dsc01699

የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ክፍሉ ለአረጋውያን እርዳታ አደረገ፡፡

ሐምሌ 24 ቀን 2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ክፍል ባሳለፍነው ሳምንት ረጅም ዘመናትን በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ላሳለፉ አረጋውያን ጊዜያዊ የአልባሳትና የሕክምና እርዳታ አደረገ፡፡

የአገልግሎት ክፍሉ አብዛኛውን የእድሜ ዘመናቸውን በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ አድርገው ለኖሩ ሰባት አባቶች የአልባሳት እገዛ dsc01699ያደረገው በ2004 ዓ.ም. መሪ እቅዱ መሠረት መሆኑን የጠቀሱት የክፍሉ ሓላፊ ወይዘሪት መቅደስ ዓለሙ፤ “ይህንን ለማቀድ ምክንያት የሆነን አባቶቻችን ከሰፊ የአገልግሎት ዘመናቸው በኋላ የሚታሰብላቸው የጡረታ አበል አለመኖሩ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ አባቶችም በቅርብ የሚረዳቸውና የሚንከባከባቸው ሰው የሌላቸው ናቸው፡፡ ስለሆነም ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳልሰጡ በቂ ትኩረት ተነፍጓቸውና ተረስተው በየመቃብር ቤቱና ንጽሕና በተጓደለባቸው ሥፍራዎች ወድቀው የሚገኙትን አባቶች፤ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር ባካሄድነው ጥናትና ባገኘነው መረጃ መሠረት መርጠን ረድተናል፡፡” በማለት ምክንያቱን አስረድተዋል፡፡

የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ክፍሉ በልዩ ልዩ ቦታዎች ለሚገኙ አረጋውያን ካበረከተው የአልባሳት አስተዋጽኦ በተጨማሪ በበጎ አድራጊdsc01709 ምእመን ቤት ተጠግተው ለሚኖሩ አንድ አባት ሙሉ የሕክምና ወጪ በመሸፈን እንዲታከሙ አድርጓአል፡፡

 

በስተመጨረሻም ወይዘሪት መቅደስ ዓለሙ “ከጊዜያዊ እርዳታ ባለፈ በቀጣይ አረጋውያኑን ለማቋቋምና ኑሮአቸውን ለማሻሻል በክፍሉ ምን ታስቧል?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይህ እቅድ በ2005 ዓ.ም. ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ክፍሉም እንደ ክፍል በአቅም ከፍ ይላል ብለን እናስባለን፡፡ እናም በቀጣዩ ዓመት ከጊዜያዊ እርዳታ ይልቅ የተሻለ እገዛ ማበርከት የምንችልበትን ዝግጅት አጠናቅቀናል፤ ጊዜው ሲደርስም ይህንኑ እንፈጽማለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡” ብለዋል፡፡

 

በተያያዘ ዜና የአገልግሎት ክፍሉ በበኪ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤት ለሚገኙ ተማሪዎች ማቋቋሚያ የሚሆን ፕሮጀክት ነድፎ እየሠራ መሆኑን በተለይ  ለመካነ ድራችን በሰጠው መግለጫ አስረድቷል፡፡ ከዚህ ቀደም  በአገልግሎት ክፍሉ አማካኝነት ለተማሪዎች ጊዜያዊ የአልባሳትና የቀለብ እገዛ የተደረገ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ግን ተግባራዊ የሆነውና  በሦስት ሔክታር መሬት ላይ  ያርፈው የእርሻ ሥራ ሙሉ ለሙሉ የተማሪዎችን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

dsc01744በሦስት ሔክታር መሬት ላይ ጤፍ ለመዝራት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ያወሱት የአገልግሎት ክፍሉ ኃላፊ ወይዘሪት መቅደስ “መሬቱን በትራክተር ከታረሰበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ ለሦስት ተከታታይ ጊዜያት የአከባቢው ገበሬዎች አርባ ጥማድ በሬዎቹን ይዘው እንዲሁም፤  ምእመናን በገንዘባቸውና በጉልበታቸው  አማካኝነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ … ከደብሩ አስተዳደር ጀምሮ ሌሎችም መደበኛ  አገልጋዮችና ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት በጋራ እንሥራ የሚለውን መርሕ የተቀበሉ ናቸው፡፡ ይህም በሌሎች ቦታዎች ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አካላት መልካም ተሞክሮ ነው፡፡” በማለት በማጠቃለያ መልእክታቸው በፕሮጀክቱ ትግበራ ላይ የተባበሩትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡