እንግዳ ተቀባዩ አባ ቢሾይ(ለሕፃናት)

ሐምሌ23፣2003 ዓ.ም
                                                                               አዜብ ገብሩ

እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ጻድቅ ከሆኑ ሰዎች የተወለደ አባ ቢሾይ የሚባል አባት ነበረ፡፡ ይህ አባት ለቤተሰቦቹ ሰባተኛ እና የመጨረሻ ልጅ ነው፡፡ አንድ ሌሊት ምን ሆነ መሰላችሁ ልጆች የአባ ቢሾይ እናት ሕልም አየች የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጸ፡፡ ጌታ እንዲህ ብሏል፤ “ያገለግለኝ ዘንድ ከልጆችሽ አንዱን ስጭኝ” እናቱም እንዲህ አለች “ሰባቱም ልጆቼ አሉ፤ የፈለግኸውን መርጠህ እንዲያገለግልህ ውሰድ”
መልአኩም አባ ቢሾይን ነካው፤ እናቱ ግን እንዲህ አለች “ከልጆቼ ሁሉ እርሱ ደካማ ነው፤ እግዚአብሔርን የበለጠ እንዲያገለግሉት ከሌሎቹ ልጆቼ ምረጥ” መልአኩም እንዲህ አላት “እግዚአብሔር ያገለግለው ዘንድ የመረጠው እርሱን ነው” ከዚያም አባ ቢሾይ ሃያ ዓመት ሲሆነው ወደ ገዳም ገባ፡፡ አባ ቢሾይ ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆነ ሰው ነበረ፡፡ ሁሌም ይጸልያል፣ ለረዥም ሰዓት ይጾማል፣ ቅዱሳት መጻሕፍን ይማራል፣ በቤቱ እንግዳ ተቀብሎ ያስተናግዳል፡፡ እግዚአብሔርን የሚያስደስት  ብዙ መልካም ሥራ ይሠራል፡፡

 

ከዕለታት አንድ ቀን አባ ቢሾይ ከበአቱ በር ላይ ተቀምጦ ሳለ በጣም የደከመው ሰው ወደ እርሱ ሲመጣ ተመለከተ፡፡ ከተቀመጠበት ተነሣና ያን ሰው ወደ በአቱ እንዲገባና እንዲያርፍ ጠየቀው፡፡ ከዚያም ያን በጣም የደከመው ሰው ውሃ አቅርቦ እግሩን ማጠብ ጀመረ፡፡ እግሩን እያጠበው ሳለም የእግዚአብሔር ድምጽ እንዲህ ሲል ሰማ “የተወደድክ ልጄ ቢሾይ ሆይ አንተ የተከበርክ ሰው ነህ” ወዲያውም የአምላካችንን እግር እያጠበ እንደነበር አስተዋለ፡፡ ተንሥቶም ተንበረከከ እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ እግዚአብሔርም ሰላምን ሰጠው፡፡
 
አያችሁ ልጆች አባ ቢሾይ እግዚአብሔርን አየው ምክንያቱም ትሑት ስለነበረና ዝቅ ብሎ የሌሎችን ሰዎች እግር ያጥብ ስለነበረ ነው፡፡ እኛም እንደ አባ ቢሾይ ትሑት መሆንና ወደቤታችን ለሚመጡት ሰዎች ሁሉ ደግ መሆን አለብን ይህን ካደረግን እግዚአብሔር ለእኛ መልካምን ነገር ያደርግልናል፡፡ በመንግሥተ ሰማይም ስለ ሠራነው መልካም ነገር ሽልማትን ይሸልመናል፡፡

                                                          ወስብሐት ለእግዚአብሔር  

የእግዚአብሔር ኃይል(ለሕፃናት)

ሰኔ15 ፣2003 ዓ.ም

ከእመቤት ፈለገ
 
በእስራኤል ሀገር ውስጥ አክዓብ የሚባል ንጉሥ ነበር፡፡ ንጉሡም በዓል የሚባል ጣዖት አምልኮ እግዚአብሔርን አሳዘነው፡፡ በዚሁ ሀገር ውስጥ የሚገኝ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የሚፈጽም ኤልያስ የሚባል ነቢይ ነበር፡፡ ንጉሡና ሕዝቦቹ እግዚአብሔርን እንዳስቀየሙት ባየ ጊዜ ዝናብ እንዳይዘንብ ጸለየ፡፡ ከብዙ ቀንም በኋላ በምድር ላይ ዝናብ አልነበረም፡፡ ከብዙ ቀንም በኋላ በሦስተኛው ዓመት “አክዓብ ጋር ሂድ በምድር ላይም ዝናብ እሰጣለሁ” ብሎ እግዚአብሔር ለኤልያስ ነገረው፡፡ በአገሪቱም ውስጥ ከፍተኛ ረሃብ ሆኖ ነበር፡፡

አብድዩ የሚባል እግዚአብሔርን የሚፈራ የንጉሡ አገልጋይ ነበር በመንገድ ሲሄድ ነቢዩ ኤልያስን አገኘው፡፡ አብድዮም ሮጠና የአክብሮት ስግደት ሰገደለት፡፡

ነቢዩ ኤልያስም “ሂድና ለጌታህ ኤልያስ እዚህ አለልህ” ብለህ ንገረው አለው፡፡ አብድዩም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ አክአብም ነብዩ ኤልያስን እንዳገኘው “አስራኤልን የምትበጠብጠው አንተ ነህ” አለው ይህንን ያለበትም ምክንያት ዝናብ ለረጅም ጊዜ ስላልነበረ ነው፡፡ ልጆች እንደምታውቁት ዝናብ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ እስራኤልን ሲበጠብጧት የነበሩት ግን ሕዝቦቹና ንጉሡ ነበሩ ምክንያቱም እግዚአብሔርን ክደው ሌላ አምላክ /ጣዖት/ ማምለክ ጀምረው ነበር፡፡

ነቢዩ ኤልያስ አክአብን አራት መቶ ሃምሳ የጣዖቱን /የበአልን/ ነቢያትን እንዲጠራቸው ለንጉሡ ነገረውና በአንድ ላይ ተሰበሰቡ፡፡ ከዚያም ነቢዩ ኤልያስ እንዲህ አላቸው “ከእግዚአብሔር ነቢያት የተረፍኩት እኔ ብቻ ነኝ፣ በእናንተ በኩል ግን አራት መቶ ሃምሳ ነቢያት አሉ፡፡ አንድ በሬ ውሰዱ አርዳችሁም በእንጨት ላይ አስቀምጡትና አምላካችሁን እየጠራችሁ ጸሎት አድርጉ እሳት አታንዱበት ከሰማይ አምላካችሁ እሳት አውርዶ ያዘጋጃችሁትን ነገር ከበላው እኔ በእናንተ አምላክ አምናለሁ፡፡ ይሄ ካልሆነና እኔ በአምላኬ በእግዚአብሔር ስም ጸልዬ ያዘጋጀሁትን እሳት ከሰማይ ወርዶ ከበላው በእግዚአብሔር ታምናላችሁ አላቸው፡፡ ሁሉም ሰው ተስማማ፡፡

በአልን ያመልኩ የነበሩት 450 የሐሰት ነብያት ቀኑን ሙሉ ቢጸልዩ ምንም ለውጥ አላመጡም፡፡

ነቢዩ ኤያልስ እሳት ከሰማይ ወርዶ እርሱ  ያስቀመጠውን እንዲወስደው ብዙ ውሃ አደረገበት፡፡ ልጆች እንደምታውቁት ውሃ እሳትን ያጠፋል፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸሎት አደረገ፡፡  እግዚአብሔር አምላክ ሆይ አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንህንና እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔን ያውቁ ዘንድ እግዚአብሔር ሆይ እባክህ ስማኝ ከዚያም የእግዚአብሔር እሳት ወርዳ እንጨቱን፣ ድንጋዩን፣ ዐፈሩን፣ ፈጽማ በላች በጉድጓድ ውስጥ ያለውን ውሃ ላሰች፡፡

ሕዝብም ሁሉ ይህን ሲያይ በግንባራቸው ተደፍተው አምላከ እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ ነው! እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው አሉ፡፡

አያችሁ ልጆች እግዚአብሔር በጣም ኃያል አምላክ ነው፡፡ እኛም የእርሱ ትእዛዛት የምንፈጽም ከሆነ ለእኛም ጥሩ ነገሮችን ማድረግ እንድንችልኃይል ይሰጠናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

አጭሩ ዘኪዮስ(ለሕፃናት)

ሰኔ11 ፣2003 ዓ.ም

አዜብ ገብሩ

ዘኪዮስ የሚባል አጭር ሀብታም ሰው ነበረ፡፡ ኢየሱሱ ክርስቶስን ለማየት በጣም ይፈልግ ነበር፡፡ ምክንያቱም ስለ እርሱ ብዙ ነገር ሲነገር ይሰማ ስለነበረ ነው፡፡ ጌታችን በዛሬው ዕለት ኢያሪኮ ወደምትባለው ከተማ ይገባል ብለው ሰዎች ሲያወሩ ዘኪዮስ ሰማ፡፡

ዘኪዮስም ይህን ሲሰማ ከቤቱ ጌታችንን ለማየት ወጣ፡፡ ከሩቅም ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ሲመጡ  አየ፡፡ “ምንድን ነው ነገሩ?” ብሎ ጠየቀ ሰዎቹም ጌታችን እየመጣ እንደሆነ ነገሩት፡፡ ዘኪዮስም ጥቂት ካሰበ በኋላ እንዲህ አለ፡፡ “እኔ አጭር ነኝ ከዚህ ሁሉ ከተሰበሰበው ሰው ለይቼ ጌታችንን እንዴት ላየው እችላለሁ?” ከዛም ወደ ተሰበሰበው ሰው ተጠጋና አንድ የሾላ ዛፍ ላይ ወጣ፡፡ ልጆች ዛፉ በጣም ረዥም ስለሆነ ለመውጣት አስቸጋሪ ነበር፡፡

ዘኪዮስ ግን ጌታችንን ለማየት ካለው ፍላጎት የተነሳ በብዙ ጥረት ዛፉ ላይ ወጣ፡፡ የተሰበሰበው ሰው ዘኪዮስ ወዳለበት ዛፍ መጠጋት ጀመረ፡፡ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች ጌታችንን ከበውት ነበር፡፡ ጌታችንን በጣም ስለሚወዱት ከእርሱ አይለዩም ነበር፡፡ የተሰበሰበው ሰው የሾላውን ዛፍ ማለፍ ጀመረ፡፡ ጌታችን ግን ቆመ፡፡ ቀና ብሎም ዘኪዮስን ተመለከተው፡፡ “ዘኪዮስ ሆይ ና ውረድ” ብሎም ጠራው፡፡ ዘኪዮስም በደስታ ከዛፉ ላይ ወረደ ከዛም ጌታችን ለዘኪዮስ እንዲህ አለው “ዛሬ ወደቤትህ እገባለሁ፡፡ ከአንተ ጋርም ራት  እበላለሁ፡፡” ዘኪዮስም በደስታ ተቀበለው በቤቱም አስተናገደው፡፡

ልጆች ጌታችን እኛ ስለራሳችን ከምናስበው በላይ እርሱ ለእኛ እንደሚያስብልን ከዚህ ታሪክ እንማራለን፡፡ ዘኪዮስ የፈለገው ጌታችንን ማየት ብቻ ነበር፡፡ ጌታችን ግን ከማየትም አልፎ ከእርሱ ጋር ራት እንደሚበላ ነገረው፡፡ ዘኪዮስ ካሰበው በላይ ጌታችን መልካም ነገርን አደረገለት፡፡ ሌላው ደግሞ ልጆች እንደዘኪዮስ እንግዳ ተቀባይ መሆን አለባችሁ፡፡ ዘኪዮስ ጌታችንን ደስ ብሎት እንዳስተናገደው እናንተም ወደቤታችሁ የመጣውን ሁሉ ትንሽ ትልቅ ሀብታም ድሃ ብላችሁ ሳትለዩ ሁሉንም በፍቅር ማስተናገድ አለባችሁ፡፡ በሉ እንግዲህ ልጆች በሌላ ጽሑፍ እስከምንገናኝ ደህና ሁኑ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ጰራቅሊጦስ(ለሕፃናት)

ሰኔ 07 2003 ዓ.

አዜብ ገብሩ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ በሰላም  አደረሳችሁ፡፡

ከትንሣኤ በኋላ ያለው ሃምሳኛው ቀን ጰራቅሊጦስ ይባላል፡፡ ይህ ዕለት ጌታ ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ያወረደበት ዕለት ነው፡፡ ልጆች ጌታ ከሞት ከተነሣ በኋላ አስራ ሁለቱ ሐዋርያት በቅዱስ ማርቆስ እናት ቤት ከሰባሁለቱ አርድዕት አና ከሰላሳ ስድስቱ ቅዱሳን አንስት ጋር በመሆን ይጸልዩ ነበር፡፡ ጌታም በተለያየ ጊዜ እየተገለጸ ያስተምራቸው ነበር፡፡ አጽናኝ የሆነውን ቅዱስ መንፈስም እንደሚልክላቸው ይነግራቸው ነበር፡፡


ታዲያ ልጆች ሐዋርያት በዚያ ተሰብስበው እየጸለዩ ሳለ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ንፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፡፡ መንፈስ ቅዱስም  በእሳት አምሳል በሐዋርያት ላይ ሞላባቸው፡፡ ከዚያም ሐዋርያት በተለያየ ቋንቋ መናገር ጀመሩ፡፡ በዚያ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎችም ሐዋርያት በተለያየ ቋንቋ ሲናገሩ ሰምተው በጣም ተደነቁ፡፡ ሐዋርያትም ለተሰበሰቡት ሰዎች በየራሳቸው ቋንቋ አስተማሯቸው፡፡ ሰዎቹም በክርስቶስ አምነው ክርስቲያን ሆኑ፡፡
ልጆች ይህን ለሐዋርያት የወረደውን መንፈስ እኛም ጥምቀትን ስንጠመቅና ቅዱስ የሆነውን ሜሮን ስንቀባ እንቀበለዋለን፡፡ ይህ ቅዱስ የሆነው መንፈስም ከእኛ ጋር ሆኖ ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቀናል፡፡ ኃጢአት እንዳንሠራም ይጠብቀናል፡፡ እንቢ ብለን ኃጢአትን ብንሠራ ሰው ብንሳደብ፣ ለታላላቆቻችን ባንታዘዝ፣ ውሸት ብንናገር፣ የጓደኛችንን ዕቃ ብንሰርቅ፣…/ ይህ ቅዱስ የሆነው መንፈስ ከእኛ ይሸሻል፡፡ ስለዚሀ ልጆች ሁል ጊዜ መልካም የሆነ ነገር ብቻ መሥራት አለብን ማለት ነው፡፡ ይህን የመሰለ ስጦታ የሰጠንን እግዚአብሔርንም ልናመሰግነውና ልናከብረው ይገባል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

እናትና አባትህን አክብር (ለህጻናት)

ግንቦት 30/2003 ዓ.ም.

                                  በአዜብ ገብሩ
“እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም፣ መልካምም እንዲሆንልህ እናትና አባትህን አክብር፡፡” ዘዳግም 5÷16
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች ደህና ናችሁ የዛሬው ጽሑፋችን እናትና አባትን ስለማክበር ነው በደንብ ተከታተሉን፡፡
ልጆች ከአሥርቱ ትዕዛዛት መካከል አንዱ እናትና አባትህን አክብር የሚለው ነው፡፡ እግዚአብሔር እናትና አባታችንን ካከበርን ሽልማት እንደሚሰጠን ነግሮናል፡፡ ሽልማቱም በምድር ላይ ስንኖር ዕድሜያችን ረዥም እንደሚሆንና፤ በዚህ ዕድሜያችንም መልካም የሆነ ነገር እንደሚያደርግልን ነው፡፡ ለእናትና ለአባታችን ስንታዘዝ እግዚአብሔር ሽልማት እንደሚሸልመንና በእኛ እንደሚደሰት ሁሉ ካልታዘዝን ደግሞ ያዝንብናል፡፡ አዎ! እናትና አባቱን የማያከብር፣ ስድብ የሚሳደብ፣ በትዕቢት ዐይን እናትና አባቱን የሚመለከት ልጅ እግዚአብሔር ደስ አይሰኝበትም፡፡ስለዚህ ልጆች እናትና አባታችን ማክበር ይገባል ማለት ነው፡፡ እናትና አባታችን ማክበር እንዳለብን ካወቅን እንዴት ነው የምናከብራቸው?
 

1.    በመታዘዝ “ልጄ ሆይ የአባትህን ምክር ስማ የእናትህንም ትእዛዝ ቸል አትበል፡፡” ምሳ.1÷8
2.    ጥሩ ልጅ በመሆን
3.    አክብሮት የተሞላበት ንግግር በመናገር
4.    በመውደድ

እንግዲህ ልጆች እናትና አባትን ማክበር ከእግዚአብሔር ዘንድ ሽልማት የሚያሰጥ መልካም ሥራ ነውና እናትና አባታችንን ልናከብር ይገባል ማለት ነው፡፡ ጌታችን ራሱ እናቱ ድንግል ማርያምን  ያከብር ነበር፤ ይታዘዛትም ነበር፡፡ እኛም እርሱን ምሳሌ አድርገን ልናከብራቸውና ልንታዘዛቸው ይገባል፡፡ እርሱም እኛን ይወደናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ቅዱስ ጳውሎስ(ለሕፃናት)

ግንቦት 23 2003 ዓ.

በእመቤት ፈለገ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? ዛሬ ስለ አንድ ትልቅ የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያ ታሪክ እንነግራችኋለን በደንብ ተከታተሉን፡፡
 
በድሮ ጊዜ በኢየሩሳሌም ከተማ የሚኖር ክርስቲያኖችን የሚጠላና በእነርሱ ላይ ክፉ ሥራ የሚሠራ ሳውል የሚባል ሰው ነበረ፡፡ ደማስቆ ወደምትባል ከተማም ክርስቲያኖችን ሊገድል ጉዞ ጀመረ፡፡
 
ደማስቆ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረው ብርሃን በዙሪያው አንጸባረቀበት እርሱም በምድር ላይ ወደቀ በዚያን ጊዜ “ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምጽ ሰማ፡፡ ሳውልም “አቤቱ አንተ ማን ነህ?” አለው፡፡ እርሱም “አንተ የምታሳድደኛ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፡፡” አለው ፡፡ልጆች ሳውል የሚያሳድደው ክርስቲያኖችን ሆኖ ሳለ ጌታችን ለምን እኔን ታሳድደኛለህ ብሎ ጠየቀው? ምክንያቱ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ቤተ ክርስቲያንን እና ክርስቲያኖችን መጥላት ወይም በእነርሱ ላይ ክፉ ነገር ማድረግ ማለት በአምላካችን ላይ ክፉ ነገር ማድረግ ማለት ስለሆነ ነው፡፡
 

ሳውል ከወደቀበት ተነሥቶ ዐይኑን ሲገልጥ ምንም ነገር ማየት አልቻለም ስለዚህ ሰዎች እጁን ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አስገቡት “ሦስት ቀንም ዐይኑ ማየት አልቻለም፤ አልተመገበም፡፡ በደማስቆ ሐናንያ የሚባል አንድ ደቀመዝሙር ነበር፤ ጌታችንም ለሐናንያ ተገልጦ ሳውል የሚባል ሰው ይሁዳ በሚባል ሰው ቤት እየጸለየ ነው አግኘው አለው፡፡ ሐናንያም እጅግ በጣም ፈራ፡፡ ለጌታችንም “ይህ ሰው በክርስቲያኖች ላይ ምን ያህል ክፉ ነገር እንዳደረገ ሰምቻለሁ፡፡ ወደዚህም የመጣው ይህን ሊያደርግ ነው” አለው፡፡ ጌታችንም እንዲህ አለው “ሂድ ይህ ሰው ከዛሬ ጀምሮ ማንንም ክርስቲያን አይጎዳም ይልቁንም ሰዎችን የሚያስተምር ትልቅ አባት ይሆናል” አለው፡፡ ሐናንያም ወደተባለው ቤት ገባ፤ በሳውል ላይም እጁን ጭኖ “ወንድሜ ሳውል ሆይ በመንገድ ላይ የተገለጠልህ ኢየሱስ ክርስቶስ ዐይንህ እንዲበራና በመንፈስ ቅዱስ እንድትሞላ እኔን ልኮኛል” አለው፡፡ ሳውልም ማየት ቻለ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፤ ምግብም በላ፡፡
 
ጌታችን ሳውል እንዲድን ብዙ ነገር አዘጋጀለት ሐናንያን ላከለት ደግሞም ማየት እንዲችል አደረገው፡፡ የሠራውን ሁሉ ይቅር ብሎት ክርስቲያን አደረገው፡፡ በኋላም ሳውል ትልቅ ሐዋርያ ሆኖ ቅዱስ ጳውሎስ ተባለ፡፡ 


ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

“ሕፃናት ወደኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው” ሉቃ.18÷16 (ለሕጻናት)

በአዜብ ገብሩ

ግንቦት 20፣ 2003ዓ.ም

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? በዛሬው ጽሑፋችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕፃናትን ምን ያህል እንደሚወድ የሚያስረዳ ጽሑፍ ይዘን ቀርበናል÷ በደንብ አንብቡት እሺ፡፡

በአንድ ወቅት ጌታችን ለምለም የሆነ ሣር ባለበት ቦታ ላይ ብዙ ሰዎች በዙሪያው ከበውት ቆመው ያስተምራቸው ነበር፡፡ ሰዎቹም የእርሱን ጣፋጭ የሆኑ ቃላት ለማዳመጥ ከተለያየ ቦታ የተሰበሰቡ ነበሩ፡፡ ሁልጊዜ ከጌታ የማይለዩት ዐስራ ሁለቱ ሐዋርያትም በዚያ ነበሩ፡፡ እነዚህ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጌታ በሄደበት ቦታ ሁሉ ይሄዳሉ፤ ከእርሱ ጋር ይጸልያሉ፤ እርሱንም ያገለግሉታል /ይታዘዙለታል/፡፡ ታዲያ ልጆች ጌታችን ቁጭ ብሎ የተሰበሰቡትን ሕዝብ እያስተማረ ሳለ ልክ እንደ እናንተ ሕፃን የሆነ ልጅ ወደ ጌታችን እየሮጠ መጣ፡፡ እንዲህም አለው “ኢየሱስ ክርስቶስን ማየት እፈልጋለሁ አለ፡፡” ከዚያም ዘወር ሲል እንደ ፀሐይ የሚያበራውን የጌታችንን ፊት አየ፤ ጣፋጭ የሆነውንም የጌታችንን ድምጽ ሰማ፡፡ ጌታችንም የሕፃኑን እጅ ይዞ “ከእኔ ጋራ ና” አለው፡፡ ወደ ሐዋርያትም ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፡፡ “በመንገድ ሳለን ስለምን ትከራከሩ ነበር?” እነርሱም ዝም አሉ፡፡ ምክንያቱም በመንገድ ሳሉ ከእኛ መካከል ከሁላችን የሚበልጥ ትልቅ ማነው? እያሉ ይከራከሩ ስለነበር ነው፡፡ ጌታችን ለጥቂት ጊዜ ዝም ብሎ ከቆየ በኋላ ሕፃኑን “ወደ እኔ ና” አለው ሕፃኑም ወደ ጌታችን ተጠጋ፡፡ ጌታችንም ሕፃኑን አንስቶ አቀፈው፡፡ ለሐዋርያቱም እንዲህ አላቸው “ከእናንተ መካከል ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ከሁላችሁ ይበልጣል፡፡” ሐዋርያትም ጌታችንን በትኩረት ይሰሙት ነበር፡፡ የሚናገረውንም ቃል ለመረዳት ይሞክሩ ነበር፡፡ ሕፃኑ ልጅ ግን ጌታችንን የተናገረውን እንዲያስረዳው ጠየቀው ጌታችንም “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው÷ አትከልክሏቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነርሱ ላሉት ናትና አለ፡፡”

ልጆች ጌታችን እንዴት እንደሚወዳችሁ አያችሁ? እናንተም ትወዱታላችሁ አይደል አዎ በጸሎታችሁ ወቅት ጌታን እንደምትወዱት ልትነግሩት ይገባል፡፡ እርሱ የሚወደውንም መልካም ሥራ ልትሠሩ ይገባል፡፡ ልትነግሩት ይገባል፡፡ ከጓደኞቻችሁ ጋር ሳትጣሉ በፍቅር ልትኖሩም ይገባል፡፡ ይህን ካደረጋችሁ ጌታችን እጅግ በጣም ይወዳችኋል፡፡ ሁሌም ከእናንተም ጋር ይሆናል ማለት ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዓሣ

ወርቅ ሠሪው ጴጥሮስ(ለሕፃናት)

በእመቤት ፈለገ

ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው የአንድ ጌጣጌጥ የሚሠራ ሰው ታሪክ ነው ተከታተሉ፡፡

ከብዙ ዓመታት በፊት ስሙ ጴጥሮስ የተባለ በጣም ጥሩ ክርስቲያን ነበር፡፡ የተለያዩ ጌጣጌጦች ማለትም ቀለበት፣ የአንገት ሃብል ይሠራ ነበር፡፡

ብዙ ጊዜም ቤተ ክርስቲያን መሄድ ያስደስተው ነበር፡፡ እርሱ በሚኖርበትም አካባቢ የሚገኝ በእግዚአብሔር የማያምን አንድ መጥፎ ሰው ነበር፡፡ ጴጥሮስንም እጅግ በጣም ይጠላው ነበር፡፡ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሊጎዳው ይፈልግ ነበር፡፡ ምክንያቱም ጴጥሮስ እግዚአብሔርን ስለሚወደው ነበር፡፡ ይህ ክፉ ሰው የአንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ጸሐፊ ነበር፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን የመንግሥት ባለሥልጣን የነበረው ሰው ቀለበት ማሠራት ፈለገ እንዲያሠራለትም ለዚያ ክፉ ሰው ሰጠው፡፡ ያ መጥፎ ሰውም ጴጥሮስን ለመጉዳት ጥሩ አጋጣሚ እንዳገኘ አሰበና ደስ አለው፡፡ ወደ ጴጥሮስም ሄደና ቀለበቱን ሰጠው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣኑ ቀለበት እንደሆነ ቆንጆ አርጎ በፍጥነት እንዲሠራ ነገረው፡፡ ጴጥሮስም ቀለበቱን ተቀብሎ ጠረጴዛ ላይ አስቀመጠውና ሌላ እንግዳ ማስተናገድ ጀመረ፡፡ ክፉውም ሰው ቀለበቱን ሰርቆ ሄደ ወንዝ ውስጥ ጣለው፡፡ ጴጥሮስ ቀለበቱን ሲፈልግ አጣው በጣም አዘነ የመንግሥት ባለሥልጣኑም ይህን ሲሰማ ምን ሊያደርገው እንደሚችል አሰበ እጅግ ጨነቀው ሱቁንም ዘግቶ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡

ቤቱ እንደገባም የሆነውን ሁሉ ለባለቤቱ ነገራት እርሷም እግዚአብሔር ከነርሱ ጋር እንደ ሆነ ምንም መፍራት እንደሌለበት ነገረችው፡፡ በሚቀጥለውም ቀን ወደ ሥራ ሄደ ነገር ግን በጣም ስለተጨነቀ ምንም ሥራ መሥራት አልቻለም፡፡ ዓሣ የሚሸጥ ሰው በየቀኑ ለጴጥሮስ ዓሣ ይዞለት እየመጣ ይሸጥለት ነበር፡፡ ያን ቀን ግን ጴጥሮስ ዓሣ ሻጩን ሲያየው “ዛሬ ምንም አልፈልግም አለው፡፡ ዓሣ ሻጩም ጥሩ ዓሣ እንደያዘ ነገረው ጴጥሮስ ግን “በፍጹም አልገዛም” አለው፡፡ ዓሣ ሻጩም ወደ ጴጥሮስ ቤት ሄደ ዓሣውን ለሚስቱ ሸጠላት፡፡

ዓሣየጴጥሮስ ሚስትም ዓሣውን ገዝታ መሥራት ስትጀምር በጣም የሚያብረቀርቅ ነገር አየች ቀለበት ነበር! ልክ ባለቤቷ ወደ ቤት ሲመጣ የተፈጠረውን ነገር ማመን አቃተው፡፡ እግዚአብሔር ሕይወቱን ጠበቀለት፡፡

ጴጥሮስን ከክፉ ነገር ሁሉ የጠበቀው አምላክ እኛንም ከክፉ ነገር ይጠብቀናል፡፡ ስለዚህ ልጆች ሁል ጊዜም ስለሚደረግልን ነገር ሁሉ እግዚአበሔርን ማመስገን አለብን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔ

በደህና ሰንብቱ ልጆች!

 

ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን (ለህጻናት)

በአዜብ ገብሩ

 

በአንድ ወቅት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፡፡ በቤተ መቅደስ ውስጥም በሬዎችና በጎችን፣ ርግቦችንም ሲሸጡ አገኘ፡፡ በዚህን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጣም አዘነ፡፡ የገመድ ጅራፍም አበጀ፡፡ በጎችንና በሬዎችን፣ ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣ፡፡ “ቤቴ የጸሎት ቤት እንጂ የንግድ ቤት አይደለችም” አላቸው፡፡

ልጆች ጌታ እነዚህ ሰዎች በቤተ መቅደስ የማይሠራ ሥራ ስለሠሩ እንዴት እንዳዘነ አያችሁ? ቤተ ክርስቲያንን ስናከብር ጌታችን በእኛ ደስ ይለዋል፤ የምንፈልገውንም ነገር ይሰጠናል፡፡ ስለዚህ ልጆች እኛም ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ እግዚአብሔርን እንዳናሳዝነው ሥርዓትን መጠበቅ አለብን፡፡

1.ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ ተሳልመን መግባት፣
2.የተቀደሰ ቦታ ስለሆነ ጫማችንን ማውለቅ፣
3.በጸጥታ ሆነን ሥርዓቱን መከታተል
4.መጸለይና እግዚብሔርን ማመስገን አለብን፡፡

 

ልጆች በቤተ ክርስቲያን ስትሆኑ ይህን ማክበር አለባችሁ ማለት ነው፡፡ ሌሎች ልጆችም ሲያጠፉ ስታዩ ምከሯቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲያወሩ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲመገቡ ብታዩ፣ በቅደሴ ጊዜ ያለ አግባብ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ ተው ልትሏቸው ይገባል፡፡
እንግዲህ ልጆች የአግዚአብሔር ቤት ስለሆነች ቤተ ክርስቲያንን ልትወዷት ይገባል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውንም ሥርዓት ሁሉ ልትፈጽሙ ይገባል፡፡ ይህን ካደረጋችሁ አግዚአብሔር ደስ ይለዋል፤ እናንተንም ይወዳችኋል፡፡

 

ደህና ሰንብቱ እሺ ልጆች!

ልጆች በቤተክርስቲያን

       በአዜብ ገብሩ

“ልጆቼ ኑ ስሙኝ እግዚአብሔርን መፍራት አስትምራችኋለሁ፡፡” መዝ 34÷11

ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ዛሬ ቤተክርስቲያን ውስጥ ስንሆን ምን ማድረግ ምን ደግሞ አለማድረግ እንደሚገባን የሚያሳየን ታሪክ ይዘን ቀርበናል፡፡ በደንብ ተከታተሉን፡፡

በድሮ ዘመን ደብረ ቀልሞን በምትባል አካባቢ የሚገኙ ሕፃናት ቅዳሴ ሊያስቀድሱ ወደ ቤተክርስቲያን ሄዱ፡፡ በቅደሴ ጊዜም ወዲያና ወዲህ እያሉ ቅደሴ ሲረብሹ እግዚአብሔር በጣም አዘነባቸው፡፡ ከዚያም እነዚህ ያጠፋት ልጆችን እንዲቀጡ መላእክትን ከሰማይ ላከ፡፡ የተላኩትም መላእክት በታዘዙት መሠረት ያጠፉትን ልጆች እንዲቀጡ መላእክትን ከሰማይ ላከ፡፡ የተላኩትም መላእክት በታዘዙት መሠረት ያጠፉትን ልጆች ቀጥተው ሲመለሱ ከተላኩት መላእክት አንዱ ግን ልጆቹን በሚቀጣበት ሰዓት አንድ የሚያምር ልጅ አጋጠመውና አዘነለት፡፡ “ይህንንስ የፈጠረው ይቅጣው” ብሎ ተወው፡፡ ይህን በማድረጉና የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመተላላፉ መልአኩ እንደሌሎች መላእክት ወደ ሰማይ ለማረግ አልቻለም፡፡ በዚያ ወድቆ ሳለ አንድ ዲያቆን ለአገልግሎት ወደ ቤተክርስቲያን ሲገባ አገኘው፡፡ ተጠግቶም “አንተ ምድራዊ ነህ ወይስ ሰማያዊ” ብሎ ጠየቀው፡፡ መልአኩም “ሥራዬ ምድራዊ አደረገኝ እንጂ ተፈጥሮዬስ ሰማያዊ ነው፡፡ ሄደህ ለካህኑ ንገርልኝና ይደልይልኝ፡፡” አለው፡፡ ዲያቆኑም ሄዶ ለካህኑ ነገረው፡፡ ካህኑም ከሥዕለ ማርያም ሥር ተደፈቶ እመቤታችንን እየተማፀነ ጸለየለት እመቤታችንም ከሥዕሏ ላይ ተገልጻ “በቀኝ እጅህ ቀኝ ክንፉን በግራ እጅህ ግራ ክንፉን ይዘህ በፈጣሪ በእግዚአብሔር ስም ተነሥ በለው” አለችው፡፡ ካህኑም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ መልአኩም ኃይሉ ተመለሰለትና ወደ ሰማይ ዓረገ፡፡

አያችሁ ልጆች በቤተክርስቲያን ውስጥ ወዲህ ወዲያ ማለት፣ መረበሽ ማውራት ቅጣት ያስከትላል፡፡ እንደውም ልጆቹ ባጠፉት ጥፋት ቅጣቱ ለመልአኩም ተርፎት ነበር፡፡ እመቤታችን ከፈጣሪ አማልዳ መልአካዊ ኃይሉን ባታስመልስለት ኑሮ በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ወድቆ ነበር፡፡ ስለዚህ ልጆች ወደ ቤተክርስቲያን ስትሄዱ ጥንቃቄ አይለያችሁ እሺ ገላችሁን ታጥጣችሁ፣ የታጠበ ንጹሕ ልብስ ለብሳችሁ፣ ነጠላችሁን መስቀለኛ ለብሳችሁ፣ ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት በቤተክርስቲያን ተገኝታችሁ፣ ወደቁርባን ስትቀርቡ በሥርዓቱ ሳትጋፉ ተራ ጠብቃችሁ መቁረብ ይገባል፡፡ አንግዲህ ልጆች ከዚህ ታሪክ ትምህርት በማግኘት እናንተ ሥርዓት አክባሪና ጨዋ ልጆች ሆናችሁ ለሌሎች ልጆች እንደምትመክሩና እንደምታስተምሩ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በሉ ደህና ሁኑ ልጆች፡፡