abunehizkiel

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚመክር ታወቀ

ጥር 3 ቀን 2005 ዓ.ም.

 

abunehizkielየቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ጥር 6 ቀን 2005 ዓ.ም. የሚካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚመክር የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፣ የደቡብና ምዕራብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከትና የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በተለይ ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ገለጹ፡፡

 

ለዕርቀ ሰላሙ ድርድር ወደ አሜሪካ የተላኩት አባቶች ተልእኳቸውን ፈጽመው በሰላም ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ያስታወሱት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የተላኩት አባቶች በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ በመሆኑ እነዚሁ አባቶች በዕርቀ ሰላም ድርድር ወቅት የደረሱበትን የውሳኔ አሳብና ተያያዥ ጉዳዮች ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ጥር 6 ቀን 2005 ዓ.ም. በሪፓርት መልክ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡

 

ቅዱስ ሲኖዶስ ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ እንደሚሰጥና ለውጤታማነቱ እየሠራ መሆኑን የሚገልጹት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ዕርቀ ሰላሙ እንዲወርድ በራችንን ከፍተን እየጠበቅን ነው፡፡ በውጭ ያሉ አባቶችም ወደ አገራቸው በሰላም ገብተው ከእኛው ጋር አንድ ሆነው በፓትርያርክ ምርጫው በመራጭነትም ሆነ በተወዳዳሪነት ሊሳተፉ ይችላሉ ብለዋል፡፡

 

የፓትርያርክ ምርጫን ከዕርቀ ሰላሙ ጎን ለጎን ለማካሄድ የታሰበው ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለ አባት፣ ምእመኑም ያለ እረኛ ተበትነው እንዳይቀሩ እንደሆነ የሚገልጹት ብፁዕነታቸው እኛም ለመንጋችን እናስባለን እንራራለን፡፡ አንድነትም እናመጣለን፡፡ ምእመኑ ተለያይቶ እንዳይቀርና በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር እንዲሆን መለያየትን ለማስወገድ እንጥራለን ብለዋል፡፡

 

ዋናው ቁም ነገር ዕርቀ ሰላም ነው የሚሉት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ለስኬታማነቱ በሽምግልናው ሂደት የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች ተጨምረውበት የዕርቀ ሰላሙ ድርድር እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

 

ከዚሁ ጋር አያይዘው የፓትርያርክ ምርጫ ደንብ መጽደቁን የሚገልጹት ብፁዕነታቸው ሥልጣኑ የምልዐተ ጉባኤው ስለሆነ በተጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ዳግም ሊታይ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

 

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ 20ኛ ዓመት ቁጥር 8፣ 2005 ዓ.ም.