የዐዋጅ አጽዋማት

በተክለሐዋርያት

የዐዋጅ አጽዋማት በቤተክርስቲያን ለምእመናን ሁሉ አሳውቆ በአንድነት የሚጾም ጾም ነው፤ በሰባትም ይከፈላል፤ እነርሱም የነቢያት  ጾም፤ ጾመ ገሃድ ወይም ጋድ፤ ጾመ ነነዌ፤ የዐብይ ጾም፤ጾመ ድኅነት፤ የሐዋርያት ጾም እና ጾመ ፍልሰታ ናቸው፡፡ በጾም ወቅት ከአንድ ምእመን የሚጠበቁ ምግባራት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሀ. ዕለት ዕለት አብዝቶ መጸለይ

በጾም ወቅት ልናዘወትራቸው ከሚገቡን ምግባራት መካከል ጸሎት አንዱ ነው፤ በጸሎት ያልታገዘ ጾም ከንቱ ነው፤ ኦርቶዶክሳዊ ምእመን በጾም ወቅትና ከጾም ወቅት ውጪ በጸሎት ትጉ መሆን ክርስቲያናዊ ግዴታው ነው፡፡ ጸሎት ከፈጣሪ የምንገኛኝበት ክርስቲያናዊ ምግባር ነው፡፡ ጸሎት ወደ ፈተና እንዳንገባ የሚረዳን የጽድቅ መሥመር ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔርን በጠራሁት ጊዜ ጽድቄን ሰማኝ ጭንቀቴንም አራቀልኝ ይቅር አለኝ ጸሎቴንም ሰማኝ››(መዝ.፬፥፩)

ለ. ከዝሙት መከልከል

ዝሙት ነፍስና ሥጋን ይጎዳል፤ በሰማይም በምድርም ከፍተኛ ቅጣትና ሥቃይን ያመጣል፡፡ ሴሰኝነት መልካም ስምን ያጠፋል፤ ክብርን ያሳጣል፤ ኅሊናን ይበጠብጣል፤ ከዚህ የሚከፋው ደግሞ ከእግዚአብሔር አንድነት የሚለይ መሆኑ ነው፡፡ ሴሰኞችና አመንዝራዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርድ ይደረግባቸዋል፡፡ ነቢዩ ‹‹ወንዶችም ደግሞ ከአመንዝሮች ጋር ይጫወታሉና፥ ከጋለሞቶችም ጋር ይሠዋሉና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰሰኑ ጊዜ፥ ሙሽሮቻችሁ በአመነዘሩ ጊዜ አልቀጣኋቸውም፤ የማያስተውልም ሕዝብ ከአመንዝራ ጋር ይቀላቀላል፡፡ (ሆሴ.፬፥፲፬)

ሐ. የስሜት ሕዋሳትን ማስገዛት

በጾም ወቅት ሁሉንም የስሜት ሕዋሳቶችን መግዛት መቻል አለብን፡፡ የስሜት ሕዋሳትን መግዛት ካልቻልን በምኞትና በፍትወት ገመድ እየጎተቱ ወደ ኃጢአት ይወስዱናል፡፡ ለዚህም ነው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ይጹም ዓይን (ዓይን ይጹም) ፤ ይጹም ልሳን(አንደበት ይጹም)፤ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ሕሱም (ጆሮም ክፉን ከመስማት ይጹም)፤ በማለት ያስተማረን ዓይን የሚያየውን ጆሮም የሚሰማውን አንደበትም የሚናገረውን ክፉ ነገር አእምሮ ወደ ሐሳብ በመቀየር ወደ ኃጢአት ሊያመራን ይችላል፡፡ በመሆኑም በጾማችን ወይም በክርስትናችን ዓይናችንን ክፉ ነገርን ከማየት አንደበታችንን ክፉን ከመናገር ጆሮአችንንም ክፉን ከመስማት ልንከለክል ይገባናል፡፡ ‹‹ኃጢአትን ወደ መውደድ አንተን ከሚስቡህ ከማየት ከመስማት ተጠበቅ›› (ማር ይስሐቅ)፡፡ ዓለሙንና በዓለም ያለውን አትውደዱ ዓለሙን የሚወድ ግን የአብ ፍቅር በእርሱ የለም በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለገንዘብም መመካት ከዓለም እንጂ ከአብ አይደለም፡፡ (፩ዮሐ.፪፥፲፭‐፲፮)

መ. ቅዱሳት መጻሕፍትን መመርመር ፤ መመልከት

ቅዱሳት መጻሕፍት የሰው ልጅ የፈጣሪውን የእግዚአብሔርን ሕግና ሥርዓት ይማርባቸው ዘንድ የተሰጡትና ከአለማወቅ ወደ ማወቅ ከሞትም ወደ ሕይወት የሚወስዱት የሚያደርሱት ከፈጣሪው ጋርም እንዴት መኖር እንደሚገባው የሚያስተምሩት የቅድስናው መሠረቶች የክርስትና ሕይወት መመሪያዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል ‹‹መጻሕፍትን ካለማወቃችሁ የተነሣ ትስታላችሁ›› በማለት ያስተማረን ቅዱሳት መጻሕፍት እንዴት መጾም እንዳለብን በጾማችን ወቅት ምን ምን ተግባራትን ማድረግ እንዳለብንና እንደሌለብንም ጭምር ያስተምሩናል በጾም የተጠቀሙ የቅዱሳን አባቶቻችንንም ታሪክ እየነገሩን እኛም እንድንጾም ያደርጉናል፡፡

በመሆኑም ኦርቶዶክሳውያን  ምእመናን በጾም ወቅት እነዚህን ቅዱሳት መጻሕፍትን አብዝቶ በማንበብ ወደ ቅድስና ሕይወት የሚወስዱ የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዛትን መረዳትና መፈፀም ተገቢ ነው፡፡

ሠ. ምጽዋትን ማዘውተር

ምጽዋት ማለት መስጠት፤መለገስ ማለት ነው፡፡ ይህም ከጾም ጋር ከሚተባበሩ ክርስቲያናዊ ምግባራት አንዱ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን ይህንም ላደርግ ደግሞ ተጋሁ›› በማለት እንዳስተማረን ምጽዋት ለምእመናን ትጋት ናት፡፡ (ገላ.፪፥፲)

ምጽዋት መስጠት ከገንዘብ ከዕውቀት ከንብረት…ላይ ለእግዚአብሔር ቤት መለገስ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ብፁዓን ትምህርቱ “ብፁዓን መሐርያን የሚምሩ ብፁዓን” ናቸው ያለውን ሊቃውንት ለምጽዋት ሰጥተው ሲተረጉሙት በሦስት መንገድ ያስቀምጡታል፡፡ እነዚህም፡-

.ምሕረት ሥጋዊ፡ ይህ የሚያስረዳው ለሥጋ የሚኾን ነገርን መለገስን ሲኾን
. ምሕረት መንፈሳዊ፡ በምክር በትምህርት ሥነ ልቡናን የሚያንጽ (የሚያበረታታ) ማድረግን ነው፡፡

. ምሕረት ነፍሳዊ፡ ደግሞ «መጥወተ ርእስ» ወይም ራስን እስከ መስጠት መድረስን ነው፡፡ (ማቴ.፭፥፯ትርጓሜ ወንጌል)

ምጽዋት ካለን ነገር ላይ ማካፈልን ያመለክታል፡፡ ለፍጹምነትም የሚያበቃ ምግባር መኾኑ የተመሰከረለት ነው፡፡ «ፍጹም እንድትኾን ለድኻ ስጥ» እንዲል (ማቴ.፲፱፥፳፩) እንደዚሁም «የሚሰጥ ብፁዕ ነው» የሚለው ኃይለ ቃል የሚያስረዳን ይህንኑ ነው፡፡ (ሐዋ.፳፥፴፭) በዕለተ ምጽአትም ከሕይወት ቃል አንዱ በምጽዋት የሚገኝ መኾኑ እሙን ነው፡፡ (ማቴ.፳፭፥፴፭) ምጽዋት በልብስ በገንዘብ እንጀራ በመቁረስ የመሳሰሉትን ለደኃ በመስጠት ለድሆችና ለጦም አዳሪዎች ማካፈል ነው፡፡ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ምእመናን ሀብታቸውን ለደኃ ያካፍሉ ነበር፡፡ (ሐዋ.፬፥፴፪፣፮፥፩) እንደዚሁም ዕውቀትን ማካፈል ምክር መለገስ ከምጽዋት የሚቈጠር ሲኾን ለእግዚአብሔር ቤትም በገንዘብ በጉልበትና በስጦታችን ማገልገል የምጽዋትን ዋጋ ያስገኛል (ዘዳ. ፲፭፥፲፩‐፲፭፤ኢሳ.፶፰፥፯፤፯፤ምሳ.፫፥፳፯፤ሮሜ.፲፪፥፰) እንግዲህ በጾማችን ለኃጢአታችን ሥርየትን፤ ምሕረትና ይቅርታን የምናገኝባቸውን የሥጋና የነፍስ በረከትንም የምንታደልባቸውን እነዚህን ክርስቲያናዊ ምግባራት በሕይወታችን አዘውትረን ልንፈጽማቸው ይገባናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!