ኪዳነ ምሕረት

የካቲት ፲፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የክርስቲያን ወገኖች ሁሉ አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቅ በዓልን ያደርጋሉ፡፡ መታሰቢያዋን ለሚያደርግ፣ ስሟን ለሚጠራ፣ ለድኆችና ለችግረኞች እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ድረስ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ልጇ ከመድኃኔዓለም ክርስቶስ ቃል ኪዳን ተቀብላለችና፡፡ ይህችም የከበረች እመቤታችን ተወዳጅ ልጇ ንጹሕ ሥጋዋን ተዋሕዶ ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ ፈጽሞ ስለእኛ መዳን ወዶና ፈቅዶ ያደረገውን መከራ ተቀብሎ ሙቶ ተነሥቶ ካረገና በአባቱ ዕሪና ከተቀመጠ በኋላ እርሷን ክብርት እናቱን ድንግል ማርያምን በደቀ መዝሙሩ በዮሐንስ ዘንድ ትቷት ነበር፡፡ ‹‹እነሆ ልጅሽ፣ እነኋት እናትህ›› ብሎ በአደራ እንዳስጠበቀው፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ትጸልይ ዘንድ ያለማቋረጥ ወደ ልጇ መቃብር ሁልጊዜ ስትሄድ ኖረች፡፡ ይኸውም ጎልጎታ ነው፡፡ አይሁድም በአዩዋት ጊዜ ቊጣንና ቅናትን ተመልተው በድንጋይ ሊወግሯትና ሊገድሏት ወደዱ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ከዐይናቸው ሠወራት፡፡ እንዳትጸልይም ተማክረው ከልጇ መቃብር ዘንድ ጠባቂዎችን አኖሩ፡፡ እርሷ ግን በየለቱ መሄድን አላቋረጠችም ነበር፡፡ ጠባቂዎቹም አያዩዋትም-የልጇ የጌትነቱ መጋረጃ ሠውሯታልና፡፡ ቅዱሳን መላእክትም መጥተው ያገለግሏታል፤ ጌታችንም ዘወትር ይጎበኛታል የምትሻውንም ሁሉ ይፈጽምላት ነበር፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱሳን መላእክት እመቤታችንን ወደ ሰማያት አሳረጓትና የጻድቃንን ማደሪያዎች ሁሉ አሳዩዋት፡፡ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ ወዳሉበት አደረሷት፡፡ ከአዳም ጀምሮ እስከዚያች ዕለት ድረስ በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን አባቶች ሁሉ ‹‹አንቺን ከሥጋችን ሥጋን፣ ከዐፅማችን ዐፅምን ለፈጠረልን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! የአምላክ ልጅ ከአንቺ ሰው በመሆኑ በአንቺ ድኅነትን አግኝተናልና ከጥፋትም የሕይወት ወደብ ሆነሽናልና…›› እያሉ ሰገዱላት፡፡

ከዚያም ወደ ተወደደ ልጇ የእሳት መጋረጃ ወደተተከለበት ወደጌትነቱ ዙፋን አደረሷት፡፡ ጌታችንም እጇን ይዞ ወደ ውስጠኛው መጋረጃ አስገብቶ ከጌትነቱ ዙፋን ላይ አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጣት፡፡ ያዘጋጀላትንም ዐይን ያላየው ጆሮ ያልሰማው በሰው ልቡና ያልታሰበ ተድላ ደስታን ሁሉ ነገራት፡፡

ከጌትነቱ ዙፋንም በታች የእስራኤል ንጉሥ አባቷ ዳዊትን የነቢያትና የመላእክት ማኅበር እንደግድግዳ ከበውት በመሰንቆ ሲያመሰግን አየችው፡፡ እንዲህም ይላል፤ ‹‹ልጄ ስሚ በጆሮሽም አድምጪ፣ ወገንሽን የአባትሽንም ወገን እርሺ ንጉሥ ደም ግባትሽን ወዷልና እርሱም ጌታሽ ነውና፡፡››

ዳግመኛም የሥቃይን ቦታ ያሳዩዋት ዘንድ መላእክት ከዚያ ወሰዷት፡፡ ለሰይጣንና ለሠራዊቱ በእርሱ ጎዳና ለሚጓዙ ሁሉ ወደተዘጋጀ ወደጨለማው ዳርቻ አደረሷት፡፡ እመቤታችንም ማርያምም ‹‹ወዮልኝ ወደዚህ እንዳይመጡ ለሰው ልጆች ሁሉ ማን በነገራቸው!›› አለች፡፡ መልአኩም ‹‹እመቤቴ ቡርክት ማርያም ሆይ! ለአንቺም ከአንቺ በኋላም በቃልኪዳንሽ ለሚታመኑ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ይኖራልና አትፍሪ›› አላት፡፡ ከዚህም በኋላ ወደቦታዋ መለሳት፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ስለኃጥአን እጅግ እያዘነች ኖረች፡፡ እንደዛሬዩቱም የካቲት ፲፮ ቀን በጎልጎታ ቦታ ቁማ በተወዳጅ ልጇ የመቃብር ቦታ ቆማ ወደልጇ እንዲህ ብላ ለመነች፡- ‹‹ልጄ ሆይ! በእግዚአብሔር አባትህ በክርስቶስ ስምህ ከአንተ ጋርም ህልው በሆነ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ እማጽንሃለሁ፡፡ በማሕፀኔ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ተሸክሜሃለሁና ጡቶቼንም አራት ዓመት እየጠባህ አድገሀልና እለምንሃለሁ እማልድሃለሁ፤ ዓለም ሁሉ ሊሸከምህ የማይችል ሲሆን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በተሸከመችህ ማሕፀኔ ያለ ድካም ከእኔ በመውጣትህ በመወለድህ በአሳደጉህ ጡቶቼ በሳሙህ ከንፈሮች በአቀፉህ እጆቼ ከአንተ ጋራ በተመላለሱ እግሮቼ አማፀንሃለሁ፡፡ በውስጡ በተኛህበት በረት በተጠቀለልክበት ጨርቅ አማፅንሃለሁ፡፡ የምወድህ ልጄ ሆይ፥ በልቡናዬ ያለውን ሁሉ ትፈጽም ትመጣ ዘንድ ወዳንተ ፈጽሜ እማልድሃለሁ፡፡››

የብርሃን እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲህ ብላ በጸለየች ጊዜ እነሆ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወረደ፡፡ ከእርሱም ጋራ አእላፋት መላእክት አሉ፡፡ በዙሪያውም ሆነው ያመሰግኑታል፡፡ እርሱም ‹‹እናቴ ማርያም ሆይ! ምን ላድርግልሽ?›› አላት፡፡ እመቤታችንም ለተወደደ ልጇ እንዲህ ብላ መለሰችለት፡- ‹‹ልጄ ወዳጄ ሆይ! ጌታዬና ፈጣሪዬ አለኝታዬና መጠጊያዬ በእናቴም ማሕፀን ሳለሁ በአንተ ጸናሁ፤ አንተም ጠበቅኸኝ፤ ሁልጊዜ ስም አጠራሬ አንተ ነህ፡፡ አሁንም ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ፤ ቃሌንም አድምጥ፡፡ እኔ እናትህ እኔም አገልጋይህ የምለምንህ ይህ ነው፡፡ መታሰቢያን ለሚያደርጉ፣ በስሜ አብያተ ክርስቲያናትን ለሚሠሩ ወይም የተራቆተውን ለሚያለብሱ፣ የተራበውን ለሚያጠግቡ፣ የተጠማውን ለሚያጠጡ፣ የታመመውን ለሚጎበኙ፣ ያዘነውን ለሚያረጋጉ፣ የተከዘውንም ደስ ለሚያሰኙ ወይም ምስጋናዬን ለሚጽፉ፣ ልጆቹንም በስሜ ለሚሰይም፣ በበዓሌም ቀን በማኅሌት ለሚያመሰግን አቤቱ ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን በሰውም ልቡና ያልታሰበውን በጎ ዋጋ ስጣቸው፡፡ በአማላጅነቴም የሚታመነውን ሁሉ ከሲኦል ነጻ አድርገው፡፡ ከአንተ ጋራ የደረሰብኝን ረኃቡንና ጥማቱን መከራውን ሁሉ አስብ›› አለችው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ‹‹እንዳልሽው  ይሁንልሽ፡፡ በሰጠሁሽ ቃል ኪዳን እንዳይታበል በራሴ ማልኩልሽ››  አላት፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት ይማረን፣ የብርሃን እናቱ ደንግል ወላዲተ አምላክ ከቃል ኪዳኗ ረድኤት በረከት ትክፈለን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፡ መጽሐፈ ስንክሳር ወርኃ የካቲት