የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ልደት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

 ሰኔ ቀን ፳፻፱ .

ዮሐንስ ማለት ‹‹እግዚአብሔር ጸጋ ነው›› ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ወንጌልም መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ፍሥሐ ወሐሴት (ተድላና ደስታ) ይለዋል፤ ወላጆቹ በእርሱ መወለድ ተደስተዋልና (ሉቃ. ፩፥፲፬)፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሰኔ ፴ ቀን የተወለደበት፤ መስከረም ፩ ቀን ቃል ኪዳን የተቀበለበት፤ መስከረም ፪ ቀን በሰማዕትነት ያረፈበት፤ ጥር ፲፩ ቀን ጌታችንን ያጠመቀበት፤ የካቲት ፴ ቀን ራሱ የተገኘችበት፤ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ራሱ ያረፈችበት (ነፍሱ የወጣችበት)፤ ሰኔ ፪ ቀን ደግሞ ፍልሰተ ዐፅሙ (ዐፅሙ የፈለሰበት) በዓል በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ይከበራል፡፡ በዛሬው ዝግጅታችንም የልደቱን ታሪክ በአጭሩ እናስታውሳችኋለን፤

በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ፣ ከቍጥር አንድ ጀምሮ እንደ ተገለጸው ካህኑ ዘካርያስ እና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ዅሉ በመፈጸም ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ፡፡ ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድም እግዚአብሔርን ዘወትር ይማጸኑት ነበር፡፡ ካህኑ ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን በማሳረግ ላይ ሳለም የእግዚአብሔር መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ጸሎቱ እንደ ተሰማና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ እንደምትወልድ፤ ስሙንም ዮሐንስ እንደሚለው፤ በመወለዱም ብዙዎች እንደሚደሰቱ፤ ልጁም በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ እንደሚኾን፤ የወይን ጠጅ እና የሚያሰክር መጠጥ እንደማይጠጣ፤ እንደዚሁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሞላበት ነገረው፡፡

ካህኑ ዘካርያስም መልአኩን ‹‹እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፡፡ እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚኾን ቀን ድረስ ዲዳ ትኾናለህ፤ መናገርም አትችልም›› አለው፡፡ ከውጪ ቆመው ጸሎት ሲያደርጉ የነበሩት ሕዝብም ዘካርያስን ከቤተ መቅደስ እስኪወጣ ይጠብቁት ነበር፤ በመዘግየቱም ይደነቁ ነበር፡፡ ከቤተ መቅደስ በወጣም ጊዜ ሊያናግራቸው ባለመቻሉ ይጠቅሳቸው ነበር፡፡ በኹኔታውም በቤተ መቅደስ ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፡፡ እርሱም ድዳ ኾኖ ኖረ፡፡ የማገልገሉም ወራት ሲፈጸምም ወደ ቤቱ ሔደ፤ ከሁለት ቀን በኋላም አረጋዊቷ ቅድስት ኤልሳቤጥ ፀነሰች፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥም በመካንነቷ ከሰዎች የሚደርስባት ሽሙጥ ተወግዷላታልና ‹‹እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ እንዲህ አደረገልኝ›› ስትል ለአምስት ወራት ተሸሸገች፡፡

የመውለጃዋ ቀን ሲደርስም ዘመነ ብሉይ ሊፈጸም፣ እግዚአብሔር ሰው ሊኾን (በሥጋ ሊገለጥ) ስድስት ወራት ሲቀረው፣ ሰኔ ፴ ቀን ንዑድ፣ ክቡር የኾነው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ተወለደ፡፡ ዘመዶቹ ስሙን በአባቱ መጠርያ ዘካርያስ› ሊሉት ቢወዱም እናቱ ግን ‹‹ዮሐንስ ይባል› አለች፡፡ የመልአኩን የብሥራት ቃል ባለመቀበሉ አንደበቱ ተይዞ የነበረው ካህኑ ዘካርያም ስሙ ዮሐንስ ይባል ብሎ ሲጽፍ አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተፈታ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶም ‹‹አንተ ሕፃን ሆይ! የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሔዳለህና፡፡ የኀጢአታቸው ስርየት የኾነውን የመዳን ዕውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፡፡ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፡፡ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል፤ እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል፤›› በማለት የቅዱስ ዮሐንስን ነቢይነት እና አጥማቂነት፣ እንደዚሁም የክርስቶስን የማዳን ትምህርት አብሣሪነት የሚመለከት ትንቢት አስቀድሞ ተናገሯል (ሉቃ. ፩፥፶፯-፸፱)፡፡

በአጠቃላይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ከአዲስ ኪዳን አበው አንዱ የኾነ፣ ንጹሓን ነቢያት፣ ቅዱስ ገብርኤልና አባቱ ዘካርያስ ትንቢት የተናገሩለት፤ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅኑት እንደ ገበሬ፣ ጽሙድ እንደ በሬ ኾኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ፤ በፍጹም ልቡ ዓለምን የናቀ፤ ከተድላዋና ከደስታዋም የተለየ፤ አምላክን ለማጥመቅ የታደለ ሐዋርያ፣ መምህር፣ ሰማዕት፣ ባሕታዊ፣ ነቢይ፣ ጻድቅ ነው፡፡ ሊቁም ከመላእክት፣ ከነቢያት፣ ከካህናት፣ ከሐዋርያት መካከል እንደርሱ መለኮትን ለማጥመቅ የተመረጠ አለመኖሩን በመጥቀስ ‹‹… ዮሐንስ ከማከ ሶበ ፈተዉ ወጽሕቁ፤ እሳተ ነዳዴ ኢተክህሎሙ ያጥምቁ፤ ራጉኤል በትጋሁ ወኢዮብ በጽድቁ፤ዮሐንስ ሆይ! ራጉኤል በትጋቱ፣ ኢዮብም በጽድቁ ቢመኙም ኾነ ቢጨነቁ እንደ አንተ የሚነድ እሳትን (መለኮትን) ሊያጠምቁ አልተቻላቸውም›› ሲል ታላቅነቱን መስክሮለታል (መልክአ ዮሐንስ መጥምቅ፣ ለአዕይንቲከ)፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ በረከቱ ይደርብን፤ ጸሎቱ ይጠብቀን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፦

  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፴ ቀን፤
  • የሉቃስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ፣ ሉቃ. ፩፥፩-፹፤
  • ገድለ ዮሐንስ መጥምቅ፡፡

ዘመነ ክረምት – ክፍል አንድ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ወቅቶች በአራት ይከፈላሉ፡፡ በቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት፣ እንደዚሁም በመጽሐፈ ግጻዌ እንደ ተገለጸው እነዚህም፡- ዘመነ መጸው (መከር)፣ ዘመነ ሐጋይ (በጋ)፣ ዘመነ ጸደይ (በልግ) እና ዘመነ ክረምት ይባላሉ፡፡ ከአራቱ ወቅቶች መካከል ከሰኔ ፳፭ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ (አሁን የምንገኝበት ወቅት) ዘመነ ክረምት ተብሎ ይጠራል፡፡

እንደ ማስገንዘብያ፡- ክረምቱ የሚጀምረው ሰኔ ፳፮ ቀን ቢኾንም ከዋይዜማው ጀምሮ የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር ዘመነ ክረምትን የሚመለከት ስለ ኾነ ከሰኔ ፳፭ ቀን ጀምረን መቍጠር እንችላለን፡፡ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንዳስረዱን ከዋይዜማው ወይም ከመነሻው ጀምረን ቀኑን መጥቀሳችን የአስተምህሮ ለውጥ አያመጣም፡፡ ይህ አቈጣጠር ለሌሎች ወቅቶች እና ለዘመነ ክረምት ክፍሎችም ተመሳሳይ መኾኑን ከወዲሁ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! በዚህ ዝግጅት ዘመነ ክረምትን የሚመለከት ተከታታይ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም የንባብ ጊዜ!

‹ክረምት› ከረመ፣ ከረመ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም የዝናም፣ የአዝርዕት፣ የአረም ጊዜ፤ እንደዚሁም ዕፅዋት፣ አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር በአረንጓዴ ዕፀዋትና በልምላሜ የምታሸበርቅበት ወቅት ማለት ነው፡፡ ይኸው ዘመነ ክረምት በሰባት ንዑሳን ክፍሎች ይመደባል፤ የክፍፍሉ መሠረት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሲኾን፣ ክፍሎቹም የሚከተሉት ናቸው፤

፩ኛ ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ያለው ጊዜ በአተ ክረምት ወይም ዘርዕ፣ ደመና፤

፪ኛ ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፱ ቀን ያለው ጊዜ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል፤

፫ኛ ከነሐሴ ፲ – ፳፯ ቀን ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ፤

፬ኛ ከነሐሴ ፳፰ እስከ ጳጉሜን ፭ (፮) ቀን ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባህ፣ ብርሃን፣ መዓልት፤

፭ኛ ከመስከረም ፩ – ፯ ቀን ዮሐንስ፤

፮ኛ ከመስከረም ፰ – ፲፬ ቀን ፍሬ፤

፯ኛ ከመስከረም ፲፭ – ፳፭ ቀን ፀአተ ክረምት (የክረምት መውጫ) ወይም ዘመነ መስቀል፡፡

እያንዳንዱን ክፍለ ክረምትም በመጠኑ እንደሚከተለው ለመዳሰስ እንሞክራለን፤

፩. በአተ ክረምት (ዘርዕ፣ ደመና)

ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ድረስ ያለው የመጀመሪያው የክረምት ክፍለ ጊዜ በአተ ክረምት ወይም ዘርዕ፣ ደመና ይባላል፡፡ በዚህ ወቅት ስለ ክረምት መግባት፣ ስለ ዘርዕ፣ ስለ ደመና እና ስለ ዝናም የሚያዘክሩ መዝሙራትና ምንባባት ይዘመራሉ፤ ይነበባሉ፡፡ ይህ ወቅት ደመና ሰማዩን የሚሸፍንበት፤ የዝናም መጠን የሚያይልበትና መሬት በዝናም ረክታ ዘር የምታበቅልበት ጊዜ ነው፡፡

በአተ ክረምት (የክረምት መግብያ)

በዘመነ ክረምት መጀመርያ (መግብያ) ሳምንት በቤተ ክርስቲያናችን የሚቀርበው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር የሚከተለው ነው፤

‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይጸግቡ ርኁባን ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሑ ነዳያን ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ወሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ደምፀ እገሪሁ ለዝናም››

የመዝሙሩ ቀጥተኛ ትርጕም፡-

‹‹የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ ዝናም በሚዘንም ጊዜ የተራቡ ይጠግባሉ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ ዝናም በሚዘንም ጊዜ ድሆች ይደሰታሉ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ አምላካችን ለሰው ልጅ ዕረፍት ሰንበትን ፈጠረ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡››

ይህ መዝሙር ከሰኔ ፳፮ ጀምሮ ያለው ወቅት ክረምቱ የሚገባበት እና ዝናም በብዛት የሚጥልበት ጊዜ መኾኑን የሚያበሥር ሲኾን፣ በተጨማሪም ዝናም በሚዘንብበት ጊዜ የሚበቅለውን እኽልና የምንጮችን መብዛት ተስፋ በማድረግ የተራቡ እንደሚጠግቡ፤ የተጠሙም እንደሚረኩ የሚያትት ምሥጢር ይዟል፡፡ እንደዚሁም ጊዜ ለበጋ፣ ጊዜ ለክረምት የሚሰጥ አምላክ ለሰው ልጅ ማረፊያ ትኾን ዘንድ ዕለተ ሰንበትን መፍጠሩንም ያስረዳል፡፡ በዚህ ሳምንት በዕለተ ሰንበት በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ምንባባትም የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው፤

፩ኛ ቆሮንቶስ ፲፭፥፴፫ – ፶፩

ፍሬ ዐሳቡ፡- አዝርዕት በስብሰው እንደሚበቅሉ ዅሉ የሰው ልጅም ከሞተ በኋላ ከሞት እንደሚነሣ፤ ሲነሣም እግዚአብሔር እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን እንደሚከፍለው፤ እንደዚሁም የሰው ልጅ ሞቱንና የሚያገኘውን ሰማያዊ ዋጋ በማሰብ ከኀጢአት መለየት እንደሚገባው ያስረዳል፡፡

ያዕቆብ ፭፥፲፮ እስከ ፍጻሜው

ፍሬ ዐሳቡ፡- ነቢዩ ኤልያስ በጸሎት ዝናም እንዳይዘንምና እንደገና እንዲጥል ማድረጉን በመተረክ እኛም እምነቱ ካለን በጸሎት ኹሉን ማድረግ እንደሚቻለን ይናገራል፡፡

ግብረ ሐዋርያት ፳፯፥፲፩ – ፳፩

ፍሬ ዐሳቡ፡- ቅዱስ ጳውሎስና ተከታዮቹ መርከባቸው በማዕበል ክፉኛ መናወጧንና በእግዚአብሔር ኃይል መዳናቸውን፤ በባሕሩ ውስጥም በጨለማ ለብዙ ጊዜ መቆየታቸውን በማውሳት ይህ ወቅት (ዘመነ ክረምት) የውኃና የነፋስ ኃይል የሚያልበት ጊዜ መኾኑን ያስተምራል፡፡

ምስባክ፡- መዝሙር ፻፵፮፥፰

ኃይለ ቃሉ፡- ‹‹ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር ዘያበቍል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡››

የመዝሙሩ ቀጥተኛ ትርጕም፡- ‹‹ሰማዩን በደመና የሚሸፍን፣ ለምድርም ዝናምን የሚያዘጋጅ፣ ሣርን በተራሮች ላይ የሚያበቅል እርሱ ነው፡፡››

የመዝሙሩ ፍሬ ዐሳብ፡- እግዚአብሔር ሰማዩን በደመና የሚሸፍን፤ ዝናምንም (ክረምትን) ለምድር (ለሰው ልጅ) የሚያዘጋጅ፤ እንደዚሁም በተራሮች ላይ ሣርን (ዕፀዋትን) የሚያበቅል አምላክ መኾኑን ያስገነዝባል፡፡

ወንጌል፡- ሉቃስ ፰፥፩-፳፪

ፍሬ ዐሳቡ፡- ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃለ እግዚአብሔርን በዘርዕ፣ የምእመናንን ልቡና (የመረዳት ዓቅም) ደግሞ በመንገድ፣ በዓለት፣ በእሾኽና በመልካም መሬት በመመሰል ቃሉን ሰምተው በሚለወጡትና በሚጠፉት መካከል ስላለው ልዩነት ማስተማሩን ያስረዳል፡፡

ቅዳሴው፡- ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ ሲኾን ይህ ቅዳሴ ስለ ዝናም፣ ደመና፣ መብረቅ፣ ባሕርና መሰል ፍጥረታት ዑደት፤ እንደዚሁም እግዚአብሔር ዓለማትን በጥበቡ ፈጥሮ የሚገዛና የሚመግብ አምላክ መኾኑን ስለሚያብራራ በዘመነ ክረምት ይቀደሳል፡፡

ጠቅለል አድርገን ስንገልጸው በዘመነ ክረምት መጀመርያ ሳምንት ከአዝርዕት፣ ከዝናም፣ ከልምላሜ፣ ከውኃ ሙላትና ከባሕር ሞገድ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ትምህርቶች ከሰው ልጅ ሕይወትና ከምግባሩ እንደዚሁም በምድር ከሚያጋጥሙት ፈተናዎች ጋር እየተነጻጸሩ ይቀርባሉ፡፡ የወቅቱን ትምህርት ከሕይወታችን ጋር አያይዘን ስንመለከተውም ዘመነ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፡፡ ገበሬ በክረምት ብርዱንና ዝናሙን ሳይሰቀቅ ለሥራ ይሰማራል፤ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሣል፡፡ ይህም ምእመናን በሰማያዊው ዓለም የምናገኘውን ተድላና ደስታ በማሰብ በምድር ቆይታችን የሚደርስብንን ልዩ ልዩ መከራ በትዕግሥት ማሳለፍ እንደሚገባን ያስገነዝባል፡፡

ይቆየን

ለተተኪ መምህራን ሥልጠና መስጠቱን የአሜሪካ ማእከል አስታወቀ

ሠልጣኞቹ ከአሠልጣኝ መምህራን እና ከኦሀዮ ደ/ሰ/ቅ/ገብርኤል ቤ/ክ የመስተንግዶ ኮሚቴ አባላት ጋር

ሰኔ ፳፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምርያ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል በኒውዮርክ ሀገረ ስብከት በኮሎምበስ ኦሀዮ ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከሰኔ ፲፮ – ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ለሦስት ቀናት የቆየ የተተኪ መምህራን ሥልጠና መስጠቱን አስታወቀ፡፡

እንደ ማእከሉ ማብራርያ በማእከሉ የትምህርት፣ ሐዋርያዊ ተልእኮ እና የምክር አገልግሎት ዋና ክፍል አዘጋጅነት በተሰጠው በዚህ ሥልጠና በቍጥር ከዐሥር ከሚበልጡ ስቴቶች ከየንዑሳን ማእከላቱ የተወከሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የተሳትፉ ሲኾን፣ የሥልጠናው ዓላማም ሠልጣኞቹ በስብከተ ወንጌል ሊያገለግሉ የሚችሉበትን ዕውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ ለማገዝ ነው፡፡

ትምህርተ ሃይማኖት (ዶግማ)፣ መንፈሳዊ አስተዳደር፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ የስብከት ዘዴ እና ክብረ ቅዱሳን በሥልጠናው የተካተቱ የትምህርት ክፍሎች ሲኾኑ፣ መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ፣ መልአከ ሰላም ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅን፣ ቀሲስ ኅብረት የሺጥላ፣ መምህር ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም እና መምህር ብርሃኑ አድማስ ሥልጠና በመስጠት የተሳተፉ መምህራን ናቸው፡፡

ለሦስት ቀናት በተሰጠው በዚህ ሥልጠና በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲኾን፣ በውይይቱ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ ከሠልጣኞቹ ለመረዳት መቻሉንም ማእከሉ በዘገባው አትቷል።

በሥልጠናው የመፈጸሚያ ዕለት እሑድ ከቅዳሴ በኋላ በተደረገው የምረቃ መርሐ ግብር በመምህር ብርሃኑ አድማስ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲኾን፣ ሠልጣኞቹም ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ በማእከሉ የተዘጋጀው የምስክር ወረቀትም በመልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ አማካይነት ለሠልጣኞች ተበርክቷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ የደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅን ሥልጠናው በደብራቸው በመሰጠቱ እርሳቸውም ኾኑ ምእመናኑ እጅግ መደሰታቸውን ከገለጹ በኋላ ለወደፊት ሥልጠናው በየጊዜው ሲዘጋጅ ደብራቸው በመስተንግዶ ተባባሪ እንደሚኾን ቃል ገብተዋል።

መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ በበኩላቸው ሥልጠናው ተግባራዊ በመኾኑ የተሰማቸው ደስታ ወሰን እንደ ሌለው ገልጸው ሠልጣኞቹ በተሰጣቸው አደራ ቤተ ክርስቲያንን በትጋት እንዲያገለግሉ መክረዋል።

አያይዘውም ለሥልጠናው መሳካት አስተዋጽዖ ያደረጉ የማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ አባላትን፣ ሥልጠናውን በትጋት ያስተባበሩ የትምህርት ክፍል ሓላፊዎችን፣ እንደዚሁም የምግብና መኝታ ሙሉ ወጭውን በመቻል በመስተንግዶው ድጋፍ ያበረከቱ ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅንን፣ በአጠቃላይ የኦሀዮ ደ/ሰ/ቅ/ገብርኤል ሰበካ ጉባኤ አመራር አባላትን እና ሕዝበ ክርስቲያኑን መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ ከልብ አመስግነዋል።

የአሜሪካ ማእከል ሰብሳቢ አቶ ማስተዋል ጌጡ በዕለቱ ባስተላለፉት መልእክት ሠልጣኞቹ በሥልጠናው የቀሰሙትን ትምህርት አስፋፍተውና አሳድገው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ በማፋጠን የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በመጨረሻም የተተኪ መምህራን ሥልጠናው ለወደፊትም በየዓመቱ እንደሚሰጥ ያስታወቁት ሰብሳቢው፣ ከአሁን በፊት የሥልጠና ዕድሉን ያላገኙ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ሥልጠናውን እንዲወስዱ ለማድረግ ማኅበረ ቅዱሳን ቅድመ ኹኔታዎችን በማመቻቸት ላይ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹እናንተ የቤተ ክርስቲያን ባለ አደራዎች ናችሁ›› – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርቱን ባስመረቀበት ዕለት ተገኝተው በሰጡት ቃለ ምዕዳን ‹‹እናንተ የቤተ ክርስቲያን ባለ አደራዎች ናችሁ›› በማለት ተመራቂዎቹ ወንጌልን ከዳር እስከ ዳር የማዳረስ አደራ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

‹‹እናንተ ከመልካም ዛፍ የተገኛችሁ መልካም ፍሬዎች እንደ መኾናችሁ ይህን ፍሬያችሁን እንድታካፍሉ ቤተ ክርስቲያን አደራ ትላችኋለች›› ያሉት ቅዱስነታቸው ‹‹መብራታችሁ በሰዉ ዅሉ ፊት ይብራ›› የሚለውን የወንጌል ቃል መነሻ አድርገው በከተማ ብቻ ሳይወሰኑ በየገጠሩ በመዘዋወር በአታላዮች የሚወሰዱ ወገኖችን እንዲጠብቁ እና እንዲያስተምሩ ተመራቂዎቹን አሳስበዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በየገጠሩ አንድ ሰባኬ ወንጌል ጠፍቶ በየከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ በአንድ አጥቢያ ከሁለት በላይ መምህራን መመደባቸውን ተችተዋል፡፡

ሴቶች በመንፈሳዊ ኮሌጁ ተምረው በመመረቃቸውና ከፊሎቹም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገባቸው መደሰታቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ይህን ፈለግ ተከትለው በየኮሌጆቹ የሚሰጠውን ትምህርተ ሃይማኖት እንዲከታተሉና ራሳቸውን በቃለ እግዚአብሔር እንዲያጎለብቱ እናቶችና እኅቶችን መክረዋል፡፡

በመጨረሻም ተመራቂዎቹ በሚሠማሩበት ቦታ ዅሉ በስብከተ ወንጌል ተግተው በማገልገል፤ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ደግሞ የሰባክያነ ወንጌልን አገልግሎት በመቈጣጠር፤ ምእመናኑም ከትክክለኞች መምህራን ትክክለኛውን ቃለ ወንጌል በመማር መንፈሳዊ ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርቱን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ አባቶች ካህናት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተመራቂ ቤተሰቦች በተገኙበት ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ አስመርቋል፡፡

ኮሌጁ ደቀ መዛሙርቱን ያስመረቀው በቀን፣ በማታ በተመላላሽ እና በርቀት መርሐ ግብር፤ በልዩ ልዩ የትምህርት ክፍል፤ በማስተርስ፣ በዲግሪ እና በዲፕሎማ ማዕረግ ነው፡፡ በዕለቱ ተመራቂዎቹ ባለ አምስት አንቀጽ የአገልግሎት ቃል ኪዳናቸውን በተወካያቸው አማካይነት አቅርበዋል፡፡ ሴቶች እኅቶቻችንም በልዩ ልዩ ማዕረግ የተመረቁ ሲኾን ከእነርሱ መካከል ጥቂቶቹ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ መሸለማቸው ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያፈራ የኖረና በማፍራት ላይ የሚገኝ አንጋፋ የትምህርት ማእከል ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ባለ አደራዎች ሰባክያነ ወንጌል መፍለቂያ የኾነው ኮሌጁ ከኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ያፈነገጠ የኑፋቄ ትምህርት ሲያዛምቱ የተገኙ ሰርጎ ገብ ተማሪዎችን ከአሁን በፊት አውግዞ እንደ ለየ፤ ለወደፊትም ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ሳይፋለስ ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ሥርዓቱን የጠበቀ ትምህርት የመስጠት ተልእኮዉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኮሌጁ የቦርድ ሥራ አመራር ሪፖርት ተገልጿል፡፡

የአባ ሙሴ ጸሊም ዕረፍት

አባ ሙሴ ጸሊም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፱ .

ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰውና ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከልዩ ልዩ ዓለማዊ ሥራ ጠርቶ ቃሉን ለመስበክ፣ ስሙን ለመቀደስ እና ክብሩን ለመውረስ ያበቃቸው ቅዱሳን ብዙዎች ናቸው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን በኃጢአት ሕይወት ከኖሩ በኋላ በንስሓ ተመልሰው ለመንግሥተ ሰማያት ከተጠሩ ጻድቃን መካከል አንዱ የኾኑትን የአባ ሙሴ ጸሊምን የዕረፍት ታሪክ በአጭሩ እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል፤

የአባ ሙሴ ጸሊም (ጥቁሩ ሙሴ) በዓለ ዕረፍት በየዓመቱ ሰኔ ፳፬ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡ አባ ሙሴ ቆዳቸው ጥቁር በመኾኑ ‹ጸሊም› (ጥቁር) በሚል ቅጽል ስም ይጠራሉ፡፡ እኒህ ቅዱስ ለሰማዕትነት ክብር ከመብቃታቸው በፊት በቆዳቸው ብቻ ሳይኾን በግብራቸውም የጠቆሩ ማለትም ኀጢአትን የሚሠሩ ነበሩ፡፡ ያለ መጠን ይበሉ፣ ይጠጡ፣ ይቀሙ፣ ያመነዝሩ እንደዚሁም ሰው ይገድሉ ነበር፡፡ በሥጋቸው ጠንካራ፣ በጕልበታቸውም ኃይለኛ ከመኾናቸው የተነሣም ሊቋቋማቸው የሚችል ማንም እንዳልነበረ መጽሐፈ ስንክሳር ይናገራል፡፡ እግዚአብሔርን ካለማወቃቸው የተነሣ በባዕድ አምልኮ ተይዘው የኖሩት አባ ሙሴ ጸሊም ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይም ነበሩ፡፡

በዚህ ዓይነት ሰይጣናዊ ሥራ ከኖሩ ከዓመታት በኋላ የሰውን ልጅ ጠፍቶ መቅረት የማይወደው አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ወደ ቤቱ መልሶ አምላክነቱን ለመመስከር፣ ስሙን ለመቀደስ፣ መንግሥቱንም ለመውረስ መርጧቸዋልና የፀሐይን ፍጡርነት፣ ግዑዝነት ገለጸላቸው፡፡ ስለዚህም ብዙ ጊዜ ወደ ፀሐይ በማንጋጠጥ ‹‹ፀሐይ ሆይ አንተ አምላክ ከሆንኽ አነጋግረኝ … የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ›› እያሉ ይመራመሩ ጀመር፡፡ አባ ሙሴ ጸሊም፣ የገዳመ አስቄጥስ መነኮሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል፤ ያዩታል፤ እንደዚሁም ያነጋግሩታል እየተባለ ሲነገር ይሰሙ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ወደ ገዳሙ ይሔዱ ዘንድ አነሣሣቸው፡፡ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደዉም ከካህናቱ አንዱ የኾኑትን አባ ኤስድሮስን ‹‹እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጥቻለሁ›› አሏቸው፡፡ እርሳቸውም እግዚአብሔርን ፍለጋ ወደ ገዳሙ መምጣታቸውን አድንቀው ከአባ መቃርስ ጋር አገናኟቸው፡፡ አባ መቃርስም የክርስትና ሃይማኖትን አስተምረው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቀው ‹‹ታግሠህ የማስተምርህን ትምህርተ ወንጌል ከጠበክ እግዚአብሔርን ታየዋለህ›› እያሉ በተስፋ ቃል እያጽናኗቸው ቆዩ፡፡ ከዓመታት በኋላም በልዩ ልዩ ዓይነት ፈተና ፈትነው አመነኮሷቸው፡፡

አባ ሙሴ ጸሊም ብዙ ገድልን ከሚጋደሉ ቅዱሳን አብልጠው መጋደል በጀመሩ ጊዜም ሰይጣን ለማሰናከልና ከገዳሙ ለማስወጣት በማሰብ ቀድሞ ያሠራቸው በነበረው ግብረ ኃጢአት ሊዋጋቸው ጀመረ፡፡ አባ ኤስድሮስም እያጽናኑ፣ እየመከሩ በተጋድሏቸው ይበልጥ እንዲጸኑ ያተጓቸው ነበር፡፡ የመነኮሳቱ የውኃ መቅጃ ሥፍራ ሩቅ ነበርና አረጋውያን መነኮሳት በመንገድ ብዛት እንዳይደክሙ አባ ሙሴ ዘወትር ውኃ እየቀዱ በየበዓታቸው ደጃፍ ያስቀምጡላቸው ነበር፡፡ እንዲህ እያደረጉ በመጋደልና በማገልገል ላይ ሳሉ ጸላዔ ሠናያት ሰይጣን እግራቸውን በከባድ ደዌ መታቸውና ለብዙ ቀናት የአልጋ ቁራኛ ኾነው ኖሩ፡፡ እርሳቸውም በደዌ የሚፈታተናቸው ጥንተ ጠላት ሰይጣን መኾኑን ተረድተው ሰውነታቸው ደርቆ በእሳት የተቃጠለ እንጨት እስኪመስል ድረስ ተጋድሏቸውን እጅግ አበዙ፡፡ እግዚአብሔርም ትዕግሥታቸውን ዓይቶ ከደዌያቸው ፈወሳቸው፤ የሰይጣንን ውጊያ አርቆ ጸጋውን አሳደረባቸው፡፡

አባ ሙሴ፣ እርሳቸው ወደሚኖሩበት ገዳም የተሰበሰቡ ፭፻ የሚኾኑ ወንድሞች መነኮሳትን በአበ ምኔትነት እያስተዳደሩ ሳሉ ‹‹በመልካም ለሚያገለግሉት ከፍተኛውን ሹመት ይስጧቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ብዙ ባለሟልነት አለና›› (፩ኛጢሞ.፫፥፲፫) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው፣ ከተጋድሏቸውና ከትሕትናቸው አኳያ ማኅበረ መነኮሳቱ ለቅስና መዓርግ መረጧቸው፡፡ ሥርዓተ ክህነት ሊፈጽሙላቸው ወደ ቤተ መቅደስ በአቀረቧቸው ጊዜም ሊቀ ጳጳሳቱ ‹‹ይህን ጠቋራ ለምን አመጣችሁት? ከዚህ አውጡት›› ብለው አረጋውያኑን ተቆጧቸው፡፡ አባ ሙሴ ይህን ቃል ከሊቀ ጳጳሳቱ በሰሙ ጊዜም ‹‹መልክህ የከፋ ጠቋራ ሆይ! መልካም አደረጉብህ›› እያሉ ራሳቸውን በመገሠፅ ከቤተ መቅደስ ወጡ፡፡ ጽናታቸውንና ትዕግሥታቸውን የተመለከቱት ሊቀ ጳጳሳቱም በሌላ ቀን አባ ሙሴን አስጠርተው በአንብሮተ እድ በቅስና መዓርግ ሾሟቸው፡፡ ከዚያም ‹‹ሙሴ ሆይ! እነሆ በውስጥም በውጪም ዅለመናህ ነጭ ኾነ›› ብለው በደስታ ቃል አናገሯቸው፡፡ ሙሴም በተቀበሉት መዓርግ እግዚአብሔርን፣ መነኮሳቱንና ገዳሙን በትጋት ሲያገለግሉ ኖሩ፡፡

እግዚአብሔር በአባ ሙሴ ላይ አድሮ ከአደረጋቸው ተአምራት መካከል ያለ ወቅቱ ዝናብ እንዲዘንብ ማድረጋቸው አንደኛው ነው፤ ከዕለታት አንድ ቀን በበዓታቸው ምንም ውኃ በሌለበት ቀን አረጋውያን በእንግድነት መጡባቸው፡፡ ውኃ የሚቀዳበት ቦታ በጣም ሩቅ ነበርና አባ ሙሴ የሚያደርጉትን አጡ፡፡ እንግዶቹን ወደ በዓታቸው ካስገቡ በኋላም ከመነኮሳቱ ተለይተው ‹‹ውኃ ካልሰጠኸኝ ቅዱሳን አገልጋዮችህን ምን አጠጣቸዋለሁ?›› እያሉ እግዚአብሔርን በጸሎት ይጠይቁት ጀመሩ፡፡ እርሱም በስሙ ለሚታመኑ ድንቅ ሥራውን መግለጥ ልማዱ ነውና ጸሎታቸውን ሰምቶ ዝናብ አዝንቦ የውኃ ጉድጓዶችን ሞላላቸው፡፡ እንግዶቹንም እንደ ሥርዓቱ እግራቸውን አጥበው፣ ምግብና ውኃ ሰጥተው አስተናገዷቸው፡፡ አረጋውያኑ በዝናቡ መጣል እየተገረሙ አባ ሙሴን ‹‹ብዙ ጊዜ ትወጣ፣ ትገባ የነበረው ለምንድን ነው?›› ብለው ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም ‹‹እግዚአብሔርን ውኃ እንዲሰጠኝ እየተማጸንኹት ነበር፡፡ በቸርነቱም ዝናምን ልኮልን ውኃን አገኘን›› አሏቸው፡፡ በዚህ ጊዜ በቅዱሳኑ ላይ አድሮ ድንቅ ድንቅ ተአምራቱን የሚገልጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑት፤ በአባ ሙሴ ቅድስናም ተደነቁ፡፡

በአንዲት ዕለት አባ ሙሴ ከአረጋውያን ጋር ወደ አባ መቃርስ ገዳም በሔዱ ጊዜ አባ መቃርስ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው ‹‹ከእናንተ ውስጥ የሰማዕትነት ክብር ያለው አንድ ሰው አያለሁ›› በማለት ለአባ ሙሴ ጸሊም ስለ ተዘገጀው የሰማዕትነት ክብር አስቀድመው ትንቢት ተናገሩ፡፡ አባ ሙሴም ይህን ቃል ሲሰሙ ‹‹አባቴ ሆይ እኔ እኾናለሁ፡፡በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደል ዘንድ አለው› የሚል ጽሑፍ አለና›› ብለው መለሱ፡፡ በብሉይ ኪዳን ‹‹በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይሙት፤ ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጥፋ›› የሚል አንድ ሰው በሠራው ወንጀል መጠን እንዲቀጣ የሚያስገድድ ሕግ ነበር (ዘፀ. ፳፩፥፳፬-፳፭፤ ማቴ. ፭፥፴፰)፡፡ አባ ሙሴ ጸሊም ለገዳማዊ ሕይወት ከመብቃታቸው በፊት ሰዎችን በሰይፍ ሲያጠፉ እንደ ነበሩት ዅሉ እርሳቸውም በሰይፍ ለመሞት መዘጋጀታቸውን ሲገልጹ ‹‹አባቴ ሆይ እኔ እኾናለሁ፡፡በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደል ዘንድ አለው› የሚል ጽሑፍ አለና›› ብለዋል፡፡ ይህም በንጹሕ ልቡናቸው ወደ እግዚአብሔር መመለሳቸውን የሚያመለክት ንግግር ነው፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ያገኙትን ዅሉ በሰይፍ የሚገድሉ የበርበር ሰዎች ወደ በዓታቸው መጡ፡፡ አባ ሙሴም አብረዋቸው የነበሩትን መነኮሳት ‹‹መሸሽ የሚፈልግ ይሽሽ›› አሏቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አባታችን አንተስ አትሸሽምን?›› ብለው ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም እኔ ‹‹‹በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደላልስለሚለው የእግዚአብሔር ቃል እነሆ ይቺን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠባበቃት ኖሬአለሁ›› በማለት ለሰማዕትነት መዘጋጀታቸውን ነገሯቸው፡፡ ይህን ቃል እየተነጋገሩ ሳሉም የበርበር ሰዎች ከበዓታቸው ገብተው በሰይፍ ቈርጠው ገደሏቸው፡፡ ከእርሳቸው ጋርም ሰባት መነኮሳት በሰማዕትነት ሞቱ፡፡ አንደኛውም ከምንጣፍ ውስጥ ተሠውረው ከቆዩ በኋላ በእጁ አክሊል የያዘ የእግዚአብሔር መልአክ ቆሞ ሲጠባበቅ በተመለከቱ ጊዜ ከተሠወሩበት በመውጣት የሰማዕትነትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ አባ መቃርስ ‹‹ከእናንተ ውስጥ የሰማዕትነት ክብር ያለው አንድ ሰው አያለሁ›› በማለት የተናገሩት ትንቢት ደረሰ፡፡ ‹‹አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው›› ሲል ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ኃይለ ቃልም በአባ ሙሴ ተጋድሎ ተፈጸመ  (ሮሜ. ፰፥፴)፡፡ የአባ ሙሴ ጸሊም ሥጋም በአስቄጥስ ገዳም ደርምስ በተባለ ቦታ እንደሚገኝ፤ ከእርሱም ብዙ ድንቆችና ተአምራት እንደሚታዩ በመጽሐፈ ስንክሳር ተገልጿል፡፡

‹‹እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ማቴ.፲፩፥፲፪/፣ አባ ሙሴ ጸሊም አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍተዋታል፤ ማለትም የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያወርሰውን የጽድቅ ሥራ ትተው ወደ ገሃነም በሚያስጥል ኃጢአት ኖረዋል፡፡ በኋላ ግን እግዚአብሔርን ፈልገው ከማግኘታቸው ባሻገር በመንፈሳዊ ተጋድሎ በመበርታት ለክህነት እና ለቅድስና በቅተው ምድራዊ ሕይወታቸውን በሰማዕትነት አጠናቀዋል፡፡ በክህደት፣ በኑፋቄ እንደዚሁም በኀጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር እቅፍ ርቀን የምንኖር ክርስቲያኖችም ከሃዲ፣ ሰውን ገዳይ፣ ቀማኛ፣ ዘማዊ የነበረውን ሰው ወደ አሚነ እግዚአብሔር እና ወደ ገቢረ ጽድቅ በመለወጥ ደግ አባት፣ መምህር፣ የሚያጽና እና ሥርዓትን የሚሠራ ካህን፣ እንደዚሁም ሰማዕት ለመኾን ያበቃችውን፤ በተጨማሪም በዅሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ስሙ ለዘለዓለሙ እንዲጠራ ያደረገችውን የንስሓን ኃይል በማስተዋል ዛሬዉኑ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፡፡ ኀጢአታችንን ይቅር ይለን ዘንድም ዘወትር እንማጸነው፡፡ እግዚአብሔር እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን፣ ኀጢአትንም ይቅር የሚል አምላክ ነውና (ዘፀ. ፴፬፥፯፤ ማቴ. ፮፥፲፪)፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን! እኛንም በአባ ሙሴ ጸሊምና በሰማዕታት ዅሉ ጸሎት ይማረን፡፡ በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፳፬ ቀን፡፡

የንጉሥ ሰሎሞን ዕረፍት

በዝግጅት ክፍሉ

ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፱ .

በየዓመቱ ሰኔ ፳፫ ቀን ንጉሥ ሰሎሞን፣ አባ ኖብ፣ ቅዱስ መርቆሬዎስ፣ ቅዱስ ቶማስ፣ ቅዱስ ፊልጶስና ሌሎችም ቅዱሳን ይታወሳሉ፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን በመጽሐፈ ስንክሳር የተመዘገበዉን የንጉሥ ሰሎሞንን የዕረፍት ታሪክ በአጭሩ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

ንጉሥ ዳዊት ሕግ ተላልፎ ከኦርዮ ሚስት ከቤርሳቤህ ጋር በዝሙት በመውደቅ እና ባሏን በማስገደል ኀጢአት በመፈጸሙ እግዚአብሔር አምላክ ነቢዩ ናታንን ልኮ ስለ በደሉ ገሠፀው፡፡ በዚህ ጊዜ ንስሐ ገብቶ መሪር ልቅሶን አለቀሰ፡፡ እግዚአብሔርም ንስሐዉን ተቀብሎ ኀጢአቱን ይቅር አለው፡፡ በኋላም በእግዚአብሔር ፈቃድ ቤርሳቤህን ሚስቱ አደረጋትና ሰሎሞንን ወለዱ፡፡ ሰሎሞን ሲያድግም በዙፋኑ እንደሚተካው ንጉሥ ዳዊት ለቤርሳቤህ ቃል ገባላት፡፡ ብላቴናው ሰሎሞን ፲፪ ዓመት በሞላው ጊዜም አዶንያስ በዳዊት ምትክ ለመንገሥ ዐስቦ በሮጌል ምድር ምንጭ አጠገብ ኤልቲ ዘዘኤልቲ በሚባል ቦታ ላሞችን፣ በጎችንና ፍየሎችን አርዶ የሠራዊት አለቆችን፤ የንጉሥ አሽከሮችንና ካህኑ አብያታርንም ጠርቶ ግብዣ አደረገ፡፡ እነርሱም ‹‹አዶንያስ ሺሕ ዓመት ያንግሥህ!›› እያሉ አወደሱት፡፡

ዳዊትም የአዶንያስን ሥራ ከቤርሳቤህና ከነቢዩ ከናታን በሰማ ጊዜ የዮዳሄን ልጅ ብንያስንና ካህኑ ሳዶቅን፣ ነቢዩ ናታንንም፣ ግራዝማችና ቀኛዝማቹን ዅሉ አስጠርቶ ሰሎሞንን በራሱ በቅሎ ላይ አስቀምጠው፡፡ ሠራዊቱም ወደ ግዮን እንዲያወርዱትና በዚያም ነቢዩ ናታንና ካህኑ ሳዶቅ ቀብተው እንዲያነግሡት፤ ሰሎሞንም በአባቱ ፈንታ በእስራኤል ላይ እንዲነግሥ ንጉሥ ዳዊት አዘዘ፡፡ ካህኑ ሳዶቅም እንደታዘዘው ሰሎሞንን የንግሥና ቅባትን ቀባው፡፡ ቀርነ መለከቱንም ነፉ፤ ሕዝቡም ዅሉ ሰሎሞንን ‹‹ሺሕ ዓመት ያንግሥህ!›› እያሉ ተከትለዉት ወጡ፡፡ ከበሮም መቱ፤ ታላቅ ደስታም አደረጉ፡፡ ከድምፃቸው ኃይል የተነሣ ምድሪቱ ተናወጠች፡፡ ሰሎሞንም በመንግሥት ዙፋን ተቀመጠ፡፡ የንጉሡ አሽከሮችም ‹‹እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ይልቅ መልካም ያድርገው፤ ዙፋኑንም ከዙፋንህ ይልቅ ከፍ ከፍ ያድርገው›› እያሉ ዳዊትን አመሰገኑት፡፡ ዳዊትም ‹‹ዐይኖቼ እያዩ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ለእኔ ለባሪያው ዛሬ የሰጠ የእስራኤል ፈጣሪ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን›› አለ፡፡

ንጉስ ዳዊት የሚሞትበት ጊዜ በደረሰ ጊዜም ‹‹እኔ ሰው በሚሔድበት በሞት ጐዳና እሔዳለሁ፡፡ አንተ ግን ጽና፤ ብልህ ሰውም ኹን፡፡ በሕጉ ጸንተህ ትኖር ዘንድ በሙሴ ሕግ የተጻፈዉን የፈጣሪህ የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዝ ጠብቅ›› ብሎ ልጁ ሰሎሞንን አዘዘው፡፡ ከዳዊት ዕረፍትም በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን በገባዖን ምድር መሥዋዕትን በሠዋ ጊዜ እግዚአብሔር በሕልም ተገልጾ ‹‹እሰጥህ ዘንድ ልብህ ያሰበዉን ለምነኝ›› አለው፡፡ ሰሎሞንም ‹‹እኔ ባሪያህ መግቢያዬንና መውጫዬን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝና ለዚህ ለብዙ ወገንህ በእውነት እፈርድ፤ ክፉዉን ከበጎው ለይቼ ዐውቅ ዘንድ ዕውቀትን ስጠኝ?›› ብሎ ለመነው፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹ብዙ ዘመንንና ባለጠግነትን፤ የጠላቶችህንም ጥፋት አለመንኸኝምና፡፡ ነገር ግን ፍርድ መስማትን ታውቅ ዘንድ ለምነሃልና እነሆ እንዳልህ አደረግሁልህ፡፡ እነሆ ከአንተ አስቀድሞ እንዳልነበረ፤ ከአንተም በኋላ እንደ አንተ ያለ እንዳይነሣ አድርጌ ብልህና አስተዋይ ልቡናን፤ ያለመንኸኝን ባለጠግነትንና ክብርንም በዘመንህ ዅሉ ሰጠሁህ›› አለው፡፡

ሰሎሞንም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እውነተኛ ሕልም እንዳለመ ዐወቀ፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዶም በጽዮን በእግዚአብሔር ታቦተ ሕግ አንጻር ባለው መሠዊያ ፊት ቆሞ የሰላም መሥዋዕትን አቀረበ፡፡ ለሰዎቹና ለእሱም ታላቅ ግብዣ አደረገ፡፡ በዚያን ጊዜም ሁለት አመንዝራ ሴቶች ወደ እርሱ መጥተው በአንድ ቤት እንደሚኖሩና በሦስት ቀን ልዩነት ልጆችን እንደ ወለዱ፤ አንደኛዋ ሴትም ልጇን በሌሊት ተጭናው በሞተባት ጊዜ ያልመተዉን የሌላኛዋን ልጅ ወስዳ የሞተዉን ልጅ እንዳስታቀፈቻት በማብራራት ‹‹የሞተው ልጅ ያንቺ ነው፤ ደኅናው ልጅ የኔ ነው›› የሚል አቤቱታ ለንጉሥ ሰሎሞን አቀረቡ፡፡ ንጉሡም የሁለቱንም ንግግር ካደመጠ በኋላ ‹‹ደኅነኛዉን ልጅ በሰይፍ ቈርጣችሁ እኩል አካፍሏቸው›› ብሎ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ያልሞተው ልጅ እናት ‹‹ልጁን አትግደሉት፡፡ ደኅናዉን ለእርሷ ስጧት›› ስትል፤ ሁለተኛዋ ሴት ግን ‹‹ቈርጣችሁ አካፍሉን እንጂ ለእኔም ለእርሷም አይኹን›› አለች፡፡ ንጉሡም እውነቱን ከሴቶቹ አኳኋን ተረድቶ ‹‹‹ልጁን አትግደሉት› ላለችው ሴት ደኅነኛዉን ሕፃን ስጧት፤ እርሷ እናቱ ናትና›› ብሎ ፈረደ፡፡ በዚህ ፍርዱ ምክንያትም እስራኤል ዅሉ ቅን ፍርድ ይፈርድ ዘንድ የእግዚአብሔር ጥበቡ በእርሱ ላይ እንዳለ አይተዋልና ንጉሡን ፈሩት፡፡

ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ማነጽ ጀመረ፡፡ ቤተ መቅደሱንም እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በ፬፻፹ኛው፤ ሰሎሞን በነገሠ በ፬ኛው ዓመት፣ በ፪ኛው ወር ጀምሮ በ፲፩ኛው ዘመነ መንግሥቱ፣ በ፰ኛው ወር ሠርቶ በ፯ ዓመታት ውስጥ ፈጸመው፡፡ የራሱን ቤትም በ፲፫ ዓመት ሠርቶ ጨረሰ፡፡ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱንና የራሱን ቤት ከፈጸመ በኋላ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጣ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሎች፣ የነገድና የአባቶቻቸዉን ቤት አለቆች ዅሉ በ፯ኛው ወር (በጥቅምት) በኢየሩሳሌም ሰበሰባቸው፡፡ ካህናቱም ታቦቷን፣ የምስክሩን ድንኳንና ንዋያተ ቅድሳቱን ዅሉ ተሸክመው ንጉሡና ሕዝቡም በታቦቷ ፊት ሥፍር ቍጥር የሌላቸዉን በጎችንና ላሞችን እየሠዉ ታቦቷን ከኪሩቤል ክንፎች በታች በቤቱ ውስጥ ወዳለው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አገቧት፡፡

ካህናቱ ከቤተ መቅደስ በወጡ ጊዜ የእግዚአብሔር ብርሃን ቤተ መቅደሱን ሞላው፡፡ ካህናቱም ሥራቸዉን መሥራትና ከብርሃኑ ፊቱ መቆም ተሳናቸው፡፡ ያንጊዜም ሰሎሞን ‹‹‹እግዚአብሔር በደመና ውስጥ እኖራለሁብሏል፤ እኔም ለዘለዓለም የምትኖርበት ማደሪያህ ቤተ መቅደሱን በእውነት ሠራሁልህ›› አለ፡፡ ከዚያም ፊቱን ወደ መሠዊያው መልሶ፣ እጆቹን ዘርግቶ፣ በጕልበቱ ተንበርክኮ ሰገደና ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አደረሰ፤ ሕዝቡንም ዅሉ መረቃቸው፡፡ ጸሎቱን ከፈጸመ በኋላም ከመሠዊያው ፊት ተነሥቶ ቆመና ‹‹ለወገኖቹ ለእስራኤል ዕረፍትን የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን›› እያለ በታላቅ ቃል የእስራኤልን ማኅበር መረቃቸው፡፡ ከዚያም ንጉሡና ሕዝቡ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቅርበው ቅዳሴ ቤቱን አከበሩ፡፡ ሰሎሞን ስለ ሰላም ለእግዚአብሔር የሠዋቸው በጎች በቍጥር ፳፪ ሺሕ ነበሩ፡፡

ዳግመኛም እግዚአብሔር ለሰሎሞን ተገልጾ ‹‹የለመንኸኝን ልመናህንና ጸሎትህን ሰማሁ፤ እንደ ልመናህም ዅሉ አደረግሁልህ፡፡ ስሜ በዚያ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖር ዘንድ የሠራኸዉን ቤተ መቅደስ አከበርሁት፡፡ ልቡናዬም፣ ዐይኖቼም በዘመኑ በዚያ ጸንተው ይኖራሉ›› ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ እግዚአብሔር ብዙ ጥበብና ጸጋን የሰጠው ይህ ታላቅ ንጉሥ ለዐርባ ዓመት እስራኤልን በቅንነት አስተዳድሯል፡፡ ከንግሥናው በተጨማሪም ለነፍስም ለሥጋም የሚጠቅሙ፣ ትንቢትንና ትምህርትን የያዙ የጥበብና የመዝሙር መጻሕፍትንም ጽፏል፤ እነዚህም፡- መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን፣ መጽሐፈ መክብብ፣ መጽሐፈ ምሳሌ፣ መጽሐፈ ተግሣፅና መጽሐፈ ጥበብ ናቸው፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን ከመንገሡ በፊት ፲፪፤ ከንግሥናው በኋላ ፵፤ በድምሩ ፶፪ ዓመታት በሕይወተ ሥጋ ከኖረ በኋላ በዛሬው ዕለት ሰኔ ፳፫ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፏል፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ እኛንም በቅዱሳን ጸሎት ይማረን፡፡ የአባቶቻችን በረከት ይደርብን፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፳፫ ቀን፡፡

ሕንጸተ ቤተ ክርስቲያን

በዝግጅት ክፍሉ

ሰኔ ቀን ፳፻፱ .

በመጽሐፈ ስንክሳር እንደ ተመዘገበልን ሰኔ ፳ ቀን በኬልቄዶን አውራጃ በቂሣርያ አገር የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ያለ እንጨት፣ ያለ ጭቃና ያለ ውኀ በሦስት ድንጋዮች በተወደደ ልጇ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የታነጸበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ከሚከብሩ ከእመቤታችን በዓላት አንደኛው ሲኾን ታሪኩንም በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

ጌታችን በዐረገ በስምንተኛው ዓመት ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ በርናባስ ወደ ፊልጵስዩስ ገብተው በክርስቶስ ስም አሳምነው ብዙ አሕዛብን ካጠመቁ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ሊሠሩላቸው ወደዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ርእሰ ሐዋርያት እያለ እኛ መሥራት አይገባንም ብለው በሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ መልእክት ላኩበት፡፡ እርሱም ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር መጥቶ ከቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ በርናባስ ጋር በኢየሩሳሌም ተገናኙ፡፡

በዚያም በአንድነት ሱባዔ ይዘው ከቆዩ በኋላ ጌታችን የሞቱትን አስነሥቶ፣ ያሉትንም ጠርቶ ቅዱሳን ሐዋርያትን በፊልጵስዩስ አገር ሰብስቦ ‹‹በእናቴ በድንግል ማርያም ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚሠራዉን የአብያተ ክርስቲያናት ሥራ ላሳያችሁ፤ ሥርዓቱንም ላስተምራችሁ ሰብስቤአችኋለሁ›› ብሎ ወደ ምሥራቅ ይዟቸው ወጣ፡፡ በዚያ ሥፍራ የነበሩትን ሦስት ድንጋዮችንም የተራራቁትን አቀራርቦ፣ ጥቃቅኑን ታላላቅ አድርጎ ቁመቱን በ፳፬፤ ወርዱን በ፲፪ ክንድ ለክቶ ለቅዱሳን ሐዋርያት ሰጣቸው፡፡

ከዚህ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት ሰም እሳት ሲያገኘው እንዲለመልም፣ ድንጋዩ በእጃቸው ላይ እየተሳበላቸው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ሠርተው ፈጽመዉታል፡፡ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራዉም ጌታችን በዐረገ በ፲፱ኛው፤ እመቤታችን በዐረገች በ፬ኛው ዓመት ሰኔ ፳ ቀን ሲኾን፣ በ፳፩ኛው ቀን (በማግሥቱ) ኅብስት ሰማያዊ፣ ጽዋዕ ሰማያዊ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወረደ፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችን ጋር ከሰማየ ሰማያት መጥቶ እመቤታችንን ታቦት፤ ሐዋርያትን ልዑካን አድርጎ፣ እርሱ ሠራዒ ካህን ኾኖ ቀድሶ ካቈረባቸው በኋላ ‹‹እምይእዜሰ አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ፤ ከዛሬ ጀምሮ እናንተም እንደዚህ አድርጉ›› ብሎ አዝዟቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡

ይህ ታሪክ ብዙ ምሳሌዎች አሉት፡፡ ይኸውም፡- የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ቁመት በነገሥታት ዘመን የነበሩ የ፳፬ቱ ነቢያት፤ አንድም የ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ አምሳል ሲኾን፣ ወርዱ ደግሞ የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው፡፡ ሦስቱ ድንጋዮች የሥላሴ አምሳል ሲኾኑ፣ ከታች አቀማመጣቸው ሦስት፤ ከላይ ሕንጻቸው አንድ መኾኑ የሥላሴን ሦስትነትና አንድነት ያመለክታል፡፡ የሠሩትም ሦስት ክፍል አድርገው ሲኾን፣ ይህም የመጀመሪያው የታቦተ አዳም፤ ሁለተኛው የታቦተ ሙሴ፤ ሦስተኛው የታቦተ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዳግመኛም የሦስቱ ዓለማት ማለትም የመጀመሪያው የጽርሐ አርያም፣ ሁለተኛው የኢዮር፣ ሦስተኛው የጠፈር ምሳሌ ነው፡፡

አንድም መጀመሪያው የኤረር፣ ሁለተኛው የራማ፣ ሦስተኛው የኢዮር አምሳል ነው፡፡ በኤረር፡- መላእክት፣ መኳንንት፣ ሊቃናት፤ በራማ፡- ሥልጣናት፣ መናብርት፣ አርባብ፤ በኢዮር፡- ኃይላት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌል ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ዘጠኙ ነገደ መላእክት የዘጠኙ መዓርጋተ ቤተ ክርስቲያን (መዓርጋተ ክህነት) አምሳል ሲኾኑ፣ ይኸውም መላእክት – የመዘምራን፤ መኳንንት – የአናጕንስጢሳውያን፤ ሊቃናት – የንፍቀ ዲያቆናት፤ ሥልጣናት – የዲያቆናት፤ መናብርት – የቀሳውስት፤ አርባብ – የቆሞሳት፤ ኃይላት – የኤጲስ ቆጶሳት፤ ሱራፌል – የጳጳሳት፤ ኪሩቤል – የሊቃነ ጳጳሳት አምሳሎች ናቸው፡፡

ይህም በታች (በምድር) የሚኖሩ ደቂቀ አዳም ከቅዱሳን በቀር ወደ ላይ (ወደ ሰማይ) መውጣት እንደማይቻላቸው፣ ከመዘምራን እስከ ጳጳሳት ድረስ ያሉ ካህናትም ከእነርሱ በላይ ያሉትን መዓርግ መሥራት (መፈጸም) እንደማይቻላቸው ያጠይቃል፡፡ እንደዚሁም በላይ የሚኖሩ መላእክት ወደ ታች መውረድ እንደሚቻላቸው ሊቃነ ጳጳሳትም ከእነርሱ በታች ያሉ ካህናትን ተልእኮ መፈጸም (መሥራት) እንደሚቻላቸው ያስረዳል፡፡

በጽርሐ አርያም መንበረ ብርሃን (የብርሃን መንበር)፤ ታቦተ ብርሃን (የብርሃን ታቦት)፤ መንጦላዕተ ብርሃን (የብርሃን መጋረጃ)፤ እንደዚሁም ፬ ፀወርተ መንበር (መንበሩን የሚሸከሙ)፤ ፳፬ አጠንተ መንበር (መንበሩን የሚያጥኑ) መላእክት አሉ፡፡ ጽርሐ አርያም – የመቅደስ፤ መንበረ ብርሃን – የመንበር፤ መንጦላዕተ ብርሃን – የቤተ መቅደሱ መጋረጃ፤ ፬ቱ ፀወርተ መንበር – የ፬ቱ ሊቃነ ጳጳሳት ወይም የመንበሩ እግሮች፤ ፳፬ቱ አጠንተ መንበር – የጳጳሳት (የኤጲስ ቆጶሳት) አምሳሎች ናቸው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡

  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ቀን፡፡
  • መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ አዲስ አበባ፣ ፳፻፭ ዓ.ም፤ ገጽ ፫፻፵፱ – ፫፻፶፩፡፡

‹‹ከእናንተ ብዙ ይጠበቃል›› ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፲፱ ቀን ፳፻፱ .

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የዕለቱን ወንጌል ሲያነቡ (ሉቃ. ፲፥፩-፲፮)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በልዩ ልዩ ትምህርት ክፍል ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ የኮሌጁ መምህራንና ሠራተኞች በተገኙበት ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ አስመርቋል፡፡ ተመራቂዎቹም የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን በሚመለከት ያዘጋጁትን የአቋም መግለጫ በተወካያቸው አማካይነት አቅርበዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሰጡት ቃለ ምዕዳን ‹‹ታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ጠብቃ ያቆየችው ትክክለኛ የኾነ አስተምህሮዋ፣ ባህል እና ትውፊቷ ሳይበረዝና ሳይፋለስ ለትውልደ ትውልድ መሸጋገር ይችል ዘንድ ከእናንተ ብዙ ይጠበቃል›› ሲሉ ተመራቂዎቹን አሳስበዋል፡፡

ዕለቱ፣ ተመራቂዎቹ የቤተ ክርስቲያንን አደራ ተቀብለው በየተሠማሩበት የሥራ መስክ ዅሉ እስከ መጨረሻው በታማኝነት ቃል የሚገቡበት ቀን መኾኑን ያስገነዘቡት ቅዱስነታቸው ‹‹የመንግሥተ እግዚአብሔር መልእክተኛ የኾነ ዅሉ መስቀሉን ተሸክሞ ለማገልገል የተመረጠ ስለ ኾነ በሚያጋጥመው የጕዞ ዐቀበት እና ቍልቍለት ሊቸገር አይገባውም፤ በማን እንደ ተመረጠ ያውቃልና ነው›› በማለት ተመራቂዎቹ ብዙ ፈተና እንደሚጠብቃቸው አውቀው ዅሉንም በትዕግሥት በማሸነፍ የሕይወት አክሊል ባለቤቶች ለመኾን ከወዲሁ እንዲዘጋጁ መክረዋል፡፡

ተመራቂዎቹ በሚላኩበት ቦታ ዅሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለትውልድ የሚጠቅም አርአያነት ያለው ሥራ ለመሥራት እንዲችሉ ቤተ ክርስቲያን ስለ እነርሱ ዘወትር እንደምትጸልይም ተናግረዋል፡፡ በቃለ ምዕዳናቸው ማጠቃለያም መንፈሳዊ ኮሌጁ በየጊዜው ተተኪ መምህራንን ለማፍራት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው ‹‹ዘመኑ የዕውቀት ነውና የመማር ማስተማር ዘዴው ዘመኑን የዋጀ እንዲኾን ከበፊቱ በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ በቤተ ክርስቲያናችን ስም አደራ እንላለን›› በማለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ ሸካ ቤንጂ ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ በበኩላቸው ‹‹በቆያችሁበት የትምህርት ዘመን ከመምህሮቻችሁ ያገኛችሁትን መንፈሳዊ ዕውቀት እግዚአብሔር ሒዱ ብሎ ወደሚልካችሁ ዓለም በመሔድ ሕዝባችሁንና ሃይማኖታችሁን ጠብቃችሁ ሳትታክቱ እንድታገለግሉ ስትል ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ መልእክቷን ታስተላልፋለች›› የሚል ቃለ በረከት ለተመራቂዎቹ ሰጥተዋል፡፡

ሊቀ ኅሩያን መሐሪ አስረስ

መምህር ማሞ ከበደ

በኮሌጁ ተምረው የሚመረቁ መምህራን በልዩ ልዩ የዕውቀት ዓይነት የበለጸጉ ሊቃውንት መኾናቸውን በማውሳት ‹‹ከአሁን በኋላ ዝናብ ዘንቦ መሬትን እንደሚያርሰው ዅሉ ከሞላው የዕውቀት ባሕራችሁ እየቀዳችሁ የምእመናንን አእምሮ እንደምታረሰርሱት ትጠበቃላችሁ›› ያሉት ደግሞ የኮሌጁ ዋና ዲን ሊቀ ኅሩያን መሐሪ አስረስ ናቸው፡፡

‹‹በኮሌጃችን ተምረው የሚመረቁ መምህራን የአብነቱን ትምህርት ከዘመናዊው ጋር አጣጥመው በዕውቀት ላይ ዕውቀት ጨምረው የሚወጡ መንፈሳውያን ሐኪሞች ናቸው፡፡ ትምህርታቸውም ደዌ ሥጋን ብቻ ሳይኾን ደዌ ነፍስንም ይፈውሳል›› ያሉት መምህር ማሞ ከበደ የመንፈሳዊ ኮሌጁ አስተዳደር ምክትል ዲን እና የኮሌጁ መምህርም ኮሌጁ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያፈራ እንደ ቆየ አሁንም በማፍራት ላይ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡

የኮሌጁ ተመራቂዎች በከፊል

በዚህ ዓመትም በብሉይ ኪዳን አንድ፤ በሐዲስ ኪዳን አንድ፤ በቀን አዳሪ ሲሚናር ዐሥራ አንድ፤ በቀን ተመላላሽ ሃያ ሦስት፤ በማታው መርሐ ግብር ሁለት መቶ ዐርባ አምስት በድምሩ ሁለት መቶ ሰማንያ አንድ ደቀ መዛሙርትን ማስመረቁን፤ ከተመራቂዎች መካከልም አካል ጉዳተኞች እና ሴቶች እንደሚገኙ መምህር ማሞ ከበደ አስታውቀዋል፡፡ አራቱን ጉባኤያት ማስተማር፤ በዲግሪ መርሐ ግብር ማስመረቅ እና የርቀት ትምህርት መጀመር ከኮሌጁ የወደፊት ዕቅዶች መካከል የሚጠቀሱ ተግባራት መኾናቸውንም አስረድተዋል፡፡

የኮሌጁ ተመራቂዎች በከፊል

አጠቃላይ የኮሌጁን የማስተማር ተልእኮ በሚመለከት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቆይታ ምክትል ዲኑ እንዳብራሩት ኮሌጁ ከኅዳር ወር ፳፻፰ ዓ.ም ጀምሮ ሰርጎ ገብ መናፍቃንን የሚከታተል ኰሚቴ አቋቁሞ ከኦርቶዶክሳዊው የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ያፈነገጠ ባዕድ ትምህርት የሚያስተምሩ ደቀ መዛሙርትን በማጣራት በየጊዜው እንዲወገዙና ከትምህርት እንዲታገዱ ሲያደርግ የቆየ ሲኾን፣ በዘንድሮው ዓመትም እምነቱ ተጣርቶ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ የሃይማኖት ሕጸጽ የተገኘበት አንድ ደቀ መዝሙር እንዳይመረቅ እገዳ ተጥሎበታል፡፡

ከግራ ወደ ቀኝ፡- ዲያቆን ዳንኤል ታደሰ እና ቀሲስ አድማሱ ሰንበታ

ከዚሁ ዅሉ ጋርም የካህናትና ሰባክያነ ወንጌል እጥረት ካሉባቸው አህጉረ ስብከት መሥፈርቱን የሚያሟሉ ሰባት ደቀ መዛሙርትን በመምረጥ ማኅበረ ቅዱሳን ሙሉ ወጫቸውን ሸፍኖ በመንፈሳዊ ኮሌጁ እያስተማረ መኾኑን፤ ከእነዚህ መካከልም ከምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት የመጡት ሁለቱ ሰባክያነ ወንጌል ቀሲስ አድማሱ ሰንበታ እና ዲያቆን ዳንኤል ታደሰ ለሦስት ዓመታት ተምረው በዘንድሮው ዓመት መመረቃቸውን ከቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡

ዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው ሁለቱ ተመራቂዎችም ማኅበሩ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን በእግዚአብሔር ስም አቅርበዋል፡፡ ለወደፊቱም በየቦታው እየተዘዋወሩ ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ተቋቁመው በክህነት እና በስብከተ ወንጌል ሰፊ አገልግሎት በመስጠት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰጣቻቸውን መንፈሳዊ ሓላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዐውደ ርእዩ በአሜሪካ ቀረበ

በዝግጅት ክፍሉ

ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹‹የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ›› በሚል ርእስ የተዘጋጀው ፭ኛው ዙር የማኅበረ ቅዱሳን ዐውደ ርእይ ከሰኔ ፲ – ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በአሜሪካ አገር መቅረቡን የአሜሪካ ማእከል አስታወቀ፡፡

ዐውደ ርእዩ በጸሎተ ወንጌል ሲከፈት

በአትላንታ ንዑስ ማእከል አዘጋጅነት በአትላንታ ከተማ በደብል ትሪ ሆቴል በቀረበው በዚህ ልዩ ዐውደ ርእይ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ የየአጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶች እና የመንፈሳውያን ማኅበራት አባላት፣ ታዳጊ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ የአሜሪካ ምእመናን መታደማቸውን የንዑስ ማእከሉንና የዝግጅት ኰሚቴውን ሪፖርት ጠቅሶ ማእከሉ ዘግቧል፡፡

ዐውደ ርእዩ በአባቶች ቡራኬ ሲጀመር

በመኪና ከአራት እስከ ዐሥር ሰዓታት ከሚወስዱ ክፍለ ግዛቶች (ስቴቶች) ጭምር ዐውደ ርእዩን ለመመልከት በአትላንታ ከተማ የተገኙ ምእመናን እንደ ነበሩም ከዝግጅት ኰሚቴው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡ የተመልካቾች ቍጥር ከመብዛቱ የተነሣ ዐውደ ርእዩ በሁለት ክፍሎች የቀረበ ሲኾን፣ ትዕይንቶቹም በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየተተረጐሙ ተመልካቾች በሚረዱት መልኩ ተብራርተዋል፡፡

የብፁዕ አቡነ ፋኑኤል መልእክትና ቃለ ምዕዳን በመጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት ሲቀርብ

ዐውደ ርእዩ በጸሎተ ወንጌል በተከፈተበት ዕለት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል መልእክትና ቃለ ምዕዳን በመጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት የአትላንታ ዳግማዊ ቁልቢ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ ቀርቧል፡፡

በመልእክታቸው እንደ ተጠቀሰው የዐውደ ርእዩ ትዕይንቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጕመው እንዲቀርቡ መደረጋቸው ይበል የሚያሰኝ ተግባር መኾኑን ብፁዕነታቸው አድንቀዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለሕዝበ ክርስቲያኑ በስፋት ለማዳረስ ይቻል ዘንድ ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በሌሎች ከተሞችም እንዲከናወን ያሳሰቡት ብፁዕነታቸው አገልግሎቱን ሀገረ ስብከታቸው እንደሚደግፍም ቃል ገብተዋል፡፡

የዐውደ ርእዩ ታዳሚ አባቶች እና ምእመናን በከፊል

በዐውደ ርእዩ ከተሰሙ መልካም ዜናዎች አንዱ አንድ መቶ ሦስት የአብነት ተማሪዎችን በአንድ ለአንድ የድጋፍ ዘዴ ለመርዳትና ለማስተማር የሚያስችል ቃል መገባቱ ሲኾን፣ በቍጥር ከአራት እስከ ዐሥር የሚደርሱ የአብነት ተማሪዎችን በግል ወጫቸው ለማስተማር አንዳንድ ምእመናን ቃል ገብተዋል፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም ለጎንደር በአታ የቅኔ ጉባኤ ቤት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል $2,628 (ሁለት ሺሕ ስድስት መቶ ሃያ ስምንት ዶላር) ምእመናን ለግሰዋል፡፡

የዐውደ ርእዩ ተሳታፊ ምእመናን በከፊል

በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ዕለት መልእክት ያስተላለፉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዐውደ ርእዩ አስተማሪ እንደ ነበር አስታውሰው በዚህም ይህን ሠራን ብሎ መታበይ እንደማያስፈልግ እና ስለ ሥራው ዅሉ እግዚአብሔርን ማመስገን ተገቢ እንደ ኾነ አስተምረዋል፡፡

የአትላንታ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ ማንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ዕርገተ ቃል ‹‹አሁን ታሪክ ተቀይሯል፡፡ የአገልግሎቱ በር ተከፍቷል፡፡ ስለኾነም ማኅበሩ በአትላንታ ሰፋፊ ራዎችን መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ከሕዝቡ ጥያቄና አስተያየት የተረዳነውም ይህንኑ ነው፡፡ ስለዚህ በርቱ›› በማለት አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

‹‹ለዚህ ዅሉ ሥራ መሳካት ምክንያቱ እግዚአብሔር ከኛ ጋር ስለ ኾነ ነው›› ያሉት የአትላንታ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ቀሲስ ያዕቆብ በበኩላቸው፣ ንዑስ ማእከሉ በዚህ ሥራ ብቻ ሳይወሰን ሌሎች መንፈሳውያን ተግባራትንም አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

ምእመናን የዐውደ ርእዩን ትዕይንቶች ሲከታተሉ (በከፊል)

በዝግጅቱ የቤተ ክርስቲያንን አስተዋጽዖ፣ ፈተናዎችንና የምእመናንን ድርሻ በስፋት እንደ ተረዱበት እና የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የዅሉም ምእመናን ጉዳይ መኾኑን እንደ ተገነዘቡበት የዐውደ ርእዩ ጐብኝዎች በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

ምእመናን የዐውደ ርእዩን ትዕይንቶች ሲከታተሉ (በከፊል)

በመጨረሻም ለዚህ መርሐ ግብር መሳካት ትብብርና እገዛ ላደረጉ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣ ለሰበካ ጉባኤ አባላትና ማኅበረ ካህናት፤ ለየሰንበት ት/ቤቶች አባላት፤ ድጋፍ በመስጠት (ስፖንሰር በማድረግ) ለተባበሩ የግል ድርጅቶች እና ለልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን (ሚዲያ) አካላት የዐውደ ርእዩ አዘጋጅ ኰሚቴ ላቅ ያለ ምስጋናውን በማኅበረ ቅዱሳን ስም አቅርቧል፡፡

ከዐውደ ርእዩ ትዕይንቶች ከፊሉ

ዐውደ ርእዩ በሚቀጥለው ቅዳሜና እሑድ (ሰኔ ፲፯ እና ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም) በዋሽንግተን ስቴት ሲያትል ከተማ እንደሚቀርብ የአሜሪካ ማእከል አስታውቋል፡፡

ከዐውደ ርእዩ ክውን ትዕይንቶች አንዱ (የአብነት ተማሪዎች በትምህርት ላይ)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ‹‹የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ›› በሚል ርእስ ያዘጋጀው ፭ኛ ዙር ዐውደ ርእይ ከግንቦት ፲፯ – ፳፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማእከል ቀርቦ በብዙ ሺሕ ሕዝብ እንደ ተጐበኘ የሚታወስ ነው፡፡

ይህን ዐውደ ርእይ በርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ማእከላት በየጊዜው እያዘጋጁ ትምህርቱ ለምእመናን እንዲዳረስ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

በቅርቡም ከአገር ውስጥ ማእከላት መካከል ባሕር ዳር ማእከል ከግንቦት ፬ – ፲፫፤ ፍኖተ ሰላም ማእከል ከሰኔ ፰ – ፲፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በቅደም ተከተል ዐውደ ርእዩን አዘጋጅተው ለብዙ ሺሕ ሕዝብ እንዳስጐበኙ ከማእከላቱ የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡

አባ ገሪማ ዘመደራ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው 

ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፱ .

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚነግረን በጉባኤ ኤፌሶን የተወገዘውን፣ በኋላም በጉባኤ ኬልቄዶን ጊዜ በመለካውያን አማካኝነት የመጣውን የሁለት አካል፣ ሁለት ባሕርይ የኑፋቄ እምነት አንቀበልም በማለታቸው በባዛንታይን ነገሥታት ስቃይ የጸናባቸው ተስዓቱ (ዘጠኙ) ቅዱሳን መነኮሳት ከሶርያና ከታናሽ እስያ ተሰደው በአልአሜዳ ዘመነ መንግሥት በ፬፻፹ ዓ.ም ወደ አገራችን ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡ በዘመኑ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥትም ከአባቶቹ በወረሰው የደግነትና እንግዳ ተቀባይነት ባህሉ በፍቅር ተቀብሏቸዋል፡፡

እነዚህ ዘጠኙ ቅዱሳን በመላው ኢትዮጵያ ተዘዋውረው ወንጌልን ሰብከዋል፤ በወቅቱ ብሔራዊ ቋንቋ የነበረዉን ግእዝን በሚገባ አጥንተው ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሱርስትና ከጽርዕ ቋንቋዎች ወደ ግእዝ ተርጕመዋል፡፡ እንደዚሁም ገዳማትንና አብያተ ክርስቲያናት አሳንጸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ከፈጸሟቸው መንፈሳውያን ተልእኮዎች፣ ካደረጓቸው ተአምራትና መልካም ሥራዎች አኳያ ቅዱሳን በሚል መዓርግ ትጠራቸዋለች፤ በስማቸውም ጽላት ቀርፃ በዓላቸውን ታከብርላቸዋለች፡፡ ዘጠኙ ቅዱሳን የሚባሉት አባቶች፡- አባ አሌፍ፣ አባ አረጋዊ፣ አባ አፍጼ፣ አባ ሊቃኖስ፣ አባ ገሪማ፣ አባ ጉባ፣ አባ ይምአታ፣ አባ ጰንጠሌዎን እና አባ ጽሕማ ናቸው (የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ.ታ፣ አባ ጎርጎርዮስ ዘሸዋ፣ ፲፱፻፺፩ ዓ.ም፤ ገጽ ፳፫-፳፬)፡፡ በዛሬው ዝግጅታችንም ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የኾኑትን የአባ ገሪማን ታሪክ በአጭሩ እናስታውሳችኋለን፤

በሮም አገር መስፍንያኖስ የሚባል ንጉሥ ነበረ፤ ሚስቱም ሰፍንግያ ትባላለች፡፡ መካን ስለነበረች በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በመማጸን ልጅ እንዲሰጣት እግዚአብሔርን ስትለምን ከኖረች በኋላ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ይስሐቅ አለችው፡፡ የያን ጊዜው ይስሐቅ የኋላው አባ ገሪማ በመንፈሳዊ ሥርዓት ካደገ በኋላም የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምሮ በዲቁና ማገልገል ጀመረ፡፡ ይስሐቅ ወላጅ አባቱ ሲሞትም በአባቱ ዙፋን ተተክቶ ለሰባት ዓመታት ሮምን በንጉሥነት ሲያስተዳድር ከቆየ በኋላ በዋሻ ይኖሩ የነበሩት አባ ጰንጠሌዎን ዘጾማዕት ‹‹ይስሐቅ ሆይ፣ ሙታኖቻቸውን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዋቸውና የማያልፈዉን የክርስቶስን መንግሥት ትሻ ዘንድ ወደ እኔ ና›› ብለው መልእክት ላኩበት፡፡ መልእክቱ እንደ ደረሰውም መንግሥቱን ትቶ በሌሊት ወደ አባ ጰንጠሌዎን ሲሔድ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾ በብርሃናውያን ክንፎቹ ተሸክሞ ዐሥር ወር የሚወስደዉን መንገድ በሦስት ሰዓታት አስጉዞ ከአባ ጰንጠሌዎን በዓት አደረሰው፡፡

አባ ይስሐቅ (አባ ገሪማ) በአባ ጰንጠሌዎን እጅ ከመነኰሱ በኋላ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ተጠምደው ቆዳቸው ከዐፅማቸው እስኪጣበቅ ድረስ ተጋድሎ ሲፈጸሙ ቆዩ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ መደራ ሔደው በእግዚአብሔር ኃይል ድንቆችንና ተአምራትን እየያደረጉ፣ በሽተኞችን እየፈወሱ፣ አጋንንትን እያስወጡ ብዙ ዓመታት ኖሩ፡፡ ካደረጓቸው ተአምራት መካከልም በጠዋት ሥንዴ ዘርተው፣ በሠርክ ሰብስበው መሥዋዕት ካሳረጉ በኋላ በማግሥቱ ከግራር ዛፍ ላይ በሬዎችን አውጥተው ሥንዴዉን አበራይተው ሰባ ሰባት የእንቅብ መሥፈሪያ መሰብሰባቸው አንደኛው ሲኾን፤ በዓለት ላይ የተከሏት ወይን ወዲያው በቅላ፣ አብባ ፍሬ እንድታፈራ ማድረጋቸውና በወይኑም መሥዋዕት ማሳረጋቸው ደግሞ ሌላኛው ተአምር ነው፡፡ አባ ገሪማ መጽሐፍ እየጻፉ ሳሉ ፀሐይ ሊጠልቅ በተቃረበ ጊዜ ጸሎት አድርሰው ጽሕፈታቸዉን እስኪፈጽሙ ድረስ እንደ ኢያሱ ፀሐይን በቦታው እንዲቆም ማድረጋቸውም በመጽሐፈ ስንክሳር ተመዝግቧል፡፡ ከእጃቸው የወደቀው ብርዕ ወዲያው በቅሎ፣ አቈጥቍጦ እንደ አደገ፤ ምራቃቸዉን ትፍ ያሉበት ሥፍራም እስከ ዛሬ ድረስ ሕሙማንን እንደሚፈውስ መጸሐፈ ስንክሳር ይናገራል፡፡

በአንዲት ዕለትም መቅኑናቸውን ተቀብለው ከመነኮሳት ጋር ሲሔዱ መንገድ ላይ ቤተ ክርስቲያን አግኝተው ሲጸልዩ ካህናቱ ቅዳሴ እንዲያሟሉላቸው ጠየቋቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሌሎቹ ምግብ በልተው ነበርና ‹‹አንችልም›› ሲሉ አባ ይስሐቅ ምግብ አልተመገቡም ነበርና መቅኑናቸዉን አስቀምጠው ቅዳሴውን አሟሉ፡፡ ባልንጀሮቻቸው ግን በልተው የቀደሱ መስሏቸው ወደ አባ ጰንጠሌዎን መጥተው ‹‹ቀሲስ ይስሐቅ ከበላ በኋላ ቀደሰ›› ብለው ከሰሷቸው፡፡ አባ ጰንጠሌዎንም አባ ይስሐቅ ሲመለሱ ‹‹የምጠይቅህ ምሥጢር ስላለኝ ሰዎችን ከአጠገብህ ገለል አድርጋቸው›› ሲሏቸው አባ ይስሐቅም ‹‹ሰዎች ብቻ ሳይኾኑ ዕንጨቶችና ድንጋዮችም ገለል ይበሉ›› ብለው መለሱላቸው፡፡ ወዲያዉኑም ዕንጨቶችና ድንጋዮች አንድ ምዕራፍ ያህል ከቦታቸው ሸሹ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ጰንጠሌዎን ‹‹ ወልድየ ይስሐቅ ገረምከኒ፤ ልጄ ይስሐቅ ሆይ! ገረምኸኝ›› እያሉ አደነቋቸው፡፡ አባ ገሪማን ሳያዉቁ የከሰሷቸው መነኮሳትም ይቅርታ ጠይቀዋቸዋል፡፡ አባ ገሪማ ተብለው መጠራት የጀመሩትም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ‹‹ገሪማ ገረምከኒ አስኬማከኒ አልባቲ ሙስና፤ አባ ገሪማ አስገረምኸኝ፡፡ ለምንኵስናህም እንከን የለባትም›› በማለት ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ አመስግኗቸዋል፡፡

ከዚያም በትግራይ ክፍለ ሀገር ልዩ ስሙ መደራ ከሚባል ቦታ ገብተው በዓት ሠርተው ለ፳፫ ዓመታት በትኅርምት ኖረው መልካም ተጋድሏቸውንና የቀና አካሔዳቸዉን በፈጸሙ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰኔ ፲፯ ቀን ተገልጦ ስማቸውን የሚጠሩትን፣ መታሰቢያቸዉን የሚያደርጉትን፣ ገድላቸዉን የሚጽፉ፣ የሚያነቡና የሚተረጕሙትን፣ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጹትንና የሚያገለግሉትን ስማቸውን በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጽፍላቸው ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ አባ ገሪማም ይህንን ታላቅ ሀብት የሰጣቸዉን እግዚአብሔርን አመስግነው ከተደሰቱ በኋላ በብርሃን ሠረገላ ተነጥቀው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በተለይ በገዳማቸው በመደራ አባ ገሪማ የተሠወሩበት ሰኔ ፲፯ ቀን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ እኛንም በጻድቁ ጸሎት ይማረን፤ በረከታቸዉም ከእኛ ጋር ትኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡-

  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፲፯ ቀን፡፡
  • መዝገበ ታሪክ ክፍል ፪፣ መ/ር ኅሩይ ኤርምያስ፣ ገጽ ፺፱-፻፡፡