ዘመነ ፍሬ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፲፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የተወደዳችሁ ምእመናን! ከአሁን በፊት ‹ዘመነ ክረምት ክፍል አራት› በሚል ርእስ ባቀረብነው ዝግጅት የሰው ልጅ ዓቅሙ በሚችለው ኹሉ ጠንክሮ እየሠራ የመኖር ተፈጥሯዊና ክርስቲያናዊ ግዴታ እንዳለበት፤ እየሠራም የድካሙን ዋጋ እንዲያገኝ መጸለይ፣ እየጸለየ ደግሞ የጸሎቱን ውጤት ለመቀበል ተግቶ መሥራት እንደሚገባው የሚያስገነዝብ ትምህርትና እንደዚሁም ከነሐሴ ፳፰ እስከ መስከረም ፩ ቀን ድረስ ያለው ክፍለ ክረምት ‹‹ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃን መዓልት›› እንደሚባል፣ በዚህ ክፍለ ክረምት ውስጥ ባሉት ቀናትም እነዚህን ፍጥረታት የሚመለከቱ ትምህርታት እንደሚቀርቡ በማስታዎስ ወቅቱን ከክርስቲያናዊ ሕይወት ጋር የሚያስቃኝ ዝግጅት አቅርበን ነበር፡፡ በተጨማሪም ከመስከረም ፩-፰ ቀን ድረስ ያለው ፭ኛው የክረምት ክፍለ ጊዜ ‹‹ዮሐንስ›› እንደሚባልና ይህ ወቅት የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሕይወት ከአዲሱ ዓመት ጋር እየተጣጣመ በስፋት የሚዳሰስበት ጊዜ እንደ ኾነ መጥቀሳችን የሚታወስ ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችንም ስድስተኛውን የክረምት ክፍለ ጊዜ የሚመለከት አጭር ትምህርት ይዘን ቀርበናል፤ እንድትከታተሉልን በአክብሮት እንጋብዛለን!

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ከመስከረም ፱ – ፲፭ ቀን ያለው ክፍለ ክረምት ‹ፍሬ› ይባላል፡፡ ‹ዘመነ ፍሬ› ደግሞ ‹የፍሬ ወቅት፣ የፍሬ ዘመን፣ የፍሬ ጊዜ› ማለት ሲኾን ይኸውም ልዩ ልዩ አዝርዕት በቅለው፣ አድገው፣ አብበው ለፍሬ የሚደርሱበት፤ የሰው ልጅ፣ እንስሳትና አራዊትም ጭምር የዕፀዋቱን ፍሬ (እሸት) የሚመገቡበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚቀርቡ ምንባባትና ትምህርቶችም ይህንኑ ምሥጢር የሚዳስሱ ናቸው፡፡ በክፍል አንድ ዝግጅታችን እንደ ተመለከትነው ዕፀዋት በጥፍር የሚላጡ (ሎሚ፣ ሙዝ፣ ትርንጎ፣ ወዘተ)፤ በማጭድ የሚታጨዱ (ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ወዘተ)፤ በምሳር የሚቈረጡ (ወይራ፣ ዋርካ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ፣ ወዘተ) በመባል በሦስት ይከፈላሉ፡፡

ተፈጥሯቸውም እንደ ሰው ልጅ ከአራቱ ባሕርያት ከነፋስ፣ እሳት፣ ውሃና አፈር (መሬት) ሲኾን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩት አራቱ ባሕርያት በዕፀዋት ሕይወት ላይ ለውጥ ሲያመጡ ይስተዋላል፤ ማለት ከነፋስ በመፈጠራቸው በነፋስ ያብባሉ፤ ያፈራሉ፡፡ ከእሳት በመፈጠራቸው አንዳንዶቹ እርስበርሳቸው ሲፋተጉ እሳት ያስገኛሉ፡፡ ከውሃ በመፈጠራቸውም ፈሳሽ ያወጣሉ፡፡ ከአፈር በመፈጠራቸው ደግሞ ሲቈረጡ በስብሰው ወደ አፈርነት ይቀየራሉ፡፡ ከፍሬ አያያዛቸው አኳያም በራሳቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ስንዴ፣ገብስ፣ ጤፍ፣ ወዘተ)፤ በጎድናቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ማሽላ፣ በቆሎ፣ ባቄላ፣ ወዘተ)፤ በውስጣቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ዱባ፣ ቅል፣ ወዘተ)፤ በሥራቸው የሚያፈሩ (ምሳሌ፡- ሽንኩርት፣ ቀይ ሥር፣ ካሮት፣ ድንች፣ ወዘተ) ተብለው በአራት ይመደባሉ /ትርጓሜ ኦሪት ዘፍጥረት ፩፥፮-፲፫/፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት የሰው ልጆችን ሕይወት ከዕፀዋት ጋር በማነጻጸር ይገልጹታል፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ  በነፋስ ባሕርዩ ፍጥነት፤ በእሳት ባሕርዩ ቍጣ፤ በውሃ ባሕርዩ መረጋጋት፤ በመሬት ባሕርዩ ደግሞ ትዕግሥት ወይም ሞት እንደሚስማማው የሚያስተምር ንጽጽር ነው፡፡ በሌላ በኩል አዝርዕት ከበሰበሱ በኋላ ፍሬ እንደሚያስገኙ ኹሉ ሰውም ከሞተ በኋላ ተነሥቶ እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን ይቀበላል፡፡ ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ በሚከተለው መንገድ ገልጾታል፤ ‹‹… የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው፡፡ በመበስበስ ይዘራል፤ ባለመበስበስ ይነሣል፡፡ በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፡፡ በድካም ይዘራል፤ በኃይል ይነሣል፡፡ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፤ መንፈሳዊ አካል ይነሣል …›› /፩ቆሮ.፲፭፥፵፪-፵፬/፡፡

ዕፀዋት የሚሰጡት ፍሬ እንደየማፍራት ዓቅማቸው ይለያያል፤ ፍሬ የማያፈሩ፣ ጥቂት ፍሬ የሚያፈሩ፣ ብዙ ፍሬ የሚያፈሩ ዕፀዋት ይገኛሉ፡፡ እንደዚሁ ኹሉ ምእመናንም በክርስትና ሕይወታችን የሚኖረን በጎ ምግባር የአንዳችን ከአንዳችን ይለያል፡፡ ፍሬ የክርስቲያናዊ ምግባር እንደዚሁም የሰማያዊው ዋጋ ምሳሌ ነውና፡፡ በክርስትና ሕይወት ያለምንም በጎ ምግባር የምንኖር ኀጥአን ብዙዎች የመኾናችንን፤ እንደዚሁም ጥቂት በጎ ምግባር ያላቸው ምእመናን የመኖራቸውን ያህል በአንጻሩ ደግሞ በጽድቅ ላይ ጽድቅ፣ በመልካም ሥራ ላይ መልካም ሥራን የሚፈጽሙ፤ ከጽድቅ ሥራ ባሻገር በትሩፋት ተግባር ዘወትር ጸንተው የሚኖሩ አባቶችና እናቶችም ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ይህንን ዓይነት የክርስቲያናዊ ሕይወት ልዩነት ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፤ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል … ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፤ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል›› በማለት ይገልጸዋል /፪ቆሮ.፱፥፮-፲/፡፡ ገበሬ በዘራው መጠን ሰብሉን እንዲሰበስብ ‹‹ለኹሉም እንደየሥራው ዋጋውን ትከፍለዋለህ›› ተብሎ እንደ ተጻፈው ክርስቲያንም በሠራው መጠን ዋጋውን ያገኛልና በጸጋ ላይ ጸጋን፣ በበረከት ላይ በረከትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይጨመርልን ዘንድ ኹላችንም መልካም ሥራን በብዛት ልንፈጽም ይገባናል፡፡ ‹‹… እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል፡፡ እናንተ ደግሞ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፡፡ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና›› እንዳለን ሐዋርያው /ያዕ.፭፥፯-፰/፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ምድርኒ ወሀበት ፍሬሃ፤ ምድርም ፍሬዋን ሰጠች›› /መዝ.፷፮፥፮፤ ፹፬፥፲፪/ የሚለውን የዳዊት መዝሙርና ሌሎችንም ተመሳሳይ ኃይለ ቃላት ሲተረጕሙ ምድር በኢየሩሳሌም፣ በቤተ ክርስቲያን፣ በምእመናን፣ በእመቤታችን፤ ፍሬ ደግሞ በቃለ እግዚአብሔር (ሕግ)፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር፣ እንደዚሁም በጌታችን በመድኂታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመሰል ያስተምራሉ፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹ምድርም ፍሬዋን ሰጠች (ትሰጣለች)›› በሚለው ኃይለ ቃል ምድር የተባለች ኢየሩሳሌም የዘሩባትን እንደምታበቅል፤ የተከሉባትን እንደምታጸድቅ፤ አንድም ይህቺ ዓለም ፍሬን፣ አምልኮተ እግዚአብሔርን እንደምታቀርብ፤ አንድም ቤተ ክርስቲያን ወይም ምእመናን እግዚአብሔርን ሲያመልኩ እንደሚኖሩ፤ ከዚሁ ኹሉ ጋርም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን ያስረዳል፡፡ ለዚህም ነው በዘወትር ጸሎታችን ‹‹ቡርክት አንቲ እምአንስት ወቡሩክ ፍሬ ከርሥኪ፤ አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽ ፍሬም የተባረከ ነው›› /ሉቃ.፩፥፳፰/ እያልን እመቤታችንንና ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን የምናመሰግነው፡፡

በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ እንደምናገኘው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስትና ሕይወትን ከዘርና ፍሬ ጋር በማመሳሰል አስተምሯል፡፡ ይኸውም አንድ ገበሬ ዘር ሲዘራ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር ከመብቀሉ በፊት በወፎች እንደ ተበላ፤ በጭንጫ ላይ የተጣለውም ወዲያውኑ ቢበቅልም ነገር ግን ጠንካራ ሥር ስለማይኖረው በፀሐይ ብርሃን እንደ ጠወለገ፤ በእሾኽ መካከል የወደቀው ደግሞ ሲበቅል በእሾኽ እንደ ታነቀ፤ ከኹሉም በተለየ መልኩ በመልካም መሬት ላይ የተጣለው ዘር ግን አድጎ መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ ፍሬ እንደ ሰጠ ያስረዳል፡፡ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ተረጐመላቸው በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ የማያስተውል ክርስቲያን ምሳሌ ነው፤ ሙሉ እምነት ስለማይኖረው በመከራው ጊዜ አጋንንት ይነጥቁታልና፡፡ በጭንጫ ላይ የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበል፣ ነገር ግን ተግባራዊ የማያደርግ ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ ይህ ምእመን በጠንካራ እምነት ላይ የጸና አይደለምና በሃይማኖቱ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በደረሰበት ጊዜ ፈጥኖ ይሰናከላል፡፡ በእሾህ መካከል የተዘራውም ቃሉን የሚሰማ ነገር ግን በዚህ ዓለም ዐሳብና ባለጠግነት ተታሎ ቃሉን የማይተገብር ክርስቲያን  ምሳሌ ነው፡፡ በመልካም መሬት የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሰምቶ የሚተገብር ክርስቲያን ምሳሌ፡፡

እንደዚህ ዓይነት ምእመን በተማረው ትምህርት ጸንቶ ይኖራል፤ መልካም ሥራም ይሠራል፡፡ በመልካም መሬት የተዘራው ዘር ስለ አንዱ ፋንታ መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ እንደሚያፈራ ኹሉ በክርስቲያናዊ ግብር ጸንቶ የሚኖር ምእመንም ሥራውን በሦስት መንገድ ማለትም በወጣኒነት፣ በማእከላዊነትና በፍጹምነት ደረጃ እንደሚወጣ፤ ዋጋውንም በሥራው መጠን እንደሚያገኝ ያስረዳል፡፡ አንድም ባለ መቶ ፍሬ የሰማዕታት፤ ባለ ስድሳ የመነኰሳት፤ ባለ ሠላሳ በሕግ ተወስነው በዓለም የሚኖሩ ምእመናን ምሳሌ ነው፡፡ በተመሳሳይ ምሥጢር ኹሉም የፍሬ መጠን በኹሉም ምእመናን ሕይወት ውስጥ እንደሚስተዋል ሊቃውንት ይተረጕማሉ፡፡ ስለዚህም በሰማዕትነትም፣ በምንኵስናም፣ በዓለማዊ ሕይወትም ውስጥ የሚኖሩ ምእመናን መልካም ግብራቸው እጅግ የበዛ ከኾነ በባለ መቶ ፍሬ፤ መካከለኛ ከኾነ በባለ ስድሳ፤ ከዚህ ዝቅ ያለ ከኾነ ደግሞ በባለ ሠላሳ ፍሬ ይመሰላል  /ትርጓሜ ወንጌለ ማቴዎስ፣ ማቴ.፲፫፥፩-፳፫/፡፡

ዕፀዋት ለመጠለያነት የማይጠቅሙ እንደዚሁም ለምግብነት ወይም ደግሞ ለመድኀኒትነትና ለሌላም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚጠቅም ፍሬ የማያስገኙ ከኾነ ተቈርጠው እንደሚጣሉ ኹሉ ምእመናንም ‹ክርስቲያን› ተብለን እየተጠራን ብቻ ያለምንም በጎ ምግባርና መንፈሳዊ ሕይወት የምንኖር ከኾነ በምድር መቅሠፍት፤ በሰማይም ገሃነመ እሳት እንደሚጠብቀንና ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጪ እንደምንኾን ከወዲሁ በመረዳት በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ‹‹… ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጧል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ኹሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል›› ተብሎ ተጽፏልና /ማቴ.፫፥፲/፡፡

ከዚሁ ኹሉ ጋርም አዝርዕት ከበሰበሱ በኋላ በቅለው፣ አብበው በራሳቸው፣ በጎድናቸው፣ በውስጣቸውና በሥራቸው እንደሚያፈሩ ኹሉ ምእመናንም በራስ እንደ ማፍራት ፈሪሃ እግዚአብሔርን፤ በጎድን እንደ ማፍራት እርስበርስ መደጋገፍንና መተሳሰብን፤ በውስጥ እንደ ማፍራት ንጽሕናን፤ በሥር እንደ ማፍራት ትሕትናን ገንዘብ ማድረግን ከዕፀዋትና ከአዝርዕት መማር ይገባናል፡፡ እንደዚሁም ዕፀዋት ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶና ከዚያ በላይ መልካም ፍሬ እንደሚያፈሩ ምእመናንም በመልካሟ መሬት በክርስትና የተዘራን የክርስቶስ ዘሮች መኾናችንን አስተውለን፣ ደግሞም ዘር የተባለውን የእግዚአብሔርን ቃል ተምረን መተግበር እንደሚገባን ተረድተን ከወጣኒነት ወደ ማእከላዊነት፤ ከማእከላዊነት ወደ ፍጹምነት በሚያደርስ የጽድቅ ሥራ በመኖር የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ መፋጠን ይኖርብናል፡፡ ከሦስቱ በአንደኛው መደብ ውስጥ ወይም በኹሉም ደረጃዎች አልፈን ዘለዓለማዊ መንግሥቱን እንድንወርስ እግዚአብሔር አምላካችን ይርዳን፡፡

ይቆየን