ቅዱስ መስቀል

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

መስከረም ፲፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ አሸጋግሮ በሰላም ለዚህ ዕለት አደረሳችሁ! ዕንቁጣጣሽ እንዴት አለፈ? መቼም ደስ ብሏችሁ እንዳሳለፋችሁ ተስፋችን እሙን ነው፡።  መልካም! የአዲስ ዓመት ትምህርት ለመጀመር እንዴት እየተዘጋጃችሁ ነው? ባለፈው ዓመት በትምህርታችን ደከም ያለ ውጤት አስመዝግበን የነበርን ዘንድሮ በርትተን በመማር በጥሩ ውጤት ከክፍል ክፍል ለመሻገር ከአሁኑ ማቀድና መበርታት አለብን፡፡ እንዲሁም ደግሞ ለአገርና ለቤተ ክርስቲያን እየጸለይን የሰላምን ዘመን ተስፋ እናድርግ! መልካም!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ባለፉት ጊዜያት ለእናንተ ያስተምራሉ በማለት በጻፍንላችሁ በርካታ ቁም ነገሮችን ስንማማር እንደነበር ታስታውሳላችሁ አይደል? አሁን ደግሞ ስለ ቅዱስ መስቀሉ በዓል ጥቂት ልናካፍላችሁ ወደድን፤ መልካም ቆይታ!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዐደባባይ ከሚከበሩ በዓላት አንዱ የቅዱስ መስቀል (የደመራ) በዓል ነው፡፡ ቅዱስ መስቀል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን የተሰቀለበትና በክቡር ደሙ የቀደሰው ጠላታችን ዲያብሎስን ድል የምናደርግበት ነው፡፡ ቅዱስ መስቀል የሰላም አርማችን፣ ጠላታችን ሰይጣንን የምንመክትበት ጋሻችን ነው፡፡ ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ መስቀል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ እኛን ከሰይጣን ባርነት፣ ከሲኦል እስራት ነጻ ካወጣን በኋላ ቅዱስ መስቀል በጌታችን ክቡር ደም ተቀድሷልና ብዙ ተአምራትን አደረገ፡፡ ይህን ጊዜ ጌታችንን ያለበደሉ በመስቀል የሰቀሉት ሰዎች  ቅዱስ መስቀሉ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ሲያደርግና የታመሙት ሲፈወሱበት ሲመለከቱ ሰይጣን ለተንኮል አነሣሣቸው፤ ቅዱስ መስቀሉንም ትልቅ ጉድጓድ አስቆፍረው ቀበሩት፡፡

ከዚያም ልጆች በጌታችን ያላመኑ ሰዎች ቆሻሻ እያመጡ በቦታው ላይ እንዲጥሉበት አደረጉ፡፡ ይገርማችኋል የእግዚአብሔር ልጆች! ሁለት መቶ ዘጠና ዓመታት ያህል ያ ቦታ የቆሻሻ መጣያ ሆነ፡፡ ከዚያም ከቆሻሻው ብዛት የተነሣ ቦታው ተራራ አከለ፤ በክርስቲያኖች ላይም ያላመኑ ሰዎች ብዙ መከራ ያደረሱባቸው ጀመር፡፡ እግዚአብሔር ባወቀ ለብዙ ዘመናት ቅዱስ መስቀል በዚያ ተቀብሮ ቆየ፡፡ በክርስቲያኖች ላይ መከራ ያደርስባቸው የነበረው ክፉው ንጉሥ አለፈና ቆስጠንጢኖስ የተባለ ንጉሥ ነገሠ:: ይህ ንጉሥ እናቱ ንግሥት ዕሌኒ እግዚአብሔርን የምታመልክ ክርስቲያን የሆነች ደግና መልካም ሴት ነበረች፡፡ ንግሥት ዕሌኒ  ልጇ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ገና ክርስትና አልተነሣም ነበርና ልጇ ክርስቲያን እንዲሆንላት ወደ እግዚአብሔር ጸለየች፤ ልጇም አምኖ ተጠመቀ፤ ከጠላቶቹ ጋር ጦርነት በሚገጥም ጊዜ በጦር መሣሪያው ላይ የመስቀልን ምልክት በማድረግ ድል ያደርግ ነበር፡፡ ንግሥት ዕሌኒ እግዚአብሔር ለዚህ ክብር ልጇን ስላበቃላት ለውለታው መታሰቢያ እንዲሆን ለብዙ ዘመናት ታሪኩ ተረስቶ የነበረውን ቅዱስ መስቀል ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች፡፡

ለንግሥት ዕሌኒ ልጇ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ሠራዊት መድቦላት ቅዱስ መስቀሉን ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች፤ ኢየሩሳሌምም በደረሰች ጊዜ ከሁለት መቶ ዘጠና ዓመታት በፊት መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ተሰቅሎ ዓለምን ያዳነበትና በክቡር ደሙ የቀደሰው ቅዱስ መስቀል ወዴት እንደደረሰ ታጠያይቅ ጀመር፤ ብዙ አረጋውያንን ጠየቀች፤ አየው፤ ሰማው የሚል ሰው ግን ለጊዜው ማግኘት አልቻለችም ነበር፤ ተስፋ ባለመቁረጥ ፍለጋዋን ቀጠለች፡፡ በመጨረሻም ኪራኮስ የተባለ አረጋዊ አግኝታ ስለ መስቀሉ ታሪክ ጠየቀችው፤ በመጀመሪያ ሰውየው ሊነግራት ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ እርሷም በየዓይነቱ ብዙ ከፈተነችወና ካስገደደችው በኋላ ከአባቶቹ የሰማውን የመስቀሉን ታሪክ ነገራት፡፡ አይሁድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል በቅንዓት ተነሣስተው፣ ጉድጓድ ቆፍረው እንደቀበሩትና ሕዝቡም በዚያ ጉድጓድ ቆሻሻ እንዲጥል እንዳስደረጉ ነገራት፤ በቦታውም ሦስት ተራሮች ነበሩና እነዚህን ተራሮች አመለከታት፡፡ ‹‹ከእነዚያ ተራሮች የጌታዬ መስቀል የት እንዳለ እርሱ ያመለክተን ዘንድ እንጸልይ›› ብላ  ደመራ አስደመረች፤ ጸሎት ተደረገና በውስጡ ዕጣን ተጨምሮ ደመራውም ተለኮሰ፡፡ ይገርማችኋል የእግዚአብሔር ልጆች! የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ወጣና ተመልሶ ወደ ምድር መጣና የጌታችን ቅዱስ መስቀል ያለበትን ተራራ አመለከተ፤ ከዚያም ቁፋሮ ተጀመረ፡፡ መጋቢት ዐሥር ቀንም ሦስት መስቀሎች ተገኙ፡፡ አንዱ መስቀልም ወንበዴው ጥጦስ የተሰቀለበት ነው፤ አንዱ መስቀል ደግሞ ወንበዴው ዳክርስ የተሰቀለበት ነው፤ ክብር ይግባውና ጌታችን የተሰቀለበት መስቀልም አብሮ ነበር፡፡ ስለዚህ ንግሥት ዕሌኒ የጌታችንን መስቀል ለመለየት የሞተ ሰው ሬሳ አስመጥታስ መስቀሉን በላያቸው አደረገችባቸው፡፡ የጌታችን ቅዱስ መስቀልም ሙቱን አነሣው፤ ሰባት ቀንም ዓለም በብርሃንም መላች፤ ብዙ ሕሙማን ተፈወሱ፤ ማየት የማይችሉም በቅዱስ መስቀሉ ተፈውሰው አዩ፤ ንግሥት ዕሌኒም እግዚአብሔርን አመሰገነች፡፡ ከዚያም በዚያ ቦታ ቤተ ክርስቲያን እንዲታነጽ አደረገችና መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ መስከረም ዐሥራ ስድስት ቀን ደመራ የሚደመረው ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉ የተቀበረበትን ተራራ እንዲገልጽላት ደመራ ደምራና ዕጣን ጨምራ ከለኮሰች በኋላ መስቀሉ ያለበት ቦታ የታወቀበትና ቁፋሮ የተጀመረበት ስለሆነ ነው፡፡ መጋቢት ዐሥር ደግሞ ቅዱስ መስቀሉ ከተቀበረበት የወጣበት መስከረም ዐሥራ ሰባት ቤተ ክርስቲያን ታንጾ አገልግሎት የተጀመረበት (ቅዳሴ ቤቱ) ነው፡፡ አያችሁ ልጆች! ቅድስት ቤተ ክርስቲያን (አባቶቻችን) ባቆዩልን ሥርዓት መሠረት ሁል ጊዜ መስከረም ዐሥራ ስድስት ቀን ደመራ ተደምሮ በዓሉ ይዘከራል፤ መጋቢት ዐሥር ቀንም የቅዱስ መስቀል ክብረ በዓል ይከበራል፡፡

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ከንግሥት ዕሌኒ እና ከልጇ ከንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ምን እንማራለን? እግዚአብሔር ያደረገላትን ውለታ አስታውሳ አይሁድ በምቀኝነት የቀበሩትን ቅዱስ መስቀል ከተቀበረበት እንዲወጣና ሕሙማን እንዲፈወሱበት አድርጋለች፡፡ ንግሥት ቅድስት ዕሌኒ ጸሎተኛ፣ መልካምና ደግ ክርስቲያን በመሆኗ እግዚአብሔር ለዚህ ክብር አበቃት፡፡ መልካም፣ ታማኝና ታዛዥ መሆን ከራስም አልፎ ለሌላውም ሰው ይጠቅማልና ልጆች! በሕይወታችን ሁል ጊዜ ሰዎችን የምንወድ፣ የምናከብር፣ በማንኛውም ቦታ ታማኞች፣ ደግ፣ ለሰዎች አሳቢና ለወላጆቻችንን የምንታዘዝ ልንሆን ይገባል፡፡ ልጆች! መማራችንና ማወቃችን ለመልካም መሆን አለበት፤ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ መስቀልን ይዞ ጠላቶቹን ድል እንዳደረገ እኛም በቅዱስ መስቀል እንባረካለን፡፡ ማንኛውንም ተግባር ስንጀምር በስመ ቅድስት ሥላሴ በቅዱስ መስቀል አማትበን ከጀመርን ሁሉ ይባረካል፤ ያሰብነው መልካም ነገር ሁሉ ይሳካል፤ ጠላታችን ሰይጣንም ወደ እኛ አይቀርብም፤ ቅዱስ መስቀሉን በአንገታችን እናስረዋለን፤ እናማትብበታለን፤ የሰይጣንን ጦር እንመክትበታለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች ስለ ቅዱስ መስቀል ታሪክ በአጭሩ ጻፍንላችሁ፡፡ ይህን ወቅት ጌታችን ለእኛ የሠራልንን ውለታ እያሰብን እኛም ለሰዎች መልካም በማድረግ፣ አብዝተን ለአገራችን ሰላምና ለሕዝባችን ፍቅር እየጸለይን እናሳልፍ ዘንድ ይገባናል፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ከቅዱስ መስቀሉ፣ ከንግሥት ቅድስት ዕሌኒና ከልጇ ረድኤት በረከቱን ያድለን! ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!