yesemayu_bm

የሰማዩ ቤተ መንግሥት (ለህጻናት)

15/04/2004 ዓ.ም

በእኅተ ፍሬስብሐት

 

በህንድ ሀገር ታከሻሊላ በተባለ ከተማ ጎንዶፓረስ የተባለ ንጉሥ ነበር፡፡ ይህ ንጉሥ በኢየሩሳሌም ስለ ነበረው የንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መንግሥት ዝና እየሰማ እርሱም በሀገሩ ማሠራት ይፈልግ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ነጋዴዎች በየሀገሩ ሲጓዙ የታወቀ ግንበኛ  እንዲያመጡለት አዘዛቸው፡፡

 

ይህንን መልእክት ከሰሙት ነጋዴዎች መካከል አንዱ ፋርስ ወደሚባለው ሀገር ተጓዘ ከዚያም ያ ነጋዴ አንዱ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስን አገኘው፡፡ ነጋዴው ቶማስ ከኢየሩሳሌም እንደመጣ ሲሰማ የግንበኝነት ሙያ ይችል እንደሆነ ጠየቀው፤ ሐዋርያው ቶማስ ወደ ህንድ ሄዶ ማስተማር ይፈልግ ነበር፡፡ ስለዚህም ይህንን ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ለመሔድ “በኢየሩሳሌም ሳለሁ ህንፃ በመገንባት እኖር ነበር፡፡” አለው፡፡

ነጋዴውም በጣም ተደስቶ ቶማስን ወደ ህንድ ወሰደው፡፡ ንጉሡም የቶማስን ሙያ ሲሰማ በጣም ደስ አለው፡፡ ከዚያም ከከተማው አጠገብ ወደሚገኘው ሔዶ ቶማስን ወሰደውና በጫካ የተሞላውን ሜዳ እያሳየ ቤተ መንግሥቱ በዚያ ቦታ ላይ እንዲሠራ ነገረው፡፡ ቅዱስ ቶማስ የቤተ መንግሥቱን አሠራር ሲነግረው ንጉሡ ተሠርቶ እስከሚያየው ቸኮለ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንጉሡ ለህንጻው መሥሪያ ብዙ ገንዘብ ለቅዱስ ቶማስ ይልክለት ጀመር፡፡

 

ቅዱስ ቶማስ ግን ገንዘቡን ሲያገኝ የሚሔደው ወደ ድሆች መንደር ነበር፡፡ በዚያም ለተራቡት ምግብ፣ ልብስ ለሌላቸው ልብስ፣ መጠለያ ቤት ለሌላቸው ደግሞ ቤት እየገዛ መስጠት ጀመረ፡፡ የታመሙትን እያዳነና እየስተማረ ይኖር ጀመረ፡፡

 

yesemayu_bm

 

ንጉሥ ጎንዶፓረስ ለሕንፃው መሥሪያ የመደበው ገንዘብ እና ጊዜ እንዳለቀ፣ ቤተ መንግሥቱን ሊጎበኝ መጣ፡፡ ወደ ቦታው ደርሶ ቢመለከት እንኳን ሕንፃው ሊሠራ ጫካው አልተነካም፡፡ ንጉሡም በዚያ የሚያልፍ መንገደኛ ጠርቶ ቶማስ የታለ? ሲል ጠየቀው፡፡

 

“ቶማስ በድሆች መንደር የተቸገሩትን እየረዳና እያስተማረ ይገኛል፡፡” ሲል መንገደኛው መለሰለት፡፡ “እርሱስ ጥሩ ግን የሰራልኝ ቤተ መንግሥት የታለ?” ብሎ መንገደኛውን ጠየቀው፡፡ መንገደኛውም “በድንጋይ የተሠራ ቤተ መንግሥት ላያዩ ይችላሉ፤ ጌታዬ፤ ነገር ግን ሕዝብዎ በጣም እንደተደሰተ መመልከት ይችላሉ፡፡” አለው፡፡

 

በዚህ ጊዜ ንጉሡ ያ ሁሉ ገንዘብ እንደባከነበት መጠራጠር ጀመረ ወዲያው ወታደሮቹ ቶማስን ፈልገው እንዲያመጡ ላካቸው፡፡ ቅዱስ ቶማስ ተይዞ እንደመጣ “ቤተ መንግሥቴን ለምን አልሠራህልኝም ጫካው እንኳን መቼ ተነሣ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ቶማስም “በእርግጥ በምድር ላይ የድንጋይ ቤተ መንግሥት ላያዩ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን በሰማይ ላይ ቤተ መንግሥት ሠርቼሎታለሁ፡፡” አለው፡፡

 

ያን ጊዜ ንጉሡ ተቆጣ፤ ቶማስን እጅ እግሩን እንዲያሰቃዩት አዞ እስር ቤት አስገባው፡፡ በዚያች ሌሊት የንጉሡ ወንድም ልዑል ጋድ በድንገት ታሞ ሞተ፡፡ የጋድ ነፍስ በመላእክት ታጅባ ወደ ሰማያት ወጣች፡፡ የጋድን ነፍስ ካጀቧት መላእክት አንዱ ብዙ ቤተ መንግሥታትን እያሳያት “እንድትኖሪበት ደስ ያለሽን ምረጪ፡፡” አላት፡፡ የጋድ ነፍስም ከቤተ መንግሥታቱ ሁሉ የሚያምረውን መረጠች “ይህ ቤተ መንግሥት የአንቺ አይደለም፤ ቶማስ ለንጉሥ ጎንዶፓረስ የሠራለት ሰማያዊ ቤተ መንግሥት ነው፡፡”

 

ጋድ ሊቀብሩት በተሰበሰቡት ሰዎች መካከል ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ተነሣ፡፡ ከዚያም ያየውን ሁሉ ለንጉሡ እና ለተሰበሰቡት ሰዎች ነገራቸው፡፡

 

ንጉሡ ይህን ሲሰማ በቶማስ ላይ በሠራው ሁሉ አዘነ፣ ያሰበው ቤተ መንግሥት መሠራቱን ሲሰማ ቶማስን ከእስር ቤት አስመጣው፡፡ እራሱ እና ቤተሰቡም በክርስቶስ አምላክነት አምነው ተጠመቁ፡፡ ለቶማስም ያለውን ገንዘብ ሁሉ “ሌላም ቤተ መንግሥት ሥራልኝ” እያለ ይሰጠው ጀመር፡፡ የሀገሩ ሰዎችም እንደርሱ ያደርጉ ጀመር፡፡

 

የተቸገሩትን መርዳት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መልካም ሥራ ነው፡፡ የተቸገሩ ሰዎችን የምንረዳ ከሆነ ደግሞ በምድር ላይ አይተነው የማናውቀውን እጅግ በጣም ያማረ ቤት ያሰጠናል፡፡