ለተተኪ መምህራን ሥልጠና መስጠቱን የአሜሪካ ማእከል አስታወቀ

ሠልጣኞቹ ከአሠልጣኝ መምህራን እና ከኦሀዮ ደ/ሰ/ቅ/ገብርኤል ቤ/ክ የመስተንግዶ ኮሚቴ አባላት ጋር

ሰኔ ፳፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምርያ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል በኒውዮርክ ሀገረ ስብከት በኮሎምበስ ኦሀዮ ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከሰኔ ፲፮ – ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ለሦስት ቀናት የቆየ የተተኪ መምህራን ሥልጠና መስጠቱን አስታወቀ፡፡

እንደ ማእከሉ ማብራርያ በማእከሉ የትምህርት፣ ሐዋርያዊ ተልእኮ እና የምክር አገልግሎት ዋና ክፍል አዘጋጅነት በተሰጠው በዚህ ሥልጠና በቍጥር ከዐሥር ከሚበልጡ ስቴቶች ከየንዑሳን ማእከላቱ የተወከሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የተሳትፉ ሲኾን፣ የሥልጠናው ዓላማም ሠልጣኞቹ በስብከተ ወንጌል ሊያገለግሉ የሚችሉበትን ዕውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ ለማገዝ ነው፡፡

ትምህርተ ሃይማኖት (ዶግማ)፣ መንፈሳዊ አስተዳደር፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ የስብከት ዘዴ እና ክብረ ቅዱሳን በሥልጠናው የተካተቱ የትምህርት ክፍሎች ሲኾኑ፣ መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ፣ መልአከ ሰላም ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅን፣ ቀሲስ ኅብረት የሺጥላ፣ መምህር ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም እና መምህር ብርሃኑ አድማስ ሥልጠና በመስጠት የተሳተፉ መምህራን ናቸው፡፡

ለሦስት ቀናት በተሰጠው በዚህ ሥልጠና በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲኾን፣ በውይይቱ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ ከሠልጣኞቹ ለመረዳት መቻሉንም ማእከሉ በዘገባው አትቷል።

በሥልጠናው የመፈጸሚያ ዕለት እሑድ ከቅዳሴ በኋላ በተደረገው የምረቃ መርሐ ግብር በመምህር ብርሃኑ አድማስ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲኾን፣ ሠልጣኞቹም ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ በማእከሉ የተዘጋጀው የምስክር ወረቀትም በመልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ አማካይነት ለሠልጣኞች ተበርክቷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ የደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅን ሥልጠናው በደብራቸው በመሰጠቱ እርሳቸውም ኾኑ ምእመናኑ እጅግ መደሰታቸውን ከገለጹ በኋላ ለወደፊት ሥልጠናው በየጊዜው ሲዘጋጅ ደብራቸው በመስተንግዶ ተባባሪ እንደሚኾን ቃል ገብተዋል።

መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ በበኩላቸው ሥልጠናው ተግባራዊ በመኾኑ የተሰማቸው ደስታ ወሰን እንደ ሌለው ገልጸው ሠልጣኞቹ በተሰጣቸው አደራ ቤተ ክርስቲያንን በትጋት እንዲያገለግሉ መክረዋል።

አያይዘውም ለሥልጠናው መሳካት አስተዋጽዖ ያደረጉ የማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ አባላትን፣ ሥልጠናውን በትጋት ያስተባበሩ የትምህርት ክፍል ሓላፊዎችን፣ እንደዚሁም የምግብና መኝታ ሙሉ ወጭውን በመቻል በመስተንግዶው ድጋፍ ያበረከቱ ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅንን፣ በአጠቃላይ የኦሀዮ ደ/ሰ/ቅ/ገብርኤል ሰበካ ጉባኤ አመራር አባላትን እና ሕዝበ ክርስቲያኑን መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ ከልብ አመስግነዋል።

የአሜሪካ ማእከል ሰብሳቢ አቶ ማስተዋል ጌጡ በዕለቱ ባስተላለፉት መልእክት ሠልጣኞቹ በሥልጠናው የቀሰሙትን ትምህርት አስፋፍተውና አሳድገው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ በማፋጠን የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በመጨረሻም የተተኪ መምህራን ሥልጠናው ለወደፊትም በየዓመቱ እንደሚሰጥ ያስታወቁት ሰብሳቢው፣ ከአሁን በፊት የሥልጠና ዕድሉን ያላገኙ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ሥልጠናውን እንዲወስዱ ለማድረግ ማኅበረ ቅዱሳን ቅድመ ኹኔታዎችን በማመቻቸት ላይ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡