‹‹ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ›› (ሚል ፫፥፯)

የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

የሰው ልጆችን ጥፋት የማይወደው ፈጣሪያችን እግዚአብሔር በንስሓ እንድንመለስ ይሻል፤ ‹‹ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ›› ብሎም ዘወትር ወደ እርሱ ይጠራናል፡፡ (ሚል ፫፥፯)

ሰዎች በሕይወታችን ውስጥ ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ፈጣሪያችን እግዚአብሔርን ማሳዘናችን እና ማስቆጣታችን አይቀሬ ነው፡፡ እርሱ የጽድቅ አምላክ ነውና ክፋትንም ሆነ ጥፋትን አይወድም፡፡ በዚህም ከእኛ ኑሮ እና የዕለት ከዕለት ተግባር ውስጥ አይጨመርልንም፤ ኃጢአታችን በበዛም ቊጥርም ከእኛ እጅጉን ይርቃል፡፡ ሆኖም ግን ዘወትር በሚጨምርልን ዕድሜ የእኛን መመለስ ይጠብቃል፡፡ ቸርነቱ እና ምሕረቱ የበዛ አምላክ በመሆኑም ከልብ ተጸጽቶ ይቅርታና ሥርየትን ለሚሻ ሁሉ ምሕረትን ያደርጋል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሲያስተምር ለተሰበሰቡት አሕዛብ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ታናሹ ልጁም አባቱን፥ ‹አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ከፍለህ ስጠኝ› አለው፤ ገንዘቡንም ከፍሎ ሰጠው፡፡ ከጥቂት ቀን በኋላም ያ ትንሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ ሀገር ሄደ፤ በዚያም በመዳራት እየኖረ ገንዘቡን ሁሉ በተነ፤ አጠፋም፡፡ ገንዘቡንም ሁሉ በጨረሰ ጊዜ፥ በዚያ ሀገር ጽኑ ራብ መጣ፤ እርሱም ተቸገረ፡፡

ሄዶም ከዚያ ሀገር ሰዎች ለአንዱ ተቀጠረ፤ እሪያዎችንም ይጠብቅ ዘንድ ወደ እርሻው ቦታ ሰደደው፡፡ እሪያዎች ከሚመገቡት አሰር ይጠግብ ዘንድ ተመኘ፤ ግን የሚሰጠው አልነበረም፡፡ በልቡም እንዲህ ብሎ ዐሰበ፡- እህል የሚተርፋቸው የአባቴ ሠራተኞች ምን ያህል ናቸው? እኔ ግን በዚህ በረኃብ ልሞት ነው፡፡ ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና እንዲህ ልበለው፡- ‹አባቴ ሆይ፥ በሰማይም፥ በፊትህም በደልሁ፡፡ እንግዲህ ወዲህስ ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ፡፡›

ተነሥቶም ወደ አባቱ ሄደ፤ አባቱም ከሩቅ አየውና ራራለት፤ ሮጦም አንገቱን አቅፎ ሳመው፡፡ ልጁም፡- ‹አባቴ ሆይ፥ በሰማይም፥ በፊትህም በደልሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ነገር ግን ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ› አለው፡፡ አባቱም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፡- ‹ያማሩ ልብሶችን ቶሎ አምጡና አልብሱት፤ ለጣቱም ቀለበት፥ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት፤› የሰባውን ፍሪዳም አምጡና እረዱ፤ እንብላ፤ ደስም ይበለን፡፡ ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኖአልና፥ ጠፍቶም ነበር፤ ተገኝቶአልና ደስ ይላቸው ጀመር፡፡›› (ሉቃ. ፲፭፥፲፩-፳፬)

ከዚህም በኋላ ‹‹ታላቁ ልጁም በእርሻ ነበርና ተመልሶ ወደ ቤቱ አጠገብ በደረሰ ጊዜ የዘፈኑንና የመሰንቆውን ድምጽ ሰማ፡፡ ከአባቱ ብላቴናዎችም አንዱን ጠርቶ፡- ‹ይህ የምሰማው ምንድን ነው?› አለው፡፡ እርሱም፡- ‹ወንድምህ ከሄደበት መጣ፤ አባትህም የሰባውን ፍሪዳ አረደ፤ በሕይወት አግኝቶታልና› አለው፡፡ ተቈጥቶም ‹አልገባም› አለ፤ አባቱም አለ፡፡ አባቱም ወጥቶ ማለደው፡፡ መልሶም አባቱን እንዲህ አለው፡- ‹እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት ተገዛሁልህ፤ ፈጽሞ ከትእዛዝህ አልወጣም፤ ለእኔ ግን ከባልንጀሮቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ የፍየል ጠቦት እንኳ አልሰጠኸኝም፡፡ ከአመንዝሮች ጋር ገንዘብህን ሁሉ የጨረሰ ይህ ልጅህ በተመለሰ ጊዜ ግን የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት፡፡ አባቱም እንዲህ አለው፡- ‹ልጄ አንተማ እኮ ዘወትር ከእኔ ጋር ነህ፤ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበር፡፡ ሕያው ሆኖአልና፥ ጠፍቶም ተገኝቶአልና፥ ደስ ሊለን፥ ሐሴትም ልናደረግ ይገባል፡፡›› (ሉቃ. ፲፭፥፳፭-፴፪)

ከዚህ ታሪክ የምንረዳው ከልብ ተጸጽቶ ወደ ፈጣሪው እግዚአብሔር የሚመለስ ማንኛውም በደለኛ ምሕረት ይቅርታ እንደሚደረግለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ኃጢአታችን ምንም ያህል የከፋ ቢሆንም እንኳን በንስሓ ሥርየትን ማግኘት እንደምንችል በቅዱስ ወንጌል አስተምሮናል፡፡ በንስሓም መንጻት እንሚያስፈልግ በዚህ እንረዳለን፤ ያለ ንስሓ ድኅነት የለምና፡፡

ሀ. ንስሓ ምንድን ነው?

ንስሓ ‹ነስሐ› ከሚለው ግእዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ ትርጓሜውም ኀዘን፣ ጸጸት፣ ቊጭት፣ መቀጮ፣ ቅጣት፣ ቀኖና፣ የኃጢአት ካሳ ማለት ነው፡፡ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገብ ቃላት ገጽ ፮፻፶፮)

ንስሓ ከኃጢአት ባርነትና ከዲያብሎስ ነፃ መውጣት ነው፡፡ የኃጢአት ልምዶችንና ክፉ ምኞትን ከመከተልም ነፃ ያደርጋል። ጌታችን መድኃታኒችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እኛን ከኃጢአት ባርነት ነፃ ካወጣን በኋላም የንስሓን ሥርዓት ሠርቶልናልና፡፡ ‹‹ወልድ አርነት ካወጣችሁ በእውነት አርነት የወጣችሁ ናችሁ›› እንዲል፤ (ዮሐ. ፰፥፴፮)

ለ. የንስሓ አፈጻጸም

ንስሓ ሦስት የአፈጻጸም ደረጃዎች አሉት፡-

፩. ንስሓ ለመግባት መወሰን

በሕይወታችን ውስጥ የሠራናውን ኃጢአት በሙሉ ለይተን ማወቅና ከእኩይ ተግባራችን መራቅ እንደዚሁም ከዚህ በፊት ለሠራነው ኃጢአት ሥርየት ለማግኘት መወሰን አለብን፡፡

፪. ኃጢአትን መተው

ንስሓ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብሎ ኃጢአትን ርግፍ አድርጎ መተው ነው። አምላካችንን እግዚአብሔርን ከልብ የምንወድ ከሆነ ከእርሱ ፍቅርና ጸጋ የሚለየንን ኃጢአት ወይም በኃጢአት መኖርን ፈጽመን ልንተው ይገባል፡፡

፫. ኃጢአትን መጥላት

የሠራነው ኃጢአት ምን ያህል ፈጣሪያችን እግዚአብሔርን እንዳስከፋ እንዲሁም ከእርሱ እንዳራቀን በመረዳትና በመጸጸት ኃጢአትን መጥላት ከዚያም መቼም ቢሆን ተመልሰን ያንን የተውነውን ክፉ ተግባር አለመፈጸም ነው፡፡ ስለዚህም ኃጢአትንና በኃጢአታችንን ምክንያት የምናጣውን ጸጋ እግዚአብሔር ሁሉ እያሰብን ፈጽሞ መራራ የሆነውን ጣዕሙንም እያስታወስን ኃጢአትን ልንጠላው ይገባል፡፡

ኃጢአት ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚያጣላን ሁሉ ንስሓም ከእግዚአብሔር ጋር መታረቂያችን ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለክርስቶስ መልእክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔርም ጋር ታረቁ ብለን ስለክርስቶስ እንለምናለን፡፡›› (፪ኛ ቆሮ.፭፥፳)

የንስሓ ሥርዓት

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ንስሓ የምንገባበትን እና ኃጢአታችንን ስንናዘዝ የምናደርገውን የንስሓ ሥርዓት ቅደም ተከተል ሠርታልናለች፡፡ በዚሁ መሠረት፡-

፩. ኃጢአትን ለንስሓ አባት መናዘዝና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን (ቅጣትን) መቀበል
፪. በንስሓ ጥምቀት መንጻት (መጠመቅ)
፫. ሥጋ ወደሙን መቀበል (መቊረብ) ያስፈልጋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በኃጢአታችን የተነሣ ከአምላካችን እግዚአብሔር ርቀናል፤ የእርሱን ምሕረትም ሆነ ቸርነት ለማግኘት ተስኖናል፤ ዓይነ ልቡናችንን የሠወረውና ልባችንን ያደነደነብን ክፋታችንና ትዕቢታችን ደግሞ ከጠፋንበት መንገድ እንዳንመለስ መሰናክል ወይም እንቅፋት ሆኖብናል፡፡ ይህን እውነት እንኳን ሰምቶ ለማመንም ሆነ ለመቀበል ፈጽሞ ተስኖናል፡፡

ስለዚህም ለንስሓ ለመብቃት እኛ ራሳችን ከፊታችን የተጋረደብንን ጠላት ማሸነፍ ከእኛ ይጠበቅብናል፤ እንደ ግብዝ በስንፍና ከመኖር ይልቅ በንስሓ ወደ እግዚአብሔር በመመለስ፤ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን እንደ ጻድቃን ሰማዕታት ሁሉ ለሃይማኖታችን መሥዋዕት መክፈል እንጂ ለኃጢአት መቼም ቢሆን መሸነፍ የለብንም፡፡

ስለሆነም ማንኛውም ኃጢአተኛ ሰው ይቅርታንና ምሕረትን ለማግኘት በመጀመሪያ የንስሓን አስፈላጊነት ተረድቶ እና አምኖ በሥርዓቱ መሠረት በንስሓ ሊነጻ ይገባል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ለንስሓ ያብቃን፤ አሜን፡፡