‹‹በገሊላ አውራጃ በቃና መንደር ርግ ሆነ፤ ውኃውንም ወደ ወይንነት ለወጠው›› (ዮሐ. ፪፥፩-፲፩)

ጥር ፱ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ አውራጃ  በዳዊት ከተማ በቤተልሔም ምድረ ኤፍራታ ተወልዶ በሠላሣ ዘመኑ በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ተጠምቆ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ዐርባ መዓልት ዐርባ ሌሊት ጾመ ጸለየ፤ በጠላት ዲያብሎስ ተፈተነ። ፈተናውን ድል አድርጎ ሱባኤውን ፈጽሞ በወጣ በሦስተኛው ቀን ከእናቱ ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም እና ከቅዱሳን ሐዋርያቱ ጋር በመሆን በገሊላ አውራጃ በቃና መንደር በሠርግ ቤት ተገኝቶ ቤተ ከብካቡን በትምህርቱ በተአምራቱ ባረከ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ድንቅ ተአምር በቃና ዘገሊላ ያደረገው በገዳመ ቆሮንቶስ ሱባኤውን ፈጽሞ በወጣ በሦስተኛው ቀን የካቲት ፳፫ ቀን ነው። ይሁንና አባቶቻችን ሊቃውንት «የውኃ በዓል ከውኃ በዓል ጋር መቀናጀት አለበት» በማለት በጥምቀት በዓል ማግስት ጥር ፲፪ ቀን እንዲከበር አድርገውታል። እኛም ይህንኑ ቀን ጠብቀን በዓሉን በማክበር ላይ እንገኛለን።

በቃና ዘገሊላ የተደረገው ይህ ተአምር በዮሐንስ ወንጌል በምእራፍ ፪ ከቁጥር ፩-፲፩ ድረስ ተጽፎ ይገኛል። በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኘውና በዚህ ስም ሊጠራ የቻለው አምላካችን፣ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ሀገር ክፍል በምትሆን ቃና በተባለችው ቦታ  በፈጸመው   ተአምር  ምክንያት መነሻነት ነው።

ከቅዱስ መጽሐፍ ላይ ተጽፎ የሚገኘው ሙሉ ቃል እንዲህ ይላል፦ «በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሠርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት። እናቱም ለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም። ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ። ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው። ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።»

በቃና ዘገሊላ የተፈጸመው ይህ ሠርግ ሙሽራ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድናስብና እንድናስታውስ ያደርገናል። ሚዜው የሙሽራው አገልጋይ ነውና መጥምቁ ዮሐንስ ሙሽራ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ መደሰቱንና ሊያገለግለው የተዘጋጀ መሆኑን ሲያስረዳ ፦ «ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምጽ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ። እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል።» ዮሐ ፫፥፳፱-፴ ይለናል። በቃና ዘገሊላ በሰርጉ ቤት ተገኝቶ ተአምሩን የጀመረው ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ እና ከሐዋርያት ጋር አብሮ ነበርና አማላጅ እና ተማላጅ ማን እንደሆነ በልዩ ምሥጢር ተስተውሎበታል። ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ በተከታታይ ልዩ የሆነውን ብሥራት ሲያሰማ እንዲህ በማለት ጽፎልናል፦ በስድስተኛው ወር ማለትም መልአኩ ገብርኤል ካህኑ ዘካርያስን «ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል» ካለው በኋላ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በክብር ተገልጦ «ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ» ብሏታል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በአብሣሪው መልአክ በቅዱስ ገብርኤል እንደተነገራት በእውነት ጸጋን የተሞላች ናትና በሠርግ ቤት የጎደለውን የጓዳውን ምሥጢር ተረድታ የሠርጉ ሥነ-ሥርዓት በሠመረና በተዋጣለት ሁኔታ እየተከናወነ ድንገት የወይን ጠጅ በማለቁ ተጨንቀውና ግራ ተጋብተው አስተናባሪዎቹ በታወኩበት ሰዓት የጭንቅ አማላጅ ናትና ወደ ልጅዋ ወደ ወዳጅዋ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወር ብላ «ወይን እኮ የላቸውም» በማለት አሳስባ ባዶ የሆኑት የድንጋይ ጋኖች ውኃ ተሞልተው ጣፋጭ ወይን ጠጅ ተገኝቶባቸዋል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ «እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ። በማለት እንደጻፈልን ከድንቅ በላይ ድንቅ በሆነ ተዋሕዶ በሥጋ መገለጡ ከእመቤታችን ተወልዶ ነውና በልደቱ ጊዜ አብራ እንደነበረችው እንዲሁ ደግሞ በሞቱ ጊዜ ከእርሱ እንዳልተለየች እንረዳለን። (፩ጢሞ.፫፥፲፮) ይህንንም ወንጌላዊው ዮሐንስ «ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር።» (ዮሐ.፲፱፥፳፭) በማለት በጻፈልን መልእክት ለማወቅ ችለናል።

በመጀመርያ በልደቱ በኋላም በሞቱ ጊዜ አብራው የነበረች ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመኗን በሙሉ በፍጹም  እንዳልተለየችው ተአምሩን በጀመረበት በቃና ዘገሊላም አብራው ነበረችና ዛሬ ትውልዱ ሁሉ የሚኮራበትን የአማላጅነት ሥራ በቃና ዘገሊላ ፈጽማለች። «አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ» በሚለው ቃል ብዙዎች ተሰናክለውበት ቢገኙም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አምልተውና አስፍተው ምሥጢራትን የነገሯቸው የተዋሕዶ ልጆች ግን በእናትና በልጅ መካከል ያለውን የንግግር ዘይቤ ተረድተው እውነቱን ሲመሰክሩ ይኖራሉ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ከእግዚአብሔር ተልኮ የመጣውን አብሳሪ መልአክ «እንደ ቃልህ ይደረግልኝ» እንዳለችው ኢየሱስ ክርስቶስም እመቤታችንን «ከአንቺ ጋር ምን አለኝ» (እንደ ቃልሽ ይሁን) በማለት ጥያቄዋን መልሷል፤ ምልጃዋን ተቀብሏል። «ጊዚዬ አልደረሰም» በማለት ቢናገርም ስለ እናቱ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ሲል የእናቱን ልመና ተቀብሎ ተአምራቱን ፈጽሟል። እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሳይነግሯት በልባቸው ያለውን የምታውቅ እናት ናትና የሰርጉ አስተናባሪዎችን ኃዘን ተመልክታ ከልጇ ከወዳጇ አማልዳ የጎደላቸውን እንደሞላች ለእኛም ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል ብላ በተፈጸመላት ቃል ጎዶሏችንን ትሙላልን። የሰዎችን ጭንቅ አውቃ ሳይነግሯት ያማለደች እናት ስሟን ጠርተው ለሚለምኗትማ የበለጠ ታደርጋለችና ሁላችንንም በተሰጣት ጸጋ ታማልደን።

ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤቷን በረከቷን ያሳድርብን አሜን!!

 ምንጭ፡ የብፁዕ አቡነ ገሪማ ስብከት