የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል አምስት  

በቴዎድሮስ እሸቱ

መጋቢት ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

፯. ኒቆዲሞስ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደኅና ናችሁ? መልካም! ይኸው ዘወረደ ብለን በመጀመሪያው ሳምንት የጀመርነው ጾም ዛሬ ኒቆዲሞስ ላይ ደርሷል፡፡ ኒቆዲሞስ የሰባተኛው ሳምንት መጠሪያ ነው፡፡ ልጆች! የአይሁድ መምህር የኾነ አንድ ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው ነበር፡፡ ይህ የአይሁድ መምህር ማታ ማታ እየመጣ ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግር ሥር ቁጭ ብሎ ትምህርት ይማር ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ማታ ማታ የሚማረው ለምን መሰላችሁ ልጆች?

አንደኛ የአይሁድ መምህር ስለ ኾነ አይሁድ ሲማር እንዳያዩት ነው፡፡ እነርሱ ሲማር ካዩት ገና ሳይማር ነው እንዴ እኛን የሚያስተምረን እንዳይሉት፤ ሁለተኛ አይሁድ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎችን ከአገራቸው ያባርሩ ስለ ነበር እንዳይባረር በመፍራቱ፤ ሦስተኛ ሌሊት ምንም የሚረብሽና ዐሳብን የሚሰርቅ ጫጫታ ስለሌለ ትምህርቱ እንዲገባው ነበር፡፡ እናንተስ በሌሊት ትምህርታችሁን የምታጠኑት እንዲገባችሁ አይደል ልጆች? በሌሊት ዐሳባችሁ አይበተንም፡፡

ታዲያ አንድ ቀን ማታ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔር መንግሥት ሊወርስ አይችልም›› ብሎ ለኒቆዲሞስ ስለ ጥምቀት አስተማረው፡፡ ኒቆዲሞስም ‹‹ሰው ከሸመገለ ካረጀ በኋላ እንዴት ድጋሜ ሊወለድ ይችላል?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ጌታችንም ዳግም ልደት ማለት ሰው በጥምቀት የሚያገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት እንደ ኾነ፣ ሰው ተጠምቆ የእግዚአብሔር ልጅ ካልኾነ መንግሥተ ሰማያትን እንደማይወርስ አስተማረው፡፡ ኒቆዲሞስም ስለ ጥምቀት በሚገባ ተረዳ፡፡

ልጆች! በዚህ ሳምንት ከሚነገረው ከዚህ ታሪክ ዅል ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል መማር እንዳለብን፤ ያልገባን ነገር ካለ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ጠይቀን መረዳት እንደሚገባን እንማራለን፡፡ እናንተም እንደ ኒቆዲሞስ ቃለ እግዚአብሔር በመማር እና ስለ እምነታችሁ ያልገባሁን በመጠየቅ በቂ ዕውቀት ልትቀስሙ ይገባችኋል፡፡ ልጆች! ለዛሬ በዚህ ይበቃናል፤ ደኅና ሰንብቱ፡፡

ገብር ኄር (ለሕፃናት)

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እንደምን ሰነበታችሁ የተወደዳችሁ ሕፃናት? መልካም! እስከ ዛሬ ድረስ የጠበቀን፣ ለወደፊትም የሚጠብቀን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ይመስገን! ልጆች! ስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹ገብር ኄር› የሚል ስያሜ አለው፡፡ ‹ገብር ኄር› ማለት ‹በጎ፣ ታማኝ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡

በዚህ ሳምንት ጸጋን (ተሰጥዎን) በአግባቡ ስለ መጠቀም እና ስለ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያስተምር ቃለ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ይነገራል፡፡ በተጨማሪም ስለ ‹ገብር ሐካይ› ጠባይ የሚያስረዳ ትምህርት ይቀርባል፡፡ ‹ገብር ሐካይ› ማለት ‹ሰነፍ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡ የእነዚህን ሰዎች ታሪክም በአጭሩ እናስታውሳችኋለን፤ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፭ ከቍጥር ፲፬ ጀምሮ እንደ ተጻፈው አንድ ሰው አገልጋዮቹን ጠራና ለአንዱ አምስት፤ ለአንዱ ሁለት፤ ለአንዱ ደግሞ አንድ መክሊት ሰጣቸው፡፡ ልጆች! ‹መክሊት› – ብር፣ ዶላር፣ እንደሚባለው ያለ የገንዘብ ዓይነት ነው፡፡

አምስት መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ነግዶ፣ ሌላ አምስት መክሊት አትርፎ ዐሥር አድርጎ ለጌታው አቀረበ፡፡ ጌታውም፡- ‹‹አንተ ጎበዝ እና ታማኝ አገልጋይ! በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለውም አትርፎ አራት አድርጎ አቀረበ፡፡ እርሱንም ጌታው፡- ‹‹አንተ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡ እርሱ ግን መክሊቱን ቀብሮ አቆየና ጌታው እንዲያስረክብ በጠየቀው ጊዜ፡- ‹‹እነሆ መክሊትህ!›› ብሎ ምንም ሳያተርፍበት መለሰለት፡፡ ጌታውም፡- ‹‹ይህን ክፉና ሰነፍ አገልጋይ እጅ እግሩን አስራችሁ ጨለማና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ሥፍራ ውሰዱት! መክሊቱን ቀሙና ለባለ ዐሥሩ ጨምሩለት!›› ብሎ አዘዘ፡፡ ‹ገብር ሐካይ› የተባለው ይህ መክሊቱን የቀበረው አገልጋይ ነው፡፡

ልጆች! ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠንን ጸጋ በአግባቡ ከተጠቀምን ትልቅ ዋጋ እንደምናገኝ፤ ጸጋችንን በአግባቡ ካልተጠቀምን ደግሞ ቅጣት እንደምንቀበል ከዚህ ታሪክ እንማራለን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለእናንተም ስታድጉ በመንፈሳዊው ሕይወታችሁ የጵጵስና፣ የቅስና፣ የዲቁና፣ የሰባኪነት፣ የዘማሪነት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ጸጋዎችን እንደየአቅማችሁ ይሰጣችኋል፡፡ በዓለማዊው ሕይወታችሁ ደግሞ የፓይለትነት፣ የመሐንዲስነት፣ የዶክተርነት፣ የመምህርነት፣ የመንግሥት ሠራተኛነት፣ ወዘተ. ሌላም ዓይነት የሥራ ጸጋ ያድላችኋል፡፡

መንፈሳዊውን ወይም ዓለማዊውን ትምህርታችሁን በርትታችሁ በመማር ካጠናቀቃችሁ በኋላ ከእናንተ ብዙ ሥራ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ልጆች! በምድር ሕይወታችሁ እንዲባረክ፤ በሰማይም የእግዚአብሔርን መንግሥት እንድትወርሱ እንደ ገብር ኄር የተሰጣችሁን ጸጋ በመጠቀም ቤተሰባችሁን፣ አገራችሁንና ቤተ ክርስቲያናችሁን በቅንነት ማገልገል አለባችሁ፡፡ በጣም ጥሩ ልጆች! ለዛሬው በዚህ ይበቃናል፤ በሌላ ዝግጅት እስከምንገናኝ ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይኹን! ሳምንቱ መልካም የትምህርት ጊዜ ይኹንላችሁ!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል አራት

፮. ገብር ኄር

በልደት አስፋው

መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፱ .

ሰላም ናችሁ ልጆች? ባለፈው ዝግጅት ስለ ደብረ ዘይት ተምረናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ስለ ‹ገብር ኄር› እንማራለን፡፡ ስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት (እሑድ) ‹ገብር ኄር› ይባላል፡፡ ትርጕሙ ‹ታማኝ፣ በጎ፣ ደግ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡ ልጆች! አንድ ባለጠጋ አገልጋዮቹ ነግደው እንዲያተርፉበት ለአንዱ አምስት፤ ለሁለተኛው ሁለት፤ ለሦስተኛው አንድ መክሊት ሰጣቸው፡፡ ልጆች! ‹መክሊት› የገንዘብ ስም ነው፡፡

ከዚያ በኋላ አምስት እና ሁለት መክሊት የተቀበሉት ሁለቱ አገልጋዮች በተሰጣቸው መክሊት ነግደው እጥፍ አትርፈው ለባለ ጌታው አስረከቡ፡፡ ስለዚህም ገብር ኄር (ታማኝ አገልጋይ) ተብለው ተመሰገኑ፤ ልዩ ክብርን አገኙ፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ግን የተቀበለውን መክሊት ቀብሮ ካቆየ በኋላ ምንም ሳያተርፍበት ለጌታው አስረከበ፡፡ ይህ አገልጋይ ‹ገብር ሐካይ› ይባላል፡፡ ‹ሰነፍ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡ በመክሊቱ ባለማትረፉ የተነሣ ቅጣት ተፈርዶበታል፡፡

የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፭ ቍጥር ፲፬-፵፮ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ብታነቡት ሙሉ ታሪኩን ታገኙታላችሁ፡፡ ልጆች! ስድስተኛው የዐቢይ ጾም እሑድ ስለ እነዚህ አገልጋዮች እና ስለ መንፈሳዊ አገልግሎት ጥቅም ትምህርት የሚቀርብት ሳምንት በመኾኑ ‹ገብር ኄር› ተብሏል፡፡ እናንተም በተሰጣችሁ ጸጋ ብዙ ምግባር መሥራት አለባችሁ እሺ? መልካም ልጆች! ለዛሬው በዚህ ይበቃናል፡፡ በቀጣይ ደግሞ ስለ ኒቆዲሞስ እንማማራለን፡፡ ሰላመ እግዚአብሔር ከዅላችን ጋር ይኹን!

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል ሦስት

በልደት አስፋው

መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

፭. ደብረ ዘይት

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ስለዅሉም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን! ባለፈው ዝግጅታችን አራተኛውን የዐቢይ ጾም ሳምንት የተመለከተ ትምህርት አቅርበንላችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ስለ አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት (ስለ ደብረ ዘይት) አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን በተግባር ላይ እንድታውሉት እሺ? መልካም ልጆች! አሁን በቀጥታ ወደ ትምህርቱ እንወስዳችኋለን፤

ልጆች! እንደምታስታውሱት አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ደብረ ዘይት›› ይባላል፡፡ ትርጕሙም ‹‹የወይራ ተክል የሚገኝበት ተራራ›› ማለት ነው፡፡ ይህ ትልቅ ተራራ (ደብረ ዘይት) ከኢየሩሳሌም ከተማ በስተምሥራቅ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ ደብረ ዘይት ተራራ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዕለተ ምጽአትን ምልክት ለደቀ መዛሙርቱ (ለሐዋርያት) የገለጸበትና ያስተማረበት ቦታ ነው፡፡ ጌታችን በዚህ በደብረ ዘይት ተራራ ተቀመጦ ‹‹ማንም እንዳያስታችሁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፡፡ እስከ መጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል …›› እያለ ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯቸዋል፡፡

እነርሱም ስለ ዕለተ ምጽአት ምልክትና የመምጫው ጊዜ መቼ እንደሚኾን ጌታችንን ጠይቀውታል፡፡ እርሱም ቀኑን ከእርሱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም እንደማያውቀውና ክርስቲያኖች ከኀጢአት ርቀው በዝግጅት መጠባበቅ እንደሚገባቸው አስረድቷቸዋል፡፡ ልጆች! ዓለም የምታልፍበት ቀን ሲደርስ (በዕለተ ምጽአት) ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመላእከት ዝማሬ፣ በመለከት ድምፅ ታጅቦ በኃይልና በግርማ ከሰማይ ወደ ምድር ይመጣል፡፡

አምላካችን በመጣ ጊዜም በተዋሕዶ ሃይማኖትና በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንቶ የተገኘ ክርስቲያን በገነት (መንግሥተ ሰማያት) ለዘለዓለሙ በደስታ ይኖራል፡፡ ያለ ክርስቲያናዊ ምግባር ማለትም በኀጢአት ሥራ የኖረ ሰው ደግሞ ለዘለዓለሙ መከራና ስቃይ ወዳለበት ወደ ሲኦል (ገሃነመ እሳት) ይጣላል፡፡ ስለዚህ አምላካችን ለፍርድ ሲመጣ ለእያንዳንዳችን እንደ ሥራችን ኹኔታ ዋጋ ይሰጠናል ማለት ነው፡፡ የጽድቅ ሥራ ስንሠራ ከኖርን ወደ መንግሥተ ሰማያት (የጻድቃን መኖሪያ) እንገባለን፤ ኀጢአት ስንሠራ ከኖርን ግን ወደ ገሃነመ እሳት (የኀጢአተኞች መኖሪያ) እንጣላለን፡፡

ልጆች! እናንተም በዕለተ ምጽአት ወደ መንግሥተ ሰማያት እንድትገቡ በምድር ስትኖሩ ከክፉ ሥራ ማለትም ከስድብ፣ ከቍጣ፣ ከተንኮል፣ ከትዕቢት እና ከመሳሰለው ኀጢአት ርቃችሁ በእውነት፣ በትሕትና፣ ሰውን በማክበር፣ በፍቅር እና በመሳሰለው የጽድቅ ሥራ ጸንታችሁ ለወላጆቻችሁ እየታዘዛችሁ ኑሩ፡፡ ይህንን ለማድረግ እንድትችሉ ደግሞ ከዘመናዊው ትምህርታችሁ ጎን ለጎን ከወላጆቻችሁ ጋር እየተመካከራችሁ (አስፈቅዳችሁ) መንፈሳዊ ትምህርት መማር፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ መንፈሳውያን ፊልሞችን መመልከትና መዝሙራትን ማዳመጥ፣ እንደዚሁም በየጊዜው መቍረብ አለባችሁ እሺ?

በጣም ጥሩ ልጆች! ለዛሬው ከዚህ ላይ ይቆየን፡፡ በሚቀጥለው ዝግጅት ስለሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ትምህርት ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከኹላችን ጋር ይኹን!

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል ሁለት  

በልደት አስፋው

መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ባለፈው ዝግጅታችን ከመጀመሪያው እሑድ እስከ ሦስተኛው እሑድ (ከዘወረደ ጀምሮ እስከ ምኵራብ) ድረስ የሚገኙትን የዐቢይ ጾም ሳምንታት የሚመለከት ትምህርት አቅርበንላችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ አራተኛውን የዐቢይ ጾም ሳምንት (መጻጕዕን) የሚመለከት ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ!

፬. መጻጕዕ

ልጆች! አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹መጻጕዕ›› ይባላል፡፡ መጻጕዕ ማለት በሽተኛ ማለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በበሽታ ተይዞ የነበረውን ሰው የፈወሰበት ዕለት ነው /ዮሐ.፭.፩-፱/፡፡

ልጆች! ቤተሳይዳ የምትባል አንዲት የጠበል መጠመቂያ ሥፍራ ነበረች፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደዚያች መጠመቂያ ሥፍራ እየመጣ ውኃውን ከባረከው በኋላ ቀድሞ ገብቶ የተጠመቀ በሽተኛ ካለበት ከማንኛውም ደዌ (በሽታ) ይፈወስ ነበር፡፡ በዚያ ሥፍራ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ከበሽታው ለመፈወስ ብሎ ሲጠባበቅ የነበረ አንድ መጻጕዕ (በሽተኛ) ነበር፡፡ ውኃው በተናወጠ ጊዜ ሌሎች ቀድመው ገብተው እየተፈወሱ ሲሔዱ እሱ ግን ለሰላሣ ስምንት ዓመት በዚያ ቆየ፡፡

ከዚያ በኋላ ጌታችን በዚያ ሥፍራ ሲያልፍ ይህንን መጻጕዕ ተኝቶ አየው፡፡ በዚህ ጊዜ ለብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› ብሎ ከጠየቀው በኋላ እምነቱንና ጽናቱን አይቶ ‹‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› አለው፡፡ በጌታችን ቃል ሰውዬው ወዲያውኑ ከበሽታው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ የእግዚአብሔርን ቸርነት እየመሰከረ ሔደ፡፡ በአጠቃላይ አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት የመጻጕዕ ታሪክ የሚነገርበት፤ እንደዚሁም የአምላካችን ቸርነቱ፣ ይቅርታው፣ መሐሪነቱ የሚታወስበት ዕለት ነው፡፡

ልጆች! ደብረ ዘይትን የሚመለከት ትምህርት ደግሞ በሌላ ቀን እናቀርብላችኋለን፡፡ ለዛሬው ከዚህ ላይ ይቆየን፡፡ እስከዚያው ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከዅላችሁ ጋር ይኹን!

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል አንድ

በልደት አስፋው

የካቲት ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደኅና ናችሁ? እግዚአብሔር ይመስገን!፡፡ ልጆች! በልዩ ልዩ ምክንያት አልችል ብለን ዘግይተናል፡፡ በቅድሚያ በገባነው ቃል መሠረት ወቅቱን ጠብቀን ትምህርቱን ባለማቅረባችን እናንተን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

ልጆች! የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ባቀረብንላችሁ ትምህርት ከሰባቱ አጽዋማት መካከል ዐቢይ ጾም አንዱ እንደኾነ፣ ዐቢይ ጾም ማለት ታላቅ ጾም ማለት እንደኾነ፣ ጾሙ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም በመኾኑ ታላቅ እንደተባለ፣ ዕድሜአቸው ሰባት ዓመት ከኾናቸው ሕፃናት ጀምሮ ዅሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዐቢይ ጾምን እና ሌሎችንም አጽዋማት መጾም እንደሚገባቸው፣ እንደዚሁም ስምንቱ የዐቢይ ጾም ሳምንታት (እሑዶች) ስማቸው ማን ማን እንደሚባል ነግረናችሁ ነበር፡፡

ልጆች! ሰባቱ አጽዋማት ማን ማን እንደሚባሉም ጠይቀናችሁ ነበር አይደል? መልሱንስ ጠይቃችሁ ተረዳችሁ? በጣም ጥሩ ልጆች! መልሱን እናስታውሳችሁ፤ ሰባቱ አጽዋማት የሚባሉት፡-

፩. ጾመ ነቢያት

፪. ጾመ ገሃድ (ጋድ)

፫. ጾመ ነነዌ

፬. ዐቢይ ጾም

፭. ጾመ ድኅነት (ረቡዕ እና ዓርብ)

፮. ጾመ ሐዋርያት

፯. ጾመ ፍልሰታ (የእመቤታችን ጾም) ናቸው፡፡

በአሁኑ ሰዓት ዐቢይ ጾምን እየጾምን ነው፡፡ የምንገኘውም ሦስተኛው ሳምንት ላይ ሲኾን ስሙም ‹‹ምኵራብ›› ይባላል፡፡ የሚቀጥለውና አራተኛው ሳምንት ደግሞ ‹‹መጻጕዕ›› ተብሎ ይጠራል፡፡

ልጆች! በዛሬው ዝግጅታችን ከመጀመሪያው እሑድ እስከ ሦስተኛው እሑድ (ከዘወረደ ጀምሮ እስከ ምኵራብ) ድረስ የሚገኙትን የዐቢይ ጾም ሳምንታት የሚመለከት ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን እንድከታተሉት በአክብሮት ጋብዘናችኋል!

፩. ዘወረደ

ልጆች! ከዐቢይ ጾም ሳምንታት መካከል የመጀመሪያው ሳምንት ‹‹ዘወረደ›› ይባላል፡፡ ዘወረደ ማለት ከላይ የመጣ፣ የወረደ ማለት ነው፡፡ ይህም አምላካችን ዓለምን ለማዳን ሲል ሥጋ መልበሱን (ሰው መኾኑን) ያመለክታል፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወርዶ፣ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ፣ ወንጌልን ለዓለም ካስተማረ በኋላ በፈቃዱ መከራ ተቀብሎ፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ከሙታን ተነሥቶ ዓለምን አድኗል፡፡ ልጆች! የመጀመሪያው ሳምንት የአምላካችን የማዳን ሥራ በስፋት የሚነገርበት ወቅት በመኾኑ ‹‹ዘወረደ›› ተብሎ ተሰይሟል፡፡

፪. ቅድስት

ሁለተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ቅድስት›› ይባላል፡፡ ቅድስት ማለት የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች ማለት ነው፡፡ ልጆች! ለምን የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች እንደተባለች ታውቃላችሁ? ቅዱስ አምላካችን እግዚአብሔር ዓለምን (ሰውን) ለመቀደስ ሲል ወደ ምድር መምጣቱንና ዐቢይ ጾምን መጾሙን ለማስረዳት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሰንበትን ክብር ለማስገንዘብ ነው፡፡ ሰንበት ቅድስት፣ የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች ዕለት ናት፡፡ ስለዚህም ልጆች! ሁለተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ቅድስት›› ተብሎ ይጠራል፡፡

፫. ምኵራብ

ልጆች! ሦስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ደግሞ ‹‹ምኵራብ›› ይባላል፡፡ ምኵራብ ማለት አዳራሽ ማለት ነው፡፡ ምኵራብ ድሮ የነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎች መንፈሳዊ ትምህርት ይማሩበት የነበረ  ሥፍራ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ይህንን የጸሎት ሥፍራ ሰዎች የንግድ ቦታ አደረጉት፡፡ ይህንን ዓለማዊ ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩትን ዅሉ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፡፡ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት›› ብሎ ከምኵራብ አስወጣቸው፡፡ ከዚያም ቃለ እግዚአብሔር አስተማራቸው፡፡ ልጆች! የእግዚአብሔር ቤት የጸሎት ቤት እንጂ የንግድ መነገጃ ሥፍራ አለመኾኑን ከዚህ ታሪክ እንማራለን፡፡

ለዛሬው በዚህ ይቆየን፡፡ ቀጣዩን ትምህርት ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሚቀጥለው ዝግጅት ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከዅላችን ጋር ይኹን!

ዐቢይ ጾም

በልደት አስፋው

የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፱ .

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ባለፈው ሳምንት ስለ ነቢዩ ዮናስ እና ስለ ነነዌ ሰዎች የጻፍንላችሁን ታሪክ አነበባችሁት? ጎበዞች፡፡ ከታሪኩ ውስጥ ያልገባችሁ ትምህርት ካለ ከቤተ ክርስቲያን መምህራን በመጠየቅ መረዳት ትችላላችሁ፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ ስለ ዐቢይ ጾም አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

ልጆች! ‹‹ዐቢይ ጾም›› ማለት ታላቅ ጾም ማለት ነው፡፡ ዐቢይ ጾም በቤተ ክርስቲያናችን በዐዋጅ እንዲጾሙ ከታወጁ ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ ጾሙ ታላቅ የተባለበት ምክንያትም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም በመኾኑ ነው፡፡

ልጆች! ይኽንን ጾም ዕድሜአቸው ሰባት ዓመት ከኾናቸው ሕፃናት ጀምሮ ዅሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች እንዲጾሙት የቤተ ክርስቲያናችን ሕግ ያዝዛል፡፡ እንዴት ነው ታዲያ ሰባት ዓመትና ከዚያ በላይ የኾናችሁ ሕፃናት አጽዋማትን እየጾማችሁ ነው አይደል? እየጾማችሁ ከኾነ በጣም ጎበዞች ናችሁ ማለት ነው፤ በዚሁ ቀጥሉ፡፡

ዕድሜአችሁ ለመጾም ደርሶ መጾም ያልጀመራችሁ ካላችሁ ደግሞ ከቤተሰቦቻችሁ ጋር ተመካክራችሁ እስከምትችሉበት ሰዓት ድረስ በመጾም ጾምን ከልጅነታችሁ ጀምራችሁ ተለማመዱ፤ የጾሙ ተሳታፊዎችም ኹኑ እሺ? በሕመም ምክንያት መድኀኒት የምትወስዱ ከኾነ ግን መድኀኒታችሁን ስትጨርሱ ትጾማላችሁ፡፡

ልጆች! የዘንድሮው (የ፳፻፱ ዓ.ም) ዐቢይ ጾም የሚጀመረው መቼ እንደ ኾነ ታውቃላችሁ? የካቲት ፲፫ ቀን ነው፡፡ የሚፈታው ማለትም የሚፈሰከው ደግሞ ከአምሳ አምስት ቀናት በኋላ ሚያዝያ ፰ ቀን ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓመት የፋሲካ በዓል ሚያዝያ ፰ ቀን ይውላል ማለት ነው፡፡

በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚገኙት አምሳ አምስቱ ቀናት በስምንት ሳምንታት (እሑዶች) የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ የእያንዳንዱ ሳምንት ወይም እሑድ መጠሪያ ስሞችም የሚከተሉት ናቸው፤

የመጀመሪያው ሳምንት (እሑድ) – ዘወረደ

ሁለተኛው ሳምንት (እሑድ) – ቅድስት

ሦስተኛው ሳምንት (እሑድ) – ምኵራብ

አራተኛው ሳምንት (እሑድ) – መጻጕዕ

አምስተኛው ሳምንት (እሑድ) – ደብረ ዘይት

ስድስተኛው ሳምንት (እሑድ) – ገብር ኄር

ሰባተኛው ሳምንት (እሑድ) – ኒቆዲሞስ

ስምንተኛው ሳምንት (እሑድ) – ሆሣዕና

ተብለው ይጠራሉ፡፡

የፋሲካ በዓል የሚከበርበት የመጨረሻው የዐቢይ ጾም እሑድ ደግሞ ትንሣኤ ወይም ፋሲካ ይባላል፡፡

ልጆች! እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ እነዚህን ሳምንታት (እሑዶች) የሚመለከት ትምህርት በየሳምንቱ እናቀርብላችኋለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ከቤተ ክርስቲያን መምህራን ወይም ደግሞ ከወላጆቻችሁ ጠይቃችሁ ሰባቱ አጽዋማት የሚባሉት ማን ማን እንደ ኾኑ አጥንታችሁ ጠብቁን እሺ?

በሉ እንግዲህ ልጆች በሌላ ዝግጅት እስከምንገናኝ ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይኹን፡፡

ይቆየን

ነቢዩ ዮናስ ክፍል ሁለት

በልደት አስፋው

የካቲት ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም  

እንዴት ናችሁ ልጆች? እኛ እግዚአብሔር ይመስገን በጣም ደኅና ነን፡፡ በትናንትናው ዝግጅታችን እግዚአብሔር አምላካችን ነቢዩ ዮናስን አስተምር ብሎ ወደ ነነዌ ሰዎች እንደ ላከው፣ እርሱ ግን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ላለመቀበል በመርከብ ተሳፍሮ ወደ ሌላ አገር እንደ ሸሸ፣ በነቢዩ ዮናስ ምክንያትም መርከቡ እስኪሰጥም ድረስ ባሕሩ በማዕበል እንደ ተናወጠ፣ በዚህ የተነሣም ተሳፋሪዎቹ ዕጣ ተጣጥለው ነቢዩ ዮናስን ወደ ባሕሩ እንደ ጣሉት ነግረናችሁ ነበር፡፡ ልጆች! ቀጣዩን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፤

እናም ሰዎቹ ነቢዩ ዮናስን ወደ ባሕር ሲጥሉት እግዚአብሔር ያዘጋጀው ታላቅ ዓሣ ዋጠው፡፡ ነቢዩ ዮናስም በዓሣው ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ቆየ፡፡ በዚያ ጨለማ በኾነ የዓሣ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀን መቆየት አያስፈራም ልጆች? በጣም ነው የሚያስፈራው፡፡ ነቢዩ ዮናስም እግዚአብሔር እንዲያወጣው በዓሣው ሆድ ውስጥ ኾኖ አብዝቶ ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም የነቢዩ ዮናስን ጸሎት ሰምቶ ዓሣውን እንዲተፋው አዘዘው፡፡ ዓሣውም ነቢዩ ዮናስን በየብስ (በደረቅ መሬት) ላይ ተፋው፡፡ ነቢዩ ዮናስም ‹‹ይህቺ አገር ማን ትባላለች?›› ብሎ የአካባቢው ነዋሪዎችን ሲጠይቅ አገሪቱ ነነዌ እንደ ኾነች ነገሩት፡፡ ይገርማችኋል ልጆች! ከዚህ በኋላ ነቢዩ ዮናስ የእግዚአብሔርን ቃል እሺ ብሎ ተቀብሎ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ገብቶ ‹‹በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለባበጣለች (ትጠፋለች)›› ብሎ አስተማረ፡፡

የነነዌ ሰዎችም ቃሉን ሰምተው ከኀጢአታቸው ተመልሰው፣ ማቅ ለብሰው ንስሐ ገቡ፡፡ ከከንጉሡ ጀምሮ ሕፃናትም ጭምር፣ እንስሳትም ሳይቀሩ ምንም ምግብ ሳይቀምሱ፣ ውኀም ሳይጠጡ ለሦስት ቀን ጾሙ፡፡ እንዲምራቸውም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፡፡ እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው መመለሳቸውንና ንስሐ መግባታቸውን አይቶ ይቅር አላቸው፤ ነነዌንም ከጥፋት አዳናት፡፡ ልጆች ነቢዩ ዮናስ እግዚአብሔርን አልታዘዝም ያለው ለምን መሰላችሁ? እኔ ነነዌ ትገለባበጣለች (ትጠፋለች) ብዬ ባስተምር ሕዝቡ ተጸጽቶ ይቅርታ ቢጠይቁ እግዚአብሔር ይቅር ሲላቸው እኔ ውሸታም ነቢይ እባላለሁ ብሎ ፈርቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የነነዌ ሰዎች ነቢዩ ዮናስንም ውሸታም ነው አላሉትም፡፡ ትምህርቱን ተቀብለው ከጥፋት በመዳናቸው እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡ እግዚአብሔር ምን ያህል ሩኅሩኅና ቸር እንደኾነ አያችሁ ልጆች? ምንም እንኳን እኛ ብንበድለውም፣ ብናሳዝነውም ተጸጽተን ንስሐ ከገባን የቀደመውን በደላችንን ደምስሶ ኀጢአታቻንን ይቅር ይለናል፡፡

ልጆች ነነዌ ከመቶ ሃያ ሺሕ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሳት የሚኖሩባት ታላቅ ከተማ ነበረች፡፡ እነኚህ ዅሉ ሰዎች ንስሐ ባይገቡ ኖሮ ነነዌን እሳት ይበላት ነበር፡፡ የነነዌ ሰዎች ከበደላቸው ተጸጽተው፣ ንስሐ ገብተው በመጾማቸውና በመጸለያቸው እግዚአብሔር ከጥፋት አድኗቸዋል፡፡ ልጆች! እኛም ዛሬ እግዚአብሔርን ብንበድለውና እርሱ የማይወደውን ክፋት ብንፈጽም እንደ ነነዌ ሰዎች ተጽጽተን ንስሐ ከገባን አምላካችን ቸር፣ ታጋሽ እና ይቅር ባይ አምላክ ስለኾነ ኀጢአታችንን ይቅር ብሎ ከጥፋት ያድነናል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች በየዓመቱ ጾመ ነነዌን የምንጾመውም እግዚአብሔር ኀጢአታቻንን ይቅር እንዲለን ነው፡፡ በሉ እንግዲህ ልጆች በሌላ ጊዜ በሌላ ታሪክ እስከምንገናኝ በደኅና ቆዩ፡፡ ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይኹን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ነቢዩ ዮናስ ክፍል አንድ

እንደምን አላችሁ ልጆች? ከአሁን በፊት ለእናንተ የሚኾኑ ትምህርታዊ ጽሑፎችን በድረ ገጻችን ስናቀርብላችሁ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በልዩ ልዩ ምክንያት ዝግጅቱን አቋርጠን ቆይተናል፡፡ ለዚህም እናንተን ይቅርታ እየጠቅን ከዛሬ ጀምሮ ወቅታዊ ይዘት ያሏቸውን ትምህርታዊ ጽሑፎች በየጊዜው እንደምናቀርብላችሁ ቃል እንገባለን፡፡ በዛሬው ዝግጅታችንም የነቢዩ ዮናስንና የነነዌ ሰዎችን ታሪክ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ መልካም የንባብ ጊዜ ይኹንላችሁ!

ነቢዩ ዮናስ ክፍል አንድ

በልደት አስፋው

የካቲት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ልጆች! እግዚአብሔር ለሕዝቡ መልእክት ለማስተላለፍ ሲፈልግ ወደ ሕዝቡ ከሚልካቸው ነቢያት መከካል አንዱ ነቢዩ ዮናስ ነው፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ምን ኾነ መሰላችሁ ልጆች፣ ወደ አንዲት ታላቅ ከተማ ሔዶ እንዲሰብክ የእግዚአብሔር ቃል ለነቢዩ ዮናስ መጣለት፡፡ ልጆች ይህች ታላቅ ከተማ ነነዌ ትባላለች፡፡ በዚህች በነነዌ ከተማ የሚኖሩ ሰዎች ኀጢአታቸው እጅግ በዝቶ ነበር፡፡ ርኅሩኁ አምላካችን እግዚአብሔር የሰውን መዳን እንጂ ጥፋቱን ስለማይፈልግ ንስሐ ግቡ ብሎ እንዲያስተምራቸው ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ላከው፡፡ ነቢዩ ዮናስ ግን የፈጣሪውን ትእዛዝ ላለመፈጸም ሊኮበልል አሰበ፡፡ ከዚያም ተርሴስ ወደምትባል አገር የምታልፍ መርከብ አግኝቶ በእርሷ ተሳፈረ፡፡ ልጆች ከእግዚአብሔር ፊት መኮብለል ወይም መሸሽ ይቻላል? አይቻልም አይደል? እስቲ ነቢዩ ዮናስ የተሳፈረባት መርከብ ምን እንደ ገጠማት እንመልከት፤

ነቢዩ ዮናስ በመርከብ ተሳፍሮ ሲሔድም እግዚአብሔር ታላቅ ነፋስን አምጥቶ በባሕሩ ላይ ታላቅ ማዕበልን አስነሣ፡፡ በዚህ ጊዜ መርከቢቱ ልትሰበር ደረሰች፡፡ ለምን እንደዚህ እንደኾነ አወቃችሁ ልጆች? ነቢዩ ዮናስ ከእግዚአብሔር ፊት ለመሸሽ በማሰቡ ነው፡፡ መርከቢቷ ውስጥ ያሉ ሰዎችም እጅግ ፈሩ፡፡ መርከቧ ክብደት ስለበዛባት ነው ብለው አስበው በውስጧ የነበረውን ዕቃ ዅሉ ወደ ባሕር ቢጥሉትም መርከቢቱ ግን ልትረጋጋ አልቻለችም ነበር፡፡ ማዕበሉም አልቆም አለ፡፡ ልጆች ይህ ዅሉ ሲኾን ግን ነቢዩ ዮናስ ተኝቶ ነበር፡፡ ከዚያም የመርከቡ አለቃ ወደ እርሱ ቀረበና ‹‹ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደኾነ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ›› አለው፡፡ በመርከቡ ውስጥ ያሉት ሰዎችም ‹‹ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እናውቅ ዘንድ ኑ ዕጣ እንጣጣል›› ተባብለው ዕጣ ሲጣጣሉ ዕጣው በነቢዩ ዮናስ ላይ ወጣ፡፡ ሰዎቹም ነቢዩ ዮናስን ‹‹ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እባክህ ንገረን?›› አሉት፡፡

ነቢዩ ዮናስም ከእግዚአብሔር ፊት መኮብለሉን በነገራቸው ጊዜ ሰዎቹ በፍርኀት ኾነው ‹‹ይህ ያደረግኸው ምንድን ነው?›› አሉት፡፡ ባሕሩንም ሞገዱ እጅግ ያናውጠው ነበርና ‹‹ባሕሩ ጸጥ እንዲል ምን እናድርግብህ?›› ሲሉ ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹‹ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃለሁ፡፡ አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፡፡ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል፤›› አላቸው (ትንቢተ ዮናስ ፩፥፩-፲፫)፡፡ ሰዎቹም ነቢዩ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ በዚህ ጊዜ ባሕሩ ከመናወጥ ጸጥ አለ፡፡ ልጆች! ባሕሩ ሲናወጥ የነበረው ለምን እንደኾነ ተረዳችሁ? ዮናስ እግዚአብሔር ያዘዘውን ትቶ ለመሸሽ በመርከቡ በመሳፈሩ ነው! እግዚአብሔርን ሳንታዘዝ ያሰብንበት ቦታ መድረስ የምንችል ይመስላችኋል ልጆች? አንችልም አይደል? አዎ፤ አንችልም፡፡ ምክንያቱም ዓለሙን ዅሉ የፈጠረ እግዚአብሔር ነውና በባሕርም ኾነ በየብስ (በደረቅ መሬት) ብንጓዝ ከእርሱ መሰወር ፈጽሞ አይቻለንም፡፡ እግዚአብሔር የሌለበት ቦታና ከእርሱ እይታ የተሰወረ ምንም ነገር የለምና፡፡

ልጆች! ቀጣዩን ክፍል ነገ ይዘንላችሁ እንቀርባለን እሺ? ለዛሬው ከዚህ ላይ ይቆየን፡፡

ጰራቅሊጦስ (ለሕፃናት)

ሰኔ 14 ቀን 2005 ዓ.ም.

በቤካ ፋንታ

 

  • እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት/ መዝ 118፥24/

ይህች ታላቅ ዕለት  ከቅድስት ሥላሴ አንዱ አካል የሆነው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለቅዱሳን ሐዋርያት፣ ለቅዱሳን አርድእትና ለቅዱሳት ሴቶች የተገለጠባት ዕለት ናት፡፡    እነዚህ ሁሉ በጸሎት ተግተው በሚጸልዩበት ወራት መንፈስ ቅዱስ  በተከፋፈሉ የእሳት ልሳን አምሳል የወረደበት ቅዱስ ቀን ነው፡፡

አስቀድሞ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት ደብረ ዘይት በተባለ ታላቅ ተራራ ላይ ሳሉ እንዲህ ብሎ አስተምሯቸው ነበር “ኀይልን ከላይ ከአርያም እስክልክላችሁ ድረስ በኢየሩሳሌም በጸሎት ቆዩ፡፡”/ሉቃ 24፡36/ መቶ ሃያው ቤተሰብም በኢየሩሳሌም ሀገር በምትገኝ በቤተ መቅደስ በአንድነት ሆነው በጸሎት በመትጋት ቆዩ፡፡ ልጆችዬ መቶ ሃያው ቤተሰብ የሚባሉት 12ቱ ሐዋርያት፣ 72ቱ አርድእት/አገልጋዮች/ እና 36ቱ ቅዱሳን አንስት/ሴቶች/ ናቸው፡፡

ከዕርገት በኋላ በአሥረኛው ቀን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያት ወዳሉበት፣ በጸሎትና በምሥጋና ወደ ሚተጉበት ሥፍራ በእሳት አምሳል /ምሳሌ/ ወርዶ በእያንዳንዳቸው ላይ ተቀመጠባቸው፡፡ ይሄንንም  ሁኔታ ተከትሎ  ምስጢር ተገለጠላቸው፣ ይፈሩ የነበሩት ሐዋርያትም ወንጌልን ለማስተማር ደፋሮች ሆኑ፣ በተለያየ ቋንቋዎች እንዲናገሩ እውቀት ተሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ ተቀበሉ፡፡ ይህንን ታላቅ ኀይል እና ሰማያዊ ስጦታን የሰጣቸውን እግዚአብሔርን በታላቅ ዝማሬና እልልታ አመሰገኑት፡፡

በዓለ ሃምሳ የሚባለውን የአይሁድን በዓል ለማክበር ከተለያዩ ሀገራት የመጡ በጊዜው  የነበሩ ቁጥራቸው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ  ሰዎች የሐዋርያቱን ታላቅ የዝማሬና የእልልታ ድምፅ ሰሙ፡፡ ከመቶ ሃያው ቤተሰብ መካከል አንዱ የሆነው  ቅዱስ ጴጥሮስ የተሰበሰቡት ሁሉም እንዲሰሙት ድምፁን ከፍ አድርጎ ቃለ እግዚአብሔርን እንዲህ ብሎ አስተማራቸው፡፡ “እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ እኛን የሰው ልጆችን ለማዳን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጥቶ ከክፉ ሥራ ተመለሱ፣ ኀጢአትን አታድርጉ፣ በቅድስና ኑሩ፣ ወደ እኔም ተመለሱ ቢላችሁ፤ እናንተ ግን ምንም በደል ሳይኖርበት ገረፋችሁት፣ አንገላታችሁት፣ በመስቀል ላይም ሰቀላችሁት፡፡ እርሱ ግን እግዚአብሔር ነውና ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ እርሱ ግን አሁንም ይቅር ባይ ነውና ከኀጢአታችሁ ተመለሱ ንስሐም ግቡ ፡፡” በማለት አስተማራቸው፡፡

የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ተገረሙ፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያት በፊት የሚያውቁት አንድ ቋንቋ ብቻ ነበረ፡፡ በዚህ ሰዓት ግን ሰባ ሁለት ቋንቋን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ገልጦላቸው ለሁሉም በየቋንቋቸው አስተማሯቸው፡፡ ይህንንም ድንቅ ተአምር ከተመለከቱት ብዙዎች እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ ወደ ሐዋርያትም ቀርበው “አባቶቻችን እናንተ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናችሁና ምከሩን፡፡ እንደ እናንተ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆንና በቅድስና እንድንኖር ምን እናድርግ?”በማለት ጠየቁ፡ በዚያች ቀን ቁጥራቸው  ሦስት ሺ ያህል ሰዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት አምነው  ክርስቲያን ለመሆን ቀረቡ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፡፡ “እነሆ ሁላችሁም ንስሐ ግቡ፡፡ በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምናችሁ ተጠመቁ፡፡” አላቸው በዚያው ዕለትም ሦስት ሺ ሰዎች ወደ ሐዋርያት በመቅረብ ኀጢአታቸውን ተናገሩ፤ ሐዋርያትም እግዚአብሔር ይፍታችሁ እያሉ ልጅነትን የሚያሰጣቸውን ጥምቀት አጠመቁዋቸው፡፡

ከዚያ ቀን ጀምሮም በየዓመቱ ይህችን ታላቅ የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን የምትባለውን በዓለ ጰራቅሊጦስን ክርስቲያኖች በታላቅ ደስታና ምሥጋና እናከብራታለን፡፡ እናንተም ልጆችዬ እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት በቤተ ክርስቲያን ተገኝታችሁ ቅዳሴ በማስቀደስ፣ መዝሙር በመዘመር እና በመጸለይ ይህችን ታላቅ በዓል ልታከብሯት ይገባል፡፡

የእግዚአብሔር አብ ጸጋ የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን  አሜን፡፡