te 2

ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያናዊ መረጃዎችን የመስጠት አቅሟን ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ

የካቲት 5 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

te 2በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል አስተባበሪነት “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስስቲያን ተልዕኮ በሉላዊቷ ዓለም እና በዘመናዊው ማኅበረሰብ” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀረበ፡፡

 

በማኅበሩ ሕንፃ ውስጥ የካቲት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ጥናታዊ ጽሑፉን ያቀረቡት አቶ ፋንታሁን ዋቄ ሲሆኑ ቀሲስ ዶክተር ደረጀ ሺፈራው መርሐ ግብሩን መርተውታል፡፡ አቶ ፋንታሁን ዋቄ በጥናታቸው ላይ ዘመናዊነትና መዘመን ምንድነው? ዘመናዊነትና መዘመን ለዓለማውያንና ለኦርቶዶክሳዊያን ክርስቲያኖችምን የተለየ ትርጉም ይኖረዋል? የዓለም ተለዋዋጭነት /Dynamizm/ ፍጥነት መገንዘብ፤ ለኦርቶዶክሳዊው ክርስትና ሉላዊነት ምን ይጠቅማል? የቤተ ክርስቲያን መዘመን እንዴት፤ ለምን? በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ሰፊ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡

 

ጥናት አቅራቢው ዘመናዊነትን “ስፋትና ጥልቀት ያላቸው ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊ፤ ፖለቲካዊና ባሕላዊ የለውጥ ሂደቶች ድምር ውጤት የሆነ የኅብረተሰብ ለውጥ ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡ ስለዚህ ዘመናዊነት አዲስነት፤ ያለፈውን መተው፤ መለወጥ፤ አሁን የተሻለ የሚሰኘውን ማድረግና መሆን”ተብሎ ሊተረጎም ይችላል በማለት የጠቀሱ ሲሆን በመንፈሳዊው እይታ ኅብረተሰብ በፈጣሪ ፈቃድ መኖር የሚገባውና በምድር ላይ የእግዚአብሔር መንግሥት መገለጫ ምሳሌ የሆነ አኗኗር ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ኅብረተሰብ ዘመነ ሲባልም ከዚህ አንጻር ሊታይ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ዘመናዊነት ሦስት መልክ አለው ይላሉ፡፡ ማለትም በአስተሳሰብ /አዕምሯዊና መንፈሳዊ/ ፤ በአኗኗር እና በአዕምራዊ ጥበብ በሚገኝ ቁሳዊ ውጤት መራቀቅ ተብሎ ሊለካ ፤ሊተነተን እንደሚችል ያብራሩ ሲሆን አያይዘውም የቤተ ክርስቲያን መዘመንን መለኪያ ሲተነትኑ “በየትውልዱና በየዘመኑ የሰው ልጅ ሕገ እግዚአብሔርን የሚጻረር አስተሳሰብ ፤እምነትና አኗኗርን በመተው ክርስቶስን ወደ መምሰል ሕይወት እንዲመጣ በቴክኖሎጂ፤ በተቋም አቅም በአስተዳደር ወዘተ ይህንን ተልዕኮ ለማስፈጸም በሚያስችል ደረጃ መዘጋጀት የአፈጻጸም ዘመናዊነት ሊባል ይችላል፡፡” በማለት በጥናታቸው አመልክተዋል፡፡

 

ሴኩላር ሂዩማኒዝም/ዓለማዊነት/ በተመለከተም  ሲያብራሩ “በእግዚአብሔር መኖር ከማያምን ሳይንሳዊ ማዕቀፈ እሳቤ የሚመነጭ የኑሮ ፍልስፍና አኗኗር ነው፡፡መሠረቱም የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ሳይንስና በኒውተን የተፈጥሮ ሳይንስ መንጭቶ የመንፈሳዊው ዓለም መኖርን የማይቀበል ትምህርት ሲሆን፤ ዘመናዊው ማኅበራዊ ሳይንስ የዚህ ማእቀፈ እሳቤ ሰለባ ነው፡፡ በዛሬው ዓለም መዘመን እጅጉን የተቆራኘው ከሴኩላር ሂውማኒዝም/ዓለማዊነት/ ጋር ነው፡፡ ሥልጣኔ ፤እድገት፤ መሻሻል፤ ማወቅ፤ ሰው መሆን ሁሉ በሴኩላር ሂውማኒዝም ማዕቀፈ አሳቤ የሚመራ በመሆኑ መደበኛ ትምህርት ፤ ዘመናዊው ሥርዓተ መንግሥት ፤ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት፤ የአስተዳደር መመሪያ ሁሉ በሴኩላር ሂዩማኒዝም መሥፈርት የሚመዘን ነው” በማለት ይገልጹታል፡፡

 

የሉላዊነት አጀማመርን በተመለከተም እንደየ ማዕቀፈ እሳቤው ወይም መሠረተ ፍልስፍናው ዘመን መነሻ እንደሚለያይና የሕገ እግዚአብሔር ሉላዊነት ለአዳም በኤደን የተሰጠችው ብቸኛዋ ሉላዊሕግ እንደነበረችየገለጹት የጥናቱ አቅራቢ አቶ ፋንታሁን ክርስትናም በዚህች በተከፋፈለች ዓለም ውስጥ ሉላዊ ሕግ ትሆን ዘንድ በጌታችን ዓለምን ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ አድርጉ ብሎ ባዘዘ ጊዜ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

 

አቶ ፋንታሁን በጥናታቸው መዘመንን በክርስቲያናዊ ትምህርትና መዘመን በሴኩላር ሂዩማኒዝም እይታ ያላቸውን ልዩነቶችን በማነጻጸርና በመተንተን ያቀረቡ ሲሆን በተለይም ሃይማኖት የሰዎችን ራስን የመግለጽ ዝንባሌ በማገድ ልማትና እድገት ላይ እንቅፋት ይሆናል፤ መንፈሳዊነት ሲጸና ድህነት ይሰፍናል በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ሴኩላር ሂዩማኒዝም /ዓለማዊነት/ መንፈሳዊነትን እንደሚዋጋ አብራርተዋል፡፡

 

የዘመነው ሴኩላር ሂዩማኒዝም ቤተ ክርስቲያንን ለመዋጋት ቴክኖሎጂን፤ ኢኮኖሚን፤ ትምህርትን፤ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ፤ የመንግሥታትte 1 ሕጎችን፤ መገናኛ ብዙኀንን በትጋት በመጠቀም ላይ እንደሚገኝና ፤በአንጻሩ ቤተ ክርስቲያን ከእነዚህ ተቋማትና ቴክኖሎጂዎች ራሷን በማግለል ትጠቃለች፡፡ይህንን ጥቃት ለመቀልበስ ቤተ ክርስቲያን ተገዳዳሪ ሉላዊ ኃይል ለማድረግ በተለያዩ አውዶች በተሰሚነትና በከፍተኛ አቅም ለማሳተፍ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ በመግለጽ የጥናታቸውን ማጠቃለያ ያሉትን  አቅርበዋል፡፡ ባቀረቡት ማጠቃለያም ክርስትና ሉላዊ ሆኖየሚቀጥለው የቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ማዕቀፈ እሳቤ ክርስቶሳዊ ማድረግና ማእቀፈ አሳቤውን የሚገልጽ አኗኗር ተግባራዊ ማድረግ፤ በማንኛውም የዘመናዊ ትምህርት የሚያድጉ የቤተ ክርስቲያን ልጆቿ በቂ የሆነ ክርስቲያናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ፤ ራሷን በመሠረታዊ ፍላጎቶች በመቻልና ከጥገኝነት የማላቀቅ ዕድሎችን ማስፋት፤በሴኩላር ሂዩማኒዝም ማዕቀፈ እሳቤ አመንጪነት የሚፈሰውን የመረጃ ጎርፍ የሚመጥን ክርስቲያናዊ መረጃ የመስጠት ዝግጅት ማጎልበት፤ ለምግባር እንቅፋት የሆኑ የዕለት ተዕለት ኑሮ ጥያቄዎችን በግልጽ በመመለስ ክርስቲያኖች የተበታተነ የግል ውሳኔእንዳይከተሉ መርዳት፤ የተቀደሰ ቤተሰብ አስተዳደርን በሚመለከት የሴኩላር ፍትሕ ዳኝነትን ከቤተ ክርስቲያን አንጻር እንዲያውቁ ማድረግና የመሳሰሉትን ጠቅሰዋል፡፡

 

ጥናታዊ ጽሑፉ እንደተጠናቀቀ ሰፋ ያለ ውይይት የተካሔደ ሲሆን ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡