‹‹አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ የበሉትም ወንዶች አምስት ሺህ ነበሩ›› (ማር.፮፥፵፬)

ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በዘመነ ሥጋዌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ከሞተ በኋላ ወደ በረሃ ሄደ፡፡ ሕዝቡም ሰምቶ ተከተለው፡፡ በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሕዝቡን እንዲያሰናብት ጠየቁት፡፡ ይህም ለዚያ ሁሉ ሕዝብ የሚሆን ምግብ ስለሌለ የሚበሉትን እንዲገዙ ነበር፡፡ እርሱ ግን ለጊዜው የተገኘውን አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ ባርኮ ሁሉንም እስኪጠግቡ ድረስ መገባቸው፡፡ ተርፎም አሥራ ሁለት መሶብ ተነሣ፡፡ የተመገቡትም ሕዝብ ሴቶችና ሕፃናት ሳይቆጠሩ አምስት ሺህ ወንዶች ነበሩ፡፡ ‹‹አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ የበሉትም ወንዶች አምስት ሺህ ነበሩ›› እንዲል፤ ሴቶቹ ያልተቆጠሩበት ምክንያት በዐደባባይ ሲበሉ በሃፍረት ዳር ዳር ስለሚሉ ነው፤ ሕፃናት ደግሞ ከሚበሉት የሚፈረፍሩት ስለሚበዛ ነው፡፡ (ማር.፮፥፵፬)

ጌታችን ያን ሁሉ ሕዝብ በመንደር አጠገብ መመገብ ሲችል ርቆ ወደ ምድረ በዳ የወጣበት ምክንያት ነበረው፡፡ ይህም፡-

‹‹ጥንት አባቶቻችሁን ከመንደር አውጥቼ (ከግብፅ አውጥቼ) ዐርባ ዘመን ሙሉ መና የመገብኋቸው እኔ ነኝ፡፡ አሁንም በሥልጣኔ፣ በተአምራቴ መገብኋችሁ›› ሲላቸው ነው፡፡

ተአምራቱን ከመንደር አጠገብ አድርጐት ቢሆን ኖሮ ‹‹ፈጣን ፈጣን ደቀመዛሙርቱን በጐን ወደ መንደር እየላከ ያስመጣው ነው›› ብለው በተጠራጠሩ ነበር፡፡ ስለሆነም ለጥርጥር ምክንያት እንዳይኖራቸው አድርጎ ተአምራቱን ገልጦላቸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በበረሃ ያውም በምሽት ሕዝቡን በውኃ አጠገብ በሣር ላይ አስቀምጧቸው መመገቡ ‹‹በፍጻሜው ዘመን በምቹ ሥፍራ በመንግሥተ ሰማያት መንፈሳዊ ምግብ እመግባችኋለሁ፡፡ በውኃ (በጥምቀት) በሚገኝ ክብርም አከብራችኋለሁ›› ሲላቸው ነው፡፡

በዚህ ታሪክ ውስጥ አምስቱ እንጀራ የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር ምሳሌ ነው፡፡ እነዚህም፤ ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፣ምሥጢረ ጥምቀት፣ምሥጢረ ቁርባን እና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ናቸው፡፡

ሁለቱ ዓሣ ደግሞ የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ፍቅረ እግዚአብሔር ማለት እግዚአብሔር አምላክን በፍጹም ነፍስና በፍጹም ሐሳብ መውደድ ነው፡፡ ፍቅረ ቢጽ ደግሞ ባልንጀራን እንደራስ አድርጐ መውደድ ነው፡፡ (ዘዳ.፮፥፭፣ማቴ.፳፪፥፴፯) በተጨማሪም እንጀራውና ዓሣው የሥጋውና የደሙ ምሳሌ ነው፡፡ ይህን የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓል በማስበም ገቢረ ተአምርም በማሰብ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕለቱን በመዘከር (ጥር ፳፰) በዓሉን ታከብራለች፡፡

ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፤ አሜን፡፡