ሊቀ ዲያቆናትና ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ጥቅምት ፲፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት አላችሁልን? ትምህርት እንዴት ነው? መቼም በክረምቱ የዕረፍት ጊዜያችሁ ትምህርት እስኪከፈት በጣም ጓጉታችሁ እንደነበር እናስባለን! ይኸው ተከፈተላችሁ! እንግዲህ በርትታችሁ ከአሁኑ መማር፣ ማጥናት፣ የቤት ሥራን መሥራት፣ ያልገባችሁን መጠየቅ ይገባችኋል፡፡ ገና ነው እያላችሁ እንዳትዘናጉ ጥናቱን አሁኑኑ ጀምሩ! የጨዋታም ሆነ ቴሌቪዥን የምታዩበት ጊዜ ከትምህርታችሁ ጋር በማይጋጭ መልኩ መሆን አለበት፡፡ ከሁሉም ትምህርታችሁን አስቀድሙ! ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ ያዘጋጀንላችሁ የሊቀ ዲያቆናትና የቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን ታሪክ ነው፡፡

ቅዱስ እስጢፋኖስ እናቱ ሐና አባቱ ስምዖን ይባላሉ፤ ደጋጎችና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ በእግዚአብሔር ፈቃድም ሁለት ልጆችን ወለዱ፤ አንዱም ቅዱስ እስጢፋኖስ ነው፤ የተወለደውም ጥር አንድ ቀን ነው፤ እስጢፋኖስ ማለት አክሊል ማለት ነው፡፡ ሕገ እግዚአብሔርን እየተማረና ለወላጆቹ እየታዘዘ በሥርዓት አደገ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን ከመረጣቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ሆኖ ያገለግልም ነበር፤ ሕዝብን እንዲያሰተምሩ በወቅቱ ተመርጠው ከነበሩ ሰባት ዲያቆናት አንዱ ነበር፤ የተሾመበት ቀንም ጥቅምት ዐሥራ ሰባት ነው፡፡ በጣም ጎበዝ እና ያወቀውን ላላወቁ ለማሳወቅ የሚተጋ ታዛዥ፣ ቅን አገልጋይም ነበር፡፡ ይገርማችኋል የእግዚአብሔር ልጆች! በወቅቱ አይሁድ የተባሉ ጌታችንን በመስቀል እንዲሰቀል ያደረጉ ክፉ ሰዎች በማስተማሩ ቀንተው ‹‹ለምን ታስተምራለህ? ለምን የክርስቶስን ስም ትጠራለህ?›› እያሉ ተቃወሙት፤ እርሱ ግን በትሕትና ሆኖ ከስሕተት መንገዳቸው እንዲመለሱና በማስተዋል እንዲጓዙ ይመክራቸው ጀመር፡፡ በአንድ ወቅትም ናዖስ ተባለ ጠንቋይ በምትሃት ሰዎችን እያሳሳተ ሳለ ቅዱስ እስጢፋኖስ ከዚህ ባዕድ አምልኮ እንዲመለሱና በእግዚአብሔር እንዲያምኑ አስተምሮ ምእመኑን ወደ ክርስትና እምነት አመጣቸው፤ በዚህን ጊዜ በሰውየው ላይ ያደረው ሰይጣን ተበሳጨ፤ ጠንቋዩ ናዖስም በምትሃት (በአስማት) አንድን በሬ እፍ ሲልበት ለሁለት ክፍል አለ፡፡

ልጆች! ከዚያም ሕዝቡ ይህንን ሲያይ እውነት መሰላቸውና ጠንቋዩን ሊከተሉ ልባቸው አመነታ፤ ቅዱስ እስጢፋኖስም ከእግዚአብሔር በተሰጠው ተአምራት የማድረግ ሥልጣን ያንን የሞተ በሬ አስነሳውና በሰው ቋንቋ እንዲናገር ናዖስን እንዲጠራ አዘዘው፡፡ በሬውም ሄዶ ‹‹ናዖስ እስጢፋኖስ ይጠራሃል›› አለው፡፡ ሰዎቹ ይህንን ተአምር ሲመለከቱ ‹‹እኛ በቅዱስ እስጢፋኖስ እምላክ እናምናለን›› ብለው ወደ ክርስትና ሃይማኖት በመምጣት ከስሕተት ተመለሱ፤ ወደ ሕይወት ገቡ፤ አይገርም ልጆች! ጌታችን አስቀድሞ በትምህርቱ ‹‹…በእኔ የሚያምን እኔ ማደርገውን ያደርጋል›› በማለት እንደገለጸው የተለያዩ ተአምራትን ያደርግ ነበር፤ ከዚያም በዚህ ቀኑበት፤ የሐሰት ክስና ባልሠራው ጥፋት ‹‹ሰደበን፤ የሙሴን የኦሪትን ሕግ ሻረ›› በማለት ከሰሱት፤ የሐሰት ምስክሮችንም አቁመው ፈረዱበት:: (ዮሐ.፲፬፥፲፪)

ልጆች! አይሁድ በሕጋቸው ወንጀለኛ ነው የሚሉትን ሰው የሚፈርዱበት በድንጋይ ተወግሮ እንዲሞት ነበር፤ በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይም ይህንን ፍርድ ፈረዱበት፤ እውነትን በማስተማሩ፣ስለክርስቶስ በመመስከሩ፣ ጠንቋዮችን፣ ሐሰተኞችን በመቃወሙ ‹‹ወንጀለኛ ነው፤ ሕጋችንን ተላልፏል፤ ሰድቦናል›› በማለት በድንጋይ ተወግሮ እንዲሞት ፈረዱበት፡፡ ከዚያም ከከተማው በስተውጭ አውጥተው ድንጋይ እያነሱ ይወግሩት (ይደበድቡት) ጀመር፤ በጣም ብዙ ድንጋዮች ተከመሩበት፤ ልጆች! የሚገርማችሁ በድንጋይ እየወገሩት፣ እየፈነከቱ ሲያደሙት እርሱ ግን ስለእነርሱ ይጸልይ ነበር፤ ልክ ጌታችንን በመስቀል ላይ ሰቅለውት ግፍ ሲፈጽሙበት ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› እንዳለው እርሱም ወደ ሰማይ ዓይኖቹን አቅንቶ ‹‹ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው…›› በማለት ይጸልይላቸው ነበር፡፡ (ሉቃ.፳፫፥፴፬) በጣም ስለደበደቡት በሰማዕትነት ዐረፈ፤ ይህ የሆነውም በተወለደበት ጥር አንድ ቀን ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት እንዲሁ አልቀረም፤ ባለማወቅም ከሚያጠፉት መካከል አንዱ የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ ስሕተቱ ተመልሶ ክርስቲያን በመሆን ወንጌልን አስተምሮና ብዙ መልእክታትን ጽፎ እርሱም በሰማዕትነት አርፏል፤ ቅዱስ እስጢፋኖስ በሰማዕትነት በማረፉ ብዙ ክርስቲያኖች በተለያየ አህጉር ተበተኑ፤ በዚህም የተነሣ በሄዱበት ቦታ ሁሉ ማስተማር ጀመሩ፤ ክርስቲያኖችም በዙ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ብዙ ቃልኪዳን ገብቶለታል ‹‹እኔን መከተል የሚወድ እራሱን ይናቅ፤ መስቀሌንም ተሸክሞ ይከተለኝ›› ያለውን አማናዊ ቃል ሰምቶ ለሙሽራው ለክርስቶስ ፍቅር እራሱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ (ማቴ.፲፮፥፳፬) ስለዚህ እኛም አምላክን ያከበሩ ቅዱሳንን እናከብራቸዋለን፤ ፍለጋቸውን እንከተላለን፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱሳን ሰማዕታትን በእምነት በምግባር እንመስላቸው ዘንድ ይገባል፤ ከቅዱስ እስጢፋኖስ ብዙ ነገር እንማራለን፤ በሥነ ምግባር የታነጽን፣ እምነታችን የጸና፣ ለወላጆቻችን ታዛዥ ልጆች ሆነን ማደግ አለብን፡፡ ቅዱስ እስጠፋኖስ እናቱና አባቱ  የሚያስተምሩትን የክርስትና ትምህርት በደንብ ያደምጥ ስለነበር መከራ በገጠመው ጊዜ በእምነት መጽናት እንዳለበት ተረድቷል፤ አያችሁ ልጆች! የተማረውን ትምህርት ሳይረሳ በሕይወቱ ተገበረው፤ የሃይማኖት ጽናትንም ለብዙዎች አስተማረ፤ እኛም ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ከእኛ በፊት የነበሩ ክርስቲያኖቸ እንዴት ይኖሩ እንደነበረ ጠይቀን በመረዳት እንደነርሱ ልንሆን ይገባል፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ የይቅርታ ሰውም ነበር፤ ለበደሉት ይቅርታ አድርጎ ምሕረትን ለመኖላቸዋልና፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ እስጢፋኖስ የይቅርታ ሰው እንደነበር ሁሉ እኛም  ቂም በቀልን መያዝ እንደሌለብን ከዚህ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ጎዱን የምንላቸውን መልሰን መጉዳት የለብንም፤ የሰላም፣ የፍቅርና የይቅርታ ሰዎች ልንሆን ይገባል፤ ያወቅነውን ለሌሎች ማሳወቅ፣ ሰዎችን በጸሎት መርዳት፣ ስለ እውነት መመስከር አለብን!

አምላከ ቅዱስ እስጢፋኖስ በረከቱን ያድለን አሜን!!! ቸር ይግጠመን፡፡

ምንጭ:- መጽሐፍ ቅዱስ (የሐዋርያት ሥራ አንድምታ)፣ መዝገበ ቅዱሳን

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!