በዓለ ፅንሰት

መጋቢት ፳፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በተከበረች መጋቢት ፳፱ ቀን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የከበረ መልአክ ገብርኤል የምሥራች የነገረበት ድኅነትን የተመላች ታላቅ በዓል ናት፡፡ በዚህም የከበረ ወንጌል ምስክር ሆኗል፡፡

ኤልሳቤጥ ከፀነሰች በኋላ በስድሰተኛው ወር መልእኩ ገብርኤል የገሊላ ክፍል የሆነች ናዝሬት ወደ ምትባል ሀገር ከዳዊት ወገን ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው የታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፡፡ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነው፡፡

መልአኩም ወደርሷ ገብቶ ‹‹ደስ ይበልሽ፤ ጸጋን የተመላሽ ሆይ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነው፡፡ አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረከች ነሽ›› አላት፡፡ እርሷም አይታ ከንግግሩ የተነሣ ደንግጣ እንዴት ‹‹እንዲህ ያለ ሰላምታ እንዴት ይደረግልኛል?›› ብላ አሰበች፡፡ መልአኩም እንዲህ አላት፤ ‹‹ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና አትፍሪ፡፡ እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፡፡ እርሱ ታላቅ ነው፡፡ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፡፡ ለያዕቆብ ወገንም ለዘለዓለም ይነግሣል፡፡ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም፡፡››

ቅዱስት ማርያምም መልአኩን ‹‹ወንድ ሳላውቅ ይህ እንደምን ይሆናል?›› አለችው፤ መልአኩም መልሶ ‹‹መንፈስ ቅዱስ መጥቶ ያድርብሻል፤ የልዑል ኃይልም ያጸናሻል፤ ከአንቺ የሚወለደው ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ነው፡፡ እነሆ ዘመድሽ አልሳቤጥ እርሷዋ ደግሞ በእርጅናዋ ፀነሰች፡፡  እርስዋም መካን ትባል ነበረ፤ ይህም የሆነው ስድስተኛው ወር ነው፡፡ ለእግዚአብሔር የሚሣነው ነገር የለምና›› አላት፡፡ ማርያም ‹‹እነሆኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደ ቃልህ ይደረግልኝ››  አለችው፡፡ (ሉቃ.፩፥፳፰-፴፰)

በዚያን ጊዜም ድንግል ስትሆን ረቂቅ ፅንስን ተቀበለች፡፡ የእግዚአብሔር አካላዊ ቃል ወልድ ዋሕድ ለኩነተ ሥጋ ወርዷልና፤ ይህም አንድ ባሕርይ አንድ ህልውና ሲሆን ከሦስቱ አካል አንዱ ነው፡፡ ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ የነበረ፣ በማይመረመር፣ እንዴትም እንደሆነ በማይታወቅ ድንቅ በሆነ ተዋሕዶ  በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ፡፡

በዚያ ጊዜም የኋላ ኋላ መለየት ከቶ የሌለውን ፍጹም ሰውነት ነሥቶና ተዋሕዶ መለኮቱ ከትስብእቱ ጋራ ያለ መለያየት አንድ ሆኗል፡፡ ይህችም ዕለት የበዓላት ሁሉ በኵር ናት፤ በእርሷም የዓለም ድኅነት ተጀምሯልና፡፡

ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከቸር አባቱና ይቅር ባይ ከሆነ መንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ ይሁን፤ አሜን፡፡

ከመጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ መጋቢት