ec_members

አውሮፓ ማእከል ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

ሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ


  • የማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት እና የአውሮፓ ማእከል 12ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል በስውድን ተከበረ።

በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ጠቅላላ ጉባኤውን ከሰኔ 29 እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም. በሀገረ ስዊድን ስቶክሆልም ከተማ አካሄደ። ከመላው አውሮፓ የተሰባሰቡ ec_membersየማኅበሩ አባላት፣ በስዊድን የተለያዩ ከተሞች የሚያገለግሉ ካህናትና ምእመናን በተሳተፉበት በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ የማእከሉ የ2004 ዓ.ም. የአገልግሎት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በውይይቱም ማእከሉ በአገልግሎት ዘመኑ አጠናክሮ የሰጣቸውን አገልግሎቶች በቀጣዩ ዓመትም አጠናክሮ እንዲቀጥልባቸው ሊፈጽማቸው ያቀዳቸው ነገር ግን በልዩ ልዩ ምክንያት መፈጸም ያልቻላቸውን ወይም ከታቀደው በታች ያከናወናቸውን አገልግሎቶች በሚቀጥለው ዓመት እንዲፈጽማቸው ውሳኔ አሳልፏል።

 

ማኅበረ ቅዱሳን በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ በተለይም በሬድዮ እየሰጠ ያለውን ሰፊ አገልግሎት ለመደገፍ ማእከሉ ባቋቋመው የሬድዮ ቤተሰብ አማካይነት እያደረገ ስላለው ድጋፍና ቀጣይ ሂደትም ተወያይቶ ጠቃሚ ውሳኔዎችን አሳልፏል። ከዚህም ጋር በዋናው ማእከል እየተተገበረ ያለው የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮጀክት በታቀደለት ጊዜና ዝርዝር ተግባራት መሠረት ይፈጽም ዘንድ ማእከሉ ባቋቋመው የድጋፍ ሰጪ አስተባባሪ ቡድን አማካይነት በመስጠት ላይ ስላለው ድጋፍ ሪፖርት ቀርቦ ጉባኤው ሰፊ ውይይት በማድረግ ልዩ ልዩ የማሻሻያ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

 

ጉባኤው ማኀበረ ቅዱሳን በቅዱሳት መካናትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ድጋፍ ገዳማት ከሚያመርቷቸው ምርቶች የአውሮፓmk_eu_12th_anniversary ምእመናን ተጠቃሚ በሚሆኑበት ሁኔታ ላይም ተወያይቶ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ለተፈጻሚነታቸው በማእከሉ ስር ላለው ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ከባድ ኃላፊነት ሰጥቷል። የጉባኤውን ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሌላው አጀንዳ “የአውሮፓ ማእከል አባላት የአገልግሎት ሱታፌ ከማኀበረ ቅዱሳን ተልእኮ አንጻር” በሚል ርእስ የቀረበው ጥናት ነበር። በማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ በተቋቋመው ቡድን ተዘጋጅቶ የቀረበው ይህ ጥናት በሁሉም የአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ አባላት በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሥር ታቅፈው በመስጠት ላይ ያሉትን አገልግሎት የዳሰሰ፣ ጥንካሬዎችንና ድክመቶችን ነቅሶ ያወጣ፣ ወደፊት ሊደረግ የሚገባውን ያመላከተ ሰፊ ጥናት ነበር። ጉባኤው በጥናቱ ላይ ሰፊና ሞቅ ያለ ውይይት አድርጎ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

 

ጉባኤው ከዋናው ማእከል የተላከለትን ሪፖርትና መልእክት በተወካዩ አማካይነት በማድመጥ ውይይት አድርጓል። ጉባኤው የማኀበራችንን 20ኛ ዓመት እንዲሁም የአውሮፓ ማዕከልን 12ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ማእከሉ በተመሠረተበት ሀገር በስዊድን በደመቀ ሁኔታ አክብሯል።

 

ga_2004_participantsበመጨረሻም ጉባኤው በቀረበለት የቀጣዩ የ2005 ዓ.ም. የአገልግሎት ዘመን ዕቅድ ላይ ተወያይቶ የማሻሻያ ዐሳቦችን በመስጠት ካጸደቀ በኋላ ማእከሉን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሚመራ አዲስ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ መርጦ የጉባኤው ፍጻሜ ሆኗል። ማእከሉ ስምንት የግንኙነት ጣቢያዎች እና አምስት ቀጠና ማእከላት ያሉት ሲሆን በስዊድን ቀጠና ማእከል የተዘጋጀው የዘንድሮው ጉባኤ የተሳካ እንደነበር የጉባኤው ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ቀጠና ማእከሉ ለጉባኤው መሳካት አስተዋጽዖ ያደረጉትን አባላትና ምእመናን እንዲሁም ተቋማት በተለይ ጉባኤው በተመቼ ሁኔታ ይካሄድ ዘንድ መሰብሰቢያ አዳራሽና የተሳታፊዎችን ማረፊያ ቤት ከሙሉ አገልግሎት ጋር በነጻ የሰጠውን በብሬድንግ የስዊድን ቤተ ክርስቲያን አመስግኗል።

 

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።