የጌታ ጥምቀት(ለሕፃናት)

ጥር 10/2004 ዓ.ም.

በእኅተ ፍሬስብሐት

የጥምቀት በዓል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበትን ዕለት የምናከብርበት በዓል ነው፡፡

 

ጌታችን ከተወለደ በኋላ 30 ዓመት ሲሆነው ዮርዳኖስ ወደሚባለው ወንዝ ሔደ፡፡ በዚያም መጥምቁ ዮሐንስ አጠመቀው፡፡ ጌታችን ሲጠመቅ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ነበር፡፡ ሌሊት ደግሞ ርግብ አይኖርም፤ ምክንያቱም ወደ ጎጇቸው ስለሚገቡ ነው፡፡ በዚያች ዕለት ግን ጌትችን ሲጠመቅ ርግብ መጥታ በራሱ ላይ አረፈች፡፡ ከዚያም ከሰማይ አንድ ድምጽ ተሰማ፤ ድምጹም

“የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡ እርሱን ስሙት” የሚል ነበር፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ድምጽ ነበር፡፡

 

በጥምቀት በዓል ጌታችን ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ እንደተጠመቀ ለማስታወስ ጥር 10 ቀን ሁሉም ታቦታት በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ውኃ ወዳለበት ስፍራ በመሔድ በድንኳን ውስጥ ያድራሉ፡፡ ይህ እለት ከተራ ይባላል፡፡ ከተራ የተባለው በአካባቢው ያለው ውኃ እንዳይፈስ ተገድቦ ሕዝቡ እንዲጠመቅበት ስለሚዘጋጅ ነው፡፡ ታቦታቱ ወደ ድንኳኑ ከገቡ በኋላ ሌሊቱን ካህናቱ ሲያመሰግኑ፣ ሲዘምሩና ሲቀድሱ እና እለቱን የተመለከተ ትምህርት ለሕዝቡ ሲያስተምሩ ያድራሉ፡፡ ጠዋት ከ12 ሰዓት ጀምሮ በተጠራቀመው ውኃ አጠገብ ጸሎት ከተደረገ እና ከተባረከ በኋላ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል፡፡ ይህ እለት ጥር 11 ቀን ጥምቀት ይባላል፡፡ ካህናቱ ሕዝቡን ጸበል ከረጩ በኋላ ልዩ ልዩ ሥርዓቶች ይደረጋሉ፡፡ ከዚያም ታቦታቱ ከድንኳን ወጥተው ወደየመጡበት ቤተ ክርስቲያን ይሔዳሉ፡፡