‹‹ስለምጽፍላችሁ ነገር እነሆ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም›› (ገላ.፩፥፳)

 ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ጥቅምት ፳፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? እየበረታችሁ ነውን? መምህራን የሚነግሯችሁን በትኩረት በማዳመጥ፣ መጻሕፍትን በማንበብና ያልገባችሁን በመጠየቅ ትላንት ከነበራችሁ ግንዛቤ የተሻለ ዕውቀትን እየቀሰማችሁ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን! መልካም!

ውድ የእግአብሔር ልጆች! ባለፉት ጊዜያት በዓላትን አስመልክተን የቅዱሳንን ታሪክ አዘጋጅተን ባቀረብንላችሁ መሠረት ከቅዱሳን የሕይወት ታሪክ በርካታ ቁም ነገሮችን ስንማማር እንደነበር ታስታውሳላችሁ አይደል? በተለይ ሥርዓትን አክብረን መኖረ እንደሚገባን፣ በቤተ እግዚአብሔር  መኖር ደግሞ ታላቅ በረከትን እንደሚያስገኝልን፣ ለቅዱሳን ስለተሰጣቸው ክብርና የቅድስና ሕይወታቸው ምን እንደሚመስል ተመልክተናል፡፡ ለዛሬ ደግሞ ያዘጋጀንላችሁ እጅግ ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ሲሆን ሐሰት መናገር እንደማይገባ እንዲሁም እውነተኛና ታማኝ መሆን እንዳለብን ልናስተምራችሁ ወደድን፤  በጥሞና ተከታተሉን!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አምላካችን እግዚአብሔር እንድንፈጽመው ካዘዘን ሥነ ምግባራት አንዱ እውነትን መናገርና እውነተኞች መሆንን ነው፤ ስለዚህም ለሊቀ ነቢያት ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ከሰጠው (ከነገረው) ዐሥርቱ ትእዛዛት አንዱን ‹‹በሐሰት አትመስክር›› በማለት እውነተኛ እንዲሆንና ሐሰትን ሕዝቡ እንዳይናገሩ፣ አንዱ አንዱን ሰው እንዳይዋሸው፣ መተማመን እንዲኖር በማለት አዞታል፡፡ (ዘፀ.፳፥፲፮)

ውድ እገግዚአብሔር ልጆች! ሐሰት መናገር ተገቢ አይደለም፤ ምክንያቱም በዋሸን (ሐሰትን በተናገርን) ጊዜ የምንዋሸው ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሐሰት እንዳንናገር ያዘዘንን ፈጣሪንም ጭምር ነውና፡፡ ሰዎችን መዋሸት በሰዎች ፊት ሐሰትን በመናገርና እውነተኛ መስሎ ለመታየት በመሞከር የምናታልለው ራሳችንንም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ በምንም ምክንያት ሐሰትን መከተል፣ ሐሰትን መምረጥ፣ ሐሰትን መናገር የለብንም፡፡ ሐሰተኛ እና የሐሰት (የውሸት) አባቷ ዲያብሎስ እንደሆነ ጌታችን እንዲህ በማለት ነግሮናል፤ ‹‹….ከዲያቢሎስ እውነት በእርሱ ስለሌለ በእውነትም አልቆመም፤ ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፤ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነው…›› (ዮሐ.፰፥፵፬)

ውድ የእግአብሔር ልጆች! ታደጊዎች እንደመሆናችሁ መጠን ልታጠፉ፣ የማይገባ ነገር ልታደርጉና ድንገት ልትሳሳቱ ትችላላችሁ፡፡ ታዲያ ጥፋታችሁን ለመሸፈን ሐሰትን (ውሸትን) በመናገር ሌላ ጥፋት መሥራት የለባችሁም፡፡ ይልቁንስ ምን መሰላችሁ ማድረግ ያለባችሁ? ስላጠፋችሁት ጥፋት ይቅርታን መጠየቅ ነው፡፡ ሐሰትን መናገር ከለመደባችሁ ወደ መጥፎ ሕይወት ትገባላችሁ፤ በሰዎች ዘንድ መታመንንም አታገኙም፡፡ እውነተኞች ከሆናችሁ ግን ሰዎች ያምኗችኋል፡፡ ስለጥፋታችሁ ከመዋሸት ይልቅ ይቅርታ ብትጠይቁ  ክብርንና መውደድን ታናገኛላችሁ፡፡ በልጅነታችሁ ታማኞች ከሆናችሁ ወደፊት ስታድጉ ስኬታማና ደስተኛ ሰዎች ትሆናላችሁ፡፡ እግዚአብሔርም እውነተኛነታችሁን አይቶ በምድርም ክብር ይሰጣችኋል፡፡  በሰዎች ዘንድ መታመንንና መከበርን ይሰጣችኋል፡፡ ስለዚህ በምንም ምክንያት ሐሰትን መናገር አይገባም፡፡ የምትፈልጉትን ነገር ከወላጆቻችሁ በአግባቡ መጠየቅ እንጂ ተደብቃችሁና ሰው ስለማያያችሁ ብትዋሹ በሁሉ ቦታ የሚገኝ እግዚአብሔር ስለሚመለከት እርሱን ታስከፉታላችሁ፤ ስለዚህ በቤት፣ በሰፈር፣ በትምህርት ቤት ውስጥና በሁሉ ቦታ ታማኞችና እውነተኞች መሆን ይገባል፤ ሐሰትን በፍጹም መናገር የለብንም፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በመጽሐፍ ቅዱስ የብዙ ታማኝ አባቶችንና እናቶች ታሪክ እናገኛለን፤ በመታመናቸውና ሐሰትን ባለመናገራቸው እውነተኞች በመሆናቸው እግዚአብሔር አክብሯቸዋል፤  ለበለጠ ለታላቅ ኃላፊነትም መርጧቸዋል፤ ሐሰትን የሚናገሩ ሰዎች ደግሞ ተቀጥተዋል፡፡  ለምሳሌ ብንመለከት በመጽሐፈ ሶስና ላይ ታሪኳን የምናገኘው ሶስና የተባለች ደግ፣ እግዚአብሔርን የምትፈራ፣ ታማኝ እውነተኛ ሴት ነበረች፡፡ ሰዎች ግን ምንም ሳታጠፋ በቅናት ተነሣሥተው  እንድትቀጣ ፈለጉና በሐሰት ያልሠራችውን ጥፋት ሠርታለች አሉ፡፡ ከዚያም ሦስት ምስክሮች መጡና በሐሰት (በውሸት) በመመሰከር ሐሰትን ተናገሩ፡፡ ከዚያም በሶስና ላይ ቅጣት ሊፈረድባት ሲል እውነተኛ የሆነ የእገግዚአብሔር አገልጋይ ነበዩ ዳንኤል መጣና በሶስና ላይ ከመፈረዱ በፊት ምስክሮቹ እውነተኛ መሆናቸው መጣራት እንዳለበት ተናገረ፡፡ ከዚያም ለየብቻ የሠራችውን ጥፋት በየት ቦታ እንደፈጸመችው እንዲናገሩ ተጠየቁ፤ ይገርማችኋል የእግዚአብሔር ልጆች! ሦስቱም ውሸታሞች ስለነበሩና በሐሰት ስለመሠከሩ የተለያየ ነገር ተናገሩ፤ ከዚህም በኋላ ሐሰተኞች መሆናቸው ተጋለጠ፤ እነርሱም አፈሩ፤ በዚህም አላበቃም በሶስና ላይ ሊፈረድ የነበረው ቅጣት በእነርሱ ተፈረደ፡፡  እርሷ እውነተኛ ስለነበረች ለጊዜው ቢያስጨንቋትም እግዚአብሔር አውነተኛ መሆኗን በነቢዩ ዳንኤል አማካኝነት ገለጸላት፡፡ እነዚያ ሐሰተኛ ምስክሮች ከመጋለጣቸውም ባሻገር በመዋሸታቸው ከባድ ቅጣት ተቀጡ፡፡ (ሶስ.፩፥፩-፷፫)

ልጆች! ሐሰትን መናገር ያስቀጣል፤ ለመከራ (ለችግር) ይዳርጋል፤ ሁል ጊዜ ታማኞች እወነትን የምንናገር ሊሆን ይገባል፤ ባላየነውና ባልሰማነው ነገር ሐሰትን መናገር(መዋሸት) አይገባም፡፡ ብናጠፋ እንኳን ጥፋታችንን ለመደበቅ መዋሸት (ሐሰትን መናገር) የለብንም፤ ጨዋዎችና ታማኞች ልንሆን ይገባል፡፡ የዚህን ጊዜ በሁሉ ዘንድ ክብርን፣ አመኔታን እናገኛለን፤ መታመን ደግሞ መታደል ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎምን ‹‹..ሐሰተኛ ምስክር ሳይቀጣ አይቀረም፤ በሐሰትም የሚናገር ይጠፋል›› በማለት እንደገለጸው እንዳንቀጣ ሐሰትን ከመናገር እንታቀብ (እንከልከል)፡፡ (ምሳ.፲፱፥፱ )

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! የማንዋሽ (ሐሰትን የማንናገር) ከሆነና እውነተኛውን ነገር በግልጽ የምንጠይቅ ከሆነ በሁሉ ዘንድ ታምነን ለታላቅ ኃላፊነት እንመረጣለን፡፡  ከምንም በላይ ደግሞ በሕይወታችን ደስተኞች እንሆናለን፤ ሳንሰቀቅ (ሳንሸማቀቅ፣ ሳናፍር) ከሁሉ ጋር በፍቅር መኖር እንችላለን፡፡ ሐሰት መናገር መጥፎና ኃጢአት ነው፡፡ በራሳችን የመተማመን ስሜታችንን ያሳጣናል፤ እንዳንታመን ያደርገናል፤ ሰዎችን ባየን ቁጥር ‹‹አወቁብን ወይስ አላወቁም›› በማለት በሰቀቀንና በጭንቀት እንድንኖር ያደርገናል፤ ይሄ ደግሞ ለከፋና ለበለጠ ችግር ያጋልጠናል፡፡ ስለዚህ ደስተኛ ለመሆንና ከሰዎች ጋር በፍቅርና በሰላም ለመኖር እውነተኞች ልንሆን ይገባል፡፡ ሐሰትን ከሕይወታችን ማራቅ አለብን! ጻድቁ ኢዮብ ‹‹..ሐሰትን የሚናገሯትን ታጠፋቸዋለች…››  እንደገለጸው ሐሰትን የምንናገራት ከሆነ የምንጎዳው እኛ ነን፤ (ኢዮ.፭፥፮) ስለዚህ ሐሰትን እንጥላ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ አገር ለሚኖሩ ምእመናን በጻፈላቸው መልእክት ‹‹በእግዚአብሔር ፊት ሐሰትን አልናገርም››  አላቸው፡፡ ሰዎችን መዋሸት እግዚአብሔርን መዋሸት ስለሆነ ሐሰትን አልነግራችሁም፤ እውነትን ነው የምነግራችሁ አላቸው። እኛም በሕይወታችን ሐሰትን ሳይሆን ለሰዎች እውነትን እንንገራቸው ፡፡ ለወላጆቻችን፣ ለታላላቅ ወንድሞቻችን፣ ለእህቶቻችንና ለመምህራኖቻችን ምንም ነገር ሲገጥመን እውነቱን እንንገራቸው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ስለ ሐሰት በአጭሩ ያዘጋጀንላችሁን ምክር በዚህ አበቃን፡፡ በተማርነው መሠረት እውነትን የምንከተልና ሐሰትን የምንጠላ ሆነን እንድናድግ እግዚአብሔር ይርዳን፤ አሜን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!