ጥምቀተ ክርስቶስ

timket-2

ጥምቀተ ክርስቶስ

በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ

ጥር ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም  

በነቢያት የተነገረው ትንቢት በወንጌል የተጻፈው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ከዘጠኙ ታላላቅ በዓላት አንዱ ነው፡፡ ጥምቀት የሚለው ቃል ‹‹ተጠምቀተጠመቀ›› ካለው ግሥ የወጣ ነው፤ ትርጕሙም በውሃ መጠመቅ ማለት ሲኾን፣ ይኸውም በወራጅ ወንዝ፣ በሐይቅ ውስጥ ወይም በምንጭ የሚፈጸም ነው፡፡ በካህናት እጅ የሚፈጸመው ጥምቀት ከሌላው ጥምቀት ይለያል፡፡

በዘመነ ብሉይ ይፈጸም የነበረው ጥምቀት የንስሓ ጥምቀት ሲሆን በዘመነ ሐዲስ የሚፈጸመው ግን የልጅነት ጥምቀት ነው፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ከሁለቱም ልዩ ነው፡፡ እርሱ ሰውን ያከብራል እንጅ ከሰው ክብርን የማይፈልግ የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ለእኛ አርአያና አብነት ለመኾን በዮሐንስ እጅ በማየ ዮርዳኖስ ተጠምቆ የባሕርይ ልጅነቱንና አምላክነቱነን ከአብ እና ከመንፈሰ ቅዱስ አስመስክሮ ዕለቱን ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ጾምን ጀምሯል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመው ሕግና የሠራው ሥርዓት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደውሃ ፈሳሽ አይደለም፡፡ ቅድመ ዓለም በልብ የመከረውን ኋላም በነቢያት ያናገረውን ትንቢትና ምሳሌ፣ ያስቈጠረውን የዘመን ሱባዔ፣ ለአዳም የሰጠውን የመዳን ተስፋ ለመፈጸም ነው እንጂ፡፡ የተነገረውን ትንቢት፣ የተመሰለውን ምሳሌም እንደሚከተለው መጻሕፍት ይነግሩናል፤

‹‹ወአሜሃ መጽአ እግዚእ ኢየሱስ እምገሊላ ውስተ ዮርዳኖስ ከመ ይጠመቅ እምኀበ ዮሐንስ፤ ያን ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ›› /ማቴ.፫፥፲፫፤ ማር.፩፥፱፤ ሉቃ.፫፥፳፩፤ ዮሐ.፩፥፴፪/፡፡ ዮሐንስ ግን አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጂ ጌታ በአገልጋዩ እጅ ይጠመቃልን? አገልጋይ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ ጌታ ወደ አገልጋዩ ይሔዳልን ብሎ አይኾንም አለው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከናዝሬት ወደ ዓይነ ከርም ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ በመጣች ጊዜ የዮሐንስ እናት ቅድስት ኤልሳቤጥ ‹‹የጌታየ እናቱ እኔ ወደ አንቺ እመጣለሁ እንጂ አንቺ ወደኔ ትመጭ ዘንድ ይገባኛልን?›› ብላ ነበርና ከዚያ አያይዞ ተናግሮታል፡፡ ጌታም መልሶ ‹‹ይህ ለኛ ተድላ ደስታችን ነው፤ አንተመጥምቀ መለኮት› ተብለህ ክብርህ ሲነገር፤ እኔምበአገልጋዩ እጅ ተጠመቀ› ተብዬ ትሕትናየ ሲነገር ይኖራል፡፡ ትንቢተ ነቢያትንም ልንፈጽም ይገባናልና አንድ ጊዜስ ተው›› አለው፡፡ አንድ ጊዜ ቢጠመቅ ሁለተኛ፤ በፈቃድ ቢጠመቅ በግድ፤ በሰውነቱ ቢጠመቅ በአምላክነቱ መጠመቅ አያሻውምና፡፡

ዮሐንስ እንዲያጠምቅ ጌታም በዮሐንስ እጅ እንዲጠመቅ በነቢያት ትንቢት ተነግሯልና ጌታችን ‹‹ትንቢተ ነቢያትንም ልንፈጽም ይገባናል›› አለ፡፡ ዳግመኛም ይህ ለምእመናን ተድላ ነውና እናንተም ብትጠመቁ መንፈስ ቅዱስ ይወርድላችኋል ለማለት፤ እንደዚሁም ይህ ለባሕርይ አባቴ ለአብ፣ ለባሕርይ ልጁ ለእኔ፣ ለባሕርይ ሕይወቴ ለመንፈስ ቅዱስ ተድላ ደስታችን ነውና ማለቱ ነው፡፡ አንዱ አካል ወልድ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ፤ እግዚአብሔር አብ በደመና ኾኖ ‹‹ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር፤ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤›› ብሎ ሲመሠክር፤ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ተገልጧልና፡፡ ጌታችን ዮሐንስን ‹‹የጀመርነውንም የቸርነት ሥራ ልንፈጽም ይገባናል … አንድ ጊዜስ ተው›› ካለው በኋላም ተወው (ለማጥመቅ ፈቃደኛ ኾነ)፡፡

ዮሐንስም ‹‹አብ በአንተ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፡፡ አንተም በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነህ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በአንተና በአብ ህልው ነው፡፡ ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለው አንተን በማን ስም ላጥምቅህ?›› ቢለው ‹‹ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጼዴቅ›› ብለህ አጥምቀኝ አለው፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ባሕር ወርደዋል፡፡ ‹‹ወተጠሚቆ እግዚእ ኢየሱስ ሶቤሃ ወፅአ እማይ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ከውኀው ወጣ፤›› /ዮሐ.፫፥፲፮/፡፡ ቃለ ወንጌል ‹‹ወናሁ ተርኅወ ሎቱ ሰማይ፤ ሰማይ ተከፈተለት›› ይላል፡፡ ይህን ሲልም በሰማይ መከፈት መዘጋት ኑሮበት አይደለም፡፡ የተዘጋ በር በተከፈተ ጊዜ በውስጡ ያለው ዕቃ በግልጽ እንዲታይ ጌታን ሲጠመቅ ከዚህ በፊት ያልተገለጸ ምሥጢር ታየ ሲል ነው፤ ይኸውም የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ነው፡፡

ከዚህ ላይ ‹‹ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሔዶ መጠመቁ ለምንድን ነው? ምነው አገልጋይ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ ጌታ ወደ አገልጋዩ ይሔዳልን? አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጂ ጌታ በአገልጋዩ እጅ ይጠመቃልን?›› የሚልጥያቄ ከተነሣ ጌታችን መምጣቱ ለትሕትና እንጂ ለልዕልና አይደለምና ነው፡፡ ዳግመኛም ለአብነት ነው፤ ጌታችን ዮሐንስን ‹‹መጥተህ አጥምቀኝ›› ብሎት ቢኾን ኖሮ ዛሬ ነገሥታት፣ መኳንንት ካህናትን ‹‹ከቤታችን መጥታችሁ አጥምቁን›› ባሉ ነበርና፡፡ ካህናት ካሉበት ከቤተ ክርስቲያን ሒዳችሁ ተጠመቁ ለማለት አብነት ለመኾን ራሱ ጌታችን ወደ ዮሐንስ ሔዶ ተጠመቀ፡፡

ጌታችን መጠመቁም ለእርሱ ክብር የሚጨመርለት ኾኖ አይደለም፤ ዮርዳኖስን ብርህት ማኅፀን እንድትኾን ለማድረግ፤ እኛ ምእመናንም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ዳግም ተወልደን መንግሥተ ሰማያት እንድንገባ ለማድረግ፤ እንደዚሁም ሥርዓተ ጥምቀትን ለማስተማርና አብነት ለመኾን ነው፡፡ ‹‹ዘኢተወልደ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይሬእያ ለመንግሥተ እግዚአብሔር፤ ዳግመኛ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ያልተወለደ ማለትም ያልተጠመቀ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ … ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኅን ወዘሰ ኢአምነ ወኢተጠምቀ ይደየን፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፡፡ ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል፤›› ተብሎ ተጽፏልና /ዮሐ. ፫፥፫፤ ማር.፲፮፥፲፮/፡፡

ያውስ ቢኾን ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለምን ነው? ቢሉ ትንቢቱን፣ ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፤ ትንቢቱ፡- ‹‹ባሕርኒ ርእየት ወጐየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ፤ ባሕር አይታ ሸሸች፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፡፡ … ርእዩከ ማያት እግዚኦ ርእዩከ ማያት ወፈርኁ፤ አቤቱ ውኆች አንተን አይተው ሸሹ፤›› ተብሎ ተነግሯል /መዝ. ፸፮፥፲፮፤ ፻፲፫፥፫/፡፡

ምሳሌው፡- ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ (ምንጩ) አንድ ነው፤ ዝቅ ብሎ በደሴት ይከፈላል፤ ከታች ወርዶ ይገናኛል፡፡ ዮርዳኖስ ከላይ (ነቁ) ምንጩ አንድ መኾኑ የሰውም መገኛው (ምንጩ) አንድ አዳም ለመኾኑ፤ ዮርዳኖስ ዝቅ ብሎ በደሴት መከፈሉ እስራኤል በግዝረት፣ አሕዛብ በቍልፈት ለመለያየታቸው፤ ዮርዳኖስ ከታች በወደብ መገናኘቱ በክርስቶስ ጥምቀት ሕዝብና አሕዛብ አንድ ወግን ለመኾናቸው ምሳሌ ነው፡፡

ዳግመኛም አብርሃም ለአምስቱ ነገሥተ ሰዶም ረድቶ አራቱን ነገሥተ ኮሎዶጎሞር ድል ነሥቶ በተመለሰ ጊዜ ደስ ቢለው ‹‹በመዋዕልየኑ ትፌኑ ቃለከ ወሚመ ታርዕየኒሁ ኪያሃ ዕለተ፤ በዘመኔ ቃልህን (እግዚአብሔር ወልድን) ትልከዋለህን? ወይስ ያቺን የማዳንህን ቀን በዓይኔ ታሳየኝ ይኾን፤›› ብሎ በጠየቀው ጊዜ ‹‹ምሳሌውን ታያለህና ዮርዳኖስን ተሻግረህ ሒድ፤›› ብሎታል፡፡ አብርሃምም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ቢሔድ መልከ ጼዴቅ ኅብስተ አኮቴት፣ ጽዋዓ በረከት ይዞ ተቀብሎታል፡፡ ይኸውም አብርሃም የምእመን፤ ዮርዳኖስ የጥምቀት፤ መልከ ጼዴቅ የካህናት፤ ኅብስተ አኰቴት፣ ጽዋዓ በረከት የሥጋው የደሙ ምሳሌ ነው /ዘፍ. ፲፬፥፲፫-፳፬/፡፡

ኢዮብና ንዕማን በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቀው ከደዌያቸው ድነዋል /፪ኛነገ.፭፥፰-፲፱/፡፡ ኢዮብና ንዕማን የአዳምና የልጆቹ፤ ደዌ የመርገመ ሥጋ፣ የመርገመ ነፍስ፤ ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ኢዮብ፣ ንዕማን፣ ጌታ የተጠመቁበት ዮርዳኖስ ወደቡ አንድ ነው፡፡ እንደዚሁም እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በኋላ በኢያሱ ጊዜ ወደ ምድረ ርስት ሲሔዱ ከዮርዳኖስ ወንዝ ደረሱ፡፡ ታቦቱን የተሸከሙና ልብሰ ተክህኖ የለበሱት ሌዋውያን ካህናት በፊት በፊት ሲጓዙ ታቦቱን የሚያጅቡ ሕዝበ እስራኤል ከታቦቱና ከሌዋውያን ካህናት ሁለት ሺሕ ክንድ ርቀው ዮርዳኖስ ከላይና ከታች ተከፍሎላቸው በየብስ ተሻግረው ኢየሩሳሌም ገብተዋል፡፡ ምእመናንም በማየ ገቦ ተጠምቀው ገነት መንግሥተ ሰማያት ለመግባታቸው ምሳሌ ነው፡፡

ኤልያስም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ብሔረ ሕያዋን ገብቷል፡፡ የኤልያስ ደቀ መዝሙር ኤልሳዕ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዮርዳኖስ ዳር እንጨት ሲቈርጡ መጥረቢያው ከውኀው ውስጥ ወደቀ፡፡ ኤልሳዕ የእንጨት ቅርፊት በትእምርተ መስቀል አዘጋጅቶ ምሳሩ ከወደቀበት ላይ ቢጥልበት የማይዘግጠው ቅርፊት ዘግጦ የዘገጠውን ብረት አንሳፎ አውጥቶታል፡፡ እንደዚሁም ዅሉ በባሕርዩ ሕማም ሞት የሌለበት አምላክ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በዮርዳኖስ ተጠምቆ፣ በቀራንዮ በዕፀ መስቀል ተሰቀሎ፣ ከጎኑ ጥሩ ውኀና ትኩስ ደም አፍስሶ በሲኦል የወደቀው አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ ነው /፪ኛነገ. ፮፥፩–፯/፡፡ ይህንን ዅሉ ምሳሌ ለመፈጸም ጌታችን በዮርዳኖስ ተጠምቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀበት ምሥጢር ምንድን ነው? ቢሉ ዲያብሎስ በአዳምና በሔዋን የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ አገዛዝ ስቃይ አጸናባቸው፡፡ ከዚያም ‹‹‹አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስአዳም የዲያብሎስ ተገዥ፤ ሔዋንም የዲያብሎስ ተገዥ አገልጋዮች ነን› ብላችሁ ስመ ግብርናታችሁን (የተገዥነታችሁን ስም) ጽፋችሁ ብትሰጡኝ መከራውን አቀልላችሁ ነበር›› አላቸው፡፡ እነሱም መከራው የሚቀልላቸው መስሏቸው ‹‹አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ›› ብሎ በማይጠፋ በሁለት ዕብነ ሩካም (ዕብነ በረድ) ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ፤ አንዱን በሲኦል ጥሎት ይኖር ነበር፡፡ በዮርዳኖስ የጣለውን ጌታችን ሲጠመቅ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ እንደ ሰውነቱ ተረግጦ አጥፍቶልናል፡፡ በሲኦል የጣለውንም በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ ነፍሳትን ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ ሲያወጣ አጥፍቶልናል፡፡ ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀበት አንደኛው ምሥጢርም ይህ ነው፡፡

ጌታችን ጥምቀቱን በውኀ ያደረገው በሌላ ያላደረገው ስለምንድን ነው ቢሉ ትንቢቱ፣ ምሳሌው ሊፈጸም፤ ትንቢት፡- ‹‹ወእነዝኃክሙ በማይ ወትነጽሑ፤ ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ፤ እናንተም ትጠራላችሁ፤›› ተብሎ ተነግሯል /ሕዝ.፳፮፥፳፭/፡፡ ምሳሌ፡- ውኀ ለዅሉ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለ ውኀ መኖር የሚችል የለም፡፡ ጥምቀትም ለዅሉም የሚገባ ሥርዓት ነው፡፡ ያለ ጥምቀት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይቻልምና፡፡ ውኀ መልክ ያሳያል፤ መልክ ያለመልማል (ያጠራል)፡፡ ጥምቀትም መልክዐ ነፍስን ያሳያል፤ መልክዐ ነፍስን ያለመልማልና (ያጠራልና)፡፡

መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥበት አየ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መውረዱም ምሥጢር አለው፡፡ ርግብ ኃዳጊተ በቀል ናት፤ መንፈስ ቅዱስም ኃዳጌ በቀል ነውና፡፡ ርግብ በኖኅ ጊዜ ‹‹ሐጸ ማየ አይኅ ነትገ ማየ አይኅ፤ የጥፋት ውኀ ጎደለ›› ስትል ቆጽለ ዕፀ ዘይት ይዛ ተገኝታለች፡፡ መንፈስ ቅዱስም ተስፋ መስቀልን ያበሥራልና፡፡ ጥምቀቱን በቀን ያላደረገው በሌሊት ያደረገው ስለ ምን ነው ቢሉ በቀን አድርጎት ቢኾን መንፈስ ቅዱስ በቁሙ ርግብ ነው በተባለ ነበርና፤ አሁንስ ርግብ አለመኾኑ መንፈስ ቅዱስ መኾኑ በምን ይታወቃል ቢሉ ጌታ የተጠመቀው ከሌሊቱ በዐሥረኛው ሰዓት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ተሐዋስያን ወፎች (ርግቦች) ከየቦታቸው አይወጡምና መንፈስ ቅዱስ መኾኑ በዚህ ይታወቃል፡፡

መንፈስ ቅዱስም መውረዱ ከውኀው ከወጣ፣ ከዮሐንስ ከተለየ በኋላ ነው፡፡ ከውኀው ውስጥ ሳለ ወርዶ ቢኾን ለቀድሶተ ማያት ነው የወረደው ባሉት ነበርና፡፡ ከዮሐንስ ጋርም ሳለ ወርዶ ቢኾን ለክብረ ዮሐንስ ወረደ ባሉት ነበርና፡፡ ረቦ ወርዷል ያሉ እንደ ኾነ አብ ምሉዕ ነው፤ አንተም ምሉዕ ነህ፤ እኔም ምሉዕ ነኝ ሲል፡፡ አሰይፎ ወርዷል ያሉ እንደ ኾነ የብሉየ መዋዕል የአብ ሕይወት ነኝ፤ የአንተም ሕይወት ነኝ፤ እኔም ብሉየ መዋዕል ነኝ ሲል፡፡ ወርዶ ራሱን ቆንጠጥ አድርጎ ይዞታል ቢሉ አብ አኃዜ ዓለም ነው፤ አንተም አኃዜ ዓለም ነህ፤ እኔም አኃዜ ዓለም ነኝ ሲል፡፡ ምሥጢሩም እናንተም ብትጠመቁ መንፈስ ቅዱስ ይወርድላችኋል ለማለት፣ አብነት ለመኾን ነው፡፡

‹‹ወናሁ መጽአ ቃል እምሰማይ ዘይብል ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ፤ ለተዋሕዶ የመረጥኩት በእርሱ ህልው ኾኜ ልገለጥበት የወደድኩት የባሕርይ ልጄ ይህ ነው፤›› የሚል ቃል ከወደ ሰማይ ተሰማ፡፡ ይህም አብ የተናገረበት ቃል ያው የሚጠመቀው አካላዊ ቃል ነው እንጂ ሌላ ቃል አይደለም፡፡ የሥላሴ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ አንድ ነውና፡፡ አብ ልብ፤ ወልድ ቃል፤ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ በመኾን አንድ አምላክ ነውና፡፡ ‹‹አብኒ ልቡናሆሙ ለወልድ ወለመንፈስ ቅዱስ ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ ወመንፈስ ቅዱስኒ እስትንፋሶሙ ለአብ ወለወልድ፤ አብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ልቡናቸው ነው፡፡ ወልድም ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ለአብ ለወልድ ሕይወታቸው ነው፤›› በማለት ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት እንደ ተናገረው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀውም በሠላሳ ዓመቱ ነው /ሉቃ. ፫፥፳፫/፡፡ በሠላሳ ዓመቱ የተጠመቀበት ምሥጢርም አዳም የሠላሳ ዓመት፤ ሔዋን የዐሥራ አምስት ዓመት ሰው ኾነው ተፈጥረው አዳም በዐርባ ቀን፣ ሔዋን በሰማንያ ቀን ከሥላሴ የተቀበሉትን ልጅነት በምክረ ከይሲ ዕፀ በለስን በልተው አስወስደው ነበረና በሠላሳ ዓመቱ ተጠምቆ መልሶላቸዋል፡፡ በሠላሳ ዓመት የመጠመቁ ምሥጢር ይህ ሲኾን እኛ ዛሬ ወንዶች በዐርባ ቀን፣ ሴቶች በሰማንያ ቀን በዕለተ ዓርብ ከቀኝ ጎኑ በፈሰሰው ማየ ገቦ ተጠምቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ሁለተኛ የምንወለድበት ምክንያትም አዳም በዐርባ ቀኑ፣ ሔዋን በሰማንያ ቀኗ ከሥላሴ ያገኙትን ልጅነት መሠረት በማድረግ ነው /ኩፋ. ፬፥፱/፡፡ የምንጠመቀውም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡ ‹‹ወእንዘ ታጠምቅዎሙ በሉ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤ ስታጠምቋቸውም በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው፤›› እንዲል /ማቴ. ፳፰፥፲፱/፡፡

ዛሬም ታቦታቱን ወደ ጥምቀተ ባሕር በማውረድ በዓለ ጥምቀቱን ለሚያከብሩ ክርስቲያኖች በሙሉ ከታቦታቱ ሁለት ሺሕ ክንድ ርቀው መከተል እንዲገባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተብሎ ተገልጿል፤ ‹‹ሕዝቡን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ተከተሉት፡፡ በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሺሕ ክንድ ይኹን፡፡ በዚህ መንገድ በፊት አልሔዳችሁበትምና፤ የምትሔዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ፤›› /ኢያ.፫፥፩–፲፯/፡፡

ይህ ኃይለ ቃል ዛሬ ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርደው ለማደራቸው መነሻ ትምህርት ነው፡፡ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀትም ጌታችን ከተጠመቀበት ከ፴ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ሲከበር ይኖራል፡፡

ከበዓለ ጥምቀቱ ረድኤት፣ በረከት ይክፈለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያም እና ታቦተ ጽዮን – ካለፈው የቀጠለ

ኅዳር ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዲያቆን ሽመልስ መርጊያ

new

አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ባቀረበ ጊዜ፣ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድኅት ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ እንደሚያድናቸው በምሳሌው ተረድቶ ተደስቶ ነበር፡፡ ጌታችን ይህን ሲያስረዳን ‹‹አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤትን አደርገ፡፡ አየም፤ ደስም አለው፤›› ብሎ ገለጠልን /ዮሐ.፰፥፶፮/፡፡ እንደ ልቤ የተባለው ንጉሥ ዳዊት በቃል ኪዳኗ ታቦት ፊት በደስታ መዘመሩም እግዚአብሔር ቃል የአዳም ተስፋ ከኾነችው ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ዓለምን እንደሚያድን በማስተዋሉ ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ይህንን እውነት መስክረዋል፡፡

ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ሲል ይናገራል፤ ‹‹ከአዳም ጎን በተገኘችው አንዲት ዐጥንት ምክንያት ሰይጣን ከአዳም ማስተዋልን አራቀ፡፡ ነገር ግን ከእርሱ አብራክ በተገኘችው በቅድስት ድንግል ማርያም ምክንያት በእርሱ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን እንደ ዳጎን ተንኮታኩቶ ወደቀ፡፡ በታቦቱ በተመሰለችው በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ባደረው በጌታችን በመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የድል ዐዋጅ ታወጀ፡፡ በቃል ኪዳኗ ታቦት ሥር ዳጎን ተሰባብሮ እንደተገኘ እንደዚሁ ክፉው ሰይጣን በታመኑበት ፊት ድል ተነሣ፡፡ ለነገር ጥላ አለውና እግዚአብሔር የማደሪያው ምሳሌ በኾነችው በቃል ኪዳኗ ታቦት ኃይሉን በዳጎን ጣዖት ላይ እንዳሳየ እንደዚሁ አጥፊያችንን በማጥፋት እግዚአብሔር ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ በኃጢአት ምክንያት በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ሰይጣንን ድል ነሳው፡፡ የእግዚአብሔር በግ በኾነው በክርስቶስ እኛን ያዳነን እግዚአብሔር አብ ስሙ የተመሰገነ ይኹን፡፡››

ቅዱስ ጀሮም እንደዚሁ ‹‹ቅድስት ድንግል ማርያም ለጌታዋ በእርግጥ እውነተኛ አገልጋዩ ነበረች፡፡ እርሷ እንደ ቃል ኪዳኗ ታቦት በሕሊናዋ ከእግዚአብሔር ሕግጋት ውጪ ሌላ ምንም ሐሳብ አልነበራትም፡፡ በውስጥም በውጪም ነውር የሌለባት ንጽሕት ናት፡፡ እንደ ቃል ኪዳኗ ታቦት በውጪም በውስጥም በቅድስና የተጌጠችና ሕጉንም ጠብቃ የተገኘች የክርስቶስ ሙሽራ ናት፡፡ በቃል ኪዳን ታቦቱ ውስጥ ከሕጉ ጽላት ውጪ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ እንዲሁ አንቺም ቅድስት ሆይ በሕሊናሽ ምንም ነውር የሌለብሽ ንጽሕት ነሽ›› ሲል የእመቤታችንን ንጽሕና አስረድቷል፡፡ እስክንድርያዊው ዲዮናስዮስም ‹‹ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካህን ይኾን ዘንድ በሰው እንዳልተመረጠ እንደዚሁ የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን የእርሱ ማደሪያ ይኾን ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ ማደሪያ የቅድስት ድንግል ማርያምን ቅድስናና ንጽሕና ያውጅ ዘንድ ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ታትሞአል፤ ታትሞም ለዘለዓለም ይኖራል›› ይላል፡፡

የሚላኑ ቅዱስ አምብሮስ ደግሞ ‹‹ነቢዩ ዳዊት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት በደስታ እየዘለለ ለአምላኩ ዘመረ፡፡ የቃል ኪዳኗ ታቦት የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌና ጥላ ካልኾነች የማን ምሳሌና ጥላ ልትኾን ትችላለች? ይህቺ ታቦት በውስጧ የሕጉን ጽላት እንደ ያዘች እንደዚሁ ቅድስት ድንግል ማርያምም የሕጉ ባለቤት የኾነውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማኅፀኗ ተሸክማዋለች፡፡ የቃል ኪዳኗ ታቦት የኦሪትን ሕግ በውስጧ እንደያዘች አማናዊቱ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያምም ወንጌል የተባለው ክርስቶስን ይዛዋለች፡፡ የመጀመሪያይቱ ታቦት የእግዚአብሔር ትእዛዛትን የያዘች ስትኾን ሁለተኛይቱና አማናዊቱ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም ግን እግዚአብሔር ቃልን በውስጧ ተሸክማዋለች፡፡ የቃል ኪዳን ታቦቱ በእርግጥ በውስጥም በውጪም በወርቅ የተለበጠ ነበር፡፡ አማናዊቱ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም ግን በውስጥም በውጪም በድንግልና የተጌጠች ናት፡፡ የቃል ኪዳኗ ታቦት የተጌጠችው ምድራዊ በኾነ ወርቅ ሲኾን አማናዊቱ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ሰማያዊ በኾኑ ጸጋዎች የተሸለመች ናት፤›› በማለት እመቤታችን የታቦተ ጽዮን ምሳሌ ስለ መኾኗ አስተምሮናል፡፡

አባታችን አዳም ድኅነቱ የሚፈጸመው በሚስቱ ምክንያት እንደ ኾነ ተረድቶ ለሚስቱ ‹‹ሔዋን›› የሚል ስም እንደ ሰጣት ንጉሥ ዳዊትም በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሚድን በመረዳቱ እመቤታችንን ‹‹አምባዬ መጠጊያ ነሽ›› ሲላት ‹‹ጽዮን›› በሚል ስም እመቤታችንን መጥራቱን ከመዝሙሩ ለመረዳት እንችላለን፡፡ ይህን ይዘው ብዙዎች ነቢያት ስለ ድንግል ማርያም ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም ተጠቅመዋል፡፡ ‹‹ጽዮን›› ማለት ትርጕሙ ‹‹አምባ፣ መጠጊያ›› ማለት ነውና፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳይያስ የራሳቸውን ሥርዐትና ሕግ ለማስጠበቅ ሲሉ በክርስቶስ ስላላመኑ አይሁድ ሲናገር፡- ‹‹እነሆ በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ ዐለት አኖራለሁ፤›› አለ /ኢሳ.፰፥፮፬፤ ፳፰፥፲፮/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ትንቢት ስለ ክርስቶስ የተነገረ መኾኑን በሮሜ መልእክቱ ጽፎልናል /ሮሜ.፱፥፴፪-፴፫/፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስና ቅዱስ ጳውሎስ ጽዮን ያሏት ቅድስት ድንግል ማርያምን መኾኑንም በዚህ ኃይለ ቃል ለመረዳት እንችላለን፡፡ የማሰናከያ ዐለት የተባለው ክርስቶስ መኾኑንም ‹‹እነሆ የብዙዎች ልብ ሐሳብ ይገለጥ ዘንድ ይህ ለእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሹሞአል፤›› በሚለው ኃይለ ቃል ማረጋገጥ ይቻላል /ሉቃ.፪፥፴፬-፴፭/፡፡ ስለዚህ የማሰናከያ ዐለት የኾነውን ክርስቶስን ፀንሳ የወለደችው ቅድስት ድንግል ማርያም ጽዮን ተብላ መጠራቷንም በእነዚህ ጥቅሶች እንረዳለን፡፡

ቅዱስ ዳዊትና ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ከጽዮን ታዳጊ ይመጣል፤ ከያዕቆብም ኃጢአትን ያርቃል፤›› /መዝ.፲፫፥፲፤ ኢሳ.፶፱፥፳/ በማለት ስለ ክርስቶስ የዓለም መድኀኒትነት አስቀድመው ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ይህን ምሥጢርም ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ ፲፩፥፳፮ ላይ ጠቅሶታል፡፡ በዚህም ቦታ ጽዮን የተባለችው ቅድስት ድንግል ማርያም መኾኗን ለማስተዋል እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ጌታችን የተወለደው ከእመቤታችን ነውና፡፡ ‹‹መድኀኒት›› የተባለው ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑንም ‹‹… በዳዊት ከተማ መድኀኒት እርሱ ክርስቶስ ተወለደ፤›› /ሉቃ.፪፥፲/ በማለት ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ገለጾልናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ኢየሱስ›› ማለት ‹‹መድኀኒት›› ማለት ነው /ማቴ.፩፥፳፩/፡፡ በዚህ መሠረት ነቢያቱ ‹‹መድኀኒት ከጽዮን ይወጣል፤›› ሲሉ መናገራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽዮን ከተባለችው ከቅድስት ድንግል ማርያም ይወለዳል ማለታቸው እንደ ኾነ ግልጽ ነው፡፡

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ‹‹ዓለም ሁለት ዓይነት ሰዎች  የሚኖሩባት ሥፍራ ናት፡፡ አንደኛው ሰው የሔዋን ዐይነት ዐይኖች ስላለው በእነዚህ ዐይኖቹ ድንጋዩንና እንጨቱን አምላክ ነው እያለ ይገዛለታል፡፡ ሌላኛው ደግሞ የቅድስት ድንግል ማርያም ዓይነት ዐይኖች ስላሉት ክርስቶስ ኢየሱስን ይመለከታል ለእርሱም ይገዛል›› ብሎ ያስተምራል /ውርስ ትርጕም/፡፡ እኛም የእመቤታችን ዓይነት ዐይኖች ስላሉን፤ እይታችንም ፍጹም፣ ንጹሕና በማስተዋል ላይ የተመሠረተ ስለ ኾነ ታቦታትን ስንመለከት እመቤታችንን፤ እመቤታችንን ስንመለከት ደግሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንመለከተዋለን፡፡ ምእመናን በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች በመኾናችን በጸጋ የክርስቶስ ወንድሞች ተብለን ተጠርተናል፡፡ ይህም የቅድስት ድንግል ማርያም ልጆች መኾናችንን ያመላክታል፡፡ ‹‹ወላጁን የሚወድ ከእርሱ የተወለደውንም ይወዳል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /፩ኛዮሐ.፭፥፩/ እኛ ኦርቶዶክሳውያንም ቅድስት ድንግል ማርያምን ስለምንወዳት ከእርሷ በሥጋ የተወለደውን ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንወደዋለን፡፡ እግዚአብሔር አብን እንደምንወድና እንደምናመልከው ዅሉ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስንም እንደ ባሕርይ አባቱ እኩል እንወደዋለን፤ እናመልከዋለን፡፡ በአጠቃላይ ሥላሴን እንደምንወድ ዅሉ ከሥላሴ አብራክ የተወለዱ ክርስቲያኖችንና በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረውን የሰውን ፍጥረት እንወዳለን፡፡

በአጠቃላይ ስለ ታቦተ ጽዮን የተጻፉ ዅሉ እግዚአብሔር ቃል ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ለፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጥላና ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በብሉይ ኪዳን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ተአምራት ለድንግል ማርያምና ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመስጠት ለልጆቿ ታስተምራለች፡፡ ነገር ግን ጽዮን የሚል ንባብ ዅሉ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የሚናገር ነው ማለታችን አይደለም፡፡ ከላይ እንደ ተመለከትነው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታችን ሲናገር ስለ እርሱ የተነገሩ ምሥጢራን ብቻ መርጦ እንደ ተጠቀመና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጽዮን የሚል ምንባብ በሙሉ ስለ ጌታችንና ስለ እመቤታችን የተጻፈ ነው ብሎ እንዳልተረጐመ ዅሉ፣ እኛም ጽዮን የሚል ቃል ባገኘን ቍጥር ስለ ድንግል ማርያም የተጻፈ ነው ብለን አንተረጕምም፡፡ እንደዚህ የምንል ከኾነ ግን ትልቅ ስሕተት ውስጥ እንገባለንና፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት ያሳትፈን፡፡ የእግዚአብሔር አብ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት በዅላችን ላይ ይደር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያም እና ታቦተ ጽዮን – የመጀመሪያ ክፍል

ኅዳር ፳ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዲያቆን ሽመልስ መርጊያ

new

በየዓመቱ ኅዳር ፳፩ ቀን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙ ታላላቅ ተአምራት የሚታሰቡበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የታቦተ ጽዮንን ተአምራት እግዚአብሔር ቃል ቅድስት ድንግል ማርያምን ታቦቱ አድርጎ ከፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጋር በማነጻጸር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ድርሻ በስፋት ታስተምራለች፡፡ ለምሳሌ እስራኤላውያን ባሕረ ዮርዳኖስን በአቋረጡበት ወቅት ታቦተ ጽዮንን የተሸከሙ ካህናት እግራቸው የዮርዳኖስን ባሕር በመንካቱ ባሕሩ ለሁለት ተከፍሎ ነበር፡፡ ይህንን ታሪክም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድና ጥምቀትን በመመሥረት ከሰይጣን ባርነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት እንዳሸጋገረን በማመሥጠር ቤተ ክርስቲያናችን ታስተምርበታለች፡፡ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤላውያን ጋር ውጊያ በገጠሙበት ወቅት ታቦተ ጽዮንን ከእስራኤላውያን ማርከው ዳጎን በሚባለው ቤተ ጣዖታቸው ውስጥ አኑረዋት በነበረ ጊዜ ታቦቷ የዳጎንን ምስል አንኮታኩታ ጥላው ነበር፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ታሪክ እንደ ምሳሌ በመጠቀም ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ከአምልኮ ጣዖት ወጥተን አንድ አምላክን ወደ ማምለክ ስለ መመለሳችንና በእመቤታችን ምክንያት ስለ ተደረገልን የእግዚአብሔር ቸርነት ትምህርት ትሰጥበታለች፡፡ እኛም በዛሬው ዘግጅታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማናዊቷ ታቦተ ጽዮን መኾኗን የሚያስቃኝ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፤

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ካወጣቸው በኋላ የአምልኮ ሥርዐታትን ይፈጽሙበት ዘንድ የምስክሩን ድንኳን፣ የቃል ኪዳኗ ታቦትንና ለአምልኮ ሥርዐቱ ማከናወኛ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትን እንዲሠሩ አዝዟቸው ነበር፡፡ ከቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥም በእግዚአብሔር ጣት ዐሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉበት የሕጉ ጽላት፤ ዐርባ ዓመት ሙሉ እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ የተመገቡትን መና የያዘች መሶበ ወርቅ፤ አሮን ለክህነት አገልግሎት ስለ መመረጡ ምስክር የኾነችው፣ ለምልማና ፍሬ አፍርታ የተገኘችው የአሮን በትር ይገኙባታል /ዕብ.፱፥፬/፡፡ ደብተራ ድንኳኗንና በውስጧ የሚገኙ ንዋየተ ቅድሳትን እግዚአብሔር በሙሴ ሲያሠራ ለሰማያዊው ምሥጢር ምሳሌና ጥላ ናቸውና ተጠንቅቆ እንዲሠራቸው አዝዞት ነበር /ዕብ.፰፥፭/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህችን ድንኳን ‹‹የአገልግሎት ሥርዐታት የሚፈጸምባት ፊተኛይቱ ድንኳን›› ብሎ ይጠራታል፡፡ በዚህ መሠረት ደብተራ ድንኳኗና በውስጧ ያሉ ንዋያተ ቅድሳት ለሰማያዊው ምሥጢር ምሳሌና ጥላ እንደ ኾኑ እንረዳለን፡፡ የደብተራ ድንኳኗ ምሳሌ የኾችው ሰማያዊቱ ስፍራም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በውስጧ አማናዊውና ሰማያዊው ምሥጢረ መለኮት ይፈጸምባታልና፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ ስለ ኾነች፤ ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያሰጥ ምሥጢርም በውስጧ ስለሚከናወንባት በእርግጥም ሰማያዊ ስፍራ ናት፡፡

ታቦተ ጽዮን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች፡፡ ይህን ለመረዳት ግን ስለ ታቦተ ጽዮን አሠራርና መንፈሳዊ ትርጉም አስቀድመን ልንረዳ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ታቦተ ጽዮንን እንዲሠራ ብልሃትን፣ ጥበብን፣ ማስተዋልን፣ ዕውቀትን ይለይ ዘንድ መንፈሱን ያሳደረበትን ከይሁዳ ወገን የኾነውን ባስልኤልን መረጠ /ዘፀ.፳፭፥፱/፡፡ እርሱም እግዚአብሔር በሰጠው ማስተዋል ከማይነቅዝ እንጨት ርዝመቷ ሁለት ክንድ ተኩል፤ ወርዱዋ አንድ ክንድ ተኩል፤ ቁመቷ አንድ ክንድ ተኩል እንዲኖራት አድርጎ ታቦቷን ሠራት፡፡ በመቀጠል በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ ለበጣት፣ ከታቦቷም ዙሪያ የወርቅ አክሊልን አደረገላት፡፡ ካህናት ታቦተ ጽዮንን ለመሸከም እንዲረዳቸውም በአራቱም መዓዘናት በወርቅ የተሠሩ ቀለበቶችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገቡ ሁለት መሎጊያዎችን ሠራ፡፡ ከጥሩ ወርቅም የስርየት መክደኛውን በቃል ኪዳን ታቦቷ ላይ በርዝመቷና በወርደዋ ልክ ሠራ፡፡ የስርየት መክደኛውን እንዲጋርዱት አድርጎም ጥሩ ከኾነ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ኪሩቤልን ሥሎ በስርየት መክደኛው ግራና ቀኝ አስቀመጣቸው፡፡ እነዚህ በጥሩ ወርቅ የተሠሩት ሁለቱ ኪሩቤል ፊታቸው ወደ ስርየት መክደኛው ኾኖ እርስ በእርሳቸው እንዲተያዩ ተደርገው የተሠሩ ናቸው፡፡ በዚህ በስርየት መክደኛው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል እግዚአብሔር ለሙሴ እየተገለጠ ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር በግልጽ ያነጋግረው ነበር፤ ለሕዝቡም በደመና ዐምድ ይታያቸው ነበር /ዘፀ.፰፥፲፩፤ ፳፭፥፳፪-፴፫/፡፡

ወደ ምሥጢሩ ትርጓሜ ስንመለስም ታቦተ ጽዮን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ስትኾን፣ በውስጧ የያዘችው የሕጉ ጽላትም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቷ ከማይነቅዝ እንጨት መሠራቷ የእመቤታችንን ንጽሕና የሚያመለክት ሲኾን፣ በውጪም በውስጥም በጥሩ ወርቅ መለበጧ ደግሞ ቅድስናዋንና በሁለት ወገን ድንግል መኾኗን የሚያስረዳ ነው፡፡ ታቦተ ጽዮን በግራና በቀኝ በኩል በተዘጋጁ አራት ከወርቅ የተሠሩ ቀለበቶች ነበሯት፤ በእነዚያ የወርቅ ቀለበቶች ውስጥም ሁለት መሎጊያዎች ይገቡባቸው ነበር፡፡ ታቦቷን ለማንቀሳቀስ ባስፈለገ ጊዜ አራት ሌዋውያን ካህናት በመሎጊያዎቹ ይሸከሟታል፡፡ ይህ ሥርዐት በሰማያትም የሚታይ እውነታ ነው፡፡ የጌታን መንበር ገጸ ሰብእ፣ ገጸ ንሥር፣ ገጸ ላህምና ገጸ አንበሳ ያላቸው አርባዕቱ እንስሳት ይሸከሙታልና /ኢሳ.፮፥፩-፭፤ ሕዝ.፩፥፩-፲፮/፡፡ ለአማናዊቷ ታቦት ለቅድስት ድንግል ማርያምም ሰላምን የሚያወሩ፣ መልካም የምሥራችንም የሚናገሩ፣ መድኀኒትንም የሚያወሩ፣ ጽዮንንም ‹‹አምላክሽ ነግሦአል›› የሚሉ፣ እግሮቻቸው በተራሮች ላይ እጅግ ያማሩ የእርሷንና የጌታችንን ስም ተሸክመው ወንጌልን ለዓለም የሚሰብኩ ኦርቶዶክሳውያን መምህራን አሏት /ኢሳ.፶፪፥፯/፡፡ የስርየት መክደኛው መቀመጫው የንጹሐን አንስት፣ መክደኛው የንጹሐን አበው፣ ግራና ቀኙ የሐናና የኢያቄም ምሳሌ ነው፡፡ በክንፎቻቸው የጋረዱት  ኪሩቤልም የጠባቂው መልአክ ቅዱስ ሚካኤልና የአብሣሪው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ምሳሌዎች ናቸው፡፡

የስርየት መክደኛው ስርየቱ የሚፈጸምበት ስፍራ ቢኾንም ነገር ግን በዚህ ቦታ ምንም ዓይነት መሥዋዕት አይቀርብም ነበር፡፡ ይህም በጊዜው አማናዊው መሥዋዕት ገና እንዳልተሠዋ ያስገነዝበናል፡፡ ይህ ስፍራ እግዚአብሔር ለሙሴ የሚገለጥበት ቦታ ነው፤ ከእርሱ ውጪ ሌላ ነገር በእዚያ ላይ ማረፍ አይችልም ነበር፡፡ ከዚህም የምናስተውለው አንድ ምሥጢር አለ፤ ይኸውም እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን ሊፈጽም ሰው በኾነ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብበት ልዩ ስፍራ እንዳዘጋጀ ያመላክተናል፡፡ ይህ ስፍራ አማናዊ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ እንደሚያስፈልግ የሚያስገነዝብ ስፍራ ነው፡፡ ይህን ለማመልከትም ለኃጢአት ስርየት የቀረበው መሥዋዕት ከታረደ በኋላ ካህኑ ደሙን በጣቱ እየነከረ ሰባት ጊዜ በስርየት መክደኛው አንጻር በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ይረጨው ነበር /ዘሌ.፬፥፮/፡፡ ነገር ግን ይህ ደም ከስርየት መክደኛው ላይ አያርፍም ነበር፤ ምክንያቱም በዚህ ስፍራ መቅረብ የሚገባው አማናዊው መሥዋዕት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነውና፡፡

ይህ የስርየት መክደኛ ለእኛ የሚያስተላለፈው ተጨማሪ መልእክትም አለው፡፡ ይኸውም አማናዊው መሥዋዕት ክርስቶስ መሥዋዕት ኾኖ ዓለምን ማዳኑ እንደማይቀርና መሥዋዕቱ የሚቀርብበት ስፍራም በቅድስተ ቅዱሳኑ (ቤተ መቅደሱ) ውስጥ እግዚአብሔር በምሕረት በሚገለጥበት በቃሉ ማደሪያ በጽላቱ ላይ መኾን እንደሚገባው ያስገነዝበናል /ዕብ.፬፥፲፮/፡፡ ይህም እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ሚልክያስ ላይ አድሮ ‹‹ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይኾናልና በየስፍራውም ስለ ስሜ ዕጣንን ያጥናሉ፤ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፤›› /ሚል.፩፥፲፩/ በማለት እንደ ተናገረው የስርየት መክደኛው አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ቍርባንን ለምትፈጽምበት ጽላት ወይም ታቦት ምሳሌ መኾኑን ያሳየናል፡፡ የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱት በጥሩ ወርቅ የተሠሩት የኪሩቤል ምስሎችም አማናዊው መሥዋዕት በሚሠዋበት ጊዜ በዙሪያው ረበው የሚገኙ የመላእክት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችን እንዳስተማሩን ሁለቱ ኪሩቤል የተባሉት ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ናቸው፡፡ ይህን ለማስገንዘብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በመንበረ ታቦቱ ላይ ምስለ ፍቁር ወልዳ እንዲቀመጥ ታዝዛለች፡፡ ምስለ ፍቁር ወልዳን  ላስተዋለ ሰው በትክክል የታቦተ ጽዮንን መንፈሳዊ ትርጕም ይረዳል፡፡

ታቦተ ጽዮን ከሌሎች የብሉይ ኪዳን ንዋያተ ቅድሳት በተለየ መልኩ እጅግ ግሩም የኾነ ምሥጢርን በውስጧ ይዛለች፡፡ ይህን ድንቅ ምሥጢር ለመረዳትም አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑ ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ጽዮን ከተማ ባስመጣበት ወቅት በታቦቷ ፊት በሙሉ ኃይሉ በደስታ እየዘለለ ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ መዝሙርን አቅርቦ ነበር /፪ሳሙ.፮፥፲፪-፲፯/፡፡ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሚኾን ድርጊት በሐዲስ ኪዳንም ተፈጽሟል፡፡ ይኸውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅድስት ኤልሳቤጥ ሰላታ በሰጠቻት ጊዜ የስድስት ወር ፅንስ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የእመቤታችንን የሰላምታ ድምፅ በሰማ ጊዜ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ኾኖ በደስታ ዘሏል (ሰግዷል) /ሉቃ.፩፥፵፬/፡፡ ቅዱስ ዳዊት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት እየተደሰተ ለአምላኩ የምስጋና ቅኔን መቀኘቱም ለሰው ልጆች ዅሉ የመዳናችን ምክንያት የኾነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን በቃል ኪዳኗ ታቦት በኩል አስቀድሞ በዓይነ ሕሊና ስለ ተመለከታቸው ነበር፡፡

ይቆየን፡፡

ፀአተ ክረምት (ዘመነ ክረምት የመጨረሻ ክፍል)

መስከረም ፳፭ ቀን ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! ከአሁን በፊት ዘመነ ክረምትን የሚመለከት ትምህርት በአምስት ተከታታይ ክፍል ስናቀርብላችሁ ቆይተናል፡፡ ለመከለስ ያህል ‹‹ክረምት›› የሚለው ቃል ከረመ፣ ከረመ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም የዝናም፣ የአዝርዕት፣ የአረም ጊዜ፤ ዕፅዋት፣ አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር በአረንጓዴ ዕፀዋትና በልምላሜ የምታሸበርቅበት ወቅት ማለት መኾኑን፣ ከሰኔ ፳፭ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ ዘመነ ክረምት እንደሚባል፣ ዘመነ ክረምት ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት፤ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን (ምግብን) ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይና የሚያሳውቅ ዘመን እንደ ኾነ፤ ይህ ዘመነ ክረምትም በሰባት ንዑሳን ክፍሎች እንደሚመደብ፣ ይኸውም፡-

፩ኛ ከሰኔ ፳፭ እስከ ሐምሌ ፲፱ ቀን ያለው ጊዜ ዘርዕ፣ ደመና፤

፪ኛ ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፲ ቀን ያለው ጊዜ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል፤

፫ኛ ከነሐሴ ፲- ፳፰ ቀን ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ፤

፬ኛ ከነሐሴ ፳፰ እስከ ጳጉሜን ፭/፮ ቀን ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባህ፣ ብርሃን፣ መዐልት፤

፭ኛ ከመስከረም ፩-፰ ቀን ዮሐንስ፤

፮ኛ ከመስከረም ፱-፲፭ ቀን ፍሬ እንደሚባል ከ ‹‹በአተ ክረምት›› ጀምሮ እስከ ‹‹ዘመነ ፍሬ›› ድረስ ባሉት የዘመነ ክረምት ጽሑፎቻችን ተመልክተናል፡፡

‹‹ዘመነ ፍሬ›› በሚል ርእስ ባቀረብነው በክፍል አምስት ዝግጅታችንም ከመስከረም ፱ – ፲፭ ቀን ያለው ክፍለ ክረምት ‹ፍሬ› እንደሚባልና ይኸውም ልዩ ልዩ አዝርዕት በቅለው፣ አድገው፣ አብበው ለፍሬ የሚደርሱበት፤ የሰው ልጅ፣ እንስሳትና አራዊትም ጭምር የዕፀዋቱን ፍሬ (እሸት) የሚመገቡበት ወቅት እንደኾነ፤ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚቀርቡ ምንባባትና ትምህርቶችም ይህንኑ ምሥጢር እንደሚዳስሱ በማስገንዘብ የምእመናንን ሕይወት ከዕፀዋትና ከፍሬ ጋር በማመሳሰል ትምህርት ማቅረባችን የሚታዎስ ነው፡፡ በዛሬው የ‹‹ፀአተ ክረምት›› ዝግጅታችንም የመጨረሻውን የክረምት ክፍለ ጊዜ የሚመለከት አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

ከመስከረም ፲፮ – ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ፯ኛው የክረምት ክፍለ ጊዜ መስቀል በመባል የሚታወቅ ሲኾን ይኸውም ፀአተ ክረምትና በአተ መጸው የሚሰበክበት፣ ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን የሚቀርቡ ትምህርቶች ነገረ መስቀሉን የተመለከቱ ናቸው፡፡ ማለትም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ድኅነት ሲል በፈቃዱ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ስለ መሞቱ፣ በሞቱም ዓለምን ስለ ማዳኑ፣ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ስላፈሰሰበት ዕፀ መስቅሉ የተቀደሰ ስለ መኾኑ፣ በምእመናን ዘንድም ትልቅ ትርጕም ያለው ስለ መኾኑ ከሌሎች ጊዜያት በላይ በስፋት የሚነገረውና ትምህርት የሚሰጠው በዚህ ወቅት ነው፡፡

ከዚሁ ኹሉ ጋርም በአይሁድ ቅናት በጎልጎታ ለ፫፻ ዓመታት ያህል ተቀብሮ የቆየው የጌታችን ዕፀ መስቀልን ለማውጣት በንግሥት ዕሌኒ አማካይነት ቍፋሮ መጀመሩ፣ መስቀሉ ከወጣ በኋላም በዐፄ ዳዊትና በልጃቸው በዘርዐ ያዕቆብ ጥረት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ደብረ ከርቤ መቀመጡ የሚዘከረው በእነዚህ ዐሥር የፀአተ ክረምት ዕለታት ውስጥ ነው፡፡ ኹላችንም ሕዝበ ክርስቲያን ይህንን የመስቀሉን ነገር በልቡናችን ይዘን በክርስትናችን ምክንያት የሚገጥመንን ልዩ ልዩ ዓይነት ፈተና በትዕግሥት ማለፍ ይጠበቅብናል፡፡

‹‹ፀአተ ክረምት›› የሚለው የግእዝ ቃላት ጥምረት ‹‹የክረምት መውጣት›› የሚል ትርጕም አለው፡፡ ይህም ከመስከረም ፲፮ – ፳፭ ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል፡፡ የፀአተ ክረምት መጨረሻ የሚኾነውም መስከረም ፳፭ ቀን ነው፡፡ የክረምት መውጣት ሲባል ለዘመነ ክረምት የተሰጠው ጊዜ በዘመነ መጸው መተካቱን ለማመልከት እንጂ ክረምት ተመልሶ አይመጣም ለማለት አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወት እስከሚያበቃበት እስከ ኅልፈተ ዓለም ድረስ የወቅቶች መፈራረቅም አብሮ ይቀጥላል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ይህንን የወቅቶች መፈራረቅ ለመግለጽ ነው ‹‹መግባት፣ መውጣት›› እያሉ በክፍል የሚያስቀምጧቸው፡፡

አንድ የጊዜ ክፍል (ወቅት) ሲያልፍ ሌላው ይተካል፡፡ ‹‹ሲሞት ሲተካ፣ ሲፈጭ ሲቦካ›› እንደሚባለው የሰው ልጅ ሕይወትም እንደዚሁ ነው፡፡ አንደኛው ሲሞት ሌላኛው ይወለዳል፤ አንደኛው ሲወለድ ሌላኛው ይሞታል፡፡ ወቅቶች የጊዜ ዑደት እንደ መኾናቸው ለሰው ልጅ ምቾት እንጂ ለራሳቸው ጥቅም የተዘጋጁ ሕያዋን ፍጥረታት አይደሉም፡፡ በመኾኑም ራሳቸውን እየደጋገሙ ይመላለሳሉ፤ የሰው ልጅ ግን አምሳሉን ይተካል እንጂ ራሱ ተመልሶ አይመጣም፡፡ እንግዲህ ክርስቶስ ለፍርድ ሲመጣ እንዳናፍር ዳግም በማናገኛት በዚህች ምድራዊ ሕይወታችን የማያልፍ ክርስቲያናዊ ምግባር ሠርተን ማለፍ ይጠበቅብናል፡፡ ከሞት በኋላ ዘለዓለማዊ ፍርድ እንጂ ንስሐ የለምና፡፡

በአጠቃላይ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹እነሆ ክረምት ዐለፈ፤ ዝናቡም ዐልፎ ሔደ፡፡ አበባ በምድር ላይ ታየ፤ የመከርም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቊርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጐመራ፤ ወይኖችም አበቡ፤ መዓዛቸውንም ሰጡ …›› /መኃ.፪፥፲፩-፲፫/ በማለት እንደ ተናገረው አሁን የክረምቱ ጊዜ አብቅቶ ሌላ ወቅት ዘመነ መጸው ተተክቷል፡፡ መጭው ጊዜ የተስፋ፣ የንስሐና የጽድቅ ወቅት እንዲኾንልን እግዚአብሔርን ከፊት ለፊታችን ማስቀደም ይኖርብናል፡፡ እርሱ ከቀደመ መሰናክሎቹን ለማለፍ፣ ፈተናዎችንም ለመወጣት ምቹ ኹኔታዎችን እናገኛለንና፡፡ ክረምቱ አልፎ መጸው ሲተካ ምድር ባገኘችው ዝናም አማካይነት የበቀሉ ዕፀዋት በአበባና በፍሬ ይደምቃሉ፡፡ እንደዚሁ ኹሉ ምእመናንም በተማርነው ቃለ እግዚአብሔር ለውጥ በማምጣት እንደ ዕፀዋት በመንፈሳዊ ሕይወታችን አፍርተን ክርስቲያናዊ ፍሬ ማስገኘት ይኖርብናል፡፡ በዚህ ፍሬያችን ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔር መንግሥት ለመውረስ እንችላለንና፡፡

ይህ መንፈሳዊ ዓላማችን ይሳካልን ዘንድም እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቀው፡፡ እንደዚህ እያልን፤ ‹‹ድኅረ ኀለፈ ክረምት ወገብአ ዝናም፤ ዘአርአይከ እግዚኦ ጽጌያተ ገዳም፤ አፈወ ሃይማኖት ነዓልድ ወፍሬ ምግባር ጥዑም፤ አትግሀነ ለስብሐቲከ ከመ ትጋሆሙ አዳም፤ ለጽብስት ንህብ ወነአስ ቃህም፡፡›› ትርጕሙም፡- ክረምት ካለፈ፣ ዝናምም ወደ ቦታው ከተመለሰ በኋላ የዱር አበቦችን ያሳየህ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ! የሃይማኖት ሽቱን እናስገኝና የሚጣፍጥ የምግባር ፍሬን እናፈራ ዘንድ ተወዳጅ እንደ ኾነው የታታሪዋ ንብና የብልሃተኛዋ ገብረ ጕንዳን ትጋት እኛንም ለምስጋናህ አትጋን›› ማለት ነው /መጽሐፈ ስንክሳር፣ የመስከረም ፳፭ ቀን አርኬ/፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ዘመነ ፍሬ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፲፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የተወደዳችሁ ምእመናን! ከአሁን በፊት ‹ዘመነ ክረምት ክፍል አራት› በሚል ርእስ ባቀረብነው ዝግጅት የሰው ልጅ ዓቅሙ በሚችለው ኹሉ ጠንክሮ እየሠራ የመኖር ተፈጥሯዊና ክርስቲያናዊ ግዴታ እንዳለበት፤ እየሠራም የድካሙን ዋጋ እንዲያገኝ መጸለይ፣ እየጸለየ ደግሞ የጸሎቱን ውጤት ለመቀበል ተግቶ መሥራት እንደሚገባው የሚያስገነዝብ ትምህርትና እንደዚሁም ከነሐሴ ፳፰ እስከ መስከረም ፩ ቀን ድረስ ያለው ክፍለ ክረምት ‹‹ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃን መዓልት›› እንደሚባል፣ በዚህ ክፍለ ክረምት ውስጥ ባሉት ቀናትም እነዚህን ፍጥረታት የሚመለከቱ ትምህርታት እንደሚቀርቡ በማስታዎስ ወቅቱን ከክርስቲያናዊ ሕይወት ጋር የሚያስቃኝ ዝግጅት አቅርበን ነበር፡፡ በተጨማሪም ከመስከረም ፩-፰ ቀን ድረስ ያለው ፭ኛው የክረምት ክፍለ ጊዜ ‹‹ዮሐንስ›› እንደሚባልና ይህ ወቅት የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሕይወት ከአዲሱ ዓመት ጋር እየተጣጣመ በስፋት የሚዳሰስበት ጊዜ እንደ ኾነ መጥቀሳችን የሚታወስ ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችንም ስድስተኛውን የክረምት ክፍለ ጊዜ የሚመለከት አጭር ትምህርት ይዘን ቀርበናል፤ እንድትከታተሉልን በአክብሮት እንጋብዛለን!

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ከመስከረም ፱ – ፲፭ ቀን ያለው ክፍለ ክረምት ‹ፍሬ› ይባላል፡፡ ‹ዘመነ ፍሬ› ደግሞ ‹የፍሬ ወቅት፣ የፍሬ ዘመን፣ የፍሬ ጊዜ› ማለት ሲኾን ይኸውም ልዩ ልዩ አዝርዕት በቅለው፣ አድገው፣ አብበው ለፍሬ የሚደርሱበት፤ የሰው ልጅ፣ እንስሳትና አራዊትም ጭምር የዕፀዋቱን ፍሬ (እሸት) የሚመገቡበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚቀርቡ ምንባባትና ትምህርቶችም ይህንኑ ምሥጢር የሚዳስሱ ናቸው፡፡ በክፍል አንድ ዝግጅታችን እንደ ተመለከትነው ዕፀዋት በጥፍር የሚላጡ (ሎሚ፣ ሙዝ፣ ትርንጎ፣ ወዘተ)፤ በማጭድ የሚታጨዱ (ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ወዘተ)፤ በምሳር የሚቈረጡ (ወይራ፣ ዋርካ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ፣ ወዘተ) በመባል በሦስት ይከፈላሉ፡፡

ተፈጥሯቸውም እንደ ሰው ልጅ ከአራቱ ባሕርያት ከነፋስ፣ እሳት፣ ውሃና አፈር (መሬት) ሲኾን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩት አራቱ ባሕርያት በዕፀዋት ሕይወት ላይ ለውጥ ሲያመጡ ይስተዋላል፤ ማለት ከነፋስ በመፈጠራቸው በነፋስ ያብባሉ፤ ያፈራሉ፡፡ ከእሳት በመፈጠራቸው አንዳንዶቹ እርስበርሳቸው ሲፋተጉ እሳት ያስገኛሉ፡፡ ከውሃ በመፈጠራቸውም ፈሳሽ ያወጣሉ፡፡ ከአፈር በመፈጠራቸው ደግሞ ሲቈረጡ በስብሰው ወደ አፈርነት ይቀየራሉ፡፡ ከፍሬ አያያዛቸው አኳያም በራሳቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ስንዴ፣ገብስ፣ ጤፍ፣ ወዘተ)፤ በጎድናቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ማሽላ፣ በቆሎ፣ ባቄላ፣ ወዘተ)፤ በውስጣቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ዱባ፣ ቅል፣ ወዘተ)፤ በሥራቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ሽንኩርት፣ ቀይ ሥር፣ ካሮት፣ ድንች፣ ወዘተ) ተብለው በአራት ይመደባሉ /ትርጓሜ ኦሪት ዘፍጥረት ፩፥፮-፲፫/፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት የሰው ልጆችን ሕይወት ከዕፀዋት ጋር በማነጻጸር ይገልጹታል፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ  በነፋስ ባሕርዩ ፍጥነት፤ በእሳት ባሕርዩ ቍጣ፤ በውሃ ባሕርዩ መረጋጋት፤ በመሬት ባሕርዩ ደግሞ ትዕግሥት ወይም ሞት እንደሚስማማው የሚያስተምር ንጽጽር ነው፡፡ በሌላ በኩል አዝርዕት ከበሰበሱ በኋላ ፍሬ እንደሚያስገኙ ኹሉ ሰውም ከሞተ በኋላ ተነሥቶ እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን ይቀበላል፡፡ ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ በሚከተለው መንገድ ገልጾታል፤ ‹‹… የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው፡፡ በመበስበስ ይዘራል፤ ባለመበስበስ ይነሣል፡፡ በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፡፡ በድካም ይዘራል፤ በኃይል ይነሣል፡፡ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፤ መንፈሳዊ አካል ይነሣል …›› /፩ቆሮ.፲፭፥፵፪-፵፬/፡፡

ዕፀዋት የሚሰጡት ፍሬ እንደየማፍራት ዓቅማቸው ይለያያል፤ ፍሬ የማያፈሩ፣ ጥቂት ፍሬ የሚያፈሩ፣ ብዙ ፍሬ የሚያፈሩ ዕፀዋት ይገኛሉ፡፡ እንደዚሁ ኹሉ ምእመናንም በክርስትና ሕይወታችን የሚኖረን በጎ ምግባር የአንዳችን ከአንዳችን ይለያል፡፡ ፍሬ የክርስቲያናዊ ምግባር እንደዚሁም የሰማያዊው ዋጋ ምሳሌ ነውና፡፡ በክርስትና ሕይወት ያለምንም በጎ ምግባር የምንኖር ኀጥአን ብዙዎች የመኾናችንን፤ እንደዚሁም ጥቂት በጎ ምግባር ያላቸው ምእመናን የመኖራቸውን ያህል በአንጻሩ ደግሞ በጽድቅ ላይ ጽድቅ፣ በመልካም ሥራ ላይ መልካም ሥራን የሚፈጽሙ፤ ከጽድቅ ሥራ ባሻገር በትሩፋት ተግባር ዘወትር ጸንተው የሚኖሩ አባቶችና እናቶችም ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ይህንን ዓይነት የክርስቲያናዊ ሕይወት ልዩነት ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፤ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል … ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፤ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል›› በማለት ይገልጸዋል /፪ቆሮ.፱፥፮-፲/፡፡ ገበሬ በዘራው መጠን ሰብሉን እንዲሰበስብ ‹‹ለኹሉም እንደየሥራው ዋጋውን ትከፍለዋለህ›› ተብሎ እንደ ተጻፈው ክርስቲያንም በሠራው መጠን ዋጋውን ያገኛልና በጸጋ ላይ ጸጋን፣ በበረከት ላይ በረከትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይጨመርልን ዘንድ ኹላችንም መልካም ሥራን በብዛት ልንፈጽም ይገባናል፡፡ ‹‹… እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል፡፡ እናንተ ደግሞ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፡፡ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና›› እንዳለን ሐዋርያው /ያዕ.፭፥፯-፰/፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ምድርኒ ወሀበት ፍሬሃ፤ ምድርም ፍሬዋን ሰጠች›› /መዝ.፷፮፥፮፤ ፹፬፥፲፪/ የሚለውን የዳዊት መዝሙርና ሌሎችንም ተመሳሳይ ኃይለ ቃላት ሲተረጕሙ ምድር በኢየሩሳሌም፣ በቤተ ክርስቲያን፣ በምእመናን፣ በእመቤታችን፤ ፍሬ ደግሞ በቃለ እግዚአብሔር (ሕግ)፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር፣ እንደዚሁም በጌታችን በመድኂታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመሰል ያስተምራሉ፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹ምድርም ፍሬዋን ሰጠች (ትሰጣለች)›› በሚለው ኃይለ ቃል ምድር የተባለች ኢየሩሳሌም የዘሩባትን እንደምታበቅል፤ የተከሉባትን እንደምታጸድቅ፤ አንድም ይህቺ ዓለም ፍሬን፣ አምልኮተ እግዚአብሔርን እንደምታቀርብ፤ አንድም ቤተ ክርስቲያን ወይም ምእመናን እግዚአብሔርን ሲያመልኩ እንደሚኖሩ፤ ከዚሁ ኹሉ ጋርም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን ያስረዳል፡፡ ለዚህም ነው በዘወትር ጸሎታችን ‹‹ቡርክት አንቲ እምአንስት ወቡሩክ ፍሬ ከርሥኪ፤ አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽ ፍሬም የተባረከ ነው›› /ሉቃ.፩፥፳፰/ እያልን እመቤታችንንና ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን የምናመሰግነው፡፡

በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ እንደምናገኘው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስትና ሕይወትን ከዘርና ፍሬ ጋር በማመሳሰል አስተምሯል፡፡ ይኸውም አንድ ገበሬ ዘር ሲዘራ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር ከመብቀሉ በፊት በወፎች እንደ ተበላ፤ በጭንጫ ላይ የተጣለውም ወዲያውኑ ቢበቅልም ነገር ግን ጠንካራ ሥር ስለማይኖረው በፀሐይ ብርሃን እንደ ጠወለገ፤ በእሾኽ መካከል የወደቀው ደግሞ ሲበቅል በእሾኽ እንደ ታነቀ፤ ከኹሉም በተለየ መልኩ በመልካም መሬት ላይ የተጣለው ዘር ግን አድጎ መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ ፍሬ እንደ ሰጠ ያስረዳል፡፡ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ተረጐመላቸው በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ የማያስተውል ክርስቲያን ምሳሌ ነው፤ ሙሉ እምነት ስለማይኖረው በመከራው ጊዜ አጋንንት ይነጥቁታልና፡፡ በጭንጫ ላይ የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበል፣ ነገር ግን ተግባራዊ የማያደርግ ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ ይህ ምእመን በጠንካራ እምነት ላይ የጸና አይደለምና በሃይማኖቱ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በደረሰበት ጊዜ ፈጥኖ ይሰናከላል፡፡ በእሾህ መካከል የተዘራውም ቃሉን የሚሰማ ነገር ግን በዚህ ዓለም ዐሳብና ባለጠግነት ተታሎ ቃሉን የማይተገብር ክርስቲያን  ምሳሌ ነው፡፡ በመልካም መሬት የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሰምቶ የሚተገብር ክርስቲያን ምሳሌ፡፡

እንደዚህ ዓይነት ምእመን በተማረው ትምህርት ጸንቶ ይኖራል፤ መልካም ሥራም ይሠራል፡፡ በመልካም መሬት የተዘራው ዘር ስለ አንዱ ፋንታ መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ እንደሚያፈራ ኹሉ በክርስቲያናዊ ግብር ጸንቶ የሚኖር ምእመንም ሥራውን በሦስት መንገድ ማለትም በወጣኒነት፣ በማእከላዊነትና በፍጹምነት ደረጃ እንደሚወጣ፤ ዋጋውንም በሥራው መጠን እንደሚያገኝ ያስረዳል፡፡ አንድም ባለ መቶ ፍሬ የሰማዕታት፤ ባለ ስድሳ የመነኰሳት፤ ባለ ሠላሳ በሕግ ተወስነው በዓለም የሚኖሩ ምእመናን ምሳሌ ነው፡፡ በተመሳሳይ ምሥጢር ኹሉም የፍሬ መጠን በኹሉም ምእመናን ሕይወት ውስጥ እንደሚስተዋል ሊቃውንት ይተረጕማሉ፡፡ ስለዚህም በሰማዕትነትም፣ በምንኵስናም፣ በዓለማዊ ሕይወትም ውስጥ የሚኖሩ ምእመናን መልካም ግብራቸው እጅግ የበዛ ከኾነ በባለ መቶ ፍሬ፤ መካከለኛ ከኾነ በባለ ስድሳ፤ ከዚህ ዝቅ ያለ ከኾነ ደግሞ በባለ ሠላሳ ፍሬ ይመሰላል  /ትርጓሜ ወንጌለ ማቴዎስ፣ ማቴ.፲፫፥፩-፳፫/፡፡

ዕፀዋት ለመጠለያነት የማይጠቅሙ እንደዚሁም ለምግብነት ወይም ደግሞ ለመድኀኒትነትና ለሌላም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚጠቅም ፍሬ የማያስገኙ ከኾነ ተቈርጠው እንደሚጣሉ ኹሉ ምእመናንም ‹ክርስቲያን› ተብለን እየተጠራን ብቻ ያለምንም በጎ ምግባርና መንፈሳዊ ሕይወት የምንኖር ከኾነ በምድር መቅሠፍት፤ በሰማይም ገሃነመ እሳት እንደሚጠብቀንና ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጪ እንደምንኾን ከወዲሁ በመረዳት በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ‹‹… ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጧል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ኹሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል›› ተብሎ ተጽፏልና /ማቴ.፫፥፲/፡፡

ከዚሁ ኹሉ ጋርም አዝርዕት ከበሰበሱ በኋላ በቅለው፣ አብበው በራሳቸው፣ በጎድናቸው፣ በውስጣቸውና በሥራቸው እንደሚያፈሩ ኹሉ ምእመናንም በራስ እንደ ማፍራት ፈሪሃ እግዚአብሔርን፤ በጎድን እንደ ማፍራት እርስበርስ መደጋገፍንና መተሳሰብን፤ በውስጥ እንደ ማፍራት ንጽሕናን፤ በሥር እንደ ማፍራት ትሕትናን ገንዘብ ማድረግን ከዕፀዋትና ከአዝርዕት መማር ይገባናል፡፡ እንደዚሁም ዕፀዋት ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶና ከዚያ በላይ መልካም ፍሬ እንደሚያፈሩ ምእመናንም በመልካሟ መሬት በክርስትና የተዘራን የክርስቶስ ዘሮች መኾናችንን አስተውለን፣ ደግሞም ዘር የተባለውን የእግዚአብሔርን ቃል ተምረን መተግበር እንደሚገባን ተረድተን ከወጣኒነት ወደ ማእከላዊነት፤ ከማእከላዊነት ወደ ፍጹምነት በሚያደርስ የጽድቅ ሥራ በመኖር የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ መፋጠን ይኖርብናል፡፡ ከሦስቱ በአንደኛው መደብ ውስጥ ወይም በኹሉም ደረጃዎች አልፈን ዘለዓለማዊ መንግሥቱን እንድንወርስ እግዚአብሔር አምላካችን ይርዳን፡፡

ይቆየን

ዘመነ ክረምት ክፍል ሦስት

ነሐሴ ፳ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በክፍል ሁለት ዝግጅታችን ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፲ ቀን ድረስ ያለው ሁለተኛው ክፍለ ክረምት ‹‹መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል›› እንደሚባል፤ ይህ ክፍለ ጊዜ የመብረቅና የነጎድጓድ ድምፅ በብዛት የሚሰማበት፤ የባሕርና የወንዞች ሙላት የሚያይልበት፤ እንደዚሁም የምድር ልምላሜ የሚጨምርበት ወቅት እንደ ኾነ በማስታዎስ ሕይወታችንን ከወቅቱ ኹኔታ ጋር በማገናዘብ መንፈሳዊ ቁም ነገር የሚያስጨብጥ ትምህርት ማቅረባችን የሚታዎስ ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ ቀጣዩንና ሦስተኛውን ክፍለ ክረምት የተመለከተ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ!

ከነሐሴ ፲ እስከ ፳፰ ቀን (ከማኅበር እስከ አብርሃም) ድረስ ያለው የዘመነ ክረምት ክፍለ ጊዜ ‹‹ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ›› ይባላል፡፡ ይኸውም የሰውን ልጅ ጨምሮ የሰማይ አዕዋፍ፣ የምድር አራዊትና እንስሳት ሳይቀሩ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርገው በደስታ መኖራቸው፤ በተጨማሪም በዝናም አማካይነት በዙሪያቸው ያለው የውሃ መጠን ከፍ ሲልላቸው ደሴቶች ኹሉ በልምላሜ ማሸብረቃቸው የሚነገርበት ክፍለ ክረምት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር ኹሉ በእነዚህ ምሥጢራት ላይ ያተኰረ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥለን ስለ ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያትና ዓይነ ኲሉ በቅደም ተከተል አጭር ማብራሪያ ለመስጠት እንሞክራለን፤

ዕጕለ ቋዓት

‹‹ዕጕል፣ ዕጓል›› ማለት ‹‹ልጅ›› ማለት ሲኾን፣ ‹‹ቋዕ›› ደግሞ ‹‹ቍራ›› ማለት ነው፡፡ ‹‹ቋዕ›› የሚለው ቃል በብዙ ቍጥር ሲገለጽም ‹‹ቋዓት›› ይኾናል፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹ዕጕለ ቋዓት›› የሚለው የግእዝ ቃላት ጥምረትም ‹‹የቍራ ልጆች (ግልገሎች)›› የሚል ትርጕም አለው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን የቍራ ጫጩቶች አስተዳደግ ከምእመናን ሕይወት ጋር ተነጻጽሮ ይነገራል፡፡ ይህም እንዲህ ነው፤ ቍራ ከእንቁላሉ ፍሕም መስሎ ይወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ እናትና አባቱ ባዕድ ነገር መስሏቸው ትተውት ይሸሻሉ፡፡ እርሱም በራበው ጊዜ ምግብ ፍለጋ አፉን ሲከፍት እርጥበት የሚፈልጉ ተሐዋስያን ወደ አፉ ይገባሉ፡፡ ከዚያም አፉን በመግጠም ይመገባቸዋል፡፡ እንደዚሁም ተሐዋስያን በአጠገቡ ሲያልፉ በእስትንፋሱ (በትንፋሹ) እየሳበ ይመገባቸዋል፡፡ እስከ ፵ ቀን ድረስ እንደዚህ እያደረገ ከቆየ በኋላ ፀጕር ያበቅላል፤ በዚህ ጊዜ በመልክ እነርሱን ስለሚመስል እናት አባቱ ተመልሰው ይከባከቡታል፡፡ ይህ የቍራ ዕድገትና ለውጥም እግዚአብሔር ፍጡራኑን የማይረሳ አምላክ እንደ ኾነና ፍጥረቱንም በጥበቡ እየመገበ እንደሚያኖራቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡

ቅዱስ ዳዊት ይህንን የቍራ የዕድገት ደረጃና የእግዚአብሔርን መግቦት በተናገረበት መዝሙሩ ‹‹ወሐመልማለ ለቅኔ ዕጓለ እመሕያው ዘይሁቦሙ ሲሳዮሙ ለእንስሳ ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውእዎ፤ ለሰው ልጆች ጥቅም ለምለሙን የሚያበቅል፤ ለእንስሳትና ለሚለምኑት የቍራ ጫጩቶች ምግባቸውን የሚሰጣቸው እርሱ ነው›› ሲል ይዘምራል /መዝ.፻፵፮፥፱/፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በትርጓሜያቸው እንደ ገለጹት ይህ ኃይለ ቃል እግዚአብሔር አምላክ ለእርሱ ለሚገዛው ለሰው ልጅ እኽህሉን፣ ተክሉን የሚያበቅልላቸው፤ ለእንስሳቱና ለአዕዋፍ (በቍራ አምሳል አዕዋፍን በመጥቀስ) ምግባቸውን የሚሰጣቸው እርሱ እንደ ኾነ ያስረዳል፡፡ ‹‹… ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውእዎ፤ … ለሚለምኑት ለቍራ ጫጩቶች›› የሚለው ሐረግም አዕዋፍ እግዚአብሔርን ምግብ እንዲያዘጋጅላቸው እንደሚለምኑትና እርሱም ልመናቸውን እንደሚቀበላቸው ያስገነዝበናል፡፡ በአንድምታው ትርጓሜ እንደ ተጠቀሰው ‹‹… ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውእዎ›› የሚለው ሐረግ ‹‹… እለ ኢይጼውእዎ›› ተብሎ ከተገለጸ የቍራ ጫጩቶች አፍ አውጥተው ባይነግሩት እንኳን እርሱ ፍላጎታቸውን ዐውቆ ምግባቸውን እንደሚሰጣቸው የሚያመለክት ምሥጢር አለው /ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት/፡፡

ምሥጢሩን ወደ እኛ ሕይወት ስናመጣውም እግዚአብሔር አምላክ ስሙን የሚጠሩትንም የማይጠሩትንም፤ ‹‹የዕለት እንጀራችንን ስጠን›› እያሉ የሚማጸኑትንም የማይጸልዩትንም በዝናም አብቅሎ፣ በፀሐይ አብስሎ ኹሉንም ሳያደላ በቸርነቱ እንደሚመግባቸው ያስተምረናል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የሰው ልጅ ለሚበላው፣ ለሚጠጣው መጨነቅ እንደማይገባው ሲናገር ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ትምህርት ሰጥቷል፡፡ እንዲህ ሲል፤ ‹‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፡፡ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና፡፡ ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱምም፡፡ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፡፡ እናንተ ከወፎች ትበልጡ የለምን? … አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም፤ አይፈትሉምም፡፡ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ኹሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም:: … ዛሬ ያለውን፣ ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የኾነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከኾነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ! እናንተንማ ይልቁን እንዴት? … የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፤ አታወላውሉም:: ይህንስ ኹሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፡፡ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል:: ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ፤ ይህም ኹሉ ይጨመርላችኋል፤›› /ሉቃ.፲፪፥፳፪-፴፩/፡፡

ስለዚህም አምላካችን እንዳስተማረን ስለምንበላውና ስለምንጠጣው ሳይኾን ስለ በጎ ምግባርና ስለ ዘለዓለማዊው መንግሥት መጨነቅ ይገባናል ማለት ነው፡፡ ራሳችንን ለገነት፣ ለመንግሥተ ሰማያት በሚያበቃ የጽድቅ ሥራ ካስገዛን የሚቀርብን ነገር አይኖርምና፡፡ ‹‹ዘእንበለ ንስአሎ ይሁብ ፍትወተነ፤ ሳንለምነው ልባችን የተመኘውን የሚሰጠን እርሱ ነው›› እንዲል /መጽሐፈ ኪዳን/፡፡ የየልባችንን መሻት ዐውቆ በረድኤቱ እየጠበቀ፤ በቸርነቱ እየመገበ የሚያኖረን አምላካችን እግዚአብሔር ስሙ ለዘለዓለሙ የተመሰገነ ይኹን፡፡

ደሰያት

በውሃ የተከበበ የብስ መሬት ‹‹ደሴት›› ይባላል፤ ‹‹ደሰያት›› ደግሞ ብዙ ቍጥርን አመላካች ነው፡፡ በዚህ ወቅት ስለ ደሴቶች ይነገራል፡፡ ምክንያቱም በዝናም አማካይነት በሚጨምረው የውሃ መጠን በድርቅ ብዛት የተጎዱ በደሴቶች የሚኖሩ ሰዎች ብቻ ሳይኾኑ እንስሳትም አዕዋፍም በሚበቅለው እኽልና በሚያገኙት ምግብ የሚደሰቱበት ጊዜ በመኾኑ ነው፡፡ ደሴቶች በውሃ የተከበቡ መሬት እንደ መኾናቸው በዚህ ወቅት በልምላሜ ያጌጣሉ ቢባልም ዳሩ ግን በማዕበልና በሞገድ መቸገራቸውም አይቀርም፡፡ ይህም የቤተ ክርስቲያን (የምእመናን ሕይወት) እና የዓለም ምሳሌ ነው፡፡ ደሴቶች በውሃ መከበባቸው ቤተ ክርስቲያን (የምእመናን ሕይወት) በክርስቶስ ደም የተመሠረተች፤ በቃለ እግዚአብሔር የታነጸች ለመኾኗ፤ ደሴቶች በማዕበልና በሞገድ እንደ መናወጣቸው ደግሞ በዓለም ውስጥ የሚከሠቱ ረሃብ፣ ጥላቻ፣ ጦርነት፣ ወዘተ የመሳሰሉ ችግሮች፤ በተለይ ሰይጣን የሚያመጣው ልዩ ልዩ ኅብረ ኀጢአት የቤተ ክርስቲያንን (የምእመናንን) ህልውና የሚፈታተኑ መኾናቸውን ያጠይቃል፡፡

ዓለም ሞገድ የበዛባት የውሃ ክፍል ናት፤ የክርስትና ሕይወት ደግሞ በውሃ የተከበበች መሬት፡፡ በውሃ የተከበበ መሬት ሞገድ፣ ማዕበልና ስጥመት እንደሚያጋጥመው ኹሉ የክርስትና ሕይወትም በምድር ላይ ልዩ ልዩ መከራና ፈተና ሊያጋጥመው ይችላልና ሃይማኖታችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን ከልዩ ልዩ ፈተና ይጠብቅልን ዘንድ ኹላችንም በፍጹም ሃይማኖት ኾነን እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ከስጥመት አድነን?›› እያልን እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ እርሱ በባሕር፣ በሞገድ፣ በማዕበልና በነፋስ የሚመሰሉ የዓለምን ውጣ ውረድና መከራ መገሠፅ፤ ሑከቱንም ጸጥ ማድረግ የሚቻለው አምላክ ነውና /ማቴ.፰፥፳፫-፳፯/፡፡

ዓይነ ኵሉ

‹‹ዓይነ ኵሉ›› በግእዝ ቋንቋ ‹‹የኹሉም ዓይን›› ማለት ነው፡፡ ይህም ፍጥረታት ኹሉ ወደ ፈጠራቸው ወደ እግዚአብሔር በማንጋጠጥ የዕለት ጕርስ፣ የዓመት ልብስ እንዳይከለክላቸው እንደሚማጸኑትና ዘወትር የእርሱን መግቦት ተስፋ በማድረግ እንደሚኖሩ ያስረዳል፡፡ ይህ ወቅትም ያለፈው እኽል ያለቀበት፤ የተዘራውም ያላፈራበት ገና የተክል ጊዜ በመኾኑ ፍጥረታት በሙሉ የፍሬውን ጊዜ በተስፋ የሚጠባበቁበት ስለ ኾነ ‹‹ዓይነ ኵሉ›› ተብሏል፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ዳዊት ‹‹ዐይነ ኵሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያከ አንተ ትሁቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ ትሰፍሕ የማነከ ወታጸግብ ለኵሉ እንስሳ ዘበሥርዓትከ›› ሲል የዘመረው /መዝ.፻፵፬፥፲፮/፡፡ ይኸውም የሰው ኹሉ ዓይን (ዓይን የተባለ ሰውነት ነው) እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጎ እንደሚኖር፤ እርሱም በዘር ጊዜ ዘሩን፣ በመከር ጊዜ መከሩን፣ በበልግ ጊዜ በልጉን እያዘጋጀ በየጊዜው ምግባቸውን እንደሚሰጣቸው፤ እንደዚሁም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ብቻ ሳይኾን በሰፊው እጁ (በማያልቅ ቸርነቱ) በሥርዓቱ ጸንተው ለሚኖሩ ለእንስሳት ጭምር ምግባቸውን እየሰጠ ደስ እንደሚያሰኛቸው የሚያስረዳ ነው /ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት/፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን መተርጕማን እንደሚያትቱት ከሰው ልጅ በቀር ከእግዚአብሔር ሥርዓት የወጣ እንስሳ የለም፤ ማለትም ሰው እንጂ እንስሳት ሕገ እግዚአብሔርን አልተላለፉም፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ አምላክነትን ተመኝቶ ‹‹አትብላ›› የተባለውን ዕፅ በመብላት ሕጉን፣ ትእዛዙን ተላልፏል፡፡ እግዚአብሔርም ይቅር ባይ አምላክ ነውና የሰውን ልጅ (የአዳምን) ንስሐ ተመልክቶ፣ ኀጢአቱን ይቅር ብሎ ሞቱን በሞቱ ሽሮ አድኖታል፡፡ እናም እግዚአብሔር በፍጡራኑ የማይጨክን፤ የለመኑትን የማይነሳ፤ የነገሩትንም የማይረሳ አምላክ መኾኑን በማስተዋልና ቸርነቱን ተስፋ በማድረግ በምድር በረከቱን እንዲሰጠን፤ ቅዱስ ሥጋውን ለመብላት፣ ክቡር ደሙን ለመጠጣ እንዲያበቃን፤ በሰማይም ዘለዓለማዊ መንግሥቱን እንዲያወርሰን በንጹሕ ልብ ኾነን ዘወትር ልንማጸነው ይገባናል፡፡ ‹‹አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /መዝ.፳፬፥፫/ እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ አያሳፍርምና፡፡ ደግሞም በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይበልጣልና፡፡

ይቆየን፡፡

አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር

ደደ

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት የታቦር ተራራ

ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

‹‹አስተርእዮ›› ሥርወ ቃሉ ‹‹አስተርአየ (አርአየ) = አሳየ፣ ገለጠ፣ ታየ፣ ተገለጠ›› የሚለው የግእዝ ግስ ሲኾን ትርጕሙም ‹‹መታየት፣ መገለጥ፣ ማሳየት፣ መግለጥ›› ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/፡፡ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር›› የሚለው ሐረግም ‹‹የእግዚአብሔር በታቦር ተራራ መገለጥ›› ወይም መታየት የሚል ትርጕም ያለው ሲኾን ይህም ከእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ጋር የተያያዘ እንደዚሁም ከምሥጢረ ሥጋዌና ከነገረ ድኅነት ጋር የተሳሰረ ታላቅ ምሥጢርን የያዘ መገለጥ ነው፡፡

ከዚህ ላይ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር›› ስንል የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ማለታችን መኾኑን ለማስታዎስ እንወዳለን፡፡ ‹‹እግዚአብሔር›› የሚለው ቃል ሦስቱም አካላት (ቅድስት ሥላሴ) በጋራ የሚጠሩበት መለኮታዊ ስያሜ ነውና፡፡ ‹‹አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ በአሐዱ ስም ሥሉሰ ያምልኩ፤ እኔ ‹እግዚአብሔር› በአልሁ ጊዜ ስለ አብም፣ ስለ ወልድም፣ ስለ መንፈስ ቅዱስም እናገራለሁ፤ (ምእመናን) በአንዱ ስም (በእግዚአብሔር) ሦስቱ አካላትን ያመልኩ ዘንድ›› እንዳለ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት /ሃይማኖተ አበው/፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን እግዚአብሔር አምላክ በብሉይም ኾነ በሐዲስ ኪዳን በአንድነቱ በሦስትነቱ በግብር (በሥራ)፣ በራእይና በገቢረ ተአምራት በልዩ ልዩ መንገድ ለፍጡራኑ ተገልጧል፡፡ በብሉይ ኪዳን ልዩ ልዩ ምልክት በማሳየት፤ በቅዱሳን ነቢያትና በመሣፍንት፣ በነገሥታት፣ በካህናትና በነቢያት ላይ በማደር ወይም በራእይ በማነጋገር፤ በተጨማሪም በጻድቃኑ ላይ ቸርነቱን በማሳየት፣ በክፉ አድራጊዎች ላይ ደግሞ መቅሠፍቱን በመላክ ሲያደርጋቸው በነበሩ ተአምራቱና ሥራዎቹ ይገለጥ ነበር፡፡

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ለአዳምና ለልጆቹ በገባው ቃል መሠረት የሰውን ሥጋ ለብሶ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በአካለ ሥጋ ተገልጦ በገቢረ ተአምራቱ፣ በትንሣኤውና በዕርገቱ አምላክነቱን አሳይቷል፡፡ የብሉይ ኪዳኑ መገለጥ በምልክት፣ በራእይ፣ በድምፅና በመሳሰሉት መንገዶች የተደረገ መገለጥ ነበር፤ የሐዲስ ኪዳኑ መገለጥ ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹መቼም ቢኾን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው›› /ዮሐ.፩፥፲፰/ ሲል እንደ ገለጸው አምላካችንን በዓይነ ሥጋ ያየንበት አስተርእዮ ስለኾነ ከመገለጦች ኹሉ የተለየ ጥልቅ ምሥጢር አለው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በሐዲስ ኪዳን በአካለ ሥጋ ያደረገውን መገለጥ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከምሥጢረ ሥላሴ ጋር በማያያዝ በሦስት መንገድ ይገልጹታል፡፡ ይኸውም በእመቤታችን፣ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ላይ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹በላዕሌኪ ወበዮርዳኖስ ወበታቦር ሥልሰ ጊዜያተ ዘአልቦ ተውሳከ ወአልቦ ሕጸተ ለውሉደ ሰብእ ያርኢ ዘሥላሴሁ ገጻተ ጽጌኪ ድንግል ተአምሪሁ ከሠተ ወበፀዳሉ አብርሀ ጽልመተ›› እንዳለ ደራሲ /ማኅሌተ ጽጌ/፡፡ ትርጕሙ እግዚአብሔር አምላክ ጭማሬም ጉድለትም የሌለበትን ሦስትነቱን ለሰው ልጅ ያሳይ ዘንድ በእመቤታችን፣ በዮርዳኖስ እና በታቦር ሦስት ጊዜ ተአምራቱን መግለጡን፤ በብርሃነ መለኮቱም ጨለማውን ብርሃን ማድረጉን የሚያስረዳ ሲኾን ይህም ጌታችን በለበሰው ሥጋ በእመቤታችን ማኅፀን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ተወስኖ ሲወለድ፤ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ዕለት እግዚአብሔር አብ ‹‹የምወደው ልጄ እርሱ ነው፤ እርሱን ስሙት›› ብሎ  ሲመሰክርና መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ራሱ ላይ ሲያርፍ፣ እንደዚሁም በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ መለኮታዊ አንድነቱና አካላዊ ሦስትነቱ መታወቁን ያመለክታል፡፡

በዛሬው ዝግጅታችን ወደምንመለከተው ትምህርት ስንመለስ ‹‹ደብረ ታቦር›› ማለት ‹‹የታቦር ተራራ›› ማለት ነው፤ ‹‹ደብር›› በግእዝ ቋንቋ ‹‹ተራራ ማለት ሲኾን ‹‹ታቦር›› ደግሞ የቦታው ስም ነው፡፡ ይኸውም ከኢያቦር ወገን በሚኾን ቦር በሚባል ሰው ስም የተሰየመ ቦታ ነው፡፡ ‹‹ታቦር›› ማለት ‹‹ትልቅ›› ማለት ሲኾን ተራራውን በ ‹‹ቦር›› ላይ ‹‹ታ››ን ጨምረው ‹‹ታቦር›› ብለው እንደ ጠሩት ይነገራል፡፡ ታቦር በፍልስጥኤም ግዛት ከገሊላ ባሕር በስተምዕራብ ደቡባዊ ክፍል የሚገኝ፤ ዕፀዋቱ መልካም መዓዛ የሚያመነጩበት፤ ከ፭፸፪ ሜትር በላይ ከፍታ ያለው ግዙፍ ተራራ ነው፡፡ በዚህ ተራራ ነቢዪቱ ዲቦራ ከባርቅ ጋር በመኾን የከነዓናውያንን ንጉሥ፣ የጦር መሪው ሲሳራንና ኢያቢስን ድል አድርገውበታል፡፡ ነቢዪቱም ከድል በኋላ መሥዋዕት አቅርባበታለች /መሣ.፬፥፭-፳፬/፡፡ እንደዚሁም ነቢዩ ሳሙኤል ትንቢት ተናግሮበታል፡፡ ንጉሥ ሳኦልም ከሦስት ሰዎች ጋር ተገኝቶበታል /፩ኛ ሳሙ.፲፥፫/፡፡ ርእሰ አበው አብርሃምና ኖኅ በዚህ ተራራ ላይ ቀስተ ደመና ተተክሎ አይተዋል፡፡ ስለዚህም ኖኅ ‹‹መካነ ብርሃን፤ የብርሃን ቦታ›› ብሎ ጠርቶታል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በተወለደ በ፴፪ ዓመት ከ፯ ወር ከ፲፭ ቀን፣ በዘመነ ማቴዎስ፣ በወርኃ ነሐሴ በዕለተ እሑድ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ገልጧል /መር አፈወርቅ ተክሌ እንደ ጠቀሱት/፡፡

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው ጌታችን ‹‹ከስድስት ቀን በኋላ›› ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደዚህ ተራራ (ደብረ ታቦር) ወጥቷል /ማቴ.፲፯፥፩/፡፡ ከዚህ ላይ ‹‹ከስድስት ቀን በኋላ›› የሚለው ሐረግ ጌታችን ሐዋርያቱን በቂሣርያ ‹‹ሰዎች ክርስቶስን ማን ይሉታል?›› ብሎ ከጠየቀበት ከነሐሴ ፯ ቀን በኋላ ያሉትን ቀናት ያመለክታል፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠው ከተስእሎተ ቂሣርያ በ፮ኛው ቀን (ነሐሴ ፲፫ ቀን) ነውና /፯+፮=፲፫/፡፡ ሙሴ ከመቃብር ኤልያስም ከብሔረ ሕያዋን በተገኙበት በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱ በተገለጠ ጊዜ ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም አጣቢ ሊያነጣው እስከማይችል ድረስ እንደ በረዶ ነጭ ኾነ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ›› እያለ ሲናገር ክርስቶስ በሰው እጅ የተሠራ ቤት የማያስፈልገው አምላከ ሰማይ ወምድር መኾኑ ይገለጥ ዘንድ ሰማያዊ ብሩህ ደመና ጋረደቻው፤ ከሰማይም ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት›› የሚል ቃል ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ መጣ፡፡ ‹‹እርሱን ስሙት›› ማለቱም ጌታችን ዓለምን ለማዳን እንደሚሞት ሲናገር ቅዱስ ጴጥሮ ‹‹አይኹንብህ›› ብሎት ነበርና ‹‹እሞታለሁ›› ቢላችሁ ‹‹አትሞትም›› አትበሉት ሲል ነው፡፡ ሙሴና ኤልያስም ከጌታችን ጋር ሲነጋገሩ ተሰሙ፤ ስለ ክርስቶስ የተናገሩት ትንቢትም በደብረ ታቦር ተረጋገጠ፡፡ በዚህ ጊዜ የፊቱን ግርማ ለማየትና የመለኮትን ድምፅ ለመስማት አልተቻላቸውምና ሙሴ ወደ መቃብሩ፣ ኤልያስም ወደ መጣበት ተመለሱ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም የመለኮትን ፊት አይተው መቆም አልተቻላቸውምና ደንግጠው ወደቁ፡፡

በብሉይ ኪዳን ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ቆይቶ ወደ ሕዝቡ ሲሔድ ፊቱ ያንጸባርቅ እንደ ነበርና የእስራኤላውያን ዓይን እንዳይጎዳ ሙሴ ፊቱን ይሸፍን እንደ ነበር ተጽፏል፡፡ ሙሴ የእግዚአብሔርን ድምፅ በመስማቱ ብቻ ፊቱ ያንጸባርቅ ከነበረ እግዚአብሔርንፊት ለፊት በዓይን ተመልክቶ ብርሃኑን መቋቋም ምን ያህል ከባድ ይኾን?

ከዚህ በኋላ ሐዋርያት ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው የኾነው ክርስቶስ ሙሴን ከመቃብር አንሥቶ፤ ኤልያስንም ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ በደብረ ታቦር እንዳወጣቸው ዐወቁ፡፡ ጌታችንም ሐዋርያቱን አጽናንቶ ኃይሉን ብርታቱን ካሳደረባቸው በኋላ ከንቱ ውዳሴን የማይሻ አምላክ ነውና፤ ደግሞም መናፍቃን ምትሐት ነው ብለው እንዲሰናከሉበት አይፈልግምና ኹሉም በጊዜው እስኪለጥ ማለትም ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የክርስቶስን አምላክነቱን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን፣ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን ለዓለም እስኪሰብኩ ድረስ በደብረ ታቦር ያዩትንና የሰሙትን ለማንም እንዳይነግሩ አዝዟቸዋል /ማቴ.፲፯፥፩-፱፤ ማር.፱፥፪-፱/፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በዘመነ ኦሪት ከሙሴ ጋር ቃል በቃል በደመና በሚነጋገርበት ጊዜ ነቢዩ ሙሴ ‹‹… ጌትነትህን (ባሕርይህን) ግለጽልኝ›› ሲል እግዚአብሔርን ተማጽኖት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ለሙሴ ‹‹በባሕርዬ ፊቴን አይቶ የሚድን የለምና ፊቴን ማየት አይቻልህም፡፡ … እኔ በምገለጽልህ ቦታ ዋሻ አለና በብርሃን ሠረገላ ኾኜ እስካልፍ ድረስ በዋሻው ውስጥ ቁመህ ታየኛለህ፡፡ በባሕርዬ አይተህ ደንግጠህ እንዳትሞት በብርሃን ሠረገላ ኾኜ እስካልፍ ድረስ ቀዳዳ ባለው ዋሻ እሠውርሃለሁ፡፡ በብርሃን ሠረገላ ኾኜ ካለፍሁ በኋላ እጄን አንሥቼልህ ከወደ ኋላዬ ታየኛለህ እንጂ በባሕርዬ ግን ፊቴን ማየት አይቻልህም›› የሚል ምላሽ ሰጥቶት ነበር /ዘፀ.፴፫፥፲፫-፳፫/፡፡ ይህም በፊት የሚሔድ ሰው ኋላው እንጂ ፊቱ እንደማይታይ ጌታም በባሕርዩ አለመገለጡን ያስረዳል፡፡ ምሥጢሩም አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በደብረ ታቦር በባሕርዩ እስኪገለጥለት ድረስ ሙሴ በመቃብር ተወስኖ እንደሚቆይ ያጠይቃል /ትርጓሜ ኦሪት ዘፀአት/፡፡

በብሉይ ኪዳን ባሕርዩን ለሙሴ የሠወረ አምላክ በደብረ ታቦር በመለኮታዊ ባሕርዩ ተገልጧል፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረው የመገለጥ ተስፋ ተፈጽሞ ይኸው አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር ኾኗል፡፡ ‹‹ጀርባዬን ታያለህ›› ያለ እርሱ ለሙሴ በደብረ ታቦር በክበበ ትስብእት ታይቷል፡፡ ነቢዩ ሙሴ እንደ ተመኘው በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን በተመለከተ ጊዜም ‹‹ፊቴን ማየት አይቻልህም›› ያለው ቃሉ ይፈጸም ዘንድ የክርስቶስን ፊት ማየት ስላቃተው ‹‹ትኄይሰኒ መቃብርየ፤ መቃብሬ ትሻለኛለች›› ብሎ ወደ መቃብሩ ተመልሷል፡፡ ‹‹ሞትን አይቀምስም›› የተባለለት፣ ክርስቶስ ለፍርድ ከመምጣቱ አስቀድሞ ወንጌልን የሚሰብከው ኤልያስ ብርሃነ መለኮቱን በግልጥ ለመመልከት ችሏል፡፡ መለኮቱን አይቶ መቆም አልቻለው ቢልም ወደ ብሔረ ሕያዋን ተመልሷል፡፡ የክርስቶስን መሞት በሥጋዊ ስሜት ተረድቶ ‹‹አይሁንብህ›› ያለው ቅዱስ ጴጥሮስና መለኮታዊ ሥልጣንን የተመኙት ቅዱሳን ያዕቆብና ዮሐንስ አብሯቸው እየኖረ የማያውቁት ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ መኾኑን ተረድተዋል፡፡ ተረድተውም ደንግጠው ወድቀዋል፡፡

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በተራራ የገለጠበት ምሥጢር

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በመንደር ሳይኾን በተራራ ያደረገው ስለምን ነው ቢሉ ተራራ የወንጌል ምሳሌ ነው፡፡ ተራራ ሲወጡት ያስቸግራል፤ ከወጡት በኋላ ግን ጭንጫውን፣ ግጫውን ሲያሳይ ደስ ያሰኛል፡፡ ወንጌልም ሲማሯት ታስቸግራለች፤ ጽድቅና ኀጢአትን ለይታ ስታሳውቅ ግን ደስ ታሰኛለችና በተራራ ትመሰላለች፡፡ ደግሞም ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፤ ተራራን በብዙ ፃዕር እንዲወጡት መንግሥተ ሰማይንም በብዙ መከራ ያገኟታልና፡፡ ‹‹እስመ በብዙኅ ፃማ ሀለወነ ንባኣ ለመንግሥተ እግዚአብሔር፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ አለን›› እንዲል /ሐዋ.፲፬፥፳፩-፳፪/፡፡

ትርጓሜ ወንጌል እንደሚያስረዳው ጌታችን መለኮቱን የገለጠበት ተራራ ታቦር መኾኑን ሐዋርያት በሲኖዶስ ጠቅሰውታል፡፡ ምሥጢሩን በሌላ ተራራ ሳይገልጥ ስለምን በደብረ ታቦር ገለጠ ቢሉ ትንቢቱ፣ ምሳሌው እንዲፈጸም ነው፡፡ ትንቢቱ፡- ‹‹ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ፤ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል›› የሚል ነው /መዝ.፹፰፥፲፪/፡፡ ይኸውም ጌታችን በደብረ ታቦር ባደረገው መገለጥ ተራሮች እንደ ሰው መደሰታቸውን፤ አንድም ልባቸው እንደ ተራራ በኑፋቄ የገዘፈ አይሁድና አሕዛብ ወይም መናፍቃን በተአምራቱ መማረካቸውን ያጠይቃል፡፡ ምሳሌው፡- በታቦር ተራራ ባርቅ ሲሳራን ድል ነስቶበታል /መሣ.፬፥፲፬-፲፮/፤ ጌታችንም በልበ ሐዋርያት (በልበ ምእመናን) ያደረ ሰይጣንን ድል የሚነሳበት ነውና ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር ገልጧል፡፡ አንድም ደብረ ታቦር የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናት፤ በደብረ ታቦር ነቢያትም ሐዋርያትም እንደ ተገኙ መንግሥተ ሰማያትንም በአንድነት ይወርሷታልና፡፡

ስለ ምን ከነቢያት ሁለቱን፣ ከሐዋርያት ሦስቱን ብቻ ወደ ተራራ ይዞ ወጣ?

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከነቢያት ሁለቱን፣ ከሐዋርያት ሦስቱን ብቻ ይዞ ወደ ደብረ ታቦር ይዞ የወጣበት ምሥጢር አንደኛ በብሉይ ኪዳን ሙሴ ‹‹ፊትህን አሳየኝ›› ብሎት ነበርና መለኮቱን ለሙሴ ለመግለጥ /ዘፀ.፴፫፥፲፫-፳፫/፤ ሁለተኛ ‹‹የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ›› ሲል የተናገረለት ኤልያስ በሕይወተ ሥጋ መኖሩን ለማሳየት /ማቴ.፲፮፥፳፰/፤ ደግሞም ኤልያስን ‹‹አንተሰ ስምዓ ትከውነኒ በደኃሪ መዋዕል፤ በኋለኛው ዘመን ምስክር ትኾነኛለህ›› /ሚል.፬፥፭/ ብሎት ነበርና የኤልያስን ምስክርነት ለማረጋገጥ፤ ሦስተኛ ጌታችን እንደሚሞት ሲናገር ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹አይኹንብህ›› ብሎት ነበርና ‹‹እርሱን ስሙት›› የሚለውን የእግዚአብሔርን አብ ምስክርነት ለማሰማት /ማቴ.፲፮፥፳፪፣ ፲፯፥፭/፤ አራተኛ አይሁድ ክርስቶስን ‹‹ከነቢያት አንዱ ነው›› /ማቴ.፲፮፥፲፬/ ይሉት ነበርና የነቢያት ጌታ መኾኑን ለማጠየቅ ነው፡፡

ከመዓስባን ሙሴን፣ ከደናግል ደግሞ ኤልያስን ማምጣቱም ደናግልም መዓስባንም መንግሥተ ሰማያትን በአንድነት እንደሚወርሱ ያጠይቃል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው›› ሲል መናገሩም ጌታችን በተአምራቱ ሲራቡ እያበላቸው፣ ሲጠሙ እያጠጣቸው፣ ሲታመሙ እየፈወሳቸው፣ ቢሞቱ እያነሣቸው፤ ሙሴም እንደ ቀድሞው ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣ ባሕር እየከፈለ፣ ጠላትን እየገደለ፤ ኤልያስ ደግሞ ሰማይን እየለጎመ፣ እሳት እያዘነመ፣ ዝናም እያቆመ በደብረ ታቦር ለመኖር መሻቱን ያመላክታል፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሦስት ጎጆ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፤ አንዱን ለሙሴ፤ አንዱን ለኤልያስ›› በማለት የእርሱንና የሁለቱን ጎጆ ሳይጠቅስ አርቆ መናገሩ በአንድ በኩል ትሕትናውን ማለትም ‹‹ለእኛ›› ሳይል ነቢያቱን አስቀድሞ ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን አለመጥቀሱን፤ እንደዚሁም ከጌታችን ጋር ለመኖር ያለውን ተስፋ ሲያመለክት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቅዱስ ጴጥሮስን ድክመት ማለትም የክርስቶስን አምላክነት በሚገባ አለመረዳቱን ያሳያል፡፡ ጌታችንን በተራራ ላይ በሰው ሠራሽ ቤት ይኖር ዘንድ ጠይቆታልና፡፡

ጌታችን ስምንቱን ከተራራው ሥር ትቶ (ይሁዳ ሳይቈጠር) ሦስቱን ሐዋርያት ወደ ተራራ ይዞ የወጣበት ምክንያት በአንድ በኩል ያዕቆብና ዮሐንስ ‹‹በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ፣ አንዳችንም በግራህ መቀመጥን ስጠን›› /ማር.፲፥፴፯/ ሲሉ መንግሥቱን ፈልገው ነበርና የልባቸውን መሻት ለመፈጸም ሲኾን በሌላ ምሥጢር ደግሞ ይሁዳን ወደ ተራራው ይዞ ለመውጣት ባለመሻቱ፤ ለይቶ እንዳይተወውም ‹‹ከምሥጢረ መንግሥቱ ቢለየኝ ከሞቱ ገባሁበት›› እንዳይለው (ምክንያት ለማሳጣት) ነው፡፡ ‹‹ያእትትዎ ለኀጥእ ከመ ኢይርአይ ስብሐተ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔርን ምስጋና (ክብር) እንዳያይ ኀጢአተኛውን ሰው አያስቀርቡት›› ተብሎ ትንቢት ተነግሮበታልና ይሁዳ የእግዚአብሔርን ክብር ለማየት አልበቃም፡፡ ኾኖም ግን በደብረ ታቦር የተገለጠው ምሥጢር ከተራራው በታች ለነበሩት ለስምንቱ ደቀ መዛሙርትም ተገልጦላቸዋል፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ በደብረ ታቦር ጌታችን በዮርዳኖስ ሲጠመቅ የተገለጠው ምሥጢረ ሥላሴና የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ገሃድ ኾኗል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ የኾነችው ደብረ ታቦር ምሥጢረ ሥላሴ ተገልጦባታል፤ የክርስቶስ አምላክነት ተረጋግጦባታል፡፡ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱ እንደ ተገለጠና የእግዚአብሔር አብ ምስክርነት እንደ ተሰማ ኹሉ ዛሬም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ሥላሴ ሲነገር፣ የመለኮት ሥጋና ደም ሲታደል ይኖራል፡፡ በደብረ ታቦር ነቢያትም፣ ሐዋርያትም እንደ ተገኙ ኹሉ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ብሉይና ሐዲስ ኪዳን ይሰበካል፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴ የሚፈጽሙ ልዑካን አምስት መኾናቸውም በደብረ ታቦር የተገኙትን ሙሴን፣ ኤልያስን፣ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ያስታውሱናል፡፡ ዘወትር በቤተ መቅደሱ የሚፈተተው ኅብስትና የሚቀዳው ወይን ደግሞ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን የገለጠው የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡

ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት በዓላት መካከል አንደኛው የኾነው በዓለ ደብረ ታቦር ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበትና ታላቅ የአስተርእዮ ምሥጢር የተፈጸመበት በዓል በመኾኑ ይህንን የመሥራቿን የክርስቶስን በዓል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን ‹‹አማን በአማን ተሰብሐ በደብረ ታቦር›› እያለች በድምቀት ታከብረዋለች፡፡ የአብነት ት/ቤት ደቀ መዛሙርት፣ በሰንበት ት/ቤትና በማኅበራት የሚያገለግሉ ምእመናንም ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠ አምላክ ብርሃነ ምሥጢሩን በየልቡናቸው እንዲገልጥላቸው ለመማጸን ጸበል ጸሪቅ አዘጋጅተው በዓሉን ይዘክሩታል፡፡ በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ከሙታን ተነሥቶ ከዘመናት በፊት የተመኘውን የአምላኩን ፊት ለማየት የታደለው ሊቀ ነቢያት ሙሴ የተወለደውም በዚህች ዕለት ነው፡፡ እኛም እግዚአብሔር በደብረ ታቦር ያደረገውን አስተርእዮ ለማስታዎስ ይህንን ጽሑፍ አዘጋጀን፡፡

ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠ ጌታ በእያንዳንዳችን ልቡናም ማስተዋሉን፣ ምሥጢሩን፣ ጥበቡን ይሳልብን፤ ያሳድርብን፡፡ ከቅዱሳኑ ጋር መንግሥቱን እንዲያወርሰን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ነሐሴ ፲፫ ቀን፡፡

መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ በመ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ ገጽ ፫፻፲፬-፫፻፲፯ እና ፬፻፩፡፡

ትርጓሜ ወንጌለ ማቴዎስ፣ ምዕ.፲፯፥፩-፱፡፡

ዘመነ ክረምት ክፍል ሁለት

ነሐሴ ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በክፍል አንድ ዝግጅታችን የመጀመሪያው የዘመነ ክረምት ክፍለ ጊዜ (ከሰኔ ፳፭ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ድረስ ያለው) ዘርዕ፣ ደመና እንደሚባል በማስታዎስ ይህ ወቅት ደመና ሰማዩን የሚሸፍንበት፤ የዝናም መጠን የሚያይልበትና መሬት በዝናም ረክታ ዘር የምታበቅልበት ጊዜ እንደኾነ ጠቅሰን የወቅቱን ኹኔታ ከሕይወታችን ጋር በማዛመድ ለመዳሰስ ሞክረን ነበር፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ሁለተኛውን የዘመነ ክረምት ክፍለ ጊዜ የሚመለከት ትምህርት ይዘን የቀረብን ሲኾን በወቅቱ ባለማስነበባችን ይቅርታ እየጠየቅን ጽፋችንን እነሆ!

ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፲ ቀን ድረስ ያለው ሁለተኛው ክፍለ ክረምት ‹‹መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል›› በመባል የሚታወቅ ሲኾን፣ ይኸውም የመብረቅና የነጎድጓድ ድምፅ በብዛት የሚሰማበት፤ የባሕርና የወንዞች ሙላት የሚያይልበት፤ የምድር ልምላሜ የሚጨምርበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ክፍለ ጊዜ ውስጥ በሚገኙ ዕለታት በቤተ ክርስቲያን በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱ፣ በቅዳሴው የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር ይህንን ኹሉ ሕገ ተፈጥሮ የሚዳስስና የእግዚአብሔርን አምላካዊ ጥበብ የሚያስረዳ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፡፡

መብረቅ እና ነጎድጓድ

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ወገብረ መብረቀ ለጊዜ ዝናም፤ መብረቅን ለዝናም ምልክት አደረገ፤›› በማለት እንደ ገለጸው መብረቅ በዝናም ጊዜ የሚገኝ ፍጥረት ሲኾን የሚፈጠረውም ውሃ በደመና ተቋጥሮ ወደ ላይ ከተወሰደ በኋላ በነፋስ ኃይል ወደ ምድር ሲወርድ በደመና እና በደመና መካከል በሚከሠት ግጭት አማካይነት ነው፡፡ ይህንን የመብረቅ አፈጣጠርም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቅቤና በዐረቄ አወጣጥ ይመስሉታል፡፡

ወተት ሲገፋ ቅቤ እንደሚወጣ፤ ልዩ ልዩ የእህል ዝርያ ከውሃ ጋር ኾኖ በእሳት ሲሞቅ ዐረቄ እንደሚገኝ ኹሉ ደመና እና ደመና ሲጋጩም መብረቅ ይፈጠራልና:: የምድር ጠቢባንም ሞቃት እና ቀዝቃዛ አየር ሲጋጩ መብረቅ እንደሚፈጠር ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ላይ ዘመናዊው ትምህርት ከመምጣቱ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መብረቅ አፈጣጠር አስቀድሞ ማስተማሩን ልብ ይሏል /መዝሙረ ዳዊት አንድምታ ትርጓሜ፣ መዝ.፻፴፬፥፯/፡፡ ነጎድጓድ ደግሞ መብረቅ በሚፈጠርበት ጊዜ የሚሰማው አስፈሪ ድምፅ ነው /ራእ.፬፥፭/::

መብረቅና ነጎድጓድ በእግዚአብሔር መቅሠፍት እና በቃለ እግዚአብሔር (በቍጣው) ይመሰላሉ፡፡ መብረቅ ብልጭታውና ድምፁ (ነጎድጓዱ) እንደሚያስደነግጥና እንደሚስፈራ ኹሉ እግዚአብሔርም መቅሠፍት ሲልክና ሲቈጣ የሰው ልጅ ይጨነቃል፤ ይረበሻልና፡፡ ‹‹ቃለ ነጎድጓድከ በሠረገላት አስተርአየ መባርቅቲሁ ለዓለም ርዕደት ወአድለቅለቀት ምድር፤ የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበረ፡፡ መብረቆች ለዓለም አበሩ፤ ምድር ተናወጠች፤ ተንቀጠቀጠችም፤›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት /መዝ.፸፮፥፲፰/፡፡ ይህም ግብጻውያን እስራኤላውያንን ከባርነት ባለመልቀቃቸው የደረሰባቸውን ልዩ ልዩ መቅሠፍትና መዓት የሚመለክት ምሥጢር ይዟል:፡

እንደዚሁም እስራኤላውያን የኤርትራን ባሕር በተሻገሩ ጊዜ ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ›› እያሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና ማቅረባቸውን ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ እግዚአብሔር አብ ከላይ ከሰማይ ኾኖ ‹‹የምወደውና የማፈቅረው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱንም ስሙት፤›› በማለት መናገሩንና ወንጌለ መንግሥተ ሰማያት (ቃለ እግዚአብሔር) በቅዱሳን ሐዋርያት፣ በሰብዓ አርድእት፣ በአበው ሊቃውንት አማካይነት በመላው ዓለም መሰበኩን ያጠይቃል /ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት/:፡

እንደ ሌሎቹ ፍጥረታት ኹሉ መብረቅና ነጎድጓድም አስገኛቸውን፤ ፈጣያቸውን ልዑል እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይህንን ሥርዓት ‹‹… ዘበጸዐዕ ይትነከር ወእመባርቅት ይትአኰት ወይትናበብ በእሳት ድምፀ ነጎድጓዱ በሠረገላት፤ በብልጭታ የሚደነቅ፤ በመብረቆች የሚመሰገን፤ በእሳት ውስጥ የሚናገር፤ የነጎድጓዱም ድምፅ በሠረገሎች ላይ የኾነ እግዚአብሔር ንጹሕ፣ ልዩ፣ ክቡር፣ ጽኑዕ ነው፤›› ሲል ገልጾታል /መጽሐፈ ሰዓታት/::

ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ ‹‹ይሴብሕዎ ሰማያት ወምድር ባሕርኒ ወኵሉ ዘይትሐወስ ውስቴታ፤ ሰማይና ምድር ባሕርም በእርስዋም የሚንቀሳቀስ ሁሉ ያመሰግኑታል፤›› በማለት ሰማዩም፣ ምድሩም፣ ባሕሩም፣ ወንዙም እግዚአብሔርን እንደሚያመሰግን ተናግሯል /መዝ.፷፰፥፴፬/፡፡ ይህም እግዚአብሔር በመላእክትም፣ በሰው ልጅም፣ አንድም በትሑታኑም በልዑላኑም፤ በከተማውም በገጠሩም እንደዚሁም በባሕር ውስጥ በሚመላለሱ ፍጥረታት ኹሉ የሚመሰገን አምላክ መኾኑን ያስረዳል፡፡ የማይሰሙ፣ የማይናገሩ፣ የማያዩ ግዑዛን ፍጥረታት እንዲህ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ ከኾነ በእርሱ አርአያና አምሳል የተፈጠረው፤ ሕያዊት፣ ለባዊትና ነባቢት ነፍስ ያለችው የሰው ልጅማ ፈጣሪውን እንዴት አልቆ ማመስገን ይገባው ይኾን?

ከዚሁ ኹሉ ጋርም ደመና እና ደመና ተጋጭተው መብረቅን እንደሚፈጥሩ ኹሉ የሰው ልጅ ባሕርያተ ሥጋም እርስበርስ ሲጋጩና አልስማማ ሲሉ በሰው ልጅ ስሜት ቍጣ፣ ብስጭት፣ ቅንዓት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ የጠባይዕ ለውጦች ይከሠቱና ኀጢአት ለመሥራት ምክንያት ይኾኑበታል፡፡ ‹‹ከልብ ክፉ ዐሳብ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በውሸት መመስከር፣ ስድብ ይወጣል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ማቴ.፲፭፥፲፱/፡፡ የመብረቅና የነጎድጓድ ድምፅ እንደሚያስፈራው ኹሉ እነዚህ በሥጋዊ ባሕርይ አለመስማማት የሚፈጠሩ የኀጢአት ዘሮችም ፍርሃትንና መታወክን በሰው አእምሮ ውስጥ እንዲመላለስ ያደርጋሉ፤ ከኹሉም በላይ በምድርም በሰማይም ቅጣትን ያስከትላሉ:: ለዚህም ነው ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ኀጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለ ፍርሃት ይኖራል፤›› ሲል የተናገረው /ምሳ.፳፰፥፩/፡፡

እንግዲህ የሰው ልጅ ራሱን ከክፉ ዐሳብና ምኞት በመጠበቅ አእምሮዉን ለመልካም አስተሳሰብና አመለካከት፤ ለክርስቲያናዊ ምግባር ቢያስገዛ በምድር በሰላምና በጸጥታ ለመኖር፤ በሰማይም መንግሥቱን ለመውረስ እንደሚቻለው በመረዳት ባሕርያተ ሥጋችን ተስማምተውልን በጽድቅ ሥራ እንድንኖር እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ይኖርብናል::

ባሕር እና አፍላግ

ባሕርና አፍላግ በቃልና በመጠን፣ ወይም በአቀማመጥ ይለያዩ እንጂ ሁለቱም የውሃ ክፍሎች ናቸው፡፡ ‹‹ባሕር›› አንድም ብዙም ቍጥርን የሚወክል ግእዝ ቃል ሲኾን ይኸውም በጎድጓዳ መልክዐ ምድር ውስጥ የሚጠራቀም ጥልቅ የኾነ የውሃ ክምችት ማለት ነው /ዘፍ.፩፥፲/፡፡ ‹‹አፍላግ›› የሚለው የግእዝ ቃልም የ‹‹ፈለግ›› ብዙ ቍጥር ኾኖ ትርጉሙም ወንዞች ማለት ነው፡፡ ይህም ከውቅያኖስ፣ ከባሕር ወይም ከከርሠ ምድር መንጭቶ ረጅም ርቀት የሚፈስ የውሃ ጅረትን አመላካች ነው /ዘፍ.፪፥፲፤ መዝ.፵፭፥፬/፡፡ በዚህ ወቅት የባሕርና የወንዞች መጠን ለዋናተኞች፣ ለመርከብና ለጀልባ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ እስኪኾን ድረስ ከቀድሞው በበለጠ መልኩ በሙላትና በኃይል ይበረታል፤ ከሙላቱ የተነሣም ሰውን፣ ንብረትን እስከ ማስጠም እና መውሰድ ይደርሳል::

ይህ የባሕርና የወንዞች ሙላትም የምድራዊ ሕይወት መከራና ፈተና፣ ሥቃይና ፈቃደ ሥጋ (ኀጢአት) ማየልን፤ ዳግመኛም በሰው ልጅ ኀጢአት ምክንያት የሚመጣ ሰማያዊም ኾነ ምድራዊ ቅጣትን ያመለክታል፡፡ እንደዚሁም የእግዚአብሔርን የተአምራት ብዛት ይገልጻል፡፡ ‹‹ወዓሠርከኒ ውስተ ማይ ብዙኅ ወኢይትዐወቅ ዓሠርከ፤ መንገድህ በባህር ውስጥ ነው፤ ፍለጋህም በብዙ ውኆች ነው፤›› እንዲል /መዝ.፸፮፥፲፱/፡፡ ይኸውም የእግዚአብሔር መንፈስ በመላው ዓለም ሰፍኖ እንደሚኖርና በሃይማኖት፣ በምግባር ጸንተው፣ ከኀጢአት ተለይተው እርሱን የሚሹ ኹሉ ይቅርታውን እንደ ውኃ በቀላሉ እንደሚያገኙት የሚያስረዳ ምሥጢር አለው፡፡ የኀጢአት ባሕር እንዳያሰጥመን፤ የኀጢአት ወንዝ እንዳይወስደን ኹላችንም ራሳችንን ከፈቃደ ሥጋ (ከስሜታዊነት) ተጠብቀን መንግሥቱን እንወርስ ዘንድ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፡

ጠል

‹‹ጠል›› የሚለው ቃል ‹‹ጠለ – ለመለመ›› ከሚል የግእዝ ግስ የወጣ ሲኾን ትርጕሙም ‹‹ልምላሜ›› ማለት ነው፡፡ ዘመነ ክረምት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ልምላሜ ቢኖርም በስፋት የሚነገረው ግን ከሐምሌ ፲፱ ቀን እስከ ነሐሴ ፲ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ይህ ወቅት የሚበሉትም የማይበሉትም አብዛኞቹ ዕፀዋት በቅለው ለምልመው የሚታዩበት ጊዜ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹በመከር ወራት የውርጭ ጠል ደስ እንደሚያሰኝ እንዲሁ የታመነ መልእክተኛ ለላኩት ነው፤›› በማለት እንደ መሰለው /ምሳ.፳፭፥፲፫/፣ ይኼ የዕፀዋት ልምላሜ በጎ ምግባር ባላቸው ምእመናንና በመልካም አገልጋዮች ይመሰላል፡

በተጨማሪም ዕፀዋት በዝናም አማካይነት በቅለው መለምለማቸው በስብከተ ወንጌል (ቃለ እግዚአብሔር) ተለውጠው፣ በሃይማኖታቸው ጸንተው፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ተግተው፣ በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ተወስነው የሚኖሩ ምእመናንን ሕይወት እና እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሚያድለውን ጸጋና በረከት ያመለክታል፡፡ ‹‹ወይረውዩ እምጠለ ቤትከ፤ ከቤትህ ጠል ይጠጣሉ (ይረካሉ)፤›› እንዲል /መዝ.፴፭፥፰/፡፡ ይኸውም በቤተ መቅደሱ ዘወትር የሚፈተተውን ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን መቀበልና ጠበሉን መጠጣት የሚያስገኘውን መንፈሳዊ ርካታ ይገልጻል፡፡

በዚህ ክፍለ ክረምት የሚለመልሙ ዕፀዋት የመብዛታቸውን ያህል በለስና ወይንን የመሰሉ ተክሎች ክረምት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ደርቀው ይቆዩና በበጋ ወቅት ይለመልማሉ፡፡ እነዚህም በመልካም ዘመን ራሳቸውን ደብቀው የሚኖሩና በመከራ ሰዓት ተነሥተው ወንጌልን የሚሰብኩ የሰማዕታት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በለስና ወይንን የመሰሉ ዕፀዋት በዝናም ጊዜ ደርቀው በፀሐይ ጊዜ እንዲለመልሙ፤ ቅዱሳን ሰማዕታትም በምድራዊ ሹመት፣ በሽልማት ወቅት ተሠውረው፤ ሥቃይና ፈተና በሚበራታበት ጊዜ ምድራዊውን መከራ ተቋቁመው ስለ እውነት (ወንጌል) እየመሰከሩ ራሳቸውን በሰማዕትነት አሳልፈው ይሰጣሉና፡፡ ኹላችንንም እንደ ዕፀዋቱ በወንጌል ዝናም ለምልመን መልካም ፍሬ እንድናፈራ የአምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ይቆየን፡፡

ዘመነ ክረምት ክፍል አንድ

ሐምሌ ፲፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በበአተ ክረምት ጽሑፋችን እንደ ጠቀስነው በኢትዮጵያ የወቅቶች ሥርዓተ ዑደት አኳያ አሁን የምንገኘው ዘመነ ክረምት ላይ ነው፡፡ በቅዱስ ያሬድ አስተምህሮ ይህ ዘመነ ክረምት በሰባት ንዑሳን ክፍሎች ይመደባል፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን የመጀመሪያውን ክፍለ ክረምት የተመለከተ ጽሑፍ ይዘን ቀርበናል፤

ከሰባቱ የዘመነ ክረምት ክፍሎች መካከል የመጀመሪያው ክፍል (ከሰኔ ፳፭ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ) ዘርዕ፣ ደመና ይባላል፡፡ በዚህ ወቅት ስለ ዘርዕ፣ ስለ ደመናና ስለ ዝናም የሚያዘክሩ መዝሙራትና ምንባባት ይዘመራሉ፤ ይነበባሉ፡፡ ይህ ወቅት ደመና ሰማዩን የሚሸፍንበት፤ የዝናም መጠን የሚያይልበትና መሬት በዝናም ረክታ ዘር የምታበቅልበት ጊዜ ነው፡፡

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ <<በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይሰበስባሉ፡፡ በሔዱ ጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው መጡ፤>> በማለት እንደ ተናገረው /መዝ.፻፳፭፥፭-፮/፣ ይህ ወቅት አርሶ አደሩ በእርሻና ዘር በመዝራት የሚደክምበትና የምርት ጊዜውን በተስፋ የሚጠባበቅበት ጊዜ ነው፤ ይህም የሰውን ልጅ የሕይወት ጉዞና ውጣ ውረድ እንደዚሁም በክርስቲያናዊ ምግባር ስለሚያገኘው ሰማያዊ መንግሥት የሚያስረዳ ምሥጢር አለው፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የውቅያኖስና የሐኖስ ድንበር ይኾን ዘንድ በውሃ መካከል ጠፈርን ፈጥሮ ከጠፈር በታች (በዚህ ዓለም) ያለው ውሃ በአንድ ቦታ እንዲወሰን ካደረገ በኋላ ከምድር እስከ ብሩህ ሰማይ ድረስ የነበረውን ውሃ ከሦስት ከፍሎ ሢሶውን አርግቶ ጠፈር አድርጎታል፡፡ ሢሶውም ከጠፈር በላይ ያለው ውሃ ሲኾን፣ ስሙም ሐኖስ ይባላል፡፡

ሢሶውንም ይህንን ዓለም ከሰባት ከፍሎ ሰባተኛውን ዕጣ አጐድጕዶ በዚያ ወስኖ ስሙን ውቅያኖስ ብሎታል፡፡ የብሱን ክፍል ደግሞ ምድር ብሎ ሰይሞታል፡፡ ምድርም እንደ ጉበት ለምልማ በታየች ጊዜ እግዚአብሔር በነፋስ ኃይል ጸጥ ካደረጋት በኋላ ከደረቅ ምድር ደረቅ ጢስ፤ ከርጥብ ባሕር ርጥብ ጢስ አስወጥቶ ደመናን አስገኝቷል /ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት ፻፴፬፥፯/፡፡

ደመና ዝናምን የሚሸከመው የማይጨበጠው ጢስ መሰል ፍጥረት ሲኾን፣ በደመና ተሸካሚነት ከውቅያኖስና ከወንዞች በትነት አማካይነት ወደ ሰማይ ተወስዶ እንደ ገና ተመልሶ ወደ ምድር የሚጥለው ውሃ ደግሞ ዝናም ይባላል፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር ጥበብ በደመና ወንፊትነት ተጣርቶ ለፍጡራን በሚመችና በሚጠቅም መጠን በሥርዓት ይወርዳል፡፡ <<ያጸንዖ በፍኖተ በድው ከመ ይዝንም ብሔረ ኀበ አልቦ ሰብእ ወኢይነብሮ ዕጓለ እመሕያው፤ ዝናሙን ሰው በሌለበት በምድረ በዳ ያዘንመዋል፤>> እንዳለ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፡፡

ይህም በረዶውን በምድረ በዳ አፍሶ የጠራውን ውሃ ሰው ወዳለበት እንዲዘንም ማድረጉን የሚያስረዳ መልእክት የያዘ ሲኾን፣ ምሥጢሩም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንበለ ዘርዕ በልዩ ጥበቡ መፀነሱንና የሰውን ሥጋ ለብሶ ማስተማሩን፤ እንደዚሁም ቅዱሳን ሐዋርያትን <<ሑሩ ወመሐሩ>> ብሎ በመላው ዓለም ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማሰማራቱን ያመለክታል /ትርጓሜ ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ ፪፥፭-፮/፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በረቂቅ ጥበቡ ውሃን ከውቅያኖሶች በደመና እየጫነ ወደ ሰማይ ካወጣ በኋላ እንደ ገና መልሶ ወደ ምድር እያዘነመ ይህንን ዓለም ሲመግብ ይኖራል፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይህንን ጥበብ በማድነቅ <<ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት አምላክነ በተነ ጊሜ ረቂቅ ዘያአቍሮ ለማይ ያዐርጎ እምቀላይ ወያወርዶ እምኑኀ ሰማይ፤ ረቂቅ በኾነ የጉም ተን ውሃውን የሚቋጥረው፤ ከወንዝ ወደ ላይ የሚያወጣው፤ ከሩቅ ሰማይም የሚያወርደው እግዚአብሔር ቅዱስ፣ ልዩ፣ ምስጉን አሸናፊ አምላክ ነው፤>> በማለት እግዚአብሔርን ያመሰግናል /መጽሐፈ ሰዓታት/፡፡

ዝናም በአንድ በኩል የቃለ እግዚአብሔር ምሳሌ ነው፤ ይኸውም ለዘር መብቀል፣ ማበብና ማፍራት ምክንያት እንደ ኾነ ኹሉ በቃለ እግዚአብሔርም በድንቁርና በረኃ የደረቀ ሰውነት ይለመልማል፤ መንፈሳዊ ሕይወትን የተራበችና የተጠማች ነፍስም ትጠግባለች፤ ትረካለችና፡፡ <<ሲሲታ ለነፍስ ቃለ እግዚአብሔር፤ የነፍስ ምግቧ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤>> እንዲል፡፡

በሌላ በኩል በዚህ ዓለም የሚያጋጥም ልዩ ልዩ ፈተናም በዝናም ይመሰላል፤ ጌታችን በወንጌል እንደ ነገረን ቃሉን ሰምቶ በሥራ ላይ የሚያውል ክርስቲያን ቤቱን በዓለት ላይ የመሠረተ ልባም ሰውን ይመስላል፡፡ ጐርፍ ቤቱን በገፋው ጊዜ አይናወጥምና፡፡

ቃሉን የማይተገብር ክርስቲያን ግን ያለ መሠረት በአሸዋ ላይ ቤቱን የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል፡፡ ቤቱ በዝናብ፣ በጎርፍና በነፋስ ተገፍቶ የከፋ አወዳደቅ ይወድቃልና፡፡ ይህም ሃይማኖቱን በበጎ ልቡና የያዘ ክርስቲያን ከልዩ ልዩ አቅጣጫ በሚደርስበት መከራ ሳይፈራና በሰዎች ምክር ሳይታለል፤ እንደ ኢዮብ ዓይነት ፈተና ቢደርስበት ሳያማርር፤ እንደዚሁም በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን እየታገዘ አጋንንትን ድል እያደረገ ሃይማኖቱን ጠብቆ እንደሚኖር፤ በአንጻሩ ሃይማኖቱን በበጎ ሕሊና ያልያዘ ክርስቲያን ግን ፈተና ባጋጠመው ጊዜ በቀላሉ እንደሚክድና ለአጋንንትም እጁን እንደሚሰጥ የሚያስረዳ ምሥጢር አለው /ትርጓሜ ወንጌል፣ ማቴ.፯፥፳፬-፳፯/፡፡

ዝናም ሲጥል የወንዞች ሙላትና ማዕበላት ቤት እንዲያፈርሱ፤ ንብረት እንዲያወድሙ በክርስቲያናዊ ሕይወት በሚያጋጥም ፈተናም በእምነት መዛል፣ መከራ፣ ችግር፣ ውጣ ውረድ ያጋጥማል፡፡ ዝናም ለጊዜው እንዲያስበርድና ልብስን እንዲያበሰበስ ፈተናም እስኪያልፍ ድረስ ያሰንፋል፤ ያስጨንቃል፤ ያዝላል፡፡ ነገር ግን ዝናም፣ ጎርፍና ማዕበል ጊዜያዊ እንደ ኾነ ኹሉ ፈተናም ከታገሡት ያልፋል፡፡

ዝናም ሲመጣ የውሆችን ሙላትና ጎርፉን ሳንፈራ ወደ ፊት የምናገኘውን ምርት ተስፋ እንደምናደርግ ፈተና ሲያጋጥመንም የምናገኘውን ሰማያዊ ዋጋ በማሰብ በትዕግሥት ማሳለፍ ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ ኹላችንም እምነታችንን በጠንካራ መሠረት ላይ በመገንባት በውሃ ሙላትና በማዕበል ከሚመሰል ውድቀት ማምለጥ ይጠበቅብናል ማለት ነው፡፡

የደመና አገልግሎቱ ዝናምን ከውቅያኖስ በመሸከም ወደ ምድር እያጣራ ማውረድ ቢኾንም ነገር ግን በሰማይ የሚዘዋወርና በነፋስ የሚበታተን ዝናም አልባ ደመናም አለ፡፡ በመልካም ግብር፣ በትሩፋት ጸንተው የሚኖሩ ምእመናን ዝናም ባለው ደመና ሲመሰሉ፣ ያለ ክርስቲያናዊ ምግባር በስመ ክርስትና ብቻ የምንኖር ምእመናን ደግሞ ዝናም በሌለው ደመና እንመሰላለን፡፡ ሐዋርያው ይሁዳ <<… በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፤ …>> በማለት የተናገረውም የእንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን ሕይወት ይመለከታል /ይሁዳ ፩፥፲፪/፡፡

ስለዚህም ውሃ ሳይይዝ በባዶው በነፋስ እንደሚበታተን ዝናም አልባ ደመና ሳይኾን፣ ዝናም እንደሚሸከም ደመና በምግባረ ሠናይ ጸንተን ልንኖር ይገባል፡፡ አንድም ዝናም ያለው ደመና የእመቤታችን የቅድስት ደንግል ማርያም ምሳሌ ነው፡፡ እርሷ ንጹሑን የሕይወት ውሃ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አስገኝታልናለችና፡፡ <<አንቲ ዘበአማን ደመና እንተ አስተርአይኪ ለነ ማየ ዝናም፤>> እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም /ውዳሴ ዘረቡዕ/፡፡ እኛም እንደ እመቤታችን የእግዚአብሔርን ቃል ሕይወታችን በማድረግ ራሳችንን ከማዳን ባሻገር ለሌሎችም አርአያና ምሳሌ ልንኾን ያስፈልጋል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ምድርን ከፈጠረ በኋላ በጥፍር የሚላጡትን (ሎሚ፣ ሙዝ፣ ትርንጎ፣ ወዘተ)፤ በማጭድ የሚታጨዱትን (ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ወዘተ)፤ በምሳር የሚቈረጡትን (ወይራ፣ ዋርካ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ፣ ወዘተ)፤ የገነት ዕፀዋትን ፈጥሯል፡፡ ተፈጥሯቸውም እንደ ሰው ከአራቱ ባሕርያት ነው፡፡

ከነፋስ በመፈጠራቸው በነፋስ ያብባሉ፤ ያፈራሉ፡፡ ከእሳት በመፈጠራቸው እርስበርሳቸው ሲፋተጉ እሳት ያስገኛሉ (አንዳንዶቹ)፡፡ ከውሃ በመፈጠራቸው ፈሳሽ ይወጣቸዋል፡፡ ከአፈር በመፈጠራቸው ሲቈረጡ በስብሰው ወደ አፈርነት ይቀየራሉ፡፡ እነዚህም በራሳቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ስንዴ፣ገብስ፣ ጤፍ፣ ወዘተ)፤ በጎድናቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ማሽላ፣ በቆሎ፣ ባቄላ፣ ወዘተ)፤ በውስጣቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ዱባ፣ ቅል፣ ወዘተ)፤ በሥራቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ሽንኩርት፣ ቀይ ሥር፣ ካሮት፣ ድንች፣ ወዘተ) ተብለው በአራት ይመደባሉ /ምንጭ፡- ትርጓሜ ኦሪት ዘፍጥረት ፩፥፮-፲፫/፡፡

እኛ የሰው ልጆችም በተፈጥሯችን (በባሕርያችን) ከዕፀዋት ጋር እንመሳሰላለን፤ በነፋስ ባሕርያችን ፍጥነት፤ በእሳት ባሕርያችን ቍጣ፤ በውሃ ባሕርያችን መረጋጋት፤ በመሬት ባሕርያችን ትዕግሥት ወይም ሞት ይስማማናልና፡፡ በሌላ በኩል የአዘርዕት ከበሰበሱ በኋላ መብቀልና ማፍራት የትንሣኤ ሙታን ምሳሌ ነው፡፡ አዝርዕት ከበሰበሱ በኋላ ፍሬ እንደሚያስገኙ ኹሉ ሰውም ከሞተ በኋላ ተነሥቶ እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን ይቀበላልና፡፡ ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ በምሳሌ አስተምሮናል፡፡ እንዲህ ሲል፤ <<… የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው፡፡ በመበስበስ ይዘራል፤ ባለመበስበስ ይነሣል፡፡ በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፡፡ በድካም ይዘራል፤ በኃይል ይነሣል፡፡ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፤ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። …>> /፩ኛቆሮ.፲፭፥፵፪-፵፬/፡፡

አዝርዕት ተዘርተው ከበሰበሱ በኋላ በቅለው፣ አብበው በራሳቸው፣ በጎድናቸው፣ በውስጣቸውና በሥራቸው እንደሚያፈሩ ኹሉ እኛም በራስ እንደ ማፍራት ፈሪሃ እግዚአብሔርን፤ በጎድን እንደ ማፍራት እርስበርስ መደጋገፍንና መተሳሰብን፤ በውስጥ እንደ ማፍራት ንጽሕናን፤ በሥር እንደ ማፍራት ትሕትናን ገንዘብ ማድረግን ከዕፀዋትና ከአዝርዕት መማር ይገባናል፡፡

እንደዚሁም ዕፀዋት ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶና ከዚያ በላይ መልካም ፍሬ እንደሚያፈሩ እኛም በመልካሟ መሬት በክርስትና የተዘራን ምእመናን ዘር የተባለውን የእግዚአብሔርን ቃል በሚገባ ተምረን ከወጣኒነት ወደ ማእከላዊነት፤ ከማእከላዊነት ወደ ፍጹምነት በሚያደርስ የጽድቅ ሥራ በመትጋት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ መፋጠን ይኖርብናል /ማቴ.፲፫፥፳፫/፡፡

በአጠቃላይ “… ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጧል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ኹሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል፤”  የሚለውን ኃይለ ቃል በማሰብ /ማቴ.፫፥፲/፣ ፍሬ የማያፈሩ ዕፀዋት በምሳር ተቈርጠው እንዲጣሉ እኛም ያለ መልካም ሥራ ከኖርን በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ፍርድ ከገነት፣ ከመንግሥተ ሰማያት የመባረር ዕጣ እንዳይደርስብን ከሃይማኖታችን ሥርዓት፤ ከቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ሳንወጣ የቅዱሳንን ሕይወት አብነት አድርገን ለጽድቅ ሥራ እንሽቀዳደም፡፡ <<እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤>> ተብሎ ተጽፏልና /ዕብ.፲፪፥፩-፪/፡፡

ይቆየን፡፡

እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ ነው፡፡ ዕብ 11:1

ግንቦት 10ቀን 2007 ዓ.ም

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

እምነት የሚለው የግእዝ ቃል ሲሆን ፔስቲስ የሚልውን የግሪክ ቃል የሚተካ ነው፡፡ ትርጉሙም አንድን ነገር መቀበልና ማሳመን ሞራላዊ ማረግጋገጫ መስጠት ማለት ነው፡፡ እምነት ማለት እውነትን መቀበልና ልባችንን ለዚህ እውነት መስጠት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እምነት ተስፋ ስለምናደርገው እውነት የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። “እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።” (ዕብ 11:1) እንዲል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስእንዲህ አለ:- “አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው።” (ማቴ 21:22) እንደገናም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው:- የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ። ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም። ” (ማቴ 17:20) “ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል።” (ማር 11:24) በማለትጌታችን በተለያዩ ጊዜና ቦታ አስተምሯል፡፡ ስለዚህ ጸሎታችን በእምነት ሊሆን ይገባል፤ በእምነት ስንጸልይ እግዚአብሔር ጸሎታችንን ይሰማል::

€œእምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፣ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። (ዕብ. 11:1ሰው ተስፋ ካለው የማይታየውን እንዳየ ሆኖ ይረዳል፡፡ እምነት ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር የምንገልጥበት፣ እርሱን ደስ የምናሰኝበት ጥበብ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እምነት እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኝበት ጥበብ መሆኑን ሲያስረዳ ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይ ቻልም ብሏል፡፡ ዕብ. 11፣6፡፡

የእምነት ፍሬ በእምነት እንድንኖርና እንድንሄድ ይረዳናል:: “በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ” (ኤፌ 6:16) እምነት የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልናጠፉ የምትችልበት ጋሻ ነው::

ከላይ እንዳየነው እምነት ከመንፈስ ቅዱስ የሚመነጭ የመንፈስ ፍሬ ነው:: ይህም ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝሕያው ፍሬ ነው:: እንዲሁም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም:: ዕብ 11:2 እንዲህ ይላል:- “ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና።”(ዕብ 11:2) እምነት መልካም ምስክርነትን ያመጣል::

በእምነት ጥንካሬአቸው የተመሰከረላቸው ሰዎች በእግዚአብሔር በመታመናቸው በሚያቃጥል የእሳት ነበልባል ውስጥ በመጣል፣ ወደ አንበሳ ጉድጓድ በመወርወር፣ በሰይፍ በመተርተር እምነታቸውን ገልጠዋል፡፡ እግዚአብሔርም በቅዱሳን የእምነት ጥንካሬ የልበ ደንዳኖችን ልብ ማርኳል፡፡ንጉሡ ናቡከደነጾር ለጣዖት አንሰግድም ብለው እምነታቸውን የገለጡትን ሠለስቱ ደቂቅን ርዝማኔው አስራ ስድስት ክንድ ከሚደርስ የእሳት ነበልባል ውስጥ በሰንሰለት አስሮ ቢወርወራቸውም ከሰውነታቸው አንዳች ሳይቃጠል በመዳናቸው፤በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ ይባረክ ዳን. 3፣25 ሲል እግዚአበሔርን አክብሯል፡፡

በዘመነ ሐዲስ በሰው ፍቅር ተስቦ ወደዚህ ዓለም የመጣው ቸሩ አምላክ ለአገልግሎት ከመረጣቸው ሰዎች አንዳንዶቹ ምንም ዓይነት መሠረታዊ የሃይማኖት ዕውቀት አልነበራቸውም፡፡ እግዚአብሔር እነዚህን አላዋቂዎችን የመረጠው በዘመኑ በዕውቀታቸው የሚታበዩ ሰዎችን ዕውቀት ከንቱ ለማድረግ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጌታችን የዓለምን ጥበብ ከንቱ ለማድረግ አላዋቂዎችን እንደመረጠ ሲያስረዳ፤እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔር የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም መረጠ፡፡ ብሏል፡፡ 1ኛቆሮ.1፣26-29፡፡

እግዚአብሔር ለእምነት አገልግሎት ሰዎችን ሲመርጥ ሞኞች ጠቢባን ይሆናሉ፤ አላዋቂዎች ሀብተ እውቀት ያገኛሉ፤ ደካማዎች ብርቱዎች ይሆናሉ፡፡ አላዋቂ የነበሩት ተከታዮቹ ጠቢባን፤ ደካማ የነበሩት ብርቱዎች እስከሚሆኑ ድረስ ለቀጣይ የእምነት ሕይ ወታቸው ብርታት እንዲሆናቸው የተለያዩ ጥያቄዎችን ለጌታችን ያቀርቡ ነበር፡፡

ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይከተሉ ከነበሩ ሰዎች ለጌታችን ካቀረቡት ጥያቄ አንዱ አለማመኔን እርዳው የሚል ነው፡፡ ጌታችን የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው የተከተሉትን በሕይወት ሰጪ ትምህርቱ በነፍስ የተመሙትን ተስፋ የቆረጡትን፣ ባዶነት የሚሰማቸውን መንፈሳዊ ዝለት የገጠማቸውን ሲፈውስ፤ በተአምራቱ ደግሞ በሕማመ ሥጋ የታመሙትን ፈውሷል፡፡ የጌታችንን ሕይወት ሰጪ ትምህርት ፈልገው የተከተሉ አብዛኛዎች በተከፈለ ልብ ነበር፡፡ መድኃኒታችን የተከፈለ ልብ ያላቸውን ማረጋጋት፣ ያዘኑትን ማጽናናት ባሕርዩ በመሆኑ ድክመታቸውን ሳይሸሸጉ የሚቀርቡትን ፈጣን ምላሽ ይሰጣል፡፡

የጌታችን ደቀ መዛሙርት ልጁን እንዲፈውሱለት የወሰደው ሰው፤ ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ የእምነት ማነስ የተነሣ ፍቱን መፍትሔ ቢያጣም ከጌታችን ዘንድ መጥቶ የእምነቱ ጉድለት በጌታችን እንዲስተ ካክልለት የልጁን ሕማም ሁኔታ ከዘረዘረ በኋላ፤ ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳን ማር.9፣22 የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ቢቻልህ የሚለውን የጥርጣሬ ቃል ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሰው ሁሉ ይቻላል፡፡ በሚል ቃል ሲያርመው የተቸገረው ሰው አለማመኑ በእርሱ እንዲጠገንለት በታላቅ ድምፅ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው ብሎታል፡፡ ይህ ሰው አምናለሁ አለማመኔን እርዳው በማለት በእምነት ሕይወት ውስጥ ያለበትን ችግር ሳይሸሸግ መናገሩን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

ምክንያቱም እያመን የማናምን፣ ንስሐ እየገባን የማንፀፀት፣ እየቆረብን ለሥጋ ወደሙ ክብር የማንሰጥ፣ እየቀደስን ያልተቀደስን ብዙዎች ነን፡፡ እኛም እናምናለን ነገር ግን እምነታችን በአንተ ይታገዝ እርዳን ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ብዙ ሰዎች ክርስቶስ መወለዱን፣ መጠመቁን፣ ከሙታን መነሣቱን (ትንሣኤውን መግለጡን) ያምናሉ፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ድርሻ እና ተስፋ ግን ይጠራጠራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር እያመንን በእምነት ሕይወት ውስጥ አንኖርም ለዚህ ማለዘቢያ ግን እምነታችን፣ አለማወቃችንና ድካማችን በጌታችን እንዲደገፍ መማጸን ነው፡፡

በማቴዎስ ወንጌል ቅዱሳን ሐዋርያት የታመመውን ልጅ ለመፈወስ አቅም ያጡበትን ምክንያት ለመረዳት፤እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለምንድነው? ሲሉ ጌታችንን ጠይቀውታል /ማቴ.17፣19/፡፡ ይህ ጥያቄ የእኛም ጥያቄ ነው፡፡ እኔ የተሰጠኝን ሓላፊነት ያልተወጣሁት ስለምንድነው? ያልቆረብኩት ስለምንድነው? ከልቤ ውስጥ የሚጉላላውን ቂም ያላወጣሁት ስለምንድነው? የበደልኩትን ያልካስኩት ስለምንድነው? የሚፈታተነኝን የሰይጣን ፈተና ማለፍ ያልቻልኩት ስለምንድነው? መንፈሳዊ ሕይወቴ ማደግ ያልቻለው፣ ራሴን ማወቅ መረዳት ያልቻልኩት ስለምንድነው? ብለን እንድንጠይቅ የቅዱሳን ሐዋርያት ጥያቄ ይጋብዘናል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት እግዚአብሔር ከጎናቸው እያለ የእምነት ጉድለት ስለታየባቸው ማድረግ የሚገባቸውን ለመፈጸም አልቻሉም፤ ነገር ግን ልባቸውን የፈነቀለውን አንገብጋቢ ጥያቄ መጠየቃቸው መልካም ነበር፡፡ ምክንያቱም በእምነት ሊያደርጉት የሚቻላቸውን ነገር ማድረግ የተሣናቸው ስለእምነታቸው ጉድለት መሆኑን ጌታችን አስረግጦ እንዲህ በማለት ነግሯቸዋል፡፡ እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ሾላ ተነቅለህ በሌላ ቦታ ተተከል ብትሉት ይታዘዝላች ኋል ሉቃ.17፣6 ብሏቸዋል፡፡ ማመን፣ ያመኑትን ማድረግ ከባድ ነገር ነው፡፡

ዛሬ ስለእምነት፣ በእምነት ሕይወት ስለመኖር፣ የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት በማድረግ የቅዱሳንን ገድልና ትሩፋት በመግለጥ ብዙ ነገር ተነግሮናል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛዎቻችን ቃሉ በጭንጫ ላይ የተዘራ ዘር ሆኖብናል፤ /ማቴ. 13፣20/ ጌታችን በጭንጫ ላይ ዘር ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ደረቀ ያለውን ሲፈታ በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበል ነው፡፡ ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል፡፡ ብሏል፡፡

በእምነት መንፈሳዊ ሕይወታቸው አልጸና ብሎአቸው ይቸገሩ የነበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን ያቀረቡት ጥያቄ መሠረታዊ ምላሽ አግኝቶ፤ የሰውነ ታቸው ለልብሳቸው፤ የልብሳቸው ለጥላቸው አልፎ ሕሙም ከመፈወስ ሙት እስከ ማስነሣት ደርሰዋል፡፡ ይኸውም ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ በዚህም አገልግሎታቸው እንደ ሠመረላቸው መረዳት ይቻላል፡፡

እኛም በሃይማኖት ስትኖሩ ራሳች ሁን መርምሩ ተብሎ እንደተነገረን፤ በቅድሚያ መንፈሳዊ ሕይወቴ ያላደገው ለምንድ ነው? ብለን ያለንን የእምነት ጥንካሬና ድክመት መመዘን አለብን፡፡ በማስከተል እንደ ታመመው ልጅ አባት አለማመኔን እርዳው የሚል ጥያቄ አቅርበን፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል ፍጹም እምነት ሲኖረን ጌታችን እንዳለው ተራራ የሆነብን ትዕቢት፣ ከፊታችን የተደ ቀነው ክፋት፣ ምቀኝነት ከሕይወ ታችን ይነቀላል፡፡ እየወላወለ የሚያ ስቸግረን ልቡናችን ክት እንዲሆን ወይም እንዲሰበሰብልን አለማመኔን እርዳው ማለት አለብን፡፡ አለማመናችን በእግዚአብሔር ሲረዳ ባሕሩ እንደ የብስ ጸንቶልን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በባሕር ላይ እንረማመዳለን፡፡ በሌላ አነጋገር እግዚአብሔር አለማመናችንን ሲረዳው የሚሣነን ነገር የለም፡፡ በእኔ የሚያምን ከእኔ የበለጠ ያደርጋል ተብሎ ለቅዱሳን የተገባው ቃል የታመነ ነው፡፡

ያ በእምነት ያልጸናው ሰው ለእግዚአብሔር አምላኩ አለማመ ኔን እርዳው ሲል ያቀረበው ጥያቄ የሁላችንንም ሕይወት የሚወክል ነው፡፡ ዛሬ እምነቱ ሥርዓቱ፣ ትውፊቱ እያ ለን በፍጹም ልብ ያለማመን ችግር አለብን፡፡ ልጁ የታመመበት ሰው አለማመኔን እርዳው ሲል በአንተ ታምኜ የምኖርበትን ኃይል ለአንተ የሚገዛ ልብ እና ሕይወት ስጠኝ ማለቱ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ከአባቶቻችን የተቀበልነው እምነት የፈተና ጎርፍ ሳይሸረሽረው ነፋስ ሳያ ዘመው በዐለት ላይ ተመሥርቶ እንዲጸናልን ዘወትር ጌታ ሆይ አለማ መኔን እርዳው ማለት አለብን፡፡ ያለማመናችን ችግር በእግዚአብሔር ካልተረዳ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በማለት ብቻ መንግሥተ ሰማያትን እንደማንወርስ ተነግሮናል፡፡ በመሆ ኑም ልባሞች ከመብራታቸው ጋር ዘይት ይዘው ሙሽራውን እንደጠበቁ፤ ባለማመን የጠወለገውን ሕይወታ ችንን በቃሉ ዝናምነት በማለምለም አለማመናችን በእግዚአብሔር ቃል መረዳት አለበት፡፡

ማንኛውም የሕይወት ውጣ ውረድ ቢያጋጥመን በእምነት ከጸናን የማናልፈው ነገር የለም፡፡ የማንዘለው የችግር እና የመከራ ግንብ፣ የማንሻገረው ባሕር እና መሰናክል የለም፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በእምነት ከእግዚአብሔር ጋር ከኖርን የሚያስፈራን አንዳች ነገር አለመኖሩን ሲያስረዳ በሞት ጥላ መካከል እንኳን ብሔድ፤ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል መዝ. 22፣4 ብሏል፡፡

ነቢዩ እንደ ነገረን አፋችንን ሞልተን በሞት ጥላ መካከል እንኳን ብሔድ ክፉን አልፈራም በማለት በእምነት ማደግ አለብን፡፡ ቅዱስ ዳዊት በሕይወት ዘመኑ መውደቅ መነሣት ያጋጠመው ሰው ቢሆንም በእምነት በመጽናቱ ፍጻሜው ሠምሮ ልበ አምላክ ለመባል በቅቷል፡፡ በመሆኑም ዛሬ በመንፈሳዊ ሕይወታችን የተደቀነብንን ፈተና የምናልፈው በእምነት ነው፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኘው በእምነት ነው፡፡ የሚመጣውን ነገር በተስፋ የሚያስረዳንም እምነት በመ ሆኑ አለማመናችንን እርዳው እያልን መጮህ ይገባል፡፡

አለማመናችን በእግዚአብሔር ሲረዳ ወይም በእምነት ስንጸና ረድኤተ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ኃያላን የሆኑትን አራዊት ሳይቀር ገራም ያደርግልናል፡፡ በዘመነ ብሉይ ነቢዩ ዳንኤል ከአናብስት ጉድጓድ ሲወረወር የተራቡት አንበሶች ለነቢዩ ገራም የሆኑት የእምነት ሰው በመሆኑ ነው፡፡ በቅድስናቸው የተመሰከረላቸው ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አናምርት /ነብሮች/ እና አናብስት /አንበሶች/ የእግራቸውን ትቢያ እየላሱ የታዘዙላቸው በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን በእምነት ነው፡፡ ዛሬ ዲያብሎስ እንደተራበ አንበሳ በፊታችን በሚያደባበት ዘመን የእምነትን ጥሩር መልበስ ያስፈልጋል፡፡ ለቀደሙት አባቶች ሥጋት የነበሩት ነገሮች ቀሊልና ታዛዥ እንደሆኑ ለእኛም ይሆኑልናል፡፡ ብዙ ጊዜ ፈቃደ ሥጋችን ፈቃደ ነፍሳችንን ሲጫነው የምንወደውን ሳይሆን የማንወደውን እናደርጋለን፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውምÃ ሮሜ. 7፣19፡፡ ሲል እንደተናገረው፤ የሥጋችን ፈቃድ ብዙ ጊዜ ነፍሴ ብይ፣ ጠጪ ደስ ይበልሽ ወደ ማለት ቢያዘነብልም ቅሉ ወደ ፈቃደ ነፍስም መለስ ብሎ እኔ ማነኝ? ጉዞዬስ ወዴት ነው? ተስፋዬስ ማን ነው? ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ፈቃደ ሥጋው እያየለ ሲያስቸግረው፤ በእንባው መኝታውን እያራሰ በእግዚአብሔር ፊት ቢያለቅስ፤ የኃጢአት አሽክላ እየተ ቆረጠለት በእምነቱ የሚደሰት ሰው ሆኗል፡፡

በእምነት ጉድለት በዲያብሎስ ሽንገላ የእምነት አቅም አጥተን ከቤተ ክርስቲያን ከቅድስና ሕይወት የራቅን ወገኖች፤ አለማመናችንን እግዚአብሔር እንዲረዳው ሳንሰለች ጥያቄ ማቅረብ አለብን፡፡ በእምነት ጉድለት ምክንያት ያጣነውን በረከት፣ ያጣነውን ጽናት እናገኛለን፡፡ ልባሞቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ይህን ለመፈጸም ለምን እኛን ተሳነን? ብለው እንደጠየቁ፤ እኛም ራሳችንን መጠየቅ አለብን፡፡ በጎ መሥራት ለምን ተሳነን?

የሰው ልጅ ወደ እምነት ፍጹም ነት ውስጥ ሲገባ ሁሉ ነገር በእግዚአብሔር እጅ እንደሆነ ይረዳል፤ ከጭንቀትም ያርፋል፡፡ በአቅማችንና በፈቃዳችን የተቸገረን መርዳት፣ አምላክን ከልብ መውደድ፣ ማመስገን የእምነት ሰው መገለጫ ናቸው፡፡

በእምነት የጸኑ አባቶችን በአንበሳ ጉድጓድ፣ በእሳት ውስጥ፣ በወህኒ ቤት በተጣሉ ጊዜ የተረዳና የእምነታቸውን ዋጋ የከፈለ እግዚአብሔር ዛሬም አለ፡፡ በመሆኑም መንፈሳዊ ሕይወታችንን በእምነት አሳድገን መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ያብቃን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር