ቅድስት አርሴማ

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

መስከረም ፳፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለከበረው ጤንነታችሁ እንዴት አላችሁ! የክረምት ወቅት አልፎ አዲሱን ዓመት ተቀብለናልና ለዚህ ያደረሰንን ፈጣሪያችንን ማመስገን ይገባል! ልጆች! መስቀል በዓል እንዴት ነበር? በሰላም በፍቅር አከበራችሁ አይደል? የእኛን ምክርም ተቀብላችሁ ለመጪው የትምህርት ዘመን ዝግጅት ስታደርጉ እንደቆያችሁ ደግሞ ተስፋችን ነው፡፡ አሁን ደግሞ ትምህርት ስለጀመራችሁ በርትታችሁ መማርን እንዳትዘንጉ! ከአሁኑ ጀምራችሁ መምህራን የሚነግሯችሁን በንቃት ተከታተሉ፤ መጻሕፍትን አንብቡ፤ ያልገባችሁን ጠይቁ፤ የቤት ሥራችሁን በአግባቡ ሥሩ፤ የጨዋታ ጊዜያችሁንና ቴሌቪዥን የምታዩበትን ጊዜ መቀነስ አለባችሁ፤ አሁን የእናንተ ተግባር፣ እይታ፣ ሥራ፣ ጉዳይ ሁሉ ትምህርት እና ትምህርት ብቻ ስለሆነ ጎበዝ ተማሪዎች ሁኑ፤ መልካም!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ ያዘጋጀንላችሁ ታሪክ የቅድስት አርሴማን ነው፤ የቅድስት አርሴማ እናት ቅድስት አትናሲያ አባቷ ቅዱስ ቴዎድሮስ ይባላሉ፤ እናትና አባቷ  እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ከካህናት ወገን የሆኑ መልካም ምግባር የነበራቸው  ነበሩ፤ ልጅ ስላልነበራቸው ልጅ እንዲወልዱ ስዕለትን ተሳሉ፤ እግዚአብሔርም ልጅን ሰጣቸው፡፡ በሥነ ምግባርና ብሉይና አዲስ ኪዳንን  እያስተማሯት  አደገች፡፡ ልጆች! በሥነ ምግባር ታንጻችሁ ለማደግ  ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ይገባል፤ አባቶችን ጠይቁ በቤት ውስጥ፣ በሠፈራችሁ፣ በትምህርት ቤት በሁሉ ነገር ታላቆችን አክባሪና ጨዋዎች ታዛዦች ልጆች ሁኑ፤ እግዚአብሔር ይባርኳችኋልና!

ልጆች! ቅድስት አርሴማ በጥሩ ሥነ ምግባር ካደገች በኋላ ለወላጆቿ እየታዘዘች በሥርዓት ኖረች፡፡  ጾመኛ፣ ጸሎተኛ፣ ደግ ሴትም ነበረች፡፡ ለሰዎችም ታዝን ነበር፤ ካደገች በኋላ ደግሞ በድንግልና ሕይወት መኖርን መረጠች፤ መንኩሳም በገዳም ታገለግል ጀመር፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እርሷ በነበረችበት ዘመን ዲዮቅልጥያኖስ የተባለ ጨካኝ ንጉሥ ነበር፤ ክርስቲያኖችን ለጣዖት ስግዱ እያለ መከራ አጸናባቸው፤ ቅድስት አርሴማ እና ሃያ ሰባት ደናግል በገዳም በጾም በጸሎት በነበሩ ግዜ ጨካኙ ንጉሥ በሰይጣን ተገፋፍቶ ቅድስት አርሴማን ሊያገባት ፈለገ፡፡ እርሷ ግን በድንግልና ሕይወት መንኩሳ መኖርን መርጣ ነበርና ከጓደኞቿ ጋር ሆና አርማንያ ወደ ተባለ አገር ተሰደዱ፡፡

ይገርማችኋል ልጆች! ለጊዜው ከጨካኙ ንጉሥ አምልጠው በገዳም ውስጥ በጾም በጸሎት ተግተው ሳለ ንጉሡ ለአርማንያ አገረ ገዢ ለንጉሥ ድርጣድስ መልእክት ላከ፤ ‹‹አንተ አገር ተሰደው የመጡ ደናግል  አሉና ይዘህ ላክልን›› አለው፤ ከዚያም አፈላልገው ቅድስት አርሴማን  አገኟት፤ ድርጣድስ ባያት ጊዜ ከደም ግባቷ ማማር የተነሣ ‹‹ላግባሽ›› ብሎ ጠየቃት፤ እርሷም ‹‹እኔ በድንግልና ሕይወት የምኖር የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ፤ ማግባት አልፈልግም›› አለችው:: በግድ አስገድዶ ሊያገባት ሲሞክር እጁን ጠምዝዛ በዐደባባይ ጣለችው፤ በዚህን ጊዜ በጣም አፈረ፤ በእርሷ እና በጓደኞቿ ደናግል መከራ እንዲያጸኑባቸውም አዘዘ፡፡ አንበሶች እንዲበሏቸው አንበሳ ካለበት ከተቷቸው፤ አንበሶቹ ግን ሳይበሏቸው ቀሩ፤ ዳግመኛም በረኃብ እንዲሞቱ ምንም መብልና መጠጥ በሌለበት ቤት አሠሯቸው፤ እግዚአብሔርም የሚበሉትን በሞሶብ የሚጠጡትን በጽዋ ከሰማይ አወረደላቸው፤ ከእሳትም ሲጨመሯቸው ደግሞ እሳቱ አላቀጠላቸውም፤ ይህን ድንቅ ተአምር እግዚአብሔር አድርጎላቸው፤ ከግፈኞች እጅ አስጣላቸው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በደናግሉ ይህ ሁሉ መከራ ደርሶ ለጣዖት ባለመስገዳቸው አሁንም ድርጣድስ የተባለውን ንጉሥ አበሳጨው፤ ቅድስት አርሴማን ለማስፈራራት ብሎ አብረዋት የነበሩትን ጓደኞቿን አንድ በአንድ በግፍ በሰይፍ ቀላቸው፤ ለሚሰውት (ለሚገደሉት) ሁሉ አክሊል ከሰማይ ይወርድላቸው ነበር፤ ቅድስት አርሴማም ‹‹ይህን እያየች አይዟችሁ ጽኑ›› ትላቸው ነበር፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ንጉሡም በቁጣ ቅድስት አርሴማን ‹‹አንቺን እንደነርሱ በቀላሉ አልገድልሽም›› በማለት ብዙ መከራ አጸናባት፣ ዓይኖቿን አወጣ፤ በብዙ ዓይነት ሥቃይም አሠቃያት፤ ስለስሙ በመመስከሯ፣ በድንግልና ሕይወት በመጽናቷ፣ የዚህን ዓለም ኑሮ ንቃ በብሕትውና በመኖሯ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ቃል ኪዳን ገባላት፤ ስሟን ጠርቶ የሚማጸን፣ ገድሏን የጻፈ ያነበበ፣ የሰማ፣ በስሟ የመጸወተውን እንደሚምርላት ቃል ኪዳን ሰጣት፤ በመስከረም ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀንም በሰይፍ ተሰይፋ ሰማዕትነትን ተቀብላለች፡፡

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! እናታችን ቅድስት አርሴማ ለሰዎ ልጆች ድኅነት ፈጣሪን ተማጽና ምሕረትን አሰጥታለች፤ በዘመኗ ብዙ ድንቅ ተአምራትን አድርጋለች፤ መከራ ላደረሱባትም ጸልያለች፤ ከብዙ ዘመን በኋላም እርሷን እንድትገደል ያደረገው ጨካኙ ንጉሥ ድርጣድስ ከክፉ ሥራው ተመልሶ ንስሓ ገብቶ እርሱም ስለ ክርስቶስ መስክሮ ለክብር ሕይወት በቅቷል፡፡ በእናታችን ቅድስት አርሴማ መከራ ላደረሱባት በመጸለይዋ ሳያውቁ ይሠሩት ከነበረው ክፉ ሥራቸው እንዲመለሱ አድርጋቸዋለች፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከቅድስት አርሴማ ታሪክ ምን እንማራለን? ወላጆቻችንን እኛ በሥርዓት፣ በጥሩ ሥነ ምግባር፣ በንጽሕና አድገን የእኛን መልካም ነገር፣ ደስታ ወግ ማዕረግን ማየት ይፈልጋሉ፤ ታዲያ እኛም ጥሩ ሥነ ምግባር ያለን ራሳችንን ከከንቱ፣ ከክፉ ነገር በመጠበቅ መኖር ይጠበቅብናል ቅድስት አርሴማ ብሉይና አዲስን እየተማረች አድጋለች፤ እኛም ከዘመናዊ ትምህርታችን በተጓዳኝ በቤተ ክርስቲያን እየተማርን ልናድግና ስለ ሃይማኖታችን ልንገነዘብ ይገባናል፤ ያኔ ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው ልጆች ሆነን እናድጋለን፡፡ የእኛ መልካም ሕይወት ለራሳችንም ለቤተሰብ አልፎም ለአገራችን ይተርፋልና ይህን ተገንዝበን ማወቅ ያለብንን ለማወቅ እንጣር፡፡ ወላጆቻችን ስለሚያደርጉልን ነገር ሁሉ ከእኛ ምንም ዓይነት ክፍያን አይጠብቁም፤ የእነርሱ ደስታ የእኛ መልካም፣ ጎበዝ፣ ብልህ፣ በእምነቱ የጸና፣ በምግባሩ የጎለበተ ልጅ ሆነን ማየቱ ብቻ ነው፡፡ ቅድስት አርሴማ ክፉ ላደረጉባት ጸልያለች፤ እኛም ይቅርባይ ቂም በቀልን የማንወድ ለሰዎች መልካም ነገርን የምንመኝ ልንሆነ ይገባል፡፡ ሰዎች ከክፉ ተግባራቸው እንዲመለሱ ልናግዛቸው ይገባል፤ ጸሎትን ጠዋት ከመኝታ ስንነሣ፣ ቀንም፣ ማታም ስንተኛ አብዝቶ መጸለይ አለብን፡፡

እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች! የቅዱሳን ታሪክ የሕይወት ተጋድሎ፣ ክብራቸውን የምንማረው እኛም እንደነርሱ ራሳችንን ከክፉ ነገር ጠብቀን መልካም ሠርተን መኖር እንዲቻለን ነውና፡፡ በምንማረው ትምህርት ቅዱሳንን አርአያ ልናደርጋቸው ይገባል፤ ትሑታን፣ ሰዎችን አክባሪ፣ በመሆን በቤተ ክርስቲያን እያገለገልን ልናድግ ይገባናል፡፡

እንግዲህ ለዛሬ በዚህ አበቃን! ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! ከቅድስት አርሴማ እና አብረዋት ሰማዕት ከሆኑ ሃያ ሰባቱ ሰማዕታት ረድኤት በረከታቸውን ይክፈለን! መልካም የትምህርት ዘመን  ይሁንላችሁ!

 ምንጭ፡- ገድለ ቅድስት አርሴማ፣ስንክሳር ታኅሣሥ ስድስት

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!