“መንፍስ ቅዱስ እናንተን ጳጰስ አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ …ተጠንቀቁ” (ሐዋ.፳፥፳፰)

ቀሲስ ሀብታሙ ተሾመ
ጥር ፳፮፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ከዚህ ኃይለ ቃል ሦስት ነገሮችን እንማራለን፤ አንደኛ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር አምላክ በደሙ ዋጅቶ የመሠረታት መሆኑን፣ ሁለተኛ ጳጰስ አድርጎ የሚሾም መንፈስ ቅዱስ መሆኑን፣ ለመንጋውና ለራሳችን መጠንቀቅ አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን መሰነባባቻ ባደረገው ንግግር ይህን ኃይለ ቃል ተናግሯል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሦስት ሺህ ዘመናት ውስጥ የቆየው ቀኖና፣ሥርዓተ ሢመት፣ ትውፊት ቅብብሎሽ በአሁኑ ዘመን ለመሻር መንጋውን እየበተነ አባቶችን እየሸረሸረ ያለውን ክስተት ሁሉ በየደረጃው ያለው የድርሻውን ለመወጣት ከማንኛውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት የምንነሣበት ጊዜ መሆኑን ነው፡፡

፩. የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአገራችን ኢትዮጵያ ባለውለታ ስለመሆኗ፡-

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአኩሪ ታሪክ፣ የድንቅ ሥልጣኔዋ፣ የባሕልና ሃይማኖተኛ ሕዝቧችዋ አኗኗር ልዩ የሚያደርጋት በራሷ ሥርዓት ስለምትመራ የቆየች አገር በመሆኗ ነው፡። ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ “ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ያለው የጸሎት ሥርዓት አንዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ነው። (መዝ.፷፯/፷፰፥፴፩)

በተጨማሪ ብዙ የታሪክ መረጃዎች እንደሚያስረዱት በኢትዮጵያ ነፃ መንግሥት የተመሠረተው ከ ፬፼፭፻፳፪ (ዐራት ሺህ አምስት መቶ ሃያ ሁለት) ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። የዛሬይቱ አክሱም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ዋና መዲና፣ የሥልጣኔ መገኛና የክርስትና እምነት መሠረት እንደሆነች ዛሬ የሚታዩት የሕዝቧ ኣኗኗርና ሃይማኖታዊነት፣ ታሪካዊ ቅርሶችዋ፣ የቆሙት ሐውልቶችዋና ልዩ ልዩ የሥነ ጥበብ ሥራዎቿ ሲመሰክሩ አክሱም አሁንም ዋነኛ የሃይማኖት መንጸባረቂያ ቅድስት ቦታ ነች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ሊቃውንትና የተማሩ ቀሳውስት ያላት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ከሰላሳ ሺህ በላይ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ከሦስት መቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ቀሳውስት ወደ ሃምሳ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ምእመናን ያላት አገር ስትሆን በዚህም ከምሥራቃውያን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ አገሮች በምእመናን ብዛት የቀዳሚነትን ሥፍራ ይዛለች። በዚያው ልክ ግን ቀኖናዋን የሚጥስ ሲበራከት ለመዋጋት ተፋልመን “አንድ ቅዱስ ሲኖዶስ፣አንድ ፓትርያሪክ” የሚለውን ልናስጠብቅ ያስፈልጋል፡፡

አገራችን በቅኝ አገዛዝ እንዳትያዝ ነጻነቷ ተጠብቆ የኖረው በሕዝቦች አንድነትና አኩሪ ታሪክ ጀግንነት ሲሆን አንድ አገር፣ አንድ ሕዝብ፣ ሰላምና ፍቅር በተግባር ያስተማረችው ደግሞ ይህች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅድስት ቤት ክርስቲያን ናት፡፡ ሆኖም ይህ ውለታ ተረስቶ በአንድ በኩል ቀኖናዋ፣ ሥርዓቷና ቀኖናዋ ከሥር መሠረት እንዲጠፋ በሌላ በኩል ደግሞ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው የተለዩት ቤተ ክርስቲያኗን በሕገ ወጥ አንዲወሩ እየተደረገ ያለ ሴራ ዝም ብለን ልናየው የሚገባ አይደለም፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ እየተገደለና እየተሰደደ የቆየ አሁን ደግሞ መልኩን ቀይሮ የመከራ መናኸሪያ ሆና የጦርነት ቦታ እንድትሆን እያደረገ ያለውን ማንኛውንም ኃይል ለመከላከል ከእስካሁነ የበለጠ መታገል ይኖርብናል፡፡ ሆኖም ግን የወሊሶው ”ሢመተ ጵጵስና” ክስተት የሚያሳየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በራሷ ሥርዓት እንዳትመራ፣ አንዳንዶች ጳጳሳት ከሥርዓቷ እንዲያፈነግጡ የሚያደረገው ምንድን ነው? ማኀበራዊ ቀውስ ወይስ ኢኮኖሚያዊ ወይንስ ፖለቲካዊ? የትኛው እንደሆነ በዓይን ብሌን መመልከትና ችግሩን ለይቶ መጋፈጥ ትልቁ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡

፪. ከጥንት ጀምሮ ቀኖና ዶግማዋን አስጠብቃ የቆየች ስለመሆኗ፡-

ቀደም ሲልም ምእመናንን ተስፋ ለማስቆረጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሲፈትናት መቆየቱ የሁለተኛው ፓትርያርክ ቅዱስ ወብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ በ፲፱፻፷፮ ዓ.ም በኢትዮጵያ ወታደራዊው አብዮት ፈንድቶ ንጉሠ ነገሥቱ ግራማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ መስከረም ፪ ቀን ፲፱፻፷፯ ዓ.ም ከሥልጣን ሲወርዱ ወዲያው የቤተ ክርስቲያኗም ንብረት ተወረሰ። ያንጊዜ በኢትዮጵያ በአንድ ቀን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅደስት ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ሁሉ በነቂስ ቢወጣ ማንኛውም ምድራዊ ኃይል ሊቋቋመው አይችልም ነበር፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ፓትርያርኩንም ከሥልጣን ከማውረዱ በፊት ደርግ “የተሐድሶ ጉባኤ” የሚል ኮሚቴ አቋቁሞ በተለያየ ክፍል በእርሳቸው ላይ የማይገታ አመጽና አድማ ሲቀሰቅስ ከቆየ በኋላ በየካቲት ወር ፲፱፻፷፰ ዓ.ም የደርግ መንግሥት “ሲጠበቅ የቆየ ፍርድ” በሚል አዋጅ አስሮ ቀደም ሲል “የተቀባ ፓትርያርክን ሞት ብቻ ነው የሚሽረው” የሚለውን ሥርዓት በሚቃረን ሁኔታ ከሥልጣን አውርደው “የተቀባ ፓትርያርክ ሳይሞት በላዩ ላይ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም” የሚለውን ሥርዓተ ቀኖና ጥሰው ሰኔ ፴ ቀን ፲፱፻፷፰ ዓ.ም ሦስተኛው ፓትርያርክ እንዲሾሙ አደረጉ። ያኔ በአንደንት አለመነሣታችን ዛሬ ሥር ነቀል ቀኖና ማፍረስ ተጀመረ፡፡

ይህ ጉዳይ ቤተ ክርስቲን በሥርዓቷ እንዳትመራ መንግሥት መዋቅራዊ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ለራሱ የሚፈለገውን በማድረግ ተጽእኖ እየፈጠረ ሥርዓት አልባ እንዲትሆን ማድረጉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ይህ ብቻ እይደለም በሐምሌ ፯ ቀን ፲፱፻፸፩ ዓ.ም ሁለተኛው ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ በደርግ ተገደሉ። አሁንም የቅደስት ቤተ ክርስቲያን “አንድ መንበር አንድ ሲኖዶስ አንድ ፓትርያሪክ፣ አንድ ሲኖዶሳዊ ጵጵስና ሹመት” የሚለው እንደጠፋና ክልልዊ ፓትርያሪክ እንዲሾም የተጀመረው በሕግ ወጥ መንገድ በክልል እንዲስፋፋ፣ አባ እስጢፋኖስ ከመነበረ ጵጰስናቸው ሲሔዱ መከልከላቸው ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ጳጳስ መንግሥት በራሱ የፈለገውን ለመመደብ ሂደት ላይ መሆኑ ማሳያ ነው፡፡

ስንገድል ዝም፣ ስንሰደድ ዝም፣ ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል ዝም ብለን ለወዲፊት ለውጥ ተስፋ ብናደርግም በምትኩ ከእነ ጭራሹ በቀኖና ጥሰት የተነሡትን እየደገፈ ሕጋዊ ዕውቅና ያላትን ቤተ ክርስቲያን በእንደዚህ አይነት ሕገ ወጥ ተግባር ስትትራመስ ዝም ብሎ ማየት ሊበቃን ይጋበል፡፡

፫. ከባለፈው ታሪክ ተመልከተን የዛሬውን ክፍተት መሙላት ግድ ስለመሆኑ፡-
በቤተ ክርስቲያን ቀኖና በመምራታቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተገድለዋል፤ ግን ለምን ተገደሉ? የሚለውን ጥያቄ ስናነሣ ከታሪክ ያገኘነው መልስ ጠንካራ ፓትርያርክ እንዲኖር በጊዜው ንጉሥ ስለማይፈለግ ነበር፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ በ፲፱፻፷፮ ዓ.ም በኢትዮጵያ ወታደራዊው አብዮት ፈንድቶ ንጉሠ ነገሥቱ ግራማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ መስከረም ፪ ቀን ፲፱፻፷፯ ዓ.ም ከሥልጣን ሲወርዱ ወዲያው የቤተ ክርስቲያኗም ንብረት ተወረሰ። ቅዱስ ፓትርያርኩ የቋንቋ፣ የጎጥ እና የብሔር ልዩነት ሳያደርጉ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዲጸኑ አስተምረው በልዩ ልዩ ሞያ ተሠማርተው አገራቸውንና ወገናቸውን እንዳገለገሉ ከዚህ በታች የተገለጸው ሕያው ምስክር ነው፡፡

 ያለምንም የብሔርና የቋንቋ ልዩነት ኢትዮጵያውያን የሚገለገሉባቸው መሠረተ ልማቶችን፣ የአገልግሎት ተቋማትንና የጥበብ እድ የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የልማት ሚና እጅግ እያደገ በመምጣቱ የቤተ ክርስቲያን ማደግ በሚመቀኙ በካድሪዎች ተጽእኖ የመንጋ ጠባቂውን እየተከተሉ ማጥፋት እንጂ ሌላ ችግር ፈጥረው አለመሆኑ የዐደባባይ ሐቅ ነው፤ ለመንጋውና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ ያለንም ለዚህ ነው፡፡

 በሀገር ውስጥ ሆነ በውጭ ለምእመናን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማሟላትና እንዲሁም በቤተ ክርስቲያናችን ትምህርትና እምነት አምልኮተ እግዚአብሔርን ለመፈጸም ለሚፈልጉ የውጭ አህጉር አማንያን አብያተ ክርስቲያናትን በማሳነፅና አገልጋዮችን በመላክ ከፍተኛ የሆነ የዕድገትና የጥንካሬ ታሪክ በማስመዝገባቸው ይህን መልካም ሥራ በቅደስት ቤተ ክርስቲያን እንዲኖር የማይፈልጉ ጭፍን ጥላቻ ያላቸው አካላት ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ በመፈለጋቸው ሲሆን አሁንም እያየን ያለነው ይህንኑ ነው፡፡

 በምሥራቁ እና በምዕራቡ ዓለም የሥራ ጉብኝት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እንዲጎበኙ በማድረግ፣ በዓለም አቀፍ የሰላም ጉባኤዎች ላይ በመገኘትና ስለ ሰላም አስፈላጊነት በመመስከር፣ የቤተ ክርስቲያን ልኡካን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት ላይ እንዲገኙ በማድረግ፣ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያናችን ስለሌላው የክርስትና ዓለም፣ ሌላውም ስለ ቤተ ክርስቲያናችን በበለጠ እንዲያውቅ ለማድረግ ይከተሉት የነበረው አቋም ለቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ መታወቅን አትርፎላታል፣ ተፈላጊውን የተራድኦ ግንኙነት ለማጠናከር አስችሏታል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ተግባር የሚገልጹ መጽሔቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየታተሙ ለውጭው ዓለም እንዲሠራጩ አድርገዋል፡፡ ግን ይህ መልካም ሥራቸው ያስገድል ነበር ወይ? መልስ ኅሊና ላለው ሰው ሁሉ ነበር?

 ለዘመናት የምእመናን ጥያቄዎች ሆነው ሲያነጋግሩ የነበሩ ጉዳዮች ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲያሳልፍባቸው በማድረግ በኩል የሚጠቀሱ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ከሰባቱ አጽማዋት አንዱ የሆነው ጾም ገሃድ፣ ጾመ ነቢያት የሚገባው በየዓመቱ ኅዳር ፲፭ እንደሆነና ዓሣ በጾም ወራት እንደማይበላ በምልዓተ ጉባኤ አቅርበው ያስወሰኗቸው ውሳኔዎችን የማይወዱ ተጻራሪ ኃይሎች በተደረገ ሤራ እንዲጠፉ ስለፈለጉ በእኩይ ሴራ ተገደሉ፤የሚደረስላቸው አልነበረም፡፡

 ለቤተ ክርስቲያን የህልውና አደጋ ጋርጦ የነበረው የወቅቱ መንግሥት ርእዮተ ዓለም፣ በሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ያደረሰው ጥፋት በእኛዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ እንዳያደርስ በጸሎት፣ በጥበብ እና በትዕግሥት በታለፈበት አመራራቸው ቢቀጥሉ ቤተ ክርስቲያን ኃያልነቷና ህልውናዋ ተጠብቆ መቆየቷን የሚጠሉ የውስጥም የውጭም አካላት በመነሣታቸው በሴራ ተገደሉ፤ ይህንን ዛሬም ያልነቃን ከሆነ መቼም የምንነቃ አይደለንም፡፡

 ቅዱስነታቸው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሀገረ ሙላድ እያላቸው፣ ተወልጄ ያደግሁበት ቦታ ይህ ነው ብለው ከመናገር ይልቅ በፍጹም ኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ ያምኑ ስለነበር የካህኑ መልከ ጼዴቅን አሰረ ፍኖት በመከተል፤ እንደ አብርሃም አበ ብዙኃንነትን አጉልተው በማሳየት ሁሉን እኩል የመመልከት ብቃታቸው በመንግሥት ኃይሎች በመጥፎ እይታ በማየታቸው እንዲገደሉ ሆነ፡፡

 በተጨማሪም አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ፬ኛ ፓትርያርክ ሆነው በአግባቡና በሥርዓቱ ነሐሴ ፳፱/፲፱፻፹ ዓ.ም. ተሾሙው ኢትዮጵያ ውስጥ በመንበራቸው ላይ ለሦስት ዓመታት ብቻ ቆይተው ከዚያ በኋላ ወታደራዊው መንግሥት ወድቆ ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ ከጥቂት ወራት በኋላ ከአዲሱ መንግሥት በፖለቲካዊ ጫና መንበራቸውን ለቀው ነሐሴ ፳፰/፲፱፻፹፫ ዓ.ም. ከአገር ወጥተው መሰደዳቸው ሁለተኛው የፖለቲካ ሁከት ተጠቃሽ ነው። ይህን ክስተት በንቃትና በአንድነት በኅብረት እንዲቆም አለመደረጉ በቅደስት ቤተ ክርስቲያን አንድንት ላይ ችግሩን የበለጠ እንዲባባስ አድርጎታል፡፡

 ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ለ፳፮ ዓመታት አሜሪካ ውስጥ ሲቆዩ ሁለት ሲኖዶስ እንዲፈጠር ያደረገው የኢሐድግ መንግሥት ለራሱ እንዲመቸው በተጽእኖ እንዲሾም ያደረገ ሲሆን በዚሁ ተጽእኖ ሁለት ሲኖዶስ የኢትየጵያና የአሜሪካን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሲኖዶስ እንዲከፈል ማድርግ ሌለኛው ተጽኖ ነው። የአሁኑ ጠቅላይ ዶ/ር ሚኒስተር ዐብይ አህመድ ሁለቱን ሲኖዶሶች አንድ እንዲሆኑ ማድረጋቸው መቼም ቢሆን የማይዘነጋ መልካም ተግባር ነው፡፡ አሁን ባለው የወሊሶው “ሢመተ ጰጵስና” በአንድ አገር ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ሲኖዶስ፣ ሁለት ፓትርያሪክና ሁለት መንበር እንዲፈጠር መደረጉ እጅግ አሳፋሪም አስገራሚም ክስተት በመሆኑ መንግሥት ሕጋዊ ከለላ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ለዚህ ጉልህ ድርሻ ያደረገው የቱ ነው? የሚለውን ሲመረመር የራሷ የቤተ ክርስቲያኗ ሦስት ጳጳሳት ለዚህ ኢ-ቀኖናዊ ተግባር ያነሣሣቸውን መነሥኤ ለይቶ መጋፈጥ ተገቢ ነው፤ ‘”የእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ’’ ዓይነት እሳቤ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በመሆኑም የወሊሶው ሢመተ ጵጵስና ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሰጠው ውሳኔ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር በመቆም ኅብረታችንን አንድንታችንን በማጠናከር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ እግዚአብሔር ይርዳን፤ አሜን፡፡

፬. የጥንቷን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለነገ ለማስቀጠል ምን ይጠበቅብናል?

የጥንቷ ቅድሰት ቤተ ክርስቲያን በሦስቱ ዘመናት በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪትና በሕገ ወንጌል ያለውን መንፈሳዊነትን መጠበቅ ማስጠበቅ ትልቁ ድርሻችን ነው፡፡ ከዘያ ቀጥሎ በየደረጃው ያሉት የቤተ ክርስቲያን አመራር (ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ሀገረ ሰብከት፣ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ቤተ ክህነትን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መዋቅሯን፣ ሕጓን፣ ቀኖናዋንና ሥርዓቷን ለመጠበቅና ማስጠበቅ የሰጡትን አመራረነት ለመፈጽም ሁሉም የደርሻውን ሊወጣ ያስፈለጋል፡፡

ጥበበኛው ሰሎሞን ‘’አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንብር ምልክት አታፍልስ’’ (ምሳ.፳፪፡፳፰)፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በፍትሕ መንፈሳዊ ወቅታዊ የቀኖና ጥሰቶች ላይ ጥር ፲፰ ፳፻፲፭ ዓ.ም. በተሰጠው አስቸኳይ ውሳኔ እኛ ምእመናን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕጓን መብቷን ማስጠበቅ የመፈጸም ድርሻችንን በመወጣት እንደ ዐይን ብሌን እርስ በእርሳችን መጠባባቅ ይኖርብናል፡፡ በተናጠል አባትም ሆነ ልጁ አመራርም ሆነ ምእመን መምህርም ሆነ ደቀ መዝሙር እንዳንጎዳ ኅብረታችንን ልናጠናከር ይገባል፡፡

ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት የሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕዝብና አሕዛብን፣ የሰው ልጅ ሁሉ በቋንቋ፣ በቀለምና በጐሣ ሳይከፋፈሉ በአንድነት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና አግኝተው ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ የተወለዱ በማየ ገቦ የተጠመቁ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ልዩነት በሌለባት በደመ ክርስቶስ የተመሠረተች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በየዘመናቱ የተነሣባትን ፈተና ሁሉ ያሳለፈችውን ዛሬም የጥንቱዋን ቤተ ክርስቲያን የነገዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሆና እንዲትቀጥል እያዘከርን መኖር ከምንጊዜውም በላይ በእጅግ መተባባር፣ መናበብና መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡

ከቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ ከኦርቶዶክስ ትምህርተ ሃይማኖት በተለየ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን በጐሣና በቋንቋ የመለየት ሂደት ቤተ ክርስቲያን ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ጠባይዋ፣ ታሪኳንና ሥርዓቷን በማይመጥን፣ ከሕግ መንፈሳዊ ውጭ በሆነ መልኩ የሚሰነዘርን ጥቃት የውጭም የውስጥም የቅደስት ቤተ ክርስቲያን ልጆችም በየደረጃው ከሚገኙ የቤተ ክህነትና የቤተ መንግሥት አመራሮች ጋር በመናበብ ችግር ፈጥረው የተወገዙት በታቻለ መጠን በይቅርታ እንዲመለሱ ካልተቻለ ደግሞ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ለቤ ተክርስቲያን ዘብ በመቆም የቅዱሳን ሐዋርያትን፣ የቅዱሳን ሰማዕታትን ልጆች ሆነን መኖር ግደታ የሆነበት ደረጃ ላይ ደረሰናልና ልንበራታ ያስፈልጋል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ውስጥ ለሀገር አንድነት፣ ለፍትሕ፣ ለጥበብ፣ ለሕዝብ ትስስር፣ ለማኅበራዊ ዕድገት፣ ለጤና፣ ለሥነ-ምግባር መሠረት እና ዐምድ፤ ምሰሶ እና ግድግዳ ሆና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈራች፣ የተከበረች እና የተወደደች፣ ዕሴቷ እና ዕምቅ የዕውቀት ሀብቷ በምሁራን የታወቀ፣ በትምህርተ ዓለም ሳይቀር የተቀረጸ፣ በእውነተኛ ሊቃውንት የተመሠከረ፣ ቅርሶቿ የተመዘገቡላት ናት፡፡ ቢሆንም ግን ይህን ሁሉ በሒደት ለማጥፋት እየተካሔደ ያለውን የቅደስት ቤተ ክርስቲያን የቀኖና ጥሰት ተስፋ በመቁረጥ ጥሰቱን ትክከል እንደሆነ ተደርጎ መገደሉን፣ መሰደዱንና የቤተ ክርስቲያን መቃጠሉን፣ የቅዱስ ሲኖዶስ መካፋልን አንድንለምደው የተሰነዘረብንን ጥቃት መመከትና አንድቷን ቤተ ክርስቲያን ለመበታተን የሚደረግውን ከምንጊዜውም በላይ ነቅተን መነሣት ይጠበቅብናል፡፡

በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ከፍተኛውና ሐዋርያዊ ተልእኮ ደረጃው ያሉ የቅደስት ቤተ ክርስቲያን አመራር እስከ ምእመናን ኅብረት ተጠናክሮ መሠረተ እምነትን፣ ሃይማኖታዊ ቀኖናን፣ የአስተዳደር ሥርዓት ሁሉ በጣሰ መንገድ በማኅበረሰብ ዕድገትና አስተዳደር ውስጥ ከሕዝብ ጋር የቆመች፣ ከፖለቲካ የጸዳች መንፈሳዊና ሕዝባዊት ተቋምነቷን በመካድ ከፍተኛ የሆነ ሕገ ወጥ ድርጊት፣ ተቋምን የመናድና መዋቅሯን የማፍረስ ተግባር የሚፈጽም ማንኛውም ምድራዊ ኃይል ዝም ብሎ መመልከት ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህም የየራሳችን ድርሻ እንድንወጣ በኅብረት ለመቆም መታገል የግድ የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ኢትዮጵያን የታደገቻት ይህች ቅደስት ቤተ ክርስቲያን ዋናውን ድርሻ የተወጣች ሲሆን ይህቸን ቤተ ክርስቲያን በቅኝ ግዞት ይዞ ‘’አንድን ቅዱስ ሲኖዶስን’’ እንደ ክልሎች ለመከፋፋል የተነሣውን ማንኛውንም ምድራዊ ኃይል ልንፋለመው ይገባል፡፡

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን ቅዱስ ሲኖዶስም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ያሉ መላው አህጉረ ስብከት፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ፣ የሊቃውንት ጉባኤ፣ የሕግ አገልግሎት መምሪያ፣ በዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የወጣቶች እና የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ መንፈሳውያን ማኅበራት፣ የምእመናን እና አገልጋዮች ኅብረት፣ ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን ለሀገር ሰላምና እደገት፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ህልውና መጠበቅና ማስጠበቅ ልንፋለም ይገባል፡፡

በተለይም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በደመ ክርስቶስ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ያለፈተና የኖረችበት ጊዜ እንደሌለ ቅዱሳት መጻሕፍትና የታሪክ መዛግብት ሲመሰክሩን በዘመነ ሐዋርያት ቢጽ ሐሳውያን፣ በዘመነ ሊቃውንት የተለያዩ መናፍቃን፣… በየጊዜው እየተነሡ ሲፈታተኗት ኑረዋል፡፡ አሁንም በግልጽ እንደሚታየው ከውጭም ከውስጥም በተደራጁ ምንደኞች ምእመናን ለማተራመስ የብሔርና የቋንቋ ልዩነት የሌለባትን ይህችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጎጥና የቋንቋ መለያ ለማድረግ እየተሠራብን ያለውን ሥራ በመገንዘብ የሰማዕታትን ጽዋ መቀበል ያስፈልጋል፡፡

በኢትዮጰያ በተለያዩ አህጉረ ስብከቶች በሕገ ወጥ መንገድ ብዙ ሕዝበ ክርስቲያን ተገድለዋል፤ ተሰደዋል፤ ቤተ ክርስቲያን ተቃጥሏል፤ ይህ ደግሞ በአንድ በኩል ተስፋ ቆርጠን እንድንተወው በሌላ በኩል ደግሞ እየተገደልን መኖሩን አውቀነውና ለምደነው እንዲጥል በሚመስል መልኩ ሲከናወን ቆይቷል፤ አሁን ደግሞ መዋቅርን በማጥፋት ቀኖናዋን መሻሩን አምነን እንድንቀበል እየተሞከረብን ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት አልፎ ሃይማኖትን የሚከፋፍል፣ የሀገር አንድነትን የሚሸረሽር እና የሚያፈርስ፣ ምእመናንን ከምእመናን፣ ካህናትን ከካህናት፣ ሊቃውንትን ከሊቃውንት ወጣትን ከወጣት የሚያጋጭና ደም የሚያፋስስ ፀጥታን የሚያናጋ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ላይ የሚያገለግሉ፣ ሁሉም ማኅበራት፣ ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን በቋንቋና በጎጥ ሳይከፋፈል አንዲት ቤተ ክርስቲያን በማለት እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ ሆነን በአንድነት ልንኖር ይገባል፡፡ “የሀገሩ ሊቀ ጳጳስ ካልፈቀደለት ኤጲስ ቆጶስነት መሾም አይገባውም፤ ይህን አፍርሶ ቢገኝ ሲኖዶስ ያወግዘዋል፤ ሹመቱም ይቀራል” በማለት በኒቅያ ጉባኤ ቀኖና በዘጠነኛው አንቀጽ መሠረት የተሰጠውን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲከበር ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ ሕጓን፣ ሉዓላዊ ሥልጣኗን እስከ አሁን የተጋፉትን ወደ ፊትም የሚጋፉትን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ለመፈጸምና ለማሰፈጸም ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ ሆነን የምንቆምበት ጊዜ በመሆኑ በተጠንቀቅ ልንጠብቅ ይገባል፡፡

በአጽራረ ቤተ ክረስቲያን ድርጊት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ እየኖሩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወይም በቦታው በመገኘት የጥፋት ድርጊቱ ተባባሪ የሆኑ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሆኑ ውጭ እየተደረገ ያለውን ተጽእኖና ጥቃት ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው ውሳኔ መሠረት ተገቢውን ክትትል በሚደረገው አፈጻጸም የድርሻችንን በከባድ አደራ እንወጣ፤ ቅዱስ ጳውሎስ ‘’የተሰጠህን አደራ ጠብቅ” እንዲል፡፡ (፩ኛጢሞ ፯፡፳) በየደረጃው የሚገኙ የቅድስት ቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ መነኮሳት፣ አገልጋይ ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበራት፣ ምእመናን እና ምእመናት ይህን ሕገ ወጥ አድራጎት ከመከላከል እና የቤተ ክርስቲያናችሁን ደኅንነት ከመጠበቅ በተጨማሪ ለዚህ ሕገ ወጥ አድራጎት ልዩ ልዩ ድጋፍ የሚያደረግ ተቋማት እና ግለሰቦችን አስፈላጊውን ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ የመከላከል ሥራችሁን እንድትወጡ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው ውሳኔ መሠረት ለመፈጸም የበኩላችንን እንድንፈጽም አምላከ ቅዱሳን ያበርታን፤ አሜን፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ቅድስት ቤት ክርስቲያንና ሀገራችንን ይጠብቅልን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፡- የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ በፁዕ አቡነ ጐርጐርዮስ ካልእ፣ ፲፱፻፸፰ ዓ.ም