ሀገረ ስብከቱ የ2004 ዓ.ም. ዕቅድ አፈጻጸምን ገምግሞ የአዲስ ዓመት ዕቅድን አጸደቀ፡፡

ነሐሴ 3 ቀን 2004 ዓ.ም.

ከጅማ ማእከል

  • ቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ አውጥቶ ያዋቀረውን ማኅበር በአክራሪነት መፈረጅ ቤተ ክርስቲያንን መፈረጅ ነው፡፡

የጅማ ሀገረ ስብከት ጠቅላላ ጉባኤ የ2004 ዓ.ም. ዕቅድና ክንውንን በመገምገም፣ የ2004 ዓ.ም. ዕቅድን በማውጣትና መመሪያ በመቀበል ሰኔ 28-29 ቀን 2004 ዓ.ም. ተካሂዶ ተጠናቀቀ፡፡

 

ጉባኤውን የመሩት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ጠቅላላ ጉባኤው የ2004 ዓ.ም. የሥራ ግምገማ ማድረጉ ካለፈው ተሞክሮ በመውሰድ ለቀጣይ የተሻለ ለመሥራትና የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማሻሻል የሚረዳ በመሆኑ በቀጣይም የተሳካ ሥራን ለመሥራት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ስለሺ አስፋው ከ2004 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በተጨማሪ ሀገረ ስብከቱ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን ለማስከፈት ይረዳ ዘንድ እየተሠራ ያለው ባለ 5 ፎቅ ሕንፃ ግንባታን በተመለከተ የሒሳብ ራፖርት አቅርበዋል፡፡ ለዚህ ሥራም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አድባራትና ግለሰቦችን አመሰግነዋል፡፡

 

በጉባኤው ማጠቃለያ ላይም ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክት በአንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ አውጥቶ ያዋቀረውን ማኅበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት ስም መፈረጅ ቤተ ክርስቲያንን መጥቀስ በመሆኑ ይህን የሚያደርጉ አንዳንድ አካላት ከድርጊታቸው መታረም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

 

በመጨረሻም በሀገረ ስብከቱ በበጀት ዓመቱ ብልጫ ሥራ የሠሩ አካላት የተሸለሙ ሲሆን የማኅበረ ቅዱሳን የጅማ ማእከል የዓመቱ ልዩ ተሸላሚ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

በሀገረ ስብከቱ በዘንድሮው ዓመት ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ወገኖች ከተለያዩ ቤተ እምነቶች ወደ ኦርቶዶክሰ ተዋሕኦ ሃይማኖት እንደተመለሰም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ የ2005 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤን በአጋሮ ከተማ እንዲዘጋጅ በመወሰን ጉባኤው ተጠናቋል፡፡

 

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 19ኛ ዓመት ቁጥር 22 ከነሐሴ 1-15 ቀን 2004 ዓ.ም.