መጋቢት 3/2004 ዓ.ም.
በዲ/ን ኅሩይ ባየ
“ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ”
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው መተርጉማን፣ ሰባኪያንና የእምነት አርበኞች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከአሕዛብነት ወደ ክርስትና የተመለሱ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን ተብለው በተጠሩበት የሦርያ ዋና ከተማ በሆነችው በአንጾኪያ ተወልዶ ያደገው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሕይወቱ በአርአያነቱ የሚጠቀስ መንፈሳዊ አባት ነው፡፡
አንደበቱ ርቱዕ፣ እውነተኛ ሰባኪ ምግባሩ የታረመ መና ባሕታዊና የቤተክርስቱያን መሪ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ የዚህ ዓለም የእንግድነት ቆይታውን ጥሎ ከተሰናበተ በኋላ ወደ 5ተኛው መቶ ዓመት ማጠናቀቂያ አካባቢ በትምህርቱ የተደነቁ በጽሑፉ የተማረኩ ከሕይወቱ የተማሩ ምእመናን “አፈወርቅ የሚል ቅጽል ስም ሰጥተውታል፡፡ “አፈወርቅ” በግሪክኛ Chyrysostomos በእንግሊዝኛው Golden mouth ተብሎ ይጠቀሳል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በ347 ዓ.ም. ተወልዶ በ407 ዓ.ም. ይህቺን ዓለም እስኪሰናበት ድረስ የተሰጠውን የክህነት አገልግሎት የተወጣ የብዙ ብዙ መጻሕፍትን የደረሰ አባት ነው፡፡ በስብከቱና በጽሑፉ የተማረከ አንድ ጸሐፊ “He terrified the comforted and comforted the terrified ዝንጉዎችን ያስደነግጣል የተጨነቁትን ደግሞ ያጽናናል” ብሎ ጽፎለታል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በተለያዩ ክፍለ ትምህርቶች በርካታ ስብከቶችን ሰብኳል፤ ከእነዚህም ውስጥ “አጋንንት በሰው ሕይወት ላይ ሥልጣን አላቸው” ብለው ለሚናገሩ ሰዎች የሰጠው ትምህርት ይጠቀሳል፡፡ ይህን ስሕተት የሆነ አመለካከት እንዲያስተካክሉ በሦስት ተከታተይ ክፍል ትምህርቱን አቀረበ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በነበረበት ዘመን ሰዎች እርስ በእርሳቸው የሚጠላለፉበት የሞራል ውድቀት የበዛበት፣ ነገሥታቱ በቤተ ክህነት ላይ እጃቸውን እያስገቡ የስልጣናቸው ማራዘሚያ ያደረጉበት እጅግ ፈታኝ ወቅት እንደነበረ በታሪክ መስታወት እንመለከታለን በአሚነ ልቡና እንዘክረዋለን፡፡
አጋንንት በሰው ሕይወት ላይ ሥልጣን አላቸው ማለት ራስን ከተጠያቂነትና ከዘለዓለማዊ ፍርድ ነጻ እንደሚያደርግ ሳይፈራና ሳይታክት አስተማረ፡፡ ከአጋንንት የሚመጣውን ፈተና በፍጹም ተጋድሎ በነጻ ፈቃድ መመከት እንደሚችል፡፡ ሰበከ “ክፋት /ኀጢአት/ የሰው የተፈጥሮ ጠባይ /ባሕርይ/ ገንዘብ” ነው እያሉ የተሳሳተ መረዳት የነበራቸውን ሰዎችን አስተካከላቸው አብሮ የተፈጠረ /የባሕርይ ገንዘብ/ የሆነ ሥራ ሊታረም እንደማይችል እያሳሰበ ኀጢያት በንስሐ በምክር፣ በተግሳጽ፣ በጾም በጸሎት በተጋድሎ ሊወገድ እንደሚችል ያስገነዝባል፡፡ ኀጢአት የሚመጣው ከራስ ድካም ካልቆረጠ ኅሊና ከሰነፈ ልቡና ከላሸቀ ኅሊና ነው፡፡ አዳምና ሔዋን ከራሳቸው ድካም ተነሥተው ኀጢአትን ሠሩ እንጂ ሰይጣን እጃቸውን ጠምዝዞ እጸ በለስን ቆርጦ እንዳልመገባቸው ይታወቃል፡፡
ለኀጢአት በር ካልተከፈተ እንዝህላልነት ከታረቀ በዓቂበ ልቡና ከተተጋ አጋንንት የወደቁና የታሠሩ ጠላቶቻችን እንጂ በእኛ ላይ ምንም ኀይል የላቸውም “ሰይጣን ታስሯል እአስራቱ የሚፈቱት ፈቃዱን የሚፈጽሙ ሰዎች ናቸው” እንደሚበላው ፈቃደ ሥጋን መፈጸም በዓለሙ ብልጭልጭ ነገር መሳብ ያለልክ መብላትና መጠጣት መጠን የሌለው ሥጋዊ ደስታና ከንቱ ቅዥት አጋንትን ኀይል ያስታጥቃል፡፡
ቅዱሱ የእግዚአብሔር ሰው ዮሐንስ ተጸጽተው ንስሓ የገቡ አባቶችን ለአብነት በመጥቀስ የእግዚብሔርን መሐሪነት አስተምሯል፡፡ እምቢ ብለው ሕይወታቸውን ከንስሐ ያራቁ ሰዎች ደግሞ በጥፋት ጎዳና መጓዛቸውን ሰበከ፡፡ በመጨረሻም “መውደቅ አዳማዊ ነው ወድቆ አለመነሣት ግን ዲያብሎሳዊ ነው” ብሎ አባታዊ ምክሩን ለገሣቸው፡፡
/ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱና ትምህርቱ 1999፥108/ “መውደቅ አዳማዊ ነው” እንዴት፥?
ከተፈጠርንበት ሰባት ባሕርያት አንዱ አፈር ነው አፈር ሲታጠብ ቢውል እንደማይነኀጻው የሰዎች ጠባይ በተለያዩ ምክንያቶች ሊጎድፍ ይችላል፡፡ ሰው እንደውሎው እንደ አካባቢው እንደ ግንዛቤው ለሚቀርቡለት ጥያቄ የራሱ የሆነ ግብረ መልስ ይኖረዋል፡፡ በቅድስና ሕይወታቸው የሚታወቁ አባቶቻችን በስሕተት መንገድ ውስጥ አልፈዋል፡፡ ለዚህም ነው አባቶቻችን “ሰው ሆኖ የማይበድል እንጨት ሆኖ የማይጨስ የለም” የሚሉት፡፡
“ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል” /ምሳ.24፥16 ብሎ ጠቢቡ መናገሩም በምድር ላይ ያለን እኛ በሥጋ ፈቃድ ተታለን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በስሕተትም ይሁን በድፍረት ልንወድቅ እንችላለን፡፡ ዋናው ጥያቄ ለምን ወደቅን? ሳይሆን ለምን አልተነሣንም ነው፡፡
ብዙ ሰዎች ለውድቀታቸው ምክንያት ማቅረብ ይወዳሉ ከተጠያቂነት ለመሸሽ /ለማምለጥ/ የማይቆፍሩት ጉድጓድ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ምክንያት ጠቃሚ ቢሆን ኖሮ አዳም ሔዋንና እባብ ከተፈረደባቸው ፍርድ ባመለጡ ነበር፡፡ ምክንያት ረብ /ጥቅም/ የሌለው በመሆኑ ለበደሌ ለውድቀቄና ለሽንፈቴ ምክንያቱ እኔ ነኝ ማለትን መለማመድ አለብን፡፡
ነቢዩ ዳዊት “አንተን ብቻ በደልሁ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ /መዝ.50፥4/ ብሎ መጸለዩ ተጠያቂነቱን በራሱ አድርጎ ነው፡፡ ነቢዩ ዮናስም የመርከቧ መታወክ የሞገዱ ማየል የነፋሱ ንውጽውጽታ በእኔ ምክንያት የሆነ ነው፡፡ ብሎ ስሕተቱን አምኗል፡፡ ነቢዩ ሙሴ እኔ አንደበቴ ኮልታፋ ነው የፈርዖን አምላክ የእሥራኤል መሪ እንዴት ታደርገኛለህ ብሎ ደካማነቱን አመነ፡፡ ለዚህ ያደረስከኝ እኔ ማን ነኝ ቤቴስ ምንድን ነው? እያሉ መጻተኛነታቸው ያመኑ ጉስቁልናቸውን የተረዱ አባቶች ራሳቸውን በመንፈስ ድኀ አድርገዋል፡፡ ቀራጩም ሲጸልይ “እኔ ኀጢያተኛውን ማረኝ” ብሎ ነበር /ሉቃ.18፥13/
መውደቅ እጅን ለዲያብሎስ መስጠት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር መለየት ነው፤ ከቅዱሳኑ ኅብረት መገለል ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመጀመሪያው ሞት ነው፡፡ በመጀመሪያው ትንሣኤ /ትንሣኤ ልቡና/ ተስፋ የሌላቸው ሰዎች ሁለተኛው ሞት /ሞተ ነፍስ/ ይፈረድባቸዋል፡፡ /ራዕ.20፥14/
- ነቢዩ ዳዊት ሳተ እግዚአብሔር ይቅር አለው
- ቅዱስ ጴጥሮስ ካደ መሐሪው አምላክ ይቅር አለው
የአባቱን ሀብትና ንብረት ከፍሎ የኮበለለው ወጣት ወደ ልቡ ሲመለስ አባቱ በይቅርታ ተቀብሎታል፡፡ እኛም መውደቃችን ሳይሆን አለመነሣታችን ሲያሳስበን ይገባል፡፡
መውደቅ /መሳሳት/ አዳማዊ ጠባይ በመሆኑ በመውደቃችን አይፈረድብንም ማንኛውም ሰው ኀጢአትን የመሥራት ዝንባሌ ሊታይበት ይችላልና፡፡ እኛን የሚያስፈርድብን በኀጢአት ላይ አቋም ይዘን በንስሓ አለመነሣታችን ነው፡፡
ዲያብሎስ ስሕተቱን ማመን አልቻለም ስለዚህ ወድቆ ቀረ በበደል ወድቀው በንስሓ ያልተመለሱ ሰዎት የግብር አባታቸውን የዲያብሎስን ፈቃድ ፈጻሚዎች በመሆናቸው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ መውደቅ አዳማዊ ጠባይ ነው ይለናል፡፡
ዲያብሎስን ተቃወሙት ከእናንተም ይሸሻል እግዚአብሔርን እሺ በሉት ወደ እናንተ ይቀርባል፡፡ /ያዕ.4፥8/ ዲያብሎስን መቃወም ፈቃዱን አለመፈጸም ነው፡፡ ዲያብሎስን መቃወም የምንችለው በጾምና በጸሎት ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሳይጸልዩ ወደ ዕለት ሥራቸው የሚሔዱትን ሰዎች እንዲህ እያለ ይመክራቸዋል፡፡ “ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተህ እግዚአብሔርን ለአምላክነቱ እንደሚገባ አምልከህ ከዚያ በኋላ ወደ ሥራህ ብትሔድ የምትሠራው ሥራ የተባረከና የሰመረ እንደሚሆንልህ አታውቅምን? የሚያስጨንቅህ የዚህ ዓለም ገዳይ አለብህ? እዚህ በምታሳልፈው ጊዜ የእግዚአብሔርን ርዳታና ምሕረት ታገኝ ዘንድ በመረጋጋትና በመጽናናት መንፈስ ሆነህ ትሔድ ዘንድ ስለዚህ ምክንያት ወደዚህ ና፡፡
እርሱ ኀይልህ ጋሻህ ይሆን ዘንድ በሰማያዊ ሥልጣን በመጠበቅ ለጠላቶችህ ለአጋንንት የማትሸነፍ ትሆን ዘንድ ወደዚህ ወደ ጸጋው ዙፋን ና፡፡ በአባቶች ከሚደርሰው ጸሎት ሲታርፍ ካለህ በማኅበር ጸሎት ከተሳተፍክ ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ከሰማህ የእግዚአብሔርን ርዳታ ካገኘህ እነዚህን መሳሪያዎች ከታጠቅህ የትም ብትሔድ እንደአንተ ያሉ ሠሪጋ የለበሱ ጠላቶችህ ክፉዎች ሰዎች ይቅርና ዲያብሎስ ራሱ ፊትህን ማየት አይችልም ነገር ግን ከቤትህ እንደተነሣህ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሳትመጣ ወደ ገበያ ወደ ሥራ ወዘተ ብትሔድ ብቻህን ያለምንም መንፈሳዊ ትጥቅና ጸጋ እግዚአብሔር ስለምትሆን ሁሉም ነገር በአንተ ላይ ይበረታብሀል፡፡ ጠላቶችህም በቀላሉ ያጠቁሃል፡፡ በቤታችን ውስጥም ሆነ በውጭ ብዙ ነገሮች እንደ ጠበቅነው ሳይሆን በተቃራኒው የሚሆኑብን አስቀድመን ለመንፈሳዊ ነገር ቅድሚያ ስላልሰጠንና ሌላውን የዚህ ዓለም ነገር ከዚያ በኋላ ማድረግ ሲገባን እኛ ግን ቅደም ተከተሉን ስለ ስለምናገለባብጥ ነው፡፡ ስለዚህ ነገሮች ዝብርቅርቃቸው ይወጣል” ይለናል፡፡
ዲያብሎስ ሆይ ብወድቅ እነሣለሁና በጨለማ ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና በእኔ ደስ አይበልህ /ሚክ.7፥8/ ማለት የምንችለው በንስሓ ወደ አባታችን ወደ እግዚአብሔር ስንመለስ ነው፡፡ ኀይልን በሚሰጠን በክርስቶስ ሁሉን ስለምንችል ክፉ ሥራውን እንጂ ዲያብሎስን አንፈራውም፡፡ የሠራዊት አምላክ አቤቱ መልስን ፈትህንም አብራ እኛም እንድናለን” መዝ.79፥7
ለንስሓ ሞት
ለአዘክሮ ኀጢአት
ለቅዱስ ቊርባን የበቃን ያድርገን
“ሁሉ ከእርሱና በእርሱ በእርሱም ነውና ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን አሜን” ሮሜ.11፥36