‹‹አንተ ሰይጣን፤  ከአጠገቤ ሂድ!›› (ማቴ.፬፥፱)

በሕግና ዕቅበተ እምነት አገልግሎት ማስተባበሪያ

መጋቢት ፲፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

መቈጣት ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ አለ፤ ሊቃውንቱ እንዲህ ዓይነቱን ቊጣ ‹‹መዓት ዘበርትዕ›› ይሉታል፤ የሚገባ ቊጣ ማለታቸው ነው፡፡ ቊጣና ተግሣጽ ከሚያስፈልጋቸው ፍጥረታት አንዱ ሰይጣን ነው፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይገባውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቈጥቶ የሚያውቀው በአይሁድና በአጋንንት ላይ ነው፡፡ ሰይጣንን ተቈጥቶ ካስወገደበት ቀን አንዱ ይህ ዛሬ የምናነሣው ነው፡፡ ሰይጣን አፍሮ ከኛ የሚርቅባት ቀን ምንኛ የተባረከች ቀን ናት? ጌታ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ገዳመ ቆሮንቶስ ገባ፡፡ ካመኑ ከተጠመቁ በኋላ ወደ መንፈሳዊው ዓለም መጓዝ ይገባል ማለቱ ነው፡፡ ገዳም ገብቶ አርባ ቀንና አርባ መዓልት ጾመ ጸለየ፡፡ ሲጠመቅ በመጠመቁ ዋጋ የሚያገኝበት ሆኖ አይደለም፡፡ ውኆችን ለማክበር በጥምቀት ምእመናን እንዲወለዱ ጥምቀትን የጸጋ ምንጭ ሊያደርጋት ተጠምቋል እንዳልን በመጾሙና በመጸለዩም እንደ ኤልያስ ወደ ሰማይ ያረገ፣ እንደ ዳንኤል የአንበሳን አፍ የዘጋ፣ እንደ ሙሴም ሕግን የተቀበለበት አይደለም፡፡ ጾምና ጸሎት ዋጋ ማሰጠታቸውን አውቀው ከእሱ በኋላ የተነሡ ምእመናን እንዲይዙት ለማስተማር ነው፡፡ በዚያውም ላይ ጥንቱንም የጎዳን መብልና መጠጥ ነው፤ አሁንም ነፍሳችን የምትታደሰው በጾምና በጸሎት ስለሆነ ነው፡፡

አምላካችን ክርስቶስ ከጾመና ከጸለየ በኋላ በሦስቱ ዐበይት ፈተናዎች ተፈተነ፡፡ ትዕቢት፣ ስስት፣ ፍቅረ ንዋይ ናቸው፡፡ የሕይወታችን ፈተናዎች ሁሉ በእነዚህ ይጠቃለላሉ፡፡ ትዕቢት ብዙ ዘውግ አላት ሌሎችም እንደዛው ነው ስለዚህ ነው፡፡ ስያሜአቸው በራሱ ‹‹አርዕስተ ኃጣውእ›› ተብለው ነው የሚጠሩት፡፡ እያንዳንዱን በሰፊው ልመልከት ብል ብራና ስለማይችልልኝ ሌላ  ጊዜ በየዘውጋቸው ከፋፍየ አያቸዋለሁ፡፡ ላሁኑ እንድንሄድ የምፈልገው ወደ ሌሎቹ ጉዳዮች ነው፡፡ ፈታኙ ፈተናውን ሳይለውጥ ፶፻፭፻ ዘመን ሙሉ ሰዎችን በዚህች ፈተና ነው ሲጫወትባቸው የኖረውና ዛሮም ለመጀመሪያው ሰው ለአዳም ያቀረበለትን ፈተና ይዞ ለጌታችን አቀረበለት፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ እነዚህ ድንጋዮች ባዶ እንዲሆኑ እዘዝ›› ብሎ በስስት፣ ‹‹መላእክቱን ስላንተ ያዝዝልሃል›› ብሎ በትዕቢት ‹‹ይህን ሁሉ እሰጥሀለሁ›› ብሎ በፍቅረ ንዋይ ሊፈታተነው ጀመረ፡፡ እንደ ሰይጣን ያለ አላዋቂ የት ይገኛል? እንዴት ይህን ያህል ዘመን ፈተናዎቹን አልቀየራቸውም? ለነገሩ ሰዎችም ሕይወት ከሚሆናቸው ከመንፈስ ቅዱስ ተለይተው ስለነበረ እንደ ድንጋይ ፈዝዘውለታልና አዳምንና የአዳምን ልጆች በሙሉ በጣለበት ፈተና ቃኤል ወንድሙን እንዲገድል የሰናዖር ሰዎች ተበታትነው እንዲቀሩ ኤልዛቤልና አክዓብ ውሻ በልቷቸው ደማቸውን ምድር ጠጥቶት እንዲቀር ያደረገው በዚህ ፈተና ነው።  ተፈታኞቹ እስካልነቁ ድረስ ምን ያደክመዋል? ዛሬም ፈተናውን ሳይቀር ዓለምን ሲያተራምሰው ይኖራል፡፡ (ማቴ.፬፥፫-፱፣ዘፍ. ፬፥፩፣ ፲፩፥፩፣ ፪ ነገ. ፱፥፴፯)

ለዚያውም ሦስቱን አርዕስተ ኃጣውዕ ድል የምንነሣባቸው ሦስቱ አርዕስተ ምግባራት ተሰጥተውን ነበር እነሱም ጾም፣ ጸሎትና ምጽዋት ናቸው፡፡ ጌታ በመጀመሪያው ጉባኤው ያሰተማረው እነዚህን ነው። ሦስቱንም ኃጢአቶች በገዳም ተገኝቶ በተግባር ድል ከነሣ በኋላ እኛም ድል የምንነሣባቸው መንገዶች እነዚህ ሦስቱ እንደሆኑ አስተማረን፡፡ ዛሬም ሰይጣንን ገሥፆ ካጠገቡ ለማራቅ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው የሚከተሉትን ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ (ማቴ. ፩፥፩-፳፬)

. መጠመቅ

ዕለተ ጥምቀት ከሰማዩ አባታችን የመለኮቱን ባሕርይ በጸጋ የምንካፈልበት ቀን ናት፤ ‹‹አይዟችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ›› ያለን አምላክ ኃይሉን ካልሰጠን ዓለምን ድል ማድረግ ስለማንችል ከእግዚአብሔር ላልተወለዱ ሰይጣንን ድል መንሣት አስቸጋሪ ነውና በጥምቀት ባገኘነው ኃይል መንፈሳዊውን ውጊያ ድል አድርገን ርስታችንን ወርሰን እንኖራለን፡፡ (ዮሐ.፲፮፥፴፫)

. መሸሽ

ጌታችን ከተጠመቀ በኋላ ወደ ገዳም መሄዱ ከክፉ ሰዎች መሸሽን እያስተማረን ነው፡፡ ኢየሩሳሌም ‹‹ወዮልሽ›› የሚያስብል ተግባር ውሰጥ ናት፡፡ አይቶ ያለቀሰላት ጊዜም ነበረ እንዲህ ፈጣሪዋን የምታሳዝን ከተማን ጥሎ መሸሽ ነው እንጂ ሌላ ምን አማራጭ ሊኖር? ይህም እንኳን በኛ ዘንድ ለማድረግ የሚከብድ ቢሆን የቀደመውን ኑሯችንን ካልቀየርን መጠመቃችን በምን ይታወቃል? ቀድሞ እንደምንኖረው እየኖርን ከሰይጣን ጋር መዋጋት አይቻልም፡፡ አሁን የጥንቱን ግብር መሸሽ ይገባናል፡፡

. የራስን ፈቃድ ለፈቃደ እግዚአብሔር ማስገዛት

‹‹መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው›› ሲል ምን ማለቱ ይመስላችኋል? መንፈስ ብዙ ትርጉም ቢኖረውም በዚህ ስፍራ ግን ፈቃዱ ተብሎ ተተርጉሟል ፈቃደ እግዚአብሔርና መንፈስ የተባለችና ጌታችን አነሣስቶ የወሰደው ቅዱስ ፈቃዱ ከሆነ እኛም የራሳችንን ፈቃድ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ብናስገዛ ሰይጣንን ‹‹ሑር እምድሕሬየ ሰይጣን›› ብለን መቈጣት እንችላለን፡፡ (ማቴ. ፬፥፩)

. መጾምና መጸለይ

ፈቃደ እግዚአብሔር በመብልና መጠጥ መኖር አይደለም፡፡ አብረሃም እግዚአብሔርን ያየው ሦስት ቀን ከማዕድ ርቆ ነው፡፡ ኤልያስም ብሔረ ሕያዋን የገባው አርባ ቀን ከምግብ ተከልክሎ ነው፡፡ ሙሴን፣ አባ ገብረ መንፈስ ቅዱስን፣ አባ ተክለ ሃይማኖትን የትኛውን ልጥራላችሁ ሁሉም አስደናቂ የሆነ አኗኗር ያላቸው ናቸው፡፡ ከእነሱ መካከል ከፀሐይ በላይ ከሰማይ በታች የኖረ አለ፤ ክንፍ አውጥቶ ወደ ሰማይ የበረረም አለ፤ ከሰባቱ የእሳት መጋረጃ ገብቶ እግዚአብሔርን ያመሰገነ አለ፡፡ ከመብልና ከመጠጥ መራቅ የጸጋ ሁሉ ምንጭ ናት፡፡

. ከጾምና ከጸሎት በኋላ ፈተና መኖሩን ማሰብ ይገባል፡፡

ቅዱሳን ከበቁ በኋላም ‹‹አቤቱ ወደ ፈተና አታግባን›› የሚለውን ጸሎተ ወንጌል አያልፉትም፡፡ ሰይጣን ሥራ የሚፈታበት ጊዜ የለውምና፡፡ ጌታም ከጾመና ከጸለየ በኋላ መፈተኑ ብትጾሙና ብትጸልዩም ፈተና አለባችሁና ተዘጋጁ ማለቱ ነው፡፡ ነገር ግን የጾመና የጸለየ ሰው በፈተና ድል አይነሣም እንዲያውም የተዘረጋ ጥሬ ላይ የሰፈሩ ወፎችን እንደማባረር አጋንንትን ዕልፍ ሁለት ዕልፍ ቢሆኑም በአንድ ቃል ማባረር ይቻላል፡፡

አስተውሉ ከሰይጣን የሚያንስ ደካማ ከክርስቲያንም የሚበልጥ ጠንካራ የለምና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድል ነሥቶ ያባረረውን ሰይጣን መልሰን ወደ ሰውነታችን እንዳናስገባው በርትተን እንጹም እንጸልይ፡፡  ለዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ይርዳን፤ አሜን።