ግንቦት 25 ቀን 2004 ዓ.ም
ዲ/ን ዮሴፍ ይኩኖአምላክ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አስተባባሪነት አገር አቀፍ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት መሥራች ጉባኤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ እየተካሔደ ነው፡፡
በ48 አህጉረ ስብከቶች የሚገኙ የሰ/ት/ቤት ኃላፊዎችና ከ160 ሰ/ት/ቤቶች የተውጣጡ የየሰንበት ትምህርት ቤቱ የሥራ አመራር አካላት የተገኙበት ጉባኤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንትና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ዛሬ ግንቦት 25 ቀን 2004 ዓ.ም ረፋድ 4፡30 በጸሎት ተከፍቷል፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የዐቢይ ኮሚቴውን መልእክት በንባብ ያቀረቡት ዲ/ን በላይ ገብረሕይወት “ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሕፃናትና ወጣቶችን የሚያቅፍ መዋቅር ሰንበት ት/ቤት አዋቅራ ልጆቿን ስታስተምር ቆይታለች፡፡ ልጆቿም ቃሏን ሰምተው ሥርዓቷን እያከበሩ በሰንበት ትምህርት ቤት ታቅፈው ሲያገለግሉ አርባ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በእነዚህ አርባ ዓመታትም በክፉም ሆነ በደጉም ሁኔታ በጉልበታቸው በዕውቀታቸው ቤተክርስቲያንን እያገለገሉ ብዙዎች አልፈው ይህ ሂደት እኛ ጋር ደርሷል፡፡ይህ በቅንነት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለማበርከት እንደነዚህ ያሉ የአንድነት ጉባዔያት ጠቀሜታ ከፍ ያለ ነው፡፡ ” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመላው ዐለም ከ7 ሚሊየን በላይ የተመዘገቡ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዳሏት የገለጹት የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ መምህር እንቈባሕርይ ተከስተ፡-“የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የ5 ዓመታት ሀገር አቀፍ መሪ ዕቅድ ላይ ለመወያየት ከመላ ሃገሪቱ ከ600 በላይ የሰንበት ት/ቤት ኃላፊዎች የዚሁ ጉባኤ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በመሆኑም ይህ ጉባኤ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ጉባኤው የ5 ዓመታት መሪ ዕቅዱን መርምሮና አዳብሮ እንደሚያጸድቀው ይጠበቃል፡ብለዋል፡፡
ከሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ንግግር በኋላ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የድሬዳዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስና የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ የበዓለ ሃምሳን በተመለከተ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
ከብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገሪማ በመቀጠል የጉባኤውን መጀመር በይፋ ያበሰሩት ቃለምዕዳን ያሰሙት ቅዱስ ፓትርያርኩ፡-˝ ይህ ዓይነት ስብሰባ ተገቢና ከተገቢም በላይ ነው፡… አትዮጵያውያን ወጣቶች በቤተክርሰቲያን ሊገኙ ይገባቸዋል ፤ ግዴታቸውም ነው፡፡˝ በማለት ጉባኤው የሰመረ እንዲሆን ልባዊ ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
የጠዋቱ መርሐ ግብር ከመጠናቀቁ በፊት ˝የወጣቱ አስተዋጽኦ በቤተክርስቲያን˝ በሚል ርዕስ ዲያቆን ዶ/ር ያየህ ነጋሽ ያዘጋጁትን ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
• አጠቃላይ የወጣቱ አኗኗርና ፈተናዎቹ፤
• በመፍትሔው ረገድ የቤተ ክርስቲያን ድርሻን መጠቆም
• በቤተ ክርስቲያን የወጣቱን አስተዋጽኦ መጠቆም … የጥናታዊው ጽሑፍ ዓላማ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ዲ/ን ዶክተር ያየህ ነጋሽ ፡-˝በሰንበት ትምህርት ቤት የዕድሜ ገደብ ዙሪያ የሚነሳው አለመግባባትና የትምህርቱ በዕድሜ በጾታ ተለይቶ በሥርዐተ ትምህርት አለመዘጋጀቱ የሰንበት ት/ቤት አገልግሎት ተግዳሮቶች ናቸው፤˝ ብለዋል ፡፡ ˝ የሰንበት ትምህርት ቤቶችንና የወጣቶችን ተግዳሮቶች ከመቅረፍ አንጻር ዋነኛዋ ባለ ድርሻ ቤተክርስቲያን ናት፤˝ የሚሉት ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢው፡-˝ ይህንን ድርሻዋን ለመወጣት ቤተክርስቲያን ለሰንበት ት/ቤት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አለባት” በማለት አሳስበዋል፡፡
በጉባዔው ላይ አግኝተን ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሰብሳቢ ዲያቆን ሔኖክ አሥራት ˝የዚህ ጉባኤ መካሄድ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ አዳዲስ የሚቋቋሙ ሰ/ት/ቤቶች ከነባሮቹ ልምድና ልዩ ልዩ እገዛ እንዲያገኙ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡” ብሏል፡፡
ዛሬ ረፋድ ላይ የተጀመረው ጉባዔ የሚጠናቀቀው ነገ ግንቦት 26ቀን 2004 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኀኒዓለም ቤተክርስቲያን በሚካሄደው ጉባኤ እንደሆነ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ለጉባኤው ከሰጡት መግለጫ ለመረዳት ችለናል፡፡