“ለሦስት ቀናት በጾምና በጸሎት በአንድ ልብ ሆነን ወደ ፈጣሪያችንን እንድንጮህ አደራ እንላለን”- ቅዱስ ሲኖዶስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የጾምና የምሕላ አዋጅ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

“የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ ለጾም አዋጅ ነገሩ!

ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ።”

ትንቢተ ዮናስ ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፭

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በተከሰተው ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ መዋቅሮቿን በመጣስ መፈንቅለ ሲኖዶስ በማድረግ በሕገ ወጥ መንገድ ኤጲስ ቆጶስነት ሢመት በሰጡትና በተሾመ ግለሰቦች ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ቃለ ውግዘት ማስተላለፉ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ እነዚህ ሕገ ወጥ ቡድኖች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ካለመቻላቸውም በላይ በመንግሥት ኃይሎች በመታገዝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታስተዳድራቸውን መንበረ ጵጵስናዎችንና ቢሮዎችን በኃይል በመውረርና በመስበር ከፍተኛ ጥፋት እያደረጉ ከመሆኑም በላይ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችን ሠራተኞች ካህናትና ምእመናን በማሰርና በማንገላታት ላይ ይገኛል፡፡ መንግሥትም ሕግ ከማስከበር ይልቅ ለሕገ ወጥ ቡድኖች ድጋፍ በመስጠት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና መብት ሊያስከብር ስላልቻለ ሁሉን ማድረግ ወደሚቻለው አምላካችን በመማፀን ጸሎትና ምሕላ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ተረድቷል።

በመሆነም ጾመ ነነዌን ምክንያት በማድረግ በመላው ዓለም የሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያን ጥቁር ልብስ ብቻ በመልበስ በጾምና በጸሎት ምሕላ በመያዝ በቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት በመገኘት ወደ እግዚአብሔር ጾም፤ ጸሎትና ምሕላ እንድታቀርቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ጥቁር ልብስ  የምንለብሰው በመከራ መጽናት ለመግለጽ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ጥቁር የእውቀት ምልክት ነው፡፡ ተማሪዎች አውቀናል ሲሉ ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፡፡ እኛ ከእውቀት በላይ የሆነውን አምላካችንን በመማፀን ከዚህም ማንም ሊያናውጽን እንደማይችል የምናረጋግጥበት፤ ጥቁር የእውነት ምልከት ነው ዳኞች እውነት እንፈርዳለን ሲሉ ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፡፡ እኛም መከራው የሚያሰቅቀን ሳይሆን ይበልጥ ልንጸናና ልንበረታ የሚገባ መሆኑን ለዓለም ሕዝብ የምናሳይበት በመሆኑ ከጥር ፳፱ እስከ የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለሦስት ቀናት በጾምና በጸሎት በአንድ ልብ ሆነን ወደ ፈጣሪያችንን እንድንጮህ አደራ እንላለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. አዲስ አበባ