ወላጆች ልጆቻችንን በመንፈሳዊ መንገድ እንዴት እናስተምር?

ዲያቆን ዮሴፍ ከተማ

ወላጆች ለወለድናቸው ልጆች ትልቅ አምላካዊ አደራ አለብን፡፡እግዚአብሔርም ልጅን ያህል ትልቅና የደስታ ምንጭ የሆነ ስጦታ ሲሰጠን ደግሞ ከትልቅ ኃላፊነት ጋር ነው፡፡ ከኃላፊነታችን  ትልቁ ለልጅ፡- ሃይማኖትን፤ ምግባርና ትሩፋትን በማስተማር ለእግዚአብሔር መንግሥት እንዲበቃ አድርጎ በፈሪሀ እግዚአብሔር ማሳደግ ነው፡፡ «ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፤ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም» እንዲል ምሳ. ፳፪፥፮፡፡

በዘመናችን መንፈሳዊ እሴቶች ተሸርሽረው በአብዛኞቹ ወላጆች «ወልጄ አሳድጌ፤ ወግ ማዕረግ አሳይቼ» የሚሉት የሥጋዊውን ፍላጎት ብቻ በመያዝ ነው፡፡ ዋናው የልጆችም ጥቅም፤ የወላጆችም ኃላፊነት ልጆቻችንን ለክብረ መንግሥተ ሰማያት ማብቃት ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ወላጅ «ልጄን ለሲኦል ነው ለመንግሥተ ሰማያት ነው የማሳድገው?» ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት፡፡

ማንም ለልጁ ክፉን አይመኝምና ሁሉም ሰው እርሱም ልጆቹም ለክብረ መንግሥቱ እንዲበቁ ይሻል፤ ስለዚህ ልጆች ዛሬ በጥሩ መሠረት ላይ መታነጽ ይኖርባቸዋል፡፡ ልጆች በልጅነታቸው ያልተዘራባቸውን በሕይወታቸው አያፈሩም፡፡አንዳንድ ወላጆች ለዓለማዊ ትምህርት ብቻ ቅድሚያ በመስጠት፤ መንፈሳዊውን ወደ ጎን ይተዋሉ፡፡ መንፈሳዊው ሕይወት ካደጉ በኋላ የሚደርስ ይመስላቸዋል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ወላጆች እኛ ራሳችን የመንፈሳዊ ሕይወት ግንዛቤ ስለሌለን አስፈላጊነቱም እምብዛም አይታየንም ወይንም በሰንበት ቀን ቤተ ክርስቲያን በመሄድ እንገድበዋለን፤ ሁሌ የሚኖሩት ሕይወት መሆኑን አናውቅም፡፡ ይህ ግን ለዚህ ዘመን የልጅ አስተዳደግ አስቸጋሪ ነው፡፡ይህ ዘመን ልጆቻችንን ወስዶ ብኩን የሚያድርጋቸው ብዙ የሕይወት ወጥመድ የሞላበት ነው፡፡ ካደጉ በኋላ በልጅነት የሌላቸውን ለማምጣት ይቸግራል፡፡ «ተስፋ ገና ሳለች ልጅህን ገሥጽ፤ መሞቱንም አትሻ» ምሳ. ፲፱፥፲፰

ስለዚህ የልጆቻችን ዕድገት ሁለንተናዊ እንዲሆን ከዓለማዊ ትምህታቸው ባልተናነሰ ወይንም በበለጠ ለመንፈሳዊው ትምህርትና ሕይወታቸው ከፍተኛ ትኩረትና ጥረት ልንሰጥ ይገባል፡፡ «ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ለሰው ምን ይጠቅመዋል?» ማር. ፰፥፴፮፤ ልጆቻችን በአስኳላ (በሳይንስ) ትምህርት ውስጥ ብቻ ቢያልፉ ምዕራባዊ ይሆናሉ፡፡

ምን ማለት ነው?

ዓለማችን በፈጣን ለውጦች ውስጥ እየተጓዘች ነው፡፡ብዙዎች የነሱ ሐሳብ፤እምነት፤ባህልና ሥርዓት በዓለም ላይ እንዲንሰራፋና የዓለም ሕዝብ የነሱ ተከታይ እንዲሆን እየተጉ ይገኛሉ፡፡ በተለይ የምዕራቡ ዓለም በዚህ ረገድ ፊታውራሪ ነው፡፡ሉላዊነት ወይንም ግሎባላይዜሽን በመባል የሚታወቀው የዘመናችን ገዢ ርእዮት ምዕራባዊ ባህልን፤የአኗኗር ዘይቤን በዓለም ላይ ለማሥረጽ የተቀረጸ ነው፡፡የሀገራችን ሥርዓተ ትምህርት ከምዕራባውያን ሥልጣኔ የተቀዳ ነው፡፡

ለመሆኑ ምዕራባዊነት መገለጫውና ግቡ ምድነው?

ምዕራባዊነት በተለይ ልጆችና ታዳጊዎች በሰፊው ተደራሽ በሚሆኑባቸው ፊልም፤ዘፈን፤ የትምህርት ሥዓታችን ወዘተ. በሰፊው የሚሰብክ ሲሆን

፩. ከመንፈሳዊነት ይልቅ ቁሳዊነትን ከፍ አድርጎ የሚያሳይ

፪. ቋሚ የሕይወት ዕሴት የሌለው እንደ ጊዜው የሚለዋወጥ ሰብእና፤ ዓለማዊነትን፤ ግብረ-ሰዶማዊነትን፤ ጾታ መቀየርን፤ የኮንትራት (በውል በተገደበ ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ) ትዳርን ወዘተ

፫. ሃይማኖት የለሽነትን ወይንም ፕሮቴስታንትነትን ግብ አድርጎ የሚሰራ ነው፡፡

ነገር ግን ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ይኸው ሕይወት ከፍ ያለና የሚያስቀና አስመስሎ በቁሳቁስ አጅቦ በማቅረብ የብዙ ወጣቶችን እና ታዳጊዎችን ቀልብ የሚማርክ ሆኗል፡፡ በዚህም አብዛኛው በተለይ የከተማው ወጣት ልቡ መማረኩ በአለባበሱ፤ በምኞቱና በአኗኗሩ ሁሉ የሚታይ ነው፡፡

ምዕራባውያኑ ይህን ዓይነቱን ሁኔታ ለመፍጠር የሚተጉት ለምንድነው?

ልብ በሉ! አንድ ማኅበረሰብ የእኛን አኗኗር የሚከተል ከሆነ ሌላው ሁሉ ቀርቶ ቢያንስ በዘላቂነት የእኛን ምርቶች ይጠቀማል፤ በየጊዜው የምናመጣውን አዳዲስ ነገር ይገዛል፡፡ ስለዚህ ዘላቂ የሆነ የገበያ ዕድል ባህላችንን በመሸጥ ብቻ እናገኛለን ማለት ነው፡፡ ይህ የምዕራባውያኑ አንዱ ግብ ሲሆን፤ በፖለቲካ፤ በሃይማኖትና በሌላም መስኮች የዓለም ቁንጮ ሆኖ የመምራትንና ለፈጠራዎቻቸው ሁሉ ተቀባይነትን ያስገኝላቸዋል ማለት ነው፡፡

ምን እናድርግ?

በመሠረቱ ልጆቻችን ላይ የተሠጠንን ኃላፊነት መወጣት የሚገባን ከምዕራባዊነት ልንታደጋቸው ብቻ አይደለም፡፡ ማንነታቸውን በትክክል አውቀው፤ በምድርም በሰማይም ተስፋ ያላቸው፤ ሥጋዊም መንፈሳዊም ዕድገትና ስኬት ያላቸው መሆን ይችሉ ዘንድ ነው፡፡

ክረምት

በተለይ ይህ ወቅት ሕፃናትና ታዳጊ ልጆች ብሎም ወጣቶቻች ከመደበኛው ትምህርት በአንጻሩም  ነፃ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ በታች ይህን ጊዜያቸውን ሊያውሉበት ይገባል ብለን ያቀረብናቸው ምክረ-ሐሳቦችም በእርግጥ በክረምቱ ጊዜ የበለጠ ቢተገበሩም በበጋውም ቢሆን መዘንጋት የሌለባቸው ነገሮች ናቸው፡፡

ኦርቶዶክሳውያን ልጆች በዚህ ክረምት የበለጠ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ማጎልበት ላይ በማተኮር፤ እግረ መንገዱን ደግሞ ለዘላቂው የክርስትና ሕይወታቸው ስንቅ የሚሆኑ እውቀትና ክህሎቶችን የሚያስጨብጧቸው ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለባቸው፡፡ እንደ ምሳሌም

፩. የአብነት ትምህርቶችን ቢከታተሉ

በየደብሩ የአብነትን ትምህርት ከጠቃሚ የአባቶች የሕይወት ምክሮችና ግብረ-ገብ ጋር ጨምረው የሚያስተምሩ ካህናት አሉ፡፡ ልጆች እነዚህን መማራቸው ለጸሎትና አጠቃላይ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ከመጥቀሙም ባሻገር በነገዋ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአገልግሎት ዕድል ፈንታ ይሰጣቸዋል፤ ይህም ቤተ ክርስቲያናችን ለምትመኘው በሁለት በኩል የተሳለ አገልጋይ ትልቅ መሠረት ነው፡፡ በአገልግሎት ውስጥ መኖር ደግሞ ለሌሎች ከመትረፍም ባሻገር ለራስ መጠበቅ የበለጠ ጠቃሚ ነው፡፡

፪. በሰንበት ትምህርት ቤቶች መርሐ ግብሮች ላይ ቢሳተፉ

እያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ልጅ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል፡፡  በጋውንም ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤት ቤተ ክርስቲያን ሕፃናትን የምትታደግበት አንዱ መዋቅር ነው፡፡ በክረምት ደግሞ በርካታ በአማራጭ የተዘጋጁ መርሐ-ግብሮች ስላሉ ሕፃናት ብዙ ያተርፉባቸዋል፡፡

፫. መንፈሳዊ የዜማ መሣርያዎችን ቢማሩ

በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርት ቤቶችና በአንዳንድ ሰንበት ትምህት ቤቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዜማ መሣርያዎች ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህም በገና፤ መሰንቆ፤ ከበሮና ዋሽንት ናቸው፡፡ ልጆች እነዚህን በዚህ ክረምት ቢማሩ እያደጉ በሄዱ ጊዜ ደግሞ የበለጠ ልምድ ስለሚሆናቸው ባለሙያ ይሆናሉ፡፡ይህም ለአገልግሎት ሕይወትም በር ይከፍትላቸዋል፡፡

፬. መንፈሳዊ ፊልሞችን፤መንፈሳዊ ታሪክና ትምህርት የያዙ የልጆች መጻሕፍትን፤ የሕፃናት መዝሙራትን ወዘተ. መመልከትና ማንበብ ቢችሉ የበለጠ ጠቃሚ ይሆንላቸዋል፡፡ በዚያውም እነዚህን ነገሮች ልምድ እንዲያደርጉ ስለሚረዳቸው ወላጆች ልጆቻቸው በእነዚህ መንገዶች ራሳቸውን በራሳቸው ስለሚያስተምሩ ብዙ ይረዳቸዋል፡፡

እነዚህን ቢያደርጉና በዘላቂነትም ገንዘብ ማድረግ ቢችሉ ለአጠቃላይ ሕይወታቸው ትልቅ ትርጉም ያለው ከመሆኑም ባሻገር ወላጆችም እግዚአብሔር የሚወዳቸውን በጎ ሥራዎች በማድረጋቸው ዋጋ ያገኙበታል፡፡

በመጨረሻም መዘንጋት የሌለበት ልጆች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጥሩ ሲሆኑ፤ በአስኳላ ትምህርታቸውም የበለጠ ብርቱዎች እንደሚሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በታችኞቹ ደረጃዎች ሳይወሰን ዛሬ በየዩኒቨርሲቲው በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያና ዋንጫ ሽልማቶቻቸውን ለቤተ ክርስቲያን ሥጦታ የሚያበረክቱ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን መመልከት በቂ ማስረጃ ነው፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!

 

ሆሣዕና (ለሕፃናት)

በቤካ ፋንታ

መጋቢት ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢየሩሳሌም በምትገኝ በአንድ ትንሽ መንደር ውስጥ ነው የምኖረው፡፡ ከተወለድኩ አምስት ዓመት ሞልቶኛል፡፡ በዕለተ ሰንበት በቤት ውስጥ እየተጫወትሁ፣ እናቴም በጓዳ ሥራ እየሠራች ሳለን በድንገት የብዙ ሰዎች የዕልልታ ድምፅ በሰፈሩ ውስጥ ሰማን፡፡ እናቴም በፍጥነት ከጓዳ ሮጣ ወጥታ ‹‹ልጄ! ልጄ! ነይ እንሒድ!›› ብላ አዝላኝ እየሮጠች ከቤት ወጣች፡፡ በኹኔታው ተገርሜአለሁ፡፡

በሰፈር ውስጥ ያሉ ጓደኞቼ ዅሉ በእናቶቻቸው ጀርባና በአባቶቻቸው ትከሻ ላይ ኾነው ከወላጆቻቸው ጋር በደስታ ዕልል ይላሉ፡፡ የሕፃናቶቹን ብዛት ሳይ ይበልጥ ተደሰትሁ፡፡ የሚያለቅስ አንድም ልጅ የለም፡፡ ‹‹ዛሬ የሕፃናት የደስታ እና የዝማሬ ቀን ነው›› ብሎ ልቤ በደስታ ፈነደቀ፡፡ ወላጆቻችን ዅሉ የዘንባባ ዝንጣፊ እየቈረጡ ያዙ፤ ለእኛም ሰጡን፡፡ ከዚያ ዕልል እያልን በደስታ ወደ ቤተ መቅደስ ሮጥን፡፡

በመንገድ ላይ በጣም ብዙ ሕዝብ አየሁ፤ እነርሱም ዘንባባ ይዘው ደስ ብሏቸው እንደኛ ወደ ቤተ መቅደስ ይሮጣሉ፡፡ በመካከላቸው አንድ ትልቅ አህያ አየሁኝ፣ ከአህያይቱም ጋር ውርንጫዋ (ልጇ) አለች፡፡ የሚያማምር ልብስ በአህያዎቹ ጀርባ ላይ ተነጥፏል፡፡ በውርንጫዋም ላይ የዅላችን ፈጣሪ፣ ንጉሣችን፣ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀምጦ ስመለከት በደስታ ዘለልሁኝ፡፡

ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መኾን በጣም ያስደስታል፡፡ ምክንያቱም እርሱ እኛ ሕፃናትን እቅፍ አድርጎ ስሞን በጉልበቱ ላይ ቁጭ አድርጎ ያስተምረናል፣ ይመክረናል፡፡ በዙሪያውም ላሉት ሰዎች ‹‹እንደነዚህ ሕፃናት ንጹሓንኑ፤ ኃጢአት አትሥሩ፤›› እያለ ይመክራቸዋል፡፡

ከዚያ ዕልል እያለ የሚያመሰግነው ሕዝብ፣ እንደዚሁም በእናትና በአባቶቻችን እቅፍ ውስጥ ያለን ሕፃናት በአንድነት ኾነን ጮክ ብለን የዘንባባውን ቅጠል እያውለበለብን መዝሙር መዘመር ጀመርን፡፡ መዝሙሩም እንዲህ የሚል ነው፤ ‹‹ሆሣዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፡፡ ሆሣዕና በአርያም፤ ሆሣዕና በአርያም፤ ሆሣዕና በአርያም፡፡›› የመዝሙሩ ድምፅ በኢየሩሳሌም ከተማ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተሰማ፡፡ በጣም ደስ ያለኝ ደግሞ የእኛ የሕፃናቱ ድምፅ ከትልልቆቹ በልጦ መሰማቱ ነው፡፡

ጌታችንን በአህያዋ ላይ ተቀምጦ ባየሁት ጊዜ ትዝ ያለኝን አባዬ መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበ ያስተማረኝን ታሪክ ልንገራችሁ፤ ታሪኩም፡- ‹‹አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፣ እጅግ ደስ ይበልሽ! አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፣ ዕልል በዪ! እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም በአህያ፣ በአህያይቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፤›› የሚል ነው (ትንቢተ ዘካርያስ ፱፥፱)፡፡

የዝማሬውን ድምፅ ሲሰሙ አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወዱት በከተማው ውስጥ ያሉ ጨካኝ ሰዎች ወደ እኛ መጡ፡፡ ሰዎቹም ሕዝቡ ዅሉ ደስ ብሏቸው እየዘመሩ፣ ዕልል እያሉ፣ የዘንባባውን ቅጠል እያውለበለቡ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን እያመሰገኑ ወደ ቤተ መቅደስ ሲሔዱ በተመለከቱ ጊዜ ተናደው ሕዝቡን ‹‹ዝም በሉ!›› ብለው ተቈጧቸው፡፡ ሕዝቡም ፈርትው ዝም አሉ፡፡

እኔና ጓደኞቼ ግን በእናታችን ጀርባ ላይ ካሉት ሕፃናት ጋር አብረን ኾነን ጮክ ብለን ‹‹ሆሣዕና በአርያም›› የሚለውን መዝሙር ሳናቋርጥ እንዘምር ነበር፡፡ የገረመኝ ደግሞ ከእኔ የሚያንሱ ሕፃናትም መዝሙሩን ጮክ ብለው ሲዘምሩት መስማቴ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ሆይ መናገር የማንችለውን እኛን እንድንዘምርልህ ስለፈቀድህልን ተመስገን!›› ብዬ አምላኬን አመስግኜ መዝሙሩን መዘመር ቀጠልሁኝ፤ ‹‹ሆሣዕና፣ ሆሣዕና፣ ሆሣዕና በአርያም …፡፡››

በኋላ ግን እነዚያ ጨካኞቹ ሰዎች ስላስፈራሯቸው ወላጆቻችን ዝም አስባሉን፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በአህያዋ ውርንጫ (በትንሿ አህያ) ላይ ቁጭ ብሎ ለጨካኞቹ ሰዎች ‹‹ከሕፃናት ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራሴ አዘጋጅቻለሁ፡፡ የእነርሱንም አፍ ይዛችሁ ዝም ብታስብሏቸው በዙሪያዬ ያሉት ድንጋዮች ያመሰግኑኛል፤›› አላቸው፡፡

ከዚያም ጌታችን፡- ‹‹የፈጠርኋችሁ ድንጋዮች ሆይ! ሕፃናት እንደ ዘመሩ እናንተም በመዝሙር አመስግኑኝ፤›› በማለት በታላቅ ድምፅ ሲናገር ግዙፍ ድንጋዮች ከመሬት ወደ ላይ እየተነሡ ‹‹ሆሣዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና እናቀርባለን …›› እያሉ በሚያስደስት ድምፅ እየመዘመሩ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ጨካኞቹ ሰዎች አፍረውና ፈርትው ተመለሱ፡፡

እኛ ሕፃናት፣ ወላጆቻችንና በዙሪያችን የነበሩ ድንጋዮችም አምላካችንን ከበን በዕልልታ እየዘመርን፤ ለአህያዎቹ መርገጫ ልብሳችንንና የዘንባባውን ዝንጣፊ እያነጠፍን ወደ ቤተ መቅደስ ገባን፡፡ በዚያም ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደስ የሚል ትምህርት አስተማረን፡፡

በመጨረሻም ‹‹ሆሣዕና›› ብለን ምስጋና ላቀረብነውና በቤተ መቅደስ ተገኝተን ቃሉን ለምንሰማው ሕፃናት ጌታችን እንዲህ ብሎ መከረን፤ ‹‹ልጆቼ በመዝሙራችሁ ተደስቻለሁ፡፡ ዅል ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን እየመጣችሁ ዘምሩልኝ፡፡አንደበታችሁ በመዝሙር አግዚአብሔርን አመስግኑበት እንጂ ዘፈን እንዳትዘፍኑበት፡፡ ዘፈንጢአት ነው፡፡››

ትምህርቱን ተከታትለን ከእናቴ ጋር ደስ እያለን ወደ ቤታችን ተመለስን፡፡ ታዲያ ዅል ጊዜ ይህችን የሆሣዕናን በዓል በውስጤ አስባታለሁ፤ መዝሙሩን መዘመር በጣም ያስደስተኛል፡፡ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻ የመከረኝንም ምክር ጠብቄ ዘፈን የሚባል በአፌ ሳልዘፍን በመዝሙር እግዚአብሔርን እያመሰገንሁ አደጌአለሁ፡፡

ልጆችዬ! ዛሬ የምታነቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፩ ከቍጥር ፩ እስከ ፲፮ እና የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፩ ከቍጥር ፩ እስከ ፲፯ ያለው ትምህርት ነው፡፡

‹‹ሆሣዕና በአርያም›› ብለን እንድናመሰግነው የፈቀደልን፤ ኃይሉን ጥበቡን የሰጠን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – የመጨረሻ ክፍል

፰. ሆሣዕና

በልደት አስፋው

መጋቢት ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ልጆች ደኅና ሰነበታችሁ? እግዚአብሔር ይመስገን! ባለፈው ዝግጅት ሰለ ሰባተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት (ስለ ኒቆዲሞስ) ተምራችሁ ነበር፡፡ መልካም ልጆች! በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ ስለ ስምንተኛውና የመጨረሻው የዐቢይ ጾም ሳምንት ማለትም ስለ ሆሣዕና አጭር ትምህርት እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

ስምንተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹ሆሣዕና› ይባላል፡፡ ትርጕሙም ‹መድኃኒት፣ አሁን አድን› ማለት ነው፡፡ ሆሣዕና ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ በክብር፣ በምስጋና ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት ዕለት ነው፡፡

በዚህ ዕለት ሕፃናትና አረጋውያን በአንድነት ኾነው፣ የዘንባባ ቅጠል ይዘው፡- ‹‹ለዳዊት ልጅ በሰማይ መድኒት መባል ይገባዋል፤ በእግዚአብሔር ስም የመጣ የዳዊት ልጅ ዳዊት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ቡሩክ ነው!›› እያሉ በአንድነት ጌታችንን አመስግነዋል፡፡

ስለዚህም ሆሣዕና በየዓመቱ በቤተ ክርስቲያናችን በመንፈሳዊ ሥርዓት ይከበራል፡፡ እኛ ክርስቲያኖችም ለመታሰቢያ ይኾን ዘንድ በራሳችን ላይ የዘንባባ ቅጠል በመስቀል ምልክት እናስራለን፡፡

ልጆች! የዐቢይ ጾም ሳምንታትን ስያሜና ታሪክ በሚመለከት በተከታታይ ክፍል ያቀረብንላችሁን ትምህርት በዚሁ ፈጸምን፡፡ በሉ ደኅና ኹኑ ልጆች! ለበዓለ ትንሣኤው በሰላም ያድርሰን፡፡ ሰላመ እግዚአብሔር ከዅላችን ጋር ይኹን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል አምስት  

በቴዎድሮስ እሸቱ

መጋቢት ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

፯. ኒቆዲሞስ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደኅና ናችሁ? መልካም! ይኸው ዘወረደ ብለን በመጀመሪያው ሳምንት የጀመርነው ጾም ዛሬ ኒቆዲሞስ ላይ ደርሷል፡፡ ኒቆዲሞስ የሰባተኛው ሳምንት መጠሪያ ነው፡፡ ልጆች! የአይሁድ መምህር የኾነ አንድ ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው ነበር፡፡ ይህ የአይሁድ መምህር ማታ ማታ እየመጣ ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግር ሥር ቁጭ ብሎ ትምህርት ይማር ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ማታ ማታ የሚማረው ለምን መሰላችሁ ልጆች?

አንደኛ የአይሁድ መምህር ስለ ኾነ አይሁድ ሲማር እንዳያዩት ነው፡፡ እነርሱ ሲማር ካዩት ገና ሳይማር ነው እንዴ እኛን የሚያስተምረን እንዳይሉት፤ ሁለተኛ አይሁድ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎችን ከአገራቸው ያባርሩ ስለ ነበር እንዳይባረር በመፍራቱ፤ ሦስተኛ ሌሊት ምንም የሚረብሽና ዐሳብን የሚሰርቅ ጫጫታ ስለሌለ ትምህርቱ እንዲገባው ነበር፡፡ እናንተስ በሌሊት ትምህርታችሁን የምታጠኑት እንዲገባችሁ አይደል ልጆች? በሌሊት ዐሳባችሁ አይበተንም፡፡

ታዲያ አንድ ቀን ማታ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔር መንግሥት ሊወርስ አይችልም›› ብሎ ለኒቆዲሞስ ስለ ጥምቀት አስተማረው፡፡ ኒቆዲሞስም ‹‹ሰው ከሸመገለ ካረጀ በኋላ እንዴት ድጋሜ ሊወለድ ይችላል?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ጌታችንም ዳግም ልደት ማለት ሰው በጥምቀት የሚያገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት እንደ ኾነ፣ ሰው ተጠምቆ የእግዚአብሔር ልጅ ካልኾነ መንግሥተ ሰማያትን እንደማይወርስ አስተማረው፡፡ ኒቆዲሞስም ስለ ጥምቀት በሚገባ ተረዳ፡፡

ልጆች! በዚህ ሳምንት ከሚነገረው ከዚህ ታሪክ ዅል ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል መማር እንዳለብን፤ ያልገባን ነገር ካለ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ጠይቀን መረዳት እንደሚገባን እንማራለን፡፡ እናንተም እንደ ኒቆዲሞስ ቃለ እግዚአብሔር በመማር እና ስለ እምነታችሁ ያልገባሁን በመጠየቅ በቂ ዕውቀት ልትቀስሙ ይገባችኋል፡፡ ልጆች! ለዛሬ በዚህ ይበቃናል፤ ደኅና ሰንብቱ፡፡

ገብር ኄር (ለሕፃናት)

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እንደምን ሰነበታችሁ የተወደዳችሁ ሕፃናት? መልካም! እስከ ዛሬ ድረስ የጠበቀን፣ ለወደፊትም የሚጠብቀን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ይመስገን! ልጆች! ስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹ገብር ኄር› የሚል ስያሜ አለው፡፡ ‹ገብር ኄር› ማለት ‹በጎ፣ ታማኝ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡

በዚህ ሳምንት ጸጋን (ተሰጥዎን) በአግባቡ ስለ መጠቀም እና ስለ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያስተምር ቃለ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ይነገራል፡፡ በተጨማሪም ስለ ‹ገብር ሐካይ› ጠባይ የሚያስረዳ ትምህርት ይቀርባል፡፡ ‹ገብር ሐካይ› ማለት ‹ሰነፍ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡ የእነዚህን ሰዎች ታሪክም በአጭሩ እናስታውሳችኋለን፤ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፭ ከቍጥር ፲፬ ጀምሮ እንደ ተጻፈው አንድ ሰው አገልጋዮቹን ጠራና ለአንዱ አምስት፤ ለአንዱ ሁለት፤ ለአንዱ ደግሞ አንድ መክሊት ሰጣቸው፡፡ ልጆች! ‹መክሊት› – ብር፣ ዶላር፣ እንደሚባለው ያለ የገንዘብ ዓይነት ነው፡፡

አምስት መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ነግዶ፣ ሌላ አምስት መክሊት አትርፎ ዐሥር አድርጎ ለጌታው አቀረበ፡፡ ጌታውም፡- ‹‹አንተ ጎበዝ እና ታማኝ አገልጋይ! በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለውም አትርፎ አራት አድርጎ አቀረበ፡፡ እርሱንም ጌታው፡- ‹‹አንተ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡ እርሱ ግን መክሊቱን ቀብሮ አቆየና ጌታው እንዲያስረክብ በጠየቀው ጊዜ፡- ‹‹እነሆ መክሊትህ!›› ብሎ ምንም ሳያተርፍበት መለሰለት፡፡ ጌታውም፡- ‹‹ይህን ክፉና ሰነፍ አገልጋይ እጅ እግሩን አስራችሁ ጨለማና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ሥፍራ ውሰዱት! መክሊቱን ቀሙና ለባለ ዐሥሩ ጨምሩለት!›› ብሎ አዘዘ፡፡ ‹ገብር ሐካይ› የተባለው ይህ መክሊቱን የቀበረው አገልጋይ ነው፡፡

ልጆች! ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠንን ጸጋ በአግባቡ ከተጠቀምን ትልቅ ዋጋ እንደምናገኝ፤ ጸጋችንን በአግባቡ ካልተጠቀምን ደግሞ ቅጣት እንደምንቀበል ከዚህ ታሪክ እንማራለን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለእናንተም ስታድጉ በመንፈሳዊው ሕይወታችሁ የጵጵስና፣ የቅስና፣ የዲቁና፣ የሰባኪነት፣ የዘማሪነት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ጸጋዎችን እንደየአቅማችሁ ይሰጣችኋል፡፡ በዓለማዊው ሕይወታችሁ ደግሞ የፓይለትነት፣ የመሐንዲስነት፣ የዶክተርነት፣ የመምህርነት፣ የመንግሥት ሠራተኛነት፣ ወዘተ. ሌላም ዓይነት የሥራ ጸጋ ያድላችኋል፡፡

መንፈሳዊውን ወይም ዓለማዊውን ትምህርታችሁን በርትታችሁ በመማር ካጠናቀቃችሁ በኋላ ከእናንተ ብዙ ሥራ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ልጆች! በምድር ሕይወታችሁ እንዲባረክ፤ በሰማይም የእግዚአብሔርን መንግሥት እንድትወርሱ እንደ ገብር ኄር የተሰጣችሁን ጸጋ በመጠቀም ቤተሰባችሁን፣ አገራችሁንና ቤተ ክርስቲያናችሁን በቅንነት ማገልገል አለባችሁ፡፡ በጣም ጥሩ ልጆች! ለዛሬው በዚህ ይበቃናል፤ በሌላ ዝግጅት እስከምንገናኝ ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይኹን! ሳምንቱ መልካም የትምህርት ጊዜ ይኹንላችሁ!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል አራት

፮. ገብር ኄር

በልደት አስፋው

መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፱ .

ሰላም ናችሁ ልጆች? ባለፈው ዝግጅት ስለ ደብረ ዘይት ተምረናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ስለ ‹ገብር ኄር› እንማራለን፡፡ ስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት (እሑድ) ‹ገብር ኄር› ይባላል፡፡ ትርጕሙ ‹ታማኝ፣ በጎ፣ ደግ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡ ልጆች! አንድ ባለጠጋ አገልጋዮቹ ነግደው እንዲያተርፉበት ለአንዱ አምስት፤ ለሁለተኛው ሁለት፤ ለሦስተኛው አንድ መክሊት ሰጣቸው፡፡ ልጆች! ‹መክሊት› የገንዘብ ስም ነው፡፡

ከዚያ በኋላ አምስት እና ሁለት መክሊት የተቀበሉት ሁለቱ አገልጋዮች በተሰጣቸው መክሊት ነግደው እጥፍ አትርፈው ለባለ ጌታው አስረከቡ፡፡ ስለዚህም ገብር ኄር (ታማኝ አገልጋይ) ተብለው ተመሰገኑ፤ ልዩ ክብርን አገኙ፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ግን የተቀበለውን መክሊት ቀብሮ ካቆየ በኋላ ምንም ሳያተርፍበት ለጌታው አስረከበ፡፡ ይህ አገልጋይ ‹ገብር ሐካይ› ይባላል፡፡ ‹ሰነፍ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡ በመክሊቱ ባለማትረፉ የተነሣ ቅጣት ተፈርዶበታል፡፡

የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፭ ቍጥር ፲፬-፵፮ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ብታነቡት ሙሉ ታሪኩን ታገኙታላችሁ፡፡ ልጆች! ስድስተኛው የዐቢይ ጾም እሑድ ስለ እነዚህ አገልጋዮች እና ስለ መንፈሳዊ አገልግሎት ጥቅም ትምህርት የሚቀርብት ሳምንት በመኾኑ ‹ገብር ኄር› ተብሏል፡፡ እናንተም በተሰጣችሁ ጸጋ ብዙ ምግባር መሥራት አለባችሁ እሺ? መልካም ልጆች! ለዛሬው በዚህ ይበቃናል፡፡ በቀጣይ ደግሞ ስለ ኒቆዲሞስ እንማማራለን፡፡ ሰላመ እግዚአብሔር ከዅላችን ጋር ይኹን!

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል ሦስት

በልደት አስፋው

መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

፭. ደብረ ዘይት

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ስለዅሉም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን! ባለፈው ዝግጅታችን አራተኛውን የዐቢይ ጾም ሳምንት የተመለከተ ትምህርት አቅርበንላችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ስለ አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት (ስለ ደብረ ዘይት) አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን በተግባር ላይ እንድታውሉት እሺ? መልካም ልጆች! አሁን በቀጥታ ወደ ትምህርቱ እንወስዳችኋለን፤

ልጆች! እንደምታስታውሱት አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ደብረ ዘይት›› ይባላል፡፡ ትርጕሙም ‹‹የወይራ ተክል የሚገኝበት ተራራ›› ማለት ነው፡፡ ይህ ትልቅ ተራራ (ደብረ ዘይት) ከኢየሩሳሌም ከተማ በስተምሥራቅ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ ደብረ ዘይት ተራራ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዕለተ ምጽአትን ምልክት ለደቀ መዛሙርቱ (ለሐዋርያት) የገለጸበትና ያስተማረበት ቦታ ነው፡፡ ጌታችን በዚህ በደብረ ዘይት ተራራ ተቀመጦ ‹‹ማንም እንዳያስታችሁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፡፡ እስከ መጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል …›› እያለ ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯቸዋል፡፡

እነርሱም ስለ ዕለተ ምጽአት ምልክትና የመምጫው ጊዜ መቼ እንደሚኾን ጌታችንን ጠይቀውታል፡፡ እርሱም ቀኑን ከእርሱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም እንደማያውቀውና ክርስቲያኖች ከኀጢአት ርቀው በዝግጅት መጠባበቅ እንደሚገባቸው አስረድቷቸዋል፡፡ ልጆች! ዓለም የምታልፍበት ቀን ሲደርስ (በዕለተ ምጽአት) ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመላእከት ዝማሬ፣ በመለከት ድምፅ ታጅቦ በኃይልና በግርማ ከሰማይ ወደ ምድር ይመጣል፡፡

አምላካችን በመጣ ጊዜም በተዋሕዶ ሃይማኖትና በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንቶ የተገኘ ክርስቲያን በገነት (መንግሥተ ሰማያት) ለዘለዓለሙ በደስታ ይኖራል፡፡ ያለ ክርስቲያናዊ ምግባር ማለትም በኀጢአት ሥራ የኖረ ሰው ደግሞ ለዘለዓለሙ መከራና ስቃይ ወዳለበት ወደ ሲኦል (ገሃነመ እሳት) ይጣላል፡፡ ስለዚህ አምላካችን ለፍርድ ሲመጣ ለእያንዳንዳችን እንደ ሥራችን ኹኔታ ዋጋ ይሰጠናል ማለት ነው፡፡ የጽድቅ ሥራ ስንሠራ ከኖርን ወደ መንግሥተ ሰማያት (የጻድቃን መኖሪያ) እንገባለን፤ ኀጢአት ስንሠራ ከኖርን ግን ወደ ገሃነመ እሳት (የኀጢአተኞች መኖሪያ) እንጣላለን፡፡

ልጆች! እናንተም በዕለተ ምጽአት ወደ መንግሥተ ሰማያት እንድትገቡ በምድር ስትኖሩ ከክፉ ሥራ ማለትም ከስድብ፣ ከቍጣ፣ ከተንኮል፣ ከትዕቢት እና ከመሳሰለው ኀጢአት ርቃችሁ በእውነት፣ በትሕትና፣ ሰውን በማክበር፣ በፍቅር እና በመሳሰለው የጽድቅ ሥራ ጸንታችሁ ለወላጆቻችሁ እየታዘዛችሁ ኑሩ፡፡ ይህንን ለማድረግ እንድትችሉ ደግሞ ከዘመናዊው ትምህርታችሁ ጎን ለጎን ከወላጆቻችሁ ጋር እየተመካከራችሁ (አስፈቅዳችሁ) መንፈሳዊ ትምህርት መማር፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ መንፈሳውያን ፊልሞችን መመልከትና መዝሙራትን ማዳመጥ፣ እንደዚሁም በየጊዜው መቍረብ አለባችሁ እሺ?

በጣም ጥሩ ልጆች! ለዛሬው ከዚህ ላይ ይቆየን፡፡ በሚቀጥለው ዝግጅት ስለሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ትምህርት ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከኹላችን ጋር ይኹን!

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል ሁለት  

በልደት አስፋው

መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ባለፈው ዝግጅታችን ከመጀመሪያው እሑድ እስከ ሦስተኛው እሑድ (ከዘወረደ ጀምሮ እስከ ምኵራብ) ድረስ የሚገኙትን የዐቢይ ጾም ሳምንታት የሚመለከት ትምህርት አቅርበንላችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ አራተኛውን የዐቢይ ጾም ሳምንት (መጻጕዕን) የሚመለከት ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ!

፬. መጻጕዕ

ልጆች! አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹መጻጕዕ›› ይባላል፡፡ መጻጕዕ ማለት በሽተኛ ማለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በበሽታ ተይዞ የነበረውን ሰው የፈወሰበት ዕለት ነው /ዮሐ.፭.፩-፱/፡፡

ልጆች! ቤተሳይዳ የምትባል አንዲት የጠበል መጠመቂያ ሥፍራ ነበረች፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደዚያች መጠመቂያ ሥፍራ እየመጣ ውኃውን ከባረከው በኋላ ቀድሞ ገብቶ የተጠመቀ በሽተኛ ካለበት ከማንኛውም ደዌ (በሽታ) ይፈወስ ነበር፡፡ በዚያ ሥፍራ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ከበሽታው ለመፈወስ ብሎ ሲጠባበቅ የነበረ አንድ መጻጕዕ (በሽተኛ) ነበር፡፡ ውኃው በተናወጠ ጊዜ ሌሎች ቀድመው ገብተው እየተፈወሱ ሲሔዱ እሱ ግን ለሰላሣ ስምንት ዓመት በዚያ ቆየ፡፡

ከዚያ በኋላ ጌታችን በዚያ ሥፍራ ሲያልፍ ይህንን መጻጕዕ ተኝቶ አየው፡፡ በዚህ ጊዜ ለብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› ብሎ ከጠየቀው በኋላ እምነቱንና ጽናቱን አይቶ ‹‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› አለው፡፡ በጌታችን ቃል ሰውዬው ወዲያውኑ ከበሽታው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ የእግዚአብሔርን ቸርነት እየመሰከረ ሔደ፡፡ በአጠቃላይ አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት የመጻጕዕ ታሪክ የሚነገርበት፤ እንደዚሁም የአምላካችን ቸርነቱ፣ ይቅርታው፣ መሐሪነቱ የሚታወስበት ዕለት ነው፡፡

ልጆች! ደብረ ዘይትን የሚመለከት ትምህርት ደግሞ በሌላ ቀን እናቀርብላችኋለን፡፡ ለዛሬው ከዚህ ላይ ይቆየን፡፡ እስከዚያው ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከዅላችሁ ጋር ይኹን!

የዐቢይ ጾም ሳምንታት (ለሕፃናት) – ክፍል አንድ

በልደት አስፋው

የካቲት ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደኅና ናችሁ? እግዚአብሔር ይመስገን!፡፡ ልጆች! በልዩ ልዩ ምክንያት አልችል ብለን ዘግይተናል፡፡ በቅድሚያ በገባነው ቃል መሠረት ወቅቱን ጠብቀን ትምህርቱን ባለማቅረባችን እናንተን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

ልጆች! የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ባቀረብንላችሁ ትምህርት ከሰባቱ አጽዋማት መካከል ዐቢይ ጾም አንዱ እንደኾነ፣ ዐቢይ ጾም ማለት ታላቅ ጾም ማለት እንደኾነ፣ ጾሙ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም በመኾኑ ታላቅ እንደተባለ፣ ዕድሜአቸው ሰባት ዓመት ከኾናቸው ሕፃናት ጀምሮ ዅሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዐቢይ ጾምን እና ሌሎችንም አጽዋማት መጾም እንደሚገባቸው፣ እንደዚሁም ስምንቱ የዐቢይ ጾም ሳምንታት (እሑዶች) ስማቸው ማን ማን እንደሚባል ነግረናችሁ ነበር፡፡

ልጆች! ሰባቱ አጽዋማት ማን ማን እንደሚባሉም ጠይቀናችሁ ነበር አይደል? መልሱንስ ጠይቃችሁ ተረዳችሁ? በጣም ጥሩ ልጆች! መልሱን እናስታውሳችሁ፤ ሰባቱ አጽዋማት የሚባሉት፡-

፩. ጾመ ነቢያት

፪. ጾመ ገሃድ (ጋድ)

፫. ጾመ ነነዌ

፬. ዐቢይ ጾም

፭. ጾመ ድኅነት (ረቡዕ እና ዓርብ)

፮. ጾመ ሐዋርያት

፯. ጾመ ፍልሰታ (የእመቤታችን ጾም) ናቸው፡፡

በአሁኑ ሰዓት ዐቢይ ጾምን እየጾምን ነው፡፡ የምንገኘውም ሦስተኛው ሳምንት ላይ ሲኾን ስሙም ‹‹ምኵራብ›› ይባላል፡፡ የሚቀጥለውና አራተኛው ሳምንት ደግሞ ‹‹መጻጕዕ›› ተብሎ ይጠራል፡፡

ልጆች! በዛሬው ዝግጅታችን ከመጀመሪያው እሑድ እስከ ሦስተኛው እሑድ (ከዘወረደ ጀምሮ እስከ ምኵራብ) ድረስ የሚገኙትን የዐቢይ ጾም ሳምንታት የሚመለከት ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን እንድከታተሉት በአክብሮት ጋብዘናችኋል!

፩. ዘወረደ

ልጆች! ከዐቢይ ጾም ሳምንታት መካከል የመጀመሪያው ሳምንት ‹‹ዘወረደ›› ይባላል፡፡ ዘወረደ ማለት ከላይ የመጣ፣ የወረደ ማለት ነው፡፡ ይህም አምላካችን ዓለምን ለማዳን ሲል ሥጋ መልበሱን (ሰው መኾኑን) ያመለክታል፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወርዶ፣ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ፣ ወንጌልን ለዓለም ካስተማረ በኋላ በፈቃዱ መከራ ተቀብሎ፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ከሙታን ተነሥቶ ዓለምን አድኗል፡፡ ልጆች! የመጀመሪያው ሳምንት የአምላካችን የማዳን ሥራ በስፋት የሚነገርበት ወቅት በመኾኑ ‹‹ዘወረደ›› ተብሎ ተሰይሟል፡፡

፪. ቅድስት

ሁለተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ቅድስት›› ይባላል፡፡ ቅድስት ማለት የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች ማለት ነው፡፡ ልጆች! ለምን የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች እንደተባለች ታውቃላችሁ? ቅዱስ አምላካችን እግዚአብሔር ዓለምን (ሰውን) ለመቀደስ ሲል ወደ ምድር መምጣቱንና ዐቢይ ጾምን መጾሙን ለማስረዳት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሰንበትን ክብር ለማስገንዘብ ነው፡፡ ሰንበት ቅድስት፣ የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች ዕለት ናት፡፡ ስለዚህም ልጆች! ሁለተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ቅድስት›› ተብሎ ይጠራል፡፡

፫. ምኵራብ

ልጆች! ሦስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ደግሞ ‹‹ምኵራብ›› ይባላል፡፡ ምኵራብ ማለት አዳራሽ ማለት ነው፡፡ ምኵራብ ድሮ የነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎች መንፈሳዊ ትምህርት ይማሩበት የነበረ  ሥፍራ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ይህንን የጸሎት ሥፍራ ሰዎች የንግድ ቦታ አደረጉት፡፡ ይህንን ዓለማዊ ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩትን ዅሉ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፡፡ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት›› ብሎ ከምኵራብ አስወጣቸው፡፡ ከዚያም ቃለ እግዚአብሔር አስተማራቸው፡፡ ልጆች! የእግዚአብሔር ቤት የጸሎት ቤት እንጂ የንግድ መነገጃ ሥፍራ አለመኾኑን ከዚህ ታሪክ እንማራለን፡፡

ለዛሬው በዚህ ይቆየን፡፡ ቀጣዩን ትምህርት ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሚቀጥለው ዝግጅት ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከዅላችን ጋር ይኹን!