‹‹አትጨነቁ…›› (ማቴ.፮፥፴፬)
ሰዎች መልካምና ክፋ ነገርን ለማሳካት ይጨነቃሉ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹አትጨነቁ›› ያለን ለክፋትና ለኃላፊው ዓለም ተጨንቀን መፍትሔ ለማናመጣለት ነገር ነው፡፡ (ማቴ.፮፥፴፬) ፈጣሪያችን ለእኛ ለልጆቹ በዚህ ምድር በእንግድነት ስንኖር ምን እንደሚያስፈልገን ያውቃል፤ የሚያሻንንም ይሰጠናል፤ እናስብ ዘንድ አስተዋይ አእምሮ ሰጥቶናል፤ ማሰብ ከሚገባን በላይ ደግሞ ልንጨነቅ ስለማይገባ ‹‹አትጨነቁ›› አለ፡፡ አበው በብሂላቸው ‹‹…አስብ እንጂ አትጨነቅ..›› የሚሉን ለዚህ ነው፡፡ በምድር ስንኖር በማሰብ በመጠንቀቅ፣ በመጠበቅ እንደ ርግብ የዋህ እንደ እባብ ደግሞ ብልህ ሆነን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ልንፈራና ልንጨነቅ እንደማይገባ ግን ክርስትናችን ያስተምረናል፡፡ ጌታችን ለአባቶቻችንን ቅዱሳን ሐዋርያት ስለሚቀበለው መከራ፣ ስለሞቱ ሲነግራቸው ባዘኑ ጊዜ ‹‹…ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም ደግሞ እመኑ…›› በማለት በአንዳች ነገር እንዳይጨነቁ ልባቸው እንዳይታወክ ነገራቸው፡፡ (ዮሐ. ፲፬፥፩)