ጾመ ሐዋርያት

በተክለሐዋርያት

ጾመ ሐዋርያት በወርኃ ሰኔ ስለሚጾም በምእመናን ዘንድ የሰኔ ጾም በመባል ይታወቃል፤ ከሰባቱ የዐዋጅ አጽዋማትም አንዱ ነው፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለስብከተ ወንጌል ከመሰማራታቸው በፊት የጾሙት ጾም ነው፡፡

ይህም ጾም ከበዓለ ኀምሳ በኋላ የሚጾም ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በአርባኛው ቀን ቅዱሳን ሐዋርያት በጸሎት ይተጉ ወደ ነበረበት ቤት በመሄድ ደቀመዛሙርቱን ይዟቸው ከቤት በመውጣት መንገድ ጀመረ፡፡ እርሱ ከፊት እየመራቸው እነርሱ እየተከተሉት ወደ ረጅሙና በረጃጅም ዛፎች ወደ ተሞላው ደብረ ዘይት ተራራ ይዟቸው ወጣ፡፡ ይህንንም እየነገራቸው ከምድር ወደ ሰማይ ከፍ፤ከፍ አለ፡፡ ነጭ የሆነች ብሩህ ደመናም አምላካችንን ተቀበለችው፡፡ከዓይናቸውም እየራቀ፤ከእይታቸው በርቀት ሳይሆን በርኅቀት ተሰወረባቸው፡፡ሐዋርያትም ኢየሱስ ክርስቶስን በጣም ይወዱት ስለነበር ሲለያቸው አዝነው አተኩረው ሰማዩን ለረጅም ሰዓት ተመለከቱ፡፡ ድንገትም ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ቅዱሳን መላእክት በአጠገባቸው ቆመው ታዩአቸው፡፡መላእክትም ሐዋርያትን እንዲህ አሏቸው፤ ‹‹እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እያያችሁ ለምን  ቆማችኋል፡፡ ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል›› አሏቸው፤ (ሐዋ. ፩፥፰-፲፩)፡፡ ሐዋርያትም የመላእክትን ማረጋጊያ ቃል ከሰሙ በኋላ  በኢየሩሳሌም ወደ ምትገኘው ቤተ መቅደስ በመሄድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነገራቸው እስኪፈጸም ድረስ ቀን ከሌሊት በአንድነት ሆነው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከመካከላቸው አድርገው በጾምና በጸሎት እየተጉ ቆዩ፡፡

የጾመ ሐዋርያት የጊዜ ቀመር ሥሌት በዓለ ጰራቅሊጦስ እንደ ገባ ባለው የመጀመሪያው ሰኞ ይውላል፡፡ ጌታችን አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ደቀ መዛሙርቱን ይህን ጾም እንደሚጾሙት እንዲህ ተናግሮ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው። ‹‹እኛና ፈሪሳውያን፥ ብዙ እንጾማለን፥ ደቀ መዛሙርትህስ ለምን አይጾሙም? አሉት›› (ማቴ.፱፥፲፬)።  ደቀ መዛሙርቱ ይህንን በጠየቁት ጊዜ ጌታችን እንዲህ ብሎ መልሶላቸው ነበር፡፡‹‹ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ የሙሽራው ሚዜዎች ሙሽራው  ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ አይችሉም፤ ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ያንጊዜም ይጾማሉ›› (ማቴ.፱፥፲፭)፡፡

እኔ ሳለሁ አይጾሙም ማለቱ እርሱ ካልሞተና ካላረገ፤ መንፈስ ቅዱስም ካልተሰጣቸው በመንፈስ ቅዱስ ባልታደሰ ሰውነት ጾመው ድል መንሳት ስለማይቻላቸው ነው፡፡ ይህን ጾም የምንጾመው ሐዋርያት ጾመው ጸልየው ድል ያደረጉትን ዓለም እኛም የምናሸንፍበት ኃይል እንዲሰጠን ፈጣሪያችንን አምላከ ሐዋርያት ተለመነን እያልን ለመማጸን ነው፡፡

ይህን ጾም እንደ ሌሎቹ አጽዋማት ሁሉ እያንዳንዱ ምእመን ሊጾመው የሚገባ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ግን አብዛኛው ምእመን ‹‹የቄስ ጾም›› ነው በማለት ከጾሙ ሽሽት ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ይህ ሥርዓተ ቤተክርስትያንን መሠረት ያደረገ ባለመሆኑ መስተካከል ይገባዋል፡፡

ሐዋርያትን አብነት በማድረግ ጾመን በረከትን ልናተርፍ ይገባናል፡፡

የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት

የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት

የቅዱሳን ሐዋርያት በረከት

የጻድቃን የሰማዕታት ጸሎት እና ምልጃ አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር

አሜን፡፡

‹‹እስከ በዓለ ኀምሳ በኤፌሶን እቆያለሁ›› (፩ኛቆሮ.፲፮፥፰)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የቤተክርስቲያን የልደት ቀን ብሎ የጠራው ቀን በዓለ ኃምሳ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ እንደሚከበር ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ምስክር ነው፡፡በዓለ ኃምሳ፤ በዓለ ጰራቅሊጦስ፤ በዓለ ጰንጠቆስጤ እየተባለም ይጠራል፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተነገረም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለቅዱሳን ሐዋርያት፤ ለሰብአ አርድእትና ለቅዱሳት አንስት ጸጋውን ያደለበት፤ ምሥጢራትን የገለጠበት፤ መንፈሳዊ ጥብዓትን (ጥንካሬን) የሰጠበት፤ ታላቅ ቀን ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ዓለምን የሞላችው ወደ ሁሉ የደረሰችው በዚህ ቀን ከመንፈስ ቅዱስ በተቀበለችው ጸጋ ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደመሠከረው መንፈስ ቅዱስ ባይወርድላት ኖሮ የቤተክርስቲያን ሕልውና ከስሞኖ ቀጭጮ ይቀር ነበርና ነው፡፡

ይህች ቀን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ ኢዩኤል አንደበት ‹‹ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፤ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ደግሞ በዚያም ወራት በወንዶችና በሴቶች ባርያዎች ላይ መንፈሴን አፈሳለሁ፡፡›› በማለት የተናገረው ትንቢታዊ ኃይለ ቃል ፍጻሜውን ያገኘበት ዕለት ናት፡፡ ይህች ቀን ቅድመ ሥጋዌ በነቢዩ አንደበት ይህን የተናገረ አምላክ በፍጹም ተዋሕዶ በሥጋ ማርያም ተገልጦ ለአባቶቻችን ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጠው የተስፋ ቃል የተፈጸመባት ዕለት ናት፡፡ (ኢዩ.፪፥፳፰፤የሐዋ.፪፥፲፯)

በዓለ ኃምሳ፤ በዓለ ጰራቅሊጦስ፤ በዓለ ጰንጠቆስጤ እየተባለ የሚጠራ እንደመሆኑ መጠን ይህ ወቅት የነገረ መንፈስ ቅዱስ ትምህርት በስፋት የሚሰበክበት ወቅት ነው፡፡ ከዚህም በመነሣት እግዚአብሔር የፈቀደልንንና የገለጠልንን ያህል ስለ መንፈስ ቅዱስ በነገረ መለኮት ትምህርት  መማር እንችላለን፡፡ በዚህ ትምህርት ውስጥም ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ማንነት እርሱ በገለጠላቸው መጠን አምልተው አስፍተው ያስተምራሉ፡፡

በመንፈስ ቅዱስ ላይ የተነሡ የክሕደትና የኑፋቄ ትምህርቶችንም ይመረምራሉ፤ ለሚነሡ የክሕደት ትምህርቶችም ኦርቶዶክሳዊ ምላሽን ይሰጣሉ፤ የክሕደቱ አመንጪ መናፍቃንንም ማንነትና የክሕደት ምክንያቶቻቸውን ይገልጣሉ፡፡

መንፈስ ቅዱስ ጸጋውን የሚያድለው እርሱም የሚገኘው አንድነትና መተባበር ባለበት ሥፍራ ነው፡፡ በዕለተ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ጸጋውን ያደላቸው በአንድነትና በእምነት ተሰብስበው በነበሩበት ሁኔታ እንደነበር መጽሐፍ ሲነግረን «በዓለ ኃምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ›› ይለናል፡፡ (የሐዋ.፪፥፩-፪) እኛም የአባቶቻችን ልጆች በመሆናችን እርሱ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሆኑን አናምናለን፡፡

 

ክፉን በጋራ እናርቅ

 መጋቤ ምሥጢር ስንታየሁ አባተ

ኢትዮጵያ ሥነ ፈለክንና ሥነ ከዋክብትን፤ በአንድ አምላክ የማምለክን ፅንሰ ሐሳብ ያበረከተች ሀገር ናት:: በእነዚህ ሁሉ ዘመናት እጅግ ሰፊና ጥልቅ የእምነት የባህል የፍልስፍና አስተምህሮዎችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ስታስተላልፍ ቆይታለች:: ይህ ማለት ደግሞ ዜጎቿ ከጥንት ጀምሮ የራሳቸው የሆነ ጠንካራ የሥነ ጾታ የትዳር የቤተሰብ አስተምህሮ አላቸው:: አንድ ወንድ በአንዲት ሴት፤ አንዲት ሴት በአንድ ወንድ ጸንተው የሚኖሬባት ሀገር ናት፡፡ ተፈጥሯቸው ከሰው እጅግ ባነሱና አእምሮ በሌላቸው በእንስሳት ዘንድ እንኳን የማይታሰብ የተመሳሳይ ጾታ ርኩስነትን የሚጸየፉ መሆናቸውም የዜጎቻችን የማይለወጥ እምነት ነው:: ይህን እምነት በሕዝቡ ልቡና በማሥረፅ ደግሞ ግንባር ቀደም መሪዎቹ የሃይማኖት መሪዎች ናቸው:: እነዚህ መሪዎች የሚያስተምሩባቸው የተቀደሱና የእግዚአብሔር በረከት መቀበያ መካናት ገዳማት አድባራት አሏቸው:: እነዚህን ሕዝቡ ከራሱ በላይ የሚሳሳላቸውን፤ ከአምላክ በረከት የሚያገኙባቸውን፤ በጫማው እንኳን የማይረግጣቸውን፤ አቧራውን በእምነት ዘግኖ በመቀባትና በውኃ በጥብጦ በመጠጣት ፈውስ የሚያገኝባቸውን የተቀደሱ ቦታዎች ከመጥፎና ከረከሰ ሥራቸው የተነሣ የሚጸየፋቸው «ሰዎች» በጉብኝት ስም የከበረውን ሲያረክሱበት ማየት የሚችል ተፈጥሯዊ ሰብእና ሊኖረው አይችልም::

በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ ከተፈጠሩ በኋላ እግዚአብሔር በማይከበርበት፤ ከክፉ ምኞታቸው የተነሣ ለርኩስ መንፈስ የተሰጡትን ግብረ ሰዶማውያንን ቀርቶ ሌላውን መፍራት አባቶቻችን አላስተማሩንም:: እኛ የፈራነው ግርማ አልባ አካላቸውን ሳይሆን ከእግዚአብሔር መንፈስ በተራቆተ ሕይወታቸው የሌላ በሆነ መንፈሳቸው ተመልተዋልና ምድራችንን እንዳያጎሰቁሉ ነው:: ከዚህም በተጨማሪ «የራሳችንን አስተሳሰብ በማንም ላይ ለመጫን አይደለም» የሚለው የቶቶ የግብረ ሰዶማውያን አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት የዳን ዌር አባባል አሳማኝ አይደለም:: «የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሰው የሚያስፈራው ነገር ያለ አይመስለኝም:: የማንንም ሃይማኖት ልንጋፋም ሆነ የራሳችንን አስተሳሰብ በሰዎች ላይ ለመጫን አይደለም ወደ ኢትዮጵያ የምንሄደው:: እንዲያውም ባህሉን ለማየትና ለመረዳት እንዲሁም ለማድነቅ ነው የምንፈልገው» የሚል መግለጫ ሰጥተዋል::

ነገር ግን ተቃራኒ አስተሳሰብን ወደ ሌላው ለማሥረፅ እኮ የግድ ማስተማር፤ መወያየት ወይም መከራከር አያስፈልግም::ማንኛውም ትምህርትና ልምድ የሚቀሰመው በማትና በመስማት ነው:: ስለሆነም ይህንን መጥፎ ተግባር ይዘው ወደ ሀገራችን እንዳይመጡ በእግዚአብሔር ስም እናሳስባለን::

ዳን ዌር በንግግራቸው «ባህሉን ለማየትና ለማድነቅ» ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ መወሰናቸውን ገልጸዋል:: የኢትዮጵያ ባህል የኢትዮጵያውያን የእምነት ተቋማት አስተምህሮ ውጤቶች ናቸው:: ባህሎቻችን የተቀረፁትና መልክ የያዙት በሃይማኖታዊ አስተምህሮዎቻችን ነው:: በዚያ ላይ እንጎበኛቸዋለን ብለው ያቀዷቸው ቦታዎች የእምነት ማእከላት እንጂ የባህል መገለጫዎች አይደሉም:: ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፤ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም፤ አክሱም ጽዮን ማርያም፤ ጎንደር ዐርባ አራቱ ታቦታት ወይስ የጣና ሐይቅ ገዳማት፤ የትኞቹ ናቸው የባህል መዳረሻዎች?

ኢትዮጵያ መመኪያዋ ጉልበቷና ተስፋዋ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን፤ ሀገራችን ያለፉትን እጅግ መራራና ዘግናኝ ጦርነቶችን የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት ተቋቁማ ያሳለፈችው  እግዚአብሔር ክንድ፤ ተስፋና መመኪያ ሆኗት እንጂ በምዕራባውያኑ ርዳታ አይደለም:: መሪዎቻችን በሁሉ ታናሽ ስትሆኑ በታላቋ ኢትዮጵያ ላይ በክቡር ዜጎቿም ላይ መሪ አድርጎ ያስቀመጣችሁን እግዚአብሔርን አስቡት:: የሃይማኖት አባቶችም በዚህ ጉዳይ ግንባር ቀደም መሪ ሆናችሁ እነዚህ ግለሰቦች ወደ ሀገራችን እንዳይገቡ ማሳሰብ አለባችሁ::

ኢትዮጵያውያን በታሪካችን ሌላውን ወረን አናውቅም:: በትዕቢት ሀገራችንን፤ እምነታችንን፤ ባህላችንንና ትውልዳችንን ሊወር የመጣውን ደግሞ እጅ ነሥተን መመለስ እንችልበታለን:: በመሆኑም ጊዜው ደርሶ አላስፈላጊ ነገር ውስጥ ሁላችንም ከመግባታችን በፊት ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ማእከላዊው መንግሥት በሥልጣን ላይ ያላችሁ ኃላፊዎች በየእምነታችን ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ሲኖዶስ ያለን የእምነት አባቶች ክፉውን በጋራ ለማራቅ እንመካከር:: በየአድባራቱና በየገዳማቱ ያለን ሁላችንም ኢትዮጵያ ተስፋዋና ኃይሏ እግዚአብሔር ስለሆነ ራሳችንን በንስሓ አንጽተን እንጸልይ::

 

«ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች»መዝ፤ ፷፯፥፴፩

በሕይወት ሳልለው 

ሀገራችን ኢትዮጵያ ክርስትናን ከተቀበሉት ቀደምት ሀገሮች አንዷ ናት፤ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር፤ ፷፯፥፴፩ ላይ «ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች» ብሏል፡፡

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ኢትዮጵያዊት ሴት ባገባበት ዘመን ኢትዮጵያ በሕገ ልቡና አምልኮተ እግዚአብሔርን ትፈጽም ነበር፤ የብሉይ ኪዳን እምነትና የሕገ ኦሪት ሥርዓት ደግሞ በንግሥተ ሳባ ዘመነ መንግሥት መጀመሩን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ ይህም የሆነው ንግሥተ ሳባ ስለ ንጉሥ ሰሎሞን ጥበብና አገዛዝ ለማወቅ እጅግ ትመኝ ስለነበር ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛ በተማረችው ትምህርተ ኦሪት ነው፡፡

በዚያን ዘመን ታምሪን የተባለ ጎበዝ የነጋዴዎች አለቃና የንግሥት ሳባ አገልጋይ ነበር፤ ብልህና አስተዋይ ስለነበር ወደ ኢየሩሳሌም በተጓዘበት ወቅት የንጉሥ ሰሎሞንን ጥበብና አገዛዝ አደነቀ፡፡ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ሲመለስ ስለንጉሡ ለኢትዮጵያዋ ንግሥት ይነግራት ነበር፤ እርሷም ይህንን በሰማች ጊዜ በዓይኗ ለማየት፤ ጥበቡንም በጆሮዋ ለመስማት ተመኘች፡፡ ለሕዝቦቿም እንዲህ አለቻቸው «ወገኖቼ!፤ ነገሬን አድምጡኝ፤ እኔ ጥበብ እሻለሁ፤ልቤም እውቀትን ትፈልጋለች፤ በጥበብም ፍቅር ተነድፌአለሁ፤ በጥበብ ገመዶችም ተይዣለሁ፤» (ክብረ ነገሥት ፳፬)፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ሀገሩ ሂዳ ጥበብን ለመመርመር እንደምትሻ ለአገልጋይዋ ነገረችው፤ ታምሪንም ምኞቷን ያሳካ ዘንድ ጉዞዋን አመቻቸላት፤ሕዝቦቿም ንግሥታቸውን ወደ ጠቢቡ ሀገር ሸኟት፡፡

ለስድስት ወር ከተጓዘች በኋላ ኢየሩሳሌም ደረሰች፤ ስለእርሷ ከነጋዴው ታምሪን የሰማው ንጉሥ ሰሎሞን በክብር ተቀበላት፤ «የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ስም፤የእግዚአብሔርን ስም በሰማች ጊዜ ሰሎሞንን በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች፤» ቀዳማዊ ነገሥት ፲፥፩-፲፫፡፡ ስለ ጥበብ የሚያውቀውን ሁሉ ነገራት፤አስተማራትም፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለዚያን ጊዜ ትውልደ አይሁድን ሲወቅሳቸው እንዲህ ብሏቸዋል፤ «በፍርድ ቀን ንግሥተ አዜብ ትነሳለች፡፡ ይህችንም የቃሌን ትምህርት ያልሰሙትን እነዚያን ትውልዶች ትዋቀሳቸዋለች፤ ትፋረዳቸዋለች፤ ታሸንፋቸዋለችም፡፡የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና»(ክብረ ነገሥት ፳፩)፤ንግሥተ አዜብ ያላትም የኢትዮጵያን ንግሥት ነው፡፡

ከዚያ በኋላ ንጉሡ ከእርሷ ዘር ሊያገኝ ወደደ፤ለስድስት ዓመት በእርሱ ግዛት ተቀመጠች፡፡ ንግሥተ ሳባም ፀነሰች፤ ሆኖም ወደ ሀገሯ የመመለሻ ጊዜ ሲደርስ ንጉሡን «እሄድ ዘንድ ተወኝ» አለችው፤ ንጉሡም እንድታስታውሰው ብሎ የጣት ቀለበቱን ከእጁ አውልቆ ሰጣት፤ በብዙ ግርማም ሸኛት፤(ክብረ ነገሥት ፴‐፴፩)፡፡

ከዘጠኝ ወርና አምስት ቀናት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ላይ በነበረችበት ወቅት ዲሰሪያ ውስጥ ባላ በተባለ ከተማ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሀገሯ ስትደርስ ከንጉሡ ሰሎሞን የተማረችውን ጥበብ እንዲሁም የተቀበለችውን የኦሪት እምነት ለሕዝቦቿ አስተማረች፤ ግዛቷንም በሕገ እግዚአብሔር እንዲመራ አደረገች፡፡

ልጇም ምኒልክ ፲፪ ዓመት በሞላው ጊዜ አባቱን እንድታሳየው ለእናቱ ደጋግሞ ይጠይቃት ጀመር፤ንግሥተ ሳባም የልጇን ጭንቀት ለማቅለል አባቱም እናቱም እርሷ እንደሆነች ልታሳምነው ሞከረች፡፡ እድሜው ፳፪ በደረሰ ጊዜ ምኒልክ አባቱን ለማየት ወደ እስራኤል እንደሚሄድ ነገራት፤ ከነጋዴው ታምሪን ጋርም ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዙ፡፡

የልጁን ወደ ሀገሩ መምጣት የሰማው ንጉሥ ሰለሞን እጅጉን በመደሰቱ በክብር ተቀበለው፤  ግርማ ሞገሱና መልኩ አባቱን ይመስል ነበር፤ ሲያገኘውም ልጁ መሆኑን አምኖ እንዲቀበል ለምልክት ብላ እናቱ የሰጠችውን ቀለበት አሳየው፡፡ ንጉሡ ግን መልካቸው መመሳሰሉ ብቻ በቂ ማስረጃ መሆኑን በፍቅር አስረዳው፤ አቅፎም ሳመው፡፡

ነገር ግን ምኒልክ የእናቱ ናፍቆት ነበረበት፤ ለአባቱም ወደ ሀገሩ መመለስ እንደሚፈልግ በነገረው ጊዜ ንጉሡ እጅግ አዘነ፡፡ ሐሳቡን ለማስለወጥ ብዙም ጣረ፤ በእርሱ ተተክቶ እንዲነግሥ ጠየቀው፤ ልጁ ግን ሊስማማ አልቻለም፡፡ በመሆኑም ንጉሥ ሰሎሞን መኳንቱን አማክሮ በስመ ዳዊት መርቆና ባርኮ ወደ ሀገሩ ላከው፤ ወደ ኢትዮጵያም በተመለሰ ጊዜ በአባቱ አገዛዝ ሥርዓት ቀዳማዊ ምኒልክ  ተብሎ ነገሠ፤ ሕገ ኦሪትም በሀገራችን በይፋ ታወጀ፡፡

 

 

ምስክርነት

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፰ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገራቸው ቃል «በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፤ በሰማርያ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮቼ ትሆኑኛላችሁ» የሚል ነው፡፡

ይሁዳ ኢየሩሳሌምን የሚያጠቃልል ግዛት ነው፤በኢየሩሳሌም የጌታችን ተአምር የተፈጸመበት፤ ብዙ ሰው ስለ እርሱ የሰማበትም ከተማ ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም ይልቅ በይሁዳ ስለ ክርስቶስ የሚያውቁም የሚሰሙም ዝቅተኛ ናቸው፡፡ ሌላው ሰማርያ ነው፤ ሳምራውያን ከአይሁድ ጋር በሥርዓት አይተባበሩም፤ በመጽሐፍ ቁጥርም፤ በባህልም፤ በቤተ መቅደስም አይገናኙም፤ አንዱ አንዱን ይጸየፈዋል፡፡

እኛስ በሕይወታችን ውስጥ ለሃይማኖታችን እየመሰከርን ነው? ከሐዋርያት ሥራ እንደምናነበው ቅዱስ እስጢፋኖስ መከራ በተቀበለ ጊዜና በክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ላይ ሰይፍ በተመዘዘ ጊዜ ሁሉም ከኢየሩሳሌም እየወጡ ተጉዘዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን፤ ቤታቸውንና ሀገራቸውን ትተው ወደ አሕዛብ ሀገር ሄዱ፤ በሔዱበት ቦታ ግን ወንጌል ተሰበከች፤ እነርሱ በሥጋ ቢጎዱ ቤተ ክርስቲያን ግን ተጠቅማለች ፡፡ የእኛ ወገኖች ቻይና፤ ዓረብ፤ አውሮፓና አፍሪካ ገብተዋል፤ ኢትዮጵያዊ ዘር ምናልባት ያልገባበት አንታርቲካ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ እነርሱ በሄዱበት ሁሉ  ወንጌል አስተማሩ የሚል መጽሐፍ ተጽፎልናል? ዛሬ ግን ኢትዮጵያ ወንጌል ተሰበከ ሳይሆን የሚሰማው ተጣሉ፤ተበጣበጡ፤ይተማማሉ ይቀናናሉ የሚል ነው፤ ይህ ነው ወንጌል? ወንጌል የሰላም፤ የፍቅርና የደኅንነት ምንጭ ነው፤የብጥብጥ፤ የጦርነት ፤የጭቅጭቅ ግን አይደለም፡፡

ከሐዋርያት ዕጣ ፈንታ በገዛ እጁ በጠፋው በይሁዳ ምትክ ሰው ለመተካት ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ «ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ከእነዚህ ሰዎች አንዱ የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል» ብለዋል፤ በሐዋርያት ሥራ ፩፥፳፪፡፡ ሁለቱን ሰዎች ዕጣ የምንጥለው ለምንድን ነው? ለሚለው የሰጡት መልስ «ከሁለቱ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር እንዲሆን» የሚል ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ፤ አስተማረ፤ ተያዘ፤ ተገረፈ፤ ተሰቀለ፤ሞተ፤ተቀበረ፤ተነሣ የሚለው ቃል የትንሣኤው ምስክር ነው፡፡

እኛስ የማን ምስክር ነን? ብዙዎቻችን ጥሩ የፊልም ተዋናዮች ነን፤ ስለ እነርሱ ተናገሩ ብንባል የምንናገረውን ስለ ቅዱስ ጳውሎስ ተርኩ ብንባል አንተርክም፡፡ ስለ አንድ ዘፋኝ የምንናገረውን ያህል ስለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፤ ስለ ቅዱስ ያሬድ ተናገሩ ብንባል አንናገርም፤ የፊልም ተዋናዮቹንና የዘፋኞቹን ፎቶ ደረታችን ላይ ለጥፈን እየተንጠባረርን የምንሄደውን ያህል የቅዱሳንን ሥዕል በቤታችን ለመስቀል እናፍራለን፡፡ ታዲያ የማን ምስክሮች ነን? ዛሬ ኢትዮጵያውያንን በየቦታው እያጨቃጨቀን ያለው ስለ ምግብ ነው? ይበላል ወይስ አይበላም፤ ያገድፋል ወይስ አያገድፍም፤ የማያገድፍ ነገር በዚህ ምድር ላይ መተው ብቻ ነው፡፡

የሁላችንም ምስክርነት የትንሣኤው መሆን አለበት፤ ለምን የትንሣኤው የሚለውን መረጡ? ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን ድል አድርጎ መነሣቱንና በሞት ላይ፤ በዲያብሎስ ላይ ኀይል እንዳለው፤ የተረዳነው በትንሣኤው ስለሆነ ነው፡፡ የትንሣኤው ምስክር ነው ወይስ ነገ የምንቃጠለውን ቃጠሎ ዛሬ እየመሰከርን ነው?‹‹እነሆ ቀን እንደ እሳት እየነደደ ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፤ ሚል.፬፥፩፡፡

ምስክሮቼ ትሆናላችሁ የሚለው ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው ለሐዋርያት ነው፤ በኋላ ግን ሃይማኖታቸውን የገለጡ፤ ያስፋፉ፤ የመሰከሩ፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ለአሕዛብ የሰበኩ ሁሉ ምስክሮች ተብለዋል፡፡ ጌታም በወንጌል፤ «በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊት የሚክደኝን ግን እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ» ብሏል፤ ማቴ. ፲፥፴፪፡፡ ዛሬ ስለ ምስክሮች ስንሰማ በአእምሮአችን የሚመጡት እነዚህ ስለ እምነት ብለው በፈቃዳቸው መከራን መቀበል የቻሉ ምስክሮች ናቸው፡፡

ከትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉት ዕለታት ስያሜያቸውና ታሪካዊ አመጣጣቸው

ዲያቆን ተመስገን ዘገየ

ከትንሣኤ ሌሊት ፩ ሰዓት ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያለው ሳምንት የፉሲካ ምሥጢር የተገለጠበት፤ ከግብፅ ወደ ምድረርስት ከሲኦል ወደ ገነት መሻገርን የሚያመላክት ሳምንት ነው። ለፉሲካ የሚታረደውም በግ ፉሲካ ይባላል (ዘዳ. ፲፮÷፪:፭÷፮)፤ ፉሲካ ማለት ደግሞ ማለፍ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትም ሳምንት የፉሲካ ሳምንት ነበር፤ (ሉቃ. ፳፪፥፲፬-፲፮፤ ዮሐ. ፲፰፥፴፰-፵)።

እርሱም ንጹሕ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ደሙን ስላፈሰሰልን ፉሲካችን ክርስቶስ ተባለ፤ ብሉይ ደግሞ የሐዲስ አምሳል ነው። ይኸውም ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ባሕረ ኤርትራን ካሻገራቸው በኋላ ወደ ምድረ ርስት፤ ነፍሳት ደግሞ በክርስቶስ መሪነት ከሲኦል ወደ ገነት መግባታቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ ዕለቱም ሙሴ የወልደ እግዚአብሔር፤ በትረ ሙሴ የመስቀል ምሳሌ፤ግብፅ የሲኦል፤ የገሃነመ እሳት፤ የፈርዖን የዲያብሎስ፤ ሠራዊቱ የሠራዊተ ዲያብሎስ፤ እስራኤል የምእመናንና ባሕረ ኤርትራ የባሕረ ሲኦል ምሳሌ ነው፡፡

ሰኞማዕዶት (ፀአተ ሲኦል)

ማዕዶት የቃሉ ትርጓሜ መሻገር ሲሆን፤ በዚህ ቀን ቤተ ክርስቲያን ነፍሳት በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከሐሳር ወደ ክብር፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሲኦል ወደ ገነት መሻገራቸውንና ፉሲካችን ክርስቶስ መሆኑን ታስባለች።

ማክሰኞቶማስ

ቅዱስ ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን፤ በቀኖት የተቸነከረው እጁንና እግሩን ካላየሁ አላምንም በማለቱ ክርስቶስም «ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን» ብሎታል። ቶማስም «ጌታዬ አምላኬም»፤ ብሎ በመለሰ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስም «ስለ አየኸኝ አመንህን? ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓንስ ናቸው» አለው (ዮሐ ፳፥፳፯-፳፱)፤ ቶማስ የጌታን ፍቅር ተገንዝቦ ትንሣኤውን ስላመነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዕለቱን ቶማስ ብላ ታስበዋለች።

ዲዲሞስ የተባለ ከአሥራ አንዱ ደቀ መዛሙር አንዱ ቶማስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዝግ ቤት ገብቶ «ሰላም ለሁላችሁ ይሁን» ባላቸው ጊዜ ከእርሳቸው ጋራ አልነበረም»። ከ፲፪ቱ ሐዋርያት አንዱ (ማቴ. ፲፥፪-፫) ቶማስ በአራማይክ ዲዲሞስ በግሪክ መንታ ማለት ነው፤ (ዮሐ. ፳፥፳፬)፡፡ ቶማስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በፋርስና በሕንድ ወንጌልን እንዳስተማረ ይነገራል። ለቶማስ ጎኑን እንዲዳስስ የፈቀደው ለሌሎችም ቅዱሳን ሐዋርያት የተቸነከረውን እጅና እግሩን ያሳየው ካህናት ሥጋውና ደሙን እንዲፈትቱ ነው፤ ዮሐንስም በእጃችን ዳሰስነው ብሏል፤ (ሉቃ. ፳፬፥፴፱)፡፡

ለማርያም መግደላዊት ግን የተነሣ ዕለት አትንኪኝ ማለቱ ለሴቶች ሥጋውን ደሙን መፈተት አልተፈቀደም ሲል ነው ብለው ሊቃውንት ያትታሉ፤ «አትንኪኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሂጅና፡- ወደ አባቴ÷ ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬ÷ ወደ አምላካችሁም አርጋለሁ አለ ብለሽ ንገሪአቸው» አላት፤ (ዮሐ. ፳፥፲፯)። ገቦ መለኮቱን የዳሰሰች እጁ በሕይወት ትኖራለች፤ በሕንድ ሀገር ከታቦት ጋር በመንበር ላይ ትኖራለች። በየዓመቱ በእመቤታችን በዓል በአስተርእዮ ሊያጥኑ ሲገቡ የሚሾመውን ወጥታ ቀኝ እጁን ትይዘዋለች፤ ዓመት አገልግሎ ያርፋል።

ረቡዕአልዓዛር

አልዓዛር ክርስቶስ ያስነሣው የማርያምና የማርታ ወንድም ነው፤ የስሙም ትርጓሜ እግዚአብሔር ረድቷል ማለት ነው፤ (ዮሐ. ፲፩፥፯-፵፰)፤ አልዓዛር የሞተው መጋቢት ፲፯ ነበር፡፡ እህቶቹም ክርስቶስ እንዲመጣ መልእክት ልከውበት ነበር፤ ክርስቶስ ግን በ፬ኛው ቀን ማለትም  መጋቢት ፳ መጥቶ ከሞት አስነሥቶታል፤(ዮሐ.፲፩፥፵፬)፡፡ ፋሲካውንም በወዳጁ በአልዓዛር ቤት ያከብር ዘንድ  ከቀደ መዛሙርቱ ጴጥሮስንና ዮሐንስን አስቀድሞ ላከ፤ ከዚያም በአልዓዛር ቤት ሆኖ የሐዲስ ኪዳንን ሥርዓት ምሥጢረ ቁርባንን ሰርቶ ለደቀ መዛሙርቱ አሳያቸው፤ አልዓዛር ከተነሣ በኋላ በሐዋርያት ኤጲስ ቆጶስነት ተሸሞ ፵ ዓመት አገልግሎ ግንቦት ፳፯ ቀን ዐርፏል (ስንክሳር ግንቦት ፳፯)፡፡

አዳም ሐሙስ

አዳም የመጀመሪያ ሰውና የሰው ሁሉ አባት ነው፤ በ፮ኛው ቀን የተፈጠረ የሰው ሁሉ ምንጭ ስለሆነ የሰው ዘር ሁሉ ከእርሱ ተገኝቷል፡፡ በዚህ ዕለት ለአዳም የተሰጠው የተስፋ ቃል ስለመፈጸሙ፤ (ዘፍ. ፫÷፲፭) አዳም ከነልጆቹ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻ ስለመውጣቱ ይታሰብበታል፡፡ ክርስቶስ በተነሳበት በአምስተኛው ቀን ሐሙስ  አዳም ይባላል፤ ጌታችን አዳምን ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ  አድንሃለሁ ብሎ  ቃል ገብቶለት  እንደነበር በቀሌምንጦስ ተጽፏል፡፡

አዳምና ሔዋን በገነት ፯ ዓመት ከቆዩ በኋላ ትእዛዙን በመተላለፋቸው ከኤደን ገነት አስወጣቸው (ኩፋ.፬፥፲፮፤ዘፍ.፫፥፳፫) «ብዙ ተባዙ» ያለው ቃል እንዳይቀር በምድር ላይ ወርደው ልጆችን ወለዱ ይላል፡፡ የተወለዱትም ልጆችም በቁጥር ፷ እንደሆኑ (፩መቃ. ፳፰፥፮) የተወለዱት ልጆች ደጎችና ክፉዎች እንደ ነበሩ በአቤልና በቃየል ታውቋል፤ (ዘፍ. ፬፥፰)፤ አዳም በዚህ ዓለም ፱፻፴ ዓመት ኑሮ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፵፻፭፻፸ ሚያዚያ ፮ ዐርፏል፡፡

ዐርብቤተ ክርስቲያን

ዐርብ የእግዚአብሔር ቅድስት ማደሪያ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ተሰይማለች፤ ይህም ሁሉም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመባት ዕለት በመሆኗ ነው፤ ዕለተ ዐርብ፤ የሥራ መከተቻ፤ ምዕራብና መግቢያ በሚሉት ስያሜዎችም ትጠራለች፡፡

በዕለቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ያደረገውን ተአምር በመስቀሉ ድኅነትን እንዳሳየ፤ በቀራንዮ የሕንጻዋ መሠረት እንደተተከለላትና ሥጋ መለኮት እንደተቆረሰላት፤ ልጆቿን ከማሕፀነ ዮርዳኖስና ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የምትወልድበት ማየ ገቦ እንደፈሰሰላት ተገልጾባታል፤(ኤፍ.፪፥፲፱፤ራዕ.፩፥፮-፰)፡፡

ቅዳሜቅዱሳት አንስት

ቅዳሜ ቅዱሳት አንስት ተብሎ ይጠራል፤ ይህም ስያሜ በስቅለት ዕለት በልቅሶና በዋይታ የሸኙትን፤(ሉቃ. ፳፫፥፳፯) በዕለተ ትንሣኤ ሽቱና አበባ ይዘው ወደ መቃብር የገሰገሱትን፤ ከሁሉም ቀድሞ ጌታችን በዕለተ ሰንበት ተነሥቶ ለተገለጸላቸው ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ሰሎሜንም መታሰቢያ ለማድረግ ነው፤«ከሳንምንቱ በመጀመሪያዩቱ ቀን ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው እጅግ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ሌሎች ሴቶችም አብረዋቸው ነበሩ (ሉቃ. ፳፬ ፥ ፩ )፡፡

እሑድዳግም ትንሣኤ

«ያም ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለ ፈሩ ተሰብስበው የነበሩት ቤት ደጁ ተቆልፎ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና÷«ሰላም ለእናንተ ይሁን» አላቸው፤ ማቴ.፳፥፲፱፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ተሰውሮ ከሰነበተ በኋላ በዕለተ እሑድ በዝግ ቤት እንዳሉ ዳግም ተገለጸላቸው፤ስለዚህም ዳግም ትንሣኤ ተባለ፡፡

(ምንጭ:-መዝሙረ ማኅሌት ወቅዳሴ፤ ሥርዓተ አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፤ የዮሐንስ ወንጌል አንድምታ፤ ምዕ. ፳፥፳፬)

 

 

ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጋላችሁ? ሉቃ. ፳፬፥፭

ቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ

በኦሪት ዘፀአት ፲፪፥፳፩-፳፰ እንደተጻፈው ይህ ዕለት በብሉይ ኪዳን ፋሲካ በመባል ይታወቃል፡፡ ትርጉሙም መሻገር ማለት ነው፤ ይህም ሕዝበ እሥራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ ወጥተው ወደ ምድረ ርስት የተሸጋገሩበት ዕለት ነው፤ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ትንሣኤ ይባላል፡፡ በዓለ ትንሣኤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል ነሥቶ ነጻነትን ለሰው ልጆች ሰጥቶ ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከኀሳር ወደ ክብር የተሸጋገርንበት ዕለት በመሆኑ ትንሣኤ እንለዋለን፤ ቅዱስ ሉቃ.  ፳፬፥፭ የጻፈውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ስለ በዓለ ትንሣኤ ጥቂት ዐበይት ነገሮችን እንመልከት፡፡

ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጋላችሁ? ይህንን ጥያቄ የጠየቀው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር አጠገብ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ሲሆን ጥያቄው የቀረበላቸው ደግሞ በማለዳ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር የሄዱት ቅዱሳት አንስት ነበሩ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዋለበት ውለው ባደረበት አድረው የቃሉን ትምህርት የእጁን ተአምራት ያዩት ቅዱሳት እናቶች የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በተባለች በዕለተ እሑድ በማለዳ የመቃብሩን ጠባቂዎችና የሌሊቱን ጨለማ ሳይፈሩ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ሽቱ ለመቀባት ገሰገሡ፡፡ መልአከ እግዚአብሔር ይህንን ጥያቄ  በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር አጠገብ አቀረበላቸው፤ ቅዱሳት አንስት የመልአኩን ጥያቄ እንደሰሙ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን ከሙታን እንደሚነሣ የተናገረውን ቃል አስታወሱ፡፡ ከዚያም ቅዱሳት አንስት ወደ ሐዋርያት ሄደው ያዩትንና የሰሙትን ሁሉ ተናገሩ፤ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤውን አበሠሩ፤ ቅዱሳን ሐዋርያትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አለመሆኑን በግልጽ ተረዱ፡፡ የተሰቀለውን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ሕማሙንና ትንሣኤውን፤ በአባቱ ዕሪና በልዕልና መቀመጡን  ዞረው አስተምረዋል፡፡

በዓለ ትንሣኤ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፤ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ተስፋ አበውና ትንቢተ ነቢያት ተፈጽሞ በትንሣኤው የሞት ሥልጣን በመሻሩ የቤተ ክርስቲያን አበው በዓለ ትንሣኤን «የበዓላት በኵር» በማለት ይጠሩታል፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማምና ሞት አሳዛኝ ታሪክ ሳይኾን ሕያው እውነት ነው፤ የዓለም መድኃኒት የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የሐዋርያት ስብከት፤ የቤተ ክርስቲያን መሠረት ነው፡፡ ስለዚህም ዘወትር በጸሎተ ቅዳሴያችን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መሞታችንን፤ ከእርሱ ጋር መነሣታችንንና ሕያው መሆናችንን እንገልጻለን፤ ሕማሙንና ሞቱን፤ ትንሣኤውን፤ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን እንሰብካለን፡፡ በበዓለ ትንሣኤ በዕለተ ስቅለት የነበረው የኀዘን ዜማ በታላቅ የደስታ ዜማ ይተካል፤ በዚህ ዕለት ቤተ ክርስቲያን ነጭ ልብስ ለብሳ የደስታ ዝማሬ ታሰማለች፡፡

ከነቢያት ወገን ታላቁ ነቢይ ኤልያስ እንዲሁም ደቀ መዝሙሩ ኤልሳዕም በእግዚአብሔር ኃይል ሙታንን እንዳስነሡ ይታወቃል፤ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፰ ቍጥር ፲፬ ታሪኳ የተጻፈው የምኵራብ አለቃ የነበረችው ልጅ፤ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፯ ቍጥር ፲፪ ታሪኩ የተጻፈው ናይን በምትባል ሥፍራ የነበችው የድሃዪቱ ልጅ እንዲሁም በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፩ ታሪኩ የሚነበበው አልአዛር በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራት ከሙታን ተነሥተዋል፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ ኮረብታ ተሰቅሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በለየበት ሰዓት ቍጥራቸው ከስድስት መቶ የሚያንስ ከአምስት መቶ የሚበልጥ ሰዎች ከሙታን ተነሥተዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ዳግመኛ ሞተዋል፤ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ግን ከሁሉ ይለያል፤ እርሱ ከሙታን ለመነሣት አሥነሽ አላስፈለገውም፣ ከሙታን የተነሣው በራሱ ሥልጣን ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በማይሞት፤ በማይለወጥ ሥጋ በመነሣቱ እንደሌሎች ዳግመኛ ሞትና ትንሣኤ የለበትም፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በቀዳማዊ ቆሮንቶስ ምዕራፍ ፲፭ ቍጥር ፳፫ እንደተናገረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ሙስና መቃብርን አጥፍቶ(በማይሞትና በማይበሰብስ ሥጋ) በሞቱ ሞትን ድል ነሥቶ፤ የሞት መውጊያን አሸንፎ፤ ሲኦልን በዝብዞ ከሙታን በመነሣቱ የትንሣኤያችን በኵር(መሪ) ተብሏል፡፡ ዳግመኛም ይህ ሐዋርያ በቆላስይስ መልእክቱ ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፲፰ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን «የሙታን በኵር» በማለት ጠርቶታል፡፡

የድኅነታችን አለኝታ የእግዚአብሔር ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በሕማሙና በሞቱ የዲያብሎስን ቁራኝነት በማጥፋት አጋንንትን ድል የመንሣትን ኃይል ሰጥቶናል፡፡ ከጥንት ዠምሮ የሰውን ነፍስ የሚጎዳ የዲያብሎስን ሥልጣን ያጠፋ ዘንድ ፤ የፈጠረውን ዓለም ያድን ዘንድ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ፈቃድ፤ በአባቱ ፈቃድና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ወደዚህ ዓለም መጥቷል፡፡ የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን  ለመስቀል ሞት አሳልፎ በመስጠት በሥጋው ሞቶ በመለኮቱ ሕያው ሆነ፡፡ የሞት አበጋዝን ዲያብሎስን ኃይል ያጠፋ ዘንድ የማይሞተው የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሞተ፤ ሕይወት መድኃኒት በምትሆን ሞቱ ሞትን ያጠፋ ዘንድ፤ ሙታንን ያድን ዘንድ እርሱ የሕያው አምላክ ልጅ ሞተ፡፡ በኪሩቤል ላይ ያለው እርሱ በከርሠ መቃብር ሦስት መዓልትና ሌሊት አደረ፡፡ ያን ጊዜ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባታችን በአዳም በደል ተግዘው ወደ ሲኦል የወረዱት ነፍሳት በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነጻ አወጥቷቸዋል፡፡ ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱና ለንጹሐን ሐዋርያቱ እንደተናገረው በሦስተኛው ዕለት በሥልጣኑ ከሙታን ተነሥቷል፤ በዚህም ሙስና መቃብርን(በመቃብር ውስጥ መፍረስ መበስበስን) አጥፍቶልናል፤ ዳግመኛ ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ በመነሣቱ ለትንሣኤያችን በኵር ኾኖልናል፤ ቆላ.  ፩ ፥ ፲፰፡፡ በትንሣኤውም ትንሣኤያችንን ገልጦልናል፤ ከሞት ወደ ሕይወት መልሶናል፤ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው ለሰውነታችን ትንሣኤን፤ ለነፍሳችን ሕይወትን ሰጥቶናል፤ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፩ ቍጥር ፳፭ እንዳስተማረን እርሱ ትንሣኤና ሕይወት ነው፤ እርሱ የሕይወታችን መገኛ ነው፡፡

በዓለ ትንሣኤን ስናከብር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አለመሆኑን ማስተዋል ይገባናል፤ የእግዚአብሔር መልአክ በመቃብሩ አጠገብ ለተገኙት ሴቶች እንደነገራቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕያዋን መካከል እንጂ በሙታን መካከል አይገኝም፡፡ አባታችን አዳም የማይገባውን አምላክነት ሽቶ ዕፀ  በለስን በመብላቱ ሞተ ሕሊና፤ ሞተ ሥጋ እንዲሁም ሞተ ነፍስ አግኝቶታል፡፡ ዳግመኛም በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ሲኦል ተፈርዶበት ነበር፡፡ ሞተ ሕሊና በኃጢአት መኖር ነው፡፡ ንዋይ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ ፪ ቁጥር ፩ «በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችኹ» በማለት እንደጻፈው በኃጢአት መኖር ሞት ነው፤ ዳግመኛም ሐዋርያው እንዳስተማረን የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው፤ ሞተ ሥጋ የሥጋ ከነፍስ መለየት ነው፤ ሞተ ነፍስ ደግሞ የነፍስ ከጸጋ እግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ በአንጻሩ ትንሣኤም በሦስት ወገን ይታያል፤ ትንሣኤ ሕሊና(ልቡና) በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መመለስ፤ ትንሣኤ ዘሥጋ እንደወለተ ኢያኢሮስ፤ እንደአልአዛር ከሞት መነሣት በኋላም በትንሣኤ ዘጉባኤ ከሞት መነሣት ነው፤ ትንሣኤ ነፍስ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት በቀኝ መቆም ነው፡፡

ከንስሐ ሕይወት ተለይቶ ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ ርቆ ስለኃጢአታችን የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማግኘት ከእርሱም ጋር መኖር አይቻልም፡፡ ሞትን ድል አድራጊው የሕይወት ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር የሚሆነው እኛም ከእርሱ ጋር መኖር የምንችለው ለኃጢአታችን ሥርየት በቀራንዮ አደባባይ የተቆረሰውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለን ሕያዋን ስንሆን ነው፡፡ ፋሲካን መፈሰክ የሚገባን የዓለምን ኃጢአት ለማስወገድ በተሠዋው በእግዚአብሔር በግ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም እንጂ በእንስሳት ሥጋና ደም ሊሆን አይገባም፡፡ ለትንሣኤ በዓል ሊያስጨንቀን የሚገባው በገንዘባችን የምንገበየው ምድራዊ መብል መጠጡ ሳይሆን በጥበበ እግዚአብሔር ጸጋ ሆኖ የተሰጠን ቅዱስ ሥጋውንና ክብር ደሙን አለመቀበላችን ነው፡፡ በዓለ ትንሣኤ ሕያው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን ይገኝ ዘንድ በትንሣኤ ልቡና ሕያዋን የምንሆንበት መንፈሳዊ በዓል ነው፤ ስለዚህም በዓለ ትንሣኤን ስናከበር በትንሣኤ ሕሊና ሕያዋን ሆነን ቅዱስ ቍርባን መቀበል ይገባናል፡፡

 ተስፋ ትንሣኤን የምናምን ክርስቲያኖች ዘመናችን ሳይፈጸም የምሕረትና የፍቅር እጆቹን ዘርግቶ ወደሚጠራን ሕያው አምላክ በንስሐ እንቅረብ፤ በፈሪሃ እግዚአብሔር በፍጹም ፍቅር የተሰጠንን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንቀበል፡፡ ያንጊዜ ትንሣኤ ልቡና እናገኛለን፤ ያን ጊዜ በምሕረቱና በፍቅሩ በትንሣኤ ዘጉባኤ በክብር ተነሥተን በቀኙ እንቆማለን፤ የሰው ዐይን ያላየውን፤ ጀሮ ያልሰማውን፤ የሰው ልብ ያላሰበውን ዓለም ሳይፈጠር ለወዳጆቹ ያዘጋጀውን ተድላ ነፍስ የሚገኝበትን ገነት መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን፡፡

 ለመንግሥቱ ጥንት ወይንም ፍጻሜ የሌለው የሕያው አምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት በምትሆን ሞቱ የእኛን ሞት ወደ ሕይወት ለውጦ ቅድስት ትንሣኤውን ገልጦልናል፤ ብርሃነ ትንሣኤውን አሳይቶናል፡፡ የቆጵሮሱ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ መልሕቅ በሚባል መጽሐፉ «በትንሣኤውም የትንሣኤያችንንም ተስፋ ምሥጢር እንናገራለን» በማለት እንደተናገረው ዳግመኛም በኒቅያ የተሰበሰቡ አበው «የሙታንን መነሣት የሚመጣውንም ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን» በማለት በቀኖና ሃይማኖት እንደጻፉልን ክርስቲያኖች በመቃብር ያሉ፤ በተለያየ አሟሟት የሞቱ ሙታን ሁሉ የሚነሡበት ትንሣኤ ሙታን መኖሩን እናምናለን፡፡

 ሕያው አምላካችን ሕያዋን ሆነን እንኖር ዘንድ በመስቀሉ ወደ ሰማያዊ አባቱ አቅርቦናል፤ በእርሱና በእኛ መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶልናል፤ በቅድስት ትንሣኤው ትንሣኤ ልቡና የንስሐ በር ከፍቶልናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማኅየዊት በምትሆን ሞቱ የገነት ደጅን ከፍቶልናል፤ ፍሬዋንም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሰጥቶናል፤ ስለዚህም ሕያዋን እንሆን ዘንድ ወደ ሕይወት መድኃኒት ቀርበን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንቀበል፡፡ በሕይወታችን ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ እንዳይሠለጥንብን፤ ትንሣኤ ሕሊና ትንሣኤ ነፍስን እናገኝ ዘንድ የትንሣኤን በዓል በሕያውነት ጸንተን እንኖር ዘንድ ምግባር ትሩፋት በመሥራት እናክብር፡፡

የትንሣኤን በዓል ስናከበር ጽኑ ድቀትን፤ ኀፍረትንና ውርደትን አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት፤ በጭፈራና በዳንኪራ፤ በጣፋጭ መብልና መጠጥ ሰውነትን ማድከምና ልዩ ልዩ ኅብረ ኃጢአት ከመሥራት እንራቅ፤ ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ በኃጢአት በፍዳ እንዳንያዝ እንንቃ፡፡ በኃጢአት የተነሣ ተስፋ ትንሣኤ እንዳናጣ ዛሬ በንስሐ እንታጠብ፤ ትንሣኤ ሕሊና እናገኝ ዘንድ እንፍጠን፤ በትንሣኤ ዘጉባኤ እጥፍ ዋጋ የምናገኝበትን ለሌሎች በጎ ማድረግን፤ ለድሆች ማካፈልን፤ ሕሙማን መጎብኘትን ገንዘብ እናድርግ፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታውና ቸርነቱ ለዘለዓለሙ ከእኛ ጋር ይሁን፤  የአባቶቻችን ጥርጥር የሌለባት የቀናች ሃይማኖታቸው፤ ድል የማትነሣ ተጋድሏቸው የመንግሥቱ ወራሽ እንድንሆን ያብቃን፤ አሜን፡፡

ቤተ ክርስቲያንን ከጠላት ስውር ደባ ለመጠበቅ ጾምና ጸሎት ያስፈልጋል!

           

በሕይወት ሳልለው

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የድህነታችን መገኛና መገለጫ ናት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ለእግዚአብሔር የሚገባ ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፤ ወደ እርሱ አቀርባችሁ ዘንድ ለአንዱ ንጹሕ ድንግል ሙሽራ ለክርስቶስ አጫቻችኋለሁና” (፪ቆሮ ፲፩፥፪) ሲል በቆሮንቶስ መልእክቱ ገልጿል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በጠላት ስትታደን እንደኖረች ታሪክ ያስረዳናል፡፡ ልጆቿም እንደሷ ብዙ መከራን እንዳዩ፤ ያለበደላቸው መከራን እንደታገሱና ለእምነታቸው ብዙ መሥዋዕትነት እንደከፈሉም አንብበን ተረድተናል፡፡ ለምሳሌ “ዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን ያሳለፈችበት ዘመን ነበር፡፡ ሁልጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ስናይ ዕለተ ዐርብን እናስባለን፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የመሠረታት፤ካህናት፤ ቀሳውስትና አገልጋዮች የሥራ ድርሻቸውን የሚያካሂዱባት የተቀደሰች ስፍራ ቤተ ክርስቲያን ናት” በማለት መጋቤ ሐዲስ ቀሲስ መንግሥቱ ማርያም፤ በአዲስ አበባ ሀገር ስብከት የቦሌ ቡልቡላ መድኃኔዓለም ቤተ ክርቲስያን የስብከተ ወንጌል ሐላፊ አስረድተዋል፡፡

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ህልውናዋ ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየክፍለ ሀገራቱ አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ መሆኑ በይፋ እየተነገረ ነው፡፡ ከጅማው ክስተት በኋላ ቤተ ክርስቲያናችን ላይ በተደጋጋሚ ችግር ደርሷል፡፡ ለዚህ የሀገር ጉዳይ መፍትሔ ለማግኘት የሃይማኖት አባቶች፤ አገልጋዮችና የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ያቃጠሉ ሰዎች ሲያልፉ በዘመነ ሰማዕታት ውስጥ ያለፈች ቤተ ክርስቲያን ግን ዛሬም ነገም ምእመኖቿን አስተምራ፤ሥጋ ወደሙን እያቀበለች ትኖራለች፡፡

“የምእመናን ድርሻ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መከራ እንዲቆም ጾምና ጸሎት ያስፈልጋል፤ያለበለዚያ ግን እሳትን ሰማዕትነት ነው ብለን አናስበውም፤መከራ ነው እንጂ፡፡  ሰማዕታት የሃይማኖት ፍሬ እንዳያመልጣቸውና አክሊልም እንዳያልፈን በማለት ይሯሯጡ ነበር፡፡ በመጀመሪያ፤ እንኳን መንፈሳዊ ሥራ ሥጋዊ  ሥራም ያለ የእግዚአብሔር ፍቃድ አይሳካም” ሲሉም መጋቤ ሐዲስ ቀሲስ መንግሥቱ ማርያም ጨምረው አብራርተዋል፡፡

ይህ የጠላት ሴራና ክፋት በተለያየ መንገድ ምእመናንንና ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የሚደረግ በመሆኑ ከሥር መሠረት ልንመረምረው ይገባል፡፡ “የአማኞችን መብት ጠብቀው የአምልኮት ሥርዓታቸውን በሀገራቸው በነፃነት እንዲፈጽሙ የሃይማኖት መሪዎች ጥብቅና ሊቆሙላቸው ይገባል፡፡ ሲሰደዱ፤ ሲገደሉና ለተለያየ ጥቃት ሰለባ ሲሆኑ ዝም ብለን ማየት የለብንም፡፡ ይህ የአገልጋዮች ምግባር እየቀዘቀዘ በመሄዱ፤ ቤተ ክርስቲያን ለዚህ አይነት ተፅዕኖ ተዳርጋለች፡፡ አንዳንድ ሰዎች በኃይል ወይም በነውጥ የሚያደርጉት አግባብ የሌለው ተግባር ሊወገዝ ይገባል” ሲሉ የቅዱስ ጳውሎስ የሐዲስ ኪዳን መምህር መጋቤ ሐዲስ አእምሮ ደምሴ ገልጸዋል፡፡

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንድትደክም፤ ምእመናን ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር እንዲሁም የትክክለኛዋ ሃይማኖት ተከታይና ክርስቲያናዊ ምግባር እንዳይኖር በስውር ተመሳስለውና በስመ ሰባኪ የጠላትን ምኞት ለማሳካት ደፋ ቀና የሚሉ ተኵላዎችም በዝተዋል፡፡ “የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፤ በውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላዎች ናቸው”፤(ማቴ ፯፥፲፭) ሲል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ነግሮናል፡፡

ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የራቁ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ቀኖና፤ ሥርዓትና ትውፊት ውጪ በመሆን ከራሳቸውም አልፎ ሌሎችን ያስታሉ፡፡ ጠላታችን ዲያብሎስ ከጥንት ጀምሮ ምእመናንን ተስፋ ማስቆረጥ፤ ከእምነታቸውና ሃይማኖታቸው ማስወጣት ተግባሩ ነውና  ልንጸና ይገባል፡፡ ይህም የሚሆነው አምነን፤ተጠምቀን በበጎ ምግባር ታንጸን በሕገ እግዚአብሔር መኖር ስንችል ነው፡፡ በመጽሐፍ እንደተጻፋው እነዚህ ጸንተው ይኖራሉ የሚላቸው ሦስት ነገሮች እምነት፤ተስፋና ፍቅር  ናቸው፤ (፩ቆሮ ፲፫፥፲፫)፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልእክቱ እንደገለጸው “ደስ የሚላችሁን እንድታደርጉ እንረዳችኋለን እንጂ እንድታምኑ ግድ የምንላችሁ አይደለም”፤ (፪ቆሮ ፩፥፳፬) ፡፡

እንዲህ እምነት በጠፋበት፤ የመናፍቅ ቅሰጣ በበዛበት፤ ዓለም በኃጢአት ማዕበል በምትናወጥበት ወቅት ከሐሰተኞች ትንቢት መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ጌታችንም እንደተናገረው “የሚያስታችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ብዙዎችንም ያስታሉ፤ጦርነትን፥ የጦርነትንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠንቀቁ፤ አትደንግጡ፤ ነገር ግን ፍጻሜው ገና ነው”፤(ማቴ ፳፬፥፬-፮)፡፡

ከጠላት ስውር ደባ ለማምለጥ የእግዚአብሔር ቸርነት ከእኛ ጋር ሊሆን  ያስፈልጋል፡፡ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ያለንን ኅብረት ማጠንክር ስንችልም ፈጣሪያችን ያድነናል፡፡ እያንዳንዳችን ቤተ ክርስቲያን መሔድ፤ ክርስቲያናዊ ምግባርን ማዘውተር፤ ዘወትር መጸለይ፤ ንስሓ መግባትና መጾምም  ይጠበቅብናል፡፡

 

 

 

 

የምእመናን ተሳትፎ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት የጠበቀ ሊሆን ይገባዋል

                     

በሕይወት ሳልለው

የሰው ልጅ ሕይወት፤ድኀነት፤ሰላም፤ ፍቅርና ደስታ መገኛ እግዚአብሔር፤ ከሕገ ኦሪት ጀምሮ በሰጠን የድኀነት መንገድ፤ በመስቀሉ ላይም በከፈለልን መሥዋዕትነት የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ከጥንት ጀምሮ ምእመናንን በመሰብሰብና በማሰተባበር ሥርዓተ አምልኮን እንዲፈጽሙ ስታስተምር ኖራለች፡፡ በሕገ ወንጌልም አምላካችን በአስተማረን መሠረት የክርስቲያኖች መማፀኛ የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ልጆቿን በፍቅርና በሥርዓት እንድታሳድግ ፈቅዷልና በእምነት፤ እንድናከብራት የእግዚአብሔር  ፈቃድ ነው፡፡

 “በብሉይ ኪዳን ይኖሩ የነበሩ ምእመናን በሕገ ልቦና (ባልተጻፈ ሕግ) ይመሩ የነበሩ አበው እና በሕገ ኦሪት (በተጻፈ ሕግ) የነበሩ ቅዱሳን አባቶች አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረጋቸው የእግዚአብሔር ረድኤት ያልተለያቸው ነበሩ፡፡የሐዲስ ኪዳንን ስንመለከት “በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕር አምላክነት አምነው፤ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቁ ክርስቲያኖች ናቸው”፤ (የምእመናን ድርሻ በቤተ ክርስቲያን)፡፡

 አንድ አምላክ፤አንዲት ጥምቀት፤ አንዲት ሃይማኖት፤(ኤፌ4፥4) ይህን የክርስትና ሕይወት መርሕ መሠረት አድርገው የሚኖሩ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች፤ ለብዙ ዓመታት  ሥርዓተ አምልኮን በሚፈጽሙባት ቤተ ክርስቲያን፤ ከሃይማኖት አባቶች፤ ከካህናት፤ እንዲሁም ከሌሎች አገልጋዮች ጋር የሚያደርጉት ሱታፌ እምነታችውን፤ሥርዓታቸውንና አምልኮታቸውን ለማጠንከር ይረዳልና፤ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መኖር ያስፈልጋል፡፡ አብዛኞቹ  ኦርቶዶክሳውያን  ምእመናን  ዓመታዊ ክብረ በዓላት ላይ ብቻ ነው፡፡

መንክር መኩሪያና ዳዊት ጌታቸው ጥር ፲፩ ቀን ፳፻፲፩ የጥምቀት በዓልን በጃንሜዳ ሲያከብሩ ያገኘናቸው ወጣቶች ናቸው፡፡መንክር ጥምቀትን ከልጅነት ጀምሮ ስለሚያከብር በየዓመቱ ጃንሜዳ ይመጣል፡፡“በዘንድሮ በዓል በበገናውና መሲንቆ፤በመዘምራንንና መዝሙሮች የቀደመውን ሥርዓት የበለጠ ወድጄዋለው፡፡አገልጋዩቹም ባሕልና ትውፊታቸንን ይዘው በመቅረባቸው እናመሰግናቸዋለን”፡፡

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ትውፊት፤ሥርዓትና፤ቀኖና በዓላትን ከማክበር በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት በተገቢው የመፈጸም ኃላፊነት እንዳለብን ያስታውሰናል፡፡ ወጣት  መንክር “አንዳአንድ የአስተዳዳር ችግር በመኖሩ ቅር ብሎኛል፡፡ካህናት እንዲሁም ሌሎች አገልጋዩች እኛን ሰብስበው አልያዙንም ከዘመኑ ጋር የመራመድ መሠረታዊ ችግር አለ፡፡ በዓልን ለማክበር ብቻ መገናኘት በቂ  አይደለም፡፡ የሃይማኖት አባቶች በጎቻቸውን  ተግተው መጠበቅ ይኖርባቸዋል”፤ሲል ቅሬታውን ገልጿል፡፡ዳዊትም ይህንን ሀሳብ በመጋራት “የአከባበር ሥርዓቱ ደስ ቢልም፤ የካህናትና የምእመናንን ኅብር ለበዓል ብቻ መሆን የለበትም፡፡ካህናት የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ማበረታታና ድጋፍ መስጠት አለባቸው”፡፡ ብሏል

አስተባባሪዎችና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች አስፈላጊውን አገልግሎት በበዓላት ቀንና በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በወቀቱ እንደሚሰጡ ቢታመንም፤እነዚህ ችግሮች ሊከሰቱ የቻሉት በአስተዳደር ችግር መሆኑን እንደ መንክር ያሉ ግለሰቦች ይናገራሉ፡፡

 የቅዱስ ጳውሎስ የሐዲስ ኪዳን መምህር መጋቤ ሐዲስ አእምሮ ደምሴ ስለዚህ ጉዳይ አነጋግረናቸው ነበር፡፡ እሳቸውም “ጉድለቶች አይጠፉም፡ የምእመናን ሱታፌ ለመጨመር ሁሉም የየድርሻቸውን መወጣት አለበት፡፡የካህናቱ ድርሻ መቀደስ፤ ማስተማርና  እና መዘመር በመሆኑ ከምእመናኑ ጋር ኅብር ለመፍጠር የሚቻለው ምእመናን የምስጋናንና፤የመዘመርን ሥርዓት ሲያዘወትሩ ነው” ይላሉ፡፡ሆኖም ግን ትምህርተ ሃይማኖትን በበቂ ሁኔታ አለመማርና አለመተግበር በወጣቱ ላይ ያመጣው አሉታዊ ተፅእኖ እንዳለም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በማኀበር የተደራጁ ወጣቶች ስሕተት መሆኑን ባለመረዳት ቅዱሳት ሥዕላትን ባልሆነ ቦታ ላይ የሚለጥፉና ለማስዋቢያ የሚጠቀሙ እንዳሉም ታይቷል፡፡ነገር ግን እነዚያ ቅዱሳት ሥዕላት በክብር ቦታቸው ሆነው የሚጸለይባቸው ስለሆኑ ተገቢ ባልሆነ ስፍራ መታየት እንደሌለባቸው በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡

 “በቲሸርትና ሌሎች አልባሳት ላይ ቅዱሳት ሥዕላትን ማሳተም ትክክል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ልብሱ ሊቆሽሽ፤ሊቀደድና ሊጣል ይችላል፡፡እነዚያ ሥዕሎች ቅዱስ በመሆናቸው ለበረከት ብለን የምናደርገው ወደ መርገም እንዳይለወጥብን ለቅዱሳት ሥዕላት ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡የምናገለግለውንም አገልግሎት ያደበዝዝብናል፡፡ሌሎች ጹሑፎችን መጻፍ ለምሳሌ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክትን ማስተላለፍ ይቻላል” ይህ የግንዛቤ እጥረት የፈጠረው ችግር ለምእመናን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት  ሥርዓትና ትውፊት እንዳልሆነ ማስረዳት ይገባል፡፡እነዚህንም ወጣቶች ከስሕተት ለመመለስ የሃይማኖት መሪዎች የማስተማርና የመምከር ከባድ  ኃላፊነት አለባቸው፡፡

በሌላ በኩል ግን መጋቤ ሐዲስ  አእምሮ የበዓል አከባባር ላይ ወጣቶች ቤተ ክርስቲያን የማገልገል ሥራ በራሳቸው ተነሳሽነትና ለበረከትም የሚያደርጉትን ተግባር ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የጠበቀ እንዲሆን በማስገንዘብ፤ በዐበይት በዓላት አከባባር ላይ ከአዲስ አበባ ጅምሮ እስከ ገጠር ቤተ ክርስቲያን ድረስ ወጣቱ የሚሰጠው አገልግሎት በአስተማሪነቱ የሚወሰድ መልካም ተግባር ነው፡፡ታቦታት ወደ ማደሪያቸው ከመድረሳቸው አስቀድመው አካባቢውን በማጽዳት፤ ሕዝቡን በመቀስቀስ፤ታቦታቱ የሚያርፉበትንና የሚጓዙበትን መንገድ በማስዋብ፤ ምንጣፍ በማንጠፍና ቄጤማ በመጎዝጎዝ፤ አቧራንና ድካምን ችለው ሲያገለግሉ ይውላሉ” ሲሉ የወጣቶችን ተሳትፎ በአድናቆት ይገልጹታል፡፡

በትዳር ሕይወት የወላጆች ኃላፊነት

                                                                  ዲ/ን ተመስገን ዘገየ
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጠረው ይለናል (ዘፍ፪-፳፮) አዳም ብቻውን ይሆን ዘንድ ያልፈቀደውና ብቻውን ቢሆን መልካም እንዳልሆነ የሚያውቅ አምላካችን የምትረዳውን ሔዋንን ከጎኑ አጥነት ፈጥሮለታል፡፡እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ መፍጠሩ ለበረከት፤ለመባዛት በመሆኑ”ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት” በማለት ሕገ በረከትን ሰጥቷአቸዋል፡፡ስለዚህ ጋብቻ በሰው ፍላጎት ብቻ የተገኘ አይደለም፡፡ስለ ጋብቻ በኦሪትም በወንጌልም ሕግ ተሰርቷል፡፡የአዳምና የሔዋን ጋብቻ የሕጋዊ ጋብቻ መሠረት ነው፡፡ጋብቻን ያከበሩ በሕጋዊ ጋብቻ የነበሩ ደጋግ ቅዱሳን በሕገ ልቡና እንደነበሩ ሁሉ በሕገ ኦሪትም ነበሩ፡፡ለምሳሌ የኢያቄምና የሐና ጋብቻ ቅዱስ ጋበቻ ነበር፡፡የተቀደሰ ጋብቻ በመሆኑ የቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆች የአምላካችን የመድኀኒታችን አያቶች ለመሆን በቅተዋል፡፡
እንዲሁም የዘካርያስና የኤልሣቤጥ ጋብቻ የተባረከ ጋብቻ ነበር፡፡ ቡሩክና ሕጋዊ በመሆኑም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ማግኘት ችለዋል፡፡ጋብቻ የቅድስና ሕይወትን በሥርዓት የሚመሩበት የቤተሰብ መንግሥት በመሆኑ ክብሩና ልዕልናው ሊጠበቅ ይገባዋል፡፡ወላጆች ልጆችን መተካት አለባቸው ሲባል“መውለድ” ብቻ ማለት አለመሆኑን በሚገባ መረዳት ይገባል፡፡ቅዱስ ዳዊትም “ናሁ ጸጋሁ ለእግዚአብሔር ውሉድ ዕሤተ ፍሬሃ ለከርሥ፤ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው (መዝ፻፳፮፥፫) ልጆች ማደግ ያለባቸው በእግዚአብሔር ትእዛዝና መንገድ ነው፡፡ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ቀርቶ አራዊትም እንኳን ልጆቻቻውን በሥርዓት ያሳድጋሉ፡፡ ለምሳሌ፤አናብስትና አናብርት አዳኝ የዱር እንሰሳት ልጆቻቻውን እንዴት እያደኑ ማደግ እንዳለባቸው ያስተምራሉ፡፡
ጠቢቡ ሲራክ “የሰው አነዋወሩ በልጆቹ ይታወቃል”ይላል (ሲራ፲፩፥፳፰) በ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን የወጣቱ ሥነ-ምግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘቀጠ መምጣቱ እውነት ነው፡፡ለዚህም ዋናው መሠረታዊ ችግር ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት በተለያየ ምክንያት እየዛለ መምጣ ነው፡፡ወላጆች ልጆቻቸውን ማስተማር ያላባቸው ቀዳሚ ትምህርት“እግዚአብሔርን መፍራት“ነው፡፡(ምሳ፩፥፯) ልጆች ለሚጠይቁት ጥያቄ እንደ ዐቅማቸው ማስረዳት ይገባል፡፡ ሕፃናትን የሚያስተምሩ ሰዎች በፍቅርና በደስታ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ልጆች ከጣፈጭ ምግብ ይልቅ የሚረኩት ከወላጆች በሚያገኙት ፍቅር ነው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አባቶች ሆይ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩ”ይላል (ቈላ፫፥፳፪) ልጆችን በፍቅር እንጂ በስድብ ፤በመደብደብ ፤በማበሳጨት፤በማስፈራራት ለማስተማር መሞከር እንደማይገባን ሐዋርያው አስተምሮናል፡፡
ሲራክ“የሰው አኗኗሩ በልጆቹ ይታወቃል (ሲራ፲፩፥፳፰) የላኪው ማንነት በተላከው እንደ ሚታወቅ የወላጆች ምንነት ማሳያ ልጆች ናቸው፡፡የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥነ ምግባር የማይታይበት ልጅ ሲያጋጥማቸው”አሳዳጊ የበደለው” ይላሉ፡፡ስለዚህ ልጆችን በሥነ ምግባር ኮትኩቶ ማሳደግ ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡አሁን አሁን በልጆቹ የሚደሰትና የሚጠቀም ወላጅ ሳይሆን በወለዷቸው ልጆች የሚያዝኑና የሚያለቅሱ ኢትዮጵያውያን ይበዛሉ፡፡ሲራክ “በሱ ጥፋት አንተ እንዳታፍር ልጅህን አስተምረው ያገለግልሃል”(ሲራ፴፥፲፫) ልጅን በሚገባ አስተምሮ ማሳደግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያሰተምሩናል፡፡ የካህኑ የዔሊ ልጆች ፊንሐስና አፍኒን በታቦተ ጽዮን ድንኳን ሥር ያመነዝሩ ነበር ያሳፍራል፡፡ ዔሊ ልጆቹ ይህን የመሰለ ኃጢአት መፈጸማቸውን እያወቀ ባለመገሰጹ ቅጣት ተቀብሏል፡፡ልዑል እግዚአብሔር ዔሊን “ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ለምን አከበርክ?(፩ኛሳሙ፪፥፳፱) በማለት ተቆጣው፡፡ሁለት ልጆቹንም ቀሰፋቸው፡፡ቅጣቱ በልጆቹና በእሱ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ለሌላም ተረፈ አንጂ፡፡
ወላጆች ሆይ ልጆቻችንን እንዴት እናሳድጋቸው?
የነገው ትወልድ ሀገሩንና ቤተሰቡን የሚጠቅም በሥነ- ምግባር የታነጸ በሥራው የተመሰገነ ይሆን ዘንድ ዛሬ ያሉትን ልጆች በአግባቡ መያዝ ልዩ እንክብካቤ ማድረግ ይገባል፡፡ወላጆች ከማንም በላይ ሕፃናትን መልካሙንና ክፉንም በማሰተማር ቅርብ ናቸው፡፡እናትና አባት ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ስለተማሩት ትምህርት መጠየቅ አለባቸው፡፡ልጆችም እንደሚጠየቁ ስለሚያውቁ ትኩረት ሰጥተው ይከታተላሉ፡፡ጥሩ ነገር በሠሩ ጊዜ ጥሩ ወጤት ባመጡ ጊዜ ሽልማት ማዘጋጀት ይገባል፡፡ወላጆች በቤት ውስጥ በቃል ሳይሆን በተግባር በክፉነት ሳይሆን በደግነት እያስተማሩ ሊያሳድጉ ይገባል፡እንዲህ ከሆነ የክፉ ምግባር ቦይ አይሆኑም፡፡አንድ ሰው በቅሎ ጠፋችበትና ወዲያ ወዲህ እየተንከራተተ ሲፈለግ በበቅሎ ሌብነት የሚጠረጠረው ሰው አብሮ ያፋልገው ጀመር፡፡ዘመድ መጥቶ “በቅሎህ ተገኘችልህ ወይ”ብሎ ቢጠይቀው አፈላላጊዬ የበቅሎዬ ሌባ ስለሆነ እንደምን አድርጌ በቅሎዬን ላገኛት እችላለሁ አለ ይባላል፡የልጆችን አእምሮዊ ዕድገት ለማሟላት ከሚደረጉ እንክብካቤዎች የሚከተሉት ይጠቀሳሉ
ተገጣጣሚ መጫዎቻዎችን በመጠቀም የቁጥር ስሌት እንዲያውቁ ማድረግ፤የቋንቋ ችሎታቸውን የሚያሳድጉ መንፈሳዊ ጹሑፎችን እንዲያነቡ ደጋግመው መንገርና ዕድሎችን ማመቻችት፡፡ወላጆች (ባልና ሚስቱ) በአንድነት ሁነው የቤተሰቡ መሪ በመሆናቸው ሊወስዱት የሚገባ ተግባር ይኖራል፡፡ልጆቻችንን በምግባር በማሳደግ የሚኖሩበትን ቤት የዕለት ከዕለት እንቅሰቃሴ እየተከታተሉ መሥመር በማስያዝ አገልጋዮች የሆኑ የቤት ሠራተኞችን ሳያማርሩ ሥራ ሳያበዙ በማሠራት መኖር ይጠበቅባቸዋል፡፡ወላጆች ይህንን ከባድ የቤተሰብ ኃላፊነት ሲወጡ በሚከተሉት ነጥቦች ቢመሩ መልካም ነው፡፡
፩.. በፍቅር፤ ልጆች ፍቅርን እንክብካቤን ከወላጆችና ከመምህራን ይፈልጋሉ፡፡የወላጆቹን ፍቅር እያገኘ ያደገ ልጅ መንፈሰ ጠንካራ፤ለሰው የሚያዝንና ታዛዥ ይሆናል፡፡አንዳንድ ወላጆች የቤተሰቡ ራስ መሆናቸውን በቊጣ በዱላ በመግለጽ ልጆቻቸውን በኃይል ብቻ ለመግዛት የሚሞክሩ አሉ ፡፡ይህ የተሳሳተ መንገድ ነውና ከስሕተት ጎዳና መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡
፪..ትኩረት በመስጠት፣ ልጆች ከፍተኛ የሆነ ክትትልና ትኩረት ይፈልጋሉ፡፡የሚያከናውኑትን እያንዳንዱን ተግባራት እየተመለከተ በጎውን በጎ የሚላቸው ሲሳሳቱ የሚያርማቸው ይሻሉ፡፡ ልጆችን በንቃት መከታተል የወላጆችና የመምህራን ግዴታ ነው፡፡ወላጆች በዕረፍት ጊዜ ከልጆቻቸው ጋር መወያየት፣መመካከር፣የወደፊት ዕቅዳቸውን ምኞታቸውን በተመለከተ በግልጽነት መረዳት ይገባቸዋል፡፡
፫. በማስተማር፤ ንግሥት ዕሌኒ ቆስጠንጢኖስን በሥርዓት ኮትኩታ በማሳደጓ የሀገረ መሪ ለመሆን በቃ፡፡አሁንስ እኛ ልጆቻችንን እንዴት እያሳደግናቸው ነው? ሰው በሕፃንነቱ ተክል ማለት ነው፡፡ተክል የሚሆነውን ሁሉ ሊሆን ይችላል፡፡ቀጥ ብሎ ያድጋል ተወላግዶም ያድጋል የተወላገደውን ለማቃናት ብዙ ዋጋ ያስክፍላል፡፡ወላጆች በልጆቻቸው ዕድገት ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ አንዱና ዋነኛው የልጆቻቸውን ተፈጥሮዊ ተሰጥኦ ማበልጸግ ነው፡፡ወላጆች ልጆችን የማሳደግ ክህሎት ለማዳበር ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ይኖርብናል፡፡ከእኛ ቤት ሲገባ ግን መጸሕፍት ይኖር ይሆን? በተለያዩ የቤተሰብና የልጆች ነክ ጉደዮች በመሳተፍ ከተቻለ የሥነ ልቡና ባለሙያና የአብነት መምህራንን በማማከር የተሻለ ዕውቀት መጨመር ይቻላል፡፡
የልጆችን ተሰጥኦ ከልጅነታቸው ጀምሮ መረዳትና እውቅና መስጠት ለወላጆች ትልቅ ስኬትና አበረታች ነገር ነው፡፡ወላጆችና የአብነት መምህራን ልጆች ችሎታቸውን የሚያወጡበትን አማራጮችና ዕድሎችን ማመቻችት ይገባቸዋል፡፡በእኛ ሀገር ደረጃ ጥረህ ለፍተህ ብላ ኑር ነው እንጂ አማራጭ አንሰጥም ይህ ዘመንን አለመዋጀት ነውና መስተካከል ይኖርብናል፡፡የልጆችን እንቅስቃሴ በመከታተል የልጆችን ፍላጎት ማወቅ ይገባል፡፡ወላጆች ከትምህርት ስኬት ባሻገር የልጆቻቸውን ማኀበራዊ መንፈሳዊና ሥነ-ልቦናዊ ሕይወት መረዳት አለባቸው፡፡ወላጆችና መምሀራን ልጆችን ሲያናግሩ ሙሉ ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡
ልጆችን በልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች ማሳተፍ ይገባል
ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ በትምህርታቸው ብቻ ስኬታማ ሆነው ትምህርታቸውን አጠናቀው እንዲመረቁ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በመንፈሳዊ ሕይወታቸውም ስኬታማነት እንዲ ዘጋጁ የማደረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ልጆችን ከትምህርት ቤት መልስ በተለያዩ ተግባራት እንዲሳተፉ ማድረግ የሚከተሉት ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፡፡
ቴሌቪዥን በመመልከትና ጌም በመጫዎት የሚያሳልፉትን ጊዜ በመገደብ በሠርክ ጉባኤና በሰንበት ትምህርት ቤት ከመደበኛው ከትምህርት ውጭ የሆኑ ተግባራት ሲሳተፉ ወሳኝና ለወደፊት ሕይወታቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ማኀበራዊ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል፡፡ በውኃ ውስጥ መዋኘትም ለልጆች የሚመች የእንቅስቃሴ አይነት ነው፡፡በሳምንት ሁለት ጊዜ (ቅዳሜና እሑድ) ቢዋኙ አካላዊ ብቃታቸውን ያሻሽላል፡፡የመተንፈስ እንቅስቃሴ በማሻሻል ሂደት ለልጆች ጤንነት የአካል ብቃት የላቀ አስተዋጽኦ አለው፡፡ከትምህርት ቤት መልስም ሆነ በዕረፍት ቀናት የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ማድረግ ወላጆች አብረው በመጫወት ካልተቻለም ልጆች ሲጫወቱ በመከታተል ,.በተግባር በማሳየት፣ልጆች ከሚሰሙት ይልቅ በሚያዩት ይሸነፋሉ፡፡ ከተነገራቸው ይልቅ የተመለከቱት በእነርሱ ኀሊና ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ወላጆች ተግባራዊ የሆነ ሕይወትን ለልጆቻቸው ሊያስተምሩ ይገባል፡፡አሁን በየቤታችሁ ልጆች ምንድን ነው የሚያዩት አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዳይጠጡ እየመከሩ እነርሱ ጠጥተው የሚገቡ አሉ፡፡አሁን የዚህ ሰውየ ልጅ ምን ይሆናል? ልቡ ባዶ ቅርጫት ራሱ ባዶ ቤት እየሆነ ነው፡፡ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ በማስገዛት ልጆችን መልካም የሆኑ ነገሮችን ማስተማር አለብን አንድ ወቅት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ “ራሱን ያሸነፈ የጎበዝ ጎበዝ ነው ሌለውን ያሸነፈ ተራ ጎበዝ ነው” ብለው ነበር፡፡ በዘመናችን ራስን ማሸነፍ ሰማዕትነት ነው፡፡
• ልጆች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በአግባቡ መጠቀም ይኖርባቸዋል
የመረጃ ልውውጥ ከማደረግ (በጎን መጥፎውንም) ማኅበራዊ ግንኙት ከማጠናከር (የጠፉ ጓደኞችን) ከማገናኘት አንጻር በአግባቡ ከተጠቀሙበት ትልቅ አስተዋጽዖ አለው፡፡የማኅበራዊ ሚዲያዎች ጉዳት ተመልሶ የማይገኝ ጊዜን ያባክናል፡፡አጠቃቀማችን በአግባቡ ካልሆነ ለትዳር ጠንቅ ነው ራሳቸውን አግዝፎ ለማሳየትና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለዝሙት የሚጠቀሙ አሉ፡፡ በዘመናችን ችግሩን መናገር በራሱ ችግር ነው እንጂ ቴክኖሎጂው እየተራቀቀ ሲመጣ የትውልዱም ጥያቄ እንዲሁ እየተበራከተ ይመጣል፡፡የ፳፩ኛውን ክ/ዘመን ትውልድ ሥነ ልቡና በመረዳት ወላጆች እንደ እባብ ብልህ በመሆን ትውልዱ ያለበትን ሁኔታ ቀድመው ምን እየመጣ እንደሆነ መመልከት ይኖርባቸዋል፡፡
የመረጃ ቴክኖሎጂ ዓለምን ወደ አንድ መንድር እየተቀረ በመምጣቱ ሀገራችንም የዚሁ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆኑ አደጋ አለው፤በአግባቡ መጠቀምና መቆጣጠር አለመቻል መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ልጆቻችን ውጤታማና ስኬታማ እንዲሆኑ ለማድረግ የመረጃ ቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን መገደብና መቆጣጠር የወላጆች ኃላፊነት ነው፡፡ልጆች በቪዲዮ ጌም መጫወት ካለባቸው በወላጆች በጥንቃቄ የተመረጡ፣አዝናኝና የልጆችን የፈጠራ ችሎታ የሚያበለጽጉ ፣ለዕድሜአቸውና ለሥነ-ልቡናቸው የሚመጥኑ ቁጣና ጥቃት ያልበዛባቸው መሆን እንዳለባቸው ባላሙያዎች አበክረው ይመክራሉ፡፡የሚያስፈሩ ቪዲዎችና ጌሞችን የሚጫወቱ ልጆች የበለጠ ቍጣና ጥላቻ የሚያሳዩ ይሆናሉ፡፡ልጆች ያለ ገደብ ቴክኖሎጂ ከተጠቀሙ የአእምሮ ዕድገታቸው ይጎዳል፡፡የትምህርት አቀባባል ድክመት ያጋጥማቸዋል፡፡ላልተፈለገ የሰውነት ውፍረት ያጋልጣል፡፡ ለማሰታወስ ችግር ያጋጥማችዋል፡፡የቴክኖሎጂ ሱሰኛ ያደርጋል፣የእንቅልፍ እጦት ያጋጥማቸዋል፡፡
የልጆች ሥነ- ምግባርና መንፈሳዊ ሕይወት በምን ምክንያት ሊበላሽ ይችላል-?
በቂ ቁጥጥር ካለማድረግና ወላጅ ልጆቹን ሥነ-ምግባር ስለማያስተምር ታላላቆቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ሥነ-ምግባርን በማስተማር ረገድ ደከሞች በመሆናቸው፡፡ ሕፃናቱ አብረው የሚውሉት አብረው የሚማሩት ሰው ማንነት እንዲሁም የሚውሉበት አካባቢ መጥፎ መሆን ለእነርሱ የማይገቡ የማይመጥኑአቸውን ፊልሞችና ድርጊቶች ስለሚመለከቱ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ሥነ- ምግባርን አስመልክቶ የሚያስተላልፉት መልእክት አነሳ መሆን የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ባለማግኘት ምክንያት አግባብነት ወደ ሌላቸው ቦታዎች ሊሄዱ በመቻላቸው ምክንያት ነው፡፡ ልጆቻችን መከራ እንዲቋቋሙ አድርገን እናሰልጥናቸው ችግር ሲመጣ የሚቋቋሙ አናድርጋቸው፡፡ሕፃናት በማይጠቅሙ ዓለማዊ ፊልሞች ጨዋታዎች ድራማዎች፤ፍቅር ሰጥመው ካደጉ በኋ ክፉ ነገር ተው ብንል እንዴት ይቻላል? ልጆቻቸውን በሥርዓት ያስተማሩና ከቅጣት ያዳኑ ደጋግ አባቶች ነበሩ፡፡መጽሐፍ “ከእግዚእበሔር ሕግ እንዳይወጡ ሴት ልጆቻቸውንና ወንድ ልጆቻቸውንም፡አስተምረው ነበርና፤የሚቀርባቸው ክፉ ጠላት አልነበረም (፩መ.መቃቢያን፲፱፥፲፫)

 ወላጆች ለልጆቻቸው የእግዚአብሔርን ድንቅ ተኣምራት ፤የጻድቃንና የሰማዕታት ገድልና የሀገራቸውን ታሪክ በሚገባቸው መጠን እያስጠኑ የማሳደግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ከወላጅ ወደ ልጆች መተላለፍ የነበረበት የቃል ትምህርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ በመምጣቱ በትውልዱ ዘንድ ክፍተቱ እየበዛ መጥቷል፡፡በጥንቱ ባሕል መሠረት ልጆች ወላጆቻቸውን ቁመው ማብላት ነበረባቸው፡፡በእራት ጊዜ የእንጨት መብራት ይዞ ያበላ ነበር፡፡ይህም ቢሆን ልጅ ለወላጅ ያለውን አክብሮት ለመግለጽ የሚደረግ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥንተ መሠረት ያለው ነው፡፡(ሉቃ፲፯፥፰፤፳፪፥፳፯)
ወላጆች ልጆቻቸውን በሥነ-ምግባር ኮትኩተው በሥነ ሥርዓት አስተምረው የማሳደግ ኃላፊነት እንዳለባቸወ ሁሉ ልጆችም ወላጆቻቸውን የመታዘዝ፤የማክበር ግዴታ አላባቸው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ”ልጆች ሆይ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና ለወላጆቻችሁ ታዘዙ”ይላል( ቈላ፫፥፳)ከሁሉ በፊት እናትና አባቱን የሚያከብር ልጅ ዕድሜው ይረዝማል(ዘጸ፳፥፲፪) ምክንያቱም ይመረቃልና፡፡ወላጆቹ የመረቁት ልጅ በእግዚአብሔር ዘንድም የተወደደ ነው፡፡ በመንፈሳዊና በምድራዊ ሀብት የበለጸገ ይሆናል፡፡”ምርቃት ትደርስህ ዘንድ ቢጠራህ አቤት ቢልክህ ወዴት ብለህ አባትህን አክብረው “(ሲራ፫፥፱) በታዛዥነታቸው፤በትሕትናቸው በወላጆቻቸው ከተመረቁት መካከል ያዕቆብንና ርብቃን ለአብነት ማንሳት ይበቃል (ኩፋ፳፥፷፭፤ዘፍ፳፬፥፷ ፤ኩፋ ፲፬፥፴፱)
ዲድስቅልያ አንቀጽ ፲፩፥፩ ”እናንትም አባቶች የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ዘንድ የክርስቶስን ጎዳና ይከተሉ ዘንድ ልጆቻችሁን አስተምሯቸው እጅ ሥራ አገልግሎት ይማሩ ዘንድ እዘዟቸው ሥራ ፈት ሁነው እንዳይቀመጡ”ይላል፡፡ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ሚያዝያ 23 ቀን 1982 ዓ.ም በሻሸመኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ሲያሰተምሩ ”ልጆቻችሁ ከመዝሙር ጋር ደግሞ ሃይማኖታቸውን ፤ሥነ ምግባራቸውን እንዲማሩ ያስፈልጋል፡፡ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትመጡ ልጆቻችሁን ይዛችሁ ኑ ብቻችሁን ከመጣችሁ የምተሠሩትን አያውቁም፤ወደየት እንደ ሄዳችሁም አያውቁም፡፡ወራሾቻችሁም አይሆኑም ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ስትመጡ ልጆቻችሁን ይዛችሁ ኑ፤ሥዕሉን ይሳሙ፤ቅዳሴ ጠበሉን ይጠጡ ፡በእምነቱ አሻሹአቸው መስቀል እንዲሳለሙ አስተምሯቸው ዕጣኑንም ያሽትቱ የሚታጠነውን፤ሥጋወደሙን ይቀበሉ፤ቃጭሉን ይስሙ፤ደወሉ ሲደወል ይስሙ፤ቄሳቸው ማን እንደሆነ ቤተ ክርስቲያናቸው ማን እንደሆነች በውስጧም ምን ምን እንደሚሠራ ያጥኑ ፤ይማሩ፡፡ ወደ ሰንበቴም ስትሄዱ ይዛችኋቸው ግቡ ወደ ሰንበቴም ዳቦውን ተሸክመው ይምጡ እነርሱም ነገ ይህንን እንዲወርሱ የነገ ባለ አደራዎች መሆናቸውን እንዲያውቁ፡፡መመካት አይገባም የሚገባ ቢሆን እኛ ከዓለም ሁሉ የበለጠ መመካት ይገባን ነበር፡፡ምከንያቱም አባቶቻችንና እናቶቻችን ሥርዓታችንንና እምነታችንን ሁሉ ሰፍረው ቆጥረው ያስቀመጡልን ስለሆነ፤ይህ ትውልድ ይህንን ከቀበረ በኋላ ይህንን ካጠፋ በኋላ እንደገና ቤተ መዘክር እንዳይሄድ ነው ሃይማኖቱን ፍለጋ፤ታሪኩን ፍለጋ፤ስለዚህ እምነታችሁን፤ሥርዓታችሁንና መንፈሳዊ ውርሳችሁ እንድትጠብቁ አደራዬ የጠበቀ ነው”ብለው ነበር፡፡

ምንጭ፤ሐመር መጽሔት ፳፮ኛዓመት ቊ ፮ ጥቅምት ፳፻፲ወ፩ ዓ.ም