በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

     

“ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፤ በማርያም ልደት ምክንያት ዛሬ ደስታ ሆነ!” (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)

በመምህር ብንያም

“አነ ጽጌ ገዳም ጽጌ ደንጎላት ዘውስተ ቄላት ወከመ ጽጌ ደንጎላት በማእከለ አስዋክ-እኔ የምድረ በዳ አበባ ነኝ በቆላ ውስጥ ያለ በሾህ መካከል የበቀለ የሱፍ አበባ ነኝ።” (መኃ.፪፥፩) ብሎ ነቢዩ ሰሎሞን እንደተናገረ ግንቦት አንድ ቀን በምድረ በዳ በአድባረ ሊባኖስ የበቀለችውን አማናዊት ንጽሕት የሱፍ ፣ የጽጌረዳ አበባ የሆነችውን በመዓዛዋ ጣዕም የዓለምን የኀጢአትን ሽታ ያስወገደችውን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት እናከብራለን፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን አስቀድሞ በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝቶ በመዝሙሩ ፮፥፲ ላይ “መኑ ይእቲ ዛቲ እንተ ትሔውጽ ከመ ጎሕ ሠናይት ከመ ወርኅ ወብርህት ከመ ፀሐይ” (ይህቺ እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጐበኝ፣ እንደ ጨረቃ የተዋበች፤ እንደ ፀሐይም የጠራች፣ ዓላማ ይዞ እንደተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ማን ናት?) በማለት እንደ ፀሐይ የሞቀ፣ እንደ ጨረቃ የደመቀ፣ ንጽሕናዋና ቅድስናዋ የመልኳ ደም ግባት በነቢያት ትንቢት አስቀድሞ የተጐበኘላት የእውነት ፀሐይ የክርስቶስ እናት የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብርና ደም ግባቷን እንደተናገረ፤ በሊባኖስ ተራራ በግንቦት ፩ በተወለደች ጊዜ ፊቷ በእጅጉ ያበራ ነበር፤ መዓዛዋም ከሽቱ ሁሉ ይበልጥ ነበር፡፡ የእመቤታችን ዜና ልደት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይደለም ፡፡በብዙ ሕብረ አምሳል እና ትንቢት ሲነገርላት የመጣች ምልዕተ ምሥጢር ናት እንጂ፡፡

ይኸውም ልደቷ በሦስት ክፍል ተነግሮላታል ፡፡

ሀ. በልበ ሥላሴ 

“እግዝእትነ ማርያም ነበረት እምቅድመ ዓለም በኅሊና አምላክ-እመቤታችን ዓለም ሳይፈጠር አስቀድማ በአምላከ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር” ተብሎ ተነግሮላታል።  እግዚአብሔር ይህን ዓለም ሳይፈጥረው ግብሩን ያውቀው ነበር እና የሚድንበትንም ከፍጥረት አስቀድሞ  በኅሊናው ያውቅ ነበር። እንዲህ ሲባል ግን ማወቅ እና ማሠራት ይለያያል። አወቀው ማለት አዳምን ክፉ አሠራው ማለት ግን አይደለም፡፡ ስንኳን እመቤታችንን ስለእኛ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር፦ “ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ መረጠን።” (ኤፌ.፩፥፬) ብሎ ተናግሯል፡፡ “እስመ እግዚእ ኀረያ-ጌታ መርጧታልና” እንድትመረጥ ሁና ብትገኝ ተመረጠች ብሎ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም ተናግሮላታል፡፡

ለ.በሥነ ፍጥረት ተነግሮታል፦ እመቤታችን በበርካታ ሥነ ፍጥረት ምሳሌ ተመስላለች።

ከረቂቁ  እስከ ግዙፉ ዓለም ድረስ ፡፡

ግብር እምግብር (ከተፈጠረ ነገር የተገኙ) ከተፈጠሩ ፍጥረታት በሰዓት እስከ ሚቆጠሩ ዕለታት ድረስ ፡፡

ከባሕር እስከ  የብስ፣ ከየብስ እስከ ባሕር ድረስ፡፡

ከዓለመ መላእክት እስከ ዓለመ ሰብእ ድረስ፡፡

ለዚህ ነው ሊቁ አባ ሕርያቆስ፦

“በመኑ በአምሳለ መኑ ናስተማስለኪ-በምን እና በምን እንመስልሻለን?” በማለት የተናገረው።

ሐ.በሕገ ልቡና እና በሕገ መጻሕፍት ተነግሮላታል።

ይህም በብዙ ኅብረ አምሳል እና በብዙ ኅብረ ትንቢት የተነገረው  ነው።

ኅብረ ትንቢት እንደሚከተለው ነው፦

“በአንተና በሴቲቱ በዘርህ እና በዘሯ መካከል ጠላትነትን አደርጋለው።” (ዘፍ.፫፥፲፭)

“ቀስቴን በደመና አደርጋለሁ” (ዘፍ.፱፥፲፫)

“እግዚአብሔርም በሴም ድንኳን ይደር።” (ዘፍ.፱፥፳፯)

“በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ትወልዳለች።” (ኢሳ.፯፥፲፬)

“ከእሴይ በትር ትወጣለች” …(ኢሳ.፲፩፥፩) ወዘተ በማለት ትንቢት ተናግረዋል።

በተለይም በጠቢቡ ሰሎሞን “ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስዩ” (መኃ ፬፥፰ ) ብሎ በአድባረ ሊባኖስ እንደምትወልድ በሚደንቅ ትንቢት ተናግሯል።

በብዙ ኅብረ አምሳል ደግሞ እንደሚከተለው ሲሆን በአምሳለ ሰዋስው (መሰላል) ለያዕቆብ (ዘፍ.፳፯፥፲፯)…በአምሳለ ሐመልማል ለሙሴ (ዘጸ .፫፥፫)

“በአምሳለ መሶበ ወርቅ፤ በአምሳለ ተቅዋመ ወርቅ፤ በአምሳለ ማዕጠንተ ወርቅ፤በአምሳለ ታቦት”ለሙሴ፡፡

በጠቅላለው በኦሪት ውስጥ የተመሰሉ ምሳሌዎች ለእመቤታችን አምሳል ናቸው፡፡

በዘመነ መሳፍንት እና በዘመነ ነገሥትም በብዙ ተመስላለች።

“በአምሳለ ጸምር ለጌዴወን” (መሳ.፮፴፭)

“በአምሳለ መሶብ ለኤልያስ” (፩.ነገ.፲፱፥፮)

“በአምሳለ ንግሥት ለዳዊት”(መዝ.፵፬፥፱)

“በአምሳለ መርዓት ‹ሙሽራ›ለሰሎሞን (መኃ፬፥፰)

“በአምሳለ ፈጣን ደመና ለኢሳይያስ” (ኢሳ.፲፱፥፩) ወዘተ በመሳሰሉ ምሳሌያት እየተመሰለች እየተነገረች ዘመነ አበውን በምሥጢር  እያለፈች አበውን በተስፋ እያጽናናች የመጣች እርሷ ናት፡፡

“ይእቲኬ መድኃኒት እንተ ኀሠሥዋ ወዖድዋ ነቢያት-ነቢያት የሿት እና የፈለጓት መድኃኒት ይህች ናት።” (፩.ጴጥ.፩፥፲) ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደነገረን፡፡ ራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔር ለአባታችን ለአዳም የሰጠው ዘለዓለማዊ ተስፋ የሚፈጸመው በእርሷ በኩል ነው።”ተስፋ ሕይወት ተሠርዐ-የሕይወት ተስፋ ተሠራልን።” ቅዱስ ያሬድ የሕይወት ተስፋም በድንግል ማርያም ተፈጽሟል።

“ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል-የአበው ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ።”እንዲል ደራሲው ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም. ስለሆነም ቀን ሲደርስ አንባ ይፈርስ እንዲሉ፦

አማናዊ ቃል ኪዳን ሊጻፍባት አማናዊት ብራና ፤

አማናዊ ካህን ሊያገለግልባት አማናዊት መቅደስ፤

አማናዊ ፀሐየ-ጽድቅ ክርስቶስ ለሚወጣባት አማናዊት  ሰማይ፤

አማናዊ ስንዴ ሊበቅልባት አማናዊት  ምድር።

ግንቦት አንድ ቀን ከቅድስት ሐናና ከቅዱስ ኢያቄም በፈቃደ እግዚአብሔር በብሥራተ መልአክ በሊባኖስ ተራራ  ተወለደች፡፡ ባሕርየ ሰብእን የፈጠረ ባሕርይዋን ሊዋሐድ ንጽሕት እናቱን ፈጠረ ፡፡ ፅንሰቷ በዘር በሩካቤ ቢሆንም ባሕርይዋ ሳያድፍ ጥንተ በደል ሳይደርስባት ተወለደች፡፡”እምጽቡር ጽሩየ ገብራ-ንጽሕት አድርጎ ሠራት።” “ከፈጠራት ጀምሮ በምንም በምን ከድንግልናዋ አልተለወጠችም።” (ሃይ.፶፫፥፳፪) ብሎ ሊቁ ቅዱስ ቴዎዶጦስ እንደተናገረ ፡፡አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም፦”ዐቀባ መንፈስ ቅዱስ እምከርሠ እማ-መንፈስ ቅዱስ ከእናቷ ማሕፀን ጀምሮ ጠበቃት።” (መ.ምሥ.፳፥፲)

ቀዳማዊት ሔዋን ያጣችውን ንጽሕና እመቤታችን ግን ሳይጎድልባት ይዛ ተወለደች፡፡

ስለዚህም ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም፦ ወመሠረተ ንጽሕነ ኮነ በማርያም ድንግል-የንጽሕናችን የቅድስናችን መሠረትስ በማርያም ድንግል ተደረገልን” አለ፡፡

አምላካችን ከበረከተ ልደቷ ያሳትፈን፡፡አሜን፡፡ይቆየን

 

“እግዚአብሔር ብርሃኔ ነው” ቅዱስ ዑራኤል

ጥር ፳፪፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

በቅዱስ ፈቃዱ ዓለምን የፈጠረው ሁሉን ቻይ አምላካችን እግዚአብሔር መላእክትን ከእሳትና ከነፋስ በቀዳሚት እሑድ ሲፈጥራቸው በነገድና ከተሞች ከፋፍሎ እንደነበርና ለእያንዳንዱም ሊቃነ መላእክት እንደሾመላቸው የመጽሐፍተ ፍጥረታት ይጠቅሳሉ፡፡

በብርሃንና በመባርቅት ላይ የተሾመው የስሙ ትርጓሜ “እግዚአብሔር ብርሃኔ ነው” የሆነው ሊቃነ መላአክት ቅዱስ ዑራኤል የከበረች በዓሉ በጥር ፳፪ ቀን ነው፡፡ ለሰው ልጆች ሁሉ ምሕረትን የሚለምነው ይህ መላእክ የአምላክን ፈቃድ፣ የፍርድና የአምልኮቱን ነገር፣ ምሥጢር የሚተርጎምና የሚያስረዳ እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስረዳሉ፡፡

የሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል ጸሎቱ፣ አማላጅነቱና ተራዳኢነቱ አይለየን፤ ከበዓሉ በረከት ረድኤት ያሳተፈን፤ አሜን!

ጊዜ ዕረፍታ ለሶልያና

ጥር ፳፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ጊዜ ዕረፍታ ለሶልያና

ወረደ ወልድ እምዲበ ልዕልና

ፀንሳው በድንግልና

ወልዳውም በድንግልና

ሆነች ማኅደረ መለኮት

በምድር ለተገኘው በከብቶች በረት

አዝላው ተጓዘች በግብጽ ውዕየት

ጭው ባለውም በረኀና ሙቀት

የሌቱን ቁርና ውኃ ጥማት

ተቋቁማ አለፈች ብርዱና ሙቀት

ሁሉን ተቀበለች ለሰዎች ድኅነት

ሆናለች እናቱ ለዓለም መድኃኒት

ደረሶ መፈጸሚያው ያ ተስፋው ቃል

አንዴ ሊሰቀል አካላዊ ቃል

በእውነት ተቀበለ መከራ መስቀል

ግን ጭንቅና ኀዘን ሆኖባት እናቱ

አምርራም አለቀሰች በመሠቃየቱ

አንዲያ ልጇን አይታ ሲሰቅሉት

በጭካኔ ታውረው በትዕቢት

አጽናኝም አጣች ፍጹም ሥቃይ ሆኖባት

ዳግምም መነሣቱን ወዳም ልትታገሥ

ጠብቃ ለማየት የናፈቃትን ልጇን ኢየሱስ

እንደተናገረውም ተነሥቶ ክርስቶስ

ቆመላት ፊቷ ለሐዋርያት ሞገስ

በዚያም ተጽናንታ በምድር ኖረችበት

የአምላክ እናት ለ፷፬ ዓመታት

አብዝታ በመመላለስ ሳታቋርጥ ጸሎት

በጌቴሴማኒ መቃብሩ ቤት

ጊዜው ደረሰና ከተወደደው ልጇ የምትሄድበት

ጊዜ ዕረፍታ ለሶልያና

ወረደ ወልድ እምዲበ ልዕልና

 

 

 

ሕፃኑ ሰማዕት

ጥር ፲፬፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ግብዝና ደካማ የሆነው የሰውን ሥጋ አሸንፎ፣ መከራን ተቀብሎ፣ ችግርን ተቋቁሞ፣ ፈተናን አልፎ መንፈሳዊ ሕይወትን ለመኖርና ክርስቲያን ለመሆን የሚደረገው ትግል እራሱን የቻለ ተጋድሎ እንደሚያስፈልገው የታወቀ ነው፡፡ እውነተኛ ለሆነው የክርስትና እምነተና ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖት የሚከፈለው መሥዋዕትም የተለየ ስፍራ አለው፡፡

እሳት ሰንሰለቱን ሳይፈሩ፣ እራሳቸውን እጅግ ለበዛ ሥቃይ አሳልፈው የሚሰጡ ሰማዕታት የተለየ ክብር አላቸው፡፡ ፍጹም በሆነው የክርስቶስ ፍቅር ዓለም የሚያመጣባቸውን መከራ ለመቀበል በሙሉ ፈቃደኝነት ቆርጠው ተነሥተው ከአላውያን ነገሥታት አልያም ከመኳንንቶች ደግሞም ከከሃድያን ደርሰው በግልጽ ለእውነተኛው ጌታ በመመስከር እውነተኛ ምስክሮች ይሆናሉ፡፡

ከሁሉም የሚደንቀው ደግሞ ከእሳት ምድጃ ቢጥሏቸው፣ ከፈላ ውኃ ውስጥ ቢጨምሯቸው፣ ለአንበሳ እና አውሬ መብል አሳልፈው ቢሰጧቸው እምነታቸው ምንም አለመቀየሩ ነው፡፡ ለሚያምኑበትና ለሚመኩበት ኃይል ብርታት የሚሆን፣ መሐሪና ይቅር ባይ አምላካችን  ጻድቃንን ቅዱሳንን ሰማዕታት ለጠላት አሳልፎ የማይሰጥ ነውና መላእክቱን ልኮ ውኃውን እንደ ውርጭ የሚያቀዘቅዝ፣ እሳቱን ውኃ የሚያደርግ፣ የተራቡ አራዊት የቅዱሳንን እግርና እጅ እንዲልሱ የሚያደርግ ነው፡፡ ዳግመኛም ለልዩ ልዩ ለሥቃይ አሳልፈው ቢሰጧቸውም የክብር ባለቤት እራሱ ከሰማየ ሰማያት ከእልፍ አላፋት መላእክት ጋር ወርዶ እንዳጽናናቸው እንዲሁም እንዳጸናቸው ገድላቸው ይናገራል፡፡ (ገድለ ቅዱሳን)

በከበረች ሐምሌ ፲፱ ቀን የጌታችን ዕጹብ ድንቅ ሥራ በተገለጠባት ዕለት የሚያስደንቅ ገድል ያደረገ የሦስት ዓመቱ ሕፃን ቅዱስ ቂርቆስ ገድልም ፍጹም ድንቅ ነው፡፡ በዚህች ቀን በፈላ የጋን ውኃ ውስጥ ቅዱሳኑ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣን ሊጨምሯቸው ሲሉ ቅድስት ኢየሉጣ በፈራች ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ›› እያለ ያረጋጋትና በተጋድሎዋ እንድትጸና ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ጋኑ ውስጥ ገቡ፡፡ ውኃውም እንደ ውርጭ ቀዘቀዘ፡፡ ይህንም ያደገረው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡

የዘመኑ የአረማዊው መኰንን የእለእስክንድሮስ ወታደሮች ከሮም ወደ ወደ ተርሴስ ከእናቱ ጋር ሸሽቶ የገባውን ሕፃኑ ሰማዕት ይዘው ፈጣሪን ክዶ ከጣዖት እንዲሰግዱ በዓይነቱ ቢያሠቃዩትም ስላልተቀበላቸው በገመድ አሳሥሮ ንጉሡ ሲያስጨንቃቸው ከቆየ በኋላ ራሳቸውን ከቆዳቸው ጋር አስላጭቶ እሳት አነደደባቸው፡፡ ዳግመኛም ከትከሻቸው እስከ እግራቸው ድረስ በሚደርሱ ችንካሮች ቸነከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ከሥቃያቸው አድኗቸዋል፡፡ አሁንም ቀኑን ሙሉ በልዩ ልዩ የሥቃይ መሣሪያዎች ቢያስጨንቃቸውም የእግዚአብሔር ኃይልና የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አልተለያቸውም ነበርና ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡ እንደ ገናም በመጋዝ ሰንጥቀው በብረት ምጣድ በቆሏቸው ጊዜ ጌታችን ከሞት አነሣቸውና በመኰንኑ ፊት ድንቅ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከተአምራቱ መካከልም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ የመኰንኑን ጫማ በጸሎት ወደ በሬነት እንዲቀየር ማድረጉ ተጠቃሽ ሲሆን፣ መኰንኑ በተአምራቱ ተቈጥቶ የቅዱስ ቂርቆስን ምላስ አስቈርጦታል፤ ጌታችንም ምላሱን አድኖለታል፡፡

ደግሞም ወታደሮቹ መንኰራኵር ባለበት የብረት ምጣድ ውስጥ አስገብተው ሥጋቸው እስኪቈራረጥ ድረስ በጎተቷቸው ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል አድኗቸዋል፡፡ በመጨረሻም ሕፃኑ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብሎ ጥር ፲፭ ቀን አንገቱ ተቆርጦ የሰማዕትነት አክሊል ተቀብሏል፡፡ በተመሳሳይም እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ሰማዕት ሆናለች፡፡ ግሩምና ድንቅ የሆነው የሰማዕታት ገድል የሁላችንም አስተማሪና አስማሪ ነው፡፡ በእነርሱ ጸሎት፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት የእኛ ኃጢአት ይስተሠረይልናልና፡፡

የቅዱሳኑ ጸሎት፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ጥር፣ ፲፭ ቀን

 

 

 

የቃና ዘገሊላ ሰርግ

ጥር፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ዲያቆን ወልዳይ መረሳ

በአዲስ ኪዳን የዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተጠቀሰው ዶኪማስ ሰርግ ባደረገበት ወቅት ድንግል ማርያምና ጌታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የታደሙባት (ዮሐ ፪፥፩-፲፩ )፣ እንዲሁም የሐዋርያው ናትናኤል የትውልድ ሀገር ገሊላ ናት (ዮሐ ፳፩፥፪ )። ጌታ በዚሁ ስፍራ ሆኖ በመናገር በቅፍርናሆም ታሞ የነበረውን የሹሙን ልጅ ከሕመሙ ፈውሶታል። (ዮሐ ፬፥፵፫-፶፬ )

ቤተ ክርስቲያን በዓላትን በቅዱሳን ስም፣ በዕለቱ በተፈጸመው ድርጊት ወይም በቦታ ስም ትሰይማለች። ይህም “በአዳሪው ስም ማደሪያው ይሰየማል” እንደሚባለው እንጂ፣ ተአምራቱን የፈጸመው ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ቤተ ክርስቲያንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትን ተከትላ ጌታ ለገለጠበት ስፍራ ክብርና ቅድስና በመስጠት በዓሉን በቦታው ስም “ቃና ዘገሊላ” ብላ ታከብራለች። (ዘጸ.፫፥፭፣ ፪ ጴጥ. ፩፥፲፰) ምንም እንኳን በቃና የተደረገው ተአምር ጌታ ተጠምቆ በቆሮንቶስ ገዳም ከተፈተነ በኋላ በየካቲት ወር የተፈጸመ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ግን “የውኃውን በዓል ከውኃ በዓል ጋር” በማዛመድ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ከጥምቀት ማግስት እንዲከበር አድርገዋል።

በዚህም መሠረት የቃና ዘገሊላ በዓል ከዘጠኙ የጌታ ንኡሳን በዓላት አንዱ ሆኖ ከዋዜማው ጀምሮ በዝማሬና በቅዳሴ በድምቀት ይከበራል። በዕለቱ የሚቀርቡት ንባባትና ዜማዎችም በቃና ዘገሊላ የተደረገውን ተአምርና ምሥጢር የሚዘክሩ ናቸው። ቤተ ክርስቲያናችን በዛሬው ዕለት የምታቀርባቸው ዝማሬዎችና የቅዱስ መጽሐፍ ንባባት በአንድ ዋና ነጥብ ላይ ያተኩራሉ፤ ይህም በቃና ዘገሊላ የተከናወነው የመጀመሪያው ተአምርና በውስጡ የያዘው ጥልቅ ምሥጢር ነው። ይህ ታሪክ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፪ ከቁጥር ፩-፲፩ ላይ በስፋት ተመዝግቦ ይገኛል። ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የዚህን ወንጌል ትርጓሜ እጅግ ረቂቅና ሰፊ በሆነ ምሥጢር ቢተነትኑትም፣ እኛ ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እንደ አቅማችን መጠን እነርሱ ካስተማሩት ጥቂቱን እንደሚከተለው በአጭሩ እንመለከታለን።

 የቃና ዘገሊላ ሰርግ

በሦስተኛው ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበር፤ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜ እናቱ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው። እርሱም “አንቺ ሴት፣ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት። እናቱም አገልጋዮቹን “እርሱ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው። በዚያም እንደ አይሁድ ሥርዓት ለመንጻት የሚሆኑ ስድስት የድንጋይ ጋኖች ነበሩ። ኢየሱስም “ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው” አላቸው፤ እስከ አፋቸውም ሞሏቸው። “አሁን ቀድታችሁ ለሰርግ አዘጋጁ (ለአሳላፊው) ስጡት” አላቸው።አሳላፊውም ወደ ወይን የተለወጠውን ውኃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደመጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር። አሳላፊውም ሙሽራውን ጠርቶ “ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን ወይን ያቀርባል፣ ከጠጡ በኋላ ግን የተለወጠውን (መካከለኛውን) ያቀርባል፤ አንተ ግን መልካሙን ወይን እስከ አሁን አቆይተሃል” አለው።

ኢየሱስ ይህን የመጀመርያ ተአምር በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ። (ዮሐ ፪፥፩-፲፩) በዚህ ቅዱስ ሰርግ ላይ የጌታ ትሕትና ተገልጦበታል፤ ክብሩ ታውቋል፤ የድንግል ማርያም ርኅራኄና አማላጅነት ታይቷል፤ የጋብቻ (የምሥጢረ ተክሊል) ክብርም በተግባር ትምህርቱ ተሰጥቶበታል።

የጌታ ትሕትና መገለጥ

ክርስቶስ በቤተልሔም በከብቶች ግርግም ተወልዶ፣ በዮርዳኖስም በባሪያውና በአገልጋዩ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ የትሕትና አባት መሆኑ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው። አሁን ደግሞ “ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ (ድሀ አደረገ)” ተብሎ እንደተጻፈው፤ (ፊል ፪፥፯) በፍጥረታቱና በባሪያዎቹ ሠርግ ላይ እንደ ዋና የክብር እንግዳ ሳይሆን እንደ ማንኛውም እንግዳ ተገኘ። ያውም የወይን ጠጅ እንኳ ለታዳሚዎቻቸው በማያበቃቸው በድሆች የሰርግ ቤት ተገኘ።

ማንንም ሳይንቅ ከባሪያዎቹ ጋር እንደ አንዱ ታዳሚ ተቀመጠ። ያንን ታላቅ ተአምርም “እዩልኝ ስሙልኝ” ሳይል፣ ወይን በሚቀመጥበት በዚያ በጓዳ ጋኖቹ ዘንድ አደረገው። ይህም በሉቃስ ወንጌል (፲፬፥፯-፲፩) ላይ “አንድ ሰው ለሰርግ ቢጠራህ ከሁሉ በላይ ባለው የክብር ቦታ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የሚከበር ሰው ተጠርቶ ከሆነ፣ አንተንና እርሱን የጠራው መጥቶ ‘ለዚህ ሰው ስፍራ ልቀቅለት’ ይልሃል፤ ያን ጊዜም እያፈርህ ወደ መጨረሻው ስፍራ ትወርዳለህ። ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ የጠራህ ሰው መጥቶ ‘ወዳጄ ሆይ፣ ወደ ላይ ከፍ በል’ ባለው ጊዜ፣ አብረውህ በተቀመጡት ፊት ክብር ይሆንልሃል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም ዝቅ የሚያደርግ ከፍ ይላል” ብሎ ራሱ ያስተማረውን ትምህርት በተግባር የፈጸመበት አርአያነት ነው። በዚህም እኛ እንዴት በትሕትና፣ ለሰው ታይታ ሳይሆን ከልብ ማገልገል እንዳለብን አስተማረን።

ክርስቶስ ማንነቱን መግለጡ

በቃና ሰርግ ቤት የተደረገው ተአምር የአዳዲስ አማኞችንና የሐዋርያትን እምነት ለማጽናትም የተደረገ በመሆኑ፣ ወንጌላዊው ዮሐንስ “ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” ይለናል። እመቤታችን ድንግል ማርያምም ጌታችን ማንነቱ የሚገለጥበት ጊዜ መድረሱን አውቃ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው። ጌታችንም “ጊዜዬ ገና አልደረሰም” ማለቱ፣ በወቅቱ ያልነበረው ይሁዳ መጥቶ ተአምሩን እንዲያይና ለወደፊት “እኔ በሌለሁበት ተአምር አድርጎ ለየኝ” የሚል ምክንያት እንዳይኖረው ለማድረግ እንደሆነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ተርጒሞታል።

የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ ክብርና ርኅራኄ ወንጌላዊው ሲገለጽ ቅዱስ ዮሐንስ ታሪኩን ሲጀምር “የኢየሱስ እናት በዚያ ነበረች” በማለት ክብሯን ይገልጻል። ወንጌላዊው በየትኛውም ስፍራ ስሟን በቀጥታ ከመጥራት ይልቅ “እናቱ” ወይም “የኢየሱስ እናት” እያለ ይጠራታል፤ ይህም ሐዋርያት ለእመቤታችን ያላቸውን ታላቅ አክብሮትና ድንግል ማርያም ያላትን የአምላክ እናትነት ጸጋ የሚያስረዳ ነው። ጌታችንም እናቱን “አንቺ ሴት” ማለቱ፣ አዳም ሔዋንን “ከአጥንቴ አጥንት ከሥጋዬ ሥጋ ናት” (ዘፍ ፪፥፳፫) እንዳላት ሁሉ፣ እርሷም የጌታ የሥጋዌው (የሰው የመሆኑ) ምክንያት መሆኗን ለማረጋገጥ ነው።

ድንግል ማርያም የወይኑ ማለቅ በሰርገኞቹ ላይ የሚያመጣውን ኃፍረት ተረድታ፣ እነርሱ ሳይጨነቁና ሳይጠይቋት ቀድማ በመለመን ርኅራኄዋን ገልጻለች። ጌታችንም የእናቱን ልመና ሰምቶ ውኃውን ወደ ወይን በመለወጥ ተአምሩን ፈጸመ።

ምሥጢረ ተክሊል

ጋብቻ ቅዱስ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ክርስቶስ ከእናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በሰርጉ ላይ ተገኝቷል። ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ የታነጸች ናት። ይህ ምሥጢርም በእግዚአብሔር ፊት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ የሚፈጸም መሆኑን ያስረዳል። ጌታችን በሰርግ ቤት እመቤታችንን “አንቺ ሴት” ብሎ መጥራቱ አዳም ሔዋንን “ከአጥንቴ አጥንት፣ ከሥጋዬ ሥጋ ናት” (ዘፍ ፪፥፳፫) እንዳላት ሁሉ፣ ስለ ሥጋዌው (ሰው ስለመሆኑ) የሚጠቁም ነው። ውኃውን ወደ ወይን መለወጡም የከበረ ደሙ ምሳሌ ነው። ስለሆነም ምሥጢረ ተክሊል በሥጋውና በደሙ የሚከብርና አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጸም ቅዱስ ሥርዓት ነው።

የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር በረከቱንና ረድኤቱን ያብዛልን። የአምላክ እናት ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ አትለየን።

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!

 

 

 

በዓለ ጥምቀት

ጥር፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

 በጥር ዐሥራ ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ በዮርዳኖስ ወንዝ ውኃ ተጠመቀ።

ይችህም ዕለት በዮናኒ ቋንቋ ኤጲፋንያ ትባላለች፤ ትርጓሜውም “መለኮት የተገለጠበት ማለት ነው።” ልዩ የሆነች የሦስትነቱን ምሥጢር ገልጦባታልና አብ ከሰማይ ሆኖ “የምወደው በርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” እያለ ሲመሰክር ወልድም በዮርዳኖስ ወንዝ ቁሞ ሳለ መንፈስ ቅዱስም በነጭ ርግብ አምሳል በወልድ ራስ ላይ ሲቀመጥ ይህ አጥማቂው ዮሐንስ እንደመሰከረ።

እንዲህ ሲል “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠምቆ ከውኃ በወጣ ጊዜ ወዲያውኑ ሰማይ ተከፈተ፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በጌታችን ራስ ላይ ተቀመጠ፤ ከሰማይም እንዲህ የሚል ቃል መጣ፤ “ይህ የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ነው፤ እርሱንም ስሙት።”

በዚች ዕለት ጌታችን ራሱን ገልጦአልና ከዚህ በፊት ሠላሳ ዓመት ያህል ራሱን አልገለጠም ነበር፤ ግን በዚች ዕለት ለእስራኤል ልጆች ራሱን ገለጠ፤ “እነሆ የእግዚአብሔር በግ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ” ብሎ መጥምቁ ዮሐንስ እንደገለጠው የከበረ ወንጌል ምስክር ሆነ።

“እኔ አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን እስራኤል ያውቁት ዘንድ በውኃ ላጠምቅ ስለዚህ መጣሁ” አለ። በዚህም በዓል የእግዚአብሔር ልጅ የክርስቶስ የጌትነቱ ክብር ተገልጧል፤ እርሱም የዓለሙን ሁሉ ኃጢአት ለማስወገድ የሚሰዋ የእግዚአብሔር አማናዊ በግ ነው።

ስለዚህም ይህ በዓል በክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ዘንድ የከበረና ከፍ ከፍ ያለ ሆነ በርሱም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ በአከበረው ውኃ ይነጹበታል፤ የተቀበሉትንም ንጽሕና ጠብቀው ቢኖሩ በውስጡ የኃጢአታቸውን ሥርየት ያገኛሉ።

ስለዚህም ከክፉ ነገር ሁሉ ተጠብቀን የፈጣሪያችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የቸርነቱን ብዛት ልናመሰግን ይገባናል፤ እርሱ ስለ እኛ ሰው ሆኖ ከኃጢአታችን አድኖናልና።

ለእርሱም ከቸር አባቱ ሕይወት ከሆነ መንፈስ ቅዱስም ጋር ክብር ምስጋና ስግደትም ይሁን፤ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን!!!

መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ጥር፣ ፲፩

 

ለፈጣሪ በበጎ ፈቃድ መገዛት ይገባል!

ጥር ፭፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ሰው በራሱ ፈቃድ በጎ አልያም በክፉ ሐሳብና ምኞት መጥፎ ሊሆን ይችላል፡፡ የአዳም ዘር ጥንተ ተፈጥሮውን ዐውቆና ተረድቶ በድንቅ ሥራው ለፈጠረው አምላክ ተገዢ የመሆን ፈቃድም የራሱ ነው፡፡ በውዴታ ብቻ ሳይሆን በግዴታም ለፈጣሪ መገዛት እንዳለብን ቅዱሱ መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡

ታዲያ ዓለምን ሁሉ ከእነ ጓዟ ለፈጠረ አልፋና ዖሜጋ፣ ኤልሻዳይ ለሆነው እግዚአብሔር መገዛት በፍቅር መሆን ሲገባው ብዙኃኑ ሰው ግን አሻፈረኝ ብሏል፡፡ ይባስ ብሎም በራሱ ፈቃድ ያለ እግዚአብሔር አምልኮ ለመኖር መወሰኑ ሳያንስ ዓለምን መግዛት እንደሚቻለው እያሰበ ነው፡፡ ሰው በራሱ ጥበብ ተጉዞ ጨረቃን አልያም ሌሎች በሰማያት ላይ ያሉ ድንቅ ፍጥረታት ላይ መድረስ ቢችልም ወደ ላይ የመምጠቅ ኃይሉ የተገደበ እንደሆነ ግን ማመን አዳግቶታል፡፡ ምንም መሣሪያ ቢሠራ፣ ምንም ተጠብቦ ወደ ሰማይ መጓዝ ቢችል እርሱ ባወቀ እንጂ የትም መድረስ አንችልም፡፡ ‹‹እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ፣ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን አወርድሃለሁ›› ተብሎ እንደተጻፈ (አብድ. ፩፥፬) ጥበብም ከእግዚአብሔር በመሆኑ እርሱን ባለመፍራት የሚደረግ ነገር ማንም ምንም ማድረግ አይቻለውም፡፡

አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ዛሬም ያለ ወደ ፊትም ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዘለዓለማዊ አምላክ የሆነ ማንም ሊያሸንፈውም የማይችል ነው፡፡ በቸርነቱ ብዛት ዓለምን ሲፈጥርም መልካም በመሆኑ ነው፡፡ ሰው ግን አምላክነትን ሽቶ ክሕደት ፈጸመ፤ ኃጢአት ሠራ፤ ከክብሩም ተዋርዶ መከራና ሥቃይ፣ ረኀብ፣ ጥም፣ እንግልት፣ ልፋት፣ ገዓር፣ ኀሣር ወዳለባት ምድር ተጣለ፡፡ በዚህም ሆኖ ሰው አምላኩን መበደል አላቆመም፡፡ የተፈቀደለትን ትቶ ያልተቀደለትን፣ የታዘዘውን ሳይፈጽም ያልታዘዘውን፣ የማይገባውን በመሻትም ፈጣሪውን መዳፈር ቀጠለ፡፡ ኃጢአት መሥራቱ ሳያንስ አምላክ ላይ መድረስ፣ ወደ ላይ መጥቆ ፈጣሪን ተዳፈረ፡፡

በኖኅ ዘመን የተፈጸመው የባቢሎናውያን ድርጊትም የዚህ ማሳያ ነው፡፡ በክፉ ምክራቸው ተነሣሥተው ፈጣሪ ወዳለበት ለመድረስ የሰናዖር ግንብን ሠሩ፡፡ መጽሐፉም እንደሚነግረን  ‹‹እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። እግዚአብሔርም አለ። ‹‹ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።›› (ዘፍ.፲፩፥፩-፱)

ታሪኩን በመቀጠል ስናነበውም አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ የሰናዖርን ግንብ አፍርሶ ባቢሎናውያኑን በትኗቸዋል፡፡ የቅድስት ሥላሴ አንድነታቸውና ሦስትነታቸው የተገለጸበት ጥር ሰባት ቀን የከበረ በዓል እንደመሆኑ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡

ዓለማችን በጎርፍ እየተጥለቀለቀች፣ በመሬት መንቀጥቀጥ እየራደች፣ በሰደድ እሳት እየተለበለበች ያለችው የአዳም ዘር አምላኩን ክዶ፣ ሀብት፣ ሥልጣንና ኃይል በመሻት በኃጢአት ሰንሰለት ታስሮ የጠላት ዲያብሎስ ተገዢ በመሆኑ ነው፡፡ ወደ ላይ እየመጠቅን ሲመለስን ወደ ታች እየወረድን እንደሆነ ማን በነገረን? በሰው ሠራሽ ሥሪት የሚንቀሳቀሱ  ቁሳዊ አካላትን በመሥራት የአምላክን ክቡር ፍጡር ሰውን ለመተካትና ፈጣሪ ለመሆን፣ ከዚያም ባሻገር የተፈጥሮ ሂደትን በሚያዛባ መልኩ ዘር የመተካትን ሂደት ሰው ሠራሽ የማድረግ ጥረት አምላክነትን የመሻት ነው፡፡ ይህም የዳረገን ለከፋ ነገር መሆኑ በግልጽ የሚታይ ሆኗል፡፡ እኛ የማይገባንን ለማግኘት ስንጥር የሚገባንን ግን ተነጠቅን፡፡ ሰው የመሆን መብታችንን አጥተናል፡፡ በነጻ፣ ያለ ክፍያ ድንቅ ተደርገን ተሠርተን እኛ ግን በውድ ዋጋ ቁሳዊ አካልን ሸምተን የሰውን ሥራ ሁሉ እንዲሠራልን ተመኘን፡፡ የራሳችንን ክብር የሚያሳጣን ነገር መሆኑን ግን ለማወቅ ዓይነ ልቡናችን ታወረ፡፡

ጥበበኛ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪትም ሆነ በሕገ ወንጌል የገለጠልን ምሥጠር ድንቅ ሥራውን ብቻ ሳይሆን በክብር ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያሰጥ ነው፡፡ ከሁሉም አስቀድሞ ግን እርሱን መፍራት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው›› እንዲል፡፡ (ምሳሌ ፩፥፯) ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ ክብሩን አላወቀም፡፡ ስለዚህ የጥንተ ተፈጥሮአችንን አስታውሰን፣ የተፈጠርንበትን ምክንያትን ዐውቀንና ተድረተን፣ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር በበጎ ፈቃድ በመገዛት ልንኖር ይገባል፡፡

አምላካችን ቸርነቱንና ምሕረቱን ያብዛልን፤ ከበዓሉ ረድኤትና በረከት ያሳትፈን፤ አሜን!

 

 

በዓለ ግዝረት

ጥር ፭፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

በዘመነ ብሉይ ግዝረት የተጀመረው በአባታችን አብርሃም ነበር፤ በዚያን ጊዜ የነበሩ ሕዘበ እግዚአብሔር ከአሕዛብ የሚለዩበትና ክብር የሚያገኙበት ሕግ መጽሐፊያዊ ግዝረት ነበር፡፡ ያም እንደ ጥምቀት ይሆንላቸው ነበርና ነው፡፡ (ዘሌ.፲፪፥፫)

የከበረ ወንጌል እንደገለጸው በዘመነ ሐዲስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በስምንተኛው ቀን ግዝረትን ፈጽሟል፡፡ “ጌታ ሰው መሆኑ ሕገ ኦሪትን ሊሽር ባለመሆኑ ሥርዓተ ግዘረትን ፈጽሞልናል፡፡” (መዝገበ ታሪክ ገጽ ፻፵፩)

በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል እንደተጻፈው “ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ፥ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ፥ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ወደ ግዘረት ቤት ወሰደችው፤ ገራዡ ምላጩን ይዞ ቀረበ፤ ነገር ግን ምላጩ እጁ ላይ ሳላ ውኃ ሆኖ ፈሰሰ። ጌታችንም በተአምራት የተገረዘ ሆኖ ተገኘ፡፡”  (ሉቃ.፪፥፳፩-፳፫)

የአምላካችን ድንቅ ሥራ ተነግሮ አያልቅምና በከበረች በጥር ፮ ቀን ሥርዓተ ግዝረትን የፈጸመልን ጌታ እኛም እርሱን አብነት አድርገን ወንድ ልጆችን በስምንት ቀናቸው እንድናስገርዝ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን ከጌታችን ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱና የመጀመሪያው የሆነውን የተቀደሰ ቀን ታከብረዋለች፡፡

ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፤ አሜን!

 

 

 

 

በበረት ውስጥ እነሆ ተወለደ!

በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል

ታኅሣሥ ፳፰፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

 

      ያቺ ድንግል ቤተ መቅደስ ሆና ሐርና ወርቅ ስታስማማ፣

መልአኩ የምትወልጅው ኢየሱስ ነው ያላትን ቃል ሳታቅማማ፣

የሚፈውስ ድውያንን፣

የሚያበራ ዕውራንን ፣

የሚተረትር ሽባዎችን ፣

የሚያነጻ ለምጻሞችን ፣

 የሚያወጣ አጋንንትን፣

ከስም በላይ ስም የሆነ፣

አልፋ ኦሜጋ የታመነ፣

ድንቅ መካር ሰው መሆንን የወደደ፣

በበረት ውስጥ እነሆ አሁን ተወለደ!

በአርያም የሚኖሩት መላእክቱ፣ ተመልክተው አምላክ ሲያዝን ለፍጥረቱ፣

ግርግም ከበው የዚያ ሕፃን ሠራዊቱ፣

በሰማያት አመስግነው እግዚአብሔርን

በምድር ላይ ለሰውም ልጅ ሰላም ይሁን

ብለው ዘምረው፣ ቤተ ልሔም የምድር ዙፋን፣

በአርያም ተሸክመው ቅዱስ አንተ የሚሉትን፣

ድንግል ማርያም ወዮሴፍ ላም አህያ ተመስለው አርባዕቱን፣

እነርሱ አንቺን ተሸክመው አንቺ ድገሞ ጸባኦትን

የአስተርእዮ ዘመን ሆኖ በምድር ላይ ሲከናወን

የሰማዩ ድንቅ ሥራ፣ ከበረት ውስጥ ሲፈነጥቅ ድህነት ፈውስን

ያነገበ የጽድቅ ጮራን፣

አንቺ ቅድስት ቤተ ልሔም፣

ቅጠል ለብሶ እንደ ሕፃን እያነባ መድኃኔ ዓለም፣

ኃያል ንጉሥ እርቃን ሆኖ ባንቺ ሲድር አልፈራሽም

እንደ ባሕር አልሸሸሽም

እንደ እምቦሳም አልዘለልሽም፡፡

እነ ኪሩብ በነደ እሳት የተሠሩ፣

በሁለት ክንፍ በዓለም ዙሪያ የሚበሩ፣

በመለኮት እሳትነት እንዳይጠፉ በሁለት ክንፍ ፊታቸውን የሠወሩ፣

በቀራቸው በሁለቱ እግራቸውን የጠፈሩ፣

 

  • ቅዱስ (፫)  ብለው ያለፋታ በመንቀጥቀጥ የሚያመልኩት፣

በግርግም ውስጥ እንደ ሕፃን ሲያለቅስ አይተው ምንስ አሉት

ፀሐይና ከዋክብትን ለፈጠረ፣

በልዩ ጌጥ ዓለማትን ላሳመረ፣

ነገሥተ ተርሴስ ወደሴያት፣

እጅ መንሻ አመሃውን ላመጡለት፣

ከዋክብትን በስማቸው ለሚጠራ፣

ፍጥረታትን ያለሳንካ ለሚሠራ፣

ከክብር አንሶ በራፊ ጨርቅ ተጠቅልሎ፣

አምላክ ሳለ ፍጡር መስሎ እንደ ነዳይ ተጎሳቁሎ፣

የዚያ ሌሊት ቢያይል ቁሩ፣

በደመ ነፍስ የሚኖሩ  ትንፋሽ ሰጥተው ሲገብሩ፣

መላእክቱ ቅዱስ(፫) ብለው በፍቅር ሆነው

የሚያመልኩት፣ በግርግም ውስጥ እንደ ሕፃን ሲያለቅስ አይተው

ምንስ አሉት ጽድቃችንም የመርገም ጨርቅ ከንቱ ሆኖ፣

መኖሪያችን በሲኦል ቋት ተወስኖ፣

ለዘመናት ስንገረፍ በእሳት ላንቃ፣

ያበቃ ዘንድ ይህ እንግልት ይህ ሰቆቃ፣

ልዑል ሁይ ክንድህን ስደድ፣

ናማ ውረድ

ና ተወለድ

ብለው ጻድቃን ሲጸልዩ ለዘመናት ፣

እርግማኑን ይሽረው ዘንድ በምርቃት፣

እነሆ አሁን

ጨለማውን አስወግዶ ብርሃኑን ያበራልን፣

ከጎሞራ ያልመሰለን ከሶዶም ግብር ያልደመረን፣

ሰማያትን በደመና የሚጋርድ፣

ተወለደ በዐውድ

እሰይ እሰይ ይኸው አሁን የምሥራች፣

የጸብ ግርዶሽ ተቀዳዶ ሰላም ሆኗል በላይ በታች፡፡

፶፻፭፻ የንስሐ የጣር ዘመን ተፈጸመ

አምላክ ወሰብእ በግርግም ውስጥ ከበጎች ጋር ከተመ!

 

 

 

የሃይማኖት ተክል!

ታኅሣሥ ፳፫፤፳፻፲፰ ዓ.ም.

ድንቅ በሆነው የፈጣሪ ሥራ ሰው ሆነን ተፈጥረን በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር የሕይወታችን መሠረት በሆነው ሃይማኖት ጸንተንና በቀናው መንገድ ተጉዘን የመንፈስ ፍሬን ለማፍራት እንዲቻለን ነው፡፡ የማንኛውም መንፈሳዊነት መሠረት ሃይማኖት ነውና፡፡ አንድ አምላክን ማመን ለእርሱ መታመን ሃይማኖት ነውና፤ ይህ ምሥጢር ገብቷቸው፣ በድንቅ ሥራቸው አብርተው፣ ፍጹም ተጋድሎአቸውን ጨርሰው ለአምላካቸው እውነተኛ ምስክሮች በመሆን ርስተ መንግሥተ ሰማያትን የወረሱ ቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን የቤተ ክርስቲያናችን ዕንቁ ፈርጥ በመሆናቸው እናከብራቸዋለን፡፡

“የሃይማኖት ተክል” የተባለው ቅዱስ አባታችን ኢትዮጵያዊው ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም የከበረች ልደት በዓሉ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ይከበራል፡፡ ጻድቁ በብሥራተ ቅዱስ ሚካኤል መሠረትም በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ልዩ ስሙ ኢቲሳ በሚባል ቦታ መጋቢት ፳፬ ተፀንሰው ታኅሣሥ ፳፬ የተወለዱት ከአባታቸው ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው እግዚ ኅረያ ነው፡፡

በተለወዱ በሦስተኛው ቀን እሑድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ     ወርደው    ‹‹ሐዱ  አብ  ቅዱስ፤   አሐዱ  ወልድ  ቅዱስ፤  አሐዱ  ውእቱ  መንፈስ  ቅዱስ፤  አንዱ  አብ  ቅዱስ  ነው፤  አንዱ  ወልድ  ቅዱስ  ነው፤  አንዱ  መንፈስ  ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት አጋእዝተ ዓለም ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም ‹‹ፍሥሐ ጽዮን››  የሚል ቢሆንም‹‹ተክለሃይማኖት›› ደግሞ ጌታችን እራሱ ነው፡፡

የሃይማኖት ተክል የተባሉት ቅዱስ አባታችን የወንጌልን ቀንበርን ተሸክመው፣ ሀገራችን ኢትየጵያን በዕርፈ መስቀል ያረሱ፣ ቅዱስ ቃሉን ሰብከውና አስተምረው፣ እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ሃይማኖትን ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለዓለም አሳውቀው፣ ጣዖታትን ሰባብረው ቀጥቅጠው ያጠፉ፣ ብዙዎችን ከኃጢአት ጎዳና መልሰው ለርስተ መንግሥተ ሰማያት ያበቁ ታላቅ አባት ናቸው፡፡

የአባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጸሎት፣ አማላጅነትና ረድኤት አይለየን፤ አሜን!!!

ምንጭ፡ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት