የ6 ወር የሥራ አመራር ስብሰባ ውሳኔዎችን አስመልክቶ ከማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ

በማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ያደረገው የ6ወሩ የሥራ አመራር ስብሰባ ወሳኔዎችን አስመልቶ ከማኅበሩ ሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ።

በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የተሠሩ የሐሰት ሰነዶችን አስመልክቶ ከማኅበሩ ሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ሥር ተዋቅሮ በርካታ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለቤተ ክርስቲያን በማበርከት ላይ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በመመራት ሕጋዊ በሆነ መንገድ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ የሚገኝ ማኅበር ነው፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዕድገትና ልማት የማይፈልጉ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን የማኅበሩን መልካም ስም በማጥፋት አገልግሎቱን ለማሰናከል በየጊዜው ይጥራሉ፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማኅበሩን ስም ለማጥፋት አመች ነው ብለው ያሰቡትን የሐሰት ሰነድ የማዘጋጀት ተግባራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ከዚህ በፊት በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የግንቦት ወር ልዩ ዕትም “የማኅበረ ቅዱሳን የ25 ዓመት ዕቅድ” ብለው ያዘጋጁትን የሐሰት ሰነድ አስመልክተን እንደገለጽነው ሁሉ አሁንም ሁለት የሐሰት ደብዳቤዎች በማኅበሩ የመቀሌ ማዕከል ስም ተዘጋጅተው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ መካነ ድር ተለቅቀዋል፡፡

እጅግ በጣም የሚያሳዝነው የሐሰት ሰነዶቹ መዘጋጀት ሳይሆን እነዚህ በከባድ ወንጀል ሊያስጠይቁ የሚችሉ የተጭበረበሩ ሰነዶች የቤተ ክርስቲያኒቱ መምሪያ ነኝ በሚል ተቋም መካነ ድር ላይ መለቀቃቸው ነው፡፡

ከሐሰት ሰነዶቹ መካከል አንዱ የተሐድሶ መናፍቃንን ዝርዝር የሚገልጽ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የመቀሌ ማዕከል የሒሳብ ሪፖርት አስቸጋሪ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ይህንን የሐሰት ሰነድ አስመልክቶ ድርጊቱ እንዲጣራና ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ለቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለመንበረ ፓትርያርክና ለሚመለከታቸው ሁሉ የሚያቀርብ ሲሆን በሐሰት ሰነዶቹ ስማቸው የተነሱ አካላትም ድርጊቱ የማኅበሩ አለመሆኑን እንዲያውቁና ምዕመናንንም እውነቱን እንዲረዱ ይህ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ መካነ ድር የተለቀቁት ሁለቱም የሐሰት ሰነዶች በቁጥር መቀጽቤ 99/2003 ዓ.ም እና መቀጽቤ 100/2003 ዓ.ም “ለማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ክፍል” በሚል አድራሻ የተላኩ ናቸው፡፡

ነገር ግን ከመቀሌ ማዕከል መዝገብ ቤት ቀሪ ሆነው የተገኙት እውነተኞቹ ደብዳቤዎች በማኅበረ ቅዱሳን የመቀሌ ማዕከል በቁጥር መቀጽቤ 99/2003 ዓ.ም እና በቁጥር መቀጽቤ 100/2003 ዓ.ም በቀን 05/09/2003 ዓ.ም በማዕከሉ የሰባኬ ወንጌልነት ተቀጥረው ሲያገለግሉ ለነበሩ /አሁን የIT ምሩቅ ናቸው/ ግለሰብ የሥራ ስንብትና የሥራ ልምድ መስጠትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ መመልከት እንደሚቻለው የሐሰት ሰነዶቹም ሆነ  እውነተኞቹ ደብዳቤዎች ቁጥራቸው ተመሳሳይ ነው።

በቀጣይነትም በሰነዶቹ ላይ ማጭበርበሩ የተደረገው በማዕከሉ መዝገብ ቤት ከተገኙት ደብዳቤዎች ሳይሆን ምን አልባትም ከባለጉዳዩ እጅ ከወጡት ደብዳቤዎች ሊሆን እንደሚችልም አንባቢ ያስተውል፡፡ ምክንያቱም የማኅተሞቹና የፊርማዎቹ አቀማመጥ ተመሳሳይነት የላቸውምና አልተጭበረበሩም ብለን እንዳናስብ ያደርገናልና፡፡

ወደ ዝርዝር ጉዳዮቹ ስንገባ ደግሞ፣

1. በአድራሻው ላይ የተጠቀሰው የማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት እንደ ክፍል ያልተዋቀረ እንደሆነ ይታወቃል። በአድራሻው የሚመጡለት ደንዳቤዎችም “ለማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ አገልግሎት” ተብለው ይደርሱታል እንጅ “ለማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ክፍል” ተብሎ በአድራሻ አይጠራም። ከዚህ በፊት በመካነ ድራችን የተለቀቁትንና በአገልግሎቱ እየወጡ የሚታተሙትን የመጽሔተ ተልዕኮ መጽሔቶችንም መመልከት ይቻላል።

2. በቁጥር መቀጽቤ 99/2003 ዓ.ም የተጻፈው የሐሰት ሰነድ “በቀን 17/07/2003 ዓ.ም በቁጥር አአ/ልዩ/05/2003 ዓ.ም 11 ገጽ አባሪ አድርጋችሁ በጻፋችሁልን ደብዳቤ ተንተርሰን የሰራነው ሥራ…” ብሎ ከማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል ጽ/ቤት ለመቀሌ ማዕከል የተላከ ለማስመሰል ይሞክራል፡፡ ነገር ግን በማኅበረ ቅዱሳን ስም የሚወጡት ማናቸውም ደብዳቤዎች ቁጥራቸው ማቅ በማለት የሚጀመሩ ናቸው። በተጨማሪም የማኅበሩ ዋናው ማዕከል ጽ/ቤት ለመቀሌ ማዕከል ልኮታል ተብሎ የተጠቀሰው ደብዳቤ የተጻፈበትን ቀን ስንመለከት፤ 17/07/2003 ዓ.ም የዋለው ቅዳሜ ዕለት ሲሆን በዚህ ቀን የማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ አገልግሎት የማይኖርበት ዕለት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምን አልባት ካላንደር ሳይዙ ጽፈውት ይሆን? የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያው በየጊዜው ከማኅበሩ ደብዳቤዎች ይደርሱታል። አአ/ልዩ/05/2003 ዓ.ም የሚለው ቁጥር አስተውሎት ውስጥ ሳይገባ በመካነ ድሩ በችኮላ መለቀቁ ማኅበሩን ለመክሰስ ካለው የግለሰቦች ጉጉት የተነሣ ይሆን?

3. በቁጥር መቀጽቤ 99/2003 ዓ.ም በተጻፈው የሐሰት ሰነድ ሒሳብ ክፍልንና ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍልን የሚመለከት ምንም ጉዳይ ሳይኖረው ወደ ሒሳብ ክፍልና የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ግልባጭ መደረጉ ለምን ይሆን? ለዚያውም በማደራጃ መምሪያው መካነ-ድር እንደተገለጠው የተደበቀ የስለላ ሥራ ከሆነ እንዴት ለእነዚህ ክፍሎች ግልባጭ ሊደረግ ይችላል? ሒሳብ ክፍልስ ከሕዝብ ግንኘነት አገልግሎቱ ጋር ምን ግንኙነት ይኖረው ይሆን? እነዚህ ጥያቄዎች በጥብቅ ሊመለሱ የሚገባቸው ናቸው።

ምን አልባት ለማጭበርበር በሚደረገው ሙከራ የአንዱ ደብዳቤ ሐሳብ ከሌላው ደብዳቤ ላይ ተቀያይሮባቸው ይሆን? የየትኛው ደብዳቤ ሃሳብ ለየትኛው ክፍል ግልባጭ መደረግ እንዳለበት ፊደል የቆጠረ የሚያስተውለው ነው።

4. በማኅበሩ የአገልግሎት ክፍሎች የሚመደቡት አባላት በሰበካ ጉባኤ ወይም በሰንበት ትምህርት ቤት የታቀፉ መሆን እንዳለባቸው በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 6/ለ ተጠቅሶ ሳለ “የሰ/ት/ቤቶችን በተመለከተ፣ የማኅበሩ አባላት በሙሉ በየሰንበት ትምህርት ቤቱ በአባልነት እንዲያገለግሉ ተደርጓል፤ እየተሰራበት ይገኛል።” የሚለው ዓረፍተ ነገር የማኅበሩ አባላት የሰ/ት/ቤትና የሰበካ ጉባኤ አባላት አይደሉም የሚለውን የአባ ሠረቀን የሐሰት የክስ ሐሳብ ለማጽናት ይሆን?

ማኅበረ ቅዱሳን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ስር የሆነው በራሱ ጥያቄ አቅራቢነት ነው፡፡ ይኸውም አባላቱ በሰ/ት/ቤቶች ታቅፈው እንዲያገለግሉለት ካለው ጽኑ ፍላጎት የተነሣ እንደሆነ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ያስፈልጋል፡፡

የሐሰት ሰነዶቹን አጠቃላይ ሐሳብ ለመረዳት ለሚሞክር ሰው፥ አጭበርብሮ ማኅበረ ቅዱሳንን ለመክሰስ እንዲሁም የፀረ ተሐድሶ መናፍቃንን ዘመቻ ለማጨናገፍ የሚደረግ ሴራ መሆኑን ማኅበሩ አያጣውም፡፡

ማኅበረ ቅዱሳንና ሌሎች ማኅበራትም በሚያደርጉት የፀረ ተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው ከተለዩት ግለሰቦች ውጭ የማንም ስም በግልጽ ተጠቅሶ አያውቅም፡፡ የተሐድሶ መናፍቃንን ምልክቶች ግን ይጠቁማል፡፡ ከተሰጡት መረጃዎች እንዲሁም ከምልክቶቹ ምእመኑ እየተረዳው እንደመጣ ይታመናል፡፡

የተሐድሶ መናፍቃኑ እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙ የሆነ፣ በብዙ ሚሊዮኖች በጀት ተመድቦለት፣ በዓላማ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ለመበርዝና ለማጥፋት እጅግ ተምረዋል ተብለው በሚገመቱ ሰዎችና በግዙፍ ድርጀቶች የሚመራና የሚታገዝ ቤተ ክርስትያኗን የሚያናጋ ነው።

ነገር ግን ትግሉ ከተጀመረ ጀምሮ አንዳንድ ግለሰቦች እንቅስቃሴውን ከግለሰቦች ጋር እያያዙት ይገኛሉ፤ የተሐድሶ ኑፋቄ ዘመቻንም እያፋጠኑት ይገኛሉ።

ይህንን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማስተጓጐል ብሎም የምእመኑን ትክክለኛ ትኩረት ለማሳጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ እንደሆነ እናምናለን፡፡

ምን አልባት ማኅበረ ቅዱሳን ስም አጥፊ ነው፣ የአባቶችና የሊቃውንት ከሳሽ ነው የሚለውን የአንዳንዶችን ክስ ለማጠናከር ይሆን? አንባቢ ይመርምር።

እግዚአብሔር ሀገራችን ኢትዮጵያን እና ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የክብረ ገዳማት የቀጥታ ዘገባ

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

እንደምን ዋላችሁ ውድ ምእመናን አሁን የክብረ ገዳማትን የቀጥታ ዘገባ ለማቅረብ እንሞክራለን።

9:23 በዝናብ ምክንያት ዘግየት ብሎ የጀመረው ይህ መርሐ ግብር በጠቅላይ ቤተ ክህነት እየተደረገ ይገኛል።

አዳራሹ ሞልቶ ምእመኑ ቆሞ በሚታይበት ሁኔታ በዚህ አመት ሙሉ ፕሮፌሰርነት ያገኙት ፕርፕፌሰር ሽፈራው በቀለ የጥናት ጽሁፋቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ።

“የገዳማት ደጀሠላሞች ዋጋ እንደሌላቸው ታስቦ መፍረስ የለባቸውም። የገዳማት የትኛውም ቤት ከመፍረሱ በፊት በአርኪኦሎጂስቶች መታየት አለባቸው”

ፕሮፌሰር እንዳሉት በሀገራችን አንድ ባህል አለን በክፉ ቀን የከበረን ነገር መሬት ውንጥ መቅበር፣ ስለዚህ እንደተቀበረ ሊቀር ይችልሉና ገዳማትና አድባራት በጥ ንቃቄ ሊያዙ ይገባቸዋል።

በመካከለኛው ዘመን ገዳማከ የትምህርትና የባህል ማእከላት ነበሩ። በአክሱም ዘመነ መንግስት የጀመረው የገዳም ሥር ዓት በዛግዌ ጊዜ ወደ በጌምድር፣ ሸዋ፣ ወሎ አንዲሁም ወደ ደቡብ ክልሎች ተስፋፍትዋል።

9:40 ም እመናን  በተለያዩ ምክንያቶች መቆራረጡን ታግሳችሁ አሁንም ከእኛ ጋር እንደምትሆኑ እናስባለን

አሁንም ፕሮፌሰር ሽፈራው የጥናት ጽሁፋቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ።

ገዳማት በተለያዩ ዘመናት ከሚገጥማቸው ችግሮችን ለምሳሌ መውደማቸውን ግንዛቤ ውስጥ አስገብተን ጥልቅ የአርኪኦሎጅ ጥናት ያስፈልጋል።

ገዳማት የቅርስ የጥበብ ምንጮች ናቸው። መስቀል በተለያዩ መልኮች የሚሰራበት ቤተ ክርስቲያን በየትም የለም፤ በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያንት ዘንድ ቢሆን።

9:55 አሁን ማኅበረ ቅዱሳን በገዳማት በኩል ያደረገውን የ10 ዓመት የልማት እንቅስቃሴ አስመልክቶ ሪፖርት በወ/ሮ አለም ጸሐይ መሠረት እየቀረበ ነው።

“የግራኝ ዜና መዋ ዕል ጸሐፊ ከየረር እስከ አዋሽ ወንዝ ድረስ ብዙ ገዳማት መቃጠላቸውን ገልጽዋል።” ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ

“በቀደምት የኢትዮጵያ ታሪክ የመንግስታት መጠናከር ለገዳማትና አድባራት መጠናከር አስተዋጾ ነበርው” ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ

“ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ እየተጠናከረ የመጣው የገዳማት ሁኔታ በደርግ ዘመነ መንግስት ተዳፈነ።” ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ

9:57 “በቆላ ተምቤን ከሚገኙት ወደ 28 የሚጠጉ ገዳማት አንዱ አብራ አንሳ ነው፤ አፄ ግ/መስቀል የመነኮሳቱን ብዛት አይተው እንደ አሳ ይበዛሉ ለማለት ስሙን እንደሰጡት ይነገራል። ዛሬ ግን 5 መነኮሳት ብቻ ቀርተዋል።” ወ/ሮ ዓለምፀሐይ

“እኛ ወደ ቦታው በሄድንበት ወቅት የሚበላ ስላልነበራቸው ከሳምንት በፊት የመጣ ጠላ ብቻ ሊሰጡን ችለዋል።”

“ሌላ ጊዜ አባ ሳሙኤል ወደ ሚባል ገዳም ሄድን፤ መቅደሱ ፈርስዋል፣ የመነኮሳትም መኖሪያ ፈርሶ ደግር ሆንዋል። አሁን በካህን ይለገላል”

“የአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃንን ገዳምን 4 ብቻ መነኮሳት የሚመግበው የ16 ዓመት ልጅ ነበር” ምእመናን ከላይ የቀረቡት ከወ/ሮ ዓለም ፀ ሐይ የግል የውሎ ዘገባ የቀረቡትን እጅግ ጥቂት ችግሮችን ነው። ከዚህ የከፋ ችግር ያለባቸው እንዳሉ ለመግለጽ እንወዳለን።

ለእነዚህ ገዳማት የቤተ ክርስቲያናችን የልማት ኮሚሽን የሚሰራው ሥራ ቢኖርም ማኅበረ ቅዱሳን ከቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው መመሪያ መሠረት መሥራቱ የግድ ሆኖበታል። ብለዋል ወ/ሮ ዓለምፀሐይ

ስለሆነም ማኅበሩ ገዳማቱ ያላቸውን ሃብት በመጠቀም ዘላቂ ፕሮጀክክት ይሠራል። በዚህም ገዳማቱ ከቁሪትነት እንዲወጡ እንዲሁም እንዳይፈቱ ያደርጋል።

10:19 አቶ አጥናፍ ከ1992-2002 ዓም በማኅበሩ የተሰሩ ሥራዎችን ዳሰሳ አቅርበዋል።

ፕሮጀክቶቹ ከአነስተኛ ጊዜአዊ ድጋፍ እያደጉ የሄኡ ናቸው። ከ2000 ብር ሥራ የጀመረው የፕሮጀክት ሥራ አሁን እስከ 5 ሚሊዮን ብር የሚደርሱ የፕሮጀክት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

እስከ አሁን በ6.9 ሚሊዮን ወደ 73 የሚጠጉ ፕሮጀክቶች ተተግብረዋል።

10:30 ክብረ ገዳማት ዘጋቢ ፊልም እየቀረበ ነው።

እስከ አሁን በተሰሩት ሥራዎች ገዳማቱ በራሳቸው ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ የተረዱበት ነው።

የዘጋቢ ፊልሙ ርዕስ “ሥርዓተ ገዳም በኢትዮጵያ”  ይሰኛል።

10:55 በቀጣይ ዓመታት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንደ አብረንታንት ዋልድባ፣ ደብረ በንኮል ባሉ ገዳማት ለመሥራት አቅደናል።

“የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ተቀምጠውበታል ወደ የሚባለው ጉንዳጉንዲ ስንሄድ የተቀበሉን አንድ መነኮስ ብቻ ነበሩ።” ዲ/ን ደረጀ ግርማ

ለ2004 ዓ.ም ወደ 18 የሚጠጉ ፕሮጀክቶች ለገዳማት አቅደናል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ችግር እጅግ የጸናባቸው ናቸው። ዲ/ን ደረጀ የቃል መግቢያ ሰነዱን እያአስተዋወቁ ይገኛሉ።

“አብረን እንሥራ ለውጥ እናመጣለን” በማለት ዲ/ን ደረጀ መልእክት አስተላልፈዋል።

ለገዳማት እርዳታ ለማድረግ የምትፈልጉ gedamat_mk@yahoo.com ወይም 0173036604664000 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ

11:10 አሁን የምእመናን አስተያየት እየተደመጠ ነው።

“ታሪክ እየጠፋ ኢትዮጵያዊነት የለም። ገዳማት ደግሞ የታሪክ ምንጮች ናቸውና የቻልነውን ልናደርግ ይገባል።”

“ይህን መርሐ ግብር በሌሎች አድባራትም ብታደርጉት የተሻለ ገንዘብ በመሰብሰብ ገዳማትን መርዳት ይቻላል።”

“እናንተ እንደተለመደው አስታውሱን እንጅ ከአሰብነው በላይ እንሰጣለን።”

“ሌሎች የጠፉ ገዳማትንም ብታስታውሱን”

“ሦስት አራት ሆነን መርዳት እንችላለን?” “ይችላል፣ ለደረሰኝ እንዲመች ግን በአንድ ስም ብትከፍሉ ይሻላል።”

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

አባታችን ሆይ

ለሑዳዱ አዝመራ ተዋሕዶ ስትጣራ የቀጥታ ዘገባ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ማኅበሩ ለሚያደርገው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የበኩላችንን ድርሻ እንወጣ፣ ሰለ አንዲት ነብስ መዳን የሰማይ መላእትም ምን ያህን እንደሚደሰቱ እናስተውል። ሐዋርያትም ደማቸውን ያፈሰሱባት አጥንታቸውን የከሰከሱባት አገልግሎት እርስዋ ናትና።

ከአሁን በህዋላ ወር በገባ በሁለተኛው ሳምንት ዘወትር ረቡዕ ስለ ስብከተ ወንጌል የምንነጋገርበት መርሐ ግብር ይኖራል።

“ለወደፊቱ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው ከንቀሳቀሱ ማኅበራትና ሰ/ት/ቤቶች ጋር እንሠራለን ይህም ችግሮቻችንን ያቃልልሉናል ብለን እናስባለን” ቀሲስ ታደሰ ጌታሁን የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አስተባባሪ

የገንዘብ ችግር፣ የሰው ኃይልና የቁሳቁስ ችግሮች አገልግሎታችን እንዳይሰፋ እያደረጉት ነው”

“ማኅበሩ በአንድ ጊዜ በአራቱም አቅጣጫ ሐዋርያዊ ጉዞ ማካሄድ ይችላል። ነገር ግን የሚከተሉት ችግሮች ፊቱ ላይ ተደቅነዋል።”

“እግዚአብሔር ማኅበሩን አንደምክንያት አድርጎ እየተጠቀመ ያለበት ጊዜ ነውና ይመስገን፤ ያልተያዙትን ለመያዝ ሰንሄድ አብሮ ያሉትን ቢያጸና። ማኅበሩ ታች ወርዶ ማኅበራትን የሚያሰለጥንበት ሁኔታ ቢፈጠር ብዙ ሥራ ይሠራል”

“ያየሁት ዶክመንታሪ ፊልም ይበቃኛል፣ አስተያየት መስጠት አልፈልግም፤ በየ 3 ወሩ 5000.00 ብር ለዚህ አገልግሎት እሰጣለሁ።” በወረቀት የተሰጠ አስተያየት

“ማኅበሩ አዲስ አበባም ላይ ትኩረት ቢያደርግ፣ ግራ ተጋብተናልና”

“በግቢ ጉባኤ ያለፍን ተመራቂዎችም ተምረን ዝም ማለት የለብንም፣ እኔ አሁን በራሴ አፍሬያለሁ። ተምሬ፣ ሥልጠና ወስጄም ተቀምጫለሁ ስለሆነም የራሳችን ድርሻ ልንወጣ ይገባል።”

“አዲስ አበባ ለሚኖሩ ካህናት ሥልጠና ተሰጥቶ፣ ወደ አገር ቤት/ገጠር/ ሲሄዱ፣ የሚሄዱበትን አካባቢ እንዲያስተምሩ ቢደረግ”

“ያየሁት ድንቅ ነገር ነው። ልጄ ነውና ወደዚህ ያመጣኝና መርቁልኝ አሁንም መርቁልኝ”

10:47 የምእመናን አስተያየት እየተሰጠ ነው።

4. ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የበዙባቸው ነገር ግን ለድብቁ የመናፍቃን ሴራ የተጋለጡን ሁኔታዎችና አካባቢዎች ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ነው።

3. ሥልጠናን

2. አምነው፣ ተጠምቀው ነገር ግን በመናፍቃንና ተሐድሶ ኑፋቄ የተጠቁትን

1. ምንም ስብከተ ወንጌል ያልተስፋፋባቸውና በመግባቢያቸው መማር የሚፈልጉትን

ዶክመንታሪ ፊልሙ ከስብከተ ወንጌል አንፃር አራት መሠረታዊ ነጥቦችን ተንተርሶ ይተነትናል።

በዚህም ማኅበሩ የተለያዩ ክፍሎች ከጎኑ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ማኅበሩ ባለው የገንዘብ አቅም ይህ ሁሉ ዓለም አቀፋዊ አገልግሎት ሊሸፍን አይችልም።

ስለዚህ የቅድስት ዋነኛ አገልግሎት የሆነውን የስብከተ ወንጌል ለማስፋፋት ወቅቱ የሚጠይቀውን ማድረግ ያስፈልጋል።

እነዚህ የትምህርት ክፍል አገልግሎቶች ከወደፊት ምን መሠራት እንዳለበት ለማመልከት በራሱ በቂ ሊሆን አይችልም።

እንዲሁም ለ1 ሥልጠና እስከ 65000 ብር ያስወጣዋል።

ማኅበሩን እስከ አሁን ካለው ልምድ ለ1 ሐዋርያዊ ጉዞ እስከ 40000 ብር ያስወጣዋል።

በተመረጡ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጥናዎችም ተሰጥተዋል።

10 ዙር የሰባክያን ሥልጠናዎች ተደርገዋል።

ማኅበሩ በአገር ውስጥ ያልተወሰነው የሐዋርያውዊ አገልግሎቱ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ወዘተ ይቀጥላል።

በማኅበሩ የሚዘጋጅ አንድ ሐዋርያዊ ጉዞ ወደ አምስት የሚጠጉ ከተሞችን የሚያካልል ነው። አንድ ልኡክ ከ25 እስከ 30 የሚጠጉ መምህራንን፣ መዘምራንን፣ የቀረጻና የሚዲያ ባለሙያዎችን ያካትታል።

ከሐመር የሠለጠኑት ደግሞ የጎሳውን መሪና 3000 የሚሆኑ ምዕመናንን አስተምረው ለማጥመቅ ችለዋል።

ከኑዌር ከሰለጠኑት ውስጥ የተወሰኑት ክህነት ተቀብለው ወደ 700 የሚጠጉ ምዕመናንን አስተምረው ለማጥመቅ ችለዋል።

ምዕመናን ያላቸውን ይዘው እንዲቆዩ የሚያደርግ፣ የቤተ ክርስቲያናቸው ፍቅር እንዲጨምር ፣ ካህናትም በቁጭት እንዲያገለግሉ የሚያደርጉ፣ ኦርቶዶክሳዊ መዝሙራትን ያስተማሩና ያሳወቁ ነበሩ

ማኅበሩ 19 ዙር ሐዋርያዊ ጉዞ አድርግዋል።

ከክኦሮሚያ እየሚሰጠው ሥልጠና የደቡብ፣ የኦሮምያ፣ የሶማሌ፣ የበቤንሻንጉልና የጋምቤላ  ክልሎችን ያቀፈ ነው።

ስብከተ ወንጌል ካልተስፋፋባቸው አካባቢዎች ለመጡ ከ200 በላይ ሰልጣኞች ለማፍራት ተችልዋል።

ማኅበረ ቅዱሳን  በክረምቱ የሰባክያን ሥልጠና 1306 ሠልጣኞችን በ1003000 ብር በጀት አፍርትዋል።

9:40 ለሑዳዱ አዝመራ ተዋሕዶ ስትጣራ የሚለው ዶክመንታሪ ፊልም ተቀንጭቦ እየታየ ነው።

9:38 “ያሰባሰበን ቸሩ ፈጣሪ ይክበር የሁሉ ጌታ፣

ሁሉ ነገር ከእርሱ የማይወጣ ይወደስ በእልልታ” የሚለው መዝሙር በጋራ እየተዘመረ ነው።

“እናንተ ኢትዮጵያዊያን ለእኛ አፍሪካዊን ደም ተጠያቂዎች ናችሁ፣ ለምዕራባዊያን አስተሳሰብ፣ ባህል፣ ሃይማኖት አሳልፋችሁ ሰጥታችሁናልና። ”  ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ በመርሐ ግብሩ ከተናገሩት ገጠመኛቸው የተናገሩት

9:29 የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ያዘጋጀውና የማኅበሩን የ19 ዓመት የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ የሚያስቃኘው ዶክመንታሪ ፊልም ለመታየት በዝግጅት ላይ ነው።

-9፡00 ላይ የማኅበሩ ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

9:26 ምዕመናን “ማርያም ሀዘነ ልቡና ታቀልል…ማርያም የልብን ሀዘን ታቀላለች” የሚለውን መዝሙር በጋራ እየዘመሩ ነው።

8:45 የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን ወረብ አቅርበዋል።

“ሠላመከ እግዚኦ ሀበነ

ወኢትግድፈነ ወኢትሚጥ ገፀከ እምኔነ

ከመ ኪያከ ንሰብህ በኩሉ መዋዕል ሕይወትነ ኢያማስነ ተስፋነ

ለእለ ንሴፈወከ ወተዘከር ዘንተ ተግባረከ”

 

እንደምን ዋላችሁ ክቡራን ምዕመናን ለሑዳዱ አዝመራ ተዋሕዶ ስትጣራ በሚል መሪ ቃል በማኅበረ ቅዱሳን የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የተዘጋጀውን መርሐ ግብር በቀጥታ ለማስተላለፍ እንሞክራለን።

ምንም እንክዋን መርሐ ግብሩ 8:30 ቢጀምርም፣ ባጋጠመን የቴክኒክ ችግር ዘግይተን ለመጀመር ተገደናል።

መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ የስብሰባ ማዕከል ለማዘጋጀት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ባጋጠመን ከአቅም በላይ ችግር ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በታቀደለት መሠረት እየተካሄደ ይገኛል።

እግዚአብሔር ይመስገን

Kibre Gedamat2003 .jpg

ክብረ ገዳማት በፆመ ፍልሰታ መጀመሪያ

ሐምሌ 26 ፣2003 ዓ.ም.                                        
 
በገዳማትና በአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን ነሐሴ 1 ቀን 2003 ዓ.ም “ክብረ ገዳማት” በሚል መሪ ቃል የ10ኛ ዓመት የገዳማትን አገልግሎት የሚያዘክር ዐውደ ጥናት በኢትዮጵያ ስብሰባ ማዕከል ከ7፡30-11፡30 አዘጋጅቷል፡፡ ዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ ዓውደ ጥናቱንና የክፍሉን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የቅስቀሳና ገቢ አሰባሰብ ተጠባባቂ ኃላፊ ከሆኑት ከዲ/ን ደረጀ ግርማ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡ 

የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ሥራ ሲጀምር በየትኛው ደረጃ ነበር የጀመረው?

ሥራው የተጀመረው በ1992 ዓ.ም ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ነው፡፡ አገልግሎቱን ሲጀምር አነስተኛ ጊዜያዊ እርዳታ በመስጠት፣ ለገዳማትና አድባራት ያለባቸውን የመባ እጥረት ከመቅረፍ አንጻር ጧፍ፣ ዕጣን ዘቢብ በመላክ እና አነስተኛ ኘሮጀክቶች ላይ መነኮሳትን ሊያበረታታ በሚችል መልኩ ድጎማ በማድረግ ነው፡፡

ክፍሉ እስከ አሁን በምን ያህል ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ እንቅስቃሴ አድርጓል? 

የዛሬ 10 ዓመት ይህ እንቅስቃሴ ሲጀመር ገዳማትና አድባራት ያለባቸውን ችግር በማጥናት ነው፡፡ አንድን ነገር ከመረዳት በፊት የጥናት ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ችግርን ማወቅ ግማሽ መፍትሔ ነው፡፡ ቢያንስ በዚህ ሰዓት ላይ የአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት ችግር ምን እንደሆነ አውቀናል፡፡ እነዚህ ገዳማትና አድባራት መጀመሪያ በነበረባቸው የድርቅ አደጋ እንዲሁም በመሬት ላራሹ አዋጅ ምክንያት በርካታ ቦታዎች ሲወሰዱ ባዷቸውን ቀርተው ነበሩ፤ ከዛ ውጭ በሰፈራና ከአስተሳሰብ ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ ችግሮች ነበሩ። እነዚህን ችግሮች ከመቅረፍ አኳያ ጅምራችን በጥቂት የአብነት ትምህርት ቤቶች ነበር፡፡ አሁን ግን በ100 የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ፕሮጀክት ጀምረናል፡፡ በጊዜያዊ እርዳታ ደግሞ ከ70 እና 80 በላይ የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ድጋፍ እያደረግን ነው። በአጠቃላይ ባደረግነው ቅኝት ከ250 በላይ የሆኑትን ችግራቸውን መለየት ተችሏል፡፡ ከአቅም ውስንነት አኳያ ሥራ እየሠራን ያለነው በ100 የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ብቻ ነው፡፡ ከዛ ውጭ ገዳማት ላይ ያለባቸውን ችግር በመቅረፍ ግን በ26 ገዳማትና አድባራት ላይ የመጀመሪያ ጥናት ተደርጎ ነው ሥራ የተጀመረው፤ ከዛ በኋላ ግን በቋሚ ፕሮጀክት ደረጃ ከ60 በላይ በሆኑ ገዳማት ተተግብሯል፡፡ የንብ ማነብ፣ የከብት ማድለብ፣ የሽመናና የግንባታ ሥራዎች ከተተገበሩት ፕሮጀክቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በየአቅጣጫው ከ100 በላይ የሆኑ ገዳማትን በቅኝትና በዳሰሳ  ደረጃ ለይተናል። በተለይ ጥንታዊያኑን ለመቃኘት ተችሏል፡፡

ነሐሴ አንድ ቀን “ክብረ ገዳማት” በሚል መሪ ቃል ሲምፖዚየም አዘጋጅታችኋል፤ ሲሞፖዚየሙ የተዘጋጀው ለገዳማት ብቻ ነው ወይስ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ያካትታል?

Kibre Gedamat2003 .jpgይህ ክፍል ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ገዳማት ላይ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ ቢያፈስም፤ የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ትውልድ የማትረፍ ሥራ በመሥራት ትኩረት አድርገን ብዙ ሲሞፖዚየሞችን አድርገናል፡፡ ለምሳሌ አብነቱ ያለ አብነት እንዳይቀር፣ ቅኔ፣ በእንተ ስማ ለማርያም፤ እነዚህ ሲሞፖዚየሞች ቀጥታ የሚያመለክቱት የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ነው፡፡ አሁን ግን እራሱን ችሎ ገዳማትን በተመለከተ ዓውደ ጥናት ሲካሔድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥ አነስተኛ ዓውደ ጥናቶች በተለያዩ ቦታዎች አድርገናል፡፡ ነገር ግን እጅግ በጣም ብዙ ምዕመናን ጠርተን እንደዚህ ዓይነት መርሐ ግብር ከማድረግ አኳያ የመጀመሪያው ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሲሞፖዚየም ማዘጋጀት ለምን አስፈለገ?

ገዳማትና አድባራት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብሎም ለሀገራችን ያበረከቱት አስተዋጽኦ የጎላ ነው፡፡ ግን ይህ የጎላው አስተዋጾአቸው ገሀድ ወጥቶ ትውልዱ እየተረዳው ነው ማለት በጣም ይከብዳል፡፡ ይህን ለማለት ያስደፈረን፥ ባጠናነው ጥናት መሠረት ከከተማ የራቁና በተለይ በጣም ትልልቅ የሆኑ ገዳማትና አድባራት የሚረዳቸው አጥተው አብዛኛዎቹ አንድነታቸው ተፈትቷል፡፡ ስለዚህ እነዚያን ታላላቅ ገዳማት በማስታወስ ትውልዱ በነዚህ ገዳማት ላይ ሥራ እንዲሠራ ለማስቻል ነው፡፡

ሁለተኛ ደግሞ በገዳማትና አድባራት ላይ በርካታ ጥናት ያጠኑ ምሁራን አሉ፡፡ በዩኒቨርስቲ ደረጃም ዶክተሮች፣ ፕሮፌሰሮች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ያጠኑት ጥናት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ነው፡፡ ግን የሚያቀርቡበት ሁኔታ፣ ቦታና ጊዜ አልነበራቸውም። ለሕዝቡም ሊደርስ በማይችል ሁኔታ ነበር። አሁን ግን እነዚህ ሰዎች በእንደዚህ ዓይነት ቦታዎች ሁኔታዎችን ብናመቻችላቸው ለሕዝቡ የገዳማትንና አድባራትን አገልግሎትና ጥቅም እንዲሁም የነበራቸውን ሀገራዊ ፋይዳ ማሳየት ይቻላል፡፡ በዚህም ትውልዱ ይህን ተረድቶ ገዳማት ላይ ለመሥራት ትልቅ አቅም ይኖረዋል ብለን ስላሰብን ነው፡፡

ሌላው ማኅበረ ቅዱሳን  በዓመት ቢያንስ ከ12 በላይ ትልልቅ የገዳማት ፕሮጀክቶችን ይዞ ይሠራል፡፡ ስለዚህ በ2004 እና በ2005 ዓ.ም ለትግበራ ጥናታቸው የተጠናቀቀላቸው በርካታ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ እነዚህን ማስተዋወቅም አስበናል፡፡

ከዚያ ውጭ እስከ አሁን ቅኔ፣ አብነቱ ያለአብነትና በእንተ ስማ ለማርያም የሚሉ ዘጋቢ ፊልሞች አዘጋጅተናል፡፡ በገዳማት ላይ ግን ወጥ አድርገን የሠራነው ሥራ የለም፡፡ ስለዚህ አጠር ብሎ ስለገዳማት በቂ መረጃ ሊሰጥ የሚችል ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅተን ለሕዝቡ በማሳየት ገዳማት የእርሱ እንደሆኑ፣ የቅርስ ማደርያ እንደሆኑ፣ በተፈጥሮ ሀብት ደኑን ተንከባክበው ያቆዩ መሆናቸውን በማዘከር፣ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡

ከዛ በላይ ደግሞ በዚህ አስር ዓመት እንቅስቃሴ ውስጥ አብረውን የነበሩ ገዳማት Gedamat_Vegetable.JPGአሉ፡፡ እነዚህ ገዳማት ያላቸውን ተነሳሽነት፣ በተሰጣቸው ትንሽ ድጋፍ ተጠቅመው ገዳማቶቻቸውን ለመለወጥ ባደረጉት ጥረት ማበረታታት ይጠበቅብናል። ከያሉበት ጠርተን ከእኛ ጋርም ተገኝተው፥ የቀደመ ክብራቸውን ለመመለስ በሚያስችል መልኩ «ክብረ ገዳማት» በሚል እንቅስቃሴ ለመጀመር አስበን ነው ነሐሴ 1 ቀን መርሐ ግብር ያዘጋጀነው፡፡

በዚህ በ10 ዓመት ውስጥ በገዳማት ላይ ምን ለውጥ አመጣን ብላችሁ ታስባላችሁ?

ተጨባጭ ለውጥ አምጥተናል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ግን ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አኳያ የገዳማትና አድባራትን ችግር ቀርፈናል ብሎ ለመናገር ደግሞ አይቻልም፡፡ በ10 ዓመት ጉዞ ውስጥ በርካታ የተፈቱና ጠፍ ሆነው የነበሩ ገዳማት ኅብረተሰቡን በማሳተፍ በተደረገላቸው አነስተኛ ድጋፍ ብዙ ለውጥ ተገኝቷል፡፡ ለምሳሌ በባሌ መካነ ሕይወት አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም አንድነቱ ተፈትቶ መነኮሳትም መንምነው መተዳደሪያ ሳይኖራቸው በጣም ተቸግረው ነበር፡፡ ዛሬ ግን በአትክልት ልማትና በወተት ልማት በተደረገላቸው ድጋፍ መነኮሳቱ በወር ከ27,000 ብር በላይ ገቢ የሚያገኙበት ሕይወት ተፈጥሮ፥ ወንበር ዘርግተው መምህራን ቀጥረው የተማሪ በጀት እንኳ በጅተው ዛሬ ገዳሙ የመነኮሳቱ ቁጥር ሰፍቶ እንመለከታለን፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ላይ በተደረገው ተደጋጋሚ ድጎማ ሁለገብ ሕንፃ በመገንባቱ ምንም እንኳ ሕንፃው በሂደት ቢሆንም አራት ቀርተው የነበሩ መነኮሳት ዛሬ ከአርባ ስድስት በላይ ሆነው ቀለብ እያነሳቸው ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ገዳም አንድና ሁለት መነኮሳት ብቻ ቀርተው ነበር፡፡ በዚያው አካባቢ የነበሩ ሰዎች አስተባብረው የሙአለ ሕፃናት ግንባታ በገነቡበት ወቅት ከ400.000 ብር በላይ በዚህ በገዳማት ክፍል ድጎማ ተደርጎ ትምህርት ቤቱ በማለቁ በዚያ ኪራይ ዛሬ ገዳሙ እየተጠቀመ የመነኮሳቱ ቁጥራቸው እየተበራከተ ጥንታዊውን ገዳም ከጥፋት ለመታደግ ተችሏል፡፡

በዝርዝር ብንቆጥራቸው በጣም በርካታ ናቸው፡፡ በአምስትያ ተክለ ሃይማኖት የውሃ ፕሮጀክት፣ በእማ ምዑዝ ገዳም የነበሩትን ችግሮች መደጎም በመቻላችን እነዚህ ገዳማት እንዲያንሠራሩና ለውጥ እንዲያመጡ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡

ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ለመርዳት ስታስቡ መነሻና መሥፈርታችሁ ምንድን ነው?

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ሕግና ደንቡ ጸድቆ ከተሰጠው ጊዜ ጀምሮ በገዳማት በአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ቤተ ክርስቲያኒቷ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንዲደግፍ ነው፡፡ እንዲደግፍም ሲባል አህጉረ ስብከት ወይም ገዳማት በአካልም በደብዳቤም መጠተው ይረዳ በማለት ይጠይቃሉ፡፡ እኛም ጥያቄአቸውን ተቀብለን ዝም ብለን አንረዳም፡፡ ቦታው ድረስ በመሄድ፣ ባለሙያዎችን በመላክ ቦታው ካለው ጥንታዊነትና ቅርስ አኳያ፣ የመነኮሳት ማኅበራዊ ሕይወትስ ምን ይመስላል የሚለው በስፋት ከታየና ከተጠና በኋላ ይህን ገዳም ብናጠናክር የቤተ ክርስቲያኒቷን እሴቶችና ጥንታዊነቷን ጠብቀን እናቆያለን፣ የትውልድ የሀገር ቅርሶችን ባሉበት እናጸናለን፣ መነኮሳትን ደግሞ ከፍልሰት መታደግና ባሉበት በልማት አሳትፎ ከማቆየት አኳያ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ ከዚያም ሀገረ ስብከቱ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት አማራጭ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ከመነኮሳቱ ፍላጎትና ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር በሚሰናሰል መልኩ፥ ከአካባቢው የአየር ጠባይ ሁኔታ፣ መነኮሳትን በማሳተፍ እንተልምና ፕሮጀክቱ ከጸደቀ በኋላ የሚረዳ አካል ይፈለግለታል፡፡ ይህም ማኅበራትን፣ ሠራተኛ ጉባኤያትን፣ በጎ አድራጊ ግለሰቦችን፣ የማኅበሩን አባላት በማስተባበር ፕሮጀክቶቹ ይተገበራሉ፡፡ ከተተገበሩም በኋላ ይህ ሥራ ከተሠራለት ገዳም ጋር ውል/ሰነድ ተፈራርመን ሥራ እንጀምራለን፡፡ በውል ሠነድ ደግሞ እናስረክባለን፡፡

ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ፕሮጀክት ስትሠሩ ከገዳማቱ ከመቀበላቸውና ከመተግበራቸው አንፃር ተነሳሽነታቸውን እንዴት ታዩታላችሁ?

አስቸጋሪም ጥሩም ነገር አለ። አንድ ገዳም ላይ ስትገባ የምትጠየቀው ብዙ ጥያቄ አለ፡፡ ለምን መጣችሁ? ለምን ትረዱናላችሁ? ሥራ ካማረን ከቤታችን አንኖርም ነበር ወይ? እዚህ ለጸሎት ነው የመጣነው። እንደውም በአንዳንድ ገዳማት ዘመናዊ ነገር አይግባባችሁ ተብለናል፡፡ አንፈልግም አንሠራም የሚሉበት ጊዜ አለ፡፡ በጉዳዩ እስክንግባባ ከአህጉረ ስብከት ጋር ብዙ የምንሠራው ሥራ አለ፡፡ አንድ ፕሮጀክት ከተጀመረ በኋላ የገዳሙ አበምኔት ሲቀየር ጉዳዩን እንደ አዲስ የማየት ነገር አለ፣ አንዳንድ ጊዜም ፕሮጀክቱ ከተሠራ በኋላ የማኅበረ ቅዱሳን ፕሮጀክት ነው እንጂ የገዳሙ ፕሮጀክት ብሎ አለመቀበል፡፡ ከግንዛቤ እጥረትና ከዕውቀት ማነስ የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ፡፡ ያን ግን በሂደት በማስተማርና በመመካከር የሚፈታ ሲሆን ሌሎች በማኅበረ ቅዱሳን ታቅፈው እድገት ያሳዩ ገዳማትን አርአያነት በመመልከት እየተሳቡ ለእኛም ይሠራልን ይህን አድርጉልን የማለት ነገር አለ፡፡

ከትናንት ዛሬ ይሻላል፡፡ አሁን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ገዳማት መምሪያ ጋር አብረን ለመሥራት አንዳንድ ውጥኖች አሉ፡፡ ተቀናጅተን የምንሠራባቸው ነገሮች የመነኮሳትን ቅበላ በየጊዜው እየተሻሻለ ነው የመጣው ለማለት እደፍራለሁ፡፡

ክፍሉ ለወደፊት ግቡ ምንድን ነው?

የመጨረሻ ግባችን ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች የተሻለ ነገር እንዲኖራቸው ነው፡፡ በአብነት ትምህርት ቤት ተቋማዊ ይዘት ኖሮት በዩኒቨርስቲ ደረጃ አድጎ በኮሌጅና በዩኒቨርስቲ ደረጃ ትምህርቱ እየተሰጠ የተማሪው ሕይወት ተሻሽሎና የራሱ ገቢ ማስገኛ ሊኖረው እንዲገባ የምናደርግበትን አጋጣሚ መፍጠር ነው፡፡ ድሮ ሕዝቡ “ስኮላር/scholar” ይሰጥ ነበር፡፡ አሁን ግን ያን አቋረጠ፡፡ ስለዚህ ተማሪው ለልመናና ለጉልበት ሥራ ነው የተዳረገው፡፡ ይህን ለማስቀረትና በራሳቸው ገቢ እንዲተዳደሩና ትኩረት ተሰጥቶት ተቋማዊ የሆነ ይዘት እንዲኖረው እንመኛለን፡፡

Gedamat_Aba.JPGገዳማትም ከልመና ወጥተው በራሳቸው የልማት ሐዋርያ የሚሆኑበት፥ በእደ ጥበብ ሆነ በሌላውም ዘርፍ የተሻለ አደረጃጀትና የተሻለ ገቢ ምንጭ ኖሮአቸው የአካባቢውን ኅብረተሰብ የሚረዱ፥ ወላጅ አልባ ሕፃናትን የሚያሳድጉ፥ በሀገር ላይ የተከሰቱ ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ላይ ምላሽ በመስጠትና ኅብረተሰቡን በመንከባከብ፣ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ተገናኝተው ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀሙ የሚችሉ፣ ሥልጠና የሚሰጥባቸው፣ ለዓለም የጥበብ መሠረትነታቸውን የሚያሳዩበት ምዕመናኑም በገዳማት ላይ አእምሮውን ለማደስ፣ እረፍት ለመውሰድና መንፈሳዊ ሕይወትን ለማበልጸግ የሚሔድባቸው፣ ዋናውና ትልቁ ነገር ገዳማት የአብነት ትምህርት ቤት ማዕከል እንዲሁም የጥናትና የምርምር ማዕከል የሚሆኑበትን ሁኔታ ማየት ነው፡፡

እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡

እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ክብረ ገዳማት

ክብረ ገዳማት( ነሐሴ 1/2003 ዓ.ም

ክብረ ገዳማት

መሠልጠን ማለት ግን ምን ማለት ነው?!

በዲ/ን ቴዎድሮስ በየነ

ሥልጣኔ ሲተነተን አንድ ገጽታ፣ አንድ መልክ፣ አንድ ወጥ ሳይሆን ብዙ መልኮች፣ ብዙ ገጽታዎች እንዳሉት ማጤን ይገባል፡፡

ሥልጣኔ የሰው ልጅ አካባቢውን ለኑሮ እንዲስማማው፣ እንዲመቸው ለማድረግና ለሕይወቱ የተመቻቸ ሥፍራ ለማድረግ የዕለት ተዕለት ተግባር ውስጥ ቀስ በቀስ የተከሰተ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሥልጣኔ ጥንትም የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ለወደፊትም የሚኖር የሰው ልጅ የተፈጥሮ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ሆኖም ግን ስለ ሥልጣኔ ብይን ሲሰጥ፣ ስለ መግለጫው ሲነገር፣ ስለ ጥቅሙ ሲዘመር፣ ስለ ግቡ /መዳረሻው/ ሲታተት፤ ሥልጣኔ ከቁሳዊ ነገር መሟላትና ከሥጋዊ ድሎትና ምቾት ጋር ብቻ ሲያያዝ ይስተዋላል፡፡ ለዚህም ይመስላል የሥልጣኔን ክስተት በዓይን በሚታዩ፣ አብረቅራቂና ሜካኒካዊ በሆኑ ነገሮች ብቻ እንድናይ ከታች ጀምሮ በትምህርት ቤት እንድንማረው የሆነው፡፡ በሚዲያ ዘወትር እንድንሰማው የተደረገው፡፡ከበደ ሚካኤል ስለ ሥልጣኔ ምንነት ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፡፡

“ሰዎች ራሳቸውን ለማረምና ኑሯቸውን ለማሻሻል ሲሉ በሥጋና በመንፈስ ያፈሩት ከመጀመሪያ ጀምሮ አሁን ድረስ የተከማቸው የሥራ ፍሬ ሥልጣኔ ይባላል፡፡”

በእኚህ ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ የሥልጣኔ ምንነት ገለጻ ውስጥ በዚህ ዘመን ሚዛን ላይ ያልወጡ ታላላቅ ቁምነገሮችን አምቆ ይዟል፡፡ ከነዚህም ውስጥ “በሥጋና በመንፈስ” በማለት ለሰው ልጅ የህላዌው መሠረት፣ የደስታው ምንጭ ሥጋዊ ፣/ቁሳዊ/ ነገር ብቻ እንዳልሆነ አስምረውበታል፡፡ መንፈሳዊም ፍሬም ሥልጣኔ እንደሆነ፡፡ ሥልጣኔ ከመጀመሪያ ጀምሮ አሁን ድረስ የተከማቸ የሥራ ፍሬ ነው ሲሉም፤ ሥልጣኔ የዛሬ ሦስት መቶ ወይም አራት መቶ ዓመት ክስተት ብቻ አይደለም ማለታቸው ነው፡፡

ዘመናዊ ሥልጣኔን ከምዕራባውያን ሥልጣኔ ጋር ብቻ አያይዞ የሥልጣኔ መልክና ገጽታ በምዕራባውያን መስታወት ብቻ የሚታይ እንዳልሆነም የጸሐፊው እይታ ያሳያል ፡፡

ዛሬ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሥልጣኔ ማለት ምዕራባዊ መስሎ መቅረብ፣ የምዕራብ ቋንቋን መናገር፣ የምዕራባውያንን የአኗኗር ዘይቤ መያዝ ይመስላል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያውያን ሠርግ ሲዘፈን እንደነበረው “የእኛ ሙሽራ ኩሪባቸው በእንግሊዝ አናግሪአቸው” የምዕራብ ቋንቋ መናገር የኩራት ምልክት፣ የሥልጣኔ ምልክት ነበር፡፡ ይህ ግን ስህተት እንደሆነ ኤቪሊንዎ የተባለ አንድ ምዕራባዊ ጸሐፊ ኢትዮጵያ ኋላቀር ነች እያሉ የሚተቹትን በነቀፈበት ጽሑፉ እንዲህ ይላል፡-

“የአንድን ኅብረተሰብ ትልቅነት የምትገምተው አውሮፓን ስላልመሰለ ወይም የ”ሰለጠኑ” አገራትን ስላልመሰለ ሳይሆን በራሱ እምነትና የእሴት ስልት ውስጥ የተቃረነ ነገር ሲሠራ ነው፡፡”

የዚህ መጣጥፍ ዐቢይ ጭብጥ ሥልጣኔ ከራስ እሴት አለመቃረን ነው የሚል ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ትውፊታችን፣ ባህላችንና ታሪካችን የኢትዮጵያውያን እሴቶች ምንነትን ይነግሩናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዛሬ እዚህ ላይ የምናየው ስለ ከበረው የዳኝነት /ፍትሕ/ ሥርዓት እሴታችን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ረዥም ዘመን ታሪካችን የዳኝነት ሥርዓት የተከበረ ነው፡፡ ፈረንጆች “the rule of law /ሕጋዊ ሥርዓት/” የሚሉትን የኢትዮጵያ ሕዝብ “የሕግ አምላክ” ይለዋል፡፡

በቆየው የኢትዮጵያ ባሕል አንድ ሰው ከመንገድ ላይ ባላጋራውን ካየ “በሕግ አምላክ ቁም” በማለት ብቻ ባላጋራውን አስቁሞ የነጠላዎቻቸውን ጫፍ ቋጥረው /ተቆራኝተው/ ያለ ፖሊስ አጀብ ወደ መረጡት ዳኛ ዘንድ ሄደው ፍርዳቸውን ይቀበሉ ነበር፡፡

“በቆረጡት በትር ቢመቱ፤ በመረጡት ዳኛ ቢረቱ፤ የእግዜር ግቡ ከብቱ፡፡” የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን በቀድሞ ዘመን “የተበደለ ከነጋሽ፤ የተጠማ ከፈሳሽ” ብለው፤ የተጠማ ውሃን እንደሚሻ ሁሉ የተበደለም ጉዳቱን ለንጉሡ አሰምቶ ትክክለኛ ፍርድ እንደሚያገኝ ያምኑ ነበር፡፡ በዚህም ምኞትና ሐሳቡን የፈጸሙ የመንፈስ ልዕልና ደረጃቸውን ያሳዩ ፈታሔ ጽድቅ /እውነተኛ ዳኞች/ በታሪኩ አይቷል፡፡ አጼ ዘርአያዕቆብ /15ኛው መቶ ክ/ዘ/፤ ልጃቸው የደሀ ልጅ ገድሎ በዳኞቻቸው ዘንድ በቀላል ፍርድ ስለ ተለቀቀ ይግባኙን ንጉሡ ወስደው የሞት በቃ ፈርደው እንዳስገደሉት ይታወቃል፡፡ ይህ ምንም ርትዕ ቢሆን፤ ከአብራክ በተከፈለ ልጅ ላይ ሞትን መፍረድ ሐቀኝነት ነው፡፡ በሌላ ዘመንና ቦታም ይህ ተመሳሳይ ታሪክ በትግራዩ ራስ ልዑል ሚካኤል ስሑል /18ኛው መ/ክ/ ተፈጽሟል፡፡ ሁለቱም ከግል ጥቅማቸው በተቃራኒ ቆመዋል፡፡ ይህ ነው ኢትዮጵያዊው መልካም እሴት፡፡ ሁለቱም መሪዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሕ ሲጓደል በብርቱ እንደሚያዝን፤ ምንም የተወሰደው ሀብት ዋጋው ያነሰ ቢሆን በዳኝነት መዛባት እጅግ አድርጎ እንደሚቆጭ ያውቃሉ፡፡ “በፍርድ ከሄደችው በቅሎዬ፤ ያለ ፍርድ የሄዳችው ጭብጦዬ ታሳዝነኛለች” የሚል ጽኑ የፍትሕ ጥማት እምነቱ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ እነርሱም የርትዕ ፍርድ ታላቅነት አሳዩት፡፡

ስለዚህም የአንድ ሥልጡን ማኅበረሰብ አንዱ መገለጫው ይህን ከመሰለ ባሕላዊ እሴቱ ጋር አለመጋጨቱ፤ አለመቃረኑ ነው፡፡ ስለ ሥልጣኔ ስናወራ ለሥጋ እርካታ መገለጫ የሆነችውን የአብረቅራቂ ቁስ ሙሌትን ብቻ ይዘን መጓዝ የለብንም፡፡ የከበሩ የባሕልና የታሪክ እሴቶቻችንም የሥልጣኔ ማነጸሪያዎች ናቸው፡፡ የሰው ልጅን ማንነትና ፍላጎት በቁሳዊ ነገር ብቻ መመዘንም፤ ሰውን ከሰውነት ደረጃ ማውረድ ነው፡፡ በዚህ መተማመን ከተደረሰ አንድ ሥልጡን ማኅበረሰብ ለመገንባት በምናደርገው ጉዞ ውስጥ ሥልጣኔን በግንጥል ጌጧ ሳይሆን በሙሉ ክብሯ እንረዳታለን ማለት ነው፡፡

ዛሬ ጊዜና ታሪክ በሰጡን ኃላፊነት ላይ ያለን ሁሉ “ደሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ” የማንል ከሆነ፤ ከግል ጥቅም ይልቅ ለብዙኃኑ ጥቅም ካልቆምን? የሰው እንባ እሳት ነው ያቃጥላል ካላልን? ከራሳችን የእምነትና የእሴት ስሌት በተቃራኒ ስለቆምን በእውነት አልሰለጠንም፡፡

ውድ አንባቢዎች አፄ ዘርአያዕቆብና ራስ ልዑል ሚካኤል ስሑል በልባቸው ካለው የእምነትና የእሴት ስሌት በተቃራኒ ያልቆሙበት ምክንያት /ሠልጥነው የታዩበት ምሥጢር/ የሚከተሉት አራቱ ይመስሉኛል፡፡

1. እግዚአብሔር አለ፤ እሱ ይፈርዳል፤ በምንሰጠው ፍርድ እሱ ይመለከታል ብለው ማመናቸው፡፡

2.  ሕሊና አለ፤ እሱን ማምለጥ አይቻልምና ብለው ለሕሊናቸው በመገዛታቸው፡፡

3. ታሪክ አለ፤ ታሪክ ይፋረደናል፤ የምንሠራውን ነገር ለታሪክ ትተነው የምንሄድ ነን፤ ከታሪክ ማምለጥ አንችልም ብለው በጽናት መቆማቸውና፣

4.  ሕዝብ አለ፤ የተደረገውን ስለሚያውቅ ይመለከተናል፡፡ ይታዘበናል፡፡ ከእነዚህ ነገሮች ማምለጥ አንችልም ብለው በመንፈሳዊ ወኔ መቆማቸው ነው፡፡

ስለ እውነተኛ ዳኝነት ከቱባ ባሕላችን ውስጥ መዘን ስናጠና የምናገኘው የትልልቆቹን መሪዎች፣ የከበሩት አበውና፣ የሚደነቁት እመው ያልተዛባ ፍርድ ክዋኔ ምሥጢሩ፤ በምንሠራው ሥራ፤ በምንሰጠው ፍርድ እግዚአብሔር፣ ሕሊና፣ ታሪክና ሕዝብ አለ ብለው ማመናቸው ነው፡፡ ከሰፈር የዕቁብ ዳኝነት እስከ ሀገር ማስተዳደር፤ ከማኅበር ሙሴነት እስከ ቤተ ክርስቲያን መምራት የቻለ ሰው በሚያስተላልፈው ውሳኔና በሚሰጠው ፍርድ ውስጥ ከላይ ያየናቸውን አራቱን የባሕላችንን እሴቶች በልቡናው ጽላት ቀርጾ በእነርሱ መመራት ካልቻለ፡፡ ፍትሕ ትጨነግፋለች፡፡ እውነት ከምድሩ ትጠፋለች፡፡ ፍቅር ጓዟን ጠቅልላ ትበናለች፡፡ ክህደት ታብባለች፡፡ ማስመሰል ትነግሳለች፡፡ ውሸት ትወፍራለች፡፡ ሥልጣኔ ቅዥት ትሆናለች፡፡

ይቆየን…..

 

«ጠቅላላ ጉባኤው አንድነታችንን ፍቅራችንን የምናጸናበት ነው፡፡» ዲ/ን ሙሉዓለም ካሣ

የአዲስ አበባ ማዕከል 17ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ሐምሌ 23 እና 24/ 2003 ዓ.ም ያደርጋል። ጉባኤውን በተመለከተ በማዕከሉ የአባላትና አገልግሎት ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ ከሆኑት ዲ/ን ሙሉዓለም ካሣ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን ቀርበናልና መልካም ንባብ።

በዘንድሮው ጠቅላላ ጉባኤ የእርስዎ ድርሻ ምንድን ነው?

ለጠቅላላ ጉባኤው አባላትን የሚጠራው የአባላትና አገልግሎት ማስተባበሪያ ክፍል ነው፡፡ በተጨማሪም በተዋቀረው ዐቢይ ኮሚቴ ጥሪዎችንና ቅስቀሳዎችን ማድረግ ነው፡፡

በጠቅላላ ጉባኤው ምን ምን ክንዋኔዎች ይካሄዳሉ?

በጠቅላላ ጉባኤያት እንደማንኛውም ጊዜ የተለመዱ አሠራሮች አሉ፡፡ ለአባላቱ የማዕከሉ የ1 ዓመት የሥራ ክንውን ይቀርባል፡፡ በዚያም ላይ አባላት ይወያያሉ፡፡ ከዚያ ውጭ ለሚቀጥለው ዓመት የተዘጋጀ ዕቅድ ይቀርባል፡፡ ያንንም እቅድ ጠቅላላ ጉባኤው ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ማዕከሉ ለአባላቱ የሚያዘጋጃቸው የመወያያ አጀንዳዎች ይኖራሉ፡፡ በዚያም ላይ ይወያያሉ፡፡ ተጨማሪ መረጃዎች ካሉ እንዲሁ ለአባላት ይቀርባል፡፡ ከዚያም ውጭ የዋናው ማዕከል ተወካይ የሚያቀርበው ግምገማ ከዚያው ጋር የሚታይ ሲሆን አዲስ የሥራ አስፈጻሚ ምርጫም ይኖራል፡፡

ከጠቅላላ ጉባኤው ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች ይኖራሉ?

ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ዝግጅት ተደርጓል። አባላት በብዛት ይገኛሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ከ2000 በላይ ለሆኑ አባላት ጥሪ አድርገናል፡፡ በደብዳቤና በወረዳ ማዕከላት ደረጃ በአጭር የስልክ ጽሑፍ /SMS/ መልእክት አስተላልፈናል። ከጠቅላላ ጉባኤ አስቀድመን የአዲስ አበባ ማዕከልን አጠቃላይ አገልግሎት የሚዳስስ ዓውደ ርእይ ይፋ ሆኖ እስከ ጠቅላላ ጉባኤ ይቀጥላል። በዚህም አባላት አስተያየታቸውን በመስጠት ሱታፌያቸውን ያሳያሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ከዚህ ውጭ ለጠቅላላ ጉባኤው አባላት እንደከዚህ በፊት ሁሉ ሙሉ ቀን ስለሚውሉ የሚያስፈልጋቸውን የምሳና የመሳሰሉት ዝግጅቶች ከወዲሁ ተጠናቋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ካለበት ዘርፈ ብዙ ኃላፊነት አንጻርና የአ.አ ማዕከልም ካሉት የአባላት ብዛት አንጻር ጠቅላላ ጉባኤው ምን ዓይነት ወሳኝነት /ውጤት/ ይኖረዋል?

እንደሚታወቀው የአ.አ ማዕከል ለዋናው ማዕከል መቀመጫ ነው፡፡ ወይም አ.አ. ማዕከል ያሉ አባላት በዋናው ማዕከል ያገለግላሉ፤ ስለዚህ በርካታ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩት፣ ታላላቅ ሥራዎች ይሠራሉ ተብሎ የሚጠበቀው አ.አ ማዕከል ነው፡፡ እንደ አባላት ብዛትም ሲታይ በሺዎች የሚቆጠሩ አባላት የሚገኙት በዚህ ማዕከል ነው፡፡ ስለዚህ ለዋናው ማዕከል ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በመስጠት የአዲስ አበባ ማዕከል አባላት ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ መሠረት ለሚቀጥለው ጊዜ ለማኅበሩም ሆነ ለቅድስት ቤ/ክን በጎ ይሆናሉ ብለን በምናስባቸው ጉዳዮች ላይ አባሉ ጥሩ ሱታፌ በማድረግ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ብለን እንጠብቃለን፡፡ በዋናው ማዕከል፣ በአ.አ. ማዕከልና በወረዳ ማዕከል ያሉ አባላት በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የሚያነሷቸው ሐሳቦች በሙሉ በአጠቃላይ ማኅበሩ አዲስ አበባ ላይ ለሚሰጠው አገልግሎት ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡ ይኸም አጠቃላይ ውጤቱ በማኅበሩ የሚያበረክተው ፋይዳ የጎላ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ከጉባኤው ከአባላት ምን ዓይነት ተሳትፎ ይጠበቃል?

ይህንን ጊዜ ከባለፈው ጊዜ ተጠንቅቀን የመረጥንበት ምክንያት አለን፡፡ በተለይ ባለፈው ሳምንት ያላደረግነው በምረቃ ምክንያት ነው። ወቅቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚመረቁበት ነበር፤ የማኅበሩ አባላት ተመራቂዎችና አስመራቂዎች መሆን እድል ስላላቸው መርሐ ግብሩን ሐምሌ 23 እና 24 አድርገነዋል። ስለሆነም፣ በመጀመሪያ ደረጃ መገኘት የአባልነት ድርሻ በመሆኑ ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡ መገኘት አንዱ መብትም ግዴታም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚያ ውጭ በሚኖሩ ውይይቶች ላይ አስተያየታቸውን በመስጠት፣ የቀረ ነገር ካለ በመሙላት፣ የተጣመመውን በማቃናት በሚቀጥለው ደግሞ እንዲህ ይሁን በማለት ያለፈውን አስተያየት በመስጠት በሚመጣውም በመምከር ሱታፌያቸውን ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ውጭ የማዕከሉ ሥራ ማስፈጸሚያ ወይም ለዚህ የሚያስፈልገው አጠቃላይ በጀት ሙሉ በሙሉ በማዕከሉ የሚሸፈን አይደለም፡፡ አባላት በሚያደርጓቸው አስተዋጽኦዎች፣ ለመስተንግዶ የሚሆኑትን ሁሉ በማበርከት ነው፡፡ ስለዚህ ይህም ሌላኛው የአባላት ሱታፌ የሚጠበቅበት ይሆናል፡፡ ከምንም በላይ በዘንድሮው የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ስላለ አባላት ለማዕከሉ አገልግሎት ይሆናሉ የሚሏቸውን ወንድሞችና እኅቶች ከወዲሁ በጸሎታቸው እንዲያግዙ ይጠበቃል፡፡ በእነዚህ ዙሪያ የአባላት ተሳትፎ ከሚጀመርበት ከቅዳሜ ጠዋት 2፡00 ጀምሮ እስከ እሑድ ማታ 12፡00 ምንም ዓይነት መርሐ ግብር ሳይኖራቸው ይህንን እንደግዴታ ወስደው ከወዲሁ መርሐ ግብራቸውን አመቻችተው በዚህ እለት እንዲገኙ ይጠበቃል፡፡

ቀደም ብለው ጠቀስ እንዳደረጉት ዘንድሮ የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ይደረጋል፡፡ ያለፈው ሥራ አስፈጻሚ ነገሮችን ተደማምጦ በመቻቻልና በመንፈሳዊነት በማከናወን በቀጣዩ ምን ዓይነት ተመክሮ ያስተላልፋል?

የማኅበረ ቅዱሳን አንዱ ትልቁ እሴት መደማመጥ ነው። ከእኔ ይልቅ ወንድሜ ይሻላል እኅቴ ትሻላለች፤ የወንድሜ ይሰማ የእኅቴ ይሰማ አንዱ እሴታችን ነው፡፡ ተነጋግረን እንኳን መግባባት ቢያቅተን እግዚአብሔር ይግለጥልን ብለን አጀንዳዎችን እናሳድራለን፡፡
እኔ በግሌ በማዕከሉ አገልግሎት ውስጥ የተደሰትኩበት መግባባቱ መስማማቱ ነው፡፡ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ የሚያሰኝ መግባባትና ስምምነት ነበረን፡፡ ስለዚህ የሚቀጥለውም ሥራ አስፈጻሚ ይሄን ያደርጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እኛም የተረከብናቸው ወንድሞችና እኅቶች ይህንን ሲያደርጉ ነበር እርሱም ከቀደምቱ እንዲሁ ተቀብለው ነበር። በዚህ መልኩ ይኸው ይቀጥላል፡፡

አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ላንሳ፤ በፊት ለዋናው ማዕከል የአገልግሎት ክፍሎች እንዲሁም የሥራ አስፈጻሚና አመራር የሚመረጡት ወንድሞችና እኅቶች በአዲስ አበባ ማዕከልና በሌሎች ማዕከላት የአገልግሎትና የሕይወት ትሞክሮ ተፈትነው አልፈው ነው፤ ስለዚህ ብዙውን ጊዜ አዲስ አበባ ማዕከል እነዚህን ወንድሞችና እህቶች በአብዛኛው አሰልጥኖ የማቅረብ ልምድ አለው፡፡ አሁንስ ያለው አካሔድ ምን ይመስላል?

በማዕከላችን በኩል በዘንድሮው ተጠናክሯል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ልምድ የሚያስፈልጋቸው የአገልግሎት ሁኔታዎች አሉ፡፡ ወደ ሥራ አስፈጻሚ ሲመጣ የማኅበሩን አሠራር፥ የቤ/ክንን ጠቅላላ ሁኔታ፥ ሌሎችንም ነገሮች ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሁለገብ እይታን የሚፈልግ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ጥንካሬዎች በአገልግሎት፣ በሒደት፣ በውጣ ውረድ ውስጥ የሚመጡ አሉ፡፡ በትምህርት በሥልጠናዎች የምናገኛቸው ብርታቶችም አሉ፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ሁኔታዎች ይታያል እንጂ ከምንም አንስተህ ወደ ሥራ አስፈጻሚ አታስገባም። የዘንድሮው ተጠናክሯል ብዬ የማስበው የአ.አ. ማዕከል ከሌሎቹ በተለየ መልኩ የተተኪ አመራር ሥልጠና አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ለዋናው ማዕከል የአገልግሎት ክፍሎችና ለአ.አ ማዕከል አገልግሎት ክፍሎች የሚሆኑ የተተኪ አመራር አባላትን ተዘጋጅተዋል፡፡ በተወሰነ መልኩ የዘንድሮ ሥራ አስፈጻሚም ጠቅላላ ጉባኤው እነዚህን አባላትንና ሌሎችንም ያካትታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ በአገልግሎት የተፈተኑና ልምድ ያላቸውን ወንድሞችና እኅቶች የተተኪ አመራር ሥልጠና የወሰዱት ወደ ሥራ አስፈጻሚ ይገባሉ ብየም እገምታለሁ፡፡ ለተተኪ አመራርነት ስናሰለጥን ቀድሞውኑ ያሉበትን ሁኔታ የንዑስ ክፍል ኃላፊዎች፣ የክፍል ኃላፊዎች የመሠከሩላቸው ወንድሞችና እኅቶች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ አንተም እንዳነሳኸው ለዋናው ማዕከልም ሆነ ለአዲስ አበባ ማዕከል አገልግሎት ክፍሎች በልምድና በሥልጠና የተዘጋጁ አባላት ወደ ኃላፊነት ይሔዳሉ።

በመጨረሻ የሚያስተላልፉት ነገር ካለ?

የዘንድሮው ጠቅላላ ጉባኤ ሐምሌ 23 እና 24 2003 ዓ.ም ይካሔዳል፡፡ ሁለቱንም ቀን አባላት ራሳቸውን ዝግጁ አድርገው እንዲቆዩ፤ እኛም እንደ ሥራ አስፈጻሚም ሆነ እንደማዕከሉ ጓጉተን የምንጠብቀው ዕለት ነው፡፡ አንድነታችንን ፍቅራችንን የምናጸናበት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ጠቅላላ ጉባኤ ሁሉም ሰው የሚገናኝበት ስለሆነ በደስታና በፍቅር የምንጠብቀው ነው፡፡ ለዚህ አገልግሎት መስተንግዶዎች ይኖራሉ በተዘጋጁ መስተንግዶዎች ለመስተናገድ፣ ጥያቄም ሐሳብም ያላቸው ደግሞ የሚመለከተውን አካል እየጠየቁ በዚያ መልኩ እንዲስተናገዱ እያሳሰብኩ ከሁሉም በላይ የጠቅላላ ጉባኤው ቀናት እስከሚደርስና በዚያው ጊዜም አባላት በጸሎታቸው እንዲያስቡን እንጠይቃለን፡፡

እግዚአብሔር ይስጥልን

አሜን አብሮ ይሰጠን፡፡
 

Temerakiwoch.JPG

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከ15,000 በላይ የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎችን አስመረቀች።

ተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
Temerakiwoch.JPG

ማኅበረ ቅዱሳን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩና በግቢ ጉባኤያት ትምህርተ ሃይማኖት ያስተማራቸውን ከ15,000 በላይ ተማሪዎች በአባቶች ቡራኬ አስመረቀ። ተመራቂዎች የአደራ ቃልም ተሰጥቷቸዋል።

በአዲስ አበባና አካባቢዋ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች ዛሬ እሑድ ሐምሌ 17 ቀን 2003 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽና በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ተክለ ሳዊሮስ ሰ/ት/ቤት አዳራሽ ተመርቀዋል።

በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በተደረገው መርሐግብር የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስና የሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ተገኝተዋል።
BitsuanAbatoch2.JPG

ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ በሰጡት ቃለ ምዕዳን «ደክመው ያስተማሯችሁን ቤተ ክርስቲያናችሁንና ማኅበራችሁን እንዳታሳፍሩ በሕይወታችሁ ልትበረቱ ልትጸኑ ያስፈልጋል።» በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የማኅበሩ ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልእክት ”በዕድሜ ዘመናችሁ ሁሉ በክርስትና እምነት እና ሥርዓተ አምልኮ መጽናትን ዐቢይ ዓላማችሁ አድርጋችሁ እንድትይዙና እንድትመላለሱበት፤ በክርስቲያናዊ ሕይወት ከመጽናት በተጨማሪም ባገኛችሁት ዕውቀት ሥጋዊ ወመንፈሳዊ ተጠቅማችሁ ሀገራችንን ኢትዮጵያን ይልቁንም እናት ቤተ ክርስቲያናችሁን በምትችሉት ሁሉ እንድታገለግሉ ይኸውም ቃለ ዐዋዲያችን በሚያዘው መሠረት በሰ/ት/ቤትና በሰበካ ጉባኤ ተጨባጭ ተሳትፎ እንድታደርጉ” ብለዋል።
Dn.Yaregal.JPGዲ/ን ያረጋል አበጋዝ “ይዞ የተገኘው ወጣት” በሚል ርእስ የዕለቱን ትምህርት አስተምረዋል። “ጌታችን 5 እንጀራና 2 ዓሣ ሲያበረክት እነዚያን ይዞ እንደተገኘው ወጣት 5ቱን የስሜት ሕዋሳት ለእግዚአብሔር ማስገዛት ይዘን መገኘት ይኖርብናል።፡ከዚህም በተጨማሪ በ2 ዓሣዎች የተመሰሉትን ዕውቀት ሥጋዊና መንፈሳዊ እንዲባርክልን መለመን አለብን” ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በማኅበሩ የአዲስ አበባ ማዕከል መዘምራን “ወይቤሎሙ ሑሩ ወመሀሩና ሌሎችን መዝሙሮችን አቅርበዋል።”
ከግቢ ጉባኤያት የተውጣጡ ተመራቂ ተማሪዎችም በብፁዓን አባቶቻቸው፣ በቤተሠቦቻቸው፣ በወንድምና እህቶቻቸው ፊት።
«ጸውዖሙ ወባረኮሙ ወይቤሎሙ አማልክት አንትሙ ወደቂቀ ልዑል ኩልክሙ፣
 ወሰኑ ወሠርዑ ሃይማኖተ እንተ ኢትጠፍዕ።
ጠራቸው፣ ባረካቸውም እናንተ አማልክት ናችሁ፤ ሁላችሁ የልዑል ልጆች ናችሁ አላቸው። እነርሱም የማትጠፋ ሃይማኖትን ደነገጉ።» የሚለውንና ስለ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት የሚናገረውን ወረብ በቁም ዜማና ጽፋት ዘምረው ወርበውታል።
 
በማኅበሩ የሀገር ውስጥ ማዕከላትና ግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ዋና ክፍል የግቢ ጉባኤያት ክፍል አስተባባሪ አቶ እንዳለ ደጀኔ እንደገለጡት ምንም እንኳን በግቢ ጉባኤያቱ የሚሰጡትን የትምህርት ዓይነቶች በአግባቡ በመማር ለምርቃት መጽሔት የበቁት ከ15,000 በላይ ቢሆኑም ማዕከላቱ በሚያዘጋጇቸው የቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸው የምረቃ መርሐ ግብር የአደራ መስቀል የሚቀበሉት ከ32,000 ተማሪዎች በላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ውስጥ 42 ማዕከላትን፣ ከ400 በላይ ወረዳ ማዕከላትና ግንኙነት ጣቢያዎችን እንዲሁም 300 ግቢ ጉባኤያት ያቀፈ ሲሆን በዛሬው ዕለት የሚመረቁትን ጨምሮ ከ120,000 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በየአጥቢያቸው አስተምሮ በአባቶች ቡራኬ አስመርቋል። በአሁኑ ወቅትም ከ150,000 በላይ ተማሪዎችን በግቢ ጉባኤያት ሰብስቦ በማስተማር ላይ ይገኛል። ከሀገር ወጭ ደግሞ 4 ማዕከላትና 4 ግንኙነት ጣቢያዎች አሉት።