በትዳር ሕይወት የወላጆች ኃላፊነት

                                                                  ዲ/ን ተመስገን ዘገየ
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጠረው ይለናል (ዘፍ፪-፳፮) አዳም ብቻውን ይሆን ዘንድ ያልፈቀደውና ብቻውን ቢሆን መልካም እንዳልሆነ የሚያውቅ አምላካችን የምትረዳውን ሔዋንን ከጎኑ አጥነት ፈጥሮለታል፡፡እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ መፍጠሩ ለበረከት፤ለመባዛት በመሆኑ”ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት” በማለት ሕገ በረከትን ሰጥቷአቸዋል፡፡ስለዚህ ጋብቻ በሰው ፍላጎት ብቻ የተገኘ አይደለም፡፡ስለ ጋብቻ በኦሪትም በወንጌልም ሕግ ተሰርቷል፡፡የአዳምና የሔዋን ጋብቻ የሕጋዊ ጋብቻ መሠረት ነው፡፡ጋብቻን ያከበሩ በሕጋዊ ጋብቻ የነበሩ ደጋግ ቅዱሳን በሕገ ልቡና እንደነበሩ ሁሉ በሕገ ኦሪትም ነበሩ፡፡ለምሳሌ የኢያቄምና የሐና ጋብቻ ቅዱስ ጋበቻ ነበር፡፡የተቀደሰ ጋብቻ በመሆኑ የቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆች የአምላካችን የመድኀኒታችን አያቶች ለመሆን በቅተዋል፡፡
እንዲሁም የዘካርያስና የኤልሣቤጥ ጋብቻ የተባረከ ጋብቻ ነበር፡፡ ቡሩክና ሕጋዊ በመሆኑም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ማግኘት ችለዋል፡፡ጋብቻ የቅድስና ሕይወትን በሥርዓት የሚመሩበት የቤተሰብ መንግሥት በመሆኑ ክብሩና ልዕልናው ሊጠበቅ ይገባዋል፡፡ወላጆች ልጆችን መተካት አለባቸው ሲባል“መውለድ” ብቻ ማለት አለመሆኑን በሚገባ መረዳት ይገባል፡፡ቅዱስ ዳዊትም “ናሁ ጸጋሁ ለእግዚአብሔር ውሉድ ዕሤተ ፍሬሃ ለከርሥ፤ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው (መዝ፻፳፮፥፫) ልጆች ማደግ ያለባቸው በእግዚአብሔር ትእዛዝና መንገድ ነው፡፡ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ቀርቶ አራዊትም እንኳን ልጆቻቻውን በሥርዓት ያሳድጋሉ፡፡ ለምሳሌ፤አናብስትና አናብርት አዳኝ የዱር እንሰሳት ልጆቻቻውን እንዴት እያደኑ ማደግ እንዳለባቸው ያስተምራሉ፡፡
ጠቢቡ ሲራክ “የሰው አነዋወሩ በልጆቹ ይታወቃል”ይላል (ሲራ፲፩፥፳፰) በ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን የወጣቱ ሥነ-ምግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘቀጠ መምጣቱ እውነት ነው፡፡ለዚህም ዋናው መሠረታዊ ችግር ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት በተለያየ ምክንያት እየዛለ መምጣ ነው፡፡ወላጆች ልጆቻቸውን ማስተማር ያላባቸው ቀዳሚ ትምህርት“እግዚአብሔርን መፍራት“ነው፡፡(ምሳ፩፥፯) ልጆች ለሚጠይቁት ጥያቄ እንደ ዐቅማቸው ማስረዳት ይገባል፡፡ ሕፃናትን የሚያስተምሩ ሰዎች በፍቅርና በደስታ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ልጆች ከጣፈጭ ምግብ ይልቅ የሚረኩት ከወላጆች በሚያገኙት ፍቅር ነው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አባቶች ሆይ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩ”ይላል (ቈላ፫፥፳፪) ልጆችን በፍቅር እንጂ በስድብ ፤በመደብደብ ፤በማበሳጨት፤በማስፈራራት ለማስተማር መሞከር እንደማይገባን ሐዋርያው አስተምሮናል፡፡
ሲራክ“የሰው አኗኗሩ በልጆቹ ይታወቃል (ሲራ፲፩፥፳፰) የላኪው ማንነት በተላከው እንደ ሚታወቅ የወላጆች ምንነት ማሳያ ልጆች ናቸው፡፡የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥነ ምግባር የማይታይበት ልጅ ሲያጋጥማቸው”አሳዳጊ የበደለው” ይላሉ፡፡ስለዚህ ልጆችን በሥነ ምግባር ኮትኩቶ ማሳደግ ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡አሁን አሁን በልጆቹ የሚደሰትና የሚጠቀም ወላጅ ሳይሆን በወለዷቸው ልጆች የሚያዝኑና የሚያለቅሱ ኢትዮጵያውያን ይበዛሉ፡፡ሲራክ “በሱ ጥፋት አንተ እንዳታፍር ልጅህን አስተምረው ያገለግልሃል”(ሲራ፴፥፲፫) ልጅን በሚገባ አስተምሮ ማሳደግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያሰተምሩናል፡፡ የካህኑ የዔሊ ልጆች ፊንሐስና አፍኒን በታቦተ ጽዮን ድንኳን ሥር ያመነዝሩ ነበር ያሳፍራል፡፡ ዔሊ ልጆቹ ይህን የመሰለ ኃጢአት መፈጸማቸውን እያወቀ ባለመገሰጹ ቅጣት ተቀብሏል፡፡ልዑል እግዚአብሔር ዔሊን “ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ለምን አከበርክ?(፩ኛሳሙ፪፥፳፱) በማለት ተቆጣው፡፡ሁለት ልጆቹንም ቀሰፋቸው፡፡ቅጣቱ በልጆቹና በእሱ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ለሌላም ተረፈ አንጂ፡፡
ወላጆች ሆይ ልጆቻችንን እንዴት እናሳድጋቸው?
የነገው ትወልድ ሀገሩንና ቤተሰቡን የሚጠቅም በሥነ- ምግባር የታነጸ በሥራው የተመሰገነ ይሆን ዘንድ ዛሬ ያሉትን ልጆች በአግባቡ መያዝ ልዩ እንክብካቤ ማድረግ ይገባል፡፡ወላጆች ከማንም በላይ ሕፃናትን መልካሙንና ክፉንም በማሰተማር ቅርብ ናቸው፡፡እናትና አባት ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ስለተማሩት ትምህርት መጠየቅ አለባቸው፡፡ልጆችም እንደሚጠየቁ ስለሚያውቁ ትኩረት ሰጥተው ይከታተላሉ፡፡ጥሩ ነገር በሠሩ ጊዜ ጥሩ ወጤት ባመጡ ጊዜ ሽልማት ማዘጋጀት ይገባል፡፡ወላጆች በቤት ውስጥ በቃል ሳይሆን በተግባር በክፉነት ሳይሆን በደግነት እያስተማሩ ሊያሳድጉ ይገባል፡እንዲህ ከሆነ የክፉ ምግባር ቦይ አይሆኑም፡፡አንድ ሰው በቅሎ ጠፋችበትና ወዲያ ወዲህ እየተንከራተተ ሲፈለግ በበቅሎ ሌብነት የሚጠረጠረው ሰው አብሮ ያፋልገው ጀመር፡፡ዘመድ መጥቶ “በቅሎህ ተገኘችልህ ወይ”ብሎ ቢጠይቀው አፈላላጊዬ የበቅሎዬ ሌባ ስለሆነ እንደምን አድርጌ በቅሎዬን ላገኛት እችላለሁ አለ ይባላል፡የልጆችን አእምሮዊ ዕድገት ለማሟላት ከሚደረጉ እንክብካቤዎች የሚከተሉት ይጠቀሳሉ
ተገጣጣሚ መጫዎቻዎችን በመጠቀም የቁጥር ስሌት እንዲያውቁ ማድረግ፤የቋንቋ ችሎታቸውን የሚያሳድጉ መንፈሳዊ ጹሑፎችን እንዲያነቡ ደጋግመው መንገርና ዕድሎችን ማመቻችት፡፡ወላጆች (ባልና ሚስቱ) በአንድነት ሁነው የቤተሰቡ መሪ በመሆናቸው ሊወስዱት የሚገባ ተግባር ይኖራል፡፡ልጆቻችንን በምግባር በማሳደግ የሚኖሩበትን ቤት የዕለት ከዕለት እንቅሰቃሴ እየተከታተሉ መሥመር በማስያዝ አገልጋዮች የሆኑ የቤት ሠራተኞችን ሳያማርሩ ሥራ ሳያበዙ በማሠራት መኖር ይጠበቅባቸዋል፡፡ወላጆች ይህንን ከባድ የቤተሰብ ኃላፊነት ሲወጡ በሚከተሉት ነጥቦች ቢመሩ መልካም ነው፡፡
፩.. በፍቅር፤ ልጆች ፍቅርን እንክብካቤን ከወላጆችና ከመምህራን ይፈልጋሉ፡፡የወላጆቹን ፍቅር እያገኘ ያደገ ልጅ መንፈሰ ጠንካራ፤ለሰው የሚያዝንና ታዛዥ ይሆናል፡፡አንዳንድ ወላጆች የቤተሰቡ ራስ መሆናቸውን በቊጣ በዱላ በመግለጽ ልጆቻቸውን በኃይል ብቻ ለመግዛት የሚሞክሩ አሉ ፡፡ይህ የተሳሳተ መንገድ ነውና ከስሕተት ጎዳና መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡
፪..ትኩረት በመስጠት፣ ልጆች ከፍተኛ የሆነ ክትትልና ትኩረት ይፈልጋሉ፡፡የሚያከናውኑትን እያንዳንዱን ተግባራት እየተመለከተ በጎውን በጎ የሚላቸው ሲሳሳቱ የሚያርማቸው ይሻሉ፡፡ ልጆችን በንቃት መከታተል የወላጆችና የመምህራን ግዴታ ነው፡፡ወላጆች በዕረፍት ጊዜ ከልጆቻቸው ጋር መወያየት፣መመካከር፣የወደፊት ዕቅዳቸውን ምኞታቸውን በተመለከተ በግልጽነት መረዳት ይገባቸዋል፡፡
፫. በማስተማር፤ ንግሥት ዕሌኒ ቆስጠንጢኖስን በሥርዓት ኮትኩታ በማሳደጓ የሀገረ መሪ ለመሆን በቃ፡፡አሁንስ እኛ ልጆቻችንን እንዴት እያሳደግናቸው ነው? ሰው በሕፃንነቱ ተክል ማለት ነው፡፡ተክል የሚሆነውን ሁሉ ሊሆን ይችላል፡፡ቀጥ ብሎ ያድጋል ተወላግዶም ያድጋል የተወላገደውን ለማቃናት ብዙ ዋጋ ያስክፍላል፡፡ወላጆች በልጆቻቸው ዕድገት ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ አንዱና ዋነኛው የልጆቻቸውን ተፈጥሮዊ ተሰጥኦ ማበልጸግ ነው፡፡ወላጆች ልጆችን የማሳደግ ክህሎት ለማዳበር ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ይኖርብናል፡፡ከእኛ ቤት ሲገባ ግን መጸሕፍት ይኖር ይሆን? በተለያዩ የቤተሰብና የልጆች ነክ ጉደዮች በመሳተፍ ከተቻለ የሥነ ልቡና ባለሙያና የአብነት መምህራንን በማማከር የተሻለ ዕውቀት መጨመር ይቻላል፡፡
የልጆችን ተሰጥኦ ከልጅነታቸው ጀምሮ መረዳትና እውቅና መስጠት ለወላጆች ትልቅ ስኬትና አበረታች ነገር ነው፡፡ወላጆችና የአብነት መምህራን ልጆች ችሎታቸውን የሚያወጡበትን አማራጮችና ዕድሎችን ማመቻችት ይገባቸዋል፡፡በእኛ ሀገር ደረጃ ጥረህ ለፍተህ ብላ ኑር ነው እንጂ አማራጭ አንሰጥም ይህ ዘመንን አለመዋጀት ነውና መስተካከል ይኖርብናል፡፡የልጆችን እንቅስቃሴ በመከታተል የልጆችን ፍላጎት ማወቅ ይገባል፡፡ወላጆች ከትምህርት ስኬት ባሻገር የልጆቻቸውን ማኀበራዊ መንፈሳዊና ሥነ-ልቦናዊ ሕይወት መረዳት አለባቸው፡፡ወላጆችና መምሀራን ልጆችን ሲያናግሩ ሙሉ ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡
ልጆችን በልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች ማሳተፍ ይገባል
ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ በትምህርታቸው ብቻ ስኬታማ ሆነው ትምህርታቸውን አጠናቀው እንዲመረቁ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በመንፈሳዊ ሕይወታቸውም ስኬታማነት እንዲ ዘጋጁ የማደረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ልጆችን ከትምህርት ቤት መልስ በተለያዩ ተግባራት እንዲሳተፉ ማድረግ የሚከተሉት ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፡፡
ቴሌቪዥን በመመልከትና ጌም በመጫዎት የሚያሳልፉትን ጊዜ በመገደብ በሠርክ ጉባኤና በሰንበት ትምህርት ቤት ከመደበኛው ከትምህርት ውጭ የሆኑ ተግባራት ሲሳተፉ ወሳኝና ለወደፊት ሕይወታቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ማኀበራዊ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል፡፡ በውኃ ውስጥ መዋኘትም ለልጆች የሚመች የእንቅስቃሴ አይነት ነው፡፡በሳምንት ሁለት ጊዜ (ቅዳሜና እሑድ) ቢዋኙ አካላዊ ብቃታቸውን ያሻሽላል፡፡የመተንፈስ እንቅስቃሴ በማሻሻል ሂደት ለልጆች ጤንነት የአካል ብቃት የላቀ አስተዋጽኦ አለው፡፡ከትምህርት ቤት መልስም ሆነ በዕረፍት ቀናት የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ማድረግ ወላጆች አብረው በመጫወት ካልተቻለም ልጆች ሲጫወቱ በመከታተል ,.በተግባር በማሳየት፣ልጆች ከሚሰሙት ይልቅ በሚያዩት ይሸነፋሉ፡፡ ከተነገራቸው ይልቅ የተመለከቱት በእነርሱ ኀሊና ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ወላጆች ተግባራዊ የሆነ ሕይወትን ለልጆቻቸው ሊያስተምሩ ይገባል፡፡አሁን በየቤታችሁ ልጆች ምንድን ነው የሚያዩት አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዳይጠጡ እየመከሩ እነርሱ ጠጥተው የሚገቡ አሉ፡፡አሁን የዚህ ሰውየ ልጅ ምን ይሆናል? ልቡ ባዶ ቅርጫት ራሱ ባዶ ቤት እየሆነ ነው፡፡ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ በማስገዛት ልጆችን መልካም የሆኑ ነገሮችን ማስተማር አለብን አንድ ወቅት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ “ራሱን ያሸነፈ የጎበዝ ጎበዝ ነው ሌለውን ያሸነፈ ተራ ጎበዝ ነው” ብለው ነበር፡፡ በዘመናችን ራስን ማሸነፍ ሰማዕትነት ነው፡፡
• ልጆች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በአግባቡ መጠቀም ይኖርባቸዋል
የመረጃ ልውውጥ ከማደረግ (በጎን መጥፎውንም) ማኅበራዊ ግንኙት ከማጠናከር (የጠፉ ጓደኞችን) ከማገናኘት አንጻር በአግባቡ ከተጠቀሙበት ትልቅ አስተዋጽዖ አለው፡፡የማኅበራዊ ሚዲያዎች ጉዳት ተመልሶ የማይገኝ ጊዜን ያባክናል፡፡አጠቃቀማችን በአግባቡ ካልሆነ ለትዳር ጠንቅ ነው ራሳቸውን አግዝፎ ለማሳየትና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለዝሙት የሚጠቀሙ አሉ፡፡ በዘመናችን ችግሩን መናገር በራሱ ችግር ነው እንጂ ቴክኖሎጂው እየተራቀቀ ሲመጣ የትውልዱም ጥያቄ እንዲሁ እየተበራከተ ይመጣል፡፡የ፳፩ኛውን ክ/ዘመን ትውልድ ሥነ ልቡና በመረዳት ወላጆች እንደ እባብ ብልህ በመሆን ትውልዱ ያለበትን ሁኔታ ቀድመው ምን እየመጣ እንደሆነ መመልከት ይኖርባቸዋል፡፡
የመረጃ ቴክኖሎጂ ዓለምን ወደ አንድ መንድር እየተቀረ በመምጣቱ ሀገራችንም የዚሁ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆኑ አደጋ አለው፤በአግባቡ መጠቀምና መቆጣጠር አለመቻል መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ልጆቻችን ውጤታማና ስኬታማ እንዲሆኑ ለማድረግ የመረጃ ቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን መገደብና መቆጣጠር የወላጆች ኃላፊነት ነው፡፡ልጆች በቪዲዮ ጌም መጫወት ካለባቸው በወላጆች በጥንቃቄ የተመረጡ፣አዝናኝና የልጆችን የፈጠራ ችሎታ የሚያበለጽጉ ፣ለዕድሜአቸውና ለሥነ-ልቡናቸው የሚመጥኑ ቁጣና ጥቃት ያልበዛባቸው መሆን እንዳለባቸው ባላሙያዎች አበክረው ይመክራሉ፡፡የሚያስፈሩ ቪዲዎችና ጌሞችን የሚጫወቱ ልጆች የበለጠ ቍጣና ጥላቻ የሚያሳዩ ይሆናሉ፡፡ልጆች ያለ ገደብ ቴክኖሎጂ ከተጠቀሙ የአእምሮ ዕድገታቸው ይጎዳል፡፡የትምህርት አቀባባል ድክመት ያጋጥማቸዋል፡፡ላልተፈለገ የሰውነት ውፍረት ያጋልጣል፡፡ ለማሰታወስ ችግር ያጋጥማችዋል፡፡የቴክኖሎጂ ሱሰኛ ያደርጋል፣የእንቅልፍ እጦት ያጋጥማቸዋል፡፡
የልጆች ሥነ- ምግባርና መንፈሳዊ ሕይወት በምን ምክንያት ሊበላሽ ይችላል-?
በቂ ቁጥጥር ካለማድረግና ወላጅ ልጆቹን ሥነ-ምግባር ስለማያስተምር ታላላቆቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ሥነ-ምግባርን በማስተማር ረገድ ደከሞች በመሆናቸው፡፡ ሕፃናቱ አብረው የሚውሉት አብረው የሚማሩት ሰው ማንነት እንዲሁም የሚውሉበት አካባቢ መጥፎ መሆን ለእነርሱ የማይገቡ የማይመጥኑአቸውን ፊልሞችና ድርጊቶች ስለሚመለከቱ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ሥነ- ምግባርን አስመልክቶ የሚያስተላልፉት መልእክት አነሳ መሆን የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ባለማግኘት ምክንያት አግባብነት ወደ ሌላቸው ቦታዎች ሊሄዱ በመቻላቸው ምክንያት ነው፡፡ ልጆቻችን መከራ እንዲቋቋሙ አድርገን እናሰልጥናቸው ችግር ሲመጣ የሚቋቋሙ አናድርጋቸው፡፡ሕፃናት በማይጠቅሙ ዓለማዊ ፊልሞች ጨዋታዎች ድራማዎች፤ፍቅር ሰጥመው ካደጉ በኋ ክፉ ነገር ተው ብንል እንዴት ይቻላል? ልጆቻቸውን በሥርዓት ያስተማሩና ከቅጣት ያዳኑ ደጋግ አባቶች ነበሩ፡፡መጽሐፍ “ከእግዚእበሔር ሕግ እንዳይወጡ ሴት ልጆቻቸውንና ወንድ ልጆቻቸውንም፡አስተምረው ነበርና፤የሚቀርባቸው ክፉ ጠላት አልነበረም (፩መ.መቃቢያን፲፱፥፲፫)

 ወላጆች ለልጆቻቸው የእግዚአብሔርን ድንቅ ተኣምራት ፤የጻድቃንና የሰማዕታት ገድልና የሀገራቸውን ታሪክ በሚገባቸው መጠን እያስጠኑ የማሳደግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ከወላጅ ወደ ልጆች መተላለፍ የነበረበት የቃል ትምህርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ በመምጣቱ በትውልዱ ዘንድ ክፍተቱ እየበዛ መጥቷል፡፡በጥንቱ ባሕል መሠረት ልጆች ወላጆቻቸውን ቁመው ማብላት ነበረባቸው፡፡በእራት ጊዜ የእንጨት መብራት ይዞ ያበላ ነበር፡፡ይህም ቢሆን ልጅ ለወላጅ ያለውን አክብሮት ለመግለጽ የሚደረግ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥንተ መሠረት ያለው ነው፡፡(ሉቃ፲፯፥፰፤፳፪፥፳፯)
ወላጆች ልጆቻቸውን በሥነ-ምግባር ኮትኩተው በሥነ ሥርዓት አስተምረው የማሳደግ ኃላፊነት እንዳለባቸወ ሁሉ ልጆችም ወላጆቻቸውን የመታዘዝ፤የማክበር ግዴታ አላባቸው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ”ልጆች ሆይ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና ለወላጆቻችሁ ታዘዙ”ይላል( ቈላ፫፥፳)ከሁሉ በፊት እናትና አባቱን የሚያከብር ልጅ ዕድሜው ይረዝማል(ዘጸ፳፥፲፪) ምክንያቱም ይመረቃልና፡፡ወላጆቹ የመረቁት ልጅ በእግዚአብሔር ዘንድም የተወደደ ነው፡፡ በመንፈሳዊና በምድራዊ ሀብት የበለጸገ ይሆናል፡፡”ምርቃት ትደርስህ ዘንድ ቢጠራህ አቤት ቢልክህ ወዴት ብለህ አባትህን አክብረው “(ሲራ፫፥፱) በታዛዥነታቸው፤በትሕትናቸው በወላጆቻቸው ከተመረቁት መካከል ያዕቆብንና ርብቃን ለአብነት ማንሳት ይበቃል (ኩፋ፳፥፷፭፤ዘፍ፳፬፥፷ ፤ኩፋ ፲፬፥፴፱)
ዲድስቅልያ አንቀጽ ፲፩፥፩ ”እናንትም አባቶች የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ዘንድ የክርስቶስን ጎዳና ይከተሉ ዘንድ ልጆቻችሁን አስተምሯቸው እጅ ሥራ አገልግሎት ይማሩ ዘንድ እዘዟቸው ሥራ ፈት ሁነው እንዳይቀመጡ”ይላል፡፡ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ሚያዝያ 23 ቀን 1982 ዓ.ም በሻሸመኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ሲያሰተምሩ ”ልጆቻችሁ ከመዝሙር ጋር ደግሞ ሃይማኖታቸውን ፤ሥነ ምግባራቸውን እንዲማሩ ያስፈልጋል፡፡ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትመጡ ልጆቻችሁን ይዛችሁ ኑ ብቻችሁን ከመጣችሁ የምተሠሩትን አያውቁም፤ወደየት እንደ ሄዳችሁም አያውቁም፡፡ወራሾቻችሁም አይሆኑም ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ስትመጡ ልጆቻችሁን ይዛችሁ ኑ፤ሥዕሉን ይሳሙ፤ቅዳሴ ጠበሉን ይጠጡ ፡በእምነቱ አሻሹአቸው መስቀል እንዲሳለሙ አስተምሯቸው ዕጣኑንም ያሽትቱ የሚታጠነውን፤ሥጋወደሙን ይቀበሉ፤ቃጭሉን ይስሙ፤ደወሉ ሲደወል ይስሙ፤ቄሳቸው ማን እንደሆነ ቤተ ክርስቲያናቸው ማን እንደሆነች በውስጧም ምን ምን እንደሚሠራ ያጥኑ ፤ይማሩ፡፡ ወደ ሰንበቴም ስትሄዱ ይዛችኋቸው ግቡ ወደ ሰንበቴም ዳቦውን ተሸክመው ይምጡ እነርሱም ነገ ይህንን እንዲወርሱ የነገ ባለ አደራዎች መሆናቸውን እንዲያውቁ፡፡መመካት አይገባም የሚገባ ቢሆን እኛ ከዓለም ሁሉ የበለጠ መመካት ይገባን ነበር፡፡ምከንያቱም አባቶቻችንና እናቶቻችን ሥርዓታችንንና እምነታችንን ሁሉ ሰፍረው ቆጥረው ያስቀመጡልን ስለሆነ፤ይህ ትውልድ ይህንን ከቀበረ በኋላ ይህንን ካጠፋ በኋላ እንደገና ቤተ መዘክር እንዳይሄድ ነው ሃይማኖቱን ፍለጋ፤ታሪኩን ፍለጋ፤ስለዚህ እምነታችሁን፤ሥርዓታችሁንና መንፈሳዊ ውርሳችሁ እንድትጠብቁ አደራዬ የጠበቀ ነው”ብለው ነበር፡፡

ምንጭ፤ሐመር መጽሔት ፳፮ኛዓመት ቊ ፮ ጥቅምት ፳፻፲ወ፩ ዓ.ም

መስጠትና መቀበል (ሐዋ፳፥፴፭)

 

                                                                                                                                                                በዲ/ን ተመስገን ዘገየ

መስጠትና መቀበል በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ አካላት መካከል ይፈጸማል፡፡ይህም ያለው ለሌለው መስጠት የሌለው ካለው መቀበልና እርስ በእርስ መመጋገብ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝገቦ እንደምናገኘው ‹‹ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው››(ሐዋ.፳፥፴፭) ይላል፡፡   በዚህ ኃይለ ቃል ላይ የሚሰጥ አለ ደገሞ የሚቀበል አለ፡፡ በዚህ ግንኙነት ውስጥ የሚሰጠው ከሚቀበለው ይልቅ ዋጋው ታላቅ ነው፡፡ ስለዚህ በክርስቲያናዊ ሕይወት መስጠት ብፅዕና የሚያስገኝ ስለሆነ ባለን ነገር ሁሉ መስጠትን ልንሻ  ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ለእያንድንዳችን የተለያየ ጸጋ ሰጥቶናል፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ባለን ጸጋ መጠን ማገልገል ነው፡፡

ለዚህም ነው ሐዋርው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ፡- ‹‹እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ መጠን ልዩ ልዩ ስጦታ አለን ትንቢት የሚናገር እንደ እምነቱ መጠን ይናገር የሚያገለግልም በማገልገሉ ይትጋ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ የሚመክርም በመምከሩ ይትጋ የሚሰጥም በልግስና ይስጥ የሚገዛም በትጋት ይግዛ የሚመጸውትም በደስታ ይመጽውት››(ሮሜ.፲፪፥፮)እንዲል፡፡ ከመልእክቱ እንደተረዳነው መስጠት ብዙ አይነት ነው፡፡ ከነሱም ውስጥ ለምሳሌ ያህል የተወሰኑትን እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን፡፡

1.ፍቅርን መስጠት

ክርስቲያናዊ ፍቅር ከልብ የተተከለ የመውደድ ኃይል አለው፡፡የክርስቲያኖች የመጀመሪያው ፍቅር የቤተሰብ ፍቅር ነው፡፡ፍቅር የሚጀምረው ከቤተሰብ ነውና፡፡”ነገር ግን በእርሱ ስለሆኑት ይልቁንም ስለቤተሰቦቹ የማያስብ ማንም ቢሆን ሃይማኖቱን የካደ ከማያምን ሰው ይልቅ የከፋ ነው(1ኛጴጥ5÷8) ፍቅር የምግባራት ሁሉ ራስ ነው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ፍሬ በማለት ከዘረዘራቸው መካከል የመጀመሪያው ፍቅር ነው (ገላ፭÷፳፪) በዘመናችን ግን ይህ የመንፈስ ፍሬ ከሰው ልጆች ልቡና ጠፍቷል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ደቀ -መዛሙርቱ  በደብረ ዘይት ስለ ዓለም ፍጻሜ በጠየቁት ጊዜ ምልክቱን ሲነግራቸው ከሰው ልጅ ዘንድ ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ አሳስቧቸዋል፡፡ ”ከዐመፃ ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” በማለት (ማቴ24÷12) የፍቅር ሸማ ከሰው ልጆች  ልቡና ውስጥ ተገፍፎ ወድቋል፡፡

“ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻው ቀርቧል እንግዲህ እንደ ባለአእምሮ አስቡ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ ፍቅር የኀጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ ”ይላል (፩ኛጴጥ፬÷፯) ወጥ ማጣፈጫው ጨውና ቅመም እንደሆነ ሁሉ የሰው ማጣፈጫውም ሃይማኖትና ፍቅር ነው፡፡የፍቅር ምንጩ ክርስቶስ  ነው፡፡ አምስት ሺህ አምስት  መቶ ዘመን ለተራቡ ሥጋውን አብልቶ ደሙን አጠጥቶናልና“ወአጽገቦሙ እምበረከቱ ለርኁባን፤ የተራቡትንም በቸርነቱ አጠገባቸው(ሉቃስ1፥53) ዘለዓለማዊ ሕያው አምላክ እግዚአብሔር በቃላት ከመነገርና  በልቡና  ከመታሰብ በላይ የሆነውን ጥልቅ ፍቅሩን የገለጠው  በመስቀል ነው፡፡በአዳም በደል ምክንያት“እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጎድን”(ኢሳ፶፫÷፮)፡፡

ነገር ግን የሰው ልጆች በኃጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይተን እንዳንቀር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በደል ሳይኖርበት የእኛን በደል ተሸክሞ  እኛን ለማዳን በመስቀል ላይ በመሞት ፍቅሩን ገልጾልናል፡፡ ሊቁ  አባ ሕርያቆስም ይህንኑ ሲመሰክር “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት፤ፍቅር ኃያል ወልድን ከዙፋኑ አወረደው እስከ ሞትም አደረሰው” ብሏል (ቅዳሴ ማርያም)፡፡

እግዚአብሔር አብ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር በልጁ በኩል ገልጦልናል፡፡ እርሱም ቅድመ ዓለም የነበረ የባሕርይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶሰ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ፍቅሩን ካሳየን በኋላ ‹‹እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት››(ዮሐ.፲፭፥፲፪) በማለት እርሱ እንዲሁ እንደወደደን እኛም እንዲሁ እንዋደድ ዘንድ አዞናል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ” ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን እንዴት ሊወድ ይችላል? (፩ኛዮሐ ፬÷፰-፲፪) በማለት ያስተማረን፡፤ ስለዚህ ነገ ነፍሳችን  ልብሰ ጸጋዋን  ተገፋ  ከክርስቶስ ፊት እራቁቷን እንዳትቆም ዛሬ በዚህ ዓለም ሳለን የፍቅር ሸማኔ ሁነን ልብሰ ጸጋ ልንሠራላት ይገባል፡፡ድሩን ሃይማኖት ማጉን ፍቅር አድርገን የክብር ልብስ የሠራንላት እንደሆነ ሞገስ ታገኛለች፡፡

ሰው ለፍቅር ዘወትር የጋለ ብረት ምጣድ ሁኖ ከተገኘ ዕድሉ የቀዘቀዘና የፈዘዘ አይሆንበትም”ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሸዋሽዋ ጸናጽል ሆኜኛለሁ….”(፩ኛቆሮ፲፫÷፩-፰) ቅዱስ ጳውሎስ እምነትን፣ተስፋንና ፍቅርን ከዘረዘረ በኋላ የሚበልጠው ፍቅር ነው ይላል፡፡ ክርስቲያኖች የሚኖረን ፍቅር እንደ ፀሐይ እንጂ እንደ ጨረቃ መሆን የለበትም፡፡ፀሐይ ሁል ጊዜ  ሙሉ ነች የእኛ  ፍቅር  ወጥ መሆን አለበት እንጂ ጥቅም ስለምናገኝ ብቻ ሰዎችን የምናፈቅር ከሆነ ጨረቃ ሁነናል ማለት ነው፡፡”በቃልና በኑሮ በፍቅርም፣በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን “(፩ኛጢሞ፬÷፲፩-፲፪)ክርስትና የምንተርከው ታሪክ ሳይሆን በፍቅር የምንኖረው ሕይወት ነው፡፡ፍቅር ለሌሎች በመስጠት ክፉ የሚያስቡትን በፍቅር ማሸነፍ ይገባል፡፡

           2.ምጽዋትን መስጠት

ምጽዋት ሥርወ ቃሉ የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡ትርጓሜውም  ስጦታ፣ችሮታ፣ልግስና  ማለት ነው፡፡ ሰዎች  በሰዎች ላይ የሚያዩትን  ችግር  በማገናዘብ የተቸገሩትን መርዳት  ከፍጹም ፈቃድና ርኅራኄ የሚያደርጉት ስጦታ ምጽዋት ይባላል፡፡ በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፮ ቊ125-127 እንደተገለጠው ምጽዋት ምሕረት ነው፡፡እግዚአብሔር ከሰጪዎች ጋር የሚሰጥ  ከተቀባዮች ጋር ሁኖ የሚቀበል  በመስጠትና በመቀበል  በሰዎች መካከል  መተሳሰብና መረዳዳት  እንዲኖር ሀብትን ለሀብታሞች የሚሰጠው ከእነርሱ የሚያንሱትን እንዲያስተናግዱበት ነው፡፡ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ምጽዋትን የተረጎሙት እንዲህ በማለት ነው “ምጽዋት ማለት የዕለት ምግብና የዓመት ልብስ  ለቸገራቸው ሰዎች ገንዘብ መስጠት ነው ደግሞም ምክር ለቸገራቸው መምከር፣ትምህርት ለቸገራቸው ማስተማር ምጽዋት ነው(ጎሐ ጽባሕ ገጽ ፳፬)፡፡

ምጽዋትን ለተቸገረ ሰው የሚሰጥ ሰው ለእግዚአብሔር መስጠቱ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም” ለደሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል፡”ይላል(ምሳ፲፱÷፲፯)ምጽዋት ብልሆች ሰዎች  በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስቀምጡት አደራ ነው፡፡ ደካሞችን በጉልበት፣ያልተማሩትን በዕውቀት የሙያ ርዳታ የሚስፈልጋቸውን በሙያ መርዳት ምጽዋት ነው፡፡ምጽዋት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ምጽዋት ሰጪዎችም በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠብቃቸው ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው በብሉይና  በሐዲስ ኪዳናት በሰፊው ተገልጦ ይገኛል፡፡”ድሆች ከምድር ላይ አይታጡምና በሀገር ውስጥ ላለ ደኃ ለተቸገረውም ወንድምህ እጅህን ትከፍታለህ ብዬ አዝዝሃለሁ”(ዘዳ፲፭÷፲፩)

“ወንድምህ ቢደኸይ እጁ ቢደክም አጽናው  እንደ እንግዳ እንደመጻተኛ  ካንተ ጋር ይኑር”(ዘሌ፳፭÷፴፭) ልዑል እግዚአብሔርም ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን አብልጦ እንደሚወድ  በነቢያቱ አንደበት ተናግሯል፡፡“……እኔ የመረጠሁት ጾም …እንጀራህን ለተራበ ትቆርስ ዘንድ ስደተኞች ደሆችን ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ የተራቆተውን ብታይ ታስበው ዘንድ አይደለምን?(ኢሳ፶፯÷፯) መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በትምህርቱ ተማርከው ለመጠመቅ የመጡትን ሰዎች እንዲህ በማለት የምጽዋትን አስፈላጊነት አስተምሯቸዋል፡፡ ”ሁለት ልብስ ያለው  ሰው  ለሌላው ያካፍል ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ “ይላል (ሉቃ፫÷፲፩)፡፡

ክርስቲያኖች የሚመጸውቱት ከተረፋቸው ሳይሆን ካላቸው ነው (ሉቃ፳፩÷፩-፬)ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ አስቀድመን እንዳየነው ምጽዋት ትልቅ የክርስትና ቁልፍ በመሆኗ ነው፡፡ብዙዎቻችን የኃጢአት ሥር በተባለው በገንዘብ መውደድ ልባችን ስለታሰረ ምጽዋት የሚመስለን ከተትረፈረፈው ኪሳችን አንድ ብር ለነዳይ መስጠት ነው፡፡ምጽዋት ብድሩ ከልዑል እግዚአብሔር ይገኛል በሚል እምነት ለተቸገሩ ሰዎች የሚሰጥ ልግስና እንደመሆኑ አቀራረቡ ከግብዝነትና ከከንቱ ውዳሴ የጠራ መሆን እንዳለበት ጌታችን አስተምሯል፡፡ የድሆችን ጩኸት ሰምቶ  በችግራቸው  በመድረስ ምላሽ የሚሰጥ  እሱ በተቸገረ ጊዜ  በጎ ምላሽ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኛል፡፡ምጽዋት የክፉ ጊዜ ዋስትና ነው፡፡

ቅዱስ ዳዊት ”ብፁዕ ዘይሌቡ ላዕለ ነዳይ ወምስኪን እምዕለት እኪት ያድኅኖ እግዚአብሔር፣እግዚአብሔር የዐቅቦ ወያሐይዎ ወያበፅዖ ዲበ ምድር፤ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው እሱንም እግዚአብሔር ከክፉ ቀን ያድነዋል”(መዝ፵÷፩-፪) ጠቢቡ ሰሎሞንም “ፈኑ ኅብስተከ ውስተ ገጸ ማይ እስመ በብዙኅ መዋዕል ትረክቦ፤እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው ከብዙ ዘመን (ቀን) በኋላ ታገኘዋለህና”(መክ ፲፩÷፩) እንዴት ሰው ዐይኑ እያየ እንጀራውን በውኃ ላይ ጥሎ ከብዙ ቀን በኋላ ያገኘዋል ልንል እንችላለን እንጀራህን በውኃ ላይ ጣለው ማለት ምጽዋትህን  ለተቸገሩት ለድሆች ስጥ  ማለት ነው፡፡ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኘዋለህ ማለት የምጽዋቱን ዋጋ በገነት በመንግሥተ ሰማያት ታገኘዋለህ ማለት ነው፡፡በውኃ ውስጥ የጣሉት እንዳይታይ ሰውረህ ሳትታይ ምጽዋት ስጥ ውኃ የበላው እንዳይገኝ ከዚያ ተመጽዋች ዋጋ አገኛለሁ ሳትል  ምግብህን በከርሠ ርኁባን  መጠጥህን  በጕርዔ ጽሙኣን አኑር ማለት ነው (ዘዳ15÷7)

ምጽዋት የሚመጸውቱ ሰዎች የሚጠቀሙትን ያህል የማይመጸውቱ ሰዎች ይጎዳሉ፡፡ብዙ በረከትንም ያጣሉ፡፡

በመጨረሻ የፍርድ ጊዜም ወቀሳ ተግሣጽ ፍዳ ይጠብቃቸዋል፡፡ ሰው ከሚረገምባቸው የጥፋት ሥራዎች አንዱ ለድሆች አለማዘንና አለመራራት ነው፡፡እስመ ኢተዘከረ ይግበር ምጽዋተ ሰደደ ብእሴ ነዳየ ወምስኪነ፤ምጽዋትን ያደርግ ዘንድ አላሰበም ችግረኛና ምስኪን አሳዷልና“ይላል (መዝ፻፰÷፲፭)ምጽዋት በመስጠት ሰው ፈጣሪውን በሥራ ይመስለዋል፡፡ለሰው ማዘን መራራት ገንዘብ መስጠት ከአምላክ ባሕርይ የሚገኝ ነውና”ወበምጽዋት ይትሜሰሎ ሰብእ ለፈጣሪሁ እስመ ውሂበ ምፅዋት ወተሣህሎ እምነ ጠባይዕ አምላካዊ “እንዳሉ (፫፻.) ፡፡

ምጽዋት መስጠት ለአምላክ ማበደር ነው፡፡ከአምላክ ጋር የሚነግዷት ንግድ ናት፡፡“ወምጽዋትሰ ልቃሕ አምላካዊት ወይእቲ ካዕበ ተናግዶ አምላካዊት ማእምንት ርብሕት“እንዲሉ  ፫፻.ዳግመኛም ቍርባን ናት በከርሠ ነዳያን የምትቀርብ ናት ”ወይእቲ ካዕበ  ቍርባን  ውክፍት  በኀበ መቅደስ  ነባቢት “እንዳሉ( ፫፻.) ራሱን  መርዳት የሚችል ሰው የሰውን ገንዘብ አይቀበል ወጥቶ ወርዶ  ራሱን ይርዳ፡

ቅዱሳን ሐዋርያትም ገንዘብ እያለው ምጽዋት የሚቀበል ወዮለት ብለዋል፡፡ምጽዋት ከክፉ ታድናለች፤ኃጢአትን ታስተሠርያለች፡፡ውኃ እሳትን እንዲያጠፋ ምጽዋትም ኃጢአትን ታጠፋለች” ለእሳት ዘትነድድ ያጠፍኣ ማይ ወከማሁ ምጽዋትኒ ታኀድግ ኃጢአተ “እንዳለ ሲራክ ፫÷፳፰፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ “ወእመ ትብሎ አንሰ ወሀብኩከ  ብዙኀ  ጊዜ እብለከ ኢትበልዕኑ አንተ በኵሉ ጊዜ፣ብዙ ጊዜ ሰጠሁት  ይበቃሃል አትበል አንተ ጠዋት ማታ ትበላ የለምን ?እንደራስህ አታየውምን ?”ይላል፡፡

ምጽዋት የሚሰጠው ለሰዎች መልካም ነገር በማድረግ ከእግዚአብሔር መልካም ነገር ለማግኘት ነው፡፡”ስጡ ይሰጣችኋል“ተብሏልና (ማቴ.፲፥፰፣2ኛቆሮ.፱፥፯—፲፪) በምጽዋት የተጠቀሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ምናሴ ጠላቶቹ ከመከሩበት መቅሠፍት የዳነው ምጽዋትን በመመጽወቱ ነበር

የጌታን ትእዛዝ፣ፈቃድና ትምህርት መሠረት አድርገው ያስተማሩ ቅዱሳን ሐዋርያትም “ካለው የሚሰጥ ብፁዕ ነው ”በሚል ኃይለ ቃል የምጽዋትን ነገር ትኩረት ሰጥተውታል (የሐዋ.ሥራ ፳÷፴፮) ዕዝ ፱÷፭)ምጽዋትንበፍቅር መመጽወት ይገባል፡፡አበው “ከፍትፍቱ ፊቱ“እንዲሉ፡፡ቅዱስ ያዕቆብ “በጎ ለማድረግ ዐውቆ ለማይሠራው  ኃጢአት ነው“(ያዕ፬÷፲፯) ይህን በጎ ምግባር ሠርተን እንዲንጠቀም የእጃችንን እስራት አምላካችን ይፍታ በእርግጥ የእግዚአብሔር ስጦታውን በቃላት ተናግረን አንጨርሰውም (፪ኛቆሮ፱÷፲፭)

  1. ለሚጠይቁን ተገቢ የሆነ ምላሽ መስጠት

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያት ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት የተዘጋጃችሁ ሁኑ ነገር ግን በቅንነትና በፍርሀት ይሁን”ይላል( ፩ጴጥ፫÷፲፭ )

ሰሎሞንም“ ልጄ ሆይ ጠቢብ ሁን ልቤንም ደስ አሰኘው ለሚሰድቡኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ”ይላል( ምሳ፳፯÷፲፩) “በውኑ ለቃል ብዛት መልስ መስጠት አይገባምን?ወይስ ተናጋሪ ሰው እንደ ጻድቅ ይቈጠራልን?ትምክህትህስ ሰዎችን ዝም ያሰኛቸዋልን?…(ኢዮ፲፩÷፪)

ዘመናችን ከየትኛውም ጌዜ  በተለየ  በእምነት ስም የተቋቋሙ ድርጅቶች ከቀን  ወደ ቀን  የበዙበትና  እንደ አሸን የሚፈሉበት መሆኑን በዐይናችን እያየን በጀሯችን እየሰማን  ነው፡ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኘውን የሦስት ሺህ ዓመታት የሃይማኖት ባላ ታሪክ ሀገራችንን ኢትዮጵያንም በየዘመኑ ከመፈታተን ያረፉበት ጊዜ የለም፡፡ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ግን ጥያቄዎችን በትሕትና በመቀበል ለመናፍቃኑ ተገቢውን ምላሽ ሲሰጡ በመቆየታቸው እናት ቤተ ክርስቲያን ከሥር መሠረቷን ከላይ ጉልላቷን ለማፍረስ የመጡት ሳይሳካላቸው እነርሱ ፈራርሰው ቀርተዋል፡፡ይህን የመናፍቃን ክዶ የማስካድና ተጠራጥሮ የማጠራጠር የኑፋቄ ዘመቻ ለመግታት የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት በጉባኤ  በማስተማር መናፍቃን ለቃቅመው ላመጡት ጥያቄ ኦርቶዶክሳውያን አባቶቸች በየዘመናቱ ተገቢውን ምላሽ  በመስጠት አሳፍረው መልሰዋቸዋል፡፡ በእምነት ስም በየጓዳው የሚቋቋሙ የመናፍቃን ድርጅቶች ዓላማ የኢትዮጵያውያንን የሃይማኖት መሠረት  በማናጋት ሕዝቡ የራሴ የሚለውን እምነቱንና ሥርዓቱን መንፈሳዊ የሆኑ ነገሮችን እንዲያጣ  ማድረግ ነው፡፡ስለዚህ ምእመናን ነቅተውና ተግተው ሊጠብቁ ይገባቸዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህንና መሰል በጎ ምግባራትን ማድረግ ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ‹‹በከንቱ የተቀበላችሁትን በከንቱ ስጡ››(ማቴ.፲፥፰) ብሎ እንዳስተማረን በተሰጠን ጸጋ ያለ መሰሰት ማገልገልና በልግስና መሥጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ብናደርግ ዋጋችን ታላቅ ነው፡፡

ምንጭ፤ ሐመር መጽሔት 26ኛ ዓመት ቁጥር 3 ሐምሌ 2010ዓ.ም

 

 

፲ቱ ማዕረጋት

ሐምሌ 14 ቀን 2006 ዓ.ም.

መምህር ደጉ ዓለም
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ
የሐዲስ ኪዳን መምህር

  • ኩኑ ቅዱሳን እስመ ቅዱስ አነ” ዘሌ.19፡2

ቅዱሳን ማለት የተቀደሱ፣ የከበሩ፣ የተመሰገኑ፣ የተለዩ፣ የተመረጡ፣ ንጹሐንየሆኑ፣ የጠሩ….. ወዘተ ማለት ነው፡፡ ቅዱሳን በዚህ ስም የሚጠሩበት ከሰው ወይም ከምድራዊ ባለሥልጣን የተቸሩት አይደለም፡፡

በሃይማኖት ጸንተው በምግባር ጐልምሰው የሥጋ ምኞታቸውን ጥለው አፍርሰው ሲገኙ የቅድስና ባለቤት ቅዱስ እግዚአብሔር እነሱን /ቅዱሳንን/ መሣሪያ አድርጐ ኃይሉንና ሥልጣኑን ቢገልጽባቸው ማኅደረ እግዚአብሔር መሆናቸው ይገለጻል፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ እሱ እግዚአብሐር ቅዱስ ተብሏልና የጌትነቱ መገለጫ የሆኑ ሁሉ ቅዱሳን ይባላሉ ጻድቃን እንደመ ላእክት ውሉደ እግዚአብሔር ይባላሉ /ኢዮ.1፡6/፣ ሮሜ.8፡14/ ቅዱሳን ጻድቃን በግብር መላእክትን መስለው ሆነው የፈጣሪአቸውን ፈቃድ ፈጽመው በመገኘታቸው ከዚህ ዓለም በመለየታቸው ቅዱሳን ሲባሉ የፈጣሪአቸውን ሕያው መንግሥት ወራሾች ናቸውና ውሉደ እግዚአብሔር ይባላሉ፡፡ በሌላም ቃል ውሉደ ብርሃን ይባላሉ፡፡ /ሉቃ.16፡8/ በዓለማቸው ይራቀቃሉና ይህን ዓለም ይጠሉታል፡፡ ውሉደ ሕይወት ይባላሉ ሞትንና የሞት ከተማ ይህን ዓለም ይንቃሉና በክብር ተነሥተው ዳግመኛ ሲሞቱ የማይገባቸው ስለሆነ /ሉቃ.10፡30/ ውሉደ ጥምቀት ተብለዋል ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትናን ተጐናጽፈዋልና፡፡ ውሉደ መንግሥትም ተብለዋል የመንግሥተ ሰማያት ባለቤቶች ናቸውና፡፡ በጸጋ እግዚአብሔር የበለጸጉ በመሆናቸው የእግዚአብሔር አዕይንተ እግዚአብሔር ተብለዋል /መዝ.33፡15/

የፈጣሪአቸው ፈቃድ በተግባራቸው ስለሚታይ የእግዚአብሔር አዝነ ፈቃድ ወደ ጻድቃን ነው፡፡ ልመናቸው ጾማቸው እንዲሁም ምጽዋታቸው ሁሉ የተወደደ መሥዋዕት ነው፡፡ ቅዱሳን በዓላማቸው ጾምን ግብዣ /ድግስ/፣ ለቅሶን ዘፈን፣ ደስታን ሐዘን አድርገው በመኖራቸው ይህ ተለዋዋጭ ዓለም በየጊዜው የሚአቀርብላቸው መርዶ በእነሱ ዘንድ ዋጋ የለውም ወይም ዋጋ አይሰጡትም፡፡ ዓለምም ለእነሱ የሚያቀርበው ዓለማዊ የምኞት ስጦታ እንደ ኢምንት የተቆጠረ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ገጸ መዓቱ ወደ ዓለማውያን ሰነፎች እንደሆነ ገጸ ምሕረቱ ወደ ቅዱሳን ነው፡፡ ስለዚህ አማላጅነታቸው ጸሎታቸው በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ “አፍቅርዎ ለእግዚአብሔር ኲልክሙ ጻድቃኑ” ቅዱሳን እውነትን ይዛችሁ ትሕትናን ተላብሳችሁ እግዚአብሔርን ውደዱት “እስመ ጻድቅ የሐስስ እግዚአብሔር” እግዚአብሔር እውነትን ትሕትናን ይወዳልና፡፡ /መዝ.30፡23/ የቅዱሳን ፍሬ ትሕትና ነው፡፡ በዓይነ ሕሊናቸው ፈጣሪአቸውን በዓይነ ሥጋቸው የእነሱን ምንነት እንዲሁም የዓለምን ከንቱነት ይመለከታሉ፡፡

 

ፍሬ የያዘ ተክል ሁሉ ቁልቁል የተደፋ ነው፤ ትሕትናን ያስተምራል፣ የጻድቃን ምሳሌ ነው፡፡ በፈሪሃ እግዚአብሔር ልቡ የተሰበረ እሱነቱን /ምንነቱን/ የመረመረ ሰው በዓይነ ሕሊናው የፈጣሪውን ቸርነት በዓይነ ሥጋው የራሱን ውድቀት ይመለከታል፡፡ ይህ አመለካከት ለጸጋ እግዚአብሔርና ለፍሬ ክብር ያደርሱታል፡፡ በመቅረዝ ላይ ያለች መብራት መሰወር እንዳይቻላት የመቅረዙ ከፍታ የግድ እንደሚገልጻት በተራራ ላይ ያለች ቤትም በእይታ እንደማትሰወር የተራራው ከፍታ እንደሚገልጻት በጥበበ እግዚአብሔር ከብረው በጸጋ እግዚአብሔር ተውበው የሚኖሩ ቅዱሳን ጻድቃንም ደረጃ በደረጃ ማዕረጋትን አልፈው ከመለኮት ባሕርይ ተካፍለው የተአምራት መገለጫ ተካፍለው የተአምራት መገለጫ ይሆናሉ፡፡ “መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኑ” /መዝ.67፡35/ “እግዚአብሔር በቅዱሳኑ በወዳጆቹ አድሮ የሚሠራው ሥራ ድንቅ ነውን፡፡ /2ኛጴጥ.1፡3/ ቅዱሳን የጸጋ ተዋሕዶ ተዋሕደው ሲገኙ ሙት ሲሆኑ ሙታንን ማስነሳት እውር ሲሆነ እውርን ማብራት፣ በዓለም ላይ ድንቅ ሥራቸው ይሆናል፡፡ የጸጋና የክብር ተሸላሚዎች ሆነዋልና በዓለም ላይ ሳሉ የሚመጣባቸውን ፈተና ሁሉ ከምንም ባለመቁጠር ተቋቁመው የጸጋ መቅረዝ ተቋሞች ይሆናሉ፡፡ በዚህም በአላሰለሰው ሕይወታቸው የአንበሳ አፍ ዘጉ /ዳን.7፡1-28/ ውኃውን ወደ ኋላው መለሱ /ዘጸ.14፡22/ ሰማይን አዘዙ /1ኛ ነገ.17፡1፣ ያዕ.5፡17/ ነበለባለ እዥሰት አበረዱ /ዳን.3፡1-13/ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ ወዳጅ እግዚአብሔር ከዘመድ ባዕድ ከሀገር የሚኖሩትን በረድኤት ይቀበላል፣ ሥጋዊ ሀገረ ተድላን ጥለው ሓላፊ ጠፊ ምድራዊ ምቾታቸውን ንቀው ጸጋውን የሚጠባበቁትን ሁሉ አብሮአቸው ይኖራል፡፡ ትዕግስትን የጥዋት ቁርስ የቀን ምሳ የማታ እራት አድርገው የሚመገቡትን ሁሉ ቤተ መቅደስ አድርጓቸው ይገኛል፡፡ 

 

ቅዱሳን በዚህ ዓለም ይጠበቡበታል፣ ወጥተው ወርደው እነሱነታቸውን ከስስት ኃጢአት ጠብቀው ለወዲያኛው ዓለም ደግሞ በትዕግሥት ደጅ ይጠኑበታል፡፡ “አሪሃ እግዚአብሔር ትፍስህተ ልብ ውእቱ ወይሁብ ሐሴተ ወያስተፌስህ ወያነውሀ መዋዕለ ሕይወት፤ እግዚአብሔርን መፍራት የልብ ደስታ ነው፡፡ ፍጹም የሥጋና የነፍስን ደስታ ይሰጣል በሕይወትም ያኖራል፡፡” “ለፈሪሃ እግዚአብሔር ይሴኒ ድሐሪቱ ወይትባረክ አመ እለተ ሞቱ እግዚአብሐርን የሢፈራ ሰው ፍጻሜው ያምርለታል እንደ ኢዮብ ከደዌው ተፈውሶ ልጅ ልጅ አይቶ ይሞታል /ኢዮብ.31፡16/ ይህ ሁሉ በረከት የቅዱሳን የሁልጊዜ ፍሬ ነው፡፡

 

ቅዱሳን ሁል ጊዜ የሚሠሩት ሰማያዊ ድርብ ድርብርብ /እንደ ሐመረ ኖኅ/ በጸጋ ላይ ጸጋ እየተጨመረላቸው ወደ 10ሩ መእረጋት ይወጣሉ፡፡ በያዙት ቀን መንገድም ኢዮባዊ ትዕግስት አብርሃማዊ ሂሩት ይስሐቃዊ ፈቃደኛነት ያዕቆባዊ ቅን አገልግሎት ጠሴፋዊ ሀዳጌ በቀልነት ሙሴአዊ ለወገን ተቆርቋሪነት እየጨመሩ በመኖራቸው ሳያውቁት የፈጣሪአቸውን ኃይል የጌትነቱ የመለኮትነቱን ድንቅ ሥራ መገለጫዎች ይሆናሉ፡፡

ማዕረጋቸውን ከዚህ ይናገሩታል፡-

የንጽሐ ሥጋ ማዕረጋት 3 ናቸ ው እነሱም፡-

  1. ጽማዌ

  2. ልባዌ

  3. ጣዕመ ዝማሬ ይባላሉ፡፡

የንጽሐ ነፍስ ማዕረጋት 4 ናቸው

  1. አንብዕ

  2. ኲነኔ

  3. ፍቅር

  4. ሁለት ናቸው፡፡

የንጽሐ ልቡና ማዕረጋት ናቸው እነሱም

  1. ንጻሬ መላእክት

  2. ተሰጥሞ

  3. ከዊነ እሳት ናቸው፡፡

የንጽሐ ሥጋ ማዕረጋት

  1. ማዕረገ ጽማዌ፡- ይህ ማዕረግ የመጀመሪያው ነውና ማስተዋል ውስጣዊ ትዕግስትን ውስጣዊ ትህትና ውስጣዊ የራስ ሚዛንን ይዞ ማሰላሰል…… ወዘተ ይጀምራል፡፡ ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ እግዚአብሔርን ብቻ መዘከር ይችሉ ዘንድ የዚህን ዓለም ውጣ ውረድ ከማውራት ይከለከላሉ፡፡ በዚህ ማዕረግ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ያያሉ፡፡ ነገር ግን ለምን እንደሚወጡና እንደሚወርዱ አያውቁም፡፡ ዮሐንስ ሐጺር የሰፋውን ስፌት ገበያ ላይ ለመሸጥ ተቀምጦ እያለ እርሱ ግን በተመስጦ እነ ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን እንዲሁም ሌሎችን መላእክት በየማዕረጋቸው እያየ ሲያደንቅ ስፌቱን የሚገዛ ሰው ቁሞ እንቅቡ ዋጋው ስንት ነው ብሎ ሲጠይቀው እርሱ የሚያየውን የሚያይ መስሎት “ሚካኤልኑ የዓቢ ወሚመ አኮ ገብርኤል ሚካኤል ይበልጣል ወይስ ገብርኤል” ብሎ በአንክሮ ጠየቀው፡፡ ይህን ሲለው ሰውየው ይሄስ እብድ ነው ብሎ ትቶት ሄዷል፡፡

  2. ማዕረገ ልባዌ፡– ደግሞ ማስተዋል ልብ ማድረግ አሰሙኝ እንጂ ስሙኝ አለማለት ልማር እንጂ ላስተምር አለማለት የተነገረው ትንቢትና ተግጻጽ ምዕዳን ሁሉ የራሱ እንደሆኑ መገመት መመርመር ዓይነ ሥጋን ከመጽሐፍ ከስነ ፍጥረት ዓይነ ነፍስን ከምስጢር….. ወዘተ ማዋል ነው፡፡ ወይም የእግዚአብሔርን ቸርነት ማድነቅ ስለሰው ያደረገውን ውለታ ማሰላሰል ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከሰው መወለዱን በገዳም መጾሙን መገረፉን ሥጋውን መቁረሱን ደሙን ማፍሰሱን መሰቀሉን መሞቱን መቀበር መነሳቱን እያሰቡ ልብን በፍቅረ እግዚአበሔር መሰበር አንደበትን በመንፈሳዊ ሕይወት መስበር ዓላማን በገጸ መስቀል/ትዕግሥት/ ማስተካከል የመሳሰሉት ናቸው፡፡

  3. ማዕረገ ጣዕመ ዝማሬ፡- ከዚህ ደረጃ ሲደርስ አንደበትን ከንባብ ልቡናን ከምስጢር ማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱሳን ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ አንደበታቸው ምንም ዝም ቢል በልባቸው ውስጥ ዝም አይሉም፡፡ ከአፍ እስትንፋስ ከአፋፍ ላይ ነፋስ እንደማይለይ ሁሉ ከአንደበታቸው ትዕግስት ከእጃዋው ምጽዋት ከልቡናቸው ትሕትና ከሰውነታቸው ንጽሕና አይለይም፡፡

  4. የሚጸልዩትና የሚይነቡት ምስጢሩ እየገባቸው ስለሚያደርጉት አይሰለቻቸውም፡፡ ከዚህ ማዕረግ የደረሰ አንደ ባሕታዊ ለብዙ ዘመናት አቡነ ዘበሰማያት /አባታችን ሆይ/ እያለ ብቻ ሲኖር መልአክ መጥቶ ይትቀደስ ስምከ በል እንጁ ቢለው ኧረ ጌታዬ እኔስ አቡነ የሚለው ኃይለ ቃል ምስጢሩና ጣዕሙ በአፌ እንደ ጨሙ እየሟሟ አልጠገበኝ ብሏል እንዴት አድርጌ ወደፊት ልሂድ ብሎታል፡፡

የንጽሐ ነፍስ ማዕረጋት 

  1. ማዕረገ አንብዕ፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ቅዱሳን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ያደረገውን ፍቅር እስከ ሞትና መቃብር የተጓዘውን የመከራ ጉዞ እያሰቡ በአንጻሩም ምረረ ገሃነመ እሳትን ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን እያሰላሰሉ ውሉደ አዳም ይህን ሁሉ መከራ ባለ መገንዘብ ወደ ሰፊው የፈቃደ ሥጋ ሲጓዝ በማየታቸው ሲአለቅሱ ይታያል፡፡ ያለምንም መሰቀቅ ሲአለቅሱ እንባቸው እንደ ምንጭ ይፈሳል፡፡ እንደ ሰን ውኃ ይወርዳል ይኸውም ለዚህ ዓለም ብለው የሚአለቅሱት ልቅሶ ፊትን ያንጣጣል ዓይንን ይመልጣል የቅዱሳን ልቅሶ ግን ፊትን ያበራል ኃጢአትን ያስወግዳል እርጥብ እንጨት ከእሳት ጋር በተያያዘ ጊዜ እንጨቱ ከነበልባለ እሳት ሲዋሐድ እንጨቱ እርጥብነቱን ትቶ ውኃውን በአረፋ መልክ እያስወገደ ይነዳል፡፡ ቅዱሳንም በግብር/በሥራ/ ከመለኮት ጋር ሲዋሐዱ የዚህ ዓለም ምስቅልቅል ሥራ በሰማያዊ የረጋ ሕይወት ተለውጦ አሠራራቸው አካሄዳቸው ፍጹም ሕይወታቸው መልአካዊ ይሆናል፡፡

  2. ማዕረገ ኲነኔ፡- ከዚህ ማዕረግ ላይ ሲደርሱ ሥጋዊ ፈቃድ ሁሉ ለነፍስ ፈቃድ ይገዛል ነፍስ በሥጋ ባሕርያት ላይ ትሰለጥናለች ምድራዊ /ሥጋዊ/ ምኞት ሁሉ ይጠፋና መንፈሳዊ /ነፍሳዊ/ ተግባር ሁሉ ቦታውን ይወርሳል ያለምንም ማወላወል መንፈሳዊ ተግባር ሁሉ ይከናወናል፡፡

  3. ማዕረገ ፍቅር፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ውሉደ እግዚአብሔር ቅዱሳን እንደ ፈጣሪአቸው ሁሉን አስተካክለው በመውደድ ይመሳሰላሉ አማኒ መናፍቅ ኃጥእ ጻድቅ ዘመድ ባእድ ታላቅ ታናሽ መሃይም መምህር ሳይሉ አስተካክለው በመውደድ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

  4. ማዕረገ ሁለት፡- ቅዱሳን ከዚህ ማዕረግ ላይ ሲደርሱ ባሉበት ሆነው ሁሉን ማየት መረዳት ይችላሉ፡፡ ጠፈር ደፈር ሳይከለክላቸው ርቀት ሳያግዳቸው ሁሉን በሁሉ ይመለከታሉ፡፡

የንጽሐ ልቡና ማዕረጋት

  1. ንጻሬ መላእክት

  2. ተሰጥሞ

  3. ከዊነ እሳት ናቸው፡፡

  1. ማዕረገ ንጻሬ መላእክት፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ የመላእክት መውጣት መውረድ ማየት ተልእኮአቸውን ያለምንም አስተርጓሚ መረዳት ማነጋገርና ማማከር የመሳሰሉትን መፈጸም፤ ለምሳሌ እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ መልአኩን 10 ዓመት ማቆም ነው፡፡

  2. ማዕረገ ተሰጥሞ፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደረስ በባህረ ብርሃን መዋኘት ባሉበት ሆኖ ወደ ላይም ወደታችም መመልከት መቻል….. ወዘተ ናቸው፡፡

  3. ማዕረገ ከዊነ እሳት /ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ/፡- የፈጣሪ ቤተ መቅደስ ሆኖ ጸጋ በተዋሕዶ ከመላእክት ጋር ሆኖ ረቆ ማመስገን ያሉበትን ሥጋ በብቻው ማየት በአካለ ነፍስ ሰማየ ሰማያትን መጐብኘት ገነት ውስጥ መግባት ናቸው፡፡

እነዚህም የቅዱሳን ማዕረጋት 10 ናቸው፡፡ /2ኛ ጴጥ.1፡4-10፣ ዮሐ.1፡40/ የአስሩ ማዕረጋት ምሳሌዎች የአስሩ ቃላት፡፡ /ዘጸ.20፡3-12፣ ዮሐ.13፡17/

በመጨረሻም ቅዱሳን የቅዱስ እግዚአብሔር ቤተ መቅደሶች ናቸው ኑሮአቸውም ቅዱስ ነው፡፡

የቅዱሳን በረከታቸው አይለየን፡፡ አሜን፡፡

  • ምንጭ፡- ዝክረ ቅዱሳን ኅዳር ፮ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም.

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር

ኅዳር 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

ሊቀ ልሣናት ቀሲስ ከፍያለው ጥላሁን

ሥነ ምግባር፡- ማለት ደግነት፣ በጎነት፣ መልካም ጠባይ ማለት ሲሆን ክርስቲያን የሚለው ቃል ሲጨመርበት ደግሞ የተሟላና የተለየ ያደርገዋል፡፡ መልካም ጠባይ ማንም ሰው ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የተሟላ ዘላቂና የሁል ጊዜ ሆኖም ለሰማያዊ መንግሥት የሚያበቃው በክርስትና እምነት ሲኖሩ ነው፡፡

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፡- በምድር እያለን ሰማያዊ ኑሮ ኖረን ለሰማያዊ መንግሥት የምንበቃበት ሕይወት ነው፡፡ ሰውን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ማስደሰት ነውና፡፡ በመሆኑም ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሚከተሉት ሕግጋት ሊለካ ይችላል፡፡

 

1.    ሕገ እግዚአብሔር

መጀመሪያውና ዋነኛው የክርስቲያን ሥነ ምግባር መለኪያው ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ አንድ ሰው ምናልባትም ሕይወቱ በሰው ፊት ሲታይ የማያስደስት በአፍአ ያለው ጠባዩ እንከን የማይወጣለት ሊሆን ይችላል፡፡ በሕገ እግዚአብሔር ተመዝኖ ካላለፈ ዋጋ የለውም በሰው ፊት መልካም ሆኖ የሚታይ ምግባር እግዚአብሔርን ሊያስደስት ያስፈልጋል፡፡ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ፡፡” ፌፌ.6፥6

 

ፈሪሳውያን ከእነርሱ ውጪ የሆነውን ሁሉ የናቁ ያለእኛ ሕገ እግዚአብሔርን አክባሪ ከእኛም በላይ ጻድቅ የለም ባዮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዞችና ሥራቸው ሁሉ ከንቱ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ እንዲያውም “ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም” ማቴ.5፥20 በማለት ደቀ መዛሙርቱን አስጠነቀቀ፡፡ እንዲያውም ከእነርሱ እርሾ /ትምህርት/ እንዲጠበቁ አስጠነቀቃቸው፡፡ “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” ማቴ.16፥6 አለ፡፡ ከዚህም ሌላ ብዙ ሠርተናል ሥነ ምግባራችን አስደሳች ነው እያሉ ለመወደስ በኩራት ይቀርቡ የነበሩትን ሁሉ አፍረው እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ ማቴ.19፣16-22

 

የንጉሥ ሳዖል ሥራ በራሱ በንጉሡ አሳብ ሲመዘን ምክንያታዊና ትክክልም ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን ሊያስደስት አልቻለም፡፡ ቃሉን ስላላከበረ ለእርሱም ስላልታዘዘ ንቀኸኛልና ንቄሃለሁ ተባለ፡፡ ከንግሥናውም ወረደ፡፡ 1ሳሙ.15፥10-22 “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡” ዕብ.11፥6

 

ክርስቲያን በጉዞው ሁሉ በጭፍን በራሱ እውቀት ብቻ አይመራም፡፡ በቃለ እግዚአብሔር ሕይወቱን እየመዘነ ሊራመድ ያስፈልጋል፡፡ “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ ራሳችሁን ፈትኑ፡፡” 2ቆሮ.13፥5 የክርስትና እምነት እያጸኑና እየጠነከሩ እየበሰሉ የሚጓዙበት ሕይወት ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ክርስቲያን ከትላንት ዛሬ ከአምና ዘንድሮ አድጐ ጠንክሮ መገኘት አለበት፡፡ “ንቁ በሃይማኖት ቁሙ ጐልምሱ ጠንክሩ” 1ቆሮ.16 በሃይማኖት መጠንከር ሲባል በጊዜውም /በተመቸ ጊዜ/ አለ ጊዜውም /ባልተመቸ ጊዜ/ መጠንከር ይገባል፡፡ “በጊዜውም አለ ጊዜውም ጽና፡፡” 2ጢሞ.4፥2 እንዲል፡፡

 

ከሰው ሕግ ይልቅ የእግዚአብሔር ሕግ ቅርብ ነው፡፡ ከሰው ሕግ መደበቅ መሸሽ ይቻላል፡፡ ከእግዚአብሔር ግን ማምለጥ አይችልም፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ሥራ በእርሱ ዘንድ የተገለጠች ናት፡፡ የጲጥፋራ ሚስት ዮሴፍን ማንም አያየኝም ኀጢአት እንሥራ ብላ ለሁለት ዓመታት ባባበለችው ጊዜ ኩፋ.27፥25 እግዚአብሔር ከእርሱ እንደማይለይ እያንዳንዱም ሥራው በፊቱ የተገለጠ እንደሆነ ያመነው ኀጢአትን እንዴት እሠራለሁ በማለት መለሰለት፡፡ ዘፍ.39፥9፣ መዝ.138፥2-12

 

ስለዚህ ክርስቲያናዊ አኗኗራችን መልካም ምግባራችን ትክክለኛ የሚሆነው በእግዚአብሔር ሲመዘን ብቻ ነው፡፡ ብልጣሶርን “በሚዛን ተመዝነህ ቀለህ ተገኘህ” ዳን.5፥27 የተባለው ለዚህ ነው፡፡ የሰው ልጁ ሕግ ተለዋዋጭና ጊዜያዊ ነው፡፡ ሕገ እግዚአብሔር ግን በዘመናት ብዛት የማይሻርና ቋሚ በመሆኑ ምግባራችን ከዚህ አንጻር ሊለካ ያስፈልጋል፡፡ “እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ፡፡ ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሠላም ነው፡፡” ሮሜ.8፥5‐6

 

2.    ሕገ ልቡና

እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ ሁኔታ የሚመራመር ክፉና በጎውን ለይቶ የሚያውቅ አእምሮ ሰጥቶታል፡፡ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፡፡” መዝ.139፥10 እንዲል፡፡ በተጨማሪም “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው፡፡”መዝ.118፥105 ብሏል፡፡ ሕግ ለሙሴ ከመስጠቱ በፊት ደጋግ አባቶች በዚህ ሕግ እየተመሩ እንደሚገባ ኖረዋል፡፡

 

የሰው ልጅ ማንም ባያስተምረውና ባይነግረው የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ያውቃል፡፡ “እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን እያንዳንዱም ወንድሙን እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና ይላል እግዚአብሔር፡፡” ኤር.31፥34 ምሳሌ አቤል “ከበጎቹ በኩራትና ከላቡ አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ ወደ ቃየል እና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም፡፡” ዘፍ.4፥4-5 ሄኖክ “አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም እግዚአብሔር ወስዶታልና፡፡” ዘፍ.5፥24 ኖኅ “ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አገኘ በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፡፡” ዘፍ.6፥9 እነዚህና ሌሎችም በሕገ ልቡና ተመርተው መልካም ተግባር የፈጸሙና እግዚአብሔርም ሥራቸውን የወደደላቸው ናቸው፡፡ ዕብ.11፥4-7

 

የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር በራቀ ቁጥር ግብሩ ወደ እንስሳነት ይለወጥና የሚወቅሰው ኅሊና እንኳን ያጣል፡፡ “የሰው ልጅ ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ፡፡” መዝ.48፥12 ናቡከደነፆር በበደል ላይ በደል በመጨመሩ ለእግዚአብሔር ሕግ አልገዛም በማለቱ ግብሩ ሁሉ የእንስሳ ሆነ፡፡ ዳን.4፥32 ስለዚህ ክርስቲያን በመጽሐፍ ከተዳፈነው የእግዚአብሔር ሕግ በተጨማሪ በልቡናው ለተቀረጸው ሕግ ይገዛል፡፡ ራሲንም እየመረመረ ይጓዛል አጥፍቶም እንደሆነ ማንም ሳይፈርድበት በራሱ ላይ ይፈርዳል፤ ንስሐ ይገባል የጠፋው ልጅና በጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ለዚህ ምስክር ይሆኑናል፡፡ ሉቃ.15፥11-19፣ ሉቃ.23፥41

 

3.    የሰው ሕግ

ይህን በሁለት ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው የአንድ ሀገር መንግሥት ወይም የሚያስተዳድር አካል ሕዝቡን ለማስተዳደር የሚያወጣው ሕግ ከሆነ ሁለተኛው ደግሞ ኅብረተሰቡ በባሕሉ ትክክል ነው ብሎ የተቀበለውና በወረቀት ያልተጻፈው ሕግ ነው፡፡ “በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ” 2ተሰ.2፥15 እንዲል፡፡

 

ክርስቲያን ለእግዚአብሔር ሕግ እንደሚገዛ ሁሉ የሰውንም ሕግ ከእግዚአብሔር ጋር እስከ አላጣላው ድረስ ሊያከብር ይገባል፡፡ አንድ ሰው ምንም ብጾም ብጸልይ፣ ለእግዚአብሔር እገዛለሁ ቢል የሚያስተዳድረውን አካልና የኅብረተሰቡን መልካም ባሕል ካፈረሰ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባሩን ጎደሎ ያደርገዋል፡፡ በሥራ ቦታ የታዘዘውን ካልፈጸመ፣ የሥራ ሰዓት ካላከበረ፣ በቤተ ክርስቲያን ያለውን ምግባሩን በሌላ ሥፍራ ካልገለጸው ዋጋ አይኖረውም፡፡ ለእግዚአብሔር እንደሚገዛ ሁሉ በሰውም ፊት ያለነቀፋ ሊኖር  ያስፈልጋል፡፡ “በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ በእነርሱም መካከል የሕይወት ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ” ፊል.2፥15

 

ሐዋርያው ከዚህም በተጨማሪ “ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን እናስባለን” ብሏል፡፡ 2ቆሮ.8፥20 ይህ ሲባል ኀጢአትም ሲሆን የሰው ሕግ ወይም ባሕል ነውና ሁሉን መፈጸም አለበት ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ያስፈልጋል፡፡

 

ለምሳሌ ከአንድ በላይ ማግባት፣ ጫት መቃም፣ ዋርሳ መያዝ፣ ባሕል በሆነበት አካባቢ የሚኖር ክርስቲያን ከሰው ጋር ለመኖር በሚል ሰበብ ይህንና ይህን የመሰለ የአረማውያኑን ኑሮ ይኑር ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ክርስቲያን በእንዲህ ዓይነት ሰዎች መካከል ሲኖር የቅድስናን ሕይወት በተግባር በመኖር ማንነቱን ሊገልጥ ያስፈልጋል፡፡ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ፡፡” ማቴ.5፥16

 

ከዚህ አንጻር ብዙ ወጣቶች ሕገ እግዚአብሔርን ከኑሮአቸው ጋር አጣጥመው መጓዝ ሲከብዳቸው ይታያሉ፡፡ በእምነት የጸኑትን ሠለስቱ ደቂቅን፣ ዮሴፍን ሶስናን አይመለከቱም፡፡ እንኳን ክርስቲያን የሚለውን ስም የተሸከሙ ሲጠራም የሰሙት የማይመስሉ አሉ፡፡ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሰውና በእግዚአብሔር ፊት የምንኖረው ኑሮ እንደመሆኑ መጠን የግል መንፈሳዊ ሕይወትና ማኅበራዊ ኑሮ በማለት በሁለት ከፍለን መመልከት እንችላለን፡፡

 

ሀ. የግል መንፈሳዊ ሕይወት፡-

የግል መንፈሳዊ ሕይወት ማለት እኛ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት የሚኖረን ሕይወት ነው፡፡ ይህም ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን ግንኙነት ይመሠረታል፡፡ አንድ ሰው ፍቅሩ እግዚአብሔር ከሆነ ምግባሩ መንፈሳዊ ሕይወቱ ይህንኑ የሚገልጥ ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረው ሕይወት የጠበቀ ለማድረግ ከሚያስፈልጉት ነገሮች ውስጥ ቃለ እግዚአብሔር፣ ንስሓ፣ ቅዱስ ቁርባን፣ ጸሎት ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡

 

ቃለ እግዚአብሔር ለአንድ ክርስቲያን የሕይወት መስመሩን የሚያቃናለት ነው፡፡ “ቃልህ ተገኝቷል እኔም በልቸዋለሁ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ በስምህ ተጠርቼአለሁና ቃልህ ሐሴትና የልብ ደስታ ሆነኝ፡፡” ኤር.15፥16

 

ንስሓ ማለት መጸጸት ማለት ነው፡፡ የክርስትና ሕይወት የንስሓ ሕይወት ነው፡፡ በንስሓ የበደለ ከበደሉ ይነዳል፡፡ ኀጢአተኛውም ጻድቅ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ለግል መንፈሳዊ ሕይወት ሥራችሁን አቅኑ፡፡” ኤር.18፥11 ከንስሐ በኋላ ቅዱስ ቊርባን መቀበል ያስፈልጋል፡፡ “የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ ሕይወት የላችሁም፡፡” ዮሐ.6፥53

 

እንግዲህ ቃሉን ሰምተን ንስሓ ገብተን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ስንቀበል የግል መንፈሳዊ ሕይወታችን የተስተካከለ ይሆናል፡፡ የግል መንፈሳዊ ሕይወት ጽናት ደግሞ ለማኅበራዊ ኑሮአችን ወሳኝ ነውና፡፡ “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አሳብ ይህንም አዘውትር፡፡ ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፡፡ በእነዚህ ጽና ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ፡፡” 1ጢሞ.4፥15

 

ለ. ማኅበራዊ ኑሮአችን

ክርስቲያን በማኅበራዊ ኑሮው ከሌሎች ጋር በሠላምና በፍቅር ሊኖር እንዲሁም አልጫውን ዓለም በምግባሩ ሊያጣፍጥ ይገባል፡፡ በመሆኑም ክርስቲያን በማኅበራዊ ኑሮ ተሳትፎ ውስጥ ሊይዝ  የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም፡-

 

ዓላማ፡- ክርስቲያን እንደ ውኃ ላይ ኩበት እየተንሳፈፈ ወንዙ ወደ ሚወርድበት አቅጣጫ አይጓዝም፡፡ እንደሚወዛወዝ ዛፍም ወደ ነፈሰበት አያጋድልም፡፡ የራሱ የሆነ ውሳጣዊ ዓላማና አቋም አለው፡፡ “በምትሄድበት ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፡፡” ኢያሱ.1፥7 ከዚህ የተነሣ የሚሠራውን በጽናትና በትጋት ይሠራል፡፡ የጀመረውን ከፍጻሜ ያደርሳል፡፡ በመከራ አይናወጥም፡፡ መስሎ ለማደር እንደ ጊዜው አይለወጥም፡፡ በዓላማ ስለሚጓዝ ዓላማውን ያሳካል፡፡

 

ክርስቲያን ምን ዓይነት ዓላማ ሊኖሩት ያስፈልጋል?

መንግሥተ ሰማያትን መውረስ፡- አንድ ክርስቲያን ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጣው ለጊዜያዊ ችግሩ ብቻ መፍትሔ ለማግኘት አስቦ ሳይሆን ሰማያዊ ክብርና ዋጋ ለማግኘት ነው፡፡ “ድንኳን የሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለን፡፡ 2ቆሮ.5፥1

 

የሚታወቅና ግልጽ ዓላማ፡- ክርስቲያን ያለ ዓላማ በጭፍን አይጓዝም፡፡ ሳይታሰብ በድንገት በአጋጣሚ የሚል ነገር በርሱ ዘንድ እምብዛም ቦታ አይኖረውም፡፡ የሚታወቅ ግልጽ ዓላማ ኖሮት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሳካለት ይጸልያል፡፡ “ሳታቋርጡ ጸልዩ፡፡” 1ተሰ.5፥18 ከዚህ አንጻር አንዱን ዓላማው አድርጎ ይጓዛል ጋብቻ ወይም ምንኩስና መካከል ሆኖ አያወላውልም፡፡

 

ራስን መግለጽ፡- ክርስቲያን በሄደበት ሁሉ ማንነቱን መግለጥ አለበት፡፡ በተራራ ላይ ያለች ከተማ መሰወር አትችልም፡፡ ይህም ሲባል እኔ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያን ነኝ እያለ በማወጅ ወይም በማስታወቂያ ሳይሆን አኗኗሩ ማንነቱን ይገልጠዋል፡፡ ይህም ኑሮው በቤተሰብ፣ በት/ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በአካባቢው ኅብረተሰብ ዘንድ ወዘተ…… መገለጥ አለበት፡፡

 

ታማኝነት፡- እውነተኛ ክርስቲያን ምሎ የማይከዳ፣ አደራ የማያጠፋ፣ የማያወላውል ለምስክርነት የሚበቃ ነው፡፡ ታማኝ ሰው መልካም የሚለውን ይናገራል፡፡ የሚናገረውን ይሠራል በሓላፊነት ቢቀመጥ ያለ አድልዎ ወገናዊነት ያስተዳድራል፡፡ “በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሀለሁ፡፡” ማቴ.25፥21 ይባልለታል፡፡ ታማኝነት ለራስ ታማኝ መሆን ለእግዚአብሔር ሰዎች በመታመን ይገለጣል፡፡ ይህም በትዳር፣ በሥራ፣ በተሰጠው ሓላፊነት መታመን አለበት፡፡ ምሳሌ ዮሴፍ ዘፍ.39፥9

 

ፍቅር፡- ክርስቲያናዊ ፍቅር የያዘ ሰው በሰውና በእግዚአብሔር ፍቅር ያለነቀፋ ይኖራል፡፡ ፍቅር የክርስቲያንነታችን መገለጫ ነው፡፡ አምላክን ከዙፋኑ ያወረደው ራሱንም እስከ ሞት አሳልፎ ለሰው ልጅ እንዲሰጥ ያደረገው ፍቅር ነው፡፡ ስለዚህ አንደ ሰው ፍቅር ከሌለው ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የለውም ማለት ይቻላል፡፡ የምናፈቅረው ማንን ነው?

 

እግዚአብሔርን፡- እግዚአብሔርን ማፍቀር ሲባል እግዚአብሔርንና የእርሱ የሆነውን ሁሉ ማፍቀር ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ፍቅረ እግዚአብሔርን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡

 

  1. ትእዛዙን ማክበር፡- እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን በመፈጸም ይገለጣል፡፡ “ትእዛዙ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፡፡” ዮሐ.14፥21

  2. የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ መውደድ ይህን በሦስት ከፍለን መመልከት እንችላለን

2.1.    ቅዱሳንን መውደድና ማክበር፡- ቅዱሳን እግዚአብሔር የመረጣቸው ያከበራቸውና የወደዳቸው ናቸው፡፡ “የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኗልና አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው የጠራቸው እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው ያጸደቃቸው እነዚህን ደግሞ አከበራቸው፡፡” ሮሜ.8፥29 ፍቅረ እግዚአብሔር የእርሱ የሆኑ ቅዱሳንን በማክበር እንገልጻለን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የትሕትናና የኦርቶዶክሳዊነት ውጤት ነው፡፡

2.2.   ሀገርን መውደድ፡- ሀገር የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን እግዚአብሔር በሰጠው ሀገር ሆኖ እርሱን ሊያመሰግን ሀገሩን ሊወድ ግዴታ አለበት፡፡ ሀገር ከሌለ ሠላም ካልሆነ እግዚአብሔርን በደስታ ማመስገን አይቻልምና፡፡ “ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ባላስብሽ ምላሴ በጉሮሮዬ ይጣበቅ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድ፡፡” መዝ.136፥5

2.3.   ቤተሰብን መውደድ፡- ክርስቲያን እምነትን፣ ምግባርን፣ ሥርዓትን በመጀመሪያ የሚማረው ከቤተሰቡ ነው፡፡ ቤተሰብ የመጀመሪያዎቹ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ነቢዩ ሙሴ የእግዚአብሔርን፣ የወገንን፣ የሀገርን ፍቅር የተማረው ከእናቱ ነውና፡፡ ወልደው፣ አሳድገው፣ አስተምረው ለትልቅ ደረጃ ያበቁትን ቤተሰቡን ክርስቲያን ሊወድ ይገባዋል፡፡ “ስለ ቤተሰቦቹ የማያስብ ማንም ቢኖር ሃይማኖትን የካደ ከማያምን ሰው ይልቅ የከፋ ነው፡፡” 1ጢሞ.5፥8

3.   የሰው ልጆችን ሁሉ ማፍቀር፡- /ፍቅረ ቢጽ/ የሰውን ልጅ ሁሉ ማፍቀሩ ፍቅረ ቢጽ ይባላል፡፡ ይህም በሥላሴ አርአያ የተፈጠረውን ሰው ሁሉ መውደድና ማፍቀር ነው፡፡ ይህም ኀጥእ ጻድቅ፣ አማኒ መናፍቅ፣ ዘመድ ባዕድ ሳይሉና ሳይለዩ ሁሉን አስተካክሎ መውደድ ነው፡፡ ይህም ትእዛዝ ጠላትን እስከመውደድ በመድረስ ነው፡፡ “በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚረግሟችሁን መርቁ፣ ለሚጠሏችሁ መልካም አድርጉ ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ፡፡” ማቴ.5፥44

 

በአጠቃላይ ክርስቲያን ከአለባበሱ ጀምሮ ውጫዊ አቋሙም ሆነ አጠቃላይ ሕይወቱ በማናቸውም ጊዜና ቦታ ሁሉ ክርስቲያንነቱን ሊገልጡ ይገባቸዋል፡፡ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ኖረው ለሰውም ብርሃን ሆኖ እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር የሆኑትን አስደሰተ የሚባለው ያን ጊዜ ነው፡፡ እንግዲህ ክርስቲያን በምድር ሲኖር በግል ሕይወቱም ሆነ በማኅበራዊ ኑሮው ምን መምሰል እንዳለበት ራሱን ከላይ በተገለጸው በሦስቱ ሕግጋት አንጻር እየመረመረ መጓዝ አለበት፡፡ በግል ሕይወቱ ዘወትር ንስሓ እየገባ ቅዱስ ቁርባን በመቀበል እየጾመ፣ እየጸለየ፣ እየመጸወተ ሰማያዊ መንግሥትን ተስፋ በማድረግ ይጓዛል፡፡ በማኅበራዊ ኑሮውም ደግሞ ሰዎችን በሐዘናቸው ጊዜ ማጽናናት፣ በደስታቸው ተካፋይ መሆን፣ ከቸገራቸው ለችግራቸው ደራሽ በመሆን እውነተኛ ፍቅሩን ሊገልጽ ያስፈልጋል፡፡ “የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁል ጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን፡፡” 2ቆሮ.4፥10

abune paulos

“የኢትዮጵያ መምህሯ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡”

ብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳ ዘአክሱም፣ ወእጨጌ ዘመንበረabune paulos ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንት ለ ሐመር መጽሔት ዝግጅት ክፍል በ1991 ዓ.ም ስለ

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አገልግሎት
  • ንዋያተ ቅዱሳት አጠባበቅ
  • ዘመናዊ የቤተ ክርስቲያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት
  • ገጠሪቱ ቤተክርስቲያ (አብነት ት/ቤቶችና ገዳማት )
  • ቤተክርስቲያን ለጥቁር አፍሪካውያን ለመድረስ ያላትን ዝግጁነትና አለማቅፋዊ አገልግሎት
  • የወጣቶች አገልግሎትና የሰንበት ት/ቤት መርሐግብር
  • የግል ሕይወታቸውና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የሰጡትን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አስተናግደነዋል። እዚህ በመጫን ያንብቡ

የመንፈስ ልዕልና

በዲ/ን አሻግሬ አምጤ
ግንቦት 2፣2003ዓ.ም

ልዕልና ከተለመደ ነገር ላቅ ማለትን፣ ሰው ሊሠራው ከሚችለው በላይ መስራትን ያመለክታል፡፡ በአስተሳሰብ ምጥቀት፣ በሚፈጸም ጀብዱ ይገለጻል፡፡ ጥብዓት፣ በመንፈሳዊ ቆራጥነት፣ ወኔ፣ በተፋፋመ አካላዊ  ሆነ መንፈሳዊ ጦርነት ለመግባት መጨከን የልዕልና መገለጫዎች ናቸው፡፡ “በሞት ጥላ መካከል እንኳን ባልፍ ክፉን አልፈራም አንተ ከእኔ ጋር ነህና” እንዳለ መዝሙረኛው፡፡

 

ልዕልና ያለፈውን እየረሱ ወደፊት ሊደርሱበት የሚሹትን ለመናፈቅ ይዳርጋል፡፡ በፈተና ተወልውሎ እንደ ወርቅ ጠርቶ ይገኛል፡፡ ለእኔ ብኲርናዬ ምኔ ናት በማለት የተናገረው ብኲርና ልዕልና መሆኗን ባለመረዳቱ ነው፡፡

ሥጋዊ ፈቃድ የጠየቀውን ሁሉ አለመተግበር፣ በስሜት የተፈጠረን ሁሉ ለማስተናገድ አለመሞከር በተቃራኒው መንፈስ በሥጋ ላይ ማሰልጠን ወይም ሥጋን ለመንፈስ ማስገዛት የልዕልና ተግባር ነው፡፡ የሰሙትን ምሥጢር መጠበቅ፣ የተቀበሉትን አደራ መወጣትም እንዲሁ ቃልን መጠበቅ፣ ታምኖ መሰማራት፣ አደራን መመለስ ለሁሉ አይቻለውም፡፡ ልዕልና በፈተና መጽናትን፣ እንደወርቅ መቅለጥን፣ ሌላው እየበላ ጦም ማደርን፣ ሌላው እየዘነጠ በድህነት መማቀቅን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የሚያልፈውን በማያልፈው አሸንፈው፣ ጊዜያዊውን በዘለዓለማዊው ተቆጣጥረው የተጋረጠባቸውን ያሸንፉታል ለልዕልና የታጩቱ፡፡

ሰው ለልዕልና የሚታጨው የፈተናን የክብር ምንጭነት አምኖ ሲቀበል ነው፡፡ አደራ ለመቀበል መብቃት፣ አደራም ለመስጠት ሰውን ማመን ልዕልና አይደለም ትላላችሁ? “መተማመን ከሌለ አደራ ሰጪም አደራ ተቀባይም አይኖርም” እንዲሉ አበው፡፡ ይህ ብቻም አይደል “አደራ ጥብቅ ሰማይ ሩቅ” በማለት ታምኖ መገኘትና አደራን መወጣትን ከሰማይ ርቀት ጋር ያነጻጽሩታል፡፡ እኒህ የተጠቀሱት የልዕልናና የአደራ ጥብቅነት ማሳያዎች ምግባርን ከሃይማኖት አዋሕደው፣ ፍቅረ እግዚአብሔርንና አክብሮተ ሰብእን አጣምረው እንዲኖሩ ኅሊናን ገርተው፣ ጊዜያዊ የሥጋ ፍላጎትን ተቆጣጥረው ይኖራሉ፡፡

 

አደራን ለተወጣ ማኅበረሰቡ የሚያቀርብለት ሙገሳ፣ ውዳሴ፣ ሞራላዊ ሽልማት ለልዕልና ያበቃል፡፡ ሌሎች አደራውን ተወጥቶ ክብር የተቸረው ከደረሰበት ለመድረስ አርአያነቱን ይከተላሉ፡፡ እውነትን ከሐሰት የማያቀላቅል፣ የገባውን ቃል የማይከዳ ይከበራል፡፡ እንዲፈራ የሚያደርገው የመንፈስ ልዕልናው ነው፡፡

 

አደራ የመተማመን፣ የጽኑ ፍቅር ውጤት በመሆኑ አደራ የሚሰጠው ለሚታመን ሰው ነው፡፡ በመተማመን የሚተገበረው አደራ የማያልፍ ዘለዓለማዊ ክብር ያጎናጽፋል፡፡

 

ክብሩ ምድራዊም ሰማያዊም ሊሆን ይችላል፡፡ “የምትጸድቅን ነፍስ ጎረቤት ያውቃታል” የሚለው ብሂል ለዚህ ትንታኔ ድጋፍ ይሆናል፡፡ አደራን ሳይወጡ ከመቅረት ይልቅ ሞትን መምረጥና ክብርን ተክሎ ማለፍ መብለጡን ሐዲስ ዓለማየሁ በማይጨው ጦርነት ጊዜ ተመልክተውት በኅሊናቸው ታትሞ የቀረን ክስተት እንዲህ ይተርኩታል፡፡

 

“ጌትየው በጽኑ ቆስለው በጣዕር ውስጥ እንዳሉ እሷ ስታስታምማቸው እንደማይተርፉ ተረድተውት ኖሮ አንቺና ተስፋው ከሞት ተርፋችሁ ሀገራችሁ ለመግባት የበቃችሁ እንደሆነ መሳሪያዬንና አባቴ ሲሞቱ ለመታሰቢያቸው የሰጡኝን ዳዊቴን ለልጄ ለንጋቱ እንድታደርሱልኝ አደራ፡፡ እንግዲህ ያች ሰው ሁሉ ነፍሷን እንድታተርፍ ያን ያህል ሲማጠናት ዐይኗ ዕያየ በቦንብ ተቃጥላ የሞተች የወዳጇን የአደራ ኑዛዜ ለመፈጸም ኖሯል፤ ምን አይነት እስከ ሞት የሚያደርስ ታማኝነት ነው ምን አይነት ሀያል ፍቅር ቢሆን ነው? ለሃይማኖቷ ብላ፣ እንዲያ ተቃጥላ ሞተች፡፡” አለ ሰውየው፡፡ /ሐዲስ፣ 1985፣86ዓ.ም/


በዚያ ፍጥረተ ዓለም በፍርሃት በሚናጥበት፣ ሳር ቅጠሉ፣ ሰው አራዊቱ በሚያረግድበት ሰዓት አደራ መስጠትም ሆነ መቀበል አስቸጋሪ ነበር፡፡ ልጄ ሆይ ሰው ሁን ያለው እንዲህ ላለው ሰዓት ይሆን እንዴ? አደራ ሰጭው የሴትየዋን ፍቅርና ታማኝነት መዝነውታል፡፡ አደራ የተሰጣቸው ሁለት ነገሮች ጠመንጃና ዳዊት ናቸው፡፡ ሁለቱም ከጠላት መጠበቂያ ናቸው፡፡ አንዱ አፍአዊ ሌላው መንፈሳዊ ጠላትን ለመውጋት ያገለግላሉ፡፡ አንደኛው ባህር ተሻግሮ የመጣን ጠላት ለመቆጣጠር፣ ሌላኛው ከርስት መንግሥተ ሰማያት ከሚነጥል ጠላት ጋር ለመዋጋት ጋሻ ጦር የሚሆን ነው፡፡

 

ሴትየዋ በዚያች ቀውጢ ሰዓት የተሰጣትን አደራ ለመፈጸም ተነስታለች፡፡ ታማኝነት፣ አደራና ታላቅ ፍቅር በአንድ በኩል ሞት በሌላ በኩል ትይዩ ሆነው ቀርበዋል፡፡ ሞትን ፈርተው ማፈግፈግ ታማኝነትን ያፈርሳል፣ ታላቅ ፍቅርን ያቀዘቅዛል፣ አደራ በላም ያደርጋል፡፡ ከሁለቱ መምረጥ ስለነበረበት ሞትን ተጋፍጦ ታማኝነትን ማስመስከር ደምቆ ታያት፡፡ ቃልን አጥሮ፣ አደራን በልቶ በቁም ከመሞት ሥጋዊ ዕረፍትን ተቀብሎ ስምን ከመቃብር በላይ ማዋልን መረጠች፡፡ ሞትን ተገዳድረው የወጡት ታማኝነት፣ ሀያል ፍቅርና አደራ የሃይማኖትና የማተብ መገለጫዎች ሆኑ የሴቷ የፍቅር መስዋዕትነት ሀያል ፍቅር እኮ ሞኝም እብድም፣ ሃይማኖተኛም ሁሉንም ያደርጋል ተባለበት፡፡ በምድራዊ አደራ ብላ የፈጸመችው የሃይማኖትና የማኅተብ መገለጫ ሆነ፡፡ ሴትየዋ በዚህ ሰማዕትነቷ ከጊዜያዊ የጭን ገረድነት ወደ ዘለዓለማዊ የፍቅር ተምሳሌትነት ተቀየረች፡፡ ያለውን የሰጠ ይመሰገናል፤ ራሱን የሰጠ ደግሞ ተከብሮ ይኖራልና፡፡ የተሰጣትን አደራ ለመወጣት ያንን መስዋዕትነት ባትከፍል በደራሲው ምናብ ገድሏ ታትሞ ባልቀረ ነበር፡፡

 

የአደራን ጥብቅነት በተመለከተ ሁለት ነጥቦችን በመጨመር ሀሳቤን ላጠቃልል፡፡ ከዛሬ ዐስራ ዐራት ዓመት በፊት በአንድ ወረዳ ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ መምህር ሆኜ ሥሠራ በአደራ ጠባቂነታቸው ሀገር ስለ መሰከረላቸው የትምህርት ቤት ጥበቃ ባልደረባዬ አጫውቶኛል፡፡ እኒህ ሰው የሰው ገንዘብ እንደማይነኩና አደራ እንደሚጠብቁ የሚያውቅ አንድ መምህር ከቦታው ሲቀየር የተረፈችውን ዐራት ቁና ገብስ የሚያደርስበት ያጣል፡፡ ለሌላ እንዳይሰጠው ከማን ለማን ያደላል፡፡ ይዞት እንዳይሄድ የዐስራ ሁለት ሰዓት የእግር መንገድ ከሌላው ጓዙ በተጨማሪ ዐራት ቁና ገብስ መያዝ ሊጠበቅበት ነው፡፡ አማራጭ ሲያጣ የሰው ገንዘብ እንደማይነኩ ለሚታወቁት የጥበቃ ሠራተኛ አደራ ብሎ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህን ያደረገው ስቀር ይጠቀሙበታል ብሎ በማሰብ ነው፡፡ ታሪኩን የነገረኝ ባልደረባዬ ተመድቦ ይሄዳል፡፡ አንድ ቀን ለዝክር ቤታቸው ሄዶ ጠላ እየጠጡ ሲጫወቱ ተንጠልጥሎ ጠቀርሻ የጠጣ ነገር ይመለከትና ምንነቱን ይጠይቃቸዋል፡፡ ምን እባክህ ያ እገሌ የሚባል ሰው አደራ አስቀምጦብኝ ይኸው ተንጠልጥሎ ቀረ ይሉታል፡፡ ባልንጀራዬም በዚህ ዘመን እንዲህ ያለ ሰው በማየቱ ተገርሞ በዓመቱ እኔ ካለሁበት ትምህርት ቤት ተቀይሮ ሲመጣ አጫውቶኛል፡፡

 

ቃሌን አጥፌና አደራዬን በልቼ ከችግሬ ላልወጣ ለምን ከፈጣሪዬ እጣላለሁ በማለት ይመስለኛል የሰውየው ጥንቃቄና ታማኝነት ስንቶቻችን ለማይሞላ ሆድ፣ ለማይረካ ፍላጎት ያውም ለነገ ለማይተርፍ ነገር አደራችንን በልተን ከፈጣሪ የተጣላን፤ ሰውም የታዘበን፡፡ 60 ዓመት በፈጣሪያቸው ረድኤት የኖሩ አባት በአንድ እለት ለምሳ ቋጥሯት የነበረችውን አገልግል የዛሬን ይብሉልኝ ብሎ በለመናቸው ጊዜ ዛሬ ያንተን አገኘሁ ብዬ በልቼ 60 ዓመት ከመገበኝ ፈጣሪዬ ልለይ እንዳሉት አባት ማለት ነው፡፡ ላይሞላ፣ ቀዳዳ ላይደፈን፣  ችግር ከልኩ ላያልፍ፣ አምላክ ያለው ላይቀር፣ እኛም ከተፈቀደልን ደረጃ ከፍ ላንል ስንቱን አደራ ኑሮ በላነው?

 

የጽሑፌ ማጠቃለያ የአለቃ ለማ ኃይሉ እና የአለቃ ተጠምቀ ታሪክ ነው፡፡ በትምህርት የኖሩት ሊቁ አለቃ ለማ ዋድላ ድላንታ ቅኔ ሲማሩ ኖረው ዐባይን ተሻግረው በዘመኑ የቅኔና የመጻሕፍት ማስመስከሪያ ከነበሩት መጀመሪያ ሞጣ ጊዮርጊስ ቀጥሎም ዲማ ጊዮርጊስ ይመጣሉ፡፡ ዲማ ጊዮርጊስም ከአለቃ ተጠምቀ ጋር ይገናኛሉ፡፡ አለቃ ተጠምቀ ዐይነስውር ናቸው፡፡ ብሉይ ኪዳንን ከነ አለቃ ለምለም በ6 ወር የወጡ ተጠምቀና ደቀመዝሙሩ አለቃ ለማ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ይነሳሉ፡፡ ዘመኑ በኢትዮጵያ ታሪክ ክፉ ቀን የተባለው፣ ሰውም ከብቱም ያለቀበት እናት የልጇን ሥጋ ሳይቀር የበላችበት አስቸጋሪ ዘመን ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ከዲማ መምህራቸውን እየመሩ ደብረ ሊባኖስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ከዚያም አንኮበር መጨረሻም አዲስ አበባ መካነ ሥላሴ በማለት አብረዋቸው ኖረዋል፡፡ በወቅቱ ርሃቡ ከመጽናቱ የተነሣ የሚበላ ጠፍቶ በሦስት ቀንም፣ በአራት ቀንም የሚቀመስ ሲገኝ አብረው እየቀመሱ ምግባቸውን ቃለ እግዚአብሔር አድርገው ክፉውን ቀን አሳልፈዋል፡፡ በጊዜው ወጣት የነበሩት አለቃ ለማ በልቼ ወደ ማድርበት ልሂድ ሳይሉ ከመምህራቸው ጋር ተናንቀው ቀኗን አሳለፏት፡፡ በሚያልፍ ቀን፣ በሚያልፍ ችግር የቀለም አባታቸውን አልለወጧቸውም፡፡ እንዲያውም ለዚህ ደረጃ ያደረሰኝ ከእሳቸው ያገኘሁት በረከት ነው ይላሉ፡፡ ይህን የመንፈስ ልዕልና የሚያገኙና ሲያገኙትም የበረከት ምንጭነቱን ተረድተው የሚገጥማቸውን ጊዜያዊ ፈተና የሚወጡ ምንኛ የተባረኩ ናቸው!

/ምንጭ፡-

  • ሐዲስ ዓለማየሁ ትዝታ፣ 1985ዓ.ም፣ ሜጋ አሳታሚ ድርጅት፣
  • መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ 1959ዓ.ም፣
  • ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ፣ ከበረሃውያን ሕይወትና አንደበት ጥር 2003ዓ.ም፣
  • ባሕሩ ዘውዴ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ አ.አ.ዩኒቨርሲቲ 1989ዓ.ም፡፡/

“አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ለእናንተ አድርጉ” /ሕዝ 18፥31/

በማሞ አየነው

የሰው ልጅ ለሥጋዊና መንፈሳዊ እንቅስቃሴው አመች በሆነ መልኩ እግዚአብሔር ለሚያፈራርቃቸው ዘመናት ቀመር ሲያወጣ ኖሯል፡፡ ጊዜያትንም ከደቂቃ ሽራፊ እስከ ሺህ ዘመናት ድረስ ከፋፍሎ ይጠቀማል፡፡ በዚህ የጊዜ ቀመርም ትናንትን ያስረጃል፤ ዛሬን ደግሞ አዲስ ያደርጋል፡፡ በጊዜ ዑደትም ብዙ ሺህ አዲስ ዓመታት አልፈው ብዙ ሺህ አዲስ ዓመታት መጥተዋል፡፡ የዘመናት መፈራረቅ ሰው የእግዚአብሔርን ሥራ እንዲያደንቅ፣ መግቦቱንም እንዳይረሳ ያደርጋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ቃል ኪዳኑን እንዳልረሳ፣ ፍጥረቱን እንዳልዘነጋ ያመለክታል፡፡

 

 

ቅዱስ ዳዊት «የሰው ሁሉ ዓይን  አንተን ተስፋ ያደርጋል፡፡ ምግባቸውንም በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ» እንዳለ፣ወራትን እያፈራረቀ፣ በዝናብ እያበቀለ፣በፀሐይ እያበሰለ ለፍጥረታት ምግባቸውን ይሰጣል።/መዝ 144፥15/ እግዚአብሔር አምላክ ዓመታት አያረጁበትም፣ አይለወጡበትም «አንተ ግን ያው አንተ ነህ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም» እንዲል /መዝ 101፥27/፡፡ ስለዚህም ዓመታት የሚቀያየሩት የሚያልቁትና የሚጀምሩትም ለሰው ልጆች ብቻ ነው፡፡ አዲስ ዓመት የክረምትን መውጣትና የመከርን መድረስ የዝናሙን ማለፍ ተከትሎ የሚከበር የአዲስ ተስፋ እና ብስራት በዓል ነው፡፡ ይህን አስመልክቶ ጠቢቡ ሰሎሞን እንዲህ ብሏል፡፡ «እነሆ ክረምት አለፈ ዝናቡም አልፎ ሄደ፡፡ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፣ የዜማም ጊዜ ደረሰ፣ የቁርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፣ በለሱ ጎመራ ወይኖችም አበቡ፣ መዐዛቸውንም ሰጡ» /መኃ 2፥11/፡፡ በአዲስ ዓመት ዓመታት ብቻ ሳይሆኑ ምድርም ገጽታዋን ትለውጣለች፡፡ የደረቁ ዛፎችና የደረቀችው መሬት አረንጓዴ ይለብሳሉ፤  አዝርእትና እፅዋት በአበባ ለዘር ለፍሬ ይደርሳሉ፡፡ ይህም በዓሉን እጅግ ደማቅና ተወዳጅ ያደርገዋል፡፡ መግቦቱን እንድናከብር እና ቃል ኪዳኑንም እንዳንረሳ እግዚአብሔር አምላክ አዝዞናልና፡፡

ስለዚህም ነው ቅድስት ቤተክርስቲያን በዓሉን በድምቀት የምታከብረው ምዕመናንንም እንዲያከብሩት የምታስተምረው፡፡ ነገር ግን አሁን አሁን እየታየ ባለው የአከባበር ሁኔታ የበዓሉን መንፈስ ፍፁም ሥጋዊ እንዲሆን ግብረ እግዚአብሔርን ፤ መግቦተ እግዚአብሔርን ከማሰብ ይልቅ የሥጋን ነገር ብቻ እያሰብን እንድናከብር የሚያስገድዱ ነገሮች ይስተዋላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አዲስ ዓመትን እንዴት ማክበር እንዳለብን የሚነገረን ነገር አለ፡፡ በክርስትና መስመር ያለ ሰው እነዚህን ጠቃሚ ነጥቦች በማየት ራሱን እንዴት ማስተካከል እንዳለበት፣ አዲሱን ዓመት እንዴት መቀበል እንዳለበት ይገልጻል፡፡ መጽሐፍ ከሚያስተምረን ብዙ ቁም ነገሮች የተወሰኑትን እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

 

1.“አዲሱን ሰው ልበሱ” /ኤፌ 4 ፥22/


የዓመታት መቀያየር በእኛ ክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ ለውጥ ካላመጣ በድሮው አሮጌ ሰውነታችን አዲሱን ዓመት ከተቀበልን ዛሬ ከትናንት በምን ይሻላል? ድሮ የነበሩንን የኃጢአት ልምዶች ዛሬ ማስወገድ ካልቻልን አዲስ ዓመት መጣ ማለት ረቡ ምንድን ነው? አዲስ ዓመት ሲመጣ በአእምሯችን ልናመላልሰው የሚገባው ነገር የመንፈሳዊ ሕይወታችን መለወጥ መሻሻልና ማደግ ነው፡፡ እነዚህን ሃሣቦች ተግባራዊ ለማድረግ አሮጌውን እኛነታችንን አውልቀን አዲሱን ሰው መልበስ ያስፈልጋል፡፡ «አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፍፋችሁታልና፤ የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታልና» እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ /ቆላ 3፥10/። አሮጌውን ሰው ከነ አሮጌ ሥራው ስንገፈውና አዲሱን ሰው ስንለብስ ነው ዓመቱን አዲስ የምናደርገው አሮጌው ሰው በምክንያትና በሰበብ አስባቦች የተሞላ ነው፡፡ ጊዜ ለሰጠው አምላክ እንኳን ጊዜ የሚሰጠው በድርድርና በቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ አሮጌው ሰው ስለንስሐ ሲነገረው “ከልጅነቴ ጀምሮ ሕግጋቱን ጠብቄያለሁ” ይላል፡፡ ስለ ሥጋወደሙ በተነገረው ጊዜ “ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው ማን ሊሰማው ይችላል»/ዮሐ 6፥60/ ይላል፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዳይገሰግስ «አባቴ ሞቷል እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ»/ሉቃ 9፥59/ ብሎ ራሱን በምክንያቶች ይከባል፡፡ ይህ ከእግዚአብሔር ጋር ያለያየን አሮጌው ሰውነታችን በአዲስ ሊቀየር ይገባዋል፡፡ አሮጌው ሰውነታችን ነፍሳችን እንድትጠማ ምክንያት ሆኗል፡፡ «እንጨትና ውኃ በሌለበት በምድረ በዳ ነፍሴ አንተን ተጠማች» እንዲል /መዝ 62፥1/ ስለዚህም ነፍሳችን ከጥሟ ትረካ ዘንድ በቃለ እግዚአብሔርም ትረሰርስ ዘንድ አዲሱን ሰው እንልበስ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም «ፊተኛ ኑሯችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ። በአእምሯችሁ መንፈስ ታደሱ፤ ለእውነትም ለሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።» እንዲል /ኤፌ 4፥22-24/፡፡

 

2.“አሮጌው እርሾ አስወግዱ” /1ቆሮ 5፥7/


ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው «ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳዊያን ካልበለጠ ወደ እግዚአብሔር መንግስት አትገቡም።» ብሎ አስተምሮ ነበር፡፡ ከጻፎችና ከፈሪሳዊያን እኩይ ግብር አንዱና ዋነኛው ደግሞ በሁለት ቢላዋ የመብላት ልምዳቸው ነው፡፡ የሙሴን ሕግ እንፈጽማለን እናስፈጽማለን ይላሉ፤ በሌላ በኩል ይሄንኑ ሕግ ራሳቸው ሲጥሱ እንመለከታለን፡፡ ጽድቅና ኃጢአትን በአንድ ሰውነታቸው ሊፈጸሙ የሚሞክሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ጽድቃችን ይህን ከመሰለ ሁኔታ እንዲለይም ጌታችን አስተምሮናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ እንዲህ ይለናል፤ «እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ….። ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም፡፡» /1ቆሮ 5፥7/፡፡ እርሾ ለሊጥ አስፈላጊ የሚሆነው ሊጡን እስከሚያቦካ ድረስ ብቻ፡፡ ሊጡን ካቦካ በኋላ አሮጌው እርሾ ይወገዳል፡፡ ካለያ ሊጡን ሆምጣጣና ጣዕም የለሽ ያደርገዋል፡፡ ሊጡ ቂጣ መሆን የሚችለውም አሮጌው እርሾ ከተወገደ በኋላ ነው፡፡
በክርስትና ሕይወታችንም ጽድቅና ኃጢአት እየተፈራረቁ ሊያስቸግሩን ይችላሉ፡፡ በአዲስ የንስሐ ሕይወት እንኖር ዘንድ ቀድሞ የነበረውና ከጽድቃችን ጋር የተቀላቀለው እኩይ ግብር ሊወገድ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ጽድቃችን ከፈሪሳውያን በምን ተሻለ? በዓልንም በቅንነትና በእውነት ቂጣ የምናከብረው አሮጌውን እርሾ ስናስወግድ ነው፡፡ በቂጣ የተመሰለው ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ለሰው ምግብ መሆን የሚችለው ከአዲሱ ማንነታችን /ከአዲሱ ሊጥ/ ጋር አብሮ የተቀላቀለው አሮጌ እርሾ ማለትም ጽድቅን ከኃጢያት አደባልቆ የሚሄደው ሰውነታችን ይህን ግብሩን እርግፍ አድርጐ መተው አለበት።

 

3.“አዲስ ልብና መንፈስም ለእናንተ አድርጉ” /ሕዝ 18፥31/


በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ትልቁ ፈተና ያለንን ነገር ጠብቆ መቆየት መቻል ነው፡፡ መንፈሳዊ ዝለት የሚፈጠረውም መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችን ተደጋጋሚና ዕድገት የሌለው መሆን ሲጀምር  ነው፡፡ መንፈሳዊ ዕድገት የሚያሳይ ሰው ለመንፈስ ዝለት አይጋለጥም፡፡ በአዲስ ልብና በአዲስ መንፈስ ሕይወቱን የሚመራ ክርስቲያን አይሰለችም፣ ለእሱ ክርስትና ሁሌም አዲስ ነው፤ አንዴ የሚፈጽሙትና የሚጨርሱት ሳይሆን የዕድሜ ልክ ሕይወት ነው፡፡ ስለዚህም ክርስትና በአዲስ ልብና በአዲስ መንፈስ የሚኖር አዲስ ሕይወት፣ የድሮውን እየረሱ ነገን ለመያዝ የሚደረግ የተስፋ ሕይወት ነው፡፡ « ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፏል፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኗል፡፡»  እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ። /2ቆሮ 5፥17/ አዲስ ዓመትንም አዲስ የምናደርገው አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ስንይዝ ብቻ ነው፡፡ የለውጥ መጀመሪያ የልቦና መለወጥ ነውና፡፡ በስሜት የሚመጣ ለውጥ ዘላቂነት የለውም፡፡ ትንሽ ነፋስ ሲነፍስ መወዛወዝ ይጀምራል፡፡ ለዚህም ነው ነብዩ የድሮው እኛነታችንን እንድናስወግድ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም እንዲኖረን የሚመክረን «አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ ስለምን ትሞታላችሁ? የሟቹን ሞት አልፈቅድምና´ /ሕዝ 18፥31/።

 

በአጠቃላይ አዲስ ዓመትን ለአዲስ ክርስቲያናዊ ሕይወት መነሻ አድርገን ብናከብር በዓሉን እውነተኛ የአዲስ ዓመት በዓል ያደርገዋል፡፡ «ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደኛ ቀርቦአል፡፡ እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ» እንዲል ሐዋርያው ያለፉትን የባከኑ ዓመታት ለማስተካከል የብርሃን ጋሻ ጦር በመልበስ የጨለማን ሥራ ማስወገድ አስፈላጊ ነው፡፡/ሮሜ 13፥12-44/ በልብስና በቤት በመኪና ብቻ ሳይሆን በልባችን መታደስ መለወጥ የሚገባን ልዩ ጊዜ ቢኖር ይኼው አዲስ ዓመት ነው።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መንፈሳዊ ተጋድሎ

በዲ/ን አሉላ መብራቱ

1.    መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ምን ማለት ነው?

መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት – አንድ ሰው የሚያምንበትን እምነት፣ የሚመራበትን ሕግ፣ የሚያልመውን ተስፋ እና የሚወደውን ነገር ተከትሎ ከግቡ ለመድረስ ማድረግ ያለበትን በማድረግ÷ ማድረግ የሌለበትን በመተው በነፃ ፈቃዱ ወስኖ፥ በሙሉ ልቡናው፥ በሙሉ ኃይሉ የሚያደርገው የውስጥና የውጭ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ፥ ጥረትና ትግል ነው፡፡
 

ሀ. ከፈቃደ ሥጋ ጋር የሚደረግ ውጊያ ነው፡፡

ሰው በዚህ ዓለም በተሰጠው ዘመኑ ራሱን ለፈጣሪው ለማስገዛት ከራሱ ጋር ብርቱ ተጋድሎ ማድረግ ግድ ይለዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛል፤ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፡፡ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም›› ብሎ የገለጸው ይህንን በሰው ሕይወት ውስጥ ያለውን የማያቋርጥ ጦርነት ነው፡፡ (ገላ 5፥12) ታላቁ አባት ኢዮብም ‹‹በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን ?›› በማለት ሰው ጽኑ ጦርነት የሚካሄድበት የጦር ሜዳ መሆኑን ገልጿአል፡፡ ይህም ጦርነት በተወሰነ ጊዜ ተነሥቶ የሚጠፋ ሳይሆን በሰው ዘመን ሁሉ የሚኖርና የዕድሜ ልክ ትግል ነው፡፡ ይህን የሥጋና የነፍስ ጦርነት በነፍስ አሸናፊነት ማጠናቀቅና ፈቃደ ሥጋን ድል አድርጎ ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ይገባል፡፡

ይህ ሲባል ግን ሥጋ ርኵስ ነው፤ ሥጋ መጥፋትና መወገድ አለበት ማለት አይደለም፡፡ ሥጋ በራሱ ርኵስ አይደለምና፤ ምክንያቱም ሥጋ የተፈጠረው በራሱ በእግዚአብሔር ነው፡፡ አምላካችን ደግሞ ርኵስ ነገር አይፈጥርም፡፡ ሰውን (ሰው የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ውጤት ነው) ከፈጠረ በኋላ ‹‹ያደረገውን ሁሉ አየ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ፡፡›› ተብሏል፡፡ (ዘፍ1፥31) ሥጋ ርኵስ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ወልድ (ቃል) ‹‹ሥጋ ሆነ›› ባልተባለ ነበር፡፡ (ዮሐ 1፥14) አዳምና ሔዋን ከኃጢአት በንጽሕና ይኖሩ ነበር፡፡ ‹‹አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፣ አይተፋፈሩም ነበር›› እንዲል (ዘፍ 2፥25)  ህፃናት፣ ልጆች  ሰውነት አላቸው ነገር ግን የኃጢአት ምኞት የላቸውም፡፡

ስለዚህ ፈቃደ ሥጋን መዋጋት ማለት ሥጋን ማጥፋት ወይም ደግሞ ተፈጥሮአዊና ንጹህ የሆነ የሥጋን ፈቃድ ማስወገድ ማለት ሳይሆን፣ ኃጢአትን በማየት፣ በመስማት፣  በመለማመድ ያደገውን÷ ወደ ኃጢአት ያዘነበለውን ፈቃዳችንን መጐሰም/መግራት ማለት ነው፡፡ ይህ ፈቃድ (ኃጢአት) ሥጋን በመጠቀም ይሠራል÷ ሥጋን ከነፍስ ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

የሰው ሥጋዊ ባሕርዩ ምግብ ሲያጣ ይራባል፣ ይደክማል፣ ሥራ መሥራት ይሳነዋል፡፡ ሲሰጡት ደግሞ ኃጢአትን ተለማምዷልና ሌላ ፈቃድ በማምጣት ጠላት ሆኖ ይፈትነዋል፡፡ ‹‹ያዕቆብ በላ፣ ጠገበ፣ ወፈረ፣ ደነደነ፣ ሰባ፣ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፣ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ፡፡ (ዘዳ 32፥15)

ሰውነት የሚፈልገውን ሁሉ እንደ ልቡ ካገኘና ያለ ገደብ የሚቀለብ ከሆነ ወደ ኃጢአት ለመገስገስ የተዘጋጀ መርከብ ነው፡፡ ሰውነት በተመቸውና ፈቃዱን ለመፈጸም ኃይል ባገኘ ጊዜ ነፍስ እየደከመች ትሄዳለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰውነት ፈጽሞ ከደከመና ከዛለ ሥራ መሥራት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ‹‹ሰውነቴን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ›› እንዳለ፡፡ በአግባቡ ሊያዝና ሊገራ ይገባዋል፡፡ (1ኛ ቆሮ 9፥27) በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ወንድሞች ሆይ ዕዳ አለብን እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ›› እንዳለ ከፈቃደ ሥጋ ጋር በመጋደል ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ይገባናል፡፡

ለ. ከርኵሳን መናፍስት ጋር የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር እንጂ›› እንዳለ መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ሰው ከሰው ጋር በመጣላት የሚያደርገው ትግል ሳይሆን ጥንተ ጠላታችን ከተባለው በእባብ ወይም በዘንዶ ከተመሰለው ዲያብሎስና ከእርሱ ጋር ካሉት ሠራዊቱና መልእክተኞቹ ጋር የሚደረግ ጦርነት ነው፡፡ (ኤፌ 6፥12)

ከአዳምና ከሔዋን ከልጃቸውም ከቃየን ጀምሮ ሰይጣን የሰው ልጆችን ዘወትር ይዋጋል፤ ከዘላለም የሞት ፍርድ ሥር ሊጥል ይሠራል፡፡ በዚህም ውጊያው ከነቢያት ፤ከሐዋርያት ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረባቸው ሰዎች እንኳ ሳይቀር ብዙዎችን ጥሏል፡፡

ዛሬም በገዛ ባሕርያችን የሚገኘውን ፈቃደ ሥጋ በመጠቀም፣ የራሱን በመጨመርና የተለያዩ ፈተናዎችን በማቀናበር ይዋጋናል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና›› በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት፡፡›› እንዳለ ጠላት ዲያብሎስ ክርስቲያኖችን በኃጢአትና ሞት ሊውጥ ዘወትር ይተጋል፡፡ ማንም ሰው ደግሞ ከዚህ ፈተናና ውጊያ ሊያመልጥ አይችልም፤ ስለዚህ ሐዋርያት ‹‹በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት››፣ ‹‹የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ፡፡›› እንዳሉን የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ለብሰን ልንዋጋው ይገባል፡፡ (1ኛ ጴጥ 5፥8-9፣ኤፌ 6፥11)

ሐ. የሚመጣውን ዓለም ደስታ ተስፋ እያደረጉ ብቻ በዚህ ዓለም ሕይወት ከደስታ ውጪ መሆን ማለት አይደለም፡፡

ደስታ በራሷ የቤተ ክርስቲያን መገለጫ የሆነች፤ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የተሰጠች፤ ንጹሕ ፈርጥ ነች፡፡ (ገላ 5፥22)

እውነት ነው፤ በዚህ ዓለም ስንኖር መከራ አለብን፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀሉን ተሸክመን እንድንከተለው አዞናል፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን በዚህ ምድር ላይ እስካለ ድረስ ከጨለማው ዓለም ገዢ ከዲያብሎስና ከሠራዊቱ የሚመጣ ልዩ ልዩ ፈተናና ከሥጋችንም ባሕርይ ከሚገኘው ክፉ ምኞትና ርኵሰት ሥራ እንዲሁም ከሌሎቹ የኃጢአትና የፈተና ዓይነቶች ጋር በማያቋርጥ እልህ አስጨራሽ በሆነ ትግል ውስጥ መኖሩ የግድ ነው፡፡ መከራና ስቃይ፣ ትግልና ጦርነት የሌለበት በዘለዓለማዊ ደስታ ብቻ የሚኖርበት ሕይወት በሚመጣው ዓለም የሚገኝ ነው፡፡

በዚህ ምድር በጉዞ ላይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ጉዞዋን ጨርሳ ድል ከነሱት አባላቷ ጋር አንድ እስክትሆን ድረስ መከራው፣ እንቅፋቱ፣ መሰደዱ፣ መራቡ፣ መጠማቱ የግድ ነው፡፡ ‹‹ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል፡፡›› እንዲል (ሐዋ 14፥22)

ይህ ሲባል ግን በዚህ ዓለም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከደስታ የተራቆቱ ዘወትር በኅዘንና በስቃይ ብቻ የሚኖሩ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ክርስቲያኖች የሚለዩትና ዘወትር ለመለየት ጥረት የሚያደርጉት የውሸት ከሆነው ኃጢአት (ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንአት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ መለየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ ይህንም የሚመስል) ከሚገኘው ደስታ እንጂ ከእውነተኛውና ከሰማያዊው ደስታ አይደለም፡፡

መንፈሳዊ ተጋድሎ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነትና ረድኤት መንፈስ ቅዱስ መሪና አስተማሪ፣ የሚያነቃቃና የሚያጽናና፣ የሚያርምና የሚገሥጽ፣ የሚረዳና የሚያጸና፣ በመሆን ስለ ክርስቶስ በክርስቶስ ጸጋ የሚከናወን በመሆኑ መከራንና ስቃይን በሚያስረሳ እውነተኛ ደስታና ሰላም የተሞላ ሕይወት ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ሲላስ ስለ ክርስቶስ በማስተማራቸው ምክንያት ገዢዎች ልብሳቸውን ገፈው በበትር እንዲመቱ አዘዙ በበትር ከመቷቸውም በኋላ በወኅኒ ቤት ጣሏቸው እነርሱ ግን ከጀርባቸው ደም እየፈሰሰ በመንፈቀ ሌሊት እንኳን እግዚአብሔርን በመዝሙር ያመሰግኑ ነበር፡፡ እውነተኛውና ሰማያዊው ደስታ በልቡናቸው ሞልቶ ነበርና፡፡ (ሐዋ 16፥22-25)

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሐዋርያት እንዲህ ይለናል ‹‹ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፏቸው  በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቷቸው፡፡ እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፡፡››(ሐዋ 5፥40-41)

ቅዱስ ዮሐንስ ካሲያን የተባለው አባት በተጋድሎ በግብጽ በረሃ ውስጥ ይኖሩ ስለነበሩት መነኰሳት ሲናገር ‹‹ እነዚህ ምድራዊ መላእክት ናቸው፤ የግብጽን በረሀዎች በደስታ ወደ ተሞላ መዝሙርና እግዚአብሔርን የማመስገኛ ገነትነት ለውጠዋልና››  ብሏል፡፡

በአጠቃላይ መንፈሳዊ ተጋድሎ ማለት ከተድላ ሥጋ፣ በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ በመሸሽ ሰማያዊና እውነተኘ በሆነ ሰላምና ደስታ ውስጥ መኖር ይህንንም ለማግኘት መጋደል ማለት ነው፡፡

2.    መንፈሳዊ ተጋድሎ ዓላማው ምንድነው?

ሀ. የድል አክሊል (የዘለዓለም ሕይወት) ለመቀበል

እግዚአብሔር አምላካችን ሰዎች ነፃ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው ከአምላካቸው ጋር መኖር ከመረጡ ሊሰጣቸው ያዘጋጀው ከመነገርና ከመታሰብ በላይ የሆነ የዘለዓለም  ሕይወት አለ፡፡ የሰው ልጅ ሕሊናዊ ነፃ ፈቃዱ ደግሞ ከአዳምና ከሔዋን ውድቀት በኋላ በየጊዜው እየደከመና ወደ ኃጢአት እያዘነበለ መጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ዘንድ ከብሮ ባየ ጊዜ ከአባቶቻችን ጀምሮ ዘወትር የሚቀና ክፉ ጠላትም (ዲያብሎስ) አለን፤ ባገኘው አጋጣሚ ስንፍናችንንና ድካማችንን እየተከተለ እነዚህንም በመጠቀም ዘወትር ከአምላካችን ሊለየን እንደሚተጋም ከላይ ተመልክተናል፡፡

ሽልማት፣ አክሊል የሚሰጠው ደግሞ ማሸነፍ ለሚችል ጎበዝ ሰው ነው፡፡ ሰነፍና ቸልተኛ ሰው ግን ሊሸለም አይገባውም አንድ ሰው ጎበዝ ወይም ሰነፍ መሆኑ የሚታወቀው ደግሞ በፊቱ ያጋጠመውን ውድድር ወይም ፈተናና መከራ ማሸነፍና ማለፍ ሲችል ብቻ ነው፡፡

ስለዚህ የመንፈሳዊ ተጋድሎ ዓላማ በገዛ ባሕርያችን ያለን መጥፎ የኃጢአት ዝንባሌና ጠላታችን ዲያብሎስ የሚያመጣብንን ፈተናና ሽንገላ ከእግዚአብሔር ርዳታና ቸርነት ጋር ሕሊናን በማንቃት፣ ራስን በመግዛትና ጠንክሮ በመጋደል አምላካችን ያዘጋጀልንን የድል አክሊል የዘላለም ሕይወትን መቀበል ነው፡፡ ‹‹ የተጠራህለትን የዘለዓለም ሕይወት ትቀበል ዘንድ መልካሙን የሃይማኖት ገድል ተጋደል›› አንዲል (1ኛ ጢሞ 6፥12) ሐዋርያቅ ቅዱስ ጳውሎስ ብዙ መከራዎችን አልፎ ገድሉን በድል አድራጊነት ሲፈጽም ‹‹ መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖቴንም ጠብቄያለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱ ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡›› ብሏል ( 2ኛ ጢሞ 4፥7-8)

ለ. ለመንፈሳዊ እድገት

ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ለፍሬ የሚበቃው የድል አክሊልን መቀዳጀት የምንችለው የማያቋርጥ (የማይቆም) መንፈሳዊ ዕድገት ሲኖረን ነው፡፡ በጥምቀት ያገኘነው አዲሱ ሕይወታችን ዘወትር ማደግ ይኖርበታል፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን በዛፍ ተክል ይመሰላል፡፡ ከችግኝ ማፍላት ጀምሮ ፍሬ እስከሚያፈራለት ጊዜ ድረስ ያለው ድካም ቀላል አይደለም፡፡ የዛፉ ችግኝ እንዲያበቅል፣ እንዲለመልም፣ አንዲያብብና እንዲያፈራ አትክልተኛው ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፤ በየጊዜው ውሃ ማጠጣት፣ ማረምና መኰትኰት፣ ፀረ ዕፅዋትና ፀረ ሕይወት የሆኑ በሽታዎችን መከላከል ያስፈልጋል፡፡ እንደዚሁ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን አድጎ ለፍሬ እስኪበቃ ድረስ ዕለተ ዕለት ጠንክረን በትዕግሥት መሥራት በመንፈሳዊ ተጋድሎ መጽናት ይገባል፡፡ የመንፈሳዊ ተጋድሎም ዓላማው መንፈሳዊ ሕይወታችንን የሚያቀጭጩ  ከጸጋ እግዚአብሔርም የሚያራቁቱ ኃጢአትና የዲያብሎስ ፈተናን በመቃወም መንፈሳዊ ምግቦችንም በመመገብ አዲሱ ሕይወታችንን ማሳደግ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

‹‹በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡›› ፊልጵስዩስ 2፡6

                                                   በማሞ አየነው
 
እነሆ የጨለማው ዘመን አለፈ፡፡ በጨለማ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦችም ብርሃን አዩ፡፡ መላእክትና ኖሎት /እረኞች/ በአንድነት እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ እርቅ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ተደረገ፡፡ የሰው ምኞትም ተፈፀመ፡፡ ሰላም፣ ፍቅር፣ ተስፋ በምድር ሰፈነ፡፡ እነዚህ ሁሉ በክርስቶስ የልደት ገፀ በረከት የተገኙ ናቸው፡፡ ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ በምድር የሚኖሩ ሰዎች በቀቢጸ ተስፋ፣ ሰላም በማጣት ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ሆነው ለብዙ ሺህ ዓመታት ኖረዋል፡፡ የነቢያት ጾም ጸሎት፣ የካህናት መሥዋዕት ምድርን ከኃጢአት ሊያነጻ አልቻለም፡፡ ምድርን ከኃጢአት የሚያነጻት ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ በመሆኑ እነሆ አምላክ ሰው ሆነ፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› ዮሐ 1፡29  በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ስለዚህም ነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በፍፁም ትህትና የሰውን ልጅ ሥጋ ለብሶ ሰው መሆንን የመረጠው፡፡

 በጌታችን ልደት ያገኘናቸውን በረከት እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

             1.ልጅነትን አግኝተናል፡፡

የሰው ልጅ የተፈጠረው በአርአያ እግዚአብሔር ሲሆን የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስሙን ይቀድስ ክብሩን ይወርስ ዘንድ ነው፡፡ ነገር ግን የምኞት ፈረስ ከልጅነት ይልቅ አምላክነት እንዲመርጥ ገፋፋው፡፡ ስለዚህም ልጅነቱን በፈቃዱ አጣ፡፡ ምንም አንኳን የሰው ልጆች ልጅነታቸውን ቢጥሉ እግዚአብሔር አምላክ ግን አባትነቱን አልተወም፡፡ በነቢያት እያደረ መምህራንን እያስነሳ ዳግመኛ ልጆቹ እንዲሆኑ መክሯል፣ አስመክሯል፣ ‹‹እናት ልጇን እንደምታጽናና እንዲሁ እኔም አጽናናችኋለሁ›› ኢሳ 66:13 በማለት አባትነቱን ተናግሯል፡፡ ይህን ያጣነውን ልጅነት ሊያስመልስልን ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም ሰው ሆነ፡፡ ባርነታችን ወደ ልጅነት፣ ባዕድነታችን ወደ ወራሽነት ተለወጠ፡፡ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንደ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ›› ገላ 4፡7 በማለት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ በልደቱ እንዳገኘን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ገልጧል፡፡ በክርስቶስ ልደት ማመን ከልደቱም በረከት መካፈል ልጅነትን የሚያሰጥ ታላቅ ምስጢር ነው፡፡ መጽሐፍም ‹‹የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፤የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም፤ ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው›› ዮሐ 1፡11 በማለት ልጅነታችንን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ልጆቹም ስለሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮህ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ›› ገላ 4:6 በማለት ልጅነታችንን እንዳገኘን ያረጋግጣል፡፡

        2.   ነጻነታችን አግኝተናል፡፡

ሰው ነጻ መሆኑ የሚታወቀው ፈቅዶ በመረጠው ነገር ያለምንም ከልካይ መኖር ሲችል ነው፡፡ ከውድቀቱ በኋላ የሰው ልጅ ያጣው ታላቅ ነገር ቢኖር ነጻ ፈቃዱን ነበር፡፡ ጽድቅን መርጦ በጽድቅ መንገድ ቢጓዝ እንኳ መንግሥቱን ለመውረስ አይችልም ነበር፡፡ ነቢያትም አምርረው ሲያለቅሱ የነበረው ‹‹ጽድቃችን የመርገም ጨርቅ ሆነ›› በማለት ነበር፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ይህን ነጻነታችንን አስመልሶልናል፡፡ ‹‹በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን›› ገላ 5፡1 እንዳለ፡፡ የጌታን ልደት መላእክቱ ለኖሎቱ ሲያበስሩም እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ›› ሉቃ 2፡14፡፡ ከእስር የተለቀቀ ሰው ነጻ እንደሆነ ሁሉ የሰው ልጅም ለሺህ ዘመናት በዲያብሎስ ግዞት ይኖር ስለነበር በልደቱ ከዚህ እስር በመላቀቁ ነጻነቱን አግኝቷል፡፡

      3.    ሰላማችን ተመልሷል ተስፋችን ተሳክቷል፡፡

በቀደመው ዘመን ከልደተ ክርስቶስ በፊት ሰው ሰላሙን አጥቶ ይኖር ነበር፡፡ ‹‹ የሰላምን መንገድ አያውቁም… መንገዳቸውን አጣመዋል፤ የሚሄዱባትም ሁሉ ሰላምን አያውቁም›› ኢሳ 59፡7 በማለት ሰላም አንዳልነበረ አስረድቷል፡፡ ልደት እውነተኛ ሰላማችንን ያገኘንባት፣ ተስፋችንም የተረጋገጠበት ልዩ ቀን ናት፡፡ ከእግዚአብሔር ፈቃድ በመውጣት ያጣነው ሰላም በልደቱ ተመልሷል፡፡ ሰላምን የሚያድል እርሱ ስለሆነም ‹‹ሰላሜን እሰጣችኋለሁ›› ብሏል፡፡ ለብዙ ዘመናት ሰላምን ብንነፈግም እውነተኛ ሰላምን ያገኘነው በክርስቶስ ልደት ነው፡፡ ‹‹ሰላም በምድር ሆነ›› ብለው መላእክት የዘመሩትም በልደቱ ነው፡፡በልደት ካገኘናቸው ገጸ በረከቶች በተጨማሪ ሌሎች ለሕይወታችን ጠቃሚ የሆኑ መልእክቶችንም አግኝተናል፡፡ በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ምሳሌ የሆነ ዐቢይ ቁም ነገሮችንም በልደቱ ገብይተናል፡፡

             ሀ. ትህትና

እግዚአብሔር አምላክ ‹‹እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝ›› በማለት ትህትና የባህርይ ገንዘቡ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ በልደቱም ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለማመን በሚከብድ ፍፁም ትህትና ራሱን ዝቅ አድርጎ ለሰዎች ተገልጧል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያዕቆብ ‹‹በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም›› ዘፍ 40:9 የሚለው የትንቢት ቃል ተፈጻሚ እንዲሆን ከይሁዳ ወገን ቢወለድም ቅሉ ከይሁዳ ግዛትም ታናሽ በሆነችው ቤተልሔም እንደተወለደ መጻሕፍት ይነግረናል፡፡ ‹‹አንቺም ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ አንቺ ከይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ›› ሚክ 5:2፣ ሉቃ 1:5 ማቴ 1:1 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከታናሿ ቤተልሔም ለመወለድ የመረጠው በበረት ግርግም ውስጥ ነው፡፡ ሁሉ የእርሱ የሆነ አምላክ ምንም እንደሌለው የሆነው የትህትናን ልዕልና ሊገልጽልን ፈልጎ ነው፡፡ ፍፁም የሆነ ትህትና መገለጫው ያለንን ነገር እንደሌለን መቁጠርና  መተው ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስም ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡ ባለፀጋ ሳለ ደሀ ሆነ ፤ ሁሉ የሞላለት ሳለ ማደሪያ ስፍራ አጥቶ በበረት (ግርግም)ተወለደ፡፡ ይህንን ትህትናውን በጥምቀቱ ገልጿል፤ ወደ ፈጠረው ዮሐንስ ሄደ ‹‹እንግዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል›› በማለት ጽድቅ ለፍፁም ትህትና የሚደረግ ሕይወት እደሆነ አስረድቶናል፤ ማቴ 3:14፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ትህትና እንዲህ በማለት ገልጾታል፡፡ ‹‹የባሪያውን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ›› ፊሊ 2:6  ‹‹ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አነሰ›› ዕብ 2፡9 ‹‹ስለዚህ የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተሰረይ….በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው›› ዕብ 2፡17 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጀመሪያው እስከ ፍጻሜው ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በትህትና የተደረጉ ናቸው፡፡ ወደ ምድር ሲመጣ ፍፁም ትህትና ባላት በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አድሮ መጣ፡፡ ሲወለድ በቤተልሔም በበረት ግርግም፣ ሲጠመቅ ባገልጋዩ በዮሐንስ እጅ፣ ወደ መስቀል ሲወጣም በፈጠራቸው ፍጡራን እጅ መሆንን ስንመለከት እውነትም እግዚአብሔር የትህትና ባለቤትና የትሁታን ወዳድ መሆኑን እንረዳለን፡፡

            ለ. ፍቅር

እግዚአብሔር ሰውን ለምን ወደደው; ብለን ብንጠይቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠን መልስ ቀላልና ግልፅ ነው፡፡ ‹‹…እንዲሁ…›› ዮሐ 3:16፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለመውደድ /ለማፍቀር/ ምክንያት የለውም፡፡ ኃጢአተኛና ጻድቅ፣ ንጹሕና ቆሻሻ፣ ምሁርና ያልተማረ፣ የሚል መመዘኛም በአምላክ ዘንድ የለም፡፡ እግዚአብሔር እንዲወደን ሰው መሆናችን ብቻ በቂ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከማፍቀሩ የተነሳ ዓለምን እንዲያድን አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከው፡፡ በልደትም የምናየው ይህን የአምላካችንን ልዩ ፍቅር ነው፡፡ ቀድሞ በነቢያት ‹‹በዘላለም ፍቅር ወድጃችኋለሁ›› ኤር 31:3 በማለት ፍቅሩን ገልጦ ነበር፡፡  ይህን ፍቅሩን ደግሞ በልደቱ በይበልጥ ገለጠው፡፡ ሰውን ለመውደድ ምክንያት የምናበዛ ሰዎች ስንቶች ነን? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልደቱ ያሳየንን ግሩም ፍቅር ለእህት ለወንድሞቻችን በማሳየት ክርስቶስን በግብር ልንመስለው ይገባል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ወርዶ በበረት ግርግም የተወለደው እስከ መስቀል ሞትም የደረሰው ለሰው ልጅ ባለው ፍፁም ፍቅር መሆኑን መገንዘብ ያደረገውን የትህትና ስራ መመልከት የልደትን መንፈሳዊ ምስጢር እንድንረዳ ያደርገናል፡፡ ካለዚያ ልደትን ለመታሠቢያነት ብቻ ከማክበር የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በእግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረ ሰውን ፍፁም በሆነ ፍቅር መውደድ ከባድ ቢሆንም እንኳ የማይቻል ነገር ግን አይደለም! ሰውን መውደድ ቀስ በቀስ እየዳበረ እስከ ፍጽምና የሚያደርስ መንፈሳዊ ሀብት ነው፡፡ በፍቅር ላይ ያልተመሠረተ መንፈሳዊ ሱታፌ፤ መንፈሳዊ ሕይወት መጨረሻው አያምርም፡፡ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ሕይወት ‹‹በሁሉ ይጸናል›› 1ኛ ቆሮ 13:7 የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደትም የፍቅር የመጨረሻው ማሳያ መሆኑን መገንዘብ ሕይወታችንን በዚህ መነጸርነት እንድናይ ያግዘናል፡፡

                  ሐ. ተስፋን መፈጸም፡-

እስራኤል ዘሥጋ የመሲሑን መምጣት በተስፋ ሲጠብቁ ቢቆዩም የክርስቶስን ሰው ሆኖ መምጣት ለመቀበል ዳተኞች ነበሩ፡፡ መጽሐፍም ‹‹የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም›› ዮሐ 1:7 ይላል፡፡ ነቢያት በሙሉ እግዚአብሔር የሰው ዘር ማዳኑን በተስፋ ሲጠብቁ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ተስፋውን ሊፈጽም አንድያ ልጁን ወደ ምድር ላከ፡፡ ተስፋችንም ተፈጸመ፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ›› ገላ 4:4 ይላል፡፡ ነቢያት ይህን ቀን በተስፋ ሲጠብቁ እንደነበር በትንቢታቸው ገልጸዋል፡፡ ኢሳ 7:14 ፣ ኢሳ 9:6 ፡፡ አምላካችን ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ የሰጠን ነገር ቢኖር ተስፋን ነው ‹‹እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፡፡›› ዘፍ 3:22 በማለት ሰው ሆኖ ወደ ምድር እንደሚመጣ ተስፋን ሰጠን፡፡ ይህንም ተስፋ ይዘን ለሺህ ዘመናት በጉጉት ጠበቅን ነቢዩ አንደተናገረው አምላክ ጻሕቀ ልቡናችን ፈጸመልን፡፡ ‹‹ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች›› ኢሳ 40:80 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው የገባውን ቃል አስታውሶ ወደ ምድር እንደመጣ ሁሉ በእርሱ ስም የሚጠሩ ክርስቲያኖችም የገቡትን ቃል፣ የሰጡትን ተስፋ በመፈጸም አምላካቸውን መምሰል ይገባቸዋል፡፡ የተሰጣቸውን ሥራ በጊዜ የማይጨርሱ፣ ጉባኤ የሚያስተጓጉሉ፣ ሰው ቀጥረው ሲያረፍዱ እንኳ ቅንጣት የማይሰማቸው ክርስቲያኖች ካሉ በእውነትም በልደት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረንን ቀጠሮ የማክበር ቃልን የመጠበቅ አሰረ ፍኖት የዘነጉ መሆናቸውን መረዳት አለባቸው፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሚያስተላልፈው ዐቢይ መልእክትም ይህን  ነው፡፡ ‹‹ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም›› እንደተባለ በቃላችን የምንገኝ፣ ባልነው የምንጸና ተአማኒ መሆን ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡

ባጠቃላይ በልደቱ ያገኘናቸውን ሀብታት በመጠበቅ፣ የተማርናቸውን ትምህርቶች በመፈጸም እውነተኛ የልደት በዓል ተካፋዮች መሆን ይገባናል፡፡ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ሰማያውያን መላእክት ከምድራውያን እረኞች ጋር በአንድ ላይ እንዳመሰገኑ እኛም በዝማሬና በምስጋና በፍፁም ደስታ ልናመሰግን ይገባል፡፡

                             ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

በጎ ያልሆኑ ተጽእኖዎች በክርስትናችን

በማሞ አየነው
 
በተደጋጋሚ ከሚያጋጥሙኝ ክስተቶች አንዱ ይህ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከምተዋወቀው አንድ ልጅ ጋር ቁጭ ብለን እየተጨዋወትን ነው፡፡ ልጁን የማውቀው ሰ/ት/ቤት ውስጥ ታታሪ አገልጋይ በነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ አሁን ከመንፈሳዊ አገልግሎቱ ራሱን አግልሏል፡፡ እንደድሮው ስለመንፈሳዊ ሕይወቱ የሚያወያየው ለአገልግሎት የሚጋብዘው፣ ሲደክም የሚያበረታው፣ ሲሰለች መንፈሱን የሚያድስለት፣ ጓደኛ የለውም፡፡
 
ከሚሳተፍባት አጥቢያ  ሰ/ት/ቤት መራቁን እንደ ትልቅ ምክንያት እያነሳ በተደጋጋሚ ነገረኝ ምክንያቱ አልተዋጠልኝም፤የራቀው ከአንድ አካባቢ እንጂ ቤተ ክርስቲያንና ሰ/ት/ቤት አሁን ካለበት አካባቢ እንዳለ አውቃለው፤ ከተለያየን በኋላ ስለጉዳዩ በደንብ አሰብኩበት፡፡ ይህ ችግር የብዙ ሰዎች ችግር እንደሆነ በተደጋጋሚ እናያለን፤ ራስን ከሚያገኛቸው ሁኔታዎች ጋር አስማምቶ ክርስቲያናዊ ሕይወትን በጊዜና በቦታ የመገደብ፣ ራስን ከሚያገኛቸው ሁኔታዎች ጋር አስማምቶ ክርስቲያናዊ ሕይወትንና አገልግሎትን የማስኬድ ችግር የብዙዎች ችግር ነው፡፡ ይህም አንድ ነገር እንዳለ ያመላክተናል።ይህም ክርስትናችን የቆመበት መሠረት በነፋስና በጎርፍ ተጠራርጎ ለመውደቅ ቅርብ መሆኑን ነው። ለዚህ ነው ጥቃቅን ምክንያቶች ግዙፍ የሚመስለንን ግን ያልሆነውን ክርስትናችንን አደጋ ላይ የሚጥሉት የሁሉም ነገር መነሻ መሠረቱ ነውና፡፡ ክርስትናም የራሱ መሠረት አለው፡፡ እስኪ በተረጋጋ መንፈስ ክርስትናችን የተገነባበትን እንመርምር፡፡ በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ውስጥ ልብ ልንላቸው የሚገቡ ነገር ግን እንደዋዛ የምናያቸውን ነጥቦችን እንደሚከተለው እንመለከታለን፡-

ሀ.  በሌሎች ጫንቃ ያረፈ ክርስትና ነው ያለዎት?

ሁሌም ልብ ልንለው ከሚገቡ ነጥቦች አንዱ ክርስትናችን ማንን ተስፋ እንዳደረገና በማንስ ላይ ተስፋውን እንደጣለ መረዳት ነው፡፡ የብዙዎቻችንን መንፈሳዊ አይን ሸፍኖ ዋናውን ነጥብ እንዳናይና የሚያደርጉ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ በአካባቢያዊና በአጥቢያ ላይ የተመሠረተ የአገልግሎተ ፍቅር፣ በማኅበራት ትክሻ ላይ የተንጠላጠለ ሱታፌ፣ ከጓደኝነትና ከመላመድ የመነጨ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ዋናውን የክርስትና ዓላማ  እንዳንረዳ ከሚያደርጉን መሰናክሎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ነጥቦች ለክርስትናችን እንደ ግብዓት የሚታዩ እንጂ የአገልግሎታችንና የክርስቲያናዊ ሕይወታችን መሠረቶች ሊሆኑ አይገባም፡፡ ልብ ብሎ ራስን መመርመር የሚገባም ለዚሁ ነው፡፡
ግድግዳና ጣሪያ ብቻ ለቤት መሠረት ሊሆኑ እንደማይችሉ ሁሉ በሰው በማኅበር መሠባሰብ ላይ የተመሠረተ ክርስትናም ዘላቂነት የለውም፡፡ ብዙዎች ከሚያገለግሉበት አጥቢያ ሲርቁ፤ በክርስትና ከሚያውቋቸው ጓደኞቻቸው ሲለዩ ከቤተክርስቲን ለመራቅ ያስባሉ፡፡ ክርስትና እዚያና እዚህ ብቻ ያለ ይመስላቸዋል፤ ክርስቲያናዊ ሕይወት የእነ እገሌ ተሰጥዖ  ብቻ አድርገው ይወስዳሉ፤ ቀስ በቀስም ተስፋ የመቁረጥና የብቸኝነት ስሜት በልባችን ሰርጾ ይገባል፡፡ ከለመድነው አሰራርና አካሄድ የተለወጠ ነገር ባየን ቁጥር እየበረገግንና እየራቅን እንመጣለን። ስለዚህ በድሮው ክርስትናችን መቀጠል ይከብደናል፡፡ ዴማስ ከለመደው ከተማና ሁኔታ የተለየ ሁኔታ ስለገጠመው ነበር በተሰሎንቄ ተስቦ የቀረው /2ኛ ጢሞ/ ብዙዎች የተሰናከሉት የሰው ልጆችን ኑሮ በማየታቸውና ከለመዱት የአኗኗር ዘየ የተለየ ነገር ስለገጠማቸውና ስለተሸነፉለትም ነበር። /ኩፋ 6፥9 ዘፍ 6፥1/  የያዕቆብ ልጅ ዲናም ከክብር ያነሰችው የለመደችውን የአህዛብ አኗኗር መቋቋም አቅቷት ነበር፡፡ ዘፍ 34፥1 የብዙዎቻችንም ክርስትና እንዲሁ ለፈተና የተጋለጠ ነው፡፡ አካባቢን ከመለወጥ ይልቅ እኛው ተለውጠን ክርስትናችን ደብዛው የጠፋብን ብዙዎች ነን፡፡ የማኅበረ እስጢፋኖስ መበታተን ክርስትናን የበለጠ እንዲስፋፋ አደረገ እንጂ ክርስትናቸውን አላጠፋባቸውም፡፡ በጊዜና በቦታ ሳይወሰኑ አሐቲ የሆነችውን ቤተክርስቲያን ማገልገል የቤተክርስቲያንን የአገልግሎት ሁኔታ የመረዳትና የክርስትናንም ውል የመያዝ ምልክት ነው፡፡ ከመንፈሳዊ ሩጫችን ጎን ለጎን ልናስተውለውና ልንረዳው የሚገባን ቢኖር እያገለገልኩና እየሮጥኩ ያለሁት ከራሴ በሚመነጭ መንፈሳዊ ግፊት ነው ወይስ በስብሰባ ድምቀት ልምድ ስለሆነብኝ? ወይንም ከሰ/ት/ቤት ልጆች መራቅ ስላልፈለግሁ ነው የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡

ለ. ከአፍአዊ አገልግሎትና ምስጢራት ከመሳተፍ የቱን ያስቀድማሉ?

በሚገባ አስተውለንና አጢነን ከሆነ ብዙ ጊዜ መንፈሳዊ ሩጫ ውስጥ የገቡ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ምስጢራት መሳተፍ ያቆማሉ፡፡ ከኪዳን፣ ከቅዳሴ፣ ከሥጋ ወደሙ የራቁ ነገር ግን ሩጫ የሚያበዙ፣ መረጋጋት የማይታይባቸው፣ በአፍአ (በውጭ) ያሉ ብዙ ጓደኞች አሉን፡፡ መንፈሳዊ በሆነ ኃይልና ዕውቀት ከማገልገል ይልቅ በስጋ ድካም ማገልገል የበለጠ ውጤት የሚስገኝ ስለሚመስላቸው ቅዳሴና ኪዳን ለነሱ ቦታ የላቸውም፤ እንደዚህ ዓይነት አገልጋዮች ይህን ከመሰለው እንቅስቃሴ ሲለዩ የክርስትና መስመር የተበጠሰ ይመስላቸዋል፡፡ የዚህ ሁሉ እንቅስቃሴ ዓላማ ሰውን ምስጢራት ወደ ማሳተፍ ማምጣት መሆኑን ይዘነጉታል፡፡
የማርታና የማርያምም ታሪክ የሚያስተላልፍልን መልእክት ይህንን ነው፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን መስማት የሚቻለው ከቅዳሴው ምስጢር መሳተፍ ስንችል ነው፡፡ በቅዳሴ ቃለ እግዚአብሔርን ሰምተን ብቻ አንበተንም፤ ለሥጋ ወደሙ ያዘጋጀናል፡፡ ዋናው የክርስትና ግብም ይህን ምስጢር መሳተፍ ነው።   ጌታችንም ሐዋርያትን ካስተማረና አእምሮአቸውን ካዘጋጀ በኋላ በመጨረሳ ሰዓት የተናገራቸው  ታላቅ ነገር ቢኖር ምስጢራትን እንዲፈጽሙ ማድረግ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው በምሴተ ሐሙስ ሥጋውና ደሙን ያቀበላቸው፡፡ማቴ 26፥26 መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ያለን ሰዎችም ልናስተውለው የሚገባን ታላቅ ምስጢርም ይህ ነው፡፡ ዕውቀትን ከማጎልበት፣ ለሌሎች መዳን ደፋ ቀና ከማለት በተጨማሪ ምስጢራትን መሳተፍና መፈፀም ይገባናል፡፡ በምስጢራት መሳተፍ ያልለመደ አገልጋይ ክርስትና ሰ/ት/ቤት፣ ማኅበራት ጋር፣ ከጓደኞቹ ዘንድ ብቻ ያለ ስለሚመስለው ከነዚህ ሲርቅ ክርስትናው ከገደል አፋፍ ላይ ይቆማል፡፡ ከምንም ነገር በላይ በምስጢራት መሳተፍ መልመድ ከቤተክርስቲያን እንዳንርቅ የሚያስተሳስረን ሕቡር ገመድ ነው፡፡ ይህን የለመደ ሰው የትም ሄደ የት ከምስጢሩ አይርቅም፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ማስተካከል የሚገባንም ከዚህ መሠረታዊ ነጥብ ጋር ነው፡፡

ሐ. እውን ሕይወትዎን እየመሩ ያሉት ለሰው ወይስ ለእግዚአብሔር?

ህገ እግዚአብሔርን እየፈጸ ምን ያለነው በእውነተኛ የእግዚአብሔር ፍቅር ተመክረን ነው ወይስ ከመንጋው ላለመለየትና ከነቀፌታ ለመራቅ ብለን ነው? ቤተ እግዚአብሔር የምንሄደው፣ የምናስቀድሰው፣ የምናገለግለው፣ … ከሰው ምላሽን ጠብቀን ከሆነ ጽድቃችን ከፈሪሳዊያን በምን ይለያል? ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ህጉን የሚፈጽሙት ለጽድቅ ብለው ሳይሆን የሙሴን ህግ ይፈጽማሉ ለመባል ብቻ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን ‹‹ ጽድቃችው ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ….›› ብሎ ያስተማረ፡፡ እያንዳንዱ የሕይወታችን ጥቃቅን ነገር መመርመር ያለብንም ያደርጋሉ ይፈጽማሉ ለመባል ሳይሆን የጌታ ፍቅር ገብቶንና ደስ እያለን በፍጹም ተመስጦ መሆን ይገባል፡፡ ፍፁም በሆነ ፈቃድ ያለተርእዮ ህግን መፈጸም ግን ጽድቃችንን ከሰው ተጽእኖ የጸዳ ያደርገዋል፡፡ ጌታም በወንጌሉ ‹‹ ቀኝህ የሚያደርገውን ግራህ አይመልከት›› ያለው ለታይታና ለሆይ ሆይታ ተብሎ ጽድቅን መፈጸም እንደማይገባን ሲያስረዳን ነው፡፡ በዚህ መነሻነት ጽድቅን አለመፈጸም ከጓደኛ ሲለዩ’ ከሚያውቁት ማኅበረሰብ ሲወጡ ክርስትናችንን ፈተና ላይ ይጥላቸዋል፡፡ ህግ የተሰጠ ከእግዚአብሔር ስለሆነ መፈጸም ያለበት ስለእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ተብሎ ብቻ ነው፡፡ መጽሐፍም ‹‹ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ›› ይላል ለሰው’ ለጓደኛ’ለማህበረሰብ  ብሎ ህግን መፈጸም የእግዚአብሔርን ለሌላ እንደመስጠት ይቆጠራል። ነገሮችን ለእግዚአብሔር ብሎ መፈጸም ክርስትናችን በጊዜ፣ በቦታና በሁኔታ እንዳይወሰን ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሌለበት  ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ የለምና ነው፡፡ ስለዚህም የትም ሆን የት ከእግዚአብሔር እቅፍ መውጣት አንፈልግም፡፡ ከእግዚአብሔር መራቅ ለሰከንዶች እንኳን ሳናቋርጥ ከምንወስደው አየር እንደመለየት ነው፤ አየር ለመውሰድ ጊዜና ቦታን እንደማንመርጥ ሁሉ ከእግዚአብሔር ከአገልግሎት ላለመራቅም ጊዜና ቦታ መምረጥ አይገባም፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች በማስተዋል ክርስትናችንን በጎ ካልሆነ ተጽእኖ ማጽዳት አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ መንፈሳዊ ሕይወታችን በጊዜና በቦታ እንዳይወሰን ለማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡ እነዚህን ሀሳቦች እናስተውል ዘንድ አስተውለንም እንተገብራቸው ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ልቦናችንን ያነቃቃል!!  አሜን።
                                                            
ወስብሐት ለእግዚአብሔር