የሻጮችና የለዋጮች ወንበር የሞላው ቤተ መቅደስ
ጥንቱን ለልማዱ የቤተ መቅደስ መሠራት ምክንያቱ ሰዎችን ለመቀደስ፣ ሕያዊት ነፍስ የተሰጠቸው ሥጋዊ ደማዊ ፍጥረት ሁሉ ጸሎቱን አድርሶ መሥዋዕቱን አቅርቦ ከእግዚአብሔር ምሕረት ሊቀበልበት አልነበረምን? ‹‹ለዘለዓለም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይኖራሉ›› ብሎ የመረጠው የነገሥታት ንጉሥ የእግዚአብሔር ልዩ ሥፍራ ነው ቤተ መቅደስ፡፡ መቅረዙና ጠረጴዛው የመሥዋዕቱም ኅብስት ነበረበት፤ የወርቁ ማዕጠንት፣ ሁለንተናዋም በወርቅ የተለበጠች የኪዳን ጽላት፣ በውስጧም መናን የተሸከመችው መሶበ ወርቅና ክህነት የጸናባት የአሮን በትር እንዲኖሩ ታዝዞ ነበር፡፡ በምድራውያን ሰዎች መካከል እንደ ምሰሶ የሚቆመው ካህን ገብቶ የሚያጥንበት ይህ ቤተ መቅደስ ምንኛ የከበረ ነው? ለሰዎች ሁሉ ራዕይን አይቶ የሚነግራቸው ባለ ራዕይ ነቢይ የማይታጣበት፣ ሊቀ ካህናቱ የሚደገፈው ያቁም፣ ንጉሡ የሚደገፈው በለዝ የሚባሉት ምሰሶዎች የሚገኙበትም ነው፡፡ ያዕቆብ እንዳለው ይህ ቤተ መቅደስ የሰማይ ደጅ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ (፩ ነገ. ፱÷፫፣ ዕብ. ፱÷፪፣ ዘፍ. ፳፰÷፲፯)
