጠፍቶ አደራ በሊታ ላለመኾን ዛሬም ሰንቀዋቸው ይገኛሉ፡፡ የሚመረምር ጠቢብ ትውልድ ቀርቦ እስከሚቀበላቸው ድረስ፡፡ ደኖቻችን ምግቦቻችንም ናቸው፡፡ ይህን ዓለም ንቀው በምናኔ ለሚኖሩ አባቶቻችን በምግብ ምንጭነት ከማገልገላቸውም አንጻር መንፈሳዊ ጥቅማቸው የጎላ ነው፡፡ ደኖቻችን የምድር ልብሶች ናቸው፡፡ በልብስነታቸው በውስጣቸው ላሉ ብርቅዬ የኾኑ እንስሳትና አራዊት መጠጊያ ኾነው ያገለግላሉ፡፡ በመኾኑም በውስጣቸው በያዟቸው ሀብታት ደኖቻችን የተቀደሱ ናቸው፡፡

ደኖቻችን ላቅ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምም አላቸው፡፡ በውስጣቸው ሕዝብ ቢመገባቸው የሚያጠግቡ፤ ቢጠጣቸው የሚያረኩ ፍራፍሬዎች፣ እንስሳትና ማዕድናት የያዙ ናቸው፡፡  እነዚህ ሀብታት በአግባቡ ቢያዙ ከሀገር አልፈው ወደ ዓለም ዐቀፍ ገበያ ቀርበው ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ማምጣት ይችላሉ፡፡ በሌላው ዓለም የሌሉ የእንስሳትም ኾነ የዕጸዋት ዝርያዎችን የያዙ ከመኾናቸው አንጻርም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ፡፡ ደኖቹ በሚፈጥሩት ልምላሜ አየር የተነሣም ሀገርን የሚያለመልም ጠለ በረከት እንዲወርድ ያደርጋሉ፡፡ ጠለ በረከት ሲወርድ ሕዝብ ጠግቦ ያድራል፤ ኢኮኖሚውም ይገነባል፡፡

ደኖቻችን መድኃኒቶቻችን ናቸው፡፡ በዚህም የሀገርን ኢኮኖሚ ከማሳደግ አኳያ ጥቅማቸው የጎላ ነው፡፡ እንደነ መጽሐፈ መድኃኒት፣ ዕጸ ደብዳቤ፣ መጽሐፈ አዕባን ወዘተ. ዓይነት ደገኛ የነገረ ሕክምና መጻሕፍት በአበው ተጽፈው ለእኛ የደረሱን፤ አባቶቻችን በእነዚህ ደኖች ቤተ ሙከራነት ባደረጉት ምርምር ነው፡፡ የዛሬው ትውልድ ልብ ገዝቶ ከላይ የተጠቀሱትን መጻሕፍት ተጠቅሞ መድኃኒት ልሥራ ብሎ ቢነሣ ንጥረ ነገሮቹን የሚያገኘው ከዚህ ነው፡፡ ሀገር ለራሱ ሕዝብ በራሱ መድኃኒት ፈበረከ ማለት ደግሞ፤ ሕዝቡ ስሙን እንኳን አንብቦ የማይረዳውን መድኃኒት በብዙ ሚልዮን ዶላር ገዝቶ ከማምጣት መዳን ይቻላል ማለት ነው፡፡

ደኖቻችን ከማኅበራዊና ባሕላዊ ጥቅማቸውም አንጻር ድርሻቸው ሰፊ ነው፡፡ የተጣላ የሚታረቀው፣ በሀገርና በወገን በመጣ ችግር ላይ ተወያይቶ መፍትሔ የሚሰጠው፣ ወጣት ኮረዳው በተፈጥሮ የተሰጠውን ችሎታ ፈትሾ የሚያዳብረው በደኖቻችን ነው፡፡

በመኾኑም በምናየውና በምንሰማው መልኩ በተፈጥሮ ደኖቻችን ላይ በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ የሚቃጣውና የሚደርሰው አደጋ በሕዝብና በሕዝቡ ማሕደር በኾነው አገር ላይ የሚቃጣና የሚደርስ አደጋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ደኖቻችን አልቀው አገር ዕርቃኗን ከመቅረቷ በፊት የሚመለከተን አካላት በሙሉ ርብርብ ልናደርግ ይገባል፡፡

ደን እንደ ኢትዮጵያ ከሰሐራ በታች ላሉ ሀገራት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በመኾኑም መንግሥታችን የእነዚህን የተፈጥሮ ደኖች ጥቅም በሚያራምደው የልማትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ አብሮ መቀመር ይኖርበታል፡፡ ይህን ስንል ግን እስከ አሁን ምንም ዓይነት ሥራ አልተሠራም በማለት አይደለም፡፡ በእኛ እምነት ቀመሩ አደጋ ለተቃጣባቸውና እየተጎዱ ላሉ ደኖች አስቸኳይ የማዳንና የመጠበቅ እርምጃ በመውሰድ ይጀምራል፡፡ ከዚህም ጋር ሁሉንም ተጠያቂ የሚያደርግ ጠንካራ የደን ሀብት አጠቃቀም ፖሊሲ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች ሀገራት እንደሚታየው ባለ ሀብቶችና ተቋማት የተፈጥሮ ደኖችን በማልማት ተግባርም እንዲሰማሩ በልዩ ልዩ መንገድ ቢያበረታታና መንግሥታዊ ድጋፍም ቢያደርግ መልካም ነው፡፡ ከዚህም ጋር ደኖቹን ለዘመናት ጠብቀው ላቆዩ /በእኛ ረገድ ለገዳማትና አድባራት/ ሙሉ የባለቤትነት መብት ቢሰጥ ለደኖቹ መጠበቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል እንላለን፡፡

ቤተ ክህነታችንም በስሩ በሚገኙ አድባራትና ገዳማት ተጠብቀው ከመንፈሳዊ ጥቅማቸው አልፎ ለሀገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ሲሰጡ ለቆዩ ደኖች ትኩረት ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ ደኖች ለቤተ ክርስቲያኗም ኾነ ለሀገር ሲሰጡ ከኖሩትና እየሰጡ ካሉት መጠነ ሰፊ ጥቅም አንጻር ቤተ ክህነቱ ለደኖች የሚሰጠው ትኩረት የበለጠ መኾን አለበት፡፡ እንደሌላው ሀብቷ ሁሉ ደኖቿ እንደትላንትናው በሁሉም ርብርብ ተጠብቀው ይቆያሉ ብሎ መቀመጥ የዋሕነት ነው፡፡ ዛሬ ሌላ ቀን ከመኾኑ አንጻር እነዚህ ደኖች የሚጠበቁበትን ሥልት መንደፍና ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ሥልቱም በዋና መሥሪያ ቤቱ ደረጃ በጉዳዩ ላይ የሚሠራ ጠንካራ ተቋም ማቋቋምንም ይጨምራል፡፡

ደኖቻችንን በመጠበቅ ረገድ በባለቤትነት ለዘመናት ተንከባክበው ከጠበቁ ገዳማትና አድባራትም የሚጠበቅ ተግባር አለ፡፡ የመጀመሪያው ተግባር ከአካባቢያቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመተባበር የደን ይዞታቸውን ሕግ ባወቀው መንገድ እንዲከበሩ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለልዩ ልዩ አገልግሎት ለማዋል በሚል ደኖቹን ከመጨፍጨፍ ተግባር መታቀብ ነው፡፡

ለዘመናት ተጠብቀው የኖሩት ደኖች ተጠብቀው እንዲኖሩ በደኖቹ አካባቢ የሚኖረው ሕዝብም ከፍተኛ ሓላፊነት አለበት፡፡ ደኖቹን ከነሙሉ ሀብታቸው ጠብቀው ያቆዩት ገዳማውያን ወይም የአድባራቱ አለቆችና ካህናት ብቻ አይደሉም፡፡ አሁን በደኖቹ አካባቢ ያለው ሕዝብ አያቶችና ቅድመ አያቶች ጭምር እንጂ፡፡ በመኾኑም ሕዝቡ ከመካከሉ ደኖችን በመቁረጥ ለማገዶና ቦታውን ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚያውለውን በተለመደ ባሕሉ ማረምና ችግሩን የሚያቃልልበትን አማራጭ መፍትሔ አብሮ መዘየድ ያስፈልገዋል፡፡ ደኑ ዛሬ ተቆርጦ የዛሬን ችግር ሊያቃልለት ይችላል፡፡ ነገር ግን በደኑ መቆረጥ መሪር ዋጋ የሚከፍሉት ልጆቹና የልጅ ልጆቹ መኾናቸውን ሊረዳ ይገባዋል፡፡
በአጠቃላይ ደኖቻችን /በተለይ በተራቆተው የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙት/ ለአካባቢው ሕዝብ ምግብ፣ መጠጥ፣ መድኃኒት፣ የማኅበራዊ እሴቶቹ ማከናወኛ፣ ለሀገርም የኢኮኖሚ ዋልታና የዕውቀት አፍላጋት ስለኾኑ ሁሉም ጥብቅና ሊቆምላቸው ይገባል እንላለን፡፡ ከተለያዩ ሪፖርቶች እንደምንረዳው የቀሩትን ጥቂት ደኖች ማጥፋት ሳይኾን፤ ቆዳው ተልጦ፣ ሥጋው ተበልቶ፣ የገጠጠው አጥንቱም እየተፈረፈረ ያለውን መሬታችንን ዕርቃን የሚሸፍኑ ደኖችን ባስቸኳይ ማልማት አለመጀመር፤ የተጀመሩትን ጥረቶችም ውጤታማ የሚኾኑበትን አግባብ አለማፋጠን የትውልድ ወንጀል ነው፡፡ ስለዚህ መሬታችን ዕርቃኑን እንዳይቀር፤ ዕርቃኑንንም ለልጆቻችን እንዳናስረክብ አደራ አለብን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር