በእመቤት ፈለገ
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች ? ዛሬ የምንነግራችሁ በጣም ደስ ስለሚለው ነጭ የበግ ግልገል ነው፡፡
በአንድ ወቅት አብረው ይኖሩ የነበሩ መቶ በጎች ነበሩ፡፡ ከነዚህ በጎች መካከል ሻሼ የተባለ በጣም ደስ የሚል እና ከጓደኞቹ በጎች ጋር መጫወት የሚወድ ነበር፡፡ በጣም የሚወዳቸው እናት እና አባት ነበሩት፡፡ ሌሎቹም እንደራሱ ወንድም እና እህት ነበር የሚያያቸው፡፡
እነዚህ መቶ በጎችን እጅግ በጣም የሚወዳቸው፤ ሌሎች እንስሳት ጉዳት እንዳያደርሱባቸው የሚጠብቃቸው እና ጥሩ ምግብ እና መጠጥ ሊያገኙበት ወደሚችሉት ቦታ የሚወስዳቸው ጎበዝ እረኛ ነበር፡፡ በእየለቱም ከመካከላቸው የጎደለ በግ እንዳይኖር 1፣2፣3፣ …. 1ዐዐ እያለ ይቆጥራቸው ነበር፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ጎበዙ እረኛ በጎቹን ይዞ በጣም ደስ ወደሚል ቦታ ወሰዳቸው፡፡ በጎቹም ወዲያው ቦታውን ሲያዩት እጅግ በጣም አስደሰታቸው፡፡ እየበሉ እና እየጠጡ መጫወት ጀመሩ፡፡ እነ ሻሼ በመጫወት ላይ እያሉ ከሌላ ቦታ የመጣ አስቸጋሪ በግ ወደ እነሱ ተቀላቀለ፡፡ ወደ ሻሼም ጠጋ ብሎ «ሌላ ከዚህ በጣም የሚያምር ቦታ አለ፡፡ ብዙ ምግብ፤ መጠጥ እና እየዘለልን ለመጫወት የሚያመች ተራራ አለ» አለው፡፡
ሻሼም ከእረኛው ከእናት እና ከአባቱ ተለይቶ ጠፋ፡፡ ቦታው ላይ እንደደረሱም መዝለል መጫወት ቀጠሉ፡፡ ሻሼም “ብዙ ምግብ እና መጠጥ የት ነው ያለው?” ብሎ ጠየቀው፡፡ አስቸጋሪው በግም «እዚህ ቦታ ምንም አይነት ምግብ እና መጠጥ የለም ነገር ግን እኛ እዚህ የመጣነው ለመጫወት ነው» አለው፡፡ ብዙ ከመጫወታቸው የተነሣ በጣም ደከማቸው፡፡ አስቸጋሪውም በግ ሻሼን ለብቻው ትቶት ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ሻሼም ወደ ቤት ለመሔድ ሲነሳ መንገዱ ጠፋበት እየመሸ ስለነበር እጅግ በጣም ፈራ እዚያው ካደረ ደግሞ ሌላ የዱር አራዊት መጥቶ ይበላዋል፡፡ ሰውነቱ እየተንቀጠቀጠ ማልቀስ ጀመረ፡፡
ሰአቱ ሲመሽ በጎቹ ከጠባቂያቸው ጋር ሆነው ወደቤታቸው ሄዱ፡፡ ጠባቂያቸውም እየጠራ መቁጠር ጀመረ 1፣2፣3፣ ……. 99 «ሻሼ የት ሄደ?» ብሎ ጠየቀ ማንም ሊመልስለት አልቻለም ሻሼ እያለ እየጮኸ ተጣራ ነገር ግን ማንም አቤት ሊለው አልቻለም፡፡
ቤት ውስጥም እንደሌለ ሲያውቅ ሌሎቹን በጎች የትም እንዳይሔዱ ነግሮ ሻሼን ለመፈለግ ወጣ፡፡ የተለያየ ቦታ መፈለግም ጀመረ በመጨረሻም ሻሼን እያለቀሰ እና እየተንቀጠቀጠ አየው፡፡
ሻሼ የእረኛውን መምጣት ሲያይ እጅግ በጣም ደስ አለው፡፡ ፍርሀቱም ለቀቀው፡፡
የበጎቹ እረኛ ሻሼን እንዳገኘው በትከሻው ተሸከመው እና ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡99ኙ በጎች ተሰብስበው የሻሼን እና የእረኛቸውን መምጣት ሲመለከቱ በጣም ተደስተው ዘለሉ፡፡
ልጆች ሁል ጊዜ ቤተሰቦቻችን እና ታላላቆቻችን የሚሉንን መስማት አለብን፡፡ አትሒዱ ያሉን ቦታ መሔድ የለብንም ቤተሰቦቻችንን እና ታላላቆቻችን የሚሉንን ከሰማን እግዚአብሔር ይባርከናል፡፡
ልጆች ይህ ምሳሌ የጌታችን ምሳሌ ነው፡፡ መላእክትን ሲፈጥር መቶ ነገድ አድርጎ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል የሳጥናኤል ነገድ በትዕቢት ምክንያት ከእግዚአብሔር መንግስት ተባረረ፡፡ በምትኩ የአዳምን ዘር አንድ ነገድ አድርጎ ፈጠረው፡፡ አዳም በሰይጣን ምክር ተታለለ፡፡ ጌታውም አትብላ ያለውን ዕፅ በላና ሞት ተፈረደበት፡፡ ይህ እንደሆነ ባየ ጊዜ ጌታችን ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክትን በሰማይ ትቶ የጠፋውን አዳምን ለመፈለግ ከድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ ሰላሳ ሦስት ዓመትም በምድር ላይ ተመላለሰ፡፡ ሞቶ፤ ተነስቶ፣ አርጎ፤ የአዳምን ዘር ከወጣበት ቤት መለሰው፡፡ ልጆች አያችሁ የጌታን ቸርነት?
ደህና ሰንብቱ