በዓለ ሢመቱ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል

ጥር ፳ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ በመሆን ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ በመብረቅና በነጎድጓድ ላይ በጥር ፳፪ ቀን የተሾመ መልአክ ነው፡፡ በመጽሐፈ ሄኖክ እንደተገለጸው መባርቅት ለጥጋብና ለበረከት እንዲበርቁ ነጎድጓድም ለሰላም እንዲሆን ያሠማራል፡፡ ለነቢዩ ሄኖክም የሰማይን ምሥጢርና ሰማያዊውን ዕውቀት ሁሉ የገለጸለት፤ የፀሐይን፣ የጨረቃን፣ የከዋክብትንና የሰማይ ሠራዊትን ብርሃንን የሚመራው ይኸው ገናና መልአክ ነው፡፡ (ሄኖ.፳፰፥፲፫)

ዑራኤል ማለት ትርጉሙ ‹‹የብርሃን ጌታ፣ የአምላክ ብርሃን›› ማለት በመሆኑም መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሆኖ በተሰቀለ ጊዜ ክቡር ደሙን በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ በብርሃነ መነሳንስ በዓለም ላይ የረጨ መልአክ ነው፡፡ ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል ጽዋ ጥበብን ያጠጣ እንዲሁም ሰማያዊውን ምሥጢር እና ዕውቀት ተሠውሮበት ለነበረው ለኢትዮጵያዊው ሊቅ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በእመቤታችን ትእዛዝ ጽዋ ጥበብን አጠጥቶ ሰማያዊውን ምሥጢር የገለጠለት ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ (ዕዝ.፪፥፩)

የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክን ከልጇ ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስትሰደድ መንገድ ወደ ግብጽ እና ወደ ሀገራችንን ኢትዮጵያ እየመራ አምጥቷቸዋል፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር የቸርነት ዝናም በምድራችን ላይ ያዘንብ ዘንድ እንዲሁም የእርሻችንን አዝመራ በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ ለምግብነት እንዲበቃ ከፈጣሪ ዘንድ ምሕረትን የሚለምን መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል እንደመሆኑ በሀገራችን ኢትዮጵያ አብዛኞቹ ቅዱሳት ገዳማት በቅዱስ ዑራኤል መሪነት ተመሥርተዋል፡፡ ድርሳኑ ላይ የማይጠቅሳቸው የሀገራችን የከበሩ ቅዱሳት ገዳማትና ቅዱሳን ነገሥታት የሉም፡፡

የሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን፡፡