ጥምቀተ ክርስቶስ

timket-2

ጥምቀተ ክርስቶስ

በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ

ጥር ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም  

በነቢያት የተነገረው ትንቢት በወንጌል የተጻፈው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ከዘጠኙ ታላላቅ በዓላት አንዱ ነው፡፡ ጥምቀት የሚለው ቃል ‹‹ተጠምቀተጠመቀ›› ካለው ግሥ የወጣ ነው፤ ትርጕሙም በውሃ መጠመቅ ማለት ሲኾን፣ ይኸውም በወራጅ ወንዝ፣ በሐይቅ ውስጥ ወይም በምንጭ የሚፈጸም ነው፡፡ በካህናት እጅ የሚፈጸመው ጥምቀት ከሌላው ጥምቀት ይለያል፡፡

በዘመነ ብሉይ ይፈጸም የነበረው ጥምቀት የንስሓ ጥምቀት ሲሆን በዘመነ ሐዲስ የሚፈጸመው ግን የልጅነት ጥምቀት ነው፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ከሁለቱም ልዩ ነው፡፡ እርሱ ሰውን ያከብራል እንጅ ከሰው ክብርን የማይፈልግ የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ለእኛ አርአያና አብነት ለመኾን በዮሐንስ እጅ በማየ ዮርዳኖስ ተጠምቆ የባሕርይ ልጅነቱንና አምላክነቱነን ከአብ እና ከመንፈሰ ቅዱስ አስመስክሮ ዕለቱን ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ጾምን ጀምሯል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመው ሕግና የሠራው ሥርዓት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደውሃ ፈሳሽ አይደለም፡፡ ቅድመ ዓለም በልብ የመከረውን ኋላም በነቢያት ያናገረውን ትንቢትና ምሳሌ፣ ያስቈጠረውን የዘመን ሱባዔ፣ ለአዳም የሰጠውን የመዳን ተስፋ ለመፈጸም ነው እንጂ፡፡ የተነገረውን ትንቢት፣ የተመሰለውን ምሳሌም እንደሚከተለው መጻሕፍት ይነግሩናል፤

‹‹ወአሜሃ መጽአ እግዚእ ኢየሱስ እምገሊላ ውስተ ዮርዳኖስ ከመ ይጠመቅ እምኀበ ዮሐንስ፤ ያን ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ›› /ማቴ.፫፥፲፫፤ ማር.፩፥፱፤ ሉቃ.፫፥፳፩፤ ዮሐ.፩፥፴፪/፡፡ ዮሐንስ ግን አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጂ ጌታ በአገልጋዩ እጅ ይጠመቃልን? አገልጋይ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ ጌታ ወደ አገልጋዩ ይሔዳልን ብሎ አይኾንም አለው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከናዝሬት ወደ ዓይነ ከርም ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ በመጣች ጊዜ የዮሐንስ እናት ቅድስት ኤልሳቤጥ ‹‹የጌታየ እናቱ እኔ ወደ አንቺ እመጣለሁ እንጂ አንቺ ወደኔ ትመጭ ዘንድ ይገባኛልን?›› ብላ ነበርና ከዚያ አያይዞ ተናግሮታል፡፡ ጌታም መልሶ ‹‹ይህ ለኛ ተድላ ደስታችን ነው፤ አንተመጥምቀ መለኮት› ተብለህ ክብርህ ሲነገር፤ እኔምበአገልጋዩ እጅ ተጠመቀ› ተብዬ ትሕትናየ ሲነገር ይኖራል፡፡ ትንቢተ ነቢያትንም ልንፈጽም ይገባናልና አንድ ጊዜስ ተው›› አለው፡፡ አንድ ጊዜ ቢጠመቅ ሁለተኛ፤ በፈቃድ ቢጠመቅ በግድ፤ በሰውነቱ ቢጠመቅ በአምላክነቱ መጠመቅ አያሻውምና፡፡

ዮሐንስ እንዲያጠምቅ ጌታም በዮሐንስ እጅ እንዲጠመቅ በነቢያት ትንቢት ተነግሯልና ጌታችን ‹‹ትንቢተ ነቢያትንም ልንፈጽም ይገባናል›› አለ፡፡ ዳግመኛም ይህ ለምእመናን ተድላ ነውና እናንተም ብትጠመቁ መንፈስ ቅዱስ ይወርድላችኋል ለማለት፤ እንደዚሁም ይህ ለባሕርይ አባቴ ለአብ፣ ለባሕርይ ልጁ ለእኔ፣ ለባሕርይ ሕይወቴ ለመንፈስ ቅዱስ ተድላ ደስታችን ነውና ማለቱ ነው፡፡ አንዱ አካል ወልድ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ፤ እግዚአብሔር አብ በደመና ኾኖ ‹‹ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር፤ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤›› ብሎ ሲመሠክር፤ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ተገልጧልና፡፡ ጌታችን ዮሐንስን ‹‹የጀመርነውንም የቸርነት ሥራ ልንፈጽም ይገባናል … አንድ ጊዜስ ተው›› ካለው በኋላም ተወው (ለማጥመቅ ፈቃደኛ ኾነ)፡፡

ዮሐንስም ‹‹አብ በአንተ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፡፡ አንተም በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነህ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በአንተና በአብ ህልው ነው፡፡ ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለው አንተን በማን ስም ላጥምቅህ?›› ቢለው ‹‹ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጼዴቅ›› ብለህ አጥምቀኝ አለው፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ባሕር ወርደዋል፡፡ ‹‹ወተጠሚቆ እግዚእ ኢየሱስ ሶቤሃ ወፅአ እማይ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ከውኀው ወጣ፤›› /ዮሐ.፫፥፲፮/፡፡ ቃለ ወንጌል ‹‹ወናሁ ተርኅወ ሎቱ ሰማይ፤ ሰማይ ተከፈተለት›› ይላል፡፡ ይህን ሲልም በሰማይ መከፈት መዘጋት ኑሮበት አይደለም፡፡ የተዘጋ በር በተከፈተ ጊዜ በውስጡ ያለው ዕቃ በግልጽ እንዲታይ ጌታን ሲጠመቅ ከዚህ በፊት ያልተገለጸ ምሥጢር ታየ ሲል ነው፤ ይኸውም የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ነው፡፡

ከዚህ ላይ ‹‹ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሔዶ መጠመቁ ለምንድን ነው? ምነው አገልጋይ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ ጌታ ወደ አገልጋዩ ይሔዳልን? አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጂ ጌታ በአገልጋዩ እጅ ይጠመቃልን?›› የሚልጥያቄ ከተነሣ ጌታችን መምጣቱ ለትሕትና እንጂ ለልዕልና አይደለምና ነው፡፡ ዳግመኛም ለአብነት ነው፤ ጌታችን ዮሐንስን ‹‹መጥተህ አጥምቀኝ›› ብሎት ቢኾን ኖሮ ዛሬ ነገሥታት፣ መኳንንት ካህናትን ‹‹ከቤታችን መጥታችሁ አጥምቁን›› ባሉ ነበርና፡፡ ካህናት ካሉበት ከቤተ ክርስቲያን ሒዳችሁ ተጠመቁ ለማለት አብነት ለመኾን ራሱ ጌታችን ወደ ዮሐንስ ሔዶ ተጠመቀ፡፡

ጌታችን መጠመቁም ለእርሱ ክብር የሚጨመርለት ኾኖ አይደለም፤ ዮርዳኖስን ብርህት ማኅፀን እንድትኾን ለማድረግ፤ እኛ ምእመናንም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ዳግም ተወልደን መንግሥተ ሰማያት እንድንገባ ለማድረግ፤ እንደዚሁም ሥርዓተ ጥምቀትን ለማስተማርና አብነት ለመኾን ነው፡፡ ‹‹ዘኢተወልደ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይሬእያ ለመንግሥተ እግዚአብሔር፤ ዳግመኛ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ያልተወለደ ማለትም ያልተጠመቀ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ … ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኅን ወዘሰ ኢአምነ ወኢተጠምቀ ይደየን፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፡፡ ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል፤›› ተብሎ ተጽፏልና /ዮሐ. ፫፥፫፤ ማር.፲፮፥፲፮/፡፡

ያውስ ቢኾን ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለምን ነው? ቢሉ ትንቢቱን፣ ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፤ ትንቢቱ፡- ‹‹ባሕርኒ ርእየት ወጐየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ፤ ባሕር አይታ ሸሸች፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፡፡ … ርእዩከ ማያት እግዚኦ ርእዩከ ማያት ወፈርኁ፤ አቤቱ ውኆች አንተን አይተው ሸሹ፤›› ተብሎ ተነግሯል /መዝ. ፸፮፥፲፮፤ ፻፲፫፥፫/፡፡

ምሳሌው፡- ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ (ምንጩ) አንድ ነው፤ ዝቅ ብሎ በደሴት ይከፈላል፤ ከታች ወርዶ ይገናኛል፡፡ ዮርዳኖስ ከላይ (ነቁ) ምንጩ አንድ መኾኑ የሰውም መገኛው (ምንጩ) አንድ አዳም ለመኾኑ፤ ዮርዳኖስ ዝቅ ብሎ በደሴት መከፈሉ እስራኤል በግዝረት፣ አሕዛብ በቍልፈት ለመለያየታቸው፤ ዮርዳኖስ ከታች በወደብ መገናኘቱ በክርስቶስ ጥምቀት ሕዝብና አሕዛብ አንድ ወግን ለመኾናቸው ምሳሌ ነው፡፡

ዳግመኛም አብርሃም ለአምስቱ ነገሥተ ሰዶም ረድቶ አራቱን ነገሥተ ኮሎዶጎሞር ድል ነሥቶ በተመለሰ ጊዜ ደስ ቢለው ‹‹በመዋዕልየኑ ትፌኑ ቃለከ ወሚመ ታርዕየኒሁ ኪያሃ ዕለተ፤ በዘመኔ ቃልህን (እግዚአብሔር ወልድን) ትልከዋለህን? ወይስ ያቺን የማዳንህን ቀን በዓይኔ ታሳየኝ ይኾን፤›› ብሎ በጠየቀው ጊዜ ‹‹ምሳሌውን ታያለህና ዮርዳኖስን ተሻግረህ ሒድ፤›› ብሎታል፡፡ አብርሃምም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ቢሔድ መልከ ጼዴቅ ኅብስተ አኮቴት፣ ጽዋዓ በረከት ይዞ ተቀብሎታል፡፡ ይኸውም አብርሃም የምእመን፤ ዮርዳኖስ የጥምቀት፤ መልከ ጼዴቅ የካህናት፤ ኅብስተ አኰቴት፣ ጽዋዓ በረከት የሥጋው የደሙ ምሳሌ ነው /ዘፍ. ፲፬፥፲፫-፳፬/፡፡

ኢዮብና ንዕማን በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቀው ከደዌያቸው ድነዋል /፪ኛነገ.፭፥፰-፲፱/፡፡ ኢዮብና ንዕማን የአዳምና የልጆቹ፤ ደዌ የመርገመ ሥጋ፣ የመርገመ ነፍስ፤ ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ኢዮብ፣ ንዕማን፣ ጌታ የተጠመቁበት ዮርዳኖስ ወደቡ አንድ ነው፡፡ እንደዚሁም እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በኋላ በኢያሱ ጊዜ ወደ ምድረ ርስት ሲሔዱ ከዮርዳኖስ ወንዝ ደረሱ፡፡ ታቦቱን የተሸከሙና ልብሰ ተክህኖ የለበሱት ሌዋውያን ካህናት በፊት በፊት ሲጓዙ ታቦቱን የሚያጅቡ ሕዝበ እስራኤል ከታቦቱና ከሌዋውያን ካህናት ሁለት ሺሕ ክንድ ርቀው ዮርዳኖስ ከላይና ከታች ተከፍሎላቸው በየብስ ተሻግረው ኢየሩሳሌም ገብተዋል፡፡ ምእመናንም በማየ ገቦ ተጠምቀው ገነት መንግሥተ ሰማያት ለመግባታቸው ምሳሌ ነው፡፡

ኤልያስም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ብሔረ ሕያዋን ገብቷል፡፡ የኤልያስ ደቀ መዝሙር ኤልሳዕ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዮርዳኖስ ዳር እንጨት ሲቈርጡ መጥረቢያው ከውኀው ውስጥ ወደቀ፡፡ ኤልሳዕ የእንጨት ቅርፊት በትእምርተ መስቀል አዘጋጅቶ ምሳሩ ከወደቀበት ላይ ቢጥልበት የማይዘግጠው ቅርፊት ዘግጦ የዘገጠውን ብረት አንሳፎ አውጥቶታል፡፡ እንደዚሁም ዅሉ በባሕርዩ ሕማም ሞት የሌለበት አምላክ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በዮርዳኖስ ተጠምቆ፣ በቀራንዮ በዕፀ መስቀል ተሰቀሎ፣ ከጎኑ ጥሩ ውኀና ትኩስ ደም አፍስሶ በሲኦል የወደቀው አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ ነው /፪ኛነገ. ፮፥፩–፯/፡፡ ይህንን ዅሉ ምሳሌ ለመፈጸም ጌታችን በዮርዳኖስ ተጠምቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀበት ምሥጢር ምንድን ነው? ቢሉ ዲያብሎስ በአዳምና በሔዋን የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ አገዛዝ ስቃይ አጸናባቸው፡፡ ከዚያም ‹‹‹አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስአዳም የዲያብሎስ ተገዥ፤ ሔዋንም የዲያብሎስ ተገዥ አገልጋዮች ነን› ብላችሁ ስመ ግብርናታችሁን (የተገዥነታችሁን ስም) ጽፋችሁ ብትሰጡኝ መከራውን አቀልላችሁ ነበር›› አላቸው፡፡ እነሱም መከራው የሚቀልላቸው መስሏቸው ‹‹አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ›› ብሎ በማይጠፋ በሁለት ዕብነ ሩካም (ዕብነ በረድ) ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ፤ አንዱን በሲኦል ጥሎት ይኖር ነበር፡፡ በዮርዳኖስ የጣለውን ጌታችን ሲጠመቅ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ እንደ ሰውነቱ ተረግጦ አጥፍቶልናል፡፡ በሲኦል የጣለውንም በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ ነፍሳትን ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ ሲያወጣ አጥፍቶልናል፡፡ ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀበት አንደኛው ምሥጢርም ይህ ነው፡፡

ጌታችን ጥምቀቱን በውኀ ያደረገው በሌላ ያላደረገው ስለምንድን ነው ቢሉ ትንቢቱ፣ ምሳሌው ሊፈጸም፤ ትንቢት፡- ‹‹ወእነዝኃክሙ በማይ ወትነጽሑ፤ ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ፤ እናንተም ትጠራላችሁ፤›› ተብሎ ተነግሯል /ሕዝ.፳፮፥፳፭/፡፡ ምሳሌ፡- ውኀ ለዅሉ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለ ውኀ መኖር የሚችል የለም፡፡ ጥምቀትም ለዅሉም የሚገባ ሥርዓት ነው፡፡ ያለ ጥምቀት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይቻልምና፡፡ ውኀ መልክ ያሳያል፤ መልክ ያለመልማል (ያጠራል)፡፡ ጥምቀትም መልክዐ ነፍስን ያሳያል፤ መልክዐ ነፍስን ያለመልማልና (ያጠራልና)፡፡

መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥበት አየ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መውረዱም ምሥጢር አለው፡፡ ርግብ ኃዳጊተ በቀል ናት፤ መንፈስ ቅዱስም ኃዳጌ በቀል ነውና፡፡ ርግብ በኖኅ ጊዜ ‹‹ሐጸ ማየ አይኅ ነትገ ማየ አይኅ፤ የጥፋት ውኀ ጎደለ›› ስትል ቆጽለ ዕፀ ዘይት ይዛ ተገኝታለች፡፡ መንፈስ ቅዱስም ተስፋ መስቀልን ያበሥራልና፡፡ ጥምቀቱን በቀን ያላደረገው በሌሊት ያደረገው ስለ ምን ነው ቢሉ በቀን አድርጎት ቢኾን መንፈስ ቅዱስ በቁሙ ርግብ ነው በተባለ ነበርና፤ አሁንስ ርግብ አለመኾኑ መንፈስ ቅዱስ መኾኑ በምን ይታወቃል ቢሉ ጌታ የተጠመቀው ከሌሊቱ በዐሥረኛው ሰዓት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ተሐዋስያን ወፎች (ርግቦች) ከየቦታቸው አይወጡምና መንፈስ ቅዱስ መኾኑ በዚህ ይታወቃል፡፡

መንፈስ ቅዱስም መውረዱ ከውኀው ከወጣ፣ ከዮሐንስ ከተለየ በኋላ ነው፡፡ ከውኀው ውስጥ ሳለ ወርዶ ቢኾን ለቀድሶተ ማያት ነው የወረደው ባሉት ነበርና፡፡ ከዮሐንስ ጋርም ሳለ ወርዶ ቢኾን ለክብረ ዮሐንስ ወረደ ባሉት ነበርና፡፡ ረቦ ወርዷል ያሉ እንደ ኾነ አብ ምሉዕ ነው፤ አንተም ምሉዕ ነህ፤ እኔም ምሉዕ ነኝ ሲል፡፡ አሰይፎ ወርዷል ያሉ እንደ ኾነ የብሉየ መዋዕል የአብ ሕይወት ነኝ፤ የአንተም ሕይወት ነኝ፤ እኔም ብሉየ መዋዕል ነኝ ሲል፡፡ ወርዶ ራሱን ቆንጠጥ አድርጎ ይዞታል ቢሉ አብ አኃዜ ዓለም ነው፤ አንተም አኃዜ ዓለም ነህ፤ እኔም አኃዜ ዓለም ነኝ ሲል፡፡ ምሥጢሩም እናንተም ብትጠመቁ መንፈስ ቅዱስ ይወርድላችኋል ለማለት፣ አብነት ለመኾን ነው፡፡

‹‹ወናሁ መጽአ ቃል እምሰማይ ዘይብል ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ፤ ለተዋሕዶ የመረጥኩት በእርሱ ህልው ኾኜ ልገለጥበት የወደድኩት የባሕርይ ልጄ ይህ ነው፤›› የሚል ቃል ከወደ ሰማይ ተሰማ፡፡ ይህም አብ የተናገረበት ቃል ያው የሚጠመቀው አካላዊ ቃል ነው እንጂ ሌላ ቃል አይደለም፡፡ የሥላሴ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ አንድ ነውና፡፡ አብ ልብ፤ ወልድ ቃል፤ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ በመኾን አንድ አምላክ ነውና፡፡ ‹‹አብኒ ልቡናሆሙ ለወልድ ወለመንፈስ ቅዱስ ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ ወመንፈስ ቅዱስኒ እስትንፋሶሙ ለአብ ወለወልድ፤ አብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ልቡናቸው ነው፡፡ ወልድም ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ለአብ ለወልድ ሕይወታቸው ነው፤›› በማለት ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት እንደ ተናገረው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀውም በሠላሳ ዓመቱ ነው /ሉቃ. ፫፥፳፫/፡፡ በሠላሳ ዓመቱ የተጠመቀበት ምሥጢርም አዳም የሠላሳ ዓመት፤ ሔዋን የዐሥራ አምስት ዓመት ሰው ኾነው ተፈጥረው አዳም በዐርባ ቀን፣ ሔዋን በሰማንያ ቀን ከሥላሴ የተቀበሉትን ልጅነት በምክረ ከይሲ ዕፀ በለስን በልተው አስወስደው ነበረና በሠላሳ ዓመቱ ተጠምቆ መልሶላቸዋል፡፡ በሠላሳ ዓመት የመጠመቁ ምሥጢር ይህ ሲኾን እኛ ዛሬ ወንዶች በዐርባ ቀን፣ ሴቶች በሰማንያ ቀን በዕለተ ዓርብ ከቀኝ ጎኑ በፈሰሰው ማየ ገቦ ተጠምቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ሁለተኛ የምንወለድበት ምክንያትም አዳም በዐርባ ቀኑ፣ ሔዋን በሰማንያ ቀኗ ከሥላሴ ያገኙትን ልጅነት መሠረት በማድረግ ነው /ኩፋ. ፬፥፱/፡፡ የምንጠመቀውም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡ ‹‹ወእንዘ ታጠምቅዎሙ በሉ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤ ስታጠምቋቸውም በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው፤›› እንዲል /ማቴ. ፳፰፥፲፱/፡፡

ዛሬም ታቦታቱን ወደ ጥምቀተ ባሕር በማውረድ በዓለ ጥምቀቱን ለሚያከብሩ ክርስቲያኖች በሙሉ ከታቦታቱ ሁለት ሺሕ ክንድ ርቀው መከተል እንዲገባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተብሎ ተገልጿል፤ ‹‹ሕዝቡን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ተከተሉት፡፡ በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሺሕ ክንድ ይኹን፡፡ በዚህ መንገድ በፊት አልሔዳችሁበትምና፤ የምትሔዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ፤›› /ኢያ.፫፥፩–፲፯/፡፡

ይህ ኃይለ ቃል ዛሬ ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርደው ለማደራቸው መነሻ ትምህርት ነው፡፡ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀትም ጌታችን ከተጠመቀበት ከ፴ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ሲከበር ይኖራል፡፡

ከበዓለ ጥምቀቱ ረድኤት፣ በረከት ይክፈለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡