ጾመ ፍልሰታ/ጾመ ማርያም/

መጋቤ ሐዲስ ብርሃን አንለይ

ፍልሰታ ማለት ፈለሰ፤ተሰደደ፤ተጓዘ፤ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሄደ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ «ፈለሰት ማርያም እምዘይበሊ ኀበኢይበሊ፤ ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም፣ ከምድር ሕይወት ወደ ሰማያዊ ሕይወት፣ ተሻገረች» በማለት ፍልሰታ የሚለውን ቃል ትርጓሜ አመሥጥሮ ገልጾታል፡፡

ጾመ ፍልሰታ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም የዕረፍት ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እመቤታችን በዚህ ዓለም ፷፬ ዓመታትን በሕይወተ ሥጋ ከቆየች በኋላ ጌታችን የእናቱን ተድላ ነፍሷን እንጂ ተድላ ሥጋዋን አይወድምና ጥር ፳፩ ቀን ፵፱ ዓመተ ምሕርት አረፈች፡፡ ዕረፍቷም እንደሌላው ሰው በሕማምና በድካም አይደለም፡፡ በገነት ዕፀዋት መዓዛ ተመስጣ ቅድስት ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይታለች፡፡ ታሪኩ በነገረ ማርያም እንደተጻፈው ሐዋርያት እመቤታችንን በአጎበር አድርገው አክብረው ወደጌቴሴማኒ መካነ መቃብር ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉም ነበርና ቀድሞ ልጇን ተነሣ ዐረገ እያሉ ሲያውኩ ኖረዋል፤  እርሷን ደግሞ ተነሣች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን ነውና «ኑ የማርያምን ሥጋ በእሳት እናቃጥለው» ብለው በምቀኝነት ተነሱ፡፡ ከመካከላቸው አንድ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ከሐዋርያት እጅ ለመንጠቅ ዘሎ ሄዶ የአልጋውን ሸንኮር ሲይዝ የታዘዘ መልአክ በረቂቅ ሰይፉ እጆቹን ቆረጠው፡፡ እጆቹም በአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ የምሕረት እናት የሆነችው ድንግል ማርያም ቅዱስ ጴጥሮስ ጸልዮ እጆቹን እንዲመልስለት ነግራው እንደነበረ አድርጎለታል፡፡

የእመቤታችን ሥጋዋን መላእክት ከዮሐንስ ወንጌላዊ ጋር በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር ወስደው አስቀምጠውታል፡፡ ሥጋዋ ያለበትን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ አይቶ እነርሱ ባለማየታቸው እመቤታችን ባረፈች በ፮ኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን እስከ ፲፬ ቀን ድረስ ከጾሙ በኋላ በ፲፬ኛው ቀን ሥጋዋን እንደገና ከጌታ ተቀብለው በጌቴሴማኒ ባለው መቃብር ቀብረውታል፡፡ ከዚህ በኋላ እንደ ልጇ በ፫ኛው ቀን ተነሥታ መላእክት እየዘመሩላት ወደሰማያት ስታርግ፤ ሐዋርያው ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሰ ዕርገቷን በማየቱ መላእክት «እመቤትህ እርሷ ናት፤ስገድላት» አሉት፤ እርሱም «ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ ይላል፤ከደመናው ሊወድቅ ወደደ» ምክንያቱም ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ፤ዛሬ ደግሞ የእርሷን ትንሣኤ ለማየት ብሎ ነው፡፡ እመቤታችንም «ትንሣኤየን ያየህ አንተ ነህ ሌሎቹ አላዩም» ብላ ሐዋርያት ገንዘው የቀበሩበትን የሐር ግምጃ ሰጥታ አጽናንታ ሰደደችው፡፡

ቅዱስ ቶማስ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የእመቤታችን ነገር እንዴት ሆነ ብሎ ጠየቃቸው፤እነርሱም አግኝተው እንደቀበሯት ነገሩት፤ እርሱም ያየውን ምሥጢር በልቡ ይዞ «ሞት በጥር፤ በነሐሴ መቃብር፤ ለሰሚውም አያምር፤ይህ እንዴት ይሆናል?»፤ ቢላቸው ቅዱስ ጴጥሮስ «ድሮም አንተ ተጠራጣሪ ነህ፤ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ እንዲሉ፤ ገንዘን የቀበረን እኛ እያለን እንዴት ትጠራጠራለህ» ብለው ወደ መቃብሯ ሄደው መቃብሯን ቢከፍቱት ባዶ ሆኖ አገኙት፡፡ በዚህ ተደናግጠው ተያዩ፤ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ «አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችን ተነሣች፤ዐረገች፤ ይኸው ምልክቱ» ብሎ ገንዘው የቀበሩበትን ሰበን አሳያቸው፤እነርሱም አምነው ሰበኗን ለበረከት ተካፈሉት፡፡

በዓመቱ ነሐሴ ፩ ቀን ሐዋርያት በመንፈሰዊ ቅናት ተነሳስተው «ቶማስ ትንሣኤዋን አይቶ እኛ ሳናይ እንዴት ይቀርብናል» በማለት ነሐሴ ፩ ቀን ሱባኤ ጀምረው በ፲፮ኛው ቀን የሐዋርያትን ሱባኤ ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር ጴጥሮስን ተራዳኢ፣ ካህን እስጢፋኖስን ሠራዔ ዲያቆን አድርጉ ቀድሶ አቅርቧቸዋል፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላም ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን  ጾመ ፍልሰታ ተብሎ ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ይጾመዋል፡፡ የጾሙና የትንሣኤዋ በረከት ተካፋይ ያድረገን፤አሜን