ዕረፍተ አቡነ ሀብተ ማርያም
በተከበረች በኅዳር ፳፮ ቀን ንዑድ ክቡር ንጹሕ መነኰስ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አባታችን አቡነ ሀብተ ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። ይህም ቅዱስ አባት የትውልድ ሀገሩ የራውዕይ በምትባል በስተ ምሥራቅ ባለች ሀገር ውስጥ ሲሆን በዚያም ስሙ ፍሬ ቡሩክ የሚባል አንድ ደግ ሰው ነበረ። ይህም ከክቡራን ሰዎች ወገን የሆነ ሰው እጅግ ሀብታምም የነበረ ሲሆን በሕጋዊ ጋብቻ ያጋቡት ቡርክት የሆነች ስሟ ዮስቴና የምትባል ሚስት ነበረችው። እርሷም በበጎ ምግባርና ሥራ የተጌጠች ናት። ይህችውም ደግ እናታችን በሕግ ተወስና ሳለች በጽኑዕ ገድል፣ በጾም በጸሎት በምጽዋትና በስገድትም ትጋደል ነበር።…