abune_nathnael

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ፡፡

ታኅሣሥ 26 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


abune_nathnaelየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልእክት “በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ እንዲሁም የሕግ ታሪሚዎች ሆናችሁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት እንኳን ለ2005 ዓ.ም. የጌታችን የአምላካችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዐለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ፡፡” ካሉ በኋላ “በጌታችን ቤዛነት እንድን ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮአልና፤ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር በዚህ አውቀናል፡፡ እግዚአብሔር ከፍጡራን ሁሉ የተለየና ከአእምሮ በላይ የሆነ መለኮታዊ ኀይል ያለው አምላክ በመሆኑ የባሕርዩን ጥልቅነት በምልአት ማወቅ ፈጽሞ የማይቻል ቢሆንም እርሱ ራሱ በገለጸልን መጠን የተወሰኑ ነገሮችን እናውቃለን፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ብሎ ምልአተ ፍቅሩን ካስረደ በኋላ በማስረጃ ሲያብራራ ቤዛ ሆኖ የሰውን ልጅ ያድን ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮአልና ፍቅሩን በዚህ አውቀናል” ይላል፡፡ እግዚአብሔር በልጁ መሥዋዕትነት ዓለምን ለማዳን ያደረገው ፍቅር ከሌላው ሁሉ የበለጠ በመሆኑ ልቆ ተነገረ እንጂ የእግዚአብሔር ፍቅር ከፍጡራን የተለየበት ጊዜ እንደሌለ ሁላችንም እናውቃለን፤ በስፋትም ልንገነዘብ ይገባልና፡፡” ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እግዚአብሔር ለፍጥረቱ በፍቅር ከሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ በቤተልሔም ለዓለም ስለሰጠው ስጦታ ሲናገሩ “የቤተልሔም ስጦታ ከስጦታዎች ሁሉ እጅግ በጣም የላቀ ነው፡፡ ምክንያቱም ሌሎች ስጦታዎች ከፍጥረቶቹ የሚገኙ የፍጥረት ውጤት ስጦታዎች ሲሆኑ የቤተልሔም ስጦታ ግን አንድ ልጁን ነውና” ብለዋል፡፡ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በማጠቃለያ መልእክታቸው “እግዚአብሔር እኛን ይህን ያህል ከወደደን እኛም እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል፤ ከልደተ ክርስቶስ የምንማረው ትምህርት ወገንን ሁሉ ማለትም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን የሰው ዘር ሁሉ መውደድና መርዳት ነው፡፡… ባለንበት ዘመን በተለያየ ምክንያት እናትና አባትን ያጡ፣ የወገንን ፍቅርና እንክብካቤ የሚሹ ብዙ የእግዚአብሔር ልጆች በየሠፈሩ አሉ፡፡ ለበዐል መዋያ ያዘጋጀነውን ኅብስተ በረከት ከተቸገሩት ሕፃናትና የሚላስ የሚቀመስ ካጡ ወገኖች ጋር በመሆን በኅብረት መመገብ ይገባናል፡፡ ይህን ስናደርግ በፍጹም ፍቅሩ የወደደንን እግዚአብሔርን በቤታችን ውስጥ እየጋበዝን እንደሆነ እርግጠኞች መሆን አለብን፡፡ “ተርቤ አብልታችሁኛልና ኑ ወደ እኔ” የሚል ቃል ኪዳን እንዳለበትም እናስታውስ፡፡” ብለዋል፡፡