‹‹ጾም የነፍስን ቊስል ትፈውሳለች›› (ቅዱስ ያሬድ)  

                                                                                              በብዙአየሁ ጀምበሬ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሚከናወኑ ዓበይት ክርስቲያናዊ ምግባራት መካከል ጾም አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ጾም ‹‹ጾመ››  ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ተከለከለ፤ተወ፤ታቀበ፤ታረመ ማለት ነው፡፡ በሱርስትና በዕብራይስጥ ቋንቋዎች ‹‹ጻም›› ሲባል በአረብኛ ቋንቋ ደግሞ ‹‹ጻመ›› በመባል ይታወቃል፡፡ (ጾም እና ምጽዋት ገጽ ፰)

የቤተ ክርስቲያናችን የሕግና የሥርዓት መጽሐፍ የሆነው ፍትሐ ነገሥት ደግሞ በአንቀጽ ፲፭ ላይ ‹‹ጾምሰ ተከልኦተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ፤ ጾምስ በታወቀው ዕለት፤በታወቀው ሰዓት ከምግብ መከልከል ነው›› በማለት ጾምን በዚህ መልኩ ይተረጕመዋል፡፡

እንግዲህ በሃይማኖታዊ ትርጉሙ ጾም ማለት ራስን ከእህል፤ከውኃ ብሎም አምላካችን እግዚአብሔር ከሚጠላቸው እኩይ ምግባራት ሁሉ ራስን በመከልከል የሥጋን ፈቃድ ለነፍስ በማስገዛት መቆየት ማለት ነው፡፡‹በዚያም ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት በእግዚአብሔር ፊት ነበረ፤ እንጀራም አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም፤ በጽላቱም ዐሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ።›› (ዘፀ.፴፬፥፳፰) ሁለቱን የድንጋይ ጽላት፥ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የተማማለባቸውን የቃል ኪዳን ጽላት፥ እቀበል ዘንድ ወደ ተራራ በወጣሁ ጊዜ፥ በተራራው ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ተቀምጬ ነበር እንጀራ አልበላሁም፥ ውኃም አልጠጣሁም›› ተብሎ እንደተጻፈ። (ዘዳ.፱፥፱)

ከዚህም ባሻገር ጾም ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ፤ ሥጋዬም ቅባት በማጣት ከሳ›› በማለት እንደናገረው በዚህ የጾም ወቅት ከጥሉላት መባልዕት ወይም የእንስሳት ተዋጽኦ የሚባሉትን ማለትም እንደ ሥጋ፤ወተት፤ዕንቁላል፤ዐይብ፤ ቅቤ ወዘተ ከመሳሰሉት ቅባትነት ካላቸው ምግቦችና ከሚያሰክሩ መጠጦች ራስን መከልከል መከልከል ያስፈልጋል፡፡ (መዝ ፻፰፥፳፬)

ነቢዩ ዳንኤልም በትንቢት መጽሐፉ ስለ መባልዕት ጥሉላት እንዲህ ብሏል‹‹በዚያም ወራት እኔም ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ፡፡ ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፤ሥጋና የወይን ጠጅም በአፌ አልገባም››(ዳን.፲፥፪-፫) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ፤‹‹ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ፤ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣናል፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና፡፡›› ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ ወንጌል ሥጋን የሚያደልበውን መብልን እንደማትሰብክና በመብል ብቻ ልባችንን ማጽናት እንደሌለብን ገልጿል (ዕብ. ፲፫፥፱)

የክርስትናችን መሠረት ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ስለ መብልና መጠጥ ከንቱነት እንዲህ በማለት አስተምሮናል፡፡ ‹‹ራሳችሁን ጠብቁ፤ በመብልና በመጠጥ፤በመቀማጠልና የዓለምን ኑሮ በማሰብ ልባችሁን አታደንድኑ፤ ያቺ ቀንም በድንገት ትደርስባችኋለች፡፡››(ሉቃ.፳፩፥፴፬)

የሰው ልጅ አብዝቶ በበላና በጠጣ ጊዜ ከአእምሮው በመውጣት እኩይ ተግባራትን ሊፈጽም ይችላል፡፡ ጥጋብና ስካር የኅሊናን አቅል በማሳጣት ለኃጢአት ይዳርጋሉ፡፡ ‹‹በቀን እንደሚሆን በጽድቅ ሥራ እንመላለስ፤በዘፈንና በስካር፤በዝሙትና በመዳራት አይሁን፤በክርክርና በቅናት አይሁን››(ሮሜ ፲፫፥፲፫)  ስካር ከእግዚአብሔር መንግሥት ያርቃል ‹‹ምቀኝነት፤መግደል፤ስካር፤ዘፋኝነት፤ይህንም የሚመስል ነው፡፡አስቀድሜም እንደ ነገርኋችሁ ይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም፡፡›› (ገላ.፭፥፳፩) ስካር የሰው አዕምሮን ያጠፋል፡፡(ሆሴ.፬፥፲፩)

ከማንኛውም ክፉ ነገሮች ሁሉ መጠበቅ፤ራስን መግዛት እና መቈጣጠር፤ በንስሓና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ፤ እርሱንም ደጅ መጥናትና ለኃጢአታችን ሥርየትን መለምን ማለት ነው፡፡ ይህንንም ስናደርግ ነቢዩ ዳንኤል ‹‹ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ።›› በማለት እንደተናገረው አምላካችን እግዚአብሔር የሚወደውን የተቀደሰውን ጾም በመጾም ለነፍሳችን መልካም ዋጋን እናገኝ ዘንድ ከሥጋዊ ምቾትና ቅንጦት በመራቅና ራሳችንን ዝቅ በማድረግ ልንጾም ይገባል፡፡(ዳን.፱፥፫)

እንግዲህ ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎ አንዱ ነው፤ ለሥጋም መንፈሳዊ ልጓም ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ፈቃደ ሥጋውን እየገታ ነፍሱን የሚያለመልምበት መንፈሳዊ ስንቅ ነው፡፡ ‹‹ጾም ቊስለ ነፍስን የምትፈውስ፤ኃይለ ፍትወትን የምታደክም፤ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ፤ከእግዚአብሔር ጸጋን የምታሰጥ፤የወንጌል ሥራ መጀመሪያ፤የጽሙዳን ክብራቸው፤የደናግል የንጽሕና ጌጣቸው፤ የዕንባ መፍለቂያዋ፤ አርምሞን (ዝምታን) የምታስተምር፤ ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ፤ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትሕትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት፡፡››(ማር ይስሐቅ አንቀጽ ፬ ምዕ. ፮)

እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በአምሳሉና በአርአያው ከፈጠረው በኋላ ከማእከለ ምድር (ኤልዳ) ወደ ኤዶም ገነት በመውሰድ ክፉውንና መልካሙን የሚለይበት አስተዋይ ኅሊና ባለቤት አድርጎ አኖረው፡፡ (ኩፋሌ ፬፥፱) በዚህም መሠረት የሰው ልጅ ‹‹ከዚህ አትብላ›› በሚል አምላካዊ ቃል ጾም ኆኅተ ጽድቅ የጽድቅ በር ሆና የተሰጠች የመጀመሪያቱ ሕግ ናት፡፡ ጾም ከምግባረ ሃይማኖት ዋነኛው ነው፤ይህም ለአንድ ክርስቲያን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ የማይለየው ምግባር ነው፡፡ ጾም የሰው ልጅ ለአምላኩ ለልዑል እግዚአብሔር ያለውን ፍቅር የሚገልጥበት፤መንፈሳዊ ተጋድሎዎችን የሚያከናውንበት፤ስለራሱና ስለወገኖቹ ኃጢአት የሚያዝንበት፤ የሚያለቅስበትና ወደ ንስሓ የሚመለስበት ታላቅ ሥርዓት ነው፡፡

የጾም አስፈላጊነት በክርስትና ሕይወት እጅግ የጎላ ነው፡፡ በመሆኑም በጾም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛትና ከሥጋዊ ከንቱ ኃጢአት ለመራቅ ይረዳናል፡፡ ሥጋ በምግብ ሲደነድን ለፍትወትና ለተለያዩ ሥጋዊ ኃጢአቶች ቅርብ ይሆናል፡፡ የሥጋ ፍላጎት በቀዘቀዘ ቊጥር ነፍስ ትለመልማለች፤ ለአምላክ ሕግና ትእዛዛት ሁሉ ተገዢ ትሆናለች፡፡ ማኅሌታዊ ቅዱስ ያሬድ  ስለ ጾም እንዲህ ብሏል፤‹‹ጾም ትፌውስ ቊስለ ነፍስ፤ ወታጸምም ኵሎ ፍትወታተ ዘሥጋ ፤ ትሜህሮሙ ጽሙና ለወራዙት፤ ጾም የነፍስን ቊስል ትፈውሳለች፤የሥጋን ፍትወታት ሁሉ ታጠፋለች፤ ለወጣቶችም ትሕትናን ታስተምራለች፡፡››

ለክርስቲያን የነፍስን ሥራ መሥራት  ከእግዚአብሔር ጋር መተባባርና አንድ ወገን እንደመሆን ያለ ምግባር ነው፡፡‹‹አሁንም ወንድሞቻችን በዚህ በሥጋችን ሳለን ፈቃደ ሥጋችንን ልንሠራ አይገባንም፡፡ ፈቃደ ሥጋቸውን የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ በወዲሁ አለን ሲሉ በወዲያው ምውታን ናቸውና፡፡ ፈቃደ ሥጋችሁንስ በፈቃደ ነፍሳችሁ ድል ከነሣችሁት ለዘለዓለሙ ሕያዋን ትሆናላችሁ፡፡ ፈቃደ ነፍስን የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና፡፡›› (ሮሜ ፰፥፲፪-፲፬) እንዲል፡፡

ጾም የኃጢአት ሥርየትን ለማግኘትና ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ይረዳል፡፡ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ወደ እርሱ በጾምና በጸሎት እንድንመለስ በነቢያት አድሮ አሥተምሮናል፡፡ ‹‹በፍጹም ልባችሁ፤በጾምም፤በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፡፡››(ኢዩ.፪፥፲፪)

ጾም በጸጸት መንፈስ ሆነን በንጹሕ ልባችን ወደ ልዑል እግዚአብሔር በንስሓ እንድንመለስ ይረዳናል፡፡ ‹‹ወሀበነ ጾመ ለንስሓ በዘይሰረይ ኃጢአት፤ ኃጢአት የሚሠረይበትን ይቅር የሚባልበትን ጾምን ሰጠን›› ጾም በደልን አምኖና ጥፋትን ተቀብሎ በፍጹም ትሕትና ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ በድያለሁ ማረኝ ይቅር በለኝ በማለት የንስሓ ዕንባን በማንባት ከእግዚአብሔር ምሕረትን የምናገኝበት ምግባር ነው፡፡

በመጽሐፍ «የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ ወጥተው ወደ ቤቴል መጡ፤ አለቀሱም፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፤ በዚያም ቀን እስከ ማታ ድረስ ጾሙ፤ በእግዚአብሔር ፊት የሚቃጠል መሥዋዕትንና የደኅንነት መሥዋዕትን አቀረቡ›› እንደዚሁም ፤«ወደ መሴፋ ተሰበሰቡ፤ ውኃም ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት በምድር ላይ አፈሰሱ፤ በዚያም ቀን ጾሙ፤ በዚያም፤ በእግዚአብሔር ፊት በድለናል አሉ፤ሳሙኤልም በእስራኤል ልጆች ላይ በመሴፋ ፈረደ›› (መሳ.፳፥፳፮፤፩ኛሳሙ.፯፥፮)

በቤተክርስቲያናችን ሥርዓተ ጾም መሠረት ጾምን የፈቃድ ጾም (የግል ጾም) እና የዐዋጅ ጾም (የሕግ ጾም) በማለት በሁለት ከፍለን የምንመለከታቸው ሲሆን የግል ጾም የምንለው ምእመናን ለንስሓ በግል የሚጾሙትን የፈቃድ ጾም ነው፡፡ ይህ ጾም ምእመናን በምክረ ካህናት ወይም ከንስሓ አባታቸው ጋር በመመካከርና ቀኖናን በመቀበል የሚጾሙት ጾም ሲሆን አንዱ ሲጾም ሌላው ማወቅ የለበትም፡፡ የዐዋጅ አጽዋማት የምንላቸው ደግሞ ዕድሜያቸው ሰባት ዓመት ከሞላቸው ሕፃናት ጀምሮ መላው ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በኅብረት በግልጽ የሚጾሟቸው አጽዋማት ናቸው፡፡